ሕዝብን ያሳተፈ ጠንካራ የተቃዋሚ አመራር ምርጫን በድል መወጣት ይችል ይሆን? (ብሩክ ለማ)
ብሩክ ለማ ከስድስት ኪሎ bThis email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በግንቦት 2002ቱ ምርጫ የ1997ቱን ያህል የሕዝብ ተሳትፎን መጠበቅና የለውጥ ተስፋን መሰነቅ ከምኞት ባያልፍም፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የግፈኛ ስርዓቱን እድሜ ለማሳጠር መትጋት ግን ተገቢ ነው። መላው ሕዝብም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ከተወጡ ቀዳዳ አይጠፋምና የምንጠብቀው ድል ላይርቅ ይችላል። በምርጫ መሳተፉ ዋና ግቡ የፖለቲካ ስልጣንን በሕዝብ ይሁንታ መቆጣጠር ቢሆንም በምርጫ ሂደት የተፈጠረ ደባና ሴራን አጋልጦ የአሸነፍኩ ባይን ህጋዊነት መንፈግና እንዲነፈግ በማድረግ ቀጣይ ትግልን ማፋፋም ሌላኛው ግብ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። የሕዝብን ስሜት በአግባቡ ተረድቶ፣ ከወያኔ የአፈና ስርዓት ጋር አገናዝቦ ትክክለኛ ስትራተጂን መቀየስ ወደ ተጠቀሰው ድል ያደርሳል። የዚህ ፅሁፍ ዓላማም በዚሁ ዙሪያ ያጠነጠነ ሲሆን በምርጫው ለመሳተፍ ሽር ጉድ የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ምረጠኝ የሚባለው ሕዝብ ቢያጤኗቸው ወደ ተሻለ ውጤት ሊመሩ ይችላሉ የሚባሉትን ይጠቁማል።
ለመታገል የተዘጋጀ ሕዝብ አለን?
በአንድ በኩል አገሪቱ ውስጥ ነፃ ተቋምም ሆነ አሰራር የሌለ መሆኑን እንዲያውም ወያኔ ያሻውን ሊያደርግ እንደሚችል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በወያኔ አድሎአዊ አገዛዝ የተንገፈገፈ፣ መብቱንና ነፃነቱን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ ቆርጦ የተነሳ ሕዝብ ያለበት አገር መሆኑን መረዳት ለስትራተጂ ቅየሳ መሰረት ይሆናል። ባሁኑ ወቅት ባብዛኛው ሕዝብ በናፍቆት እየተጠባበቀ ያለው ዝምታውን አፈንድቶ ከስቃይ የሚገላገልበትን ነው። በድጋፍና በተቃውሞ የተሰለፈውን ሕዝብ ለማነፃፀር ብንሞክር ልዩነቱ የሰማይና የምድር መሆኑን እንገነዘባለን። ይሄ እንግዲህ በቁሳዊ ጥቅም ተነካክቶ ለይስሙላ እደግፋለሁ የሚለውን ሁሉ ጨምሮ ማለት ነው። ያለፈው የምርጫ ተሞክሮ የሚያስረዳው ካድሬዎቹ ራሳቸው እንኳን ወያኔን እንደማይደግፉት እና የመንግስትነት እድሜው እንዲያጥር አበክረው የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው።እድሜ ለምርጫ 97! ሁሉን አሳይቶናል።
ያለፈው ምርጫ በአገሪቱ ያሉ ተቋማት መጠቀሚያ መሳሪያ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያ ወዘተ ለወያኔ ያላቸውን ወገንተኝነት በማያወላዳ ሑኔታ ገልፀዋል። ምርጫ ቦርድ ኮሮጆ አስገለብጦ እውቅና ሲሰጥ፤ ፍርድ ቤት ደግሞ ለበዳዩ ወያኔ ፈርዷል፤ ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ሰላም መትጋት የሚገባቸው ፖሊስ፣ ደህንነትና መከላከያ ሰላማዊውን ሕዝብ ለወያኔ ብለው ሰላም ሲነፍጉትና በጥይት አረር ሲቆሉት ተስተውለዋል። በጠራራ ፀሃይ ግንባር ግንባራቸውን በርቅሰው የንፁሃኑን ዜጋ ህይወት እንደዋዛ የቀጠፉት እኒሁ የፀጥታ ተቋማት ተብዬ ናቸው። ይሄም አልበቃ ብሎ ምርጫው ያስከተለው የስልጣኔን አጣለሁ መደናገጥ ብዙ አፋኝ ህግጋቶች እንዲፈለፈሉ አድርጎ ቀጣዩ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ስራ ላይ እንዲውሉ ተደርገዋል። አትናገርም፣ አትፅፍም፣ አትሰበሰብም፣ አትሰለፍም፣ አትደራጅም፣ ለመብትህ መታገል አትችልም ወዘተ የሚሉ ሕግጋቶች በተከታታይ ተፈልፍለዋል። ብዙዎችም የነዚሁ ሕግጋቶች ሰለባ ሆነዋል።
ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን የተቀረው ሕዝብ እንዳለ ሆኖ ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት ውስጥ ያሉት እንኳ በሙሉ የወያኔ ቅጥረኞች፣ የመሰሪ አላማ አስፈፃሚዎች ናቸው ማለት አይቻልም። በየተቋማቱ ከተሰገሰጉ ጥቂት ዘረኛ አደርባዮች በስተቀር ባብዛኛው የእለት ጉርሱን ለማግኘት፣ የልቡን በልቡ ይዞ የተጠጋ፣ ለሙያው ታማኝ የሆነ፣ ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የተዘጋጀ ነገር ግን አጋጣሚውን የተነፈገ ዜጋ ነው። ደብተርና እስክሪብቶ ይዞ የወጣን ተማሪ ግንባሩን እየበርቀሱ በየአጥሩ ስር ያስቀሩት ሁሉም አግዓዚ ውስጥ ያሉ ወታደሮች እንዳልሆኑ ይታወቃል። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ተመልምሎ አግዓዚ ውስጥ የሚያገለግል፣ የቤተ-መንግስት ጠባቂ የነበረና ከ97ቱ ምርጫ ማግስት ከገዳዮቹ ጋር የተሰለፈ አብሮ አደጌ የነበረውን ሁኔታ በቁጭት አጫውቶኛል። በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የተዋቀረው ፖሊስ የሚታመኑና የማይታመኑ በሚል ጥቅማ ጥቅሞችን አበላልጠው፣ የበታቹን መሪ የበላዩን ተመሪ በማድረግ ያሰማሩበት ምክንያቱ ዘር ላይ የተመሰረተ ወገንተኝነት ብቻ ሳይሆን ሙያንና ሕዝብን ለማገልገል በሚደረግ ሙከራ ጭምር ነው። በምርጫው ማግስት ለሕዝብና ለሙያዬ ነው የምገዛው ብለው ፍለፊት የወጡትን ግለሰቦች ከየተቋማቱ ተለቅመው መወገዳቸውን ልብ ልንል ይገባል። ያልደፈረውንና ሙያ በልብ ብሎ የተቀመጠውን ደግሞ ቤት ይቁጠረው። ለዚህም ነው ለኔ ይመሰክሩልኛል ብሎ ከቱባ ስልጣናቸው አንስቶ አጣሪ ኮሚሽን ያደረጋቸው ጀግኖች ለወያኔ ሳይሆን ለህዝባቸው፣ ለንዋይ ሳይሆን ለህሊናቸውና ለሙያቸው አድረው በ97 ምርጫ ማግስት ወያኔ የፈፀመውን ግፍ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለአለም ማሕበረሰብ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ያጋለጡት።
ከሁሉም በላይ ሊሰመርበት የሚገባው በየቦታውና በየጊዜው በተለያዩ የሙያ መስክ የተሰማሩ ወገኖቻችንን አባል ካልሆናችሁ ስራ አታገኙም፣ ማዳበሪያ የለም፣ እርዳታ አታገኙም፣ እድገት የለም፣ ትባረራለህ ወዘተ እየተባሉ በወያኔ ቱባ ባለስልጣናትና ድህንነቶች እንደሚዋከቡ ነው። የተወሰኑትም ለጊዜያዊ ጥቅም ብለው የተባሉትን ይፈፅማሉ። በቅርቡ በመሰረታዊ የስራ ለውጥ (BPR) ስም ወያኔ አባላትን ለመመልመል እንደሞከረ ይታወቃል። የአባልነት ቅፅ የሞላ ጥናቱ ሲያቅፈው ያልሞላውን ደግሞ ተፍቶታል። እምብዛም ትምህርት የሌለው፣ በልምድ እውቀትን ያካበተ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሳያምንበት ምን ሊወስን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በግል ስራ የሚተዳደረውንም ህብረተሰብ ሕግን ከለላ በማድረግ ከመበዝበዙ ባሻገር መጠነ ሰፊ ወከባዎችና ሕገ ወጥ ተግባራት ይፈፀምባቸዋል። ሕይወታቸውን ለማቆየት ብለው የተቀላቀሉ ቢኖሩም፡ ብዙ ስቃይና ውርጂብኝ ተቋቁመው እየታገሉ ያሉ በጣም ብዙ መሆናቸውን ለአፍታ መዘንጋት የለብንም። ብዙዎች በተለይ ወጣቱ ወያኔ የሚያደርስበትን በትር በመቋቋም፣ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የተቃውሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ በማሰማት ላይ ይገኛል። የታላቁ ሩጫ ትዕይንትን ማስታወስ ተገቢ ነው። በአንድ ገጠር በምርጫ 97 ዋዜማ በደህንነት የተደበደበ የአንድነት ታዛቢ በደም የጨቀየ ጭንቅላቱን በፋሻ ጠቅልሎ፡ ህመሙን በመቋቋም፡ በሌሊት ምርጫ ጣቢያ ተገኝቶ በመታዘብ የትግል አጋርነቱን አስመስክሯል። ለአብነት ይህንን ጠቀስኩ እንጂ በየአካባቢው ብዙ መሰል ጀግኖች መኖራቸው እሙን ነው። ዛሬም እየተደበደቡ የማደራጀት ስራ የሚሰሩ፣ ትክክለኛውን አቅጣጫ ለሕዝብ ማስተማር የሚሞክሩ በጣም ብዙ ናቸው።
በሚያዝያ 1997 የተደረጉትን የድጋፍ ሰልፎች ብናጤን፤ ወያኔ በጠራው ሰልፍ ላይ ለገንዘብ፣ ቅንጅት በጠራው ላይ ደግሞ ለእውነተኛ አጋርነት ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ተሳትፏል። በሁለቱም ሰልፎች ላይ በመገኝት ሁለት ዓላማዎችን አሳክቷል። በወያኔው ሰልፍ ላይ ተገኝቶ አልተሳተፍክም ከሚባል ጥርጣሬና ሊያመጣ ከሚችለው መዘዝ ሲተርፍ ስራ የነበረውም ሆነ ያልነበረው የግንዘብ ተጠቃሚ ሆኗል። በቅንጅት ሰለፍ ላይ ይኼንኑ እውነታ በዜማ አስተጋብቶታል። በፉከራ ያላበቃው ይኼው ሕዝብ የምርጫው እለት ወያኔን አሽቀንጥሮ በመጣል እውነተኛ ፍላጎቱን በተግባር አረጋግጧል። ያ ሕዝብ ዛሬም አለ። መቼም ምርጫው በሚስጥር መሆኑ ቀርቶ በይፋ እንኳ ቢከናወን ወያኔ የድምፅ ብልጫ ያገኛል ማለት ዘበት ነው።
ነፃነት የተጠማ ሕዝብን ማን እና እንዴት ለድል ማብቃት ይቻላል?
የሚቀጥለው ምርጫ ውጤት ሊሰምር የሚችለው ይህንን ነፃነት የተጠማ ሕዝብ በትክክለኛ ጎዳና ማስጓዝ ከተቻለ ብቻ ነው። የተልፈሰፈሰ አካሄድ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ አይነት ውጤት ነው የሚኖረው። እንደ ማንኛውም ግጥሚያ ምርጫም የተቃራኒ ቡድንን ጥንካሬና ድክመት እንዲሁም አካባቢያዊ ሁኔታን ያገናዘበ፣ እንደ ሁኔታው በቀላሉ ሊለወጥ የሚችል ስትራተጂ መንደፍንና መተግበርን ይጠይቃል። የእኛን አገር የምርጫ ጨዋታ ለየት የሚያደርገው የመጫወቻ ሜዳውም ሆነ ዳኝነቱ ወገንተኛ መሆኑ ነው። ይሄ እውነታ ደግሞ በበለጠ ሁኔታ የአመራር ብቃትን፣ የዓላማ ፅናትንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። አለመታደል ሆኖ ለኢትዮጵያችን ተስፋ የነበሩ፣ ችግሮቻችንን ታሪክ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱትን ግማሹን በጥይት ሲገድሉ፣ ሌላውን ለስደት ሲዳርጉ የተቀሩትን አስረው አስቀምጠዋቸዋል።
ከዚህ አዙሪት ልንላቀቅ የምንችለው ሁሉም በያለበት የድርሻውን ሲወጣ ብቻ ነው። ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ ድርጅቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። ይኼ ፅሁፍ ከሚቀጥለው ምርጫ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው በምርጫው ለመሳተፍ ሽር ጉድ የሚሉትን ተለጣፊ ሳይሆን እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብቻ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች በበደል የተንገፈገፈንና ለለውጥ ዝግጁ የሆነን ሕዝብ በትክክለኛ ጎዳና በመምራት ለድል የማብቃት ሃላፊነትም ግዴታም አለባቸው። የነዚህን ድርጅቶች ጥሪ ተቀብሎ በመተግበርና ለትክክለኛ ጉዞው የበኩሉን አስተዋፅዖ በመወጣት የሚቀጥለውን ምርጫ በድል አድራጊነት ለመወጣት ሕዝቡም የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል። በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እይታ የእስካሁኑ የምርጫ ተሞክሮአችን የሚያሳየን (በ97 ከተስተዋለው በስተቀር) ራዕይ ማጣትን፣ የአመራር ችግርንና ቁርጠኛ አለመሆንን ነው።
የትግራይን ሕዝብ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ ከንባታውን ለማቀፍ አይችልም። የሃዲያውም እንደዚሁ የሌላውን ብሄረሰብ ለማሳተፍ በተግባር ዝግጁ አይደለም። የሃዲያው ፓርቲ ምርጫ ቢያሸንፍ እንኳ መንግስት መመስረት ስለማይችል ፖሊሲውን ማስፈፀም አይችልም። እንኳን የፌዴራል መንግስትን ለማዋቀር የክልል መንግስትን እንኳ መመስረት አይችልም። አሁን ባለው ሁኔታ ማንም ብሄረሰብን መሰረት አድርጎ የሚንቃሳቀስ ፓርቲ ብቻውን የፌዴራል መንግስትን ሊመሰርት አይችልም። በክልል ደረጃም ይከብዳል። ስለዚህ ብሄረሰብን አማክለው የተነሱ ፓርቲዎች ባጠቃላይ ተወዳዳሪዎቻቸውን ፓርላማ ከማስገባት የዘለለ ራዕይ የሌላቸው መናጆዎች ናቸው ማለት ነው። እስካሁንም የታዘብነው የነዚህ ፓርቲ አመራሮች ብቻ ፓርላማ ሲገቡ ነው። በተጨማሪም አንድ ግለሰብ የፖለቲካ ፓርቲን የሚቀላቀለው ወይንም የሚተወው ፓርቲው የሚከተለውን አቅጣጫ በመመርመር እንጂ ወዶና ፈቅዶ ባልሆነው እሱነቱ ላይ ተመስርቶ ባለመሆኑ ተሳትፎን ይገድባል። በሌላ መልኩ ደግሞ በብሄር አለመደራጀት ማለት የብሄር ጥያቄን አይፈታም ማለት አይደለም።
ወያኔ ይህንን ጠንቅቆ ስለተረዳ በብሄር የተዋቀረን ድርጅት እምብዛም አይፈራም። ለቅንጅት በኋላም ለአንድነት ያለው ፍራቻ ግን ወደር የለውም። በብሄር የተዋቀረ ፓርቲ ለወያኔ ሁሌም ቢኖርለትና ምርጫ ቢወዳደርለት ስልጣኑን ስለማይነካው ነገር ግን ሕጋዊ አሸናፊ እንዲሆን ስለሚራዳው ደስተኛ ነው። ስለዚህ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች ራዕያቸውን ሊመረምሩ ይገባል። የሌሎችን ድጋፍ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ መደራጀትና መስራት አስፈላጊነቱ የጎላና ወቅታዊ ነው። የቀድሞው ቅንጅት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቀልብ የገዛው ያራምድ የነበረው አቅጣጫ ሁሉን ያሳትፍ ስለነበረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ምንም እንኳ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ አደረጃጀትን ለመቀየር ባያመችም ከሌሎች ጋር ለመስራት ግን ቁርጠኝነትን ማሳየት አማራጭ የለውም። ብሄርን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች በሰከነ አመራር ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል ወደ ህብረት የሚያመጣቸውን ጎዳና መፈለግ ይኖርባቸዋል። ሕዝብ የተጠማው ሕብረትንና አንድነትን እንጂ መከፋፈልንና ጎጠኝነትን እንዳልሆነ ልብ ሊሉት ይገባል። እመራዋለሁ የሚባለውም ሕዝብ ምን እሆን ይሆን ከሚል ፍራቻና ጥርጣሬ በመነጨ እንጂ የፖለቲካ ስልጣንን ተቆጣጥሮ ለውጥ የማያመጣን በሙሉ ልቡ አምኖና ተቀብሎ እንደማይደግፍ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ትክክለኛ ራዕይን ሰንቆ ከፍፃሜ ለማድረስ መትጋት ያስፈልጋል።
ሕብረት በመፍጠር ሂደትም ሆነ ከሕብረት ማግስት ለብዙሐኑ ውሳኔ መገዛት ተገቢ ነው። ከዚህ በፊት እንደተስተዋለው በጋራ የተወሰነን ውሳኔ በተናጠል ማፍረስ ኢዲሞክራሲያዊ ነው። ሕዝብን እወክላለሁ፣ እመራለሁ ከሚል ግለሰብ የሚጠበቅ አይደለም። ይህንን ድርጊት በፈፀሙት ላይ ሕዝብ ከፍተኛ አዘኔታ የተሰማው ሲሆን በግለሰቦቹ ላይ አሳድሮ የነበረውን እምነት እንዲሸረሸር ሆኗል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት የአመራር ብቃትና ቁርጠኝነት ናቸው። ሕዝብን ወደተፈለገው ግብ ለማድረስ ወቅቱ የሚጠይቀውን ስልት መንደፍና መከተል ብሎም በቁርጠኝነት መከወን ያስፈልጋል። የፓርቲ መሪ ወይንም አመራር አባል ነኝ ለማለት ብቻ ፓርቲ መስርቶ መንቀሳቀስና ምርጫ ሲደርስ መንደፋደፍ ዋጋ አይኖረውም። ለውጤት መስራት ያስፈልጋል። ለውጤት ሲሰራ ወያኔ ዝም ብሎ ይመለከታል ማለት አይደለም። ነገር ግን ያንን ሊቋቋም የሚችልን ስልት መንደፍ ያስፈልጋል። ካልሆነ ደግሞ እውነቱን ለሕዝብ ግልፅ አድርጎ ሌላ አቅጣጫን መያዝ ብልህነት ነው። የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ “አማራጭ ስላጣን ነው ምን እናድርግ?” ሲሉ ተደምጠዋል። ይኼ የሚያሳየው ቁርጠኛ አለመሆንን እና ተንበርካኪነትን ነው። የጠፋው ቁርጠኝነት እንጂ አማራጭማ ሞልቷል። ሌሎችም እያደረጉት ነው። አመራር ላይ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከውጤት ጋር የተያያዘ የስልጣን የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል። ውጤት ካላስገኙ ቦታውን ለሌላ መልቀቅ ወይንም ደግሞ የትግል አቅጣጫ ለውጥን ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣምና አንዱን ጉዳይ፣ በተለይ ደግሞ ሕዝብን የመምራትና ወደስልጣን የማምጣት ጉዳይ በተለይ በአመራሩ ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ሁለትና ከዚያ በላይ ዓይነት ስራ መስራት ጥንካሬ ቢሆንም ጥሩ ውጤት ሳያመጡ እዛም እዚህም መርገጥ ግን ከንቱ ነው። ሌላኛው የፓርቲ መሪ ያሳለፉትን አመት ለመገምገም ሞክረው ያሳተሟቸውን ጥናታዊ ፅሁፎች ብዛት ጠቅሰዋል። (የፅሁፎቹ ይዘት በዋናነት ከሚታገሉለት ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ከማድረግ ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም።) በርግጥ አንድ ሰው ባሳለፍኩት ዓመት ምን ሰራሁ ብሎ ራሱን መገምገሙ የሚያስደስት ቢሆንም ከጥናታዊ ፅሁፌስ ባሻገር እመራሃለሁ፣ ለድል አበቃሃለው ያልኩትን ህዝብስ የት አደረስኩት? ሕዝቡስ ምን እያለኝ ነው? የሚሉትንም ማንሳት ተገቢ ነው። ለወደፊትስ እንዴት አድርጌ እመራዋለሁ? ካልሆነስ? የሚሉትም በቀጣይ እቅድ ውስጥ ቢካተቱ ጥሩ ነበር። እቃወመዋለሁ ከሚባለው ወያኔ እኩል እድሜ አስቆጥሮ የሕዝብን የነፃነት ጥማት በወጉ ሳያረካ ስለጥናታዊ ፅሁፍ ማውራት ተገቢነቱ አጠያያቂ ነውና ሕዝብ ተስፋ ከመቁረጡ በፊት ራሳቸውን ቢገመግሙ መልካም ነው።
ምንም እንኳ የዲምክራሲ ግንባታ ሂደት ቢሆንም መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰብዓዊና ሕጋዊ መብቶች መከበር ጊዜን የሚጠይቁ ባለመሆናቸው ትግሉ ጊዜ ይፈጃልና ለልጅ ልጆቻችሁ ቢሆን እንኳ እስቲ በትዕግስት ጠብቁ ብሎ ማወጅ ሕዝብን ከትግል ጎዳና ማራቅ ነው። በሚቀጥለው ምርጫ ምንም አትጠብቁ፣ ምንም አንፈጥርም እንደማለት ነው። በተጨማሪም እኔው እየተንተፋተፍኩ ለመምራት እሞክራለሁ፣ ሌላም ቢመጣ በዚሁ ጎዳና ይጓዛል አይነት ዲስኩር ነው። ምናልባትም ይኼ ንግግር ሃላፊነትን ከመሸሽና ከዓላማ ቢስነት የመነጨ ካልሆነ በስተቀር ከአመራር አባል የሚጠበቅ አይደለም። ይህንን ራዕይ ሰንቆ መጓዝ አንድ እርምጃ እንኳ አያራምድም።
እኛ የምርጫ ፓርቲ ነን ብሎ በአደባባይ መለፈፍ ብቻ ሳይሆን በአሸናፊነት ለመወጣት ተግቶ መስራት ተገቢ ነው። ለምርጫ አመቺ ሁኔታ ከሌለ ደግሞ አለመሳተፍና ሕዝብ እንዳይመርጥ ማድረግም ሌላኛው አቅጣጫ መሆን አለበት። ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ከማያደርግ ነገር ግን ከዚህ በፊት እንደታየው የፓርቲ አመራርን ብቻ ፓርላማ ለማስገባት ከሚደረግ ሩጫ መታቀብ ተገቢ ነው። ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከዚህ በፊት ፓርላማ ይገቡ የነበሩት ምንም እንዳልፈየዱ፤ ይልቁንም በአገሪቱ ውስጥ የብዙሃን ፓርቲ ያለ ያስመሰሉበት፤ መናጆ በመሆን ለወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ህጋዊነትን በመቸር እድሜውን ያራዘሙበት ሁኔታ ስለሆነ አለመሞከሩ ተገቢ ነው። ሁኔታውን መርምረው ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ እና ሕዝቡ በራሱ ግምገማ በምርጫው ባይሳተፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሕዝብ ይፋቱና አጎብዳጅነታቸው ይፋ ይሆናል ማለት ነው። በሌላ በኩል የሕብረት ጉዞአቸውን አጠናክረው የአመራር ብቃታቸውን፣ ስክነታቸውንና ፅናታቸውን ካስመሰከሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው ይሰለፋል። ለሚያሰሙት ጥሪ ሁሉ ፈጥኖ ምላሽ ይሰጣል። የሚጠበቀው ድልም አይርቅም። ይኼ ካልሆነ ግን ሕዝብ አንቅሮ እንደሚተፋቸው ለአፍታም መዘንጋት የለባቸውም።
ሕዝብስ ምን ያድርግ?
በሚቀጥለው ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታው እንደፈቀደ በምርጫው አለመሳተፍ ወይንም በነቂስ ወጥቶ የሚፈልገውን መምረጥና ውጤቱን ማስከበር ይኖርበታል። ቅድመ ምርጫን ገምግሞ በምርጫው ባለመሳተፍ ሕዝቡ ድል አድራጊ በመሆን የሚቀጥለውን የትግል መድረክ ማዘጋጀት ይችላል። የተልፈሰፈሰ የተቃዋሚ ፓርቲ አካሄድ ካለና የወያኔ አፈና የበዛበት የቅድመ ምርጫ ሁኔታ ከታየ ወይንም ወያኔ እንደ እስስት በየጊዜው ራሱን ስለሚቀያይር ይኸው ሊፈጠር ይችላል ብሎ ካመነ በምርጫው መሳተፍ አስፈላጊ አይሆንም። በምርጫ ዋዜማ ተለሳልሶ በምርጫው ወቅትና ማግስት ሊያመጣ የሚችለው ስለማይታወቅ የተቃዋሚዎችን ጥንካሬ መፈተሽ ተገቢ ነው። የሕዝብን ድምፅ ለማስከበር የሚጥር ተቃዋሚ ፓርቲ ሲኖር ብቻ ወደ ምርጫ ማቅናት ተገቢ ይሆናል።
ምናልባትም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የታዩባቸውን ችግሮች ፈትተውና ጠንከር ብለው ከተገኙ፤ በተለይ ደግሞ የሕዝብን ድምፅ ለማስከበር ቁርጠኝነትን ካሳዩ በምርጫ መሳተፉ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በነቂስ ወጥቶ መምረጥና ውጤቱን ማስጠበቅ ተገቢ ይሆናል። በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እንዳየነውና በማየት ላይ እንዳለነው ድምፅን ለማስከበር የሚደርገውን ትግል ምንም ኃይል ሊገታው አይችልም። ወያኔም በምንም መልኩ ሊቋቋመው አይችልም። በሕዝብ እንቢተኝነትና መስዋዕትነት የሚፈለገውን ድል ማጣጣም ይቻላል። ታግሎ የሚያታግል፣ የሰከነ የአመራር ብቃት ግን ከተቃዋሚዎች ይጠበቃል።
ማጠቃለያ
ሕዝብን ያማከለ ጠንካራ የተቃዋሚ አመራር የሚቀጥለውን ምርጫ በሚገባ ሊያሸንፍ ይችላል። በመሳተፍ ብቻ ሳይሆን ባለመሳተፍም ድል ማድረግ እንደሚቻል ልብ ሊባል ይገባል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕብረት ሊያስጉዝ የሚያስችላቸውን ትልም ቀይሰው በምርጫው ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን ድል ለማድረግ በሰከነ አመራር የሚተጉ ከሆነ የሕዝብን አመኔታና ይሁንታ ያገኛሉ። ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ስለሚመርጣቸው አሸናፊነታቸው ይረጋገጣል ማለት ነው። ወያኔ ውጤቱን ላለመቀበል ቢዳዳው እንኳ ሕዝብን በማሰለፍ ማስከበር ይቻላል። የተልፈሰፈሰ ተቃዋሚና የወያኔ አፈና ከመጠን ካለፈ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚቀጥለው ምርጫ መሳተፍ የለበትም። አለመሳተፉ ደግሞ የወያኔን ህጋዊነት ስለሚነሳ ቀጣዩ ትግል ይህንን እንቢተኛ ዘረኛ ቡድን በተለየ የትግል ስልት ከሌሎች ጋር ኃይልን በማቀናጀት መተግተግ ይሆናል ማለት ነው።
ለሕዝብ ድምፅ የበላይነት ሁላችንም እንረባረብ!



