ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ከጥቂት ሣምንታት በፊት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ አምስት ገጾች የያዘ መግለጫ አውጥቷል። በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አደገኛ ሁኔታ ላይ እየወደቀ እንደሆነ የገለጸው መድረክ፣ ኢትዮጵያ ወደ አንድ ግለሰብ አምባገነንነት እያመራች እንደሆነም በመግለጫው ያትታል።

 

”በዚሁ ሂደት ኢህአዴግም በተግባር የኢሠፓ አልጋ ወራሽነቱን አስመስክሮ ሀገሪቷን ወደ አንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት ዘመን ይዟት ተሟል። በአመራር ደረጃም መተካካት እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነገረን የባጀው በተግባር ግን ተራ በኢትዮጵያ ገዢዎች ዘንድ የተለመደው የሹም ሽር ከመሆኑም በላይ በመንበረ-ሥልጣኑ ላይ የተቆናጠጡትን የሥልጣን መሠረት ለማስፋትና ብሎም ቀጣይነቱን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማረጋገጥ የተሰራ ቀመር ነው። ከዚህ የዘለለ አንዳች የዴሞክራሲ ሽታ የለውም የጉልቻ መለዋወጥ ከመሆን አልዘለለም። በደርግ ጊዜም የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የአንድ ግለሠብ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እንደነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስረዳት ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው።” ሲል ነበር መድረኩ ኢህአዴግ ዳግማዊ ኢሠፓ እንደሆነ የገለጸው።

 

ኢህአዴግ በቅርቡ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በሚል በሰፊው እያስተዋወቃቸው ያሉ ፕሮጄክቶች አሉ። ስለነዚህ ፕሮጄክቶች መድረኩ በመግለጫው የሰጠው አስተያየት የለም። ነገር ግን በተዘዋዋሪ መንገድ፣ የሚታቀዱ የልማት ሥራዎች፣ መልካም አስተዳደርና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ እውን ሊሆኑ እንደማይችሉ፣ የመድረኩ መግለጫ ይገልጻል። ”በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም መስኮች ነፃነቱን በተገፈፈበት ሁኔታ ልማት ሊመጣ አይችልም። ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ከእውነተኛ ነፃነት ጋር በእጅጉ የተዛመዱ ጉዳዬች ናቸው። ነፃነት በሌለበት አገር እነዚህን ነገሮች ሁሉ አሰፈንኩ ማለት እንደተለመደው ከተራ ፌዝ አያልፍም። ነፃነት በሌለበት ልማት እውነ አይሆንም። አለ በቢባልም ዘለቄታ አይኖረውም።” በማለት ነበር መድረክ ለማስረዳት የሞከረው።

 

ነገር ግን የመድረኩ መግለጫ ላይ መሰረታዊ ችግሮች አያለሁ። የመድረኩ መግለጫ እውነትን ያዘለ ቢሆንም መቶ በመቶ ኢህአዴግን በመቃወም ላይ ብቻ ያነጣጠረ፣ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚያወቁትን መልሶ የሚደጋግም፣ ውሃ ያልቋጠረ መግለጫ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

 

ከአንድ ዓመት በፊት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መድረክን ሲቀላቀል አብዛኞቻችን በደስታ ነበር የተቀበልነው። በዘር መከፋፈል ቀርቶ፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ቅልቅሉ … ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ድንኳን ሥር መሰባሰባቸው፣ በአጠቃላይ የመድረክ መመስረት ታሪካዊና ትልቅ ድል እንደሆነ ስንናገር ቆይተናል።

 

ታዲያ ከአንድ ዓመት በፊት የተገኘን ድል፣ ዛሬም በማውራት ብቻ መወሰን ያለብን አይመስለኝም። መድረኩ አሁንም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረበት ደረጃ ብዙ ፈቀቅ ያለ አይመስለኝም። ኢህአዴግን ከመቃወም ውጭ በይፋ ለህዝብ ያቀረባቸው ህዝብን የሚያታግሉ አማራጮችን በሰፊው ሲያስተዋውቅ አንሰማም።

 

ኢህአዴግ ደገፍነውም አልደገፍነውም አጀንዳዎቹን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጧል። እነዚህን አጀንዳዎች ተግባራዊ ያድርጋቸው አያድርጋቸው እርሱ ሌላ የመነጋገሪያ ነጥብ ነው።

 

ነገር ግን ቢያንስ ቢያንስ ህዝብ ሊረዳው የሚችል፣ የተጨበጡ ግቦችን ይዞ ተነስቷል። ከሞያሌ እስከ ትግራይ፣ ከጅቡቲ ወይንም በርበራ እስከ ሱዳን ድንበር፣ በአዲስ አበባ የሚያልፍ፣ የባቡር ሃዲድን ለመገንባት እቅድ ዘርግቷል። ደርግ ሲወድቅ፣ የኢትዮጵያ የኤሌትሪክ አቅም ከ500 ሜጋ ዋት በታች ነበር። አሁን ወደ 2000 ሜጋ ዋት አካባቢ ነው ይባላል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ2000 ሺህ ወደ 10000 ሺህ ለማሳደግና ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በምግብ እራሷን እንድትችል ለማድረግ ዓላማ እንዳለው ኢህአዴግ እየተናገረ ነው።

 

እነዚህ ኢህአዴግ ያስቀመጣቸው የልማትና የትራንስፎርሜሽን ዓላማዎች መድረኩም የራሱ ዓላማ አድርጎ ማንገብ ያለበት ይመስለኛል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን እንድትችል፣ የባብሩ ሃዲዶች ከድንበር እስከ ድንበር እንዲገነቡ መደገፍና ማገዝ የሚገባው ይመስለኛል። እነዚህን የልማት እቅዶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማገዝ ኢትዮጵያን ማገዝ ነው፤ ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ናቸውና። እነዚህ ግቦች የኢህአዴግ ግቦች ብቻ ሊሆኑ አይገባም።

 

ለምሳሌ መብራት በሌለባት በአንዲት የገጠር ከተማ አንድ የኢህአዴግ ካድሬና አንድ የመድረክ አደራጅ ይሄዳሉ እንበል። ሁለቱም በተለያዩ ጊዜ ነዋሪውን ይሰበስቡትና መግለጫ ይሰጣሉ። የኢህአዴጉ ካድሬ ”እኛ መብራት በመንደሩ እንዲገባ እናደርጋለን” ይላል። በነጋታው ደግሞ የመድረኩ አደራጅ፣ ስለ መብራት ምንም ሳያወራ፣ የኢህአዴግን ጸረ-ዴሞክራሲያዊነትና አምባገነንነት ብቻ ዘርዝሮ ንግግሩን ይቋጫል። ሁለቱን ባዳመጣው ነዋሪ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የቱ ነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው። ያለ ምንም ጥርጥር መብራት አናስገባለን ያለው የኢህአዴግ ካድሬ ነው ተቀባይነት የሚኖረው።

 

የመድረኩ አደራጅ ”እኛም መብራት እናስገባላቹሃለን። ነገር ግን ከኢህአዴግ የሚለየን ነገር አለ።ኢህአዴግ የሚታመን አይደለም። ላለፉት አሥራ ስምንት ዓመት መብራት ያላስገባላችሁ አሁን እንዴት ሊያስገባላችህ ይችላል? የኢህአዴጉ ሊቀመንበር ደርግን ከወደቀ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉም በአስር ዓመት ውስጥ በቀን ሦስቴ ምግብ እንደሚያገኝ ተናግረው አልነበረም ወይ? አሁን እስቲ እናንተም ልጆቻችሁም እንኳን ሦስቴ አንዴም የምትመገቡት በችግር አይደለም ወይ? የፈረንጆች ፉርኖ ዱቄት ቢቆም በሚሊዮን የሞቆጠሩ እንደ ቅጥል ይረግፉ አልነበረም ወይ?” የሚል መከራከሪያ ቢያቀርብ ግን የመንደሩ ነዋሪዎች ለመድረኩ አደራጅ ነበር ድጋፍ የሚሰጡት።

 

እንግዲህ ቁልፉ ”መድረኩም መብራት ያስገባል” ማለቱ ላይ ነው። እንዲሁ በባዶ ኢህአዴግን መቃወም ውጤት አያመጣም። አብዛኛው ህዝባችን በድህነት፣ በችግር፣ በመኃይምነት፣ በበሽታ እየተጎሳቆለ ያለ ህዝብ ነው። አብዛኛው ህዝባችን በውጭ አገር እንደምንኖር ወይንም በአዲስ አበባ ትንሽ እውቀት እንደቀመስን ሰዎች፣ ሊበራል ዴሞክራሲ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚል ልዩነት አያውቅም። ህዝቡ የሚፈልገው ኑሮው እንዲሻሻልለት ነው። በመሆኑም መድረኩ እራሱን በዚህ አንጻር ከህዝቡ መሻትና ፍላጎት ጋር ማዛመድ ያለበት ይመስለኛል።

 

ሌላው ሁለተኛው ነጥቤ፣ መድረኩ የተቃዋሚ ቡድን ከመሆን አልፎ አገር መምራት እንደሚችል በግልጽ ማሳየት እንዳለበት የሚጠቁም ነው። ለዓመታት የምናያቸው እንደ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ የመሳሰሉ አንጋፋ የተቃዋሚ መሪዎች፣ ላበረከቱት አገራዊ አገልግሎት ያለኝን ትልቅ ከበሬታ በመግልጽ፣ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን ፈለግ ተከትለው፣ በአዲስ ራዕይና በአዲስ መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ለሚችሉ ወጣቶች ኃላፊነታቸውን ማስረክብ ያለባቸው ይመስለኛል። የመድረኩ አመራርና አሰራር ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል። የመድረኩ ዘገምተኛ አካሄድ መቆም ይኖርበታል እላለሁ።

 

በሦስተኛነት ለማንሳት የምፈልገው መድረኩ ያለ ውሳኔ ያንጠለጠላቸው አንዳንድ አጀንዳዎቹን በተመለከተ ነው። ከነዚህ አጀንዳዎች መካከል በቀዳሚነትና በዋናነት የሚጠቀሰው በኢትዮጵያ ምን አይነት ፌዴራል አወቃቀር ይኑር የሚለው አጀንዳ ነው። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ጨምሮ በርካታ የመድረክ አባል ድርጅቶች እንዲሁም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አሁን ያለውን በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሰረተው ከፋፋይ ፌደራል አወቃቀር መቀየር አለበት ብለው ያማናሉ። መድረኩ በዚህ ቁልፍ ጥያቄ ላይ አሁንም፣ ከዓመት በኋላ፣ ውሳኔ ላይ አለመድረሱ ብዙ እየጎዳው ያለ ይመስለኛል።

 

አንድ አገርን እመራለሁ የሚል ድርጅት ተነጋግሮ፣ ተማምኖ አብይ በተባሉ ጉዳዮች ላይ፣ ከአንድ ዓመት በላይ አቋም መውሰድ ካልቻለ፣ ነገ ስልጣን ቢጨብጥ አገራዊ የሆኑ አንገብጋቢ ጉዳዮች ቢመጡ፣ በቀላሉ የመወሰንና የመምራት ችግር ሊያጋጥመው ይችላል የሚል እድምታን የሚፈጠር ነው።

 

መድረኩ እንደሚመስለኝ የአብዛኛው ህዝብን ፍላጎት ያንጸባረቀውን ፌደራላዊ አወቃቀር ተቀብሎ መቀጠል የሚኖርበት ይመስለኛል። ይኸውም ቋንቋን፣ የህዝብ አሰፋፈርን፣ ኢኮኖሚን፣ የህዝቡን ፍላጎት የመሳሰሉ ጠቃሚ ነጥቦችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ፌደራል አወቃቀር ነው።

 

መድረኩ በዚህ ቁልፍ ጉዳይ በሆነው በፌደራል አወቃቀር ላይ ግልጽ አቋም መውሰዱ፣ ሌላ ትልቅ ጥቅም ሊያመጣለትም ይችላል። እንደ መኢአድ ያሉ አንጋፋ ደርጅቶች ወደ መድረኩ እንዲቀላቀሉም ይረዳል።

 

በነገራችን ላይ ”መድረኩ” ስል በመድረኩ ያሉ ድርጅቶችን በነጠላ ማለቴ አይደለም። መድረክ በመድረክነቱ ዘገምተኛ ቢሆንም ጥሩ እየሰሩ ያሉ የመድረክ አባል ድርጅቶች አሉ። ለምሳሌ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ የዴሞክራሲ ታጋዮችን ካምፕ ለማስፋት፣ እንደ መኢአድና ብርሃን ለዴሞክራሲ ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ሰምቻለሁ። አንድነት ከነዚህ ድርጅቶች ጋር የሚያደርገው ንግግር አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያስደስተ ጉዳይ ነው። ሌላው ደግሞ ፓርቲው ከ70% በመቶ በላይ የላእላይ ምክር ቤት አመራር አባላቱ ወጣቶች መሆናቸውና በቅርቡ በሥራ አስፈጻሚው ሳይቀር የወጣቶችንና የሴቶችን ቁጠር ለማሳደግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንዳለ መዘገቡ ነው። ይህም የአንድነት ፓርቲ ላይ ብዙዎቻችን ትልቅ ተስፋ እንዲኖረን አድርጓል። የአንድነት ፓርቲ እንቅስቃሴ በተመለከተ በሚቀጥለው ጊዜ በሰፊው የምመለስበት ጉዳይ ይሆናል)


ግርማ ካሣ

(This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ