ልጅ ተክሌ ከአምስተርዳም

ስፖርትና ፖለቲካ፦ ከቫንኩቨር እስከ አምስተርዳም

መቼም ሰዊትዘርላንድና ኮለን ተጫውተው ሰዊትዘርላንድ ዋንጫ በላ። በዝግጅቱም ላይ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተው ነበር። ከጣሊያን እስከ ኖርዌይ እስከ እንግሊዝ የመጡ ቡድኖች ተጫውተው … የሚል ጽሁፍ አትጠብቁም። ከዚያም ጠልቀን መሄድ አለብን። ፈርዶብኝ ይሄ ክፉኛ የተጸናወተኝ ሁሉንም ነገር በፖለቲካ መነጽር የማየት በሽታ ጸንቶብኛል።

 

ስለዚህም የስፖርትና የሀይማኖት፤ የባህልና የሙዚቃ ድግሶችን ሁሉ የማየው በፖለቲካ ቅኝት ነው። ለዚህም ነው ከቫንኩቨር ወደ አምስተርዳም ስጓዝ “የአባ ጳውሎስ ጓዶች ከአባ መርቆሬዎስ ጓዶች ጋር ንግግር ሊጀምሩ ነው” ሲባል ስሰማ የፖለቲካ ህዋሶቼ የቆሙት። ታየኝ እኮ አስራስምንት አመት ህግ ተፋረሰ እያሉ በየፍርድ ቤቱ ሲያካስሱን የነበሩ ጳጳሳት እነሆ በሽምግልና ስም ካባ ጳውሎስ ካባ ስር ሲገቡ። በዚህ ጉዳይ ላይ የተሟላ መረጃ እስክናገኝ ምንም አልልም ብዬ ነበር። አሁን ግን ሁለቱም ወገኖች መግለጫ አውጥተዋል። በጠቅላላው ጉዳይና በመግለጫዎቹ ላይ ሰሞኑን አወጋለሁ። እስከዚያው ግን የጠላት መግለጫ ጠንከር እንዳለ ሳላምን አላልፍም። ቀድሞውንም ችግር ፈጥሮ የነበረው በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው በደል ካልሆነና ያንዱ ፓትሪያርክ በሌላኛው የመተካታቸው ጉዳይ ከሆነ የዋልንበትን አረም በላው ማለት ነው። እንጂ ዋንጫውን ስዊትዘርላንድ በላ ኔዘርላንድ ለኔ ብዙም አይጨንቀኝም። ሁሉም አበሻ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ። እነሆ እኔ ከስፖርትና ባህል ትእይንቱ በኋላ አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ አይደለሁም። ይልቅስ ያሳሰበኝ ይሄ ነው። የሚከተለው።

 

ፓርቲው፤ እኛ 40 ከመቶ፡ ሙዚቃው 0 ከመቶ

 

በዚህ ስምንተኛው የአውሮፓ ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ዝግጅት ስኬት ከሰዉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እስከ እንደ ኢሳት ባሉ አገር ወዳድ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እየተደሰትኩ ሳለ እነሆ በመጨረሻ በማሳረጊያው አንድ በሽታችን አወከኝ። ይሄንን ነገር ከዚህ በፊትም አንስቻለሁ። አሁንም እደግመዋለሁ። አሁን ያሉ ሁኔታዎች የሚጠቁሙት ወደፊትም እንደምደግመው ነው። ኦሮሞና ኦሮምኛን ይመለከታል። ያያቴን ቋንቋ። ያባቴን ባህል። ደረጀ ዳዲ በዚህ አስር ዓመት ውስጥ ከኢትዮጵያዊነቱ ይልቅ ኦሮሞነቱ እየገዛው የመጣ ወዳጄ ነው። ከሶስት አራት አመት በፊት ባንድ ዘመን መለወጫ እለት አብዱ ኪያር የሚባለው ዘፋኝ ወዳለበት ፓርቲ ሄደ። “አማርኛ ተዘፈነ ሰዉ ሁሉ ተነሳ፣ ትግሪኛም ተዘፈነ ሰዉ ሁሉ ተነሳ፣ ጉራጊኛም ተዘፈነ ሰዉ ሁሉ ተነሳ። ከዚያም ረፍት ሆነና ዲጄው ገባ። ኦሮምኛ ዘፈን ተከፈተ። የሚወጣ ጠፋ።” ይልቅስ አጪያሽና ንፋስ ወዳድ በዛ። የደረጄን የመጨረሻውን አረፍተ ነገር አላስታውሰውም። የማዘንና የመከፋት ቅላጼ እንደነበረው ግን ትዝ ይለኛል። የኦሮምኛ ዋና የመጫወቻ ሙዚቃ ሳይሆን ማረፊያ ሆነ አይነት ነገር።

 

በአምስተርዳም የስፖርትና ባህል ዝግጅት መዝጊያ እለት ከተዘጋጀው ብርሀኑ ተዘራ፣ ጆኒ ራጋና ኩኩ ሰብስቤ ከተሳተፉበት የሙዚቃ ድግስ (“ፓርቲ”) የደረስነው ዘግይተን ነበር። ከእኩለ ሌሊት በኋላ ከጠዋቱ 1 ሰዓት። ከኛ በኋላ ራሱ ከመቶ ሰው በላይ ስለመጣ የኛ መዘግየት አያስገርምም። በነገራችን ላይ ይሄ በአበሻ ፓርቲ ላይ ከሚጀመርበት ሰዓት አራት አምስት ሰዓት ዘግይቶ መምጣት መቼ እንደሚቆም ማሰብ ይደክመኛል። ግራ ይገባኛል። ትኬት የያዙ ሰዎች የአውሮፓ ፋሽን ማእከልን በር ከበው ትኬታቸውን እያውለበለቡ በር እየደበደቡ፤ አንዳንዶቹም “ሌባ ሌባ’ እያሉ ነው የደረስነው። በግልጽ ባልገባን ምክንያት ሰዉን ማስገባት ተቋርጦ ስለነበር ታክሲ እያመጣ በር ላይ የሚያራግፈው ሰው ተከማቸ። ከሰላሳ ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት እገታ በኋላ በሩ ተሰበረ። ትኬታ የያዘውም ያልያዘውም ግር ብሎ ገባ። እኛም በጥቁር ገበያ ልንገዛ ስንደራደርበት የነበረውን ትኬት ሽመታ አቋርጠን ገባን። አገር ቤት ድንኳር ሰባሪዎች ነበርን አሁን በር ሰባሪዎች ሆንን ማለት ነው። ከውስጥ ብርሀኑ ተዘራ ያቀልጠዋል። ቀውጢ አድርጎታል። ጆኒ ራጋ መጣ። ኩኩ ሰብስቤም ተከተለች። ኦሮምኛ ዘፈንን የበላው ጅብ አልጮህ አለ። እነሆ እረፍት ሆነ፡ ያ የሳን ሆዜው ወዳጄ ደረጀ ዳዲ የጠቀሰው ችግር አምስተርዳምም እንደነበረ አለ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፡ ምናልባትም ባለማወቅ ግን ልማድ ሆኖ ኦሮምኛ አልተዘፈነም። ወይም በበቂ አልተዘፈነም።

 

ዘፈን ያዋህዳል፣ ዘፈን ያለያያል፤ ዘፈንም ያዋጋል

 

ዲጄው “ኩቺ” ከቀንም ከሜዳው ጀምሮ ሰዉን ለማስደሰት ሚዛን እየጠበቀና እያሰባጠረ ሙዚቃን ከማሰማት አልቦዘነም። ኩቺ የሰዉን መዝናናት ከግምት አስገብቶ፡ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ቃና በሌለው መንፈስ ስራውን ባግባቡ ተወጥቷል። ነገር ግን እንደሁልግዜው ሁሉ ከፍተኛ የኦሮምኛ ሙዚቃ እጥረት ተስተውሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጆች ወይንም የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር ከግማሽ በላይ ሆኖ ሳለ፡ በኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ድግሶች ላይ ኦሮምኛ ዘፈኖችና ዘፋኞች እንደዋንኛ ወይንም ተፎካካሪ የባህል ዘፋኞች ሆነው በብዛትና በጥራት አለመግባታቸው ሁልግዜም ያሳስበኛል። ብዙውን ግዜ በሰሜን አሜሪካ ስንቀሳቀስ እንደ ቀልድም ቢሆን ወደዲጄዎቹ ጠጋ ብዬ “አንድ እንኩዋን የኦሮምኛ ዘፈን እንዴት እንነፈጋለን ያለበለዚያማ መገንጠል ሲያንሰን ነው” ብዬ ማስፈራራት አዘወትራለሁ። እነሆ በአምስተረዳምም አንድ ተጣለልን። ቢሆንም ግን ይሄ ነገር ሌላ ነገር አስታወሰኝ። እነሆ ግማሽ ያህሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ኦሮሞ ነው ወይንም ኦሮሞ ደም አለው በሚባልበት ሰዓት ከአምስት ስድስት ሰዓት ፓርቲ ውስጥ አስር ከመቶ እንኩዋን የኦሮምኛ ዘፈን አለመግባቱ፡ ለኦሮምኛ ቋንቋና ባህል መበደልና በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ሰፊና ተገቢውን ቦታ ማጣት ተደርጎ የሚጠቀሰውን ክስ ያጠናክረዋል። 

 

ለአበሻው የሚዘጋጁ ፓርቲዎች ኦሮሞ እንደማይመጣ ተደርገው ታስበው የሚዘጋጁ ይመስላል። ወይንም አማርኛ ተናጋሪዎች ብቻ የሚገኙበት ፓርቲ ይመስላል። ባንድ በኩል በትግሪኛና በጉራጊኛ የምንጨፍረው ቋንቋውን አውቀን ሳይሆን በየጣልቃው ማስገባት ስለተለመደ ጭምር ሲሆን፡ በሌላ በኩልና በተቃራኒው ደግሞ ቋንቋውን ባንናገረውም የኦሮምኛ ዘፈኖች በበቂና በአይነት በኢትዮጵያዊያን የሙዚቃ ድግሶች ውስጥ አለመኖራቸው፡ ባህሉ በርግጥም በአማርኛ ባህል ተውጧል ወይንም ኦሮምኛ የመጨረሻ አናሳ ቁጥር ያለው ነው ወይንም ኦሮምኛ ለኦሮሞዎች ብቻ እንጂ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ የትግርኛንና የጉራጌኛን የኤሌኤሌባባንና የጨምበላላን ያህል ቦታ አጥቷል የሚለውን ክስ አጠናክሯል። ዘፈን ያዋህዳል። ዘፈንም ያለያያል። መፍትሄው ቀላል ነው። ሰዉን ኦሮምኛ ዘፈን አስለምዱት። ይበቃል። ደግሞ ወደ ሌላ ልዝለል።

 

ስፖርትና ፖለቲካ፤ ብርቱካንና ወጣቱ

 

የተዘጋጀው ፓርቲ ውስጥ ገብተን ስንጫወት የብርቱካን ምስል ያለበትን ቲ-ሸርት ለብሼ የተመለከተኝ አንዱ ልጅ ወደጎን ጎተት አድርጎ እንዲህ አለኝ። “ብርቱካን ነጻ ሳትወጣማ አገራችን አንመለስም።” አለኝ። ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነበርና ባረቄ ተገፋፍቶ የሳበኝ መሰለኝና ፈገግ ካልሆነም ፈቀቅ ብዬ ላልፈው ከጀልኩ። ልጁ አላቆመም። በኢትዮጵያ ያለውን የነጻነት እጦት እንዲህ ሲል ገለጸው፤ “እኛ እዚህ ነጻ አገር ስለምንኖር የብርቱካንን ምስል ያለበት ልብስ ለብሰን መሄድ እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እንኩዋን የብርቱካንን ምስል አምስት ስድስት ብሩቱካን ይዘህ ከተገኘህ በጥርጣሬ ሊደበድቡህ ይችላሉ” ብሎ በህወሀት/ኢህአዴግ ቀለደ። ቀልዶ አላበቃም። ደግሞ አመረረ። “ስንት አምስት ስድስት ሰው የገደለ፤ የሶስት ወር ህጻን የደፈረ፤ አሰቃቂ ወንጀል የፈጸሙ ነፍሰ ገዳዮች ሰው ጨፈጨፉ የሚባሉ ስንት ግፈኞች አየር እንዲቀበሉ፣ ጸሀይ እንዲሞቁና በዘመድ እንዲጎበኙ እየተፈቀደላቸው አንዲት ሴት በጨለማ ክፍል ማሰር እጅግ በጣም የሚዘገንን ነው።” አለኝ። የሚገርም ባይሆንም ደስ የሚል ስሜት ነው። ሰው የሚያስታውሰው ካገኘ እየጨፈረም፣ እየተዝናናም፣ እየተጫጫሰም ቢሆን ለሱ የሚታገሉትን ለሱ የሚታሰሩትን ያስባል ማለት ነው?።

 

ስለኢሳትና የኢሳት ደጋፊዎች

 

ያንዳንድ ሰዎች ብርታት ይደንቃል። ገና በጥቂት ቀን የአምስተርዳም ቆይታዬ የግል ህይወታቸውን በድለው፡ የሚጠቡ ልጆቻቸውን ትተው ኢሳትን በቴክኒክ ለመርዳት በቀን 18 ሰዓት ለተከታታይ ቀናት የሚሰሩ ሰዎችን ተመልክቻለሁ። አንዳንዶቹ ከለንደን ድረስ ጓዛቸውን ሸክፈው ተጉዘው የመጡ የኢሳት ደጋፊዎችን ተመልክቻለሁ። ሞራል ይሰጣል። እልህ ያስይዛል። ሆን ብሎ የተደረገ ይሁን አይሁን አላውቅም፤ የኢሳት ድንኳን የአምስተርዳም ስፖርት በዓል የተዘጋጀበት መግቢያው በር ላይ ነበር። ማንም ሲገባ ኢሳትን መሳለም ግዴታው ነው። ከፊት ለፊት ደግሞ የምግብ መግዣ ኩፖን ይሸጣል። ቦታችን ለማየትም ለመገላመጥም ይመቻል። ስለኢሳት መቼ መቀጠል የሚጠይቁት ሰዎች ቁጥር ስፍር ቁጥር የለውም። ጠላቶቻችን ከዚህም በላይ ቁርጠኝነት ቢኖራቸውም ያንዳንዱ ሰው ቁርጠኝነትና አገልግሎት ያስቀናል። ለኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ የራሳቸውን ስጋና ቃሪያ ሽንኩርትና መጥበሻ አምጥተው ሶስቱንም ቀን ምግብ ሲቸበችቡ የሰነበቱ ሰዎች እንደነበሩም ሰምቻለሁ። 

 

ጥቃቅን ነገሮች፤ ጥቃቅን ጉዳዮች

 

እነሆ በአምስተርዳም የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል እለት ብዙ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ክስተቶችን ተመልክቻለሁ። ያላገባን ሰዎች ብዙ ምርጫዎች ነበሩን። አይን አዋጅ እስኪሆንብን። በተለይ በመጨረሻው እለት ሁሉም ቆነጃጅት ለማጥመድ ተዘጋጅቶ የወጣ ይመስል ነበር። ትንሽ ያስቀየመኝ ነገር እኚህ መድረክ ላይ ወጥተው ካልታየን እያሉ ዘፋኙን አንቀው የሚያስቸግሩ ጨፋሪዎች ናቸው። እጅግ ያናድዳሉ። አንዳንዶቹ ራሳቸውን በቅጡ በመስታወት አይተው የወጡም አይመስለኝም። ወይንም ሰውና መጠጥ ስለራሳቸው ያላቸውን ግምት አሳስቷቸዋል። ያንዳንዶቹ እንኩዋን ልጅነት መሰለኝ። የሆነ ሰዓት ላይ ደግሞ መጠጥ ሽያጭ ተቋረጠ። ሁለት ካርቶን ውስኪ ተሰረቀ። ኖርዌዮች በዚህ ይታማሉ። ውስኪውን የዘረፉት ደግሞ እንደገና ርስ በርሳቸው ተደባደቡ። በዚህ አፍሬያለሁ። በማይጨስበት ቦታ ላይ የሚያጨሱ፤ ወልልና ግድግዳ በውሀና በመጠጥ ያጨቀዩም ተመልክቻለሁ። ብቻ በካናዳም በአውሮፓም የታዘብኩት የአበሻ ወጣቶች/አዋቂዎች መጥፎ ባህርይ ይሄ አበሻ ድግስ ላይና ፈረንጅ ዳንስ ቤት የሚያሳዩት የተለያየ ባህርይ ነው። ፈረንጅ ቤት ሰጥ ለጥ ብሎ የሚጫወተው አይናፋር ወጣት አበሻ ደጅ ሲረግጥ አንበሳ ይሆናል። ባጠቃላይ ግን ከላይ ከጠቅሰኳቸው አምስተርዳም ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ከምንጠየቅባቸው ችግሮች በስተቀር የአምስተርዳሙ ዝግጅት ስኬታማ ነበር። በተለይ በዚህ ዝግጅት ላይ የኢትዮ ፎረሙ ክንፉ አሰፋ የተጫወተውን ሁለገብ ሚና ሳላደንቅ አላልፍም።

 ነሀሴ፡ 2010

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ