የአቶ መለስ ዜናዊ ደብዳቤ
በሸዋይልማ ኪዳኔ
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)
Ethiopian Peoples‘ Revolutionary Democratic Front (EPRDF)
ጉዳዩ፦ የወ/ት ብርቱካንን አፈታት አስመልክቶ የተሰጠ ማብራሪያ
የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ከእስር ቤት በምህረት መለቀቅን አስመልክቶ በቀበሌ፣ በወረዳ እና በዞን ደረጃ በሚገኙ አባላትና ካድሬዎቻችን እንዲሁም በዳያስፖራ በሚገኙ ደጋፊዎቻችን ዘንድ የመንግሥትን እርምጃ በሚገባ አልተረዱም የሚሉ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ስለቀረቡልኝ፤ ይህን ደብዳቤ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቴ ሳይሆን እንደ ኢህአዴግ ሊቀመንበርነቴ ለመጻፍ ተገድጃለሁ።
ሁላችሁም እንደምታውቁት ከምርጫ 97 ዓ.ም. ጋር ተያይዞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰው የነበሩትን የቅንጅት የአመራር አባላትና ተባራሪዎቻቸው የነበሩትን አንዳንድ ጋዜጠኞችን ሰብስበን ቃሊቲ ከአሰርን በኋላ፤ ፍርድ ቤታችን አቅርበን ክስ መስርተንባቸው ለበርካታ ወራት ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቶ፤ ጥፋታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠ፤ ዳኞቻችን የኢትዮጵያ ወንጀለኛ ሕግ አንቀጽ በሚያዘው መሰረት የዕድሜ ልክ እስራት ፈርደውባቸው እንደነበር የምትዘነጉት አይመስለኝም።
ይሁንና የቅንጅትን ፍርደኞች ለማስፈታት በፕሮፌሠር ኤፍሬም ሰብሳቢነት የሚመራ የተባበሩ የሀገር ሽማግሌዎች የሀገራችንን የሽምግልና ባህል ተጠቅመው አንዴ ወደ መንግሥት፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ እስረኞቹ ሲመላለሱ ከርመው በመጨረሻ ላይ ታሳሪዎቹ በጋራና በየግላቸው የኢትዮጵያን ህዝብና የኢህአዴግ መንግሥት ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ተመልክተው ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ፤ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ይቅርታ ተሰጥቷቸው በነፃነት መንቀሳቀስ ችለዋል።
ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስና፤ ሴትየዋ ለሥራ ጉዳይ በሄዱበት ወቅት ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ እንደሌለና መንግሥት ይቅርታውን ሳልጠይቅ ነው የሰጠኝ በማለት ለደጋፊዎቻቸው እንደተናገሩ ዜናው መጀመሪያ በኤምባሲያችን በኩል ደረሰን። ቀጥሎም ይህን ቃል ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ የሚያሳይ የቪዲዮ ፊልም በእጃችን ገባ። ሴትያዋ ወደ ሀገር እንደተመለሱ ይህን ቃላቸውን እንዲያስተባብሉ በትዕግስት ከወር በላይ ጠብቀን መልስ ስላላገኘን የኢህአዴግ መንግሥት የሰጣቸውን ይቅርታ አንስቶ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አደረጋቸው።
የኢህአዴግ መንግሥት ሴትየዋን በማሰሩ የልማት አጋሮቻችን ከሆኑት የአሜሪካን መንግሥትና የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም አንዳንድ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንድንፈታት ከፍተኛ ጫና ሲያደርጉብን ነበር። በተለይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሴትየዋን ”የሕሊና እስረኛ” ነች የሚል መግለጫ ማውጣቱ የሀገራችንን ለጋ ዴሞክራሲና በሕገ መንግሥታችን ዋስትና ያገኘውን የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥላሸት ለመቀባት የተደረገ ሙከራ እንደነበር ሳትገነዘቡት የቀረ አይመስለኝም።
ሆኖም ግን መንግሥታችንን በጣም ያሳዘነው ጉዳይ ቢኖር ከዚህ ሪፖርት በኋላ እዚህ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ የተቃዋሚ ድርጅት እስኪመስለን ድረስ በሴትየዋ ጉዳይ ከእኛ ጋር ንትርክ ውስጥ ገብቶ ነበር። በዚህም ሳያበቃ በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መስሪያ ቤት ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ላይ ሴትያዋ የሕሊና እስረኛ ነች ተብሎ መውጣቱ መንግሥታችንን እጅግ በጣም አሳዝኖት እንደነበር በሚገባ የምትታውቁት ጉዳይ ይመስለኛል። የመንግሥትን እርምጃ በቅጡ ያልተረዱ እና በተቃዋሚዎች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የተወናበዱ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሳይቀሩ ሴትየዋን እንድንፈታ ግፊት አድርገውብናል። በተለይም የስዊድን መንግሥት በሴትያዋ ጉዳይ አላስፈላጊ ሙግት ውስጥ በመግባቱ መንግሥታችን ኤምባሲያችንን እስከመዝጋት የሚያደርስ እርምጃ እንዲወስድ አስገድደውታል።
መንግሥት በግል ከሴትያዋ ጋር ምንም ዓይነት ቂም በቀል ወይም ቁርሾ እንደሌለው ደጋግሜ ገልጫለሁ። መንግሥት እያለ የነበረው አንድና አንድ ብቻ ነበር። ሕገ መንግሥቱ ይከበር። ሆኖም ግን መንግሥት በሆደ ሰፊነት ሴትየዋን ከአንዴም ሁለቴ ይቅርታ እንዲጠይቁና እንዲፈቱ የሚፈልግ መሆኑን ገልፆ አማላጅ ቢልክም፤ አልሰማ በማለታቸው የሳቸውን ጉዳይ ወደ ጎን አድርጎ ሙሉ ትኩረቱን ወደ አራተኛው ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ላይ እንዲያዞር ተገድዶ ነበር። በምርጫውም ለእኛ ኢህአዴጎች እስኪገርመን ድረስ ከጠበቅነው በላይ መቶ ፐርሰንት ሊባል የሚችል ውጤት በማስመዝገብ ምርጫውን ማሸነፍ ችለናል። በህዝብ የተመረጠው አዲሱ የኢህአዴግ መንግሥት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የሴትየዋ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ወሰነ። ይህ እንዲሆን የተፈለገው ከወዳጅ መንግሥታት ለሚደረግብን ጫና ተንበርክከን ሳይሆን ሴትየዋ በሕግ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪ በመሆናቸው እና በምርጫ ወቅት የተቃዋሚ ድርጅቶች ደጋፊ የሆኑ ዜጎቻችን ላሳዩት ጨዋነት ያለንን አድናቆትና አክብሮት ለመግለፅ በመፈለጋችን ብቻ ነው።
በመሆኑም የሀገር ሽማግሌዎቹን ሰብሳቢ በማስጠራት መስከረም 5 ቀን 2003 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽ/ቤት የተዘጋጀውን የይቅርታ ማመልከቻ ወስደው ሴትየዋን አግባብተው እንዲያስፈርሙ በጠየቋቸው መሰረት አስፈርመው ያመጡትን ደብዳቤ ቅጂ ሰጥተናቸዋል። የሴትየዋን የይቅርታ ማመልከቻ ለይቅርታ ቦርድ ሰብሳቢ ለሆኑት የፍትህ ሚኒስቴሩ በመምራት የይቅርታ የምስክር ወረቀቱን አዘጋጅተው ለፊርማ በአስቸኳይ ለሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት እንዲቀርብና ሴትያዋ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ ሴትየዋ ከመፈታታቸው በፊት ማረሚያ ቤት ውስጥ ቃለ ምልልስ ለኢቲቪ እንዲሰጡ መመሪያ ተላልፏል። የሴትያዋን በድጋሚ በይቅርታ መፈታት አስመልክቶ የፍትህ ሚኒስቴራችን መስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም. ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች ጥረት በስህተት ሳይጠቀስ በመዘንጋቱ የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ሊሰጡ የነበረውን ጋዜጣዊ መግላጫ እንዲሰረዝ ትዕዛዝ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አልነበረኝም።
ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ ለሁለተኛ ጊዜ ለሴትየዋ ይቅርታ የተሰጠበትን ምክንያት አጓጉል ትርጉም እየሰጡ መንግሥታችንን ለውጭ ኃይሎች ተንበርካኪ አድርጎ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት በሙሉ ፋይዳ ቢስ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ሀገራችን ኢትዮጵያ የራስዋን የውስጥ ጉዳይ ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ልትፈታ የምትችልበት መልካም የሽምግልና ባህል ያላት ሀገር መሆኗን ማሳየት ችለናል። ይህ ባህላችን ገና ለገና የበጀት ድጋፍ ስለሰጡን ብቻ ሊጫኑን ለሚፈልጉ የውጭ ኃይልች ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን፤ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ግን እንዲኮሩብን ሊያደርግ የሚችል ተግባር ነው የሚል እምነት የኢህአዴግ መንግሥት አለው።
ደብዳቤዬን ከመጨረሴ በፊት ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ የ5 ዓመት የልማትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን በተመለከት የተወሰኑ ጉዳዮች ማንሳት እፈልጋልሁ። እኛ ኢህአዴጎች በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አመራር ሰጪነት የተዘጋጀውን የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ህዝቡን በተለይም የኢህአዴግ የጀርባ አጥንት የሆነውን ገበሬውን ከጎናችን በማሰለፍ ሙሉ በሙሉ ከተንቀሳቀስን የዛሬ አምስት ዓመት ሀገራችንን የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ማሰለፍ እንደምንችል ጥርጥር የለኝም። በዕቅዱ መሰረት በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የምግብ ዋስትና ይረጋገጣል። ሀገራችን የምግብ ዕርዳታ አያስፈልጋትም። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ኢንደስትሪው መምራት ይጀምራል። 2395 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ይዘረጋል። 800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ይመነጫል። አንድ ቢሊዮን ዶላር ከጨርቃ ጨርቅ ገቢ ይገኛል። ትላልቅ የግንባታ ዕቃዎች ሀገሪቱ ውስጥ ይመረታሉ። በአጭሩ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በተመጽዋችነት ስሟ አይነሳም። ልማታዊ መንግሥታችን ለዕቅዱ ተግባራዊነት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል በትጋት እንደሚሠራ ቃል እገባለሁ።
ከሠላምታ ጋር
(የማይነበብ ፊርማ)
መለስ ዜናዊ
የኢህአዴግ ሊቀመንበር
መስከረም 27 ቀን 2003 ዓ.ም.
የኢህአዴግ ዋና ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
http://www.eprdf.org.et የስልክ ቁጥር : ... e-mail : ... የፋክስ ቁጥር : ...
ማሳሰቢያ ለአንባብያን፦
ይህ ደብዳቤ የተጣፈው የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እስር አስመልክቶ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ምን ሊሉ እንደሚችሉ በማሽሟጠጥ ሲሆን፤ ደብዳቤውን ያዘጋጁት ሸዋይልማ ኪዳኔ ናቸው።



