ዣንጥራር ተክሌ (ከቫንኩቨር-ካናዳ)

አረጋሽ ለአድዋ፤ አድዋም ለአረጋሽ

ብለህ ብለህ አረጋሽን? ደግሞ ምን አመጣህብን?

ይሄንን የምጽፈው እንድታምኑ አይደለም። ሀሳብን ያለማብላላትና ያለማቁላላት፤ ለተቃውሞ ተቀባብለው ለተቀመጡ ሰዎች ለግንዛቤ እንዲረዳ ነው። አንዳንድ ሰዎች አሁን ይሄንን የማውሪያ ጊዜ ነው እንዴ? ሌላ ስንት ነገር እያለ ይላሉ።

 

ግን ደግሞ አንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች አይደገሙም። ቢደገሙም አመታት ቆይተው ነው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት ውስጥ ስለመወገዳችው ፍንጭ የሚሰጥ ምንም ነገር የለም። አስራ ስምንት አመት ያየነው ፍንጭ ደግሞ እስካሁን ምንም አልወለደም ባልልም፡ የተወለደው ሁሉ በእንጭጭ እየቀረብን ነው። 

 

ከዚህ ቀደም፡ በኤርትራ በቀር የኢትዮጵያ መዳን በማንም የለም ብዬ የጻፍኩትን ጽሁፍ የሚያስታውሱ ሰዎች፤ ይሄ ሰውዬ ጤነኛም አይደለም የሚል ፈጣን ድምዳሜ ላይ ይደርሱ ይሆናል። ሁለቱንም ያልኩበት ሁኔታ የተለያየ ነውና ያኛውን እንደተውኩት፣ ይሄኛውን እንዳነሳሁት እንዳታስቡ። ሁሉንም አምንበታለሁ። የኤርትራውንም የትግራዩንም የድህነት (የመዳን) መንገድ። እኔና ሌሎች በጣት የምንቆጠር በቫንኩቨር የምንኖር ጓደኞቼ በአድዋ አቶ መለስን ሊፎካከሩ የተነሱትን ወ/ሮ አረጋሽ አዳነን በገንዘብ ለመርዳት ትንሽ ላይ ታች እያልን እንደሆነ ሲዘገብ ብዙ ሰዎች ግራ ገብቷቸዋል። እኛንም ግራ የገባን መስሏቸዋል። ወ/ሮ አዳነችን ለመርዳትም ይሁን ይሄንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ ስለኢትዮጵያ የያዝኳቸው ግምቶች ነበሩ። አሉም። (እዚህ ጽሁፍ ውስጥ እኔና እኛ እያልኩ ነው የምጽፈው። እኔ በምልበት ቦታ ላይ እኔ ብቻ ነኝ። እኛ ስል ደግሞ እኛ።)

 

ኢትዮጵያዊ ግምቶቼና መላምቶቼ፦

 

ስለኔ እንዳትሳሳቱ። አንደኛ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ አለ ብዬ አላምንም። ይሄንን እኔ ብቻ አይደለሁም፡ ይሄንን አለምአቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችም ይሉታል። ይሁን እንጂ ሁለተኛ፡  አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን መወዳደር እንፈልጋለን ብለው የሚነሱ ደፋሮች ካሉ፤ በርግጥም ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ እንደሌላ ለማጋለጥና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት እንደ አንድ የመንቀሳቀሻ እድልም ለመጠቀም በመጪው “ምርጫ” ቢሳተፉ መልካም ነውና ልናግዛቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ሶስተኛ፤ በዚህም ይሁን በሌላ ምርጫ ወይንም በሰላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እናመጣለን ብለን ካሰብን መጀመሪያ ማሸነፍ ያለብን በትግራይ ነው። በትግራይ ማሸነፍ ካልቻልንና አሁን ስልጣን ላይ ያለው ስርአት በሀይል ከተለወጠ፡ ከዚህ ስርአት ጋር የተባበሩ ሁሉ፡ የህይወትም ይሁን የሌላ ዋስትና የላቸውም። ይሄ የቅርብ ግዜ የፖለቲካ ታሪካችን ነው። በኢትዮጵያም ይሁን በሌላው የዓለም ታሪክ ስልጣን በሀይል ነጥቆ፤ ስልጣን የተነጠቀውን ሀይልና ደጋፊዎች ያላጠቃ መንግስት ወይም አገዛዝ የለም። ይሄ ወደ አራተኛው መላምት ይወስደኛል።

 

አራተኛ በሰለማዊም ይሁን በአመጽ ትግል በሚመጣ ለውጥ ምክንያት ልንጠቃ እንችላለን ብለው ለሚያስቡና፤ ሳያምኑበት ይሄንን ስርአት ለሚደግፉ ሰዎች ለውጥ ቢመጣ እንደማናጠቃቸው ዋስትና ልንሰጣቸውና ከጎናችን ልናሰልፋቸው ይገባል ማለት ነው። እንደ አረጋሽና ስዬ ያሉ ሰዎችን ምርጫ  በሌለው ምርጫ እንዲያሸንፉ መርዳትና ከጎናችን ማሰለፍ በትግራይ ህዝብና በሕወሀት ደጋፊዎች ዘንድ መረጋጋት እንዲኖርና ፍርሀት እንዳይኖር ያደርጋል። ባለፈው የሁለት ሺህ ምርጫ ህወሀት አንዱ ህዝቡን የለያየበትና አሁንም ድረስ እንደነአቶ ግዛቸው ሽፈራው አይነት ሰዎች እዚህ ሰሜን አሜሪካን የመጣች ጊዜም ብርቱካን ሚደቅሳ ራሷ ይቅርታ የጠየቀችበት አንዱ ፖለቲካዊ ጉዳይ ይሄ ቅንጅቶች ትግሬን ለማጥቃት መጡ ብሎ አቶ መለስና ወዳጆቹ ከነዙት ፍራቻ የመነጨ ነው። አሁን ግን ቢያንስ በምንም መልኩ እሱን አሳልፈው የማይሰጡትና ለሱም የተዋጉለት ልጆች እነ ስዬ አብርሀ፣ እነ አረጋሽና ገብሩ ስላሉለት ያንን ያረጀ ፍርሀት ደግሞ መጠቀም አይችልም። በሌላ አነጋገር የምንመሰርተው አንድነት አንድነት የሚል ድርጀት፤ በርግጥም አንድነትን የሚያሳይ መሆን አለበት እንጂ ጠላት ነው ያሉትን ሁሉ ሊውጥ የተዘጋጀ የአማሮች ስብስብ መምሰል የለበትም። ስለዚህም ነው አረጋሽን ለአድዋ ያልነው። አረጋሽ ለአድዋም ይሁን ለኢትዮጵያ እንደምትመጥን ግን ታሪኳና ንስሀዋ ይናገራል።

 

አረጋሽ አዳነ ጣይቱ ብጡልን ብትሆንስ?

 

የኢትዮጵያው እስክንድር ነጋ ቀደመኝ እንጂ፡ እኔም አረጋሽን ስልክ ደውዬ አግኝቻት ለአንድ ሰዓት ያህል አውግተን በር። የትግርኛ ተናጋሪዎች አማርኛ ደስ ይላል። እንደወረደ ነው። ቅኔና ተንኮል የለውም። ቀና ነው። ከአረጋሽ ቃለ ምልልስ የተረዳሁት መለስ ለአረጋሽ የግል ጠላቷም እንደሆነ ነው። ሕይወቷንና ወጣትነቷን ከሰዋችለት ድርጅትና ክብር አውርዶ መሬት ከስክሶ ያለጡረታ ያስቀራት ጠላቷ ነው። ምርጫ ስለጠፋና ህዝቡን እኔ ከሌለሁ ተበላህ እያለ እያስፈራራ ነው የያዘው ባይ ነች። እኔ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በሰላማዊና ምርጫ በሚባል ፌዝ ለውጥ ይመጣል ብዬ ባላምንም በዚያ መንገድ ለውጥ ይመጣል ብለው ለሚያምኑ ግን ትግራይን ማሸነፍ የግድ ነውና፤ የትግራይን ልብ ለመርታት ደግሞ ከልጆቹ የተሻለና የቀረበ የለም። አረጋሽ ሴቲቱ ደግሞ ለዚህ ብቁ እጩ ነች። አረጋሽ ለአድዋ ጣይቱ ብጡልን የማትሆንበት ምክንያት አይታየኝም።

 

የዛሬ መቶ አስራ አራት ዓመት አካባቢ አጼ ምኒሊክ ጣሊያንንና ባንዳውን ሲረቱ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡልም ጡር እየመሩ የድሉ ተካፋይ ነበሩ። እነሆ ዛሬም ታሪክ ራሱን ሊደግም ነው። ያኔ በታንክ ነበር። አሁን ግን አረጋሽ በሾኬ ብላለች። ታንኩንም ቢሆን ገና በሀያዎቹ እያለች እኩዮቿ ከተማ ውስጥ ሲዳሩ እሷ በጫካ አስኪዳዋለች። እነሆ አሁንም ሞራሏ ሳይሞት ይሄንን ባንዳ ልትገጥም ከተነሳች ቢቻል ጥይት ማቀበል እንጂ የታባቷ ይህቺ የቀድሞ ሕወሀት ብሎ ማንጉዋጠጥ ብልህነት አይደለም። ፖለቲካዊ ጅልነት ነው። ያልደገፈና ለብሩ የሰሰተ እጁንም አፉንም ይሰብስብ። ጀግናንማ ማበረታታት ነው እንጂ። ችግሩ እኛ የጠላት ጀግንነት አይታየንም። ጠላት ሆኖ ሳለም ወዳጅ ሆኖ ሳለም። የጀግኖችን ሁሉ ታሪክ ብንገመግም ግን ጠላቶቻቸውን አይንቁም። ለዚህ ነው ታላቁ ወዳጄ ጋሽ ተክሌ እንዳጫወተኝ ካልረሳሁት ለአጼ ቴዎድሮስ ወንድምና ባላጋራ ጋረድ እንዲህ ተብሎ የተገጠመለት፡

 

ጋረድ ሞተ እንኩዋን ተቀበረ፣

ወንድምህ ነውና እንፈራው ነበረ።

 

ጋረድ አጼ ቴዎድሮስን ይቀናቀን የነበረ፤ ጀግና ተዋጊ ነው። በሁዋላ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ሲዋጋ ተገደለ (ታሪኩን ካልተሳሳትኩኝ)። እና አልቃሽ ነች እንዲያ ብላ የተቀኘችለት። አጼ ቴዎድሮስም ጀግንነቱን ያውቁለታል። ያው የሳቸው ወንድም እንደሳቸው ነው።

 

አንዳንድ ሰዎች፡ እኛ ለዴሞክራሲ እንታገላለን የምንል ሰዎች የወያኔን ለዚያውም የሕወሀት ማእከላዊ ምክርቤት አባል የነበረችንና በኋላ በራሳቸው የውስጥ ንትርክ ከነበረችበት የስልጣን መንበር የተባረረችን ሴት ታሪክ ስንጽፍ ግርም ሊላቸው ይችላል። ፋይዳውም ላይታያቸው ይችላል። እኔ እንደመሰለኝ ግን አንዱ እስካሁንም ለውጤት ላለመብቃታችን ምክንያት ጠላት አድርገን የምናስቀምጠውን ሀይል አመጣጥና ታሪክ ሆን ብለን ለመርሳት መሞከራችን ነው። ያ አንድም ጠላትን እንድንንቀው፡ ሌላም ደግሞ ጠላትን እንዳናውቀው አድርጎን ይሄንን ሀያል ጠላት ለመጣል ከኛም የሚፈለገውን በቅጡ እንዳናውቅ አድርጎናል። ያረጋሽን ታሪክ መስማት አለብን። በተለይ ደግሞ ሰላማዊ ትግል አልቆለታል ወይንም አይቻልም የምንልና ይሄንን ስርአት በጠብ መንጃ ብቻ ነው የምንጥል የምንል እንደኔ አይነት ሰዎች ያረጋሽን ታሪክ እስኪያቅለሸልሸን መስማት አለብን። የትጥቅ ትግልን ነገር አውቀነው ብንገባበት ይሻላል።

 

ይህቺ ሴት ማናት? ማንስ ነበረች? መለስንስ እንዴት ታየዋለች?

 

ወደ ጫካ ስትገባ እድሜዋ የሀያዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር። ሀያ ሶስት ሀያ አራት አካባቢ። በ1968። በጭራሽ አልጠበቅኩም። ያው እንደትግል አጋሮቿ እሷም አቋራጭ መስላኝ ነበር። ኖ ኖ፡ አይደለችም። በ1961 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብታ፡ በ1965 በሶሻል ወርክ በድግሪ ተመረቀች። እስከ 1968 ድረስ አዲስ አበባ ሰራች። ከዚያ ግን ሽራሮ ሄዳ 9 ወር ሰራች። ዘጠኙን ወር የተላከችበትን ስራ ብቻ አይደለም የሰራችው። ያልተላከችበትን ግን የተነሳችበትንም ጭምር እንጅ። ሽራሮ አካባቢ እየሰራች አካባቢውንም እየተለማመደች ድርጅታቸው እስኪጠናከር ቆየችና ድርጅታቸው ሴቶችን መቀበል ሲጀምር ቆርጣ ገባች። ጫካ።

 

እና በምን በምን ሀላፊነት አገለገልሽ? በየትኛዎቹ ውጊያዎችስ ተሳትፈሻል? ብዬ ጠየቅኳት። መጀመሪያ ቅድመ-ግንባር የሚሉት ደረጃ አለ ወታደራዊ ስልጠና የምናገኝበት። ከዚያ ግን የፖለቲካ ስራ እንድሰራ ተመደብኩኝ። በተለያዩ ስፍራዎችና ምድቦች አገልግያለሁ። በተለይ በማንቃትና በማደራጀት፤ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ሀላፊነቶች በደጀንም ጭምር አገልግያለሁ። የስራ ክፍፍል አለ እንጂ አጠቃላይ የነበርንበት ሁኔታ የውጊያ ነበር። በነገራችን ላይ የተወለደችው መቀሌ ነው። ከዚያ ግን አድዋ ነው ያደገችውና ትምህርት የጨረሰችው።

 

በ1975 ዓ.ም. የማእከላዊ ም/ቤት አባል ሆና ተመረጠች። እስከ 1993 ድረስም በዚያ ሀላፊነት ስትሰራ ነበር። በ1992 በዋናው የምርጫ እቃቃ ዘመን ለፌደራል ምክር ቤት አባልነት ተወዳድራ አሸነፈች። ያው ምርጫው ምርጫ እንዳልነበር ታምናለች ያኔም ቢሆን። ብቻዋን ተወዳድራ ነው ያሸነፈችው። ግን ምን ዋጋ አለው፡ በ1993 መለስ አወረዳቸው። የወረድንበት ሁኔታ ህግን የተከተለ አልነበረም ባይ ነች። ካድሬዎች ትግራይ በየቀበሌውና በየቤቱ እየዞሩ እምቢ ካላችሁ የረድኤት ምግብ አንሰጣችሁም እያሉ ነው ያስፈረሙት። ህዝቡ ተቃውሞ ነበር። መርጠናታል፤ ምንም እንከን አላገኘንባትም ለምንድነው አሁን አውርዱ የምትሉን ብሎ ሰዉ ተቃውሞ ነበር። በራስ እንደሚደርስ ነገር የሚያስተምር ነገር የለም። በራሷ ሲደርስባት ነቃች፤ በረታች እንጂ ባጠቃላይ ቀድሞውንም የታገሉለት ነገር፣ የሞቱለት ዓላማ ግቡን እንዳልመታ ነው የምታምነው። በፊትም አሁንም። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ባሰ ባይ ነች። ያ ብዙ ወጣት የተሰዋለት የዴሞክራሲ ጥያቄ አልተመለሰም። አሁን አምባገነንነት እየሰፈነ ነው ያለው። የለየለት አምባገነንት። እንደገና ድርጅት ውስጥ ገብቼ መታገል የመረጥኩትም ለዚያ ነው አለችኝ።

 

በነገራችን ላይ ምን አጣላችሁ? ምንስ ለያያችሁ? ደም አልተቃባችሁ?

 

ከሻእቢያ ወረራ በፊት አስረኛ ዓመት ጉባኤያችንን ከማካሄዳችን በፊት ራሳችንን ለመገምገም ፕሮግራም ነበረን። “እንደድሮው አይደላችሁም። ብዙ ችግር አለ። ፍትህ የለም፤ እንንገላታለን።” የሚል ወቀሳ ከህብረተሰቡ በመሰንዘሩ አስረኛ አመታችንንና ጉባኤያችንን  ከማክበራችን በፊት መሰረታዊ ግምገማ ለማድረግ ዝግጅት ስናደርግ የኤርትራና ኢትዮጵያ ጦርነት ተነሳ። ግምገማው ቀረና ወደ ጦርነቱ ተመለስን። ከጦርነቱ በኋላ እንደገና ግምገማ ለማድረግ ስንሰናዳ አለመግባባት ተፈጠረ። ተለያየን። ዋናው የሉአላዊነት ጥያቄ ቀረና የሙስና ጉዳይ መጣ። አቋረጥኳትና በነገራችን ላይ ሀብት አለሽ ይባላል እና እስኪ እሱንም ንገሪኝ አልኳት። በክፍፍሉ ግዜ ሙስና አለ ብዙ ህገ ወጥ ሀብት ያካበቱ አሉ ተባለ። ስለዚህ ሙስና ካለ ሀብታችንን የሚመረምር ነጻ አካል ይቋቋምና ይጣራ አልን። የማይታወቅ ሀብት ያለው ከተገኘ ተጠያቂ ሆኖ ይጣራ ስንል፤ እነሱ እነመለስ ግን ፍላጎታቸው አንድ ሰው አቶ ስዬን ለይቶ መምታት ስለነበርና ምርመራው ከተካሄደ በሙሉ የመለስ አጋፋሪዎች ስለሚጠየቁ የሱን ወዳጁች ለመጠበቅ ሲባል መለስ እምቢ አለ። በኋላም አቶ ስዬን ወስደው አሰሯቸው።

 

አሁንስ ደመወዝ አለሽ? አልኳት። ምንም። ጡረታ የለኝም። ይቅርታ ካልጠየቃችሁ አይሰጣችሁም ተብለን ያለ ጡረታ ነው ያለነው። የመንግስት ቤት ተከራይቼ ነው ያለሁት። ከተጣላን በኋላ ትልልቅ የምናከብራቸው ሽማግሌዎች ተልከው ተመልሰን እንድንገባ ተለምነን ነበር። ያን ግዜ አገር ቤት ገብታችሁ ነጠላ አንጥፋችሁ ለምናችሁ ትበላላችሁ ወይንም በረሀብ ትሞታላችሁ ብሎ ዝቶ ይቅርታ ጠይቀን እንድንገባ ሲለምነን፤ የለም የታገልነው ለዓላማ ነው። እንደውም በሕይወት ተርፈን ስልጣን እንይዛለን ብለን ያሰብንም አልነበርንም። ዛሬ ያ ሁሉ ወጣት ተሰውቶ እኔ ልመና ፈርቼ ባላጠፋሁት ጥፋት ይቅርታ ጠይቄ አልገባም ብዬ ቀረሁ። እነመለስ ግን እኛን ለማስጠላት፡ ካድሬውን ሁሉ እየወሰዱ የኔ ያልሆነ ቤትና ንብረት የአረጋሽ ነው እያሉ ሲያሳዩ ነበር። አንድ ጊዜ በ1992 ዓ.ም. ሄደሽ መርቂ ብለው የላኩኝንና የመረቅኩትን የግል ሆስፒታል የአረጋሽ ነው እያሉ እያሳዩ፣ ያንድ አሜሪካን ያለች ጓደኛዬ መኖሪያ ቤትንም እንደዚሁ የሷ ነው እያሉ ካድሬውን አሳስተውታል። እኔ ደመወዜ ጥቂት ነበረች። ከዚያ ላይ ምን ያህል ተርፎ ምን ያህል ተጠራቅሞ ቤት ልገዛ እንደምችል እንጃ።

 

ስላሁኑ ምርጫስ፡ እውን ታሸንፊያለሽ?

 

እንዴት ነው ግን ባሁኑ ምርጫ፤  እንደልብ እየተዘዋወርሽ መቀስቀስ፣ ማስታወቂያ መለጠፍ ትችያለሽ? አባላት አሏችሁ? ቢሮስ? እሷም መለሰች። ማስታወቂያ መለጠፍ እችላለሁ። ችግሩ ግን ዘወር ስንል ካድሬዎች እየመጡ ይገነጥሉታል። አየህ በምርጫ ለማሸነፍ ህዝብ ሁላችንንም ሰምቶ የሚፈርድበት የተረጋጋ መንፈስ ሊኖር ይገባል። አሁን ያ የለም። እውነተኛ ምርጫ ከተደረገ፤ በደንብ የማሸንፍበት እድል አለ። ሕዝቡ አሁን ባለው አገዛዝ ደስተኛ አይደለም። በዘመድ ይሰራል። ጉቦ በዝቷል። የአስተዳደር ችግር፣ የፍትህ እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ የውሀና የሌሎች አገልግሎቶች መጓደል ሰፍኗል። በሬድዮና በቴሌቪዥን የሚነገረውና የሚለፈፈው ድልና ልማት በተግባር የለም። ህዝብ ሌላ አማራጭና ምርጫ ይፈልጋል። አስራ ስምንት አመት ሙሉ የተለፈፈው ምንም ነገር የለም።

 

ስለመተዳደሪያዋም ጠየቅኳት። መጀመሪያ ስራ አጥቼ ተንከራትቻለሁ። ቀጣሪዎች ሁሉ እኛን እንዳይቀጥሩ ተከልክለው ነበር። አንዱ ግን የመጣው ይምጣ ብሎ ቀጠረኝ። ስራ ጀመርኩ። አሁን ግን ወደ ምርጫ ስገባ ጫና በዛበትና ከስራ አባረውኛል። (አንባቢያን፡ እንግዲህ ይሄንን ሁሉ የምተረትረው ይህቺን ሴት ለምን ከመለስና ተከታዮቹ ጋር ለምናደርገው ትግል አስፈላጊ አጋር መሆን እንደምትችል ለማሳየትና መረዳት እንዳለባት ለማሳመን ነው)።

 

ሌላ ስስ ብልት ነካሁ። በነገራችን ላይ ትዳር ነበረሽ? ልጅስ? እዚህ ጋር አሳዘነችኝ። ትግል ላይ ሆነን እስከ 1977 ድረስ ትዳርም ይሁን ግንኙነት መመስረት አይቻልም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ተፈቀደ። ቢሆንም እኔ መጀመሪያውንም ወደ ትግል ስገባ እተርፋለሁ የሚል ህልም አልነበረኝምና ትዳርና ቤተሰብ የሚባለው ነገር የሚታሰብ አልነበረም። በኛ መስዋእትነት ህዝባዊ መንግስት ይመሰረታል ነው እንጂ ለራሴ ብዬ የሰዋሁትና የሰጠሁት ጊዜ አልነበረም። ቢኖርም አናሳ ነው። ልጅስ አልኳት ደግሜ፤ ድምጿ ሰለለብኝ። አሳዘነችኝም ልጅም ትዳርም ሳትል ሁሉ ነገር ሰውታ የታገለችለት ትግል በመጨረሻ መሬት ጣላት። ግን ይሄን ያህል ጊዜ ታግለሽ፣ ህይወትሽን ሁሉ ለዚህ ጉዳይ ሰጥተሽ፣ እንዴት እንዲህ ሊጨክኑብሽ ቻሉ? ፖለቲካ እንደዚህ ነው ማለት ነው? ምናለ በጡረታ እንኩዋን ቢያገሉሽ? ምን ብትበድይ ነው ይሄንን ያህል የሚያስጨክን ነገር አለ እንዴ? መልሷ አጭርና ሀይለኛ ነበር። “አረ እኔ አላውቅም። እኔ የማውቀው ፖለቲካ እንደዚህ አይደለም። እንደመሰለኝና አሁን እንደተረዳሁት ስልጣን ሲያዝ ሰዉን ያበላሸዋል። የስልጣን ፍቅር አደገ። የስልጣን ቁርኝት ነው። ግምገማ ከመጣ ያንን ክብር ሊቀንስ ሆነ። ስለዚህ አፈና ተጀመረ። ሀሳብን ማፈንና በሬድዮና በቴሌቪዥን ማስፈራራት ተጀመረ። ሌላው እኛን እንዳይከተል እኛን ማዳከምና መምታት ዋና ስልት ሆነ። አንገቱን ቀና አድርጎ እንኩዋን የሚጠይቅ ካለ እንኳን ማስፈራሪያና ሞራል መምቻ ሆንን። አሁን ያሉት ሰዎች ምቾትና ድሎትን ከአላማ በላይ አድርገው ወሰዱ። ለሌላው ማስተማሪያ።

 

እንደማሳረጊያ፡ እንደመደምደሚያ

 

“ምርጫው” ፍትሀዊ ምርጫ አይሆንም። ቢሆንም ባይሆንም ግን የውስጥም የውጭም ትግላችን የሚፈሩንን ሰዎች ወይንም ቡድኖች ያካተተና የማረከ መሆን ካለበት እንደ አረጋሽ ያሉትን ሰዎች ማቅረብ አለብን። ያለበለዚያ ግን ያለፈውን እየቆሰቆስን ሀጢያተኝነት እንዲሰማቸው የምናደርግ ከሆነ እነሱ ካጡት በላይ አያጡም። ለኛ ግን ይጎዳናል። በ2005 አዲስ አበባ ነበር። ዘንድሮ ግን ትግራይ ነው። መቀሌ። የጠፋነው በትግራይ ነው ስል ሐወሀት የተወለደውና ያደገው አሁንም የመሸገው በዚያ ነውና ነው። ስለዚህ መሸነፍ ካለበት ቀድሞ መሸነፍ ያለበት በዚያው በትግራይ ነው። በትጥቅ ትግሉም የተረታነው በዚያው በትግራይ ነው። በሰላማዊ ትግል ሕወሀትን ማሸነፍ ካለብን የምናሸንፈውም በዚያው በትግራይ ነው። ትግራይን ደግሞ ያለ ስዬና ያለአረጋሽ አይታሰብም። ይሄ ውጊያ ከኛ ይልቅ ለነሱ ወሳኝ ነው። ይሄ ሰው አዋርዷቸዋል። ይሄ ሰው ገድሏቸዋል። ጉዳዩ ፖለቲካዊ ብቻም አይደለም። የግልም ነው። ለዚህም ነው፡ ቫንኩቨር የምንገኝ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ለዚህች ሴት ሞራል ለመስጠትና የኛን ውጊያ ስለምትዋጋ ትጥቅ ባይገዛም የመንፈስ ስንቅ እንዲሆናት ትንሽ ገንዘብ ለመስጠት የተሰናዳነው። ሲያትል ያሉ የማትጠረጥሯቸው ወዳጆቻችንም ይሄንን የተቀደሰ ስራ ለማገዝ በርቱ ብለው ያላቸውን እየወረወሩ ነው።

 

መጋቢት/ሚያዚያ፡ 2002 ዓ.ም.

  

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ