”መብረቅ መከላከያው” የአቶ መለስ ፎቶ
ሲሣይ አጌና (ከአዲስ አበባ)
”ክቡር ጠ/ሚኒስትሩን እኛ አገር ብዙ ብዙ ልንላቸው እንችላለን። በሌላ ሀገር ያላቸው ክብር ግን እንደ አሸናፊ አትሌት ነው። በጂ 8 በለው፣ በጂ 20 ስብሰባ ላይ ሲገኙ ትልቅ ክብር ነው ያላቸው” - አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ
ኢትዮጵያ ሆቴል ጎን-ነቢል ካፌ በረንዳ ላይ ጋዜጣና የውጭ መጽሔቶች ለማየት ላለፉት ረዥም ዓመታት ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ብቅ እላለሁ። ከሁለት አመት በፊት በመስከረም 2001 በአንዱ ቅዳሜ ቀን እዚሁ ካፌ በሥራ ላይ የሚገኝ የግል ፕሬስ ጋዜጠኛ ወዳጄን አገኘዋለሁ። ... በጨዋታ መሀል አቶ መለስ በዚያው ሰሞን ለመንግሥት ሚዲያዎች የሰጡትን መግለጫ አንስተን ስንወያይ:- ... ”የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃለምልልስ ዋና ዋና ጉዳዮች ለምን በጋዜጣችሁ ላይ አታወጡም። ብዙ ሰው ቲቪ ሥለማያይ አንባቢ ይኖረዋል” የሚል ሃሳብ ሥወረውርለት የሰጠኝ አጭር ምላሽ ”ከባድ ነው” የሚል ነበር። ምክንያቱን ሲያብራራም ”አሁን ሕዝቡ ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ነው። በእናንተ ግዜ (ከምርጫ 97 በፊት ማለቱ ነው) ይህን ማድረግ ቀላል ቢሆንም፣ አሁን ግን ከባድ ነው፣ ኪሳራው ብቻ ሳይሆን በስልክ የሚመጣውም ስድብ እረፍት ይነሳሃል” ... ይህ ጋዜጠኛ በአሁኑ ወቅት ኑሮውን በምዕራቡ አለም ሥላደረገ ይህን ፅሁፍ ካየ ጉዳዩን በዝርዝር ይሄድበት ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። ...
ጋዜጠኛው ከሚነግረን በተቃራኒ የአቶ መለስ ምስል በተለያየ መንገድ እየታተመ በመሸጥ ላይ ይገኛል። በአቶ መለስና በህወሓት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍትም በብዛት ወደ ገበያው እየገቡ ነው። ... ጋዜጠኛው እንደሚለው አቶ መለስ እየተጠሉ ናቸውን ወይንስ በርሳቸው ዙሪያ የተሰሩ ሕትመቶች እንደሚነግሩን እየተወደዱ? ወይንስ እየተፈሩ ይሆን? የአቶ መለስ በሕዝብ መወደድ ወይንም መጠላት የመልክና የቁመና ጉዳይ ሳይሆን፣ የሥርዓታቸውን ስኬት ወይንም ውድቀት መለኪያ ጭምር በመሆኑ ሊመረመር ይገባዋል። የኢሕአዴግ መንግሥት በስኬት ላይ ሥለመሆኑ የሚያወራውን ሕዝቡ መቀበል አለመቀበሉን ለመፈተሸም ተወዳጅ ናቸው አይደሉም የሚለውን መመልከቱ የተወሰነ ሥዕል ይሰጠናል። የኢሕአዴግ ዋነኛ የቅስቀሳ አንኳር ጉዳዮች ተዓምራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዘርፈ ብዙ ልማት እንዲሁም የአቶ መለስ የአመራር ብቃትና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት የሚሉት ናቸው። ስለልማቱም ስለ ኢኮኖሚ እድገቱም በቀደሙት ሁለት ፅሁፎቼ የዳሰስኩ በመሆኑ ይህም በዓብይነት የሚነሳ ነውና በዝርዝር እንመልከተው።
... የአቶ መለስን ፎቶ በቲሸርት ላይ ማተም፣ በቁልፍ መያዣ ላይ የርሳቸውን ምስል ማንጠልጠል ወዘተ እንቅስቃሴዎች ከ2000 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ ታይተዋል። በየአደባባዩ ፎቶቸው እየተሰቀለ ይገኛል። በዚህ ረገድ መስቀል አደባባይ፣ አራት ኪሎ፣ ስታዲየም ወዘተ አካባቢዎች ይጠቀሳሉ። በቁልፍ መያዠ፣ በቲሸርት፣ በካላንደር፣ በመጽሐፍ ጠ/ሚ/ሩን የማወደስ ስራ በአንድ በኩል የተደራጀ የፓርቲ ስራ እንደሆነ ሲታመን፣ ሀገሪቱ ውስጥ ያለው አፈናም በዚህ ረገድ የሚጫወተው ሚና ለመኖሩም ምልክቶች እየተነበቡ ነው። የጠ/ሚ/ር መለስ ምስል ያለበት ቁልፍ መያዠ በየትራፊክ መብራቱ ላይ ይታይ የነበረው ዝነኛው የሙዚቃ ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከታሰረና የርሱን ምስል የያዘ ቁልፍ መያዠ ይሸጥ በነበረበት ወቅት ነው። ቴዲ ከእስር ከተፈታ በኋላ የሰው ምስል የያዘ ቁልፍ መያዠ ሲሸጥ አይታይም።
ቲሸርቱንም በተመለከተ የአቶ መለስ ፎቶግራፍ ካኒቴራ ላይ መታተም የጀመረው በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ ላይ ሲሆን፣ ይህ ወቅት የቅንጅት መሪዎች ከእስር የተፈቱበት ስለነበር የነርሱም ፎቶ በተመሳሳይ ታትሞ ይሸጥ ነበር። እነርሱ ሕዝብን አሳዝነው የክብር ቦታቸውን በፈቃዳቸው ሲለቁ፣ የአቶ መለስ እንደገና ከቴዲ አፍሮ ቲሸርት ጋር ገበያ ላይ ዋለ። ቴዲ አፍሮ ከተፈታ በኋላ የአቶ መለስን ምስል በጣም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ሱቆች ካልሆነ እንደቀድሞው ማየት አልቻልንም። የብርቱካን ፎቶ ያለበት ቲ ሸርት ከአንዳንድ የፓርቲ አባሎች ባሻገር ሌሎች ሊለብሱት ስላልደፈሩ የአቶ መለስን ፎቶ ግራፍ ገበያ ላይ ማቆየት አላስቻለም ... ለምን? ለምን የሚለውን ለመመለስ በሽግግሩ መንግሥት ግዜ ጋዜጣ አዙዋሪዎች አደጋ የሚሻገሩበት መላ ይታወሰናል። በዚያ ዘመን የነበረው የፕሬስ ነጻነት ከዛሬው ጋር ሲነጻፀር ጭለማን ከብርሃን ጋር የማወዳደር ያህል ነው። ያኔ በአንጻራዊ አይን ፍጹም ነጻነት የነበረበት ግዜ ቢሆንም፣ ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የደበራቸው ሰሞን ጋዜጣ አዙዋሪዎችን መንገድ ላይ አታዞሩም እያሉ ፖሊስ ያሰማሩባቸዋል። አዙዋሪዎቹም ከነጻው ፕሬስ ጋዜጣ በላይ መንግሥታዊውን ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ በማስቀመጥ ፖሊሶች ሲመጡባቸው እሱን እያሳዩ ስራቸውን በጥበብ ይከውናሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣንም ”መብረቅ መከላከያ” እያሉ ይጠሩት ነበር።
ከምርጫ 97 በኋላ ደግሞ የቴዲ አፍሮንና የቅንጅት መሪዎችን ምስል ለመሸጥ የአቶ መለስ ፎቶ እንደ”መብረቅ መከላከያ” አገልግሏል ማለት ነው። ያም ሆኖ ጠ/ሚ/ር መለስን የሚያፈቅሩ የሉም ማለት አይደለም። ሚሊዮኖች ጭለማ ውስጥ ቢሆኑም ፀሐይ የወጣላቸው ለግዜውም ይሁን ለዘላቂው ከጭለማ ጋር የተላለፉ፣ በሥርዓቱ ያላቅማቸው የተጠቀሙ ጥቂት እንዳልሆኑም መታወቅ ይኖርበታል። ... ”መብረቅ መከላከያው” አሁን ወደ ካላንደርም ተሸጋግሯል። ቀደም ሲል በዚህ በካላንደር በኩል አሳሳቢ ነገር አልነበረም። አሁን እመቃው እየተጠናከረ በመሆኑ ”እብድ” እንኳን የልቡን አይናገርም። ኦሎምፒያ ላፓሪዚያን ካፌ አካባቢ የማይጠፉ ሰዎች ”ከኢሕአዴግ ጋር ወደፊት!” እያለ የሚጮኻውን ወፈፌ ያስታውሱታልና ምስክሮቼ ናቸው። አንድ ሰው የውስጡን አውጥቶ ካልተናገረ ምኑን ወፈፌ ሆነ አውቆ አበድ እንጂ የሚለው መከራከሪያን ለግዜው እንዝለለው። ከየመሸታ ቤቱና ከየመንገዱ እየዞሩ ወሬ ለቅሞ መክሰስ እና ማሰር ከምርጫ 97 ወዲህ በመጀመሩ የ”እብዱ” ጥንቃቄ ተገቢ ነው ባይ ነኝ። ከየመንገዱ ወሬ እየለቀሙ ክስ እንደሚመሰርቱ ደግሞ እነሆ ማስረጃ። ... ”የቃሊቲው መንግሥት” በሚል ርእስ ከ3 አመት በፊት በፃፍኩት እና እንዳይታተም ከተከለከለው መጽሐፌ ላይ ልዋስና ላስነብባችሁ፡-
ቁጥር አ/አ/ሕግ/3140/3140/99
ቀን 14/6/99
አ/ም/ወ/ሕግ መ/ቁ. 3140/99
የአ/ክ/ከ/ፖ/ም/መ/ቁ. 3120/99
ከሳሽ፦ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ
ተከሳሽ፦ ተስፋዬ ወንዱ በኮ - ዕድሜ 45 ዓመት
አድራሻ፦ አ/ክ/ከ ቀበሌ 11 የቤት ቁ.
ወንጀሉ
በ1996 ዓ.ም. የወጣወን የወ/ህ/ቁ 486/ሀ የተመለከተውን በመተላለፍ
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሽ በ26/05/99 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን፣ በአ/ክ/ከ ቀበሌ 17 ክልል ልዩ ቦታው ቱሪስት ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ምን መንግሥት አለ? ተማሪ ደብተሩን እንደያዘ በቀይ ለባሽ ወታደር እና በፌፌራል ፖሊስ እየተገደለ ምን መንግሥት አለ? መንግሥት አለ ብላችሁ ነው እንዴ የተቀመጣችሁት? ተማሪ በጥይት እየረገፈ ህዝቡ እየታረደ ያልቃል፤ ወያኔ ለሱማሌ ያጎበድዳል እያለ ህዝብን በሚቀሰቅስ ሁኔታ የሐሰት ወሬዎችን በመንግሥት ላይ በማውራት በፈፀምወ የሐሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል ተከሷል።
የማስረጃ ዝርዝር
የሰው ምስክር 1) ...
2) ...
... ሞልቶ የፈሰሰውን፣ ለአፍሪካም የተረፈውን ዲሞክራሲ አያችሁት አይደል! ... ሰክሮ እንኳን የዘባረቀ መድረሻው ቃሊቲ ነው። … ወደ ካላንደሩ እንመለስ። በካላንደር ላይ ምሥላቸው ታትሞ የኢትዮጵያ መሪዎች በሚል የቀረቡት ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ዮሃንስ፣ ዓፄ ምኒሊክ፣ ዓፄ ኃ/ሥላሴ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ሲሆኑ፣ በሌላም በኩል የተዘጋጀው ካላንደር ደግሞ የጎጃሙን ንጉስ ተ/ኃይማኖትን፣ የጅማውን አባጂፋር፣ የወላይታውን ካዎ ጦና ያካተተ፣ የላይኛዎችን ያከለ ”የኢትዮጵያ ነገስታት እና መሪዎች” የሚል ካላንደር በየአመቱ መግቢያ ላይ ሲሸጥ ማየት የተለመደ ነው። በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ የአቶ መለስም ፎቶግራፍ በካላንደር ላይ ታትሟል። የታተመው ግን ከቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ሳይሆን። ከዩ.ኤ.ስ. አሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በቡድን 20 ሀገሮች ጉባኤ ላይ የተነሱት ነው።
የነገስታቱ ካላንደር በአንድ በኩል። አቶ መለስ ከባራክ ኦባማ ጋር ያሉበትን ካላንደር በሌላ በኩል ቸርቻሪዎቹ በአመቱ መግቢያ ላይ ሲያዞሩ ታይተዋል። በነገራችን ላይ የኢሕአዴግ ሰዎች አቶ መለስ በቡድን 8 እና 20 ሀገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ ሲገኙ በተረኛነት በያዙት አሕጉራዊ የሃላፊነት ቦታ ወዘተ መሆኑ ተዘንግቶ በፓርቲያቸውና በርሳቸው የአመራር ስኬት እንደሆነ እንዲታመንና ለውስጥ ችግር መሸፈኛ ይረዳ ዘንድ በጣም ያስጮሁታል። እንደ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ጭምር ተቀብለው ያስተጋቡታልና እንመርምረው። አቶ መለስ በቡድን 8 እና 20 ጉባኤዎች በርግጥ የአፍሪካ ወኪል ሆነዋልን? ... በቡድን 8 መሪዎች ጉባኤ ላይ 7 ግዜ የተገኙት የሴኔጋሉ አብዱላሂ ዋዴ፣ የአልጄሪያው አብዱልአዚዝ ቡታፍሊካ፣ የናይጄሪያ መሪዎች (ኦባሳንጆ፣ ጉድላክ ጆናታን) እንዲሁም ቋሚ ተሰላፊ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ወኪል ሳይባሉ ሶስት ግዜ ብቻ የተገኙት አቶ መለስ የ እንደምን የአፍሪካ ወኪል ሊባሉ ይችላሉ? ... ለግንዛቤም ይጠቅማልና በጥቂቱ እንመልከት ...
ቡድን 8 እ.ኤ.አ. በህዳር 1975 የዛሬ 35 ዓመት በ6 ሀገራት ተመሰረተ። በአመቱ ካናዳን አክሎ ቡድን 7 እየተባለ እስከ 1997 ከመጣ በኋላ በተጠቀሰው ዓመት ሩሲያን ጨምሮ ቡድን 8 መባል ጀመረ። ... ታሪኩ ይቀጥላል። አምና በሐምሌ 36ኛውን ጉባኤ በካናዳ አካሂዷል። 37ኛው ደግሞ የፊታችን ሀምሌ በፈረንሳይ ይከውናል። ቡድኑ በዚህ 35 ዓመታት ባለፈው ጉዞ ውስጥ በጉባኤው ለመጀመሪያ ግዜ ሌሎች ሀገራት በተጋባዥነት እንዲሳተፉ የፈቀደው እ.ኤ.አ. በ2000 ዓ.ም. ለ26ኛ ግዜ በጃፓን ባካሄደው ጉባኤ ነበር፣ ከዚህን ግዜ ጀምሮ ደቡብ አፍሪካ በቋዋሚነት ያለማቋረጥ በጉባኤው በመሪዎ እየተወከለች ትገኛለች። በፊት በታቦ ምቤኬ አሁን ደግሞ በጃኮቭ ዙማ።
... ደቡብ አፍሪካ G8+5 በሚባለው ቡድን ውስጥ ከቆየች በኋላ ከ2008 ጀምሮ በመሪዎች ደረጃ መሰብሰብ የጀመረው የG 20 አባልም ነች። ደቡብ አፍሪካ በቋሚ ተሰላፊነት ከ2000 ጀምሮ ብትቆይም፣ የናይጄሪያ፣ የአልጄሪያ እና የሴኔጋል መሪዎች ከዚሁ ግዜ ጀምሮ በቋሚነት ባይሆንም እየተሳተፉ ይገኛሉ። ማሊ ከ2001 ጀምሮ፣ ግብጽና ሞሮኮ ደግሞ ከ2003 ጀምሮ እንዲሁም ጋና እና ኡጋንዳ ከ2004 ጀምሮ ሲሳተፉ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ የተጋበዘችውና ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊም በቡድን 8 ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ግዜ የተገኙት በፈረንጀች አቆጣጠር በሀምሌ 2005 (ከሰኔ 29 እስከ ሀምሌ 1/1997) በስኮትላንድ በተካሄደውና የቀድሞው የብሪታኒያ ጠ/ሚ/ር ቶኒ ብሌር በመሩት በ31ኛው ስብሰባ ላይ ነው።
ከዚያ በኋላ በሩሲያና በጀርመን በተካሄዱት 32ኛና 33ኛ የመሪዎች ስብሰባ ከአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ በቀር የተጋበዘ የአፍሪካ ሀገር አልነበረም። ለ34ኛ ግዜ በሀምሌ 2008 በጃፓን በተካሄደው ጉባኤ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ግዜ ስትጋበዝ፣ ጋና እና ታንዛኒያም ለሁለተኛ ግዜ ተሳትፈዋል። የአልጄሪያው አብዱልአዚዝ ቡታፍሊካ፣ የሴኔጋሉ አብዱላሂ ዋዴ ለአምስተኛ ግዜ ተሳተፉ። ናይጄሪያም ለአምስተኛ ግዜ ተካፈለች። በሃምሌ 2009 በጣሊያን በተካሄደው 35ኛ ጉባኤ የአልጄሪያ፣ የሴኔጋልና የናይጄሪያ መሪዎች ለስድስተኛ ግዜ ተጋበዙ። በዚህ ጉባኤ የግብጽ (ለሁለተኛ ግዜ)፣ የአንጎላና ሊቢያ መሪዎችም ተሳታፊ ነበሩ።
ባለፈው ሰኔ 2010 በካናዳ በተካሄደው 36ኛ ጉባኤ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል ለሰባተኛ ግዜ ሲገኙ፣ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ግዜ ተሳተፉ። ማላዊም ነበረች። 37ኛው እንግዲህ ከ7 ወር በኋላ በፈረንሳይ ይካሄዳል። በቡድን 8 ሀገራት ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፎ ይህ ነው። በቋዋሚነት ተሳታፊ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ እያለች፣ በተከታይነት ብዙ ግዜ በመሳተፍ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያና እና ሴኔጋል እያሉ አቶ መለስ የአፍሪካ ወኪል ሆኑ የሚያስብል ምንም ምክንያት የለም።ደቡብ አፍሪካን በአባልነት ያቀፈው ቡድን 20ን በተመለከተም ቡድኑ ራሱ በመሪዎች ደረጃ ጉባኤ ማካሄድ የጀመረው በ2008 ሲሆን፣ በዓመት ሁለቴ እያካሄደ 4ኛው ላይ ደርሷል። 5ኛው የፊታችን ህዳር በደቡብ ኮርያ ይካሄዳል።
ጉባኤው በዓመት ሁለቴ የሚካሄድ በመሆኑ ባለፈው ሰኔ በተካሄደው 4ኛው ጉባኤና ፊታችን ሕዳር 2 እና 3/2003 ሴኡል ደቡብ ኮርያ በሚካሄደው 5ኛው የቡድን 20 መሪዎች ሥብሰባ ከአፍሪካ የተጋበዙት የማላዊና የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው። የማላዊው ፕሬዝዳንት ቢንጉዋ ሙታሪካ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በመሆናቸው፣ አቶ መለስ ደግሞ በወቅቱ የኔፓድ የመሪዎችና መንግሥታት ኮሚቴ ሊቀመንበርነታቸው እንደተጋበዙ በግልጽ ተቀምጧል። በፒትስበርግ ጉባዔም የተገኙት በዚሁ በኔፓድ ሊቀመንበርነታቸው እንደሆነ በግልጽ ሰፍሯል። ከመሰል ሁኔታዎች ውጭ አቶ መለስ በስኬት ሊጋበዙ የሚችሉበት ሁኔታ አልተመዘገበም። የዲሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የኢኮኖሚ በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ውጤታቸው በአፍሪካ የመጨረሻ ረድፍ ላይ በመሆኑ በተለይ የሚጋበዙበት ሁኔታ እንደሌለ እንደ እንቁራሪቷ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው ጠባቧን ሰማይ ለማያዩት ሁሉ ግልጽ ነው።
ባለከባድ ሚዛኖቹ የቡድን 20 ሀገራት (የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ) በአጠቃላይ የዓለምን 85% ብሄራዊ ምርት እንዲሁም 80% የአለምን ንግድ የሚሸፍኑ ናቸው። በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር 2ኛ ብትሆንም ለአፍሪካ ብሄራዊ ምርት ከ1% ያለፈ አስተዋጽኦ የማታደርገው እና ከአፍሪካ የ558 ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ (የ2008 መረጃ) ሁለት ቢሊዮን ዶላር የማይሞላ ድርሻ ያላት ድኃና ደካማ ሀገር በሀብታሞቹ ዘንድ የአፍሪካ ወኪል የምትሆንበት ምክንያት እንደማይኖር ሰነዶች ሳይመረመሩም መገመት ይቻላል።
አቶ መለስ በቡድን 8 ጉባኤ ለመጀመሪያ ግዜ የተገኙት የሰኔ 1/1997 ግድያ ተካሄዶ ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ መሆኑ ለብዙዎች ግር የሚያሰኝ ቢሆንም፣ ግብዣው አስቀድሞ ስለሚላክ ከግድያው በፊት የተመዘገበው አመርቂ የምርጫ እንቅስቃሴ ለጥሪው አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ ይታመናል። አቶ መለስ ከዚህ ግዜ በኋላ በቡድን 8 ሆነ 20 ስብሰባ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ መሪነታቸው ሳይሆን ከጥር 2007 ጀምሮ በያዙት የኔፓድ ሊቀመንበርነታቸው በመሆኑ፣ ይህንን ሥፍራ ተረኛ አፍሪካዊ መሪ ሲይዘው እሳቸውን በባለፀጎቹ ሀገራት ስብሰባ ላይ ማየታችን ያበቃል፡የኢትዮጵያ መንግሥት ሚዲያዎችም የባለጸጎቹን ሀገራት ስብሰባ ከቀዳሚ ዜናነት ወደግርጌ ርዕስነት ይወስዱታል። ምናልባት ዜና መሆኑም ያኔ ያበቃ ይሆናል።
... ዕውነታው ይህ ነው። በምክንያት የሚመሩ ሰዎች እነዚህን ዝርዝር መረጃዎች ባያገኙ እንኳን የሁኔታዎችን አካሄድ ለማወቅ የማይቸገሩ በመሆናቸው በመንግሥት ሚዲያዎች በሚናፈስ የውዳሴ ወሬ የእነዚህን ቀልብ መሳብ አይቻልም። በርግጥ ከምክንያት ይልቅ በስሜት የሚነዱ ሰዎችን ለመያዝ ያለውን በመቀባባት ብቻ ሳይሆን የሌለውን በመፍጠርም ማሳመን ይቻላል። በተቃራኒ የቆመውን ስሜታዊ ደግሞ የሚታይ፣ የሚዳበሰውንም ይዞ ለማሳመን መሞከር ደግሞ ከንቱ ድካም ነው። በስሜት ስለሚነዱ ሰዎች የቃሊቲ ወህኒቤት ትውስታዩን በምሳሌነት ላንሳ። በ1998 ዓ.ም ቃሊቲ ወህኒ ቤት ዞን አንድ በታሰርንበት ወቅት ወደ 300 እስረኛ በሚኖርበት አዳራሽ ሁለት ቴሌቪዥኖች ይገኛሉ። አንደኛው ቴሌቪዥን ያለበት ጥግ ላይ ሴት ደፍሮ የገባ የጨፈነ የኢሕአዴግ ደጋፊ ሲኖር፣ አጠገቡ የሚተኛውና ሰው ገድሎ የገባው ደግሞ እልም ያለ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ነው። ለኢሕአዴጉ ደጋፊ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚነገር በሙሉ እውነት ሲሆን፣ ይህ ሰው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ”የቃሊቲ እስረኞች በሙሉ ማታ ማታ ቤታቸው እያደሩ ጠዋት ወደእስር ቤት ይመለሳሉ” ብሎ ቢዘገብ የማይጠራጠር ከራሱ በላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የሚያምን ዓይነት ነው። ለእንደዚህ አይነቱ ታዲያ ብዙ መድከም ያስፈልጋል? ከዚህኛው በተቃራኒ ላለው ደግሞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው በሙሉ አንድም እውነት የማይገኝበት ውሸት ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ”አቶ መለስ በጽህፈት ቤታቸው ዛሬ መግለጫ ሰጡ” ብሎ በምስል አስደግፎ ቢዘግብ እንኳን ለሱ ”ቁጩ” ነው። ... ለዚህ በቡድ 8 ጉባኤ ላይ መገኘታቸውን ላልተቀበለ፣ በቡድን 8 ጉባኤ ላይ የተገኙት በተፈላጊነታቸው ነው ብሎ ማሳመን ይቻላል?
እንደዚህ ጫፍና ጫፍ ከቆሙት ውጭ በመረጃ ማነስ ወይንም ጥቅም ለማሳደድ ሲሉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚወራውን የሚያምኑ ወይንም ያመኑ የሚመስሉ እንደ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አይነት ሰዎች ያጋጥማሉ። በኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ ተጋብዞ መገኘቱን ”ፍትህ” ለተባለ ጋዜጣ በመስከረም 21/2003 የተናገረው ኃይሌ ገብረስላሴ ”ለጠ/ሚኒስትር መለስ ሪከርድ የሰበርክበትን ማሊያ ሸልመሃቸዋል። ለመሆኑ በየትኛው ሥራቸው ነው የሸለምካቸው?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ”በጣም ይገባቸዋል። ላየሁት ነገር መሸለም አለባቸው። እኔኮ ቲሸርትና ቁምጣ ለሌላም ሰው ሸልሜያለሁ። እስካሁን ይህን አለማድረጌ ይህንን ቀን ስጠብቅ ነው ማለት ነው።” ኃይሌ አላበቃም። ወረድ ይልና ”... ምን መሰለህ እኛ የራሳችንን ዜጎች ከፍ ካላደረግናቸው፣ ካለከበርናቸው ማን ያከብርልናል? አንድ ነገር ልንገርህ! ክቡር ጠ/ሚኒስትሩን በእኛ አገር ብዙ ብዙ ልንላቸው እንችላለን። በሌላ ሀገር ያላቸው ክብር ግን እንደ አሸናፊ አትሌት ነው። በጂ 8 በለው፣ በጂ 20 ስብሰባ ላይ ሲገኙ ትልቅ ክብር ነው ያላቸው። ሌላው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ንጉስህን ታዘዝ ይላል፣ በቃ”
አቶ መለስ እንደ አሸናፊ አትሌት የሚታዩት የት ሀገር እንደሆነ ከኃይሌ በቀር ያየ ወይንም የሰማ ይኖር ይሆን? አቶ መለስ በባለጸጎቹ ሀገራት መሪዎች ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን እንጂ እነ ኦባማ ለአቶ መለስ ታላቅ ክብር እንዳላቸው መች አወቅን? ኦባማ ጋናን ለማንቆለጳጰስ አክራ የሄዱት በስሕተት አዲስ አበባ የመጡ መስሏቸው ነበር ለካ! … ኃይሌ የተናገረው በቅንነት ከሆነ በአለም ላይ ካለው ሥምና ዝና የሚመጥን አለም አቀፍ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚቀርቡት ቢመክሩት አይከፋም፣ ሳይመረምር በድፍረት ያለማስተዋል የሚወረውራቸው ቃላት ግምት ላይ እየጣሉት ነው። … የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃይሌ ወይንም ሌላ ሰው ዝነኛ ስለሆኑ ዕውነቱን እንጋርድህ ቢሉት ይቀበላል ብሎ ማመን ለሕዝብ ካላ ዝቅተኛ ግንዛቤ የሚመነጭ፣ ካለፈው ያለመማር ነው። ሼሕ መሐመድ አላሙዲን ጣሪያ የነካ ተወዳጅነታቸው ንቧን ደረታቸው ላይ የለጠፉ ግዜ መሬት ላይ ሲከሰከስ ያላየ ነበር? ...
ኢሕአዴጎች በስፖርቱ ብቻ ሳይሆን በኪነጥበቡም መስክ ያሉ ሰዎችን በዚህ ረገድ እናተርፍባቸዋለን በሚል እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። በተለይ በ2003 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ በብዛት በአንድ አዳራሽ በማሰባሰብና ቀጥታ በቴሌቪዥን በመልቀቅ የኢህአዴግ ካድሬነትን ተግባር እንዲወጡ አድርገዋል። የኢህአዴግ መንግሥት ለአንድ ምሽት ለእያንዳንዱ አርቲስት እንደደረጃው ከአራት ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ክፍያ በመፈፀም ለሕዝብ ቅርብ በሆኑ ወገኖች ዘንድ ወደ ሕዝብ ለመቅረብ ሞክሯል። ... በኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ያዘኑና ያፈሩ መኖራቸው እርግጥ ነው። ከነርሱ አንዳንዶች በስግብግብነት ሌሎች ብዙዎች ደግሞ በፍርሃት ማለትም እምቢ ቢሉ በእንቅስቃሴያቸው ላይ የሚመጣውን ጫና በመፍራት እንደተቀላቀሉ በአደባባይም ባይሆን ቢያንስ በየካፌው ያወራሉ። ሚሊየነሮች ተጨማሪ ሚሊዮኖች ለመስራት ሲስገበገቡ የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ በዕለት ጉርሳቸው ላይ የመጣውን ፈተና እንዲጋፈጡ መጠበቅ ፍትሃዊ አይሆንም።
ቁም ነገሩ ይሕ አይደለም። ኢሕአዴግ የህዝብን ልብ ለማሸነፍ የህዝቡን ኩርፊያ መመርመር ይገባዋል። ከውሸት አደግን ልፈፋ በመውጣት በእውነት ለማደግ ያላስቻሉ ችግሮችን ማበጠርና ለመፍትሄው መንቀሳቀስ እንጂ ዳቦ እና ነፃነት የራበውን ሕዝብ ሁለቱም በሌሉበት በአፍ ጉቦ ብቻ እንዴት መማረክ ይቻላል? ... ይህ የኢህአዴግ አካሄድ አንድ ነገር አስታወሰኝ። ቃሊቲ ወህኒ ቤት በነበርንበት ወቅት የሰማሁት ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ ከምባታ አካባቢ በአንድ ወረዳ ውሥጥ በሙያቸውም። በባሕሪያቸውም እጅግ ተወዳጅ የሆኑ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ነበሩ። የኢሕአዴግ ሰዎች በእኚህ ሰው ተወዳጅነት ለማትረፍ ሰውየውን በተፅዕኖ አባል በማድረግ ለፓርላማ ምርጫ ዕጩ ያደርጓቸዋል።
ኢሕአዴጎች ሰውየው እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ በመሆናቸውም ኮሮጆ ወደ መዝረፍ አልገቡም። ሆኖም ዶክተሩ ተሸነፉ። እንዴት ሊሆን ቻለ ብለው ኢሕአዴጎች ሲገረሙ አንድ የአካባቢው አዛውንት ”ዶክተር እኮ ለኛ ልዩ ሰው ነው። እንወደዋለን። ታዲያ ምን ያደርጋል ”አተካራ” በፖፖ ሲቀርብለት ማን ይበላል?” ማለታቸው ተጠቅሷል። ”አተካራ”? በአካባቢው ተወዳጅ ምግብ ነው። የአዲስ አበባውንም የአርቲስቶቹን ዝግጅት ከዚሕ አንጻር ካየነው ዶሮ ወጥ ወይንም ክትፎ ወይንም ሌላ ተወዳጅ ምግብ በፖፖ ሲቀርብ በውጤቱ ምግቡ ከመበላት ይልቅ ምግቡ ራሱ የሚጠላበትን ሁኔታ ይፈጥራል ማለት ነው።
... ወደ ነጥባችን እንመለስ። የአቶ መለስን ሕይወት ታሪክ መሰረት አድርገው የህወሓትን ታሪክ ጭምር የሚዳስሱ መጻሕፍት እና ፊልሞች መበርከታቸው የገበያውን መኖር የሚያመላክቱ ይመስላሉ። አሳታሚዎች የማይሸጥና የሚያከስር፣ ገበያው የማይቀበለውን ተቀራራቢ ነገር እንደማያሳትሙ ይታወቃል። ሥለዚህ ገበያው አለ ማለት ነው። ገበያው አለ ማለት ደግሞ የጠ/ሚኒስትሩን ተፈላጊነት ወይም ተወዳጅነት በተወሰነ ደረጃ አያንጸባርቅም ማለት አይደለም። ይህ ከገበያው ሕግ አንጻር ካየነው ነው። ነገር ግን በአቶ መለስና በህወሓት ዙሪያ ያሉ መጻሕፍትን የሚጽፉና የሚያሳትሙ ከሽያጭ በፊት ከፍተኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በሀገሪቱ አሉ የሚባሉ ነጋዴዎች ለእነዚህ መጻሕፍት የሕትመት ወጪ በመሸፈን እንዲሁም በርካታ መጽኀፍት በአንድ ግዜ በመውሰድ ለት/ቤቶች ወዘተ በመስጠት በከፍተኛ ድጎማ ተመሳሳይ ሕትመቶችን እያበረታቱ ነው።
በዚህ ረገድ አቶ ጌቱ ገለቴ የተባሉ ነጋዴ አንዱን መጽሐፍ ብቻ የ50 000 (ሃምሳ ሺ) ብር መግዛታቸውን በ”Fortune” ጋዜጣ ላይ አንብበናል። እኚህ ሰው ለኢሕአዴግ ማጠናከሪያ በምርጫው ዋዜማ ከፍተኛ ገንዘብ ካዋጡ ነጋዴዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ግማሽ ሚሊዮን ብር ነው ያዋጡት። እኚህ በግልፅ የኢሕአዴግ ደጋፊነታቸው ከምርጫ 97 ዋዜማ ጀምሮ የሚታወቁ ነጋዴ ይቅርና ሌሎች ነጋዴዎችም ለኢሕአዴግ በብዛት ገንዘብ አዋጥተዋል። (ኢሕአዴግ ለ2002 ምርጫ ቅስቀሳ 56.7 ሚሊዮን ብር ማውጣቱንና አሁን በባንክ 100.3 ሚሊዮን ብር እንዳለው በቅርቡ በአዳማው ጉባኤ ራሱ ፓርቲው ይፋ አድርጓል) የኢሕአዴግ ሥርዓት አካሄድ የማይመቻቸው አንድ በሩቅ የማውቃቸው ነጋዴ ንብረቶቻቸው በሀራጅ መሸጥ በጀመሩበት ወቅት ለኢህአዴግ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የፊት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሳያቸው ቀሪ ንብረታቸውን ለማዳን የሚደረግ መፍጨርጨር አድርጌ ነው የወሰድኩት። ..በቫት፣ በአራጣ ወዘተ እየተሳበበ (የተወሰነ እውነት ሊኖር ይችላል) ለአመታት ያፈሩትን ሀብት ንብረት ተነጥቀው፣ የባንክ አካውንታቸው ጭምር ተገልብጦ ባለፀጎች ወደ ድሆች ሰፈር በሚገፉበት ሥርዓት ነጋዴው ብዙ ምርጫ አለው ብዬ አላምንም።
... ትኩዕ ባዓታ የተባሉ ሰው ”መለስ ከልጅነት እስከ ዕውቀት” በሚል ርዕስ አቶ መለስ በተለያዩ ግዚያት ለተለያዩ ሚዲያዎች የሰጡትን ቃለምልልስ በ156 ገፆች በሃምሌ 2002 ለንባብ አብቅተዋል። ይህንን መጽሐፍ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት በአንደኛ ደረጃ ስፖንሰርነት ሲደግፈው፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ኮርፖሬሽን በ2ኛ ደረጃ ስፖንሰርነት። አኪር ኮንስትራክሽን፣ ሐረር ቢራና ፅዮን ሆቴል ሦስተኛ ደረጃ ስፖንሰሮች እንደሆኑ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ በግልጽ ተመልክቷል። ይህ መጽሐፍ ከታተመ በኋላም የሚደረግለት ድጋፍ ለመቀጠሉ ማሳያው በሕወሃት የተቋቋመው መስፍን ኢንጂነሪንግ ይህንና ሌሎች መፅሀፍት በብዛት ለትግራይ ት/ቤቶች ሲያስረክብ በኢትዮጵያ ቴለቪዥን መስከረም 16/2003 ምሽት ተመልክተናል። ቀደም ካሉት ማለትም ባለፈው ከወጡትም ሌላ ናሙና መውሰድ ይቻላል።
በሓይላይ ሀድጉ በትግርኛ ተጽፎ በብርሀኑ አባዲ ወደ አማርኛ የተመለሰው ”ፅንዓት” መጽሐፍ በርካታ የገንዘብ ደጋፊዎች ነበሩት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክብር ስፖንሰር ሲሆን፣ ሁሉም የመንግሥት ባንኮች ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ስፖንሰር ሆነዋል። ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ መድህን ኢንሹራንስ፣ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ የፌደራል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለመጽሐፉ መታተም የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ከነዚህ በተጨማሪ ዩቴክ የተባለ ድርጅት እንዲሁም በሕወሀት የተቋቋሙት መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካና መስፍን ኢንጂነሪንግም ለዚሁ መጽሐፍ ድጋፍ አድርገዋል። በዚህም የተነሳ እንደ አቶ ጌቱ ገለቴ እና መስፍን ኢንጂነሪንግ ያሉት በእምነት/አቋም ድጋፍ ሲያደርጉ፣ ሌሎች ደግሞ በፍርሃት፣ በእጅ መንሻነት በተመሳሳይ የሚሳተፉ በመሆኑ የመፅሀፎቹ ተደራርቦ መውጣት የገበያ ፍላጎት ማሳያ ሊሆን አልቻለም። የጠ/ሚኒስትሩን ተወዳጅነት የምናረጋግጥበትም ሳይሆን ቀርቷል። ... ተቋማቱ በእርግጥ ድርጅቶቻቸውን የማስተዋወቅ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እንደ ምርጫ 97 ጋዜጦች በመቸብቸብ ጣሪያ የነካውንና በአንድ መጽሐፍ ብቻ መቶ ሃምሳ ሺ ኮፒ በተሸጠው የይስማክ ወርቁ ”ዴርቶጋዳ” እና በኋላ በወጣው ”ራህማቶራ” መጽሐፍ ላይ ስፖንሰር በሆኑ ነበር። ምክንያቱም መልዕክቱ አብዛኛው ቤት የመድረስ ዕድል አለውና።
የ2002 ምርጫ ግንቦት 15/2002 በተካሄደ ማግስት በመስቀል አደባባይ ኢሕአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ ለጠ/ሚ/ር መለስ ሲያጨበጭብና ሲያፏጭ የነበረው ሕዝብም ይህ ድጋፉ ለተሰጠው ውሎ አበል የሚቀርብ ምስጋና ይሁን ለጠሚኒስትሩ ያለ አድናቆት ማረጋገጥ አልተቻለም። ጠ/ሚኒስትር መለስ ተወዳጅ እየሆኑ ሥለመምጣታቸው የኢሕአዴግ ደጋፊዎች የሚናገሩትን በሀገሪቱ ዕምብርት አዲስ አበባ እየኖርኩም፣ የትውልድና የዕድገት ከተማዬ ከመሆኗ አንጻር ባለኝ ሰፊ ግኑኝነትም ላየውና ልደርስበት አልቻልኩም።
ከኢሕአዴግ ሰዎች እስከዛሬ በአንፃራዊ መልኩ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት የነበራቸው እኔ እስከማውቀው አቶ አርከበ ዕቁባይ ብቻ ናቸው። የተወዳጅነታቸው ምክንያት በአዲስ አበባ ላይ በከንቲባነታቸው ዘመን ለውጥ ስላመጡ ብቻ ሣይሆን ሰውየው አቀራረባቸው ቀላልና ከዕብሪት የፀዱ ስለሆኑ ጭምር ይመስለኛል። ለአቶ ግርማ ብሩና ለአቶ ስዩም መስፍን እንዲሁም በሥልጣን ላይ ካሉት ውስጥ ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በተወሰነ ደረጃ የተሻለ አመለካከት ይንጸባረቃል። ... የማይወደዱም፣ የማይጠሉም ማለትም በሕዝቡ ዘንድ ከቁም ነገር የማይቆጠሩት ባለሥልጣናት ይበዛሉ።
ርግጥ ነው አቶ መለስን በአንደበተ ርዕቱዕነታቸው፣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታቸው የሚያደንቋቸው ጥቂቶች አይደሉም። ይህ ማለት ደግሞ ይወዷቸዋል ማለት እንዳልሆነም ማብራራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። አቶ መለስን የሚወዱ የኢህአዴግ ደጋፊዎች የዲሞክራሲ ዕመርታ፣ የኢኮኖሚ ግስጋሴ በማለት ለመውደዳቸው የሚሰጡት ምክንያት ሕዝብ በኑሮው አልዳሰሰውም፣ በሌላም በኩል ዛሬም በዓለም ከግርጌዎቹ ሀገራት ይበልጥ ስር መውረዳችንን የሚያሳዩ ጥናቶች በየኮምፒውተር ስክሪኖቻቻን ላይ እያፈጠጡ በመሆናቸው ለቃሊቲው የኢ.ቲ.ቪ. አፍቃሪ ካልሆነ ለሌሎች ገበያ አትመችም።
የዲሞክራሲ ትግሉ ሲረዝም፣ አፈና ሲበረታ፣ ድሉ ሲርቅና ሲጨነግፍ ማሊያ በሚገልብጡ የሕሊና ሰባራዎች ሰፈር ከሚቀርበው መከራከሪያ በግሌ ”ሚዛን ደፍቶ” ያገኘሁት የሰለሞን ተካልኝን ነው። ሰለሞን ተካልኝ አቶ መለስን የወደዳቸው በቅንድባቸው ማማር መሆኑን ዘፍኖ ስለነገረን፣ ቅንድባቸው ያምራል አያምርም የሚል ሙግት ውስጥ የሚገባ ያለ አይመስለኝም። ዕይታ እንደተመልካቹ ነውና። ሰለሞን ተካልኝ ”ሳሙና”፣ ”የሩዋንዳን ታሪክ” ... ወዘተ እያለ ሲያዜም የቅንድባቸውን ማማር ሣያስተውል ሊሆን ስለሚችል ወላዋይ ሊባል አይገባም።
… ሕሊናቸውን በሆዳቸው የከለሉ ሰዎች የአቶ መለስ የፖለቲካ ሥልጣን ሲዝል፣ ተረኛው በቦታው ሲቀጥል ጠ/ሚ/ሩንና ሥርዓታቸውን ለመወንጀል፣ ዛሬ በወርቅ የሚያቀልሙትን ሥም ለማክሰል የሚጣደፉ በመሆናቸው ሁሌም ከዕውነት ጋር ሲተላለፉ ይኖራሉ። ሁሌም የጉልበት አገዛዝ እንዲፋፋ፣ አፈና እንዲስፋፋ ምቹ ማዳበሪያ ሆነው ይቀጥላሉ። ... አቶ መለስ የሻዕቢያ ልሳን ከሆነው ”ሕውየት” መጽሔት ጋር በ1989 ባደረጉት ቃለምልልስ ”ምን አይነት ሰው ትጠላለህ?” ተብለው ሲጠየቁ፤ አቋም የሌለው ወላዋይ እንደሚጠሉ፤ አላማው መጥፎ ቢሆንም አቋም ያለው ሰው እንደሚያከብሩ ገልጸው ነበር። የተናገሩት የዕውነት ባሕሪያቸውን ከሆነ በተለይ ከ1997 ምርጫ በኋላ ሥንት አቋም የለሽ አይተው እንደተጠየፉ የሚያውቁት ርሳቸው፣ ወ/ሮ አዜብ እና እግዚአብሔር ብቻ ነው።
አቶ መለስ ከ1997 በፊት ካልተወደሱ ከብዙ ትርምስ በኋላ ዛሬ አፈና ስላሰፈኑ የሚወደዱበት ምክንያት ሕሊናዊ አይደለም። ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ”ማርያምን ትወዳታለህ ወይ” ተብሎ ሲጠየቅ ”እንዴት አልወዳት፣ ከግንድ የሚያላትም ልጅ እያላት” ያለውን ቀልድ ኃይማኖታዊውን ጉዳይ ትተን ቁም ነገሩን ሥንመረምር ተወደው ከሆነ የጠ/ሚ/ሩ የመወደድ ምስጢር ይገለፅልናል። ... እመቤታችን ድንግል ማርያም የምትወደደው ግን በፍራቻ ሣይሆን ልጅዋ ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በከፈለልን ፍፅም ዋጋ በፍቅር እንጂ በፍርሃት አለመሆኑን እግረመንገዴን አስታውሳለሁ። ዝርዝሩን ለሃይማኖት ልሂቃን እተወዋለሁ። ... እኔም ሳልፈራ ቀርቼ አይደለም። እውነት እየተናነቀኝ፣ እያዩና እየሰሙ መቃጠል ከፍርሃቱ ባላነሰ ውስጤን እየበላው በመቸገሬ እንጂ።
... አዎን ጉልበት የጠዋት ጤዛ ነው። እንደ ኢሕአዴግ የሕዝባዊ ተቀባይነት ቀውስ ውስጥ የገባ መንግሥት ደግሞ እንደ ሰፈሬ ሰው ጋሽ ተረፈ አባባል ”ፀጉራም ውሻ” ማለት ነው። ዕውነት ነው ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ሞቶ ይገኛል። ሞተ ሲሉት ሕይወት ዘርቶ ይታያል። ኢሕአዴግ በ1997 በምርጫው አበቃለት ከተባለ በኋላ አፈር ልሶ-ነፍስ ዘርቶ እንደታየው ሁሉ አለ ሲሉት ሞትም ይመጣልና አስቀድሞ ”መቁረብ” (የዜጎችን ጥያቄ መመለስ) ሐጢያትን የሚደመስስ፣ የሕዝብን ፍቅር የሚመለስ ነው። እነ አቶ ስዬ ከተባረሩ በኋላ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር። በኋላም በቅርቡ የተሰናበተው ፓርላማ የመንግሥት ም/ተጠሪ የነበሩት ወ/ሮ ነጻነት አስፋው በ1996 በአንድ አዲስ አበባ በሚገኝ የምዕራብ ኤምባሲ በተደረገ የኮክቴል ግብዣ ላይ የተናገሩትን ማስታወሱ ለፀጉራም ውሻ ምሳሌዬ አብነት ይሆናል። ወ/ሮ ነፃነት ጥቂት ጋዜጠኞችና የጋዜጠኛ ማሕበር መሪዎች ጭምር በታደሙበት መድረክ ”ለሚቀጥሉት አንድ መቶ አመታት ኢሕአዴግን የሚፈታተን ተቃዋሚ በኢትዮጵያ ምድር አይፈጠርም” ነበር ያሉት። መቶ አመት ሳይሆን መቶ ቀን ሣይሞላው ኢሕአዴግ በቅንጅት የደረሰበትን ሽንፈት አይተናል። ሠላማዊውና ዲሞክራሲያዊው ጉዞ በጉልበት ሲቀለበስም ሁላችንም እዚያው ነበርን።
ሃሳቤን ልሰብስብና ላጠቃለው። እውነቱን እንነጋገር። በዕውነተኛው የኢኮኖሚው ዕድገት ሀገሪቱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም። የዲሞክራሲው ጉዞ መቀልበሱ፣ የጉልበት አገዛዝ መንገሱም ማይስተባበል እውነት ነው። በጤናውም፣ በትምህርቱም በተለይ ከጥራት አንጻር ቁልቁል እንጂ ሽቅብ ጉዞው በአፍ ብቻ ሆኗል። አቶ መለስም ሆኑ ፓርቲያቸው ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል መርተው ለድል መብቃቱ ቢሳካላቸውም ሀገሪቱን ወደፊት መውሰድና ሕዝቡዋን ከችግርና ችጋር ማውጣት አልሆነላቸውም። ሕዝብ በስቃይና በሰቀቀን ላይ ይገኛል። ያልተሳካላቸው ለምን እንደሆነ በግምት ሳይሆን በባለሙያ ጥናት ቢደገፍ የተሟላ ስዕል የሚሰጥ ቢሆንም፣ ከሚታየው በመነሳት እንደትልቅ ችግር ሊነሳ የሚችለው የሕዝባዊ ተቀባይነት ቀውስ ነው።
ለዚህ ደግሞ እንደመነሻ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉት ቡድኑ ወደሥልጣን ሲመጣ ገዢ መደብንና ሕዝብን ለይቶ ለመመልከት አለመቻሉ፣ የዘር ልዩነት በማራገብ በጥላቻ መጥቶ በቂም የመግዛት ዝንባሌውና ራሱን በተግባር ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መቸገሩ ወዘተ ያስከተለው ተቃራኒ ሕዝባዊ ጥላቻ አቅምና ችሎታው ያላቸው ሰዎች ሥርዓቱን እንዳይቀርቡት አድርጓል። የቀረቡትንም አሳዷል። አቅምና ችሎታ የሌላቸውን ታማኞች ከየክልሉ በመልመል ሥልጣን እየሠጠና አንዳንዱንም ፊደል እያስቆጠረ የአቅም ማነሱን ባለዲግሪ በሚል ማዕረግ ለመሸፈን ብዙ ጉድ እንደታለፈ ያው እነርሱው ጋር የነበሩ ሰዎች ፅፈው አንብበናል። ዕኩልነት አፍአዊ ብቻ ሆኖ በተግባር የብሔረሰብ ጭፈራ ከማሳየት ያለፈ ጠብ የሚል ነገር መጥፋቱ፣ ራዕይ አልባነት፣ ሥልጣንን በሥልጣን ላይ ለራስ ፍላጎት ከመቆየት ያለፈ ግብ አለመመዝገቡ ወዘተ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
የእድገት፣ የልማት ዋነኛው ግብአት ሕዝባዊ መተማመን መሆኑ ዛሬም ትኩረት አላገኘም። የዕውነት ያደጉት የሚነግሩን ግን ያለሕዝብ ይሁንታ ቀጣይነት ያለው ዕድገት የማይቻል መሆኑን ነው። በአፍሪካ መልካም አስተዳደር እውን እንዲሆን በሚሰራው በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ድረ ገጽ ላይ የሰፈረውን የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንትን ንግግር ልጥቀስ ”sustainable development requires states to be legitimate in the eyes of their citizens and to deliver the core function of the state” አዎን! ቀጣይነት ላለው ልማት መንግሥት በዜጎች ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል። መንግሥታዊ ሃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ሕዝባዊ ተቀባይነት አስፈላጊ መሆኑን ነው አማኑኢል ባሮሶ ያስገነዘቡት።
መብታችን ተነካ፣ ሕዝባችን ፍትሕ አጣ፣ በደል በረታብን ብለው የዩኒቨርስቲ ትምርህታቸውን ጥለው፣ የተሻለ ኑሮ ገፍተው በቁርጠኝነት በረሃ የወረዱ ሰዎች በፅናታቸው ትግላቸው ሰምሮ ሥልጣን ሲይዙ ጭቆናን በጭቆና፣ ለመካስ ሲንቀሳቀሱ ሥናይ በደልና ብሶት ብቻ ሣይሆን ጥላቻም ለያሳምፅ እነደሚችል ያስገነዝበናል። አላማቸው ቢያንስ ከምናየው ውጤት አንጻር ለሐገር ባይጠቅምም ለሚያምኑበት ነገር ላሳዩት ቁርጠኝነት ግን አድናቆት ይገባቸዋል። መንገድ መሪዎቹን አይጨምርም። በአጠቃላይ ያ ትውልድ ሰልፉ ይለያይ እንጂ በርግጥም ቆራጥ ነበር። ...
እናጠቃለው።
በ1994 ጠ/ሚ/ር መለስ ከዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር በተወያዩበት ወቅት ”ክቡር ጠ/ሚ/ር ኳሷ በርሶ እግር ሥር ነች” ያሉ አንድ የንግድ ሥራ ኮሌጅ መምህር ”ይህችን ሓገር ወደ መጥፎም ወደ ጥሩም የመውሰድ ሥልጣን በእጅዎ ነው። ሌሎች ከማጀብ ያለፈ ሚና የላቸውም” በማለት ነበር ሃሳባቸውን ያጠቃለሉት። አቶ መለስ ከዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር በ1994 ሲወያዩ በአቶ ተወልደ ወ/ማርያም የሚመራውንና አቶ ስዬ ያሉበትን ቡድን ሸኝተው ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ መጠቅለል የጀመሩበት ግዜ ነበር፣ ወደ 10 አመት ከተጓዙ በኋላ ደግሞ የእነ አቶ ስዬን ያህል የወሳኝነት ሚና ባይኖራቸውም ነባር የህወሐትና የብአዴን ዋና ሰዎችን ጠርገው የቀደመ የፖለቲካ ተሳትፎ ያልነበራቸውን፣ በትግሉም ውስጥ ያላለፉትን አሰባስበው ሥልጣናቸውን በብቸኝነት ያጠናከሩበት ግዜ ላይ ደርሰናል። በትግሉ ውሥጥ ካለፉ ታጋዮች ብቸኛው ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ናቸው። እርግጥ ነው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከማያዙት ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር ሁለት ናቸው። ከቀሪዎቹ 21 ሚኒስትሮች ሃያዎቹ (ጠ/ሚ/ሩ አንደኛው አባል አይደሉም ብለዋል) ኢህአዴግን ያወቁትና የተቀላቀሉት ሥልጣንም፣ ገንዘብም ከያዘ በኋላ በመሆኑ ኢሕአዴግን በኣላማው ይውደዱት ወይንም ለእህል ውሃ ይቅረቡት ማረጋገጫ መንገድ የለም።
አቶ መለስ እነዚህን መሰብሰባቸው ሥልጣናቸውን ከማጠናከር ባሻገር ግፊት በርትቶ ሥልጣን የሚለቁበት ሁኔታ ቢፈጠር ሥልጣንን በህጋዊና ፓርላመንተሪ በሆነ ሥርዓት ከ 5 ዓመት በኋላ ወደ ወ/ሮ አዜብ ለማሸጋገር የማይጠይቁ ሰዎችን በፓርቲም በመንግሥትም መዋቅር ውስጥ ወደላይ አምጥተዋል። ከመቼውም ግዜ በላይ ኳሷን በቁጥጥር ስር አውለዋል። በረኛ በሌለበት በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሚገኝን ኳስ ወደ ግብ መትቶ የማስገባት ያህል የዚህችን ሀገር ዕጣ ፈንታ የመወሰን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በመዳፋቸው ሥር አስገብተዋል። ወደ ብርሀን ሊወስዱን ከፈለጉ ሁሉ በእጃቸው ነው። ከጨለማው መውጫ መንገድ ... ዲሞክራሲ! ዲሞክራሲ! ዲሞክራሲ! ... ብቻ ነው።
አዎን! ሕዝባዊ አስተዳደር ባለበት የህግ የበላይነት አለ፣ ሕዝባዊ መንግሥት ባለበት ሰብዓዊ መብት ይከበራል። ሕዝባዊ መንግሥት ባለበት ነጻ ተቋማት ይኖራሉ። ነጻ ተቋማት ካሉ ነጻ ምርጫም ይካሄዳል። ነጻ ፍርድ ቤትም ይኖረናል። ... ይህ ዕውን ሲሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በየትኛውም መንግሥት ያልተደረገ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እናያለን። ወይንም ኢሕአዴግ በሕዝባዊ ድምጽ በሥልጣኑ ይቀጥላል። አቅም ያላቸው ይጠጉታል። የእህል ውሀው ማህበር ይፈርሳል። … ያኔ ብሄራዊ እርቅ ይፈጠራል። ያኔ የተበደለ ይካሳል። የተሰደደ ይመለሳል። የሰማዕታት ክብር ይወሳል። ያኔ በቁጥር ሳይሆን በእውነት ማደግ እንጀምራለን። አዎን ያኔ የአቶ መለስ ፎቶ ያለበት ቲሸርት ለመብረቅ መከላከያ ሳይሆን በፍቅር ይለበሳል። እግዚሕአብሔር ይርዳን! እርሳቸውንም እግዚያአብሔር ቀናውን ያሳያቸው። ”እግዚያአብሔር ሲጣላ አይመታም በበትር። እያደናገረ ያሳስታል ምክር” ይባላልና ሩቅ ምስራቅ ከማማተር አጠገባችን ወዳለው ፈጣሪ ማንጋጠጥ መጨረሻውን ለሁሉም ያማረ ያደርገዋል።
ሲሣይ አጌና (ከአዲስ አበባ)
ለአስተያየትዎ እነሆ ኢ-ሜይል
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጥቅምት 12/2003 ዓ.ም.



