ሀብታሙ አሰፋ (ከላስ ቬጋስ)

በኢትዮጵያ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ነው። በህዝቡ ዘንድ ጎልቶ የሚደመጥ አንድ መራር ቀልድ ነበር። የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ የሩሲያው ኬጂቢ እና የኢትዮጵያው የወያኔ የስለላ ቡድን ከፌዴራል ፓሊስ ጋር ተጣምሮ ለአንድ ግዳጅ ይቀርባሉ። ግዳጁ ነብር አድሮ ማምጣት ነው።

 

ሁለቱ ኃያላን የተባሉትን ፈጥነው አመጡ። የአቶ መለስ ደህንነት እና ፌዴራል ፖሊስ ቢጠበቁ ይቀራሉ። ግዳጁን የሰጡት ቢቸግራቸው ምን ሆናችሁ ጠፋችሁ ይላሉ። እንደተለመደው የአቅም ችግር አለ ዘግይተንም ቢሆን ደርሰናል ይላሉ። የዘገየው የወያኔ ቡድን ያመጣው በደም የጨቀየች የምታነክስ እጅግ ኮስማና ውሻ ነበር። ‘ምነው ይህች እኮ ውሻ ናት፤ የታዘዛችሁት ነብር እኮ ነው’ ሲባሉ፤ “በምርመራ ሂደት ነብር ነኝ ብላ አምናለች” ነበር ያሉት።

 

ህዝቡ እነ አቶ መለስ በየጊዜው ንፁሃንን እየቀጠቀጡ ወንጀል መለጠፋቸውን ስለሚያውቅ የፈጠራት ቀልድ ነበረች። ሥርዓቱ በየጊዜው ይቃወሙኛል ያላቸውን ለመግደል ለማሰርና የቀረውንም ለማሸበርና ከተቃውሞ ለማቀብ ንፁሃንን ወንጀል ሲለጥፍባቸው ኖሯል።

 

ያንን መራር ቀልድ ያስታወሰኝ ሰሞኑን በአቶ መለስ ፕሮፓጋንዳ ሰፊ ትኩረት የተሰጠው “የጨለማ ጉዞ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ሞትና ዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውን ዜጎች አስመልክቶ የፈጠራ ወንጀሉ ባለ እዳ ለማድረግ የተሰራጨው አማተር የፊልም ቅንብር ነው። ከዚያ መራር ቀልድ ጋር የማጣቅሳቸው አብነቶችም አላጣም።

 

በእነ አቶ መለስ የሰሞኑ አማተር የፕሮፖጋንዳ ፊልም አብይ ትኩረት ሶስት ነገር ማስተላለፍ ይመስላል። ዋነኛው “ሽብርና” “አሸባሪ” ሲባል ቢያንስ ዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ጆሮውን ይሰጠንና የምንለውን ሁሉ ያምነናል በሚል ነው። ሁለተኛው ሞትና ዕድሜ ልክ የፈረድንባቸው በበቂ ማስረጃ ነው ለማለት ነው። ሦስተኛ አሁን በአገር ቤቱ ተቃውሞ ያሰጋናል የሚሉትን አንድነት ከግንቦት ሰባት ጋር አጣብቆ ለመጨፍለቅ ለተወጠነው ፕሮፓጋንዳ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ህዝቡን ማሸበር ነው።

 

ደርግ የቻለውን ገሎ ገሎ በግፍ ያሰቃየውን ሁሉ አሰቃይቶ ኋላ ላይ ለኢህአፓ አባላት አንድ ስልት አመጣ። ያ ስልት አብዮቱን ምህረት በመጠየቅ በህዝቡ ፊት መናዘዝ ነበር። በዚህም “ማሪኝ አብዮቴ” ብለው ያልሰሩትን እንደሰሩ እንዲናዘዙ፣ እንዲጨፍሩ የተደረጉ ነበሩ። ለህዝቡ ልጆችህ ወንጀለኛነታቸውን አምነዋል ለማለት ነበር። በዚያ መንገድ “ማሪኝ አብዮቴ” ብለውም የተባለው ምህረት ቀርቶ በአብዮቱ ሰይፍ የተበሉ ብዙዎች ናቸው።

 

እነ አቶ መለስም ታምራትን ጠልፈው ሲጥሉ “ተመክሬ ተመክሬ አልሰማ ብዬ ነው” ብለው እንዲናዘዙ ማድረጋቸው አይዘነጋም። ታምራት ለፍርድ ቤት ልጆቼንና ባለቤቴን እንገድላለን ስላሉኝ ነው ብለዋል። በርካቶችን ግርግዳ እያስደገፉ ከግምጃ ቤት ከወጣ መሣሪያ ጋር ፊልም እያነሱ ያው በተለመደው ስልት ለአብዮታዊው “ፍርድ” ቤት እያቀረቡ የመሰላቸውን ሲፈርዱባቸው ኖረዋል።

 

የሰሞኑን የፕሮፓጋንዳ ፊልም “አማተር” ያልኩት አንዳንድ መጠይቆችን ስለሚያስነሳ ነው። መሰረታዊው ጥያቄ ወያኔ በተለመደ ስልቱ ሰዎቹንም ከአብዮታዊው ፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ይሰራና በዚያ መሰረት ፍርድ ተሰጠ ይባላል።አሁን ባዲሱ ስልት ከ”ፍርድ” በኋላ የተሰራ መሆኑ ነው።

 

መጀመሪያ መንግሥት ሊገለብጡ ነው አሉ። መልሰው መንግሥትስ የመገልበጥ አቅም አልነበራቸውም ባለሥልጣናትን ለመግደል ነው ተባለ። ለመሆኑ የትኛው ባለሥልጣን አቶ መለስ ወይስ እርስዎ ሲባሉ በረከት የለም አሉ። ያኔ በሰዎቹ ላይ የተጀመረው ወፌ ይላላ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድብደባ እና ለማሪኝ አብዮቴ የተዘጋጀውን ፊልም አማተሩ የፊልም ፀሐፊ አቶ መለስ አልጨረሱት ይሆናል።

 

በዚህ ፊልም ሰዎችን ለግል ጉዳያቸው ሲንቀሳቀሱ እየተከታተሉ ፊልም ማንሳት ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። በፍ/ቤቱ ተደብድበናል፣ በግዳጅ ቃል ሰጥተናል፣ የተደበደብነው በገለልተኛ ሀኪም እንታይ ብለዋል። አድማጭ አልተሰጣቸውም። መጀመሪያውኑ ወንጀሉ ሲፈጠር ውሳኔው ተሰጥቷል። ይህን ድርሰት በመተወን ሒደት የታሪክ መዛባት መፍጠር እንደ ሌሎቹ ቴአትር ቤቶች በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ በፍትህ ስም ካባ ያጠለቁት ተዋንያን ቃለ ተውኔቱን ከማንበብ ውጭ መስማትም ሆነ ሌላ ትእዛዝም መስጠት አይችሉም።

 

ዱባይ ድረስ ሔደች የተባለችው ፊልም አንሽ ምነው በታሪኩ የተጠቀሱት የግንቦት ሰባት መሪዎች ሲገናኙ አላነሳችም? የቅንጅትን የም/ቤትና የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ደህንነቱ እየቀዳ አንዳንዴም ልደቱ በሚስጢር እየጻፉ ኢፍቲን ላይ የሚያወጡ ጎበዞች እንዴት ይህንን መሳይ ወንጀል መቅረፅ ሳይችሉ ቀሩ? የታለ በየቀኑ የሚጠለፈው ስልክ? ፊልሙን አማተር ነው ያልኩት እነዚህንና ሌሎችንም ጥያቄዎች የማይመልስ በተለመደው አይነት ስልት የተሠራ በመሆኑ ነው።

 

በ1993 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የአካዳሚክ ነፃነታችን ይከበር ብለው ተቃውሞ አሰሙ። ይሔ ሕጋዊና ሠላማዊ ጥያቄ ያልተዋጠለት ሥርዓት እንደለመደው በጥይት ምላሽ ሰጠ። የከተማው ህዝብ ተማሪዎቹን ለመከላከል ተቃውሞ ስላሰማ የተኩስ እሩምታ ቀጠለ። በዕለቱ ከ70 በላይ ንፁኀን ሞቱ። የሞቱት 31 ብቻ ናቸው አለ። ለእነዚህና ከዛ በፊትና ዛሬም ለሚገሏቸው አልተጠየቁም።

 

የግጭቱ ዋነኛ ጠንሳሾች የተባሉት ዶ/ር ብርሃኑና ፕሮፌሠር መስፍን በተለመደው መንግሥት የመገልበጥ ወንጀል ወህኒ ወረዱ።

 

ከተማሪዎቹ መሪ የተባለው ፋሲል (አሁን ካናዳ ይመስለኛል) ከተያዘበት በግዳጅ ቃሉን ይሰጣል። በዚህ ያልረኩት እነ አቶ መለስ በምርመራ ክፍል ታማኝ ጋዜጠኛቸውን ኃይለራጉኤል ታደሰን ከቴሌቪዥን ይልኩና ልጁ በል የተባለውን ይናዘዛል። በጊዜው ፕሮግራሙ እንደተላለፈ በወቅቱ እሠራበት በነበረው ሩሕ ጋዜጣ ላይ አንድ ካርቶን ወጣ። ካድሬው ጋዜጠኛ ሙሉ የሚሊቴሪ ልብስ አልብሰን ሽጉጥ ይዞ ተማሪውን ሲጠይቀው የሚያሳይ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይሄ ተማሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደብዳቤ ጻፈ። በኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ ወጣ። ተገድጄ ነው የሰጠሁት ብሎ ሂደቱን ገለፀ። ማንም አልተጠራጠረውም።

 

እነ መለስ ቢያንስ ይሔን ተማሪ በሕይወት ስላመለጣቸው የሰሞኑን ቀሽም ፊልም ሲያይ ይታዘበናል ብለው አልተጠነቀቁም። ይህ ልጅ ከብዙዎቹ ህያው ምስክሮች አንዱ ነውና።

 

አቶ ስዬ አብርሃን ሲያስሩ እስር ቤት የወረወሩትን አቶ ታምራት ላይኔን ፈለጉት። ራሳቸው አቶ ታምራት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት መንበረ ፀሐይ የመሀል ዳኛ በሆነበት በስዬ ላይ እንዲመሰክሩ ያንን ካደረጉ እዳ እንደሚቀልላቸው ተናገሩ። በወቅቱ ለዚህ ያግባቧቸው ወ/ሮ እንወይ ገ/መድህን የተባሉት የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተሰኘው ማስመሰያ ተቋም ዳይሬክተር ነበሩ። አቶ ታምራት ለሁለተኛው ዙር ጥያቄ ባለመቀበላቸው ከስዬ ጋር ለክስ ድጋሜ ተጠሩ። ይህን ሲያደርጉ ምነው ዛሬ ድረስ ወንጀሉን አቆያችሁት ብሎ የሚጠይቅ የለም በሚል እብሪት ነው።

 

ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት ከአርበኞች ግንባር ጋር ተወንጅለው በታሰሩበት ወቅት ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ ነበር። ሟቹ የእነ መለስ ታማኝ ካድሬ ጋዜጠኛ ግዛው ዳኜ የታሰሩበት ድረስ ይሔዳል። ካሜራ ከጥቁር መስታወት ጀርባ ደግኖ በተለመደው ስልት ዶክተሩን ሊያስለፈልፍ ይሞክራል። በቁጣ ሰድበው ያባርሩታል። ማታ በቴሌቪዥን ዶክተሩ እንደዱዳ ከንፈራቸው እየተንቀሳቀሰ የተፈለገው ፕሮፓጋንዳ ተሠራባቸው።

 

የመምህራን ማኅበር ዋና ፀሐፊ የነበረውን አሰፋ ማሩን ህዝብ እያየ ሳምሶናይት አንጠልጥሎ ወደ ሥራ ሲሄድ በአደባባይ ረሸኑት። ማታ በቴሌቪዥን መሣሪያ አጠገቡ ተደርጎ አስከሬኑ ሲዘለፍ አመሸ።

 

ህዝቡ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የፈጠራ ወንጀልና ንፁሃንን ለተፈጠረባቸው ወንጀል ተባባሪ የማድረግን ከንቱ ሙከራ ተመልክቷል። እንደታሰበውም ዓለም አቀፍ ህብረተሰብ እንዴት? ለምን? መቼ? ብሎ የማይጠይቅ አይደለም። በፊልም ቀዶ ጥገና የተጨማመረበት አዲሱ ፊልም እንዲያም ሆኖ የተፈለገውን ውጤት አላመጣም።

 

ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ያለ ወንጀሏ ያሰሯት ራሳቸው አቶ መለስና የሽማግሌዎቹ መሪ እና ሽማግሌዎቹ የተባሉት በቴሌቪዥን ቀርበው የሰጡትን በመካድ ነው። የተፈቱበት ሒደት ሽምግልና ነው። ለይቅርታ ቦርድ የሚባለው ብርቱካንም ሆነች ሌሎች ምህረት አልጠየቁም። ቁም ነገሩ ይህን ሐቅ በብርቱካን ቃል መደፍጠጥ ነበር። አልተሳካም።

 

እነ አቶ መለስ ብቻቸውን ተወዳድረው የሚያሸንፉበት ምርጫ ሲቃረብና ዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ጭምር የዘረኛ ሥርዓታቸውን አደረጃጀት እንዲለወጥ መጠየቅ ሲጀምር በተለመደው ስልት ዘመቻ ያዙ።

 

በዚህ ዘረኛ ሥርዓት ማስፈራራትና ማሸበር፣ የዜጎችን የነፃነት መንፈሥ ለመስበር መጣር፣ ይህን ነፃነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚጓዙበትን ጎዳና ሁሉ እንዘጋለን ብለው ማሰባቸው የዋህ ያሰኛቸዋል።

 

በሥልጣን ላይ ያለው ዘረኛ ሥርዓት በየጊዜው የሚፈበርካቸውን የሰሞኑ የመሰሉ አማተር ፊልሞች የሚያሳየው ሥርዓቱ መሸበሩን፣ ዕድሜ ባገኘም ቁጥር ንፁሃንን እየገደለና እየጨፈጨፈ ለመቀጠል መወሰኑን ነው። ለጊዜው ግን አቶ መለስን “አማተሩ ፊልምዎ ቀሽም ነው! ለዛሬ አልተሳካልዎትም!” እንበላቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ