ተቃዋሚው ብቃት አለውን? (ኩችዬ)
ኩችዬ - መጋቢት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. (ኤፕሪል 1 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.)
በህዝብ አዕምሮ ውስጥ ጥርጣሬ የመፍጠርን ያህል የፕሮፓጋንዳ ድል የለም። ለዚህ ማስረጃ ከፈለጋችሁ የሂትለር ቀኝ-እጅና የፕሮፓጋንዳ ጠበብት የነበረውን ጎብልስን ጠይቁት። ዓለም ሲፈጠር የት ነበርክ ትሉኛላችሁ እንጂ፤ ከያን ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል ጥርጣሬ መፍጠር የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ የሆነው።
ቀልጠፍ ብዬ ወደተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና “በርግጥ ተቃዋሚው ሀገር የመምራት ብቃት አለውን?” የሚል ጥያቄ መናፈስ የጀመረው በ‘97 ምርጫ ማግስት እንደነበር ትዝ ይለኛል። ቅንጅት ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ቆሽታቸው ያረረ ደጋፊዎች ሳይቀሩ ነው አባባሉን የብስጭታቸው መወጫ ያደረጉት - ትልቅ ስህተት! በጣም ትልቅ ስህተት! ኢህአዲግ ደግሞ እንኳንስ ይችን ያህል ቀዳዳ አግኝቶ እንዲያውም እንዲያው ነው በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን የጥርጣሬና የብሽቀት መንፈስ ደህና አድርጎ አራገበው።
እዚህ ላይ ባንድ ነገር እንስማማ። የሰው ልጅ በፍጥረቱ ተጠራጣሪና የ7 ቀን 24 ሰዓት ኑሮው በስጋት የታጠረ መሆኑን አትክዱም። ለዚህ አይደል እንዴ ኢንሹራንስ የሚገዛው? አጥር የሚያጥረው? ብቻውን የሚያወራውና የሚቃዠው? ልብ ብላችሁ ከሆነ ፖለቲከኞች ይህን ሰብዓዊ ደካማ ጎን ደህና አድርገው ነው የሚበዘብዙት …
“ነውጠኞች የቀድሞውን ሥርዓት ሊያመጡብህ ነው! እኛ ከሌለን ሀገር ትበተናለች! ሠላማዊ ኑሮህ ይናጋል! የብሔረሰቦች ነፃነት ይገፈፋል! የርስ በርስ ጦርነት ይነሳል! የእስልምና አክራሪዎች ሀገርህን ይወሩታል! ተቃዋሚው ሀገር የማስተዳደር አቅም የለውም! …”
የኢህአዲግ ፕሮፓጋንዳ መዘውር ከላይ ለአብነት የጠቀስኋቸውን የስጋት መርዕዶች በመደጋገም እንደሚጠቀምባቸው እናውቃለን። “በመደጋገም” የምትለዋን ቃል እንደዋዛ አትዩብኝ። በፕሮፓጋንዳ ሣይንስ “ስጋት” ታላቅ ወንድም ቢሆን “ድግግሞሽ” ደግሞ ታናሹ ነው። እዚህ ላይ የኢህአዲግ ዘመቻ በኢትዮጵያ ውስጥ የስጋት ድባብ አልፈጠረም የሚለኝ ቢመጣ “አንተ የሰጎኗ ወንድም ነህ!” ከማለት አላስተርፈውም። ዕለት ተለት በስጋት አየር ውስጥ የሚኖሩት ወገኖቻችን ቀርተው ያሜሪካና ያውሮፓ መንግሥታትም የዚህ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጭዳ ሆነዋል። “ህምምም!” በሚያሰኝ ጥርጣሬ ውስጥ ለመውደቃቸው አንድና ሁለት የለውም። ራሳቸው ሳይደብቁ ይነግሩን የለም እንዴ?
ታዲያ ሁለት ዓቢይ ችግሮች ይታዩኛል። አንደኛው ችግር ተቃዋሚው ወገን የዚህን ፕሮፓጋንዳ አደገኛነት ተገንዝቦ ቀጣይነት ያለው አምካኝ ፕሮፓጋንዳ በፈረንጁ ሰፈር ጭምር አለማካሄዱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ችግር ደግሞ የተቃዋሚው የፖለቲካ ገጽታ በመንግሥት እንዲነደፍ መፈቀዱ ነው። በሁለቱም ላይ ያለኝን የተሙን ሃሳብ አካፍላችኋለሁ።
በደፋር አስተያየት ልጀምርና ይህ ዘመን ኢትዮጵያን ወደከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር ከምን ጊዜውም የበለጠ ተነሳሽነት የገነነበት፤ የሠለጠነ የሰውና የማቴሪያል ኃይል የተከማቸበት ነው እላለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚው ክፍል፤ በተለይም “መድረክ” ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ያለው ብቃት ከየትኛውም ፓርቲና ስብስብ የላቀ ነው እላለሁ። እንዳላሰለቻችሁ በሦስት ዋቢዎች ብቻ ልወሰን።
የፖለቲካ ፕላትፎርም።
የአንድነት/መድረክ ፖለቲካ ፕሮግራም የዜጎችን ችግር አበጥሮ የተረዳ ብቻ ሳይሆን ያጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎቻቸውንም የሚዘረዝር ነው። ያልተገደበ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እንደሚኖር፤ የግል መሬትና ንብረት የሕገ መንግሥት ጽኑ ድጋፍ አግኝተው የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እድገት አንቀሳቃሽ ሞተር እንደሚሆኑ፤ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ለድርድር የሚቀርብ እንደማይሆን፤ ብሔረሰቦችን የሚከፋፈል ፖሊሲ ተወግዶ ያንድ ሀገርና ያንድ ታላቅ ራዕይ ልጆች በሚያደርግ ፖሊሲ እንደሚተካ፤ 85 ሚሊዮን ህዝብ ህልውናውንና ስትራቴጅያዊ ጥቅሙን አደጋ ላይ በማይጥል መልክ ወደ ባሕር የመውጣት መብቱ እንደሚከበር፤ … ወዘተ ያስቀምጣል። ትናንት የቅንጅት ዛሬ ደግሞ ያንድነት የሆነው ራዕይ ገዥው ፓርቲ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ከሚለው ራዕይ በዓይነትም በጥራትም የተሻለ፤ እጅግ በጣም የተሻለ ለመሆኑ ህዝብ በቅጡ ያውቃል። ለዚህ ነበር በ‘97ቱ ምርጫ ቅንጅትን የሾመው። ለዚህም ነው ዛሬ በአንድነትና በመድረክ ዙሪያ በሚያስደንቅ ቁርጠኝነት እየተሰባሰበ ያለው። ሌላውን ለጊዜው እንተወውና በትግራይ ክልል እየተገለፀ ያለው የፓራዳይም ለውጥ አላስደነቃችሁም? ጥልቅና የምሥራች ትርጉም እንዳለው አልተረዳችሁም?
በቢሮክራሲ ልቀጥል።
ማንኛውም ለሥልጣን የሚበቃ መንግሥት ሀገሪቱ አዳብራ ባቆየችው ያስተዳደር መዋቅር (ቢሮክራሲ) መገልገሉ ሐቅ ነው። ይህ የጦር ሠራዊቱን ይጨምራል። ምኒልክ ከዮሐንስ፤ ኃይለሥላሴ ከምኒልክ፤ ደርግ ከኃይለሥላሴ፤ ኢህአዲግ ከደርግ በተረከቡት ቢሮክራሲ ነው ሀገር የመሩት። ሌላው ሐቅ ደግሞ እያንዳንዱ መንግሥት የተረከበውን ቢሮክራሲ አሻሽሎና አዳብሮ ለሚቀጥለው መንግሥት የማስረከቡ እውነታ ነው። በዚህ ስሌት እንደ ኢህአዲግ ጠንካራ መሠረት ያለው፤ በተማረ የሰው ኃይልና በዘመናዊ የማኔጅመንት ዘይቤዎች የዳበረ ቢሮክራሲ የወረሰ መንግሥት አልነበረም። ኢህአዲግ ራሱ ምን ዓይነት የመንግሥት አስተዳደርና የማኔጅመንት ልምድ ይዞ በ1991 አዲስ አበባ እንደደረሰ የያኔ ሬዙሜውን ማየት ይበቃል። በራሴ ላይ የጣልኩት የገጽ ማዕቀብ ከለከለኝ እንጂ ከአፄ ዮሐንስ እስከ ኢህአዲግ ያሉት መንግሥታት ሥልጣን ሲይዙ የነበረባቸውን ፈተና አነጻጽርላችሁ ነበር። ላለፉት መንግሥታት ከልብ ታዝኑላችኋላችሁ።
እዚህ ላይ ያች ልማዴ እንዳትቀር አንዳፍታ ከመሥመር ወጣ ልል ነው። ስለ ቢሮክራሲ ካወጋን ዘንድ “ቢሮክራሲ” ከፍተኛ የሥም ማጥፋት ዘመቻ የተካሄደበት ያገር ሀብት ነውና ይህን የተዛባ አመለካከት ማቃናት አለብን እላለሁ። ካጭር ትርጉሙ ብንነሳ “ቢሮክራሲ” ያንድ ትልቅና ውስብስብ መዋቅር አስተዳደራዊ አቅም ነው። በሹመት እየመጡ አናት ላይ ጉብ ከሚሉት አላፊዎች በስተቀር ሌላው ህዝበ-ሠራዊት በሙያ ሚዛን እየተለካ እንደሚቀጠርበት ግዙፍ ሀገራዊ ፋብሪካ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። መንግሥት ቢለወጥ፤ ሹም ከርቸሌ ቢወርድ፤ ጎርፍ ቢያጥለቀልቅ፤ ቢሮክራሲ ከቦታው ንቅንቅ አይልም። እንደ ዝቋላ ተራራና እንደ አዋሽ ወንዝ ካስቀመጡት ቦታ የሚገኝ ውሉን የማይስት ያገር ሀብት ነው ማለት ነው። ቢሮክራሲን ያልሆነ ጥላሸት የቀባው ባላባቱን፣ ከበርቴውን፣ ካፒታሊስቱንና ኢምፔሪያሊስቱን የህዝብ ጠላት በማድረግ አንጀቱ ያልራሰለት የኮሚኒስት ሥርዓት ነበር። እንዲያው በሞቴ ኮሚኒስቶች የሚሉትን ከቁብ የሚጥፍ ሰው ተርፎ ይሆን?
በፓራዳይም ለውጥ ላጠቃል።
ሦስተኛው ቁምነገር ደግሞ ለመድረክ መፈጠር ምክንያት የሆነ የፖለቲካ ክስተት መኖሩ ነው። የብሔር ፖለቲካ ከመሣሪያነት አልፎ ማቴሪያላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንደማያስገኝለት ህዝቡ መረዳት ከጀመረ ሰንበት ብሏል። መቼም ፖለቲከኞች ብልጥ አይደሉም? የፓራዳይም ለውጥ ህዝብ ውስጥ ሥር መስደዱን ከማረጋገጣቸው በፊት የአቋምና ያሰላለፍ ለውጥ አያደርጉም። ለዚህ ነው እንገነጠላለን ከሚሉት ጀምሮ ለዘብተኛ እስከሚባሉት ድረስ በብሔር ፖለቲካ ላይ ያላቸውን አቋም ሲከልሱ እያየን ያለነው። ዓለም ወደ አንድ ትንሽ መንደርነት እየተለወጠች በምትገኝበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የብሔር ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች ከሌላ ፕላኔት እንደመጡ ፍጡሮች ይቆጠራሉና መለወጣቸው “እሰዬ!” የሚያሰኝ ነው። የብሔር ፓለቲካ ያራምዱ የነበሩ ፓርቲዎች በመድረክ ውስጥ መሰባሰባቸው፤ በብሔር ፖለቲካ ዓለም ውስጥ ስማቸው የተጠራ እንደነ ስየ አብርሃ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ ገብሩ አሥራት፣ አረጋሽ አዳነና ቡልቻ ደመቅሳን የመሳሰሉ በመድረክ ውስጥ መሰባሰባቸው አንዳንዶች ሊያምኑ ከሚፈልጉት በላይ ጥልቅ መልዕክት ያዘለ ነው። ባጋጣሚና በድንገት የተከሰተ ፓራዳይም ሳይሆን ከ45 ዓመት ተሞክሮ የተወለደ ነው።
እዚህ ላይ “ተቃዋሚው ኢትዮጵያን ለመምራት ብቃት አለውን?” ከሚል ጥያቄ ጋር ምን አገናኘው ብትሉ አልፈረድባችሁም። አያችሁ! ኢህአዲግ ባለሙያና ደጋፊ የሚጨልፈው የብሔር ፖለቲካን በውድም በግድም ከሚያራምዱ ቁጥራቸው እየቀነሰና ወርዳቸው እየጠበበ ከሚገኝ የኅብረተሰብ ኩሬዎች ነው። ባንጻሩ ደግሞ መድረክ ደጋፊና ባለሙያው የሚቀዳው እጅግ ሰፊ ከሆነ የኅብረተሰብ ኃይቅ ነው። ለዚህ ነው ተቃዋሚው ክፍል፤ በተለይም “መድረክ” ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ያለው ብቃት ከየትኛውም ፓርቲና ስብስብ የላቀ ነው ያልኩት - እመነሻዬ ላይ። የለየልኝ ቅን-አሳቢ መሆኔን ደጋግሜ ተናዝዣለሁና ቀሪዎቹ በብሔር ፖለቲካ ጠርዝ ላይ የሚገኙ ያገሬ ልጆች ከፊታቸው የተጋረደውን መጋረጃ እየቀደዱ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን እና ትልቅነትን እንዲያቅፉ እመኛለሁ።
ወዳጆቼ! ይህችን ጽሑፍ ካነበባችሁ በኋላ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በብስጭትም ሆነ በተንኮል ተነሳስታችሁ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ችሎታ ላይ የጥርጣሬ አሉባልታ ብታናፍሱ ባደባባይ እሞግታችኋለሁ። ሲናፈስም ዝም ብላችሁ ካያችሁ ለእሰጥ-አገባ ተዘጋጁ። የምሬን ነው!
ኩችዬ - መጋቢት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. (ኤፕሪል 1 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.)
“Is the Ethiopian Opposition Viable?”
April 1, 2010.



