ድብቅነት - ዘላፊነት - ቀጥሎስ?
መሣፍንት ዘፈረንሣይ ለጋሲዮን ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
“… አቶ ስየም እንዳሉት ሰው ከስህተቱም ሆነ ከስኬቱ ይማራል (እሳቸው የተማሩት ምን እንደሆነ ሲናገሩ አልሰማሁም እንጂ)። አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ ከናንተ በላይ ከስህተት መማርን ማሳየት የነበረበት ማን ነበር? አሁንም ጊዜ ጥላችሁ አልሄደችም - ይቅርታ ለመጠየቅ በለበጣ ቀነ-ቀጠሮ ማስቀመጡን ትታችሁ፤ ህዝብ ፊት በመቆም የቆሸሸ እጃችሁን ታጠቡ። ማንነታችሁንም አደባባይ አውጡ። …
ስጀምር
የመድረክ አመራር አባላት ሰሞኑን በሀገረ አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ስብሰባ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። የተበላ ዕቁብ በሆነው በመጪው ምርጫና በአጠቃላይ ኢህአዴግ በቀደደው እንደመንደር ቦይ በጠበበ የትግል መንገድ ተጉዘን ራሱን ከሥልጣን ጋር በአሚር (ማስቲች) ያጣበቀውን ኃይል ነቅለን እንጥላለን በሚለው የትግል ስልታቸው ላይ ተስፋ እንደሌለኝ ለጊዜው አላንሳውና፤ ተሳካም አልተሳካም በህዝባችን ላይ የተጫነውን የጭቆና ቀንበር ከጫንቃው አውርደው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሥርዓት በሀገሪቱ ለመዘርጋት የአገዛዙን የግፍ በትር ችለው እየታገሉ ላሉት ለነዚህ ኃይሎች ላቅ ያለ አድናቆትና ክብር እንደምቸር መግለፅ እወዳለሁ። ተቃዋሚ ኃይሎች እርስ በርስ በሚነታረኩበትና በሚተራመሱበት በአሁኑ ጊዜ የመድረክ ኃይሎች “አብረን እንሥራ” ብለው መነሳታቸው በራሱ የሚያስመሰግናቸው ነው። ዓላማቸው ከምር ያሳዘኑትን ህዝብ በዳግም ሕብረት ለመካስ ከሆነ እሰየው ያስብላል። በአሜሪካ ባደረጓቸው ስብሰባዎች ላይ ተገኝቶ ድጋፉን የሰጣቸው ህዝብም ተስፋ ያደረገው ይህንኑ ነው የሚል እምነት አለኝ።
ወደ ዋናው ጉዳዬ ሳልፍ
እኔና እኔን መሰል ዜጎች ዋነኛ ችግር የሆነብን በእንደዚህ ዓይነት የህዝብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የበግ ለምድ እየለበሱ በሚገቡና ቀድሞ በበደሉት ህዝብ ላይ ዛሬም እያላገጡ ያሉ ሰዎች ጉዳይ ነው። የበደላቸው አለመፅዳት ሳያንስ ህዝብን ለማሞኘት መሞከር ብሎም አጋጣሚን ተጠቅሞ እንዳሻቸው ለመዝለፍ በመቁነጥነጥ ላይ ያሉት የነዚህ ሰዎች ሁኔታ በእርግጥ ያሳምማል።
በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከተደረጉት የመድረክ ስብሰባዎች መሃል ዋሽንግተን ዲሲ ላይ የተካሄደውን ከሚዲያዎች አግኝቼ ስመለከት፤ አንዳንድ ቀልቤን የሳቡ ነገሮችን አገኘሁበት፤ እናም “ዋነኛ” ባልኩት ነጥብ ላይ ትንሽ ለማለት ፈልጌ ነው ብዕሬን ማንሳቴ። በዚህ ስብሰባ ላይ በርካታ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበትን የጥያቄና መልስ ክፍል ሰፋ ባለ ሁኔታ የተጠቀሙበት አቶ ስየ አብርሃ እንደመሆናቸው የማጣቅሰው የርሳቸውን ንግግር ይሆናል። ሌሎች ባልደረቦቻቸውም (ማለቴ ቀድሞ የኢህአዴግ አሁን ደግሞ የመድረክ ጓዶቻቸው) በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይ ነገሮችን ጠቃቅሰዋልና ጽሑፌ እነዚህንም ሰዎች መድረሱ አይቀርም።
የቀድሞ የኢህአዴግ ሹማምንት የነበሩት የመድረክ ሰዎች ይህንን ዘረኛ መንግሥት ሥልጣን ላይ የሰቀሉ ብቻ ሳይሆኑ በህዝብና በሀገር ላይ እየተሠራ ያለውን ግፍና በደል አንድም ሳያጓድሉ በአግባቡ ሲፈፅሙ የነበሩ መሆናቸው ፀኃይ የመታው ሐቅ ነው። ዛሬ ቀን ሲጥላቸው እነርሱ የሰቀሉትን ራሳቸው በፈለጉት መልኩ የማውረድ አባዜ ተጠናወታቸውና ህዝብን አስተባብሮ ለመታገል በመድረኩ ተሰይመዋል። አካሄዳቸው ጤናማ ቢሆን እሰየው ነበር። ነገር ግን የሚናገሩትንና የሚሠሩትን ያስተዋለ፤ እነዚህን ሰዎች “አበጃችሁ!” ከማለት ይልቅ ስለነሱ ቁጭ ብሎ እንዲያስብ ይገደዳል። ለምን?
“ከወያኔ መንገድ ተለይቻለሁ” ብሎ በሌላ ጎዳና ህዝብን አስከትሎ ለመጓዝ መሞከር ብቻውን “አበጀህ፣ እንኳን ደህና መጣህ፣ አብረኽን ሆነህ የድርሻህን አበርክት” ለመባል አያበቃም። ለዚህ መሰል ክብርና ሙገሳ ለመብቃት ከሁሉ በፊት ራስን ከሠሩት በደል በይቅርታና በንስኀ አፅድቶ ለህዝብ ማቅረብ የግድ ይላል። እንዲህ አይነቱ ተግባር አንድም ግለሰቡ በሠራው ጥፋት መፀፀቱን ለህዝብ ለማሳየትና ሌሎች ወደጠማማው መንገድ ገብተው እንዳይሳሳቱ ትምህርት ለመስጠት ሲረዳ፤ በተጨማሪም በቀና መንገድ ላይ ያለውን ህዝብ ድጋፍና ትብብር ያለጥርጣሬ ለማግኘት ያስችላል። ባጭሩ እንዲህ ዓይነት ሰዎች የመሪነትን ይሁንታ ከተመሪው ያገኙ ዘንድ እንደግብዓት ማቅረብ ያለባቸው ዋነኛ ነገር ለሠሩት ጥፋት የሚጠይቁትን ይቅርታ ነው።
ለአቶ ስየና ጓዶቻቸውም ቀድሞ ከበደሉት፣ ዛሬ ደግሞ “የቀድሞውን እርሳና ልምራህ …” ከሚሉት ህዝብ ሊቀርብላቸው የሚችለው ቀላሉ የመመዘኛ ጥያቄ፤ ጥፋትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ነው። የሰዎቹ ነገር ግን ዛሬም ድረስ እንደተሸፋፈነ ነው። አጠገባቸው ያሉት የቀድሞ የቅንጅት መሥራቾች “አስቀይመነዋል” ያሉትን የትግራይ ህዝብ ጊዜ ሳይወስዱ ወ/ት ብርቱካን ከእስር እንደወጡ በአሜሪካ፣ በቅርቡም ኢ/ር ግዛቸው በትግራይ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። የቀድሞዎቹ ወያኔያውያን ግን ይቺን ይቺን ቁጭ ብለው ከመመልከት ባለፈ ፈለግ ለመከተል አለመፈለጋቸው ያስገርመኛል። (አንባቢዬ፤ እዚህ ላይ የቅንጅቶቹ ሰዎች ይቅርታ በጠየቁበት ጉዳይና እነአቶ ስየ ሲሠሩ በኖሩት ወንጀል መሃል ያለው ልዩነት ቁንጫና ዝሆን ካላቸው ልዩነት እንደሚበልጥ ልብ ይበሉልኝ!)። ጥፋትን ሳያምኑ፣ ከስህተት መማራቸውን አስረግጠው ሳያሳዩና የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ ሳይጠይቁ ዓይንን በጨው አጥቦ ህዝብን “ለሥልጣን አብቃኝ” ብሎ እዚህም እዚያም እየሄዱ መስበክ ምን ዓይነት ማላገጥ ይሆን?
እነዚህ የቀድሞ የወያኔ ባለሟሎች ያደፈ እጃቸውን ባለማፅዳታቸው ፍትህ በጉጉት የምትጠብቃቸው ሰዎች ሆነው ሳለ፤ ቀን ጥሏቸው ወደእርሱ ሲመጡ ህዝባችን በጨዋነቱ ፊት ሳይነሳ ተቀብሏቸዋል። ይህን መሰል ትህትናን ማሳየት ደግሞ ሞኝነት ወይም አላዋቂነት አይደለም፤ አስተውሎት እንጂ! የኢትዮጵያ ህዝብ በየጊዜው የበደሉት ሰዎች መልካቸውን፣ ስማቸውን አሊያም ኃይማኖታቸውን እየለዋወጡ ከመሃሉ ተጠማዘው ሲገቡ በዝምታ የሚቀበለው “መከራው ይምከረው” እያለ እንጂ ዘወትር ከሚወተውትለት “ይቅርታ” በላይ እንደሚገባው አጥቶት አይደለም። ቀድሞ የወያኔ ዛሬ ደግሞ የመድረክ ታጋይ ሆነው ብቅ ያሉት ሰዎች ግን ይህንን እንደ አላዋቂነት ወስደውት ነው መሰል በየአጋጣሚው የሚናገሯቸው ነገሮች “ወቸ ጉድ!” የሚያስብሉ ናቸው።
በኔ አረዳድ በመድረክ የሰሞኑ ስብሰባም ሆነ የሀገር ቤት እንቅስቃሴ ላይ ለነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ ከህዝብ የሚቀርቡላቸው ይቅርታን የተመለከቱ ጥያቄዎች የሚሹት መልስ እንደ ዶ/ር ነጋሶ አባባል ‘ሂሳብ ማወራረድ’ ወይም ጣት መቀሳሰር ሳይሆን፤ ጥፋታቸውን በእውነት ማመናቸውንና መፀፀታቸውን ማሳወቅ ብሎም፣ ለመሪነት ብቁ መሆናቸውን ለሚዛን ማቅረብ ብቻ ነው። ነገር ግን አቶ ስየና ጓዶቻቸው ይህ ጉዳይ ሲነሳባቸው ዛር እንዳለባት ባለውቃቢ ያስጓራቸዋል። ማስፈራሪያ አይሉት ማደናገሪያ ነገርም ያናግራቸዋል። ከዋሽንግተን ዲሲው ስብሰባ የታዘብኩትም ይህንኑ ነው።
ከአቶ ስየ ንግግር “ይቅርታ መጠየቅ ካለብኝ የምጠይቃችሁ የኔ ትግል ለይቅርታ ተቀባይነት ካበቃችሁ በኋላ ነው” የሚል አስደማሚ ነገር አድምጫለሁ። የበደሉትን ህዝብ “ለዛሬ ይቅርታ ትጠየቅ ዘንድ ብቁ አይደለህምና በቀጠሮ እንገናኝ” ብሎ ማለት ጉድ አይደለም? ንቀትስ አይሆንም? ይህን መሰል ዘለፋ በአደባባይ የሚናገር ሰው ከቀድሞ ትዕቢቱና ማንአለብኝነቱ ለመላቀቁ ሊያስረዳኝ የሚችል ካለ ለማዳመጥ ዝግጁ ነኝ።
“ከወያኔ ጋር በተያዘው ትግል ውጤት ለማምጣት የሚቻለው በህዝብ ውስጥ ያለውን የሚረብሽ ስሜት ማከምና መተማመንን መፍጠር ሲቻል ነው” ይላሉ ስየ። ያሉት እውነት ነው - ችግሩ ይኸው የቤት ሥራ ከራሳቸው መጀመር እንዳለበት ለማወቅ ወይም ለማሳወቅ አለመፈለጋቸው ሆነ እንጂ! “የህዝብን ተስፋ መጠበቅና አለማጨለም ያስፈልጋል” እያሉ ራስን በጨለማ ሰውሮ ለማቅረብ መሞከር ጤናማ አካሄድ ነው አልልም። አያልቅበቱ አቶ ስየ ህዝቡ ከስሜቱ በላይ እንዲያድግ ሲመክሩም ተሰምተዋል። ገርሞኛል! ሩቅ ሳይሄዱ እዛው አሜሪካ ያገኙት ህዝብ “እስኪ ቢገባቸው” ብሎ ያሳያቸው አቀባበል እነዚህን ቃላት ሳይናገሩ እንዲውጧቸው የሚያደርግ አልነበረም?
ሰውዬው ገባንበት የሚሉት ትግል ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት “የፖለቲካ ኬሚስትሪ” የሚጠይቅ እንደሆነ ሲናገሩም ሰምቻለሁ። ትግሉን የሚመራው ኃይል ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያጣመረ መሆን እንዳለበት ሲያስረዱ ነው - ትክክል ናቸው! የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ፈታኝ ዘመናትን የተሻገረው በሕብረቱና በአንድነቱ መሆኑን ጠንቅቀን የምናውቀውም አይደል? ከተያያዥ ገለፃቸው እንደተረዳሁት ግን “እኛ ያልተካተትንበት ትግል ፋይዳ አይኖረውም” እያሉ መሰለኝ። ኬሚስትሪው ነገሮችን አዋህዶ የተፈለገውን ውህድ ለማግኘት በቅድሚያ የምናዋህዳቸውን ነገሮች ምንነት ጠንቅቀን ማወቅና መጠናቸውንም ማስላት እንደሚያስፈልግ ያስተምራል። እነአቶ ስየ ልባቸውን ከፍተው ሳያሳዩና ማንነታቸውን ሳያሳውቁ ህዝብን “ተከተለኝና የስሌቴ ቀመር ማሟያ ላድርግህ” ብለው ሲሉ የትኛውን የውህደት ሥርዓት በመጠቀም ሊያጃጅሉን እየሞከሩ እንደሆነ አልገባኝም።
ከቀናት በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር በዚህ ጽሑፌ ባተኮርኩበት ጉዳይ ዙሪያ ስንጨዋወት፤ አቶ ስየ ከዚህ ቀደም በአውራምባ ታይማስ ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለ-ምልልስ አነሳልኝ። አቶ ስየ ይኽው የይቅርታ ጉዳይ ተነስቶላቸው ሲመልሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ለይቅርታ ተቀባይነት ስላልበቃ ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ እንዳልሆኑ ተናግረው ነበር። ይኽው ወዳጄ ከጅምሩ ሰውዬው ጥፋተኛ መሆናቸውን የሚያምኑ ሰው ላለመሆናቸው መረጃዎችን ጠቅሶ ያስረዳል።
በቅርቡ ቢቢሲ የወያኔ ግፈኞች በጫካ ዘመናቸው በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ለነበረው ወገን የተቸረውን እርዳታ ለጦር መሣሪያ መገብያ ማዋላቸውን በማስረጃ አስደግፎ ይፋ ባወጣው ጉዳይ ላይ አቶ ስየና የቀድሞ አጋሮቻቸው ዛሬም ከወያኔ ጎን በመቆም ከማስተባበል ውጭ የተነፈሱት አንዳች እውነት የለም። የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተንፈራጦ በተቀመጠበት በኤፈርት ጉዳይ ላይ ያላቸውም አቋም ለወዳጄ ሃሳብ ማጠናከሪያ ነው። አቶ ስየ በዋሽንግተን ዲሲው ስብሰባ ላይ ሲናገሩ “ኤፈርት ከወያኔ እጅ ወጥቶ ለባለቤቱ መመለስ አለበት” ከማለት ውጪ በአመሰራረቱና ብሎም አሁን በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ለመሳተፍ የሚውተረተሩትን ዜጎች ሽባ እያደረገ ጉዞውን መቀጠሉን ለመኮነን ጨርሶ አልወደዱም።
ሳጠቃልል
የትዝብቴን ጫጭሬአለሁ። በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ልባዊ ለሆነ ፀረ-ወያኔያዊ ትግልና ለትግሉ አራማጆች ሁሌም ክብር አለኝ። ትንሽም ብትሆን ደግሞ ምክርም አላጣም — “አብረዋችሁ የሚሠሩትን ሰዎች ማንነት አስተውሎት ስጡት” የሚል። ከጊዜያዊ ስሌት ባላለፈ በሚፈጠር ስብስብ ዙሪያ ህዝብን “ና ተከተለን” እያሉ ነጋ ጠባ መዘመር ከትናንት ስህተት አለመማርን አመላካች ነውና፤ “ደግማችሁ አስቡበት” ባይ ነኝ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከናንተ እንቅስቃሴ ብዙ እየተማረ ነውና።
በጽሑፌ ለጎነተልኳቸው ሰዎችም፤ ራስን ደብቆ ህዝብን በማሞኘት ለዘላለም መኖር እንደማይቻል እናገራለሁ። አቶ ስየም እንዳሉት ሰው ከስህተቱም ሆነ ከስኬቱ ይማራል (እሳቸው የተማሩት ምን እንደሆነ ሲናገሩ አልሰማሁም እንጂ)። አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ ከናንተ በላይ ከስህተት መማርን ማሳየት የነበረበት ማን ነበር? አሁንም ጊዜ ጥላችሁ አልሄደችም — በለበጣ ቀነ-ቀጠሮ ማስቀመጡን ትታችሁ፤ ህዝብ ፊት በመቆም የቆሸሸ እጃችሁን ታጠቡ። ማንነታችሁንም አደባባይ አውጡ። ህዝብ ከዚህ በላይ ከእናንተ የሚፈልገው ምንም ነገር የለም! … አለበለዚያ ግን “ከወያኔ መንገድ ተለይተናል” በማለት ብቻ ታማኝነትን አገኛለሁ ብሎ ማለት የሚያረጋግጠው ነገር ቢኖር ዛሬም እንደበፊቱ ከአፍንጫ አሳልፎ ማየት አለመቻልን ብቻ ነው። በዚህ ዓይነት ከድብቅነት ወደዘላፊነት እንደተሸጋገራችሁ ሁሉ ቀጥሎ ደግሞ ምን እንደምታስከትሉ ጊዜ ያሳየናል።
አበቃሁ!
የእውነት፣ የዓላማና የውጤት ሰው ይበለን! - አሜን!!
መሣፍንት ዘፈረንሣይ ለጋሲዮን
( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ሚያዝያ 2002 ዓ.ም.



