ዘውገ ፋንታ ከስያትል

እሑድ አፕሪል 18 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. የኢትዮጵያ ገዥ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በስያትል ተገኝተው፣ “ከባንክ የተቀመጠ ዕንቁ” ካሏቸው የኢትዮጵያ ወገኖች ጋር የኢትዮጵያን አስከፊ ሁናቴ አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። መልስ ያልተገኘላቸውን ብዙ ጥያቄዎች ልዕካኖቹ ወደ ሀገራችን ይዘው ተመልሰዋል። ትዝብትን ያተረፈ ንግግር ግን ተንጸባርቋል። በጣም ሳይጋነን የምትታወስ ትንሽ የታሪክ ቀን ነበረች ማለት ይቻላል።

 

ዱሮ በወያኔዎች በሚዘጋጅ ስብስብ ላይ ተግተልትሎ ይመጣ የነበረው የትግራይ ክፍለ ሀገር ተወላጅ በዚህ ስብሰባ አልተገኘም። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን አኩርፈው ወይም በወረት ወደ ስየ አብርሃ እና ገብሩ አስራት የፖለቲካ ጎራ ዘው ብለዋል። አለበለዚያ ሠርግ አለብኝ ብሎ የማይቀረው ሀገር ወዳድ ጀግና ሁሉ አልታየም። በተጨማሪም፣ በተቀዋሚው ጎራ በሠላም ትግል ለዲሞክራሲ ለውጥ ቀልጣፋ አርበኞች የነበሩት ለግላጋ የትግሉ ጄነራሎችም አልታዩም። ስለዚህ አዳራሹና ቀየው ጭር ያለ መሆኑ በወሬ መካከል ተነስቷል። እንደሚመስለው የጊዜው የፖለቲካ ቀዛፊዎችና ተከታዮች ያተኮሩት በየከተማው ለሚዞሩት ለክቡር ነጋሶ፣ ግዛቸው፣ ስየ እና ገብሩ … አቀባበል እንደሆነ ታውቋል። ቁጥራቸው ከሃምሳ የማይበልጥ በድብቅ ከተዘጋጀው ስብስብ ተገኝተው ከልዑካኖቹ ጋር አንዳንድ ጊዜ በመፋጠጥ፣ ሌላም ጊዜ በመገረም እኽ! እንዴ! እያሉ ሰዓቶቹ አልፈዋል።

 

ውይይቱ በሠላም ተካሂዷል። ልዑካኖቹ በዚህ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ባህል ተማርከው እንደተመለሱ አይጠረጠርም። ስለሆነም፣ ያዩትን የዲሞክራሲ ፀባይ ለማይበገሩት ጠ/ሚ መለስ ያስረዳሉ የሚል ተስፋ አለ። የዚህ ስብስብ ፍሬ ይኼ ብቻ ነው። ዳሩ ግን ስብሰባው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በሠላም ተካኼደ እንዳይባል፣ ካድሬው መኮንን ካሣ በስብስቡ ወቅት ያስነሳውን ቀውስ መጥቀሱ ተገቢ ነው። በአሜሪካ/ስያትል የወያኔው ዋና ተጠሪ መኮንን ካሣ በአኳኋኑ በር ጠባቂ ወይም የሴኩሪቲ ኃላፊ ይመስል ነበር። ይህንን ምግባሩን አላግባብ በመጠቀም አንዱን ተጋባዥ (አድማጭ) “ጥያቄ አትጠይቅም፣ ቁጭ በል!” በማለት በኃይለ ቃልና ትዕዛዝ በመናገሩ የከረረ እንካስላንቲያ ተጀመረ። የመኮንን ካሣ ገጽ ደም የሚያፈላ ይመስላል፣ ሌሎች ሰዎች ተጨመሩበትና ስድቡ ስለተፋፋመ ውይይቱ ቆመ። ይኼም ፀሐፊ በር በሩን መመልከት ጀምሮ ነበር። ከልዑካኖቹ መካከል አንዱ የተባረከ መኮንን ካሣን ከቦታው ስላስገለለው ውይይቱ በሠላም ቀጥሏል።

 

ውይይቱ ሰፊ ጥያቄዎች የተሰነዘሩበት ነበር። ልዑካኖቹም ሁሉንም ጥያቄ መልሰዋል። ዳሩ ግን ለአስራ ዘጠኝ ዓመቶች አጥብቆ የሚያውቀውንና የተረዳውን ህዝብ “የምትሉት ውሸት ነው” በማለት ለማሳመን ልዑካኖቹ ያደረጉት ጥረት ከንቱ ሆኗል። ታሪክ በንግግር ሊቀየር የሚቻል ቢሆን፣ የልዑካኖቹ ሙከራ በቀየረው ነበር። ጥያቄው ሲከር፣ ከመልስ ይልቅ አንድ ሰው ኢትዮጵያን በዓይኑ ካላየ ለማመን እንደማይቻል ተጠቁሟል። የ”ባንኩ ዕንቁ” የተባለው ወገን በናት ሀገሩ ላይ ያለውን አስጊና አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ከባድ ጥያቄዎች ማቅረቡና ውሸት ፕሮፓጋንዳ አልቀበልም ማለቱ፣ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና ናፍቆት ሀገሩን በቅርቡ በዓይኑ በማየቱና ባለማየቱ አንጻር ስለተመዘነ ይኼንን ፀሐፊ ጭምር አስቀይሟል። የወያኔ አገዛዝ ፍልስፍናና ምግባር ጥያቄዎችን ፈጥሮ እንጂ መልስን ወልዶ አያውቅም። ልዑካኖቹ እንኳን ስያትል መጥተው አይተውን ሄዱ። ከውይይት በኋላ ጨዋታና ግብዣ አልነበረም፣ በወያኔ ዘመን ኖሮም አያውቅም። በሽሽግ ግብዣ የሚያደርጉላቸው ካድሬዎቻቸው መጨረሻውን አላሳመሩላቸውም። የስብሰባው መልካም ውጤት ልዑካኖቹ መጥተው ተናግረው መመለሳቸው ብቻ ነው።

 

የልዑካኖቹ የጉዞ ዓላማ

የኢህአዲግ (EPRDF) ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ጉብኝት ምክንያት የአስራ ዘጠኝ ዓመታት ውጤታማ ሥራቸውን በውጭ ላለው የኢትዮጵያ ወገን የማያውቅ ካለ ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል። ከፍተኛ ባለሥልጣኖች የተላኩበት ምክንያት፣ ወያኔ በሚመጣው ምርጫ ከሥልጣን እንዳይወርድ ባይሰጋም፣ የደነገጠ ስለሆነ ከምርጫው በኋላ ለሚሆነው ደጋፊ ነፍስ ለመፈለግ ይመስላል። ዳሩ ግን፣ ከሰፊው ስደተኛ ህዝብ የፖለቲካ አካል ከሆነው፣ ከፊሉ ለመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲና ኢዲፓ፣ ሌላው ለመድረክ፣ የቀረው ደግሞ በሁለገቡ ፖለቲካ ድርድር የተከተተ ስለሆነ፤ የወያኔው መንግሥት እንደለመደው ደልሎ እንኳን የሚወስደው የተረፈ ነፍስ የለም።

 

ወያኔ በሀገር ውስጥ ከህዝቡና ከተቃዋሚው ፓርቲዎች ጋር በሠራው ኃጢያቱ ላይ እየተከራከረና እየተፋተገ ሳለ፤ በሀገር ውጭ ደግሞ፣ የመድረኩ ክቡር ነጋሶ ጊዳዳ፡ ስየ፣ ገብሩ፣ ግዛቸው፣ … ወዘተ የገንዘብ ዕርዳታና የፖለቲካ ድጋፍ ከሚሰበስቡት ጋር ለመሻማት ፈልጎ፣ በውጭም መቦጫጨቅን አትርፏል። የመድረክ ልዑካኖች የወያኔን ሰፊ የጥፋት ጉዞ እኛም ነበርንበትና አጥብቀን እናውቀዋለን እያሉ፤ ስለዲሞክራሲ መዳኽና መንፏቀቅ፣ ስለኢኮኖሚው መንገዳገድ፣ በቋንቋ ልዩነት ላይ ስለተመሰረተው ፌደራሊዝም ቅጠ-ወጥነትና አደገኛ ሂደት፣ ስለምርጫው ሰለባዎች፣ ለሱዳንና ለሌሎች ሀገሮች ስለተዳረጉት የኢትዮጵያ አድማስ ምድርና ወደብ፤ በግፍ ያለፍርድ ስለታሰረውና ስለተገደለው “አትንኩን፣ አትግፉን እናወጣዋለን” እያሉ የአዲስ አበባን ወያኔ መሪ እያጋለጡ ይገኛሉ። እነዚህን የውስጥ አዋቂዎች ለመስማት የዱሮ ወያኔዎች ሩጫቸውን ወደዚያ አዳራሾች አድርገዋል። መለስን የከዳው ወይም የሸሸው ካድሬ አሁን ሠንጋም ቢጣልለት ወይም ሔክታር መሬት ቢመራ ከአዲስ አበባ ከመጡት ባለሥልጣኖች ስብስብ መራቃቸው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የሚመሩት የወያኔ መንግሥት ያበቃለት መሆኑን ያሳያል። የዚህን ሥርዓት ግባት ለማሳየት ይች ጽሑፍ ባጭሩ ቀርባለች።

 

ፕሮፓጋንዳዎችና የሀገር ጉዳይ ጥያቄዎች

ልዑካኖቹ ንግግራቸውን ጀምረው በየተራ ሲያቀርቡ ተጋባዡ ሳይሰለች ጥያቄውን በልቡ እያሰላሰለ ፕሮፓጋንዳውን ረግቶ አዳምጧል። ልዕካኖቹ ስለከተሞች መስፋፋት፣ ብዙ የአውራ ጎዳናዎች መዘርጋት፣ ስለኤሌክትሪክ መስፋፋትና ከኩራዝ ወደ አምፖል ዘመን መሸጋገር፣ ስለትምህርትና ጤና አገልግሎት መዳበርና ሐኪም ከማያስፈልግበት ደረጃ መደረሱን፣ በኢኮኖሚ መዳበር ኢትዮጵያ ከዓለም ታዳጊ ሀገሮች የሚነጻጸር የዕድገት ርምጃ ማሳየቷን በቁጥር አማካይነት አኩሪ ኢትዮጵያን አድምቀው አስቀምጠዋታል። እኽኽ! … እያለ እየተንቆጠቆጠ ያዳመጠው ወገን ትዕግስቱ ስላላለቀ፣ የተረጋጉት ልዑካኖቹ በመቀጠል ስለፍትሕና ዲሞክራሲ ከሠለጠነው ዓለም ጋር እያወዳደሩ አስቀመጡት። የጥያቄ ጊዜ እንዲጀምር በአዳማጩ መሰልቸትና መለዋወስ ምልክት ንግግሩ ተቋጭቶ ሞቅ ወደአለው ወደ ጥያቄና አስተያየት ጊዜ ተገባ። በዚህ ወቅት ነው የወያኔው ልዑካኖች ከተሰበሰበው ወገን ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸውን የተረዱት።

 

አንድ ጠያቂ በጋለ መንፈስ ስለጋምቤላ ህዝብ ጭፍጨፋና አሁንም በእስር ቤት ስለሚማቅቁት የፖለቲካ እስረኞች ስም እየጠራ ቅንጣት የዲሞክራሲ አሠራር በወያኔ አገዛዝ እንደሌለ በመግለጽ፤ ይኼ ዓለም ያወቀው የሰብዓዊ መብት ገፈፋ ስለሆነ ወያኔ ከዓለም ኅብረተሰብ ህሊና ውጭ እስከመቼ ድረስ ሊቆይ ያስባል? ሲል ተገርሞ ጠየቀ።

 

ሌላው ደግሞ በየክፍለ ሀገሩ የተገደሉትንና የታሰሩትን እንደ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ በመጥቀስ አሉ የተባሉት የዓለም ሰብዓዊ መብት ጠባቂና ተመልካቾች የወያኔውን መንግሥት ያወገዙ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በአምባገነንነት ቢገዙም አንድ ቀን ተጠያቂነት እንደሚመጣባቸው እያመለከተ ልዑካኖቹ ምን መልስ እንዳላቸው ጠየቀ።

 

ልዑካኖቹ በየተራ በመናገር፣ በጥያቄ የቀረበው ሁሉ ሐሰት ነው አሉ። ልዑካኖቹ ለመናዘዝ ወይም ጥፋቱን አምነው ይቅር ለማለት መጡ የሚለው ፈጽሞ የማይታሰብ ሃሳብ ነው። ከአቋማቸው ፈንከች ሳይሉ፣ የፖለቲካ እስረኛ በኢትዮጵያ እንደሌለና ዳኛ ብርቱካንም በወንጀል ሥራ የታሰረች መሆኗን ጠቅሰው ታሪኩን ተናገሩ። የዘነጉት ነገር ግን በቅርቡ የተቀዋሚው መኢአድ ፓርቲ ከሁለት መቶ በላይ የሆኑትን በእስር ቤት ያሉትን የፖለቲካ እስረኞች ማስፈታቱና በሺ የሚቆጠሩ አሁን በእስር ቤት እንደሚገኙ እነሱንም ለማስፈታት እየታገሉ መሆናቸውን ነው። መቼም እውነትን መቀበልና ማመን እንደ ኃጢአት የሚቆጥር እንደ ወያኔ ያለ መንግሥት በዓለም የለም። ይኼ ባህል በሠራተኞቹ ሁሉ ደም ስር ገብቷል። የአገዛዙ ስልት ሆኗል። በዚሁ የተነሳ፣ ዱሮም ባይኖር፣ በልዑካኖቹና በአድማጩ መካከል መተማመንና መግባባት ጠፋ።

 

ሌላው ጠያቂ ይኼ የወያኔ መንግሥት ኢትዮጵያውያንን በሀገር ውስጥም በውጪም ዓለም እያዋረደ መሆኑን እና ታሪካችንንና ክብራችን እያወደመ መሆኑን በምሳሌ አድርጎ ገለጸ። በተለይ የወያኔ ካድሬ ሁሉ የገንዘብ ፍቅሩ ጣራ የሌለው መሆኑንና በዚሁም ምክንያት ለምንም ያልበቁ ሴቶችን በገንዘብ እንደ በግ እየሸጡ በዐረብ ሀገሮች በውርደት የሚኖሩት ሰቀቀኑንና ውርደቱን አልችል እያሉ እራሳቸውን የገደሉትን እየጠቀሰ አሁንም የወያኔው መንግሥት $ 14,000 (አሥራ አራት ሺህ የአሜሪካ ዶላር) በራስ እየተቀበለ በህፃን የሚነግድ አረመኔ መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ አስረዳ። በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የዚህ ጉዳይ ክፍል ኃላፊ ነኝ ያሉት ከልዑካኖቹ አንዱ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ አንድ ሰው ወደ ዐረቦች ሀገር ለሥራ ልሂድ ሲል ሁሉን ካሟላ አትሄጂም/አትሄድም ለማለት በሕግ የማይቻል ነው አሉ። ድርጊታቸውንም ከአሜሪካና ሌሎች ሀገሮች ሕግና ሥራ ጋር አነጻጽረውታል። ይኼን የህፃን ልጅ ሽያጭ የሀገር ጠንቅነቱንና አደጋውን የሚያውቅና የሚረዳ ሌላ መንግሥት እንጂ ወያኔ እንዳልሆነ ግልጽ ሆኗል።

 

አንድ ሌላ ጠያቂ ወያኔ እራሱን ከአጼ ኃይለሥላሴና ደርግ ጋር እያወዳደረ ይኼን አሻሽያለሁ ይላል። ዳሩ ግን ኢትዮጵያ በሁሉ ረገድ ወደ ኋላ እንጂ ወደፊት እየሄደች አለመሆኗን ገልጾ፤ በድህነት ወደ ኋላ፣ በዲሞክራሲና በሰው መብት ወደ ኋላ፣ በሽታና ችግር ያጠቃት የምጽዋት ሀገር እየተባለች መሆኗን ወገንም የውጭም ዓለም አምኖ የተቀበለውን እንዴት ብላችሁ የደኸየችውን ኢትዮጵያን ከዳበሩት ሀገሮች ግስጋሴ ጋር ታነጻጽራላችሁ? ብሎ ጠየቀ። የተሰጠው መልስ - ኢትዮጵያን ሂዶ ስላላየ ለማመን መመዘኛውን ቁጥር ለመቀበል እንደሚያዳግተው ተነገረው። ምናልባት እነሱም የዲሞክራሲን ጉዳይ ለማወቅ የብልጽግናን ሂደት ለማየት አሜሪካና አውሮፓ መጥተው ስላላዩ ነው ብሎ በሰጡት ምሳሌ መገመት ይቻላል። በ19 ዓመቶች የሠሩትን ማድነቃቸው በ5 ዓመታት የኢትዮጵያኖች ሰፊ ጉልበትና የኢትዮጵያ በርካታ ሀብት ምን ሊያሠራና ከምን የብልጽግና ደረጃ ሊያደርስ እንደሚችል ፈጽሞ ሊያውቁትና ሊረዱት ባለመቻላቸው ነው። አዲስ መንግሥት ሲቋቋም የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሲመሰረት፣ ድህነት ሲጠፋና ብልጽግና ሲስፋፋ እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ተደስቶ መኖር ሲጀምር ለማየት ሁላቸውንም ሌላ ሃያ ዓመት ያኑራቸው ብሎ መፀለይ ነው።

 

ሌላው ወገን በሙስሊም ኢትዮጵያውያኖች ላይ የሚደርሰውን በደል ከነማስረጃው ተንትኖ በማቅረብ፣ ለምን የኢህአዲግ መንግሥት ሆነ ብሎ በወገኖች መካከል ጠብ እንደሚጭርና አንዱ ዜጋ ሌላውን በኃይማኖትና ጎሣ እንዲጠላላ እና በደል እንዲፈጽም ያደርጋል? ለምንስ እራሱ ሰው እየላከ ግጭት እየፈጠረ፣ በሌላ እያሳበበ የባሰ ግጭትና በደል እንዲፈጸም ያደርጋል? በማለት ጠይቆ፤ የተፈጸመው ግድያ የወያኔ እጅ እንዳለበት የተረጋገጠ ስለሆነ ኃላፊነት መውሰድ አለባችሁ ሲል አሳሰበ። እንደተለመደው መንግሥት ይህንን ድርጊት የማይፈጽም፤ እንደውም የሚከላከል መሆኑን በመግለጽ፣ ኃጢአቱን በሌሎች ላይ ወይም በሞተ ሰው ላይ ማውረስ የተለመደ ዘዴ ሆኗል።

 

ሌላው በወያኔው መንግሥት ኢትዮጵያ ወደብ ማጣቷን፣ የአድማስ ምድሯን መቀማቷን፣ ህዝቦቿ መሰደዳቸውን፣ የደንና የእርሻ ለም መሬቷ እየተመረጠ ለባዕድ ሀገሮች መሸጡን፣ ሀገሪቱ ያልታወቀ የአየር፣ ውሃና አፈር መመረዝና መጥፎ ጥፋት ላይ እየተዳረገ መሆኑን፣ ወያኔ ሀገሪቱንና ህዝቡን ለማውደም ቆርጦና ታጥቆ መነሳቱን የተሰማውን ቁጭት ገልጾ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ ያልፈጸመው በደል አለ ወይ? ሲል ጠየቀ።

 

የተሸጠው መሬት እጅግ አነስተኛ መሆኑን እና ዓለም የሚያደርገው የልማት ዘይቤ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም በማያውቁት የምድርና አየር መበከል ጣጣ አደጋ ውስጥ ኢትዮጵያ መግባቷን ባያውቁም፣ ቢያውቁም ፈጽሞ የማያሳስባቸው ስለሆነ፣ በጥበቧ እንኳን ልትነጻጸር ቀርቶ ልትታወቅ ከማትችለው የአሜሪካ እጅግ ከረቀቀና ከተወሳሰበ አስተዳደርና የንግድ ደንብና ሕግ ጋር ዲክታተሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፈጽመውን የጥፋት ሥራ በዚያ ማነጻጸሪያ ሊሸፍኑ ይሞክራሉ። አሜሪካ የንግድም ሆነ የአስተዳደር ሕጎቿ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካና ሌላ ኃይሏ ሁሉ ከንግዱ ጋር አብሮ ይሠራል። ወያኔ ከዚያ በታች ላሉት ኃያል ሀገሮች ጥቅም እየሠራን ነው ቢል ይሻላል፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም እየሠራን ነው ማለት ከቀልድ ይቆጠራል። ወደ ውጭ የሚጎርፈው የኢትዮጵያ ሀብት በሀገሪቱ ውስጥ ቀርቶ በሥራ ቢውል እርሻውን ለማካሄድ የግብጽና ቻይና ገንዘብና ጉልበት ባላስፈለገ ነበር። ስለተወሰደው ዳርቻ መሬት ልዑካኖቹ “ለሱዳን የተሸጠ ወይም የተሰጠ መሬት የለም” በማለት በሁለቱ መካከል የተደረሰበት ስምምነት አልተፈረመም በማለት ለጥያቄው ቁልጭ ያለ መልስ ስለሰጡ፣ በዚህ ምላሻቸው የተነካው ይኼ ጸሐፊ እጁን አውጥቶ ልዑካኑን ሊጠይቅ ተገደደ።

 

ከዚህ ቀጥሎ ላለው ጽሑፍ ይኼ ፀሐፊ ከማለት ይልቅ፣ ለአንባቢና ለመጻፍ እንዲመች “እኔ” በማለት እጽፋለሁ። ከወያኔ ልዑካኖች ስብሰባዎች ስገኝ ይኼ ሁለተኛው ምናልባት ሦስተኛው ጊዜዬ ነው። በአሥራ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ብዙ ተካሂደዋል። በመጀመሪያው ስብሰባ ላይ አስተናጋጆቹ የራሴ ጓደኞች የነበሩት ያሁኖቹ ከፍተኛ ካድሬዎች ሠለሞን ታደሰ፣ ዕዝራ ተሾመ እና ተስፋዬ ነበሩ። እነሱ አሁን በሌላ አገልግሎት ላይ ስለሆኑ መኮንን ካሣ ቦታቸውን ተረክቧል። በዚያ የመጀመሪያዬ የስብሰባ ተሳትፎ ላይ፣ እጅግ አንጸባርቀው በበር የቆሙት አስተናጋጆች ከላይ የተጠቀስኳቸው ሲሆኑ፣ ከበሩ ላይ ስደርስ “እንዳትረብሽ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጡኝ። ለአመላቸው እንጂ የኔን ፀባይ ሳይረዱ ቀርተው አይደለም። ከውስጥ የነበረው ታላቁ እንግዳ አምባሣደር ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ እንደ አሁኖቹ ማራኪ ተናጋሪ አይደለም። ንግግሩን ጨርሶ ጥያቄ መቀበል ሲጀምር፣ ለመጠየቅ እጄን አወጣሁ። እየታለፍኩ ስብሰባው ሊያበቃ ሲል አንድ የትግራይ ሴት በትግርኛ ይህ ሰው ብዙ ጊዜ እጁን አውጥቶ ለምን አለፋችሁት ብላ ጩኻ ጠየቀች። በሷ አቤቱታ እንድጠይቅ ስለተፈቀደል ጥያቄየን አቀረብኩ። አምባሣደሩ ጥያቄን ለመመለስ ባለመፈለጉ ፊቱን ወደ ሌላ ስላዞረ፣ ሌላ ጥያቄ ያለው ሰው ተባለ። ለሌሎች የተሰጠውን መልስ ግማሹን ሰምቼ ወጣሁ። ከበሩ አጠገብ የቆሙት ከላይ ጓደኞች ያልኳቸው ሰዎች ደስ እንዳላቸው በግሩም ፈገግታቸው አሳዩኝ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ሌላ የወያኔ ስብሰባ ሄድኩ። አሁንም ጥያቄ ለመጠየቅ እጄን አውጥቼ ሌላ ጠያቂ ቢጠፋ ጊዜው አለቀ ተብሎ ሳልጠይቅ ስብሰባው አለቀ።

 

በዛሬው ስብሰባ ለመጠየቅ አስቤ አልሄድኩም። ውሳኔዬ እንዳልጠይቅ ነበር። ብጠይቅም የማገኘው አጥጋቢ መልስ እንደሌለ በመረዳት ነበር። ዳሩ ግን ከልዑካኑ አንዱ ኢትዮጵያ ለሱዳን የሰጠችው፣ የለወጠችው ወይም የሸጠችው የለም ብለው በመናገራቸው፣ መጠየቅ ግዴታ ሆነብኝ። እጄን አወጣሁ። በተሰጠኝ ዕድል፣ አንደኛ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን መሰጠቱ በካርታ ገና ባያሳዩትም፣ በመሬቱ ላይ ለብዙ ዘመን ኗሪ የነበረው የተፈናቀለና የተሰደደ መሆኑ እንደማይካድ፤ ሁለተኛ፣ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን የወሰን ዳርቻ እንደማታውቅ አስረድተው፣ ዳሩ ግን፣ ከሱዳን የወሰድነውን መሬት ለሱዳን መልሰናል ማለታቸው እጅግ የተዛባ ጉዳይ መሆኑን አመልክቼ፤ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን የተሰጠ መሆኑ ይኼ ማስረጃ እንደሆነ ገለጽኩ።

 

ቀጥሎም፣ ልዑካኖቹ ስለሀገር ግንባታ የሰጡትን ሰፊ ትንተና ጠቅሸ፣ ግንባታው በ”ኤትኒክ ፌደራሊዝም” አስተዳደር የተመሰረተ ስለሆነ ቤትን በአሸዋ ላይ እንደመሥራት ነው ብዬ በምሳሌ ገለጽኩ። ቀጥየም አስተዳደር የአፈርን ሀብት፣ የመሬትን አቀማመጥ ሁኔታ፣ የወንዝና የባህርን፣ የህዝብን አሰፋፈር በመሳሰሉት ላይ ሲሆን፤ አፋኝ የሌለው ሰፊ ልማት ይቻላል፣ ለኢትዮጵያም ተገቢው ይኼ ነው በማለት ገለጽኩ። በንጉሡ መጨረሻ ዘመን ላይ በሱዳንና ኢትዮጵያ የተደረገውን ስምምነት ካርታውን የሠራሁ መሆኔን በመግለጽ ውል ወይም ስምምነት የለም የሚባለው ኢትዮጵያን ከጉዳት ላይ ለመጣል ካልሆነ በስተቀር፣ ስህተት መሆኑን የታሪክ ምስክር መሆኔን ገለጽኩ።

 

ለዚህ መልስ በዚሁ ሥራ ዐዋቂ የተባሉት ከልዑካኑ አንዱ በቦታው ስለነበሩ መልስ እንዲሰጡ ተደርጎ፤ በንጉሡ ዘመን የተፈጸመውን ሳያስተባብሉ ገለጻ አድርገዋል። በተጨማሪም ሌላው ባለሥልጣን ስለፌደራል አስተዳደሩ በቋንቋ ላይ መሆኑ መልካም ነገርና ለጎሣዎች ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን አብራርተው በመሬት አቀማመጥ ቢሆን ዕድገትን እንደሚያግድ አስረዱ። ባለሥልጣኑ አጥበቀው የተረዱ አለመሆናቸውን የሚያጠራጥረው፣ ቋንቋ ተስፋፊ እንደሆነና ድንበር ሊደረግለት እንደማይችል፤ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ ወዘተ ከሰሜን ዳርቻ እስከ ደቡብ ዳርቻ፣ ከምስራቅ ሀገር ዳርቻ እስከ ምዕራብ ዳርቻ ሊነገርና ሊስፋፋ የሚችል መሆኑንና አጥር እንደሚያስፈልገው፤ አስተዳደር ግን ዳርቻው የህዝብ አሰፋፋር፣ የመሬት አፈጣጠር፣ አቀማመጥ እንዲሁም የወንዝ፣ ባህር፣ የሸለቆ፣ የተራራ፣ የደን የመሳሰሉት የሚያስተካክሉት መሆኑን ዕውቀትን ይጠይቃል። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ የተጠነሰሰው አስተዳደር በዓለም ዙሪያ ተመሳሳይና አቻ ያልተገኘለት ልዩ አስተዳደር እንደውም የህዝብ ብጥብጥን መፈተኛና መመዘኛ ወይም መከፋፈያ መሆኑን መረዳት የህዝቡ ኃላፊነት መሆኑን ማሳወቅ ይገባል።

 

መደምደሚያ

ስብስቡ በዚህ ዓይነት ውይይት የተካሄደ ነበር። ተሳታፊው ተናጋሪዎቹም ሊደሰቱ ምክንያት አላቸው። ማን በምን መደሰት እንዳለበት ወይም መደሰት እንደሌለበት መፍረድ ወይም መበየን አይቻልም ወይም አይገባም። በእኔ አስተያየት ግን፣ ባለሥልጣኖቹ ከተናገሩት ይልቅ ከሰሙት ዕውቀትና ምርምር ሊማሩ ይገባቸዋል። ከዚህ ላይ ያልተጠቀሱ ብዙ የክርክርና የውይይት ነጥቦች ነበሩ። ሁሉም አሳሳቢ ናቸው። ይኼን ጽሑፍ ለማቅረብ ሃሳብም ዕቅድም አልነበረኝም። ስለዚህ የጠቀስኳቸው ላስታውስ የቻልኳቸውን ብቻ ነው።


ዘውገ ፋንታ

ስያትል 2010 እ.ኤ.አ.

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

(ጥያቄ ወይም ሃሳብዎን ለፀሐፊው ለማካፈል ከፈለጉ በሚከተለው ኢ-ሜይል መላክ ይችላሉ።)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!