አለቃ ተክሌ - ቫንኩቨር (ካናዳ)

ትንሽ ወደኋላ፤ የጠፉት በጎች ሲወለዱ

ጥቅምት 1992 ዓ.ም. (መሰለኝ)። አዲስ አበባ ኢትዮጵያ። ሶሰት አራት መልካቸው ያመረ፤ ወጣት፣ ሱፍ የለበሱ ቁመናቸው ብቻ ሳይሆን አቋማቸውም ጭምር የሚመሳሰል፤ ግማሹ እስላም ግማሹ ክርስቲያን፣ ግማሹ ጉራጌ ግማሹ አማራ ግን ደግሞ የሚመቹ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች/ጎልማሶች የፖለቲካ ፓርቲ አቋቋሙ ተብሎ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሲነገር ከምር የወሰድናቸው አልነበርንም። ብንኖርም ብዙ አልነበርንም።

 

ከተመሰረቱ ከጥቂት ወራት በኋላ አሁን በህይወት የሌለና ሕወሀትን አጥብቆ የሚጠላው ወዳጄ ስንታየሁ፤ ስቴዲየም አካባቢ ወደሚገኝ ቢሯቸው ወሰደኝ። አንዳንዶቹን ነገሮች ረስቼያቸው ይሆናል። አብዛኛውንና ጠቃሚ ነገር በሙሉ ግን አስታውሳለሁ። ሲናገር የማይጠገበውን ወጣት ነበር ላገኝ የፈቀድኩት። ልደቱን። ግን ሌላኛውም ያው ነው። ልደቱን ሌላ ሰው ይዞታል። ስለዚህ ሙሼን አገኘሁት። በጠባብ ቢሮዋቸው ተጫወትን። ሰማናቸው። ቅጽ ልሙላ አልሙላ አላስታውስም። ግን ከዚያም በፊት እንደወደድኳቸው በዚያን እለትም ከዚያም በኋላ ወደድኳቸው። ከኢትዮጵያ እስክወጣ ድረስ አንጀቴን የሚያርሱ፣ የልቤን የሚያደርሱ የምወዳቸው ፖለቲካዊ አምልኮ የማመልካቸው የምን ዶ/ር ብርሃኑ፣ የምን ፕሮፌሠር መስፍን፣ የምንስ ሀይሉ ሻውል የኛ ልሳናት፤ የኛ የፖለቲካ አማልክት እነ ሙሼ ነበሩ። እነ ልደቱ። ኢዴፓ።

 

አቶ አላሙዲን ኢህአዴግ እንዲሆኑ ያጠመቃቸው ማን ነበር? ጊዜ የለኝም ቪዲዮውን ለ”መጎልጎል”። እኔንም በሩቁም ቢሆን በፖለቲካ ያሳደገኝ፤ አሁንም ድረስ የሆነውን ሁሉ ሆኖ ስላለፈው ዘመኑና ስላለፈው ትግሉ የምወደው፤ ሰዎች እንደሚያወሩበት ሳይሆን፤ ከዚያ በተቃራኒ ስለኢትዮጵያ መስዋእትነት የከፈለ፣ የታሰረ። እስር ቤት ያሟሸ፤ የተደበደበ። የተገፋ ፖለቲከኛችን ልደቱ ነበር። የልደቱ ነገር ሁልግዜም ያቃጥለኛል። ልናጣው የማይገባ ልጅ ነበር። አጣነው። በርግጥ እሱም እኛን አጥቶናል። ምክንያቱም እኛ ከዚያው አለን። እሱን ግን ከነበረበት አጣነው። ያ ስለኛ የታሰረው፣ ስለኛ የተደበደው ልጅ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ከደብዳቢዎቻችን ጎን ተሰልፎ የነሱ ልሳን ሆኖ ሲናገር ስሰማው አቃጠለኝ። እኛ በሸሸንበት ሰዓት ሁሉ እኛ በጫርነው እሳት ባልሰራው ሀጢያት የተገረፈው ልደቱ እነሆ ዛሬ ስለፖለቲካ እስረኞች መኖር አለመኖር ሊወያይ ከኢህአዴግ ተፈራርሞ ጊዜ እየጠበቀ ነው።

 

ሌላ ትዝታ፤ አሜሪካን ድምጽና ልደቱ

እስከዛሬም ድረስ የማልረሳው የዛሬ ስድስት አመት ሰባት አመት አካባቢ ኬንያ እያለሁ ከአሜሪካን ድምጽ ጋር አንጀቴን ያራሰ “ክላሲክ” ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። ከሱ አስቀድመው በሬዲዮው አቶ መለስ ቀርበው ነበር። ልደቱ መጣ። አቤት ንግግር። አቤት ገለጻ፤፡ “ገዢው ቅን ልቡና ስለሌለው እንጂ ቅን ልቡና ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለማምጣት እንኩዋንስ አስር አስራአምስት አመታት አምስት አመትም አይፈጅ ነበር” አይነት ንግግር። በየግዜው፡ ልደቱን የወደድነው የልባችንን ስለሚናገር፤ የውስጣችንን ስለሚያወጣ ነበር። ከዚያም በኋላ የራሱ “ኤጎ” አሸንፎት በርግጥ የሌሎችም የቅንጅት ሰዎች አስተዋጽኦ ታክሎበት ከቅንጅት ተጣልቶ ሲወጣ ታግሰነውና ችለነው የለም ይሄ ልጅ ሀብታችን፣ አርበኛችን፣ ቀራጫችን፣ ሞዴላችን ነው ብለን እስከ ቅርብ ግዜም ድረስ የቆየን ነበርን። በርግጥም ትንሽ ተገፍቶም ተከፍቶም ነበር። የዶ/ር ብርሀኑ መጽሀፍ እንደሚያትተውም በቅንጅት ምስረታ ወቅት ልጁን ለማግለልና ከስልጣን ለማራቅ ትንሽ ፖለቲካዊ ተንኮል ቢጤ ነበረች።

 

ይሄ ልጁ “ባንዳ ነው፡ ልደቱ ተሸጦ ነው፤ ገንዘብ ገዝተቶት ከሀዲ” ምናምን የሚለውን ትርፍ ነገር አልቀበለውም። አይጠቅመንምም። ለወንድሜ ልደቱ ጥፋት ከዚያ መለስ ያለው ስያሜ በቂ ነው። ትንሽ ስለከፋኝ ነው፤ ወደኋላ የሄድኩት። የማይታፈስ የፈሰሰ ፈሳሽ ነገር። ወደ አሁን ልመለስ። ወደዛሬ። ወደዚህ ሁለት ሶስት ዓመት። ለምሳሌ ለአቶ ስዬ የጻፈው ወረቀት። ያ ነው ይሄ ልጅ አበዛውኮ፣ ዝም ካልነው እውነትና እውነተኛ ያስመስለዋል ብዬ እንድጽፍ ያነሳሳኝ እንጂ በሱ ላይ እንኩዋን ትችት የሚያስጽፍ የሚጨክን አንጀት አልነበረኝም። ግን አበዛው። ወጥ ረገጠ። በመለስና ቤተሰቡ ላይ የጠላነውን በሱም ተመለከትን። “እና ምን ይጠበስ?” ንግግር አበዛ።

 

ስለፊርማና ስምምነት፤ ስለምርጫና ሩጫ

ጤናማ አእምሮ ይዞ፤ ማንም ስምምነትን የሚጠላ የለም። አልፎ አልፎ ይኖር ይሆናል። ግን ከኢህአዴግ ጋር በሚደረግ ፊርማ የኢትዮጵያ ችግር የሚቀረፍ ቢሆን፤ አይደለም ባንድ ባስር ጣት በእግራችንም ለመፈረም የተዘጋጀን ነን። ግን ልደቱ፡ ሀምሌ ላይ ይቅርታ ጠየቁ ብሎ ፈቶ መልሶ ባመቱ ታህሳስ ላይ ይቅርታ ካደች ብሎ ምንም ክፋትና ሀጢያት የሌላትን ሴት ያሰረ ውል አፍራሽ ስርአት ሆኖ ሳለ፤ የራሱን ህገ መንግስት ካጸደቀበት ግዜ ጀምሮ ህገ-መንግስቱን እየረጋገጠ እዚህ ለመድረሱ ከልደቱ በላይ ምስክር የለም ብለን መናገር ስንችልና የዚህን ህግ አፍራሽ ጠባሳ ተሸክሞ እየዞረ፤ የጻፈውን ሕገ መንግስት ያላከበረ ስርአትን እንዴት አድርገን ነው በመርህ አንጻር ከዚያ ያነሰውን ስምንነት ያከብራል የምንለው? ነው እንጂ ጥያቄው ስምምነትን የሚጠላ ጤናማ ሰው የለም።

 

ምርጫ ካለ ምርጫው የቀረው አምስት ወር ነው። እስካሁን ድረስ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንዴት ነው በፈረቃ የምንጠቀመው የሚለው አልተቋጨም። በተቃራኒው ግን ኢህአዴግ በየቀበሌው፣ በየመንደሩ፣ በየከተማው የራሱን ድርጅትና አባላት አደራጅቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የስምም ይሁን የግብር አባላት መልምሎ ቁጭ ብሏል። ሕወሀት/ኢህአዴግ እንደ መንግስትም እንደ ፓርቲም ሀያ አራት ሰዓት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ህዝቡን ሲያደነቁረው ኢዴፓና ሌሎች ፓርቲዎች ግን ቅንጣት ታህል የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ምጽዋት የተሰጣቸውም አይመስለኝም። አቶ ልደቱ፡ ይሄ ስምምነት ገነመኔ የሚባል ነገር ላልጣመን ሰዎች ስሌቱ እኮ ቀላል ነው። እንደው አንተም አውቀህ ተኝተህ እንጂ የድሮው ልደት ብትሆን ከኔ በጣፈጠና በተከሸነ መልኩ ጉዳዩን አሳምረህ ታስቀምጠው ነበር።

 

ሀይሌ ገብረስላሴ ካሸነፈ ተፎካካሪ ሯጮቹ ሁሉ ካንድ መነሻ ጀምረው ነው እንጂ ሀይሌ አምስት ዙር ቅደምና ሌሎቹ ይለቀቃሉ ተብሎ አይደለም። ለኔ ምርጫ እንደ ሩጫ ነው በቀላሉ። ድርጅቶች እኩል መነሳት ካልቻሉ እኩሉ ይቅርና አሁን ከዚህ በኋላ በቀረው ግዜ እንኩዋን እንደ ልብ በየቦታው ተንቀሳቅሳችሁ እንድትደራጁ፡ ቢሮ እንድትከፍቱ አባላት እንድትመለምሉ፡ ሰልፍ እንድትወጡ እንድትሰበሰቡ ካላመቻቸና የሰልፍ ፈቃድ ለመስጠት ሳምንት ሁለት ሳምንት የሚጠበቅ ከሆነ እንዴት ተደርጎ ነው ፍትሀዊ ምርጫ የሚደረገው። መረጃ ልስጥ? በዚህ ሳምንት መኢአድ ባህር ዳር ሰልፍ ጠርቶ ደብረ ማርቆስና ደምበጫ ላይ አባላቱ ለሰአታት ታስረው በኛ ጥፋት ነው የታሰርነው ብላችሁ ፈርሙ ተብለው ሲገደዱ እንደገና በክልሉ ሳይቻል ቀርቶ አዲስ አበባ ተደዋውለው ሲያስፈቷቸው፤ ስምምነቱ ካላይ እንጂ ገና ወደታች አልወረደም እያለ አቶ ተስፋዬ የሚባል የመኢአድ አባል ከባህርዳር ሲያማርር ሰማሁ። ጉዳዩ ከስምምነትም በላይ ነው። ለነገሩ፤ አቶ ልደቱ ይሄንን ያጣዋልን?

 

ልደቱ ሆይ፡ በዚህ ዘጠኝ አመት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ አንተ ከኔ የተሻለ እውቀት ይኖርሃል። በዚህ ረገድ ግን እኔን አስተያየት ከመስጠት የሚያግድ መሰረታዊ ለውጥ ያለ አይመስለኝም። እዚያ በነበርኩበት ሰዓት ኢህአዴግ ሰልፍ በፈለገበት ሰዓት ሁሉም በእጁ ሁሉም በደጁ ነውና ቲቪውን ሬዲዮውን ፖሊሱን፤ ወታደሩን ሁሉ በቅጽበት ማሰለፍ ይችላል። ባንድ ማታ አዋጅ ያሻውን ያደርጋል። ተቃዋሚዎች ግን ይሄ ሁሉ መብት አይደለም ቅንጣትም አልተከበረላቸውም ብሎ ላንተ መንገር ለቀባሪው ሳይሆን ለሟቹና ለሞተው ሞቱን የመንገር ያህል ነው። ሞተሀል ብሎ።

 

ጽሁፍህ፡ የምትለውና የምታደርገው፡ ሶስተኛ አማራጭ

ጽሁፍህን አነበብኩት። ባጭሩ ያበሳጫል። ተቃዋሚዎች ጋር ችግር የለም እያልኩህ አይደለም። ርእሴ እሱ ስላልሆነ አላነሳውም። እንጂ በችሎታቸውና በብቃታቸው ሳይሆን በቲፎዞ ብዛት ብቻ አንተን የመሰለ አንበሳ እያለ፤ እንደ ሀይሉ ሻውል ያለ ተወዳድሮ ማሸነፍ የማይችል በንግግር እንኩዋን መያዣ መጨበጫ የሌለው’ በስማ በለውና ያለስሌት እንዳመጣላቸው የሚናገሩ የሽማግሌ አኩራፊ ሰው ስትመርጡ ነው ነገር የተበላሸው። ያኔ በቅንጅት ግዜ ማለት ነው። አንተን የማቅህ መሰለኝ። እሳቸውንም። ሀሳቡንና ራዕዩን ተናግሮ እንጂ፤ በአጃኩዋሚ በሌለበት የሚመረጥ ሰው አይመቸኝም። ያኔ ያ ነው የሆነው። ያኔ ብቻ አይደለም። ከዚያም በፊት። ፕሮፌሠር አስራት ሞተው፤ አቶ ሀይሉ ሻውል ቀኛዝማችን ተክተው በሌሉበት ለመአህድ ተመረጡ ሲባል ገና ነው የቀፈፉኝ።

 

አንተን አውቅህ ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ልሳን ነበርክ። ዛሬ የሕወሀት/ኢህአዴግ ልሳን ሳትሆን። ሰዉ እንደሚለው አይደለም ኢህአዴግ ያልኩህ። የምትሰጠው ሀሳብ ሁሉ አቶ መለስና በረከት የሚሉትን ሆነብኝ። ምሳሌ፡ ሶማሊያን ስለመውረር። “ትክክል ነው፡ የአገራችንን ሉአላዊነት ለመከላከል ምናምን” አልክ። የፓርላማ አባላትን በር ላይ ስለመፈተሽና ቀበቶ ስለማስወለቅ ተጠየቅክ። “ልክ ነው የሽብርተንነትና የደህንነት ስጋት ስላለ።” ስለ ኢህአዴግ ሬከርድ ተጠየቅክ፡ “ከፍተኛ ልማት አለ፤ ተከዜም ሄደን መረቅን፡” ይውጣላችሁ የምትል ይመስላል። ስለፖለቲካው ምህዳር መስፋትና መጥበብ ሲጠይቁህ ሰማሁ ሌላ ቀን። አንተ ዋናውን ፈላጭ ቆራጭ ትተህ ተቃዋሚዎችን መውቀስ ጀመርክ። ቮካል ዲያስፖራ …. ምናምን የሚል ስም ቀድተሀል ደግሞ። ኢህአዴግን ወክለህ የምትናገር መሰልክ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ልሳን መሆንህ ቀረና የወያኔ ልሳን ሆንክ። ወይም መሰልክ። አሁንም ልብ በል ስላንተ ውስጤ የጠለቀ ፍቅር ከመኖሩ የተነሳ ያለኸው የተሳሳተና ያንተ ያልሆነ ጎራ ውስጥ ነውና ወደፊትም የኛ ነህ ብዬ ነው የማስበውና ነው ይሄንን የምልህ። ሰው ያለውን ይበል። ሶስተኛ አማራጭ አልክና መጣህ።

 

ሶስተኛው አማራጭህ ግን የመጀመሪያው አማራጭህ ግልባጭ እንጂ ሶስተኛ አይደለም። ቀድሞ ኢህአዴግን ነበር የምትቃወመው፡ አሁን ተቃዋሚዎችን መቃወም ጀመርክ። አሁን ለኢህአዴግ የራራው አንጀትህ ለተቃዋሚዎች አልራራም አለ። ይሄ ነው ሶስተኛው አማራጭ። ጭፍን ደጋፊዎች ወይንም ጭፍን ተቃዋሚዎችም አንሆንም ካልክ ጭፍን የሶስተኛ አማራጭ አራማጅም መሆን የለብህም። በሶስተኛው አማራጭ፡ “ሰው” እንጂ “አቋም” አልቀያየርክም። ስለ ሰላም ስምምነቱ ተጠየቅክ። እንደው በምን ተአምር አውቀኸው ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ደግፎታል የምትለው? ይሄ ትክክለኛ የኢህአዴግ ቅጂ ነው። ሕወሀት/ኢህአዴግ ነው እንደዚያ የሚለው። ኢህአዴግ ነው አዋጅና ምርጫ በ99 ከመቶ የሚያጸድቀው።

 

ልደቱ አቃጠልከን። ብቻ አይደለም፤ የኮራንብህን አሳፈርከን። ካፈርኩ አይመልሰኝ ሆነ አካሄድህ። አሁን እውነት ከሀይሉ ሻውል ጋር አብረህ ልትሰራ ነው? አቶ ሀይሉና አንተ አትገናኙም። አቶ ሀይሉ የግርግረና የፊውዳል ስነ ልቡና ያላቸው አኩራፊና ጀሌ አብዥ ሰው ናቸው። መለስና በረከትም እንደዚያው። አንተ ነበርክ ለየት ያልከው። እመነኝ አልልህም ውስጥህ ያውቀዋልና። ካቶ ሀይሉም ይሁን ከበረከት አንድ ቀን አታድሩም። የድሮውን ልደቱን ከሆንክ። እናም ከላይ እንዳልኩህ፡ “ታርጌትህ” ተለወጠ እንጂ ስልትህ ያው የድሮው ነው። ያንን ስልትህን ግን ጠላት ላይ ስትጠቀምበት ነበር የምወደው። ወዳጅ ላይ አይደለም ልደቱ።

 

ልደቱ፡ ግብዝ ሆንክብኝ። ባንድ በኩል ሶስተኛ አማራጭ ብለህ ስለመቻቻልና ስለበሰለ ፖለቲካ፡ ከጥላቻ ስለመራቅ፡ እንዲያውም ከፍ ብለህ ስለታላላቅ የታደሉ አገር መሪዎች ትናገራለህ። በሌላ በኩል ደግሞ አንተ ራስህ ትሳደባለህ። እንደውም ጥላቻህን ንግግርህና ጽሁፍህ ውስጥ ሲንቀለቀል የተመለከተ የድሮ ወዳጅህና አድናቂህ ያገርህ ልጅ “ደግሞ እንደሱ ጥላቻ ያለው ሰው አለ እንዴ?” ብሎ ጠየቀኝ። አርባ ዓመት ውቅያኖስ ውስጥ የኖረ አለት ዋና መማር ካልቻለ፤ ከአቶ ስዬ ይልቅ ለዚያ ጥሩ ምሳሌ አንተ ሆንክብኝ። ያንን ተረት ባልተጠቀምክ። መሳደብንና አፍ እላፊን እያወገዝክ መልሰህ ስትሳደብ ግብዝነት እንጂ ሌላ ምንድር ነው? አቶ ስዬን ቢሰቅሉትም የማይቆጨኝ ሰው ነኝ። አይመቸኝም። ግን ከክርስቶስ ወዲህ በስቅለት ባላምንም። ግን ከታላላቅ ሰዎች የምትጠብቀው ስለመቻቻልና አብሮ ስለመስራት እንጂ ስለጥላቻና ስለለመራራቅ ከሆነ ታዲያ ስታብል ካልሆነ በስተቀር እንደምን መልሰህ እኚያን ሰው “አርባ አመት ውቅያኖስ ኖረው ያልተማሩ” ደንቆሮ፣ መሀይም ትላቸዋለህ? እንደዚያ እኮ ነው ያልከው። ብንጨምቅዎት ምንም ፍጭጭ አይልዎትም ስትል።

 

ልብ አድርግ፤ ልደቱ እኔ አፍቃሬ ስዬ ሆኜ ሳይሆን ካንተው የማስመሰል የሚመስል መነሻ ተነስቼ ነው። የምርህን ከነበረ ባንድ በኩል ስለመቻቻል እየተናገርክና የዓለማችንን የታደሉ አገሮች ታላላቅ መሪዎች እየጠቀስክና ስለመቻቻል እየተናገርክ መልሰህ ደግሞ ገና አንድም አንቀጽ ሳትዘልቅ፡ ካርባ አመት በኋላ ቢጨምቁዎት ውሀ የማይወጣዎት ድንጋይ አልካቸው። ስለዚህ ልደቱ በሶስተኛው አማራጭህ ሰው ነው የምታጠቃው እንጂ፤ ጥቃትህንና አቋምህን አልለወጥቅክም። በፊትም ጥላቻን የተሞላህ ነህ፤ አሁንም ያው ጥላቻን የተሞላህ ነህ። ልዩነቱ በፊት የምትጠላው እኛም የምንጠላውን ነበርና ወደድንህ። አሁን ግን እኛን መጥላት ጀመርክ። ስለዚህም ተከዜን ምረቃ ሄድኩ አልክ። በተከዜ ግንባታና ምረቃ የሚያዝን ሰው የለም። ተከዜ ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ትካዜ ላይ ከተገነባ እናዝናለን። ያም ነው የሆነው።

 

ልደቱ የፕሬዝዳንት ኦባማን የምርጫ ዘመቻ ተመልክተሀዋል? አሁን ስልጣን ከያዙም በኋላ ያለውን አቋም ትከታተላለህ? አንድም ቀን ተቀናቃኞቹን አንስቶ ሲያፈርጥ አልተመለከትንም። እሱን አንዴ በአሸባሪነት፡ አንድ ግዜ ደግሞ በዘረኛነት ሌላ ግዜ ደግሞ በሀሺሽ ተጠቃሚነት እየወነጀሉት ሁሉ እሱ ግን አረ በላቸው ሲሉት ሁሉ ፍንክች አይልም። አንተ ለመምሰል የምትሞክረው እንደኦባማ ያሉትን በሳልና አዋቂ ፖለቲከኞች ነው። ግን እየሆንክ ያለኸው ከዚያ የራቀና የተለየ ነው። ልደቱ አቃጠልከን። እኛን የምንወድህን ማለቴ ነው። የማይወዱህማ አይወዱህም።

 

አርባ አመት ዋና ስላለመማር፡ አንተም አርባ ገባህ መሰለኝ?

ባንድ በኩል እኔ እርስዎን ለመሞገት የሚያስችል በቂ ሀሳብ አለኝ ብዬ ስለማስብ የምሞግትዎት እርስዎ በመረጡት ስልት አይደለም ትልና፤ በሌላ በኩል ግን ጽሁፍህ በሙሉ አቶ ስዬን በከሰስክበት ስልትና መንገድ የተቃኘ ነው። ከላይ የጠቀስኩልህ ምሳሌ አለ አርባ አመት ባህር ውስጥ ቆይቶ ዋና ስላለመቻል። ስለዚህ በስሱ “ውሸታም ነህ” ልደቱ። ገና ከርዕስህ ላይ ወደየት እንደምትሄድ ታስታውቃለህ። አለበለዚያማ፡ ባንድ በኩል የሰዎችን ስብዕና ሳልነካ በአመንክዮ ብቻ እጽፋለሁ እያልክ በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ስዬን ከጋዜጣው አንባቢዎች ያነሰ እውቀት ያላቸው ሀሁ ቆጣሪ ናቸው፤ አይገባቸውም ብሎ ማለት ምን ማለት ነው። አሁንም ልብ በል ስለአቶ ስዬ ተጨንቄ አይደለም። እንዳልከውም አቶ ስዬ የሰላማዊ ትግል የማይገባቸው ደነዝ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን አንተ ያንን ሳላነሳ የምናገር ቅዱስ ሰባኪ ነኝ ብለህ መልሰህ ደግሞ ያንኑ ታነሳና ሰውዬውን አፈር ድሜ ታስግጣለህ። አቶ ስዬስ ከራሳቸው ተጋጩ አንተ ግን ርስ በርሱ የሚጋጭ እናቴ ከፈሱ የተጣላ የምትለው አይነት ነገር ሆንክብኝ።

 

ባንተና በመለስ መፈራረም ኢትዮጵያ የምትድን ቢሆን ምነው እኛ ሺህ ግዜ በተሳሳትንና አንተ ትክክል ሆነህ ኢትዮጵያ በዳነች። ደግሞም በፊርማ ሰላማዊ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ የለም በሀይል ነው እነዚህ ሰዎች መውረድ ያለባቸው በጠብመንጃ ካልሆነ በስተቀር በሰላም እንዲወርዱ አንፈልግም የምንል ሰዎች የለንም። ዋናው ነገር ለውጥ መምጣቱ ነው። ለውጡ በናንተ እጅ መጨባበጥም ይምጣ እንትን መላላስ ያ አያስጨንቅም። ግን አይሆንም። ሰዎቹ ጥሟቸዋል። በፊርማም እዚህ አልደረሱምና የምር ፊርማ አይገባቸውምም። ልደቱ አንተ ከኔ በላይ የምታውቀውንና የተሰዋህለትን ነገር እንዳስታውስህ ስታስገድደኝ እንዴት ታቃጥለኛለህ መሰለህ። አቃጠልከን። ያቶ ስዬ ሀሳብስ ርስ በርሱ ተቃረነ ያንተ ሀሳብ ግን ርስ ብረሱ ተማከነ።

 

ልደቱ፡ ይሄን አላደርግም ባላልክና እኔም ይሄንን ባላደረግኩ። እኔ የግለሰቦችን ስብዕና አልነካም አልክ እንጂ የጽሁፍህ ዋና ጭብጥ እንደውም የሰውዬውን ሰብዕና መንካት ነው። በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች አላደርግም ያልከውን ነገር ነው በተቀሩት ገጾች ሁሉ ያደረግከው። ስላንተ ወያኔ መባልና ስላቶ ስዬ ባለስልጣንነት ስለአንተ የፖለቲካ አክሮባት መቻልና፤ ስለአቶ ስዬ የፖለቲካ አክሮባት አለመቻል ስለአቶ ስዬ መርዛማነትና ስለአቶ ስዬ አምባገነንነት፤ ስለአቶ ስዬ የቦናፓርቲዝም ትንታኔና ሽንፈት ከዚያ ስለፖለቲካ ጅምናስቲክ አስፈላጊነትና መስታወት ውስጥ ቁጭ ብሎ ድናጋይ ስላለመወርወር እንዲሁም ስለ መድረክ የትም የማያደርስ ፈረስነት፡ … ልደቱ አቶ ስዬ አርባ አመት ዋና ባይለምዱና የጥንቱም ያሁኑም ስዬ አንድ ቢሆኑ፤ ቀድሞ የሆኑትን ነው የሆኑት። አንተ ግን ሌላ ሰው ሆንክ። ዳን እንደሚሉት አይነት አይደለም ግን ድህነትህ። ዋና ትችል የነበርከው ሰው ሰመጥክ። ደግሞኮ ተረቱ አርባ ይበል እንጂ ሰላሳም ሀያም አመት ውሀ ውስጥ ለኖረ ሰው ይሰራል። የማይዋኝ ድንጋይ መዋኘት ሳይችል ቢቀር አይገርምም። የሚዋኘው ሲሰምጥስ። ሰመጥክ። እኛንም አቃጠልከን።

 

እንደ መደምደሚያ፤ አሁንም ተስፋ አልቆርጥብህም

ልደቱ፡ ሶስተኛ አማራጭ ብለህ መጥተሀል። ከዚያ ውስጥ ያየሁት ለውጥ እንዳልኩህ ተቃዋሚ ወይንም ፀረ-ኢህአዴግ ያሰኘህን አቋም መቀነስህን ወይም ጨርሶ መተውህንና በምትኩ ፀረ-ተቃዋሚ አቋም መያዝህን ነው። ከዚያ ውጪ ግን የምትለውን መሆን አልቻልክም። ባንድ በኩል ስብዕናዬ መሸከም ከምችለው በላይ ተጎድቷል እኔ ባለጌ አይደለሁም በሰለጠነ ክርክር ነው የምረታው እያልክ መልሰህ ደግሞ ያኩራፊና ተሳዳቢ ፖለቲካህን ትቀጥላለህ። ርስ በርስ አትጋጭ።

 

ስትናገር እኛንም አስብ። ቂመኛ አትሁን። እንደተጎዳህና አላግባብ እንደተጠቃህ የምናምን ሁሉንም በግላጭ በፍትህ መንደር መነጋገር ሲቻል በተወሰነ መልኩም ቢሆን ልትካስ ትችላለህ ብለን የምናስብ ሰዎችም ነበርን አለንም። አንተ ግን ድሮም ችኩል ነበርክ አሁንም ቸኮልክ። የድሮው ችኩልነትህ ግን በኛ ላይ ሳይሆን በጠላት ላይ ስለነበር ወደንህ አንጀታችንን እያራስክልን ኖርን። አሁን ግን በኛው ላይ ተነሳህብን። የድሮው ችኩልነትህ የኛን ዉስል የሚያብስ ነበር። የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶት ለመተንፈስ ነበር። አሁን ግን እንደምሰማው፣ ራሴም እንደማምነው እኛን ለማበሳጨት ቸኮልክ። ምናለ ዝም ብትል? አለ አቶ ዘውገ ባለፈው ሰሞን። ይሄ ልጅ በተናገረ ቁጥር ስህተት እያበዛ ስለሆነ፡ ለሱ የሚበጀው ዝም ቢል ነው አለ። ልደቱ ሆይ በምትለውም መንገድ የፖለቲካ ቅኝትህ የተስተካከለ አይመስለኝም። ለምን ዝም ብለህ ስራህን አትሰራም። ሰዎች ሰደቡህ፤ ጻፉብህ፣ ተናገሩህ፣ ተፉብህ፣ ተዋቸው። እና ስራህን ስራ። ኦባማ ለሚናገሩት ሁሉ ቢመልስና እንዳንተ አርባ አመት ውቅያኖስ ውስጥ የኖረው ጆን መኬን መዋኘት አይችልም ቢል የራሱ ደጋፊዎች እንኩዋን እንዴት እንደሚጠሉት አስብ። በቃ ልክ እንደድሮህ ኢትዮጵያን በሚበጃት ነገር ላይ አተኩር። አታቂም። ካለበለዚያ ከእስካሁኑ የባሰ ገደል ውስጥ ትገባለህ።


 

አለቃ ተክሌ - ቫንኩቨር (ካናዳ)

ታህሳስ 2009

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ