አሸብር ከጀርመን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በቅድሚያ ስለመለስተኛ ፕሮግራሙ አስተያየት ለመስጠት ጉዞ ስጀምር፤ መንግድ ላይ ያገጠመኝን ከዚሁ ፐሮግራም ጋር ዝምድና ያለው ዶ/ር ማራራ ጉዲና የመድረክ ሊቀመንበር ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ውስጥ ስለጥምር መንግሥት አመሰራረት ከመድረክ ጋር ለማነጻጸር እንደምሳሌ አድርገው ስላቀረቡት የጀርመን ፌዴራል ሪፑብሊክ ጥምር መንግሥትን በተመለከተ ንጽጽሩ ጉድለት ስላለው ለማስተካከል ይረዳል የምለውን ልበል፤

 

የቀረበላቸው ጥያቄ፤-

ሪፖርተር፦ የስምንት ፓርቲዎች ጥምር በሆነው መድረክ ውስጥ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ የፓርቲ መሪዎች እንዳሉ ይነገራል። ከፊሎቹ ሊበራል ዴሞከራሲ፤ ከፊሎቹ ሶሻል ዲሞክራሲ … ፖለቲካ አራማጆች ናቸው ይባላል። በዚህ ሁኔታ ተስማምቶ መቀጠል ይቻላል ይላሉ? በነገራችን ላይ ጠያቂው የተለያየ ርኢተአለም የሚያራምዱ የፓርቲ መሪዎች ሲል ምን ማለቱ ነው? የመድረኩ አባላት ፓርቲዎቹ ወይስ የፓርቲው መሪዎች? መድረኩ ፓርቲዎቹ በጋራ ተስማምተን መለስተኛ ፕሮግራም አውጥተናል ሲል እንዴት እንደገና ተስማምታችሁ ልትሰሩ ትችላላችሁ የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ አልገበኝም። ወደዋናው ጉዳይ ልመለስ፤

 

በተሰጠው መልስ ዶ/ር መረራ እንዳሉት ከ1945 ዓ.ም. በኋላ በ1949 ዓ.ም. የተቋቋመው የጀርመን ፌዴራል ሪፑብሊክ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የሚተዳደረው በጥምር መንግሥት ነው። የጥምር መንግሥት ጥያቄ የሚመጣው ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ነው። በምርጫ ውድድር ጊዜ እያንዳንዱ ፓርቲ በተቻለው ቢቻል የፓርላማውን አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ብቻውን መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችለውን ድምጽ ለማግኘት፤ ያም ባይሆን በተቻለው ከፍትኛ ድምጽ በማግኘት ከሌሎች የበለጠ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ነው የሚጥረው። ይህም ሲባል ደግሞ አብላጫ ድምጽን አግኝቶ ብቻ ገዥ ለመሆን ያለው ዕድል በጣም ጠባብ መሆኑንም ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በምርጫ ዘመቻ ጊዜ በተውሰነ ደረጃም ቢሆን፤ ማን ከማን ጋር ጥምር መንግሥት መፍጠር እንደሚፈልግ ፍንጭ አያሳይም ማለት ባይሆንም፤ የምርጫውን ውጤት በቅድሚያ ለማወቅ ስለማይቻል ወሳኙ ከምርጫው በኋላ የሚገኘው ውጤት ነው። ያም ሆነ ይህ እንግዲህ ከምርጫው በኋላ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የተስማሙት ድርጅቶች ቁጭ ብለው በምርጫው ጊዜ ለህዝብ የገቡትን ቃል ሳይሆን እነደያአቅማቸው ድርድሩ ያስገኘላቸውን ተቀብለው እስከሚቀጥለው የምርጫ ጊዜ የሚያገለግል የስራ ፕሮግራም ነድፈውና በውል ተፈራርመው መንግስቱን የቋቁማሉ።

 

ከዚህ ተነስተን መድረክን ስንመለከት ግን የምናየው ጉዳይ ሌላ ነው። መድረክን የፈጠሩት 8 ድርጅቶች በጋራ አብረው የነደፉት ፕሮገራም የጋራ የምርጫ ማነፌስቶ ሆኖ መድረክ ለምርጫ ውድድር ቀርቦበታል። በዚህም የጥምር መንግስቱ መቋቋም ጥያቄ አልቆለታል ማለት ነው። መድረክ - አቶ መለስ በሚገዟት ኢትዮጵያ በምትባል ምድር በሚካሄድ ምርጫ፤ - ተወዳድሮ አሽንፎ ስልጣን ይዞ ስራ ላይ የሚየውለውም ይህንኑ ፕሮግራም ነው። በዚህም እንደጀርመን ጥምር መነግሰት እናቋቁማለን የሚለው መልስ ቦታ አይኖረውም ማለት ነው። ከዚህ በላይ በዚህ ነጥብ ሳልቆይብት ወደ መለስተኛው ፐሮገራም ልሸጋገር፤

 

መነሻው፤ „ የኢትዮጵያ ህዝቦች ያጋጠማቸውን የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ለመቀየር ብዙ መስዋዕትነት ያስከፈል ትግል አካሂደዋል። ሌላው ቀርቶ ከሰላሳ አምስት ዓመት በፊት ባካሄዱት ትግል ዘውዳዊው አገዛዝ የተገረሰሰበት ሁኔታ ቢፈጥሩም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ስልጣን የያዙት ወታደራዊ መኮንኖች ለሰብአዊ መብት መከበር የተደረገውን ትግል፤ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እና ለብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር የተደረገውን ትግል በመደፍጠጥ ሕዝቡን ተመልሰው ለከፋ ስቀይና አፈና ዳርገውታል። የፐለቲካ ልዩነት ወንጀል ሆኖ ለቀይ ሽብር የተዳረገበት፤ የሰው ህይወት ዋጋና ክብር ያጣበት የደርግ ዘመን ዘግናኝ ታሪካችን አሁንም ድረስ ከዜጎች ህሊና ያልጠፋበት ትዝታ ነው። ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በነበረው አፈናና ወከባ ተደናግጠው ትግላቸውን አላቋረጡም፤ የልቁንስ ትግላቸውን ይበልጥ በማጠናከር የደርግን ሃይል ማንኮታኮት ችለዋል። በደርግ ዘመን የተፈጸፈው ሌላው የማይረሳው የታሪካችን ገጽታ ደግሞ በተቃዋሚ ድርጅቶች መካካል መቻቻልና መግባባት ጠፍቶ እርስ በእርሳቸው ያደርጉት ሽኩቻና ደም መፋሰስ ነው። “ (ከመድረክ መለስተኛ ፐሮግራም ሰኔ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. መግቢያ ገጽ 4 የተወሰደ)

 

አንባቢዎች ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ጽሁፍ አባበሉ ያልሆነ ነው፤ ያልተፈጸመ ነው፤ በማለት ለማስተባበል ወይም ለመጨመርና ለመቀነስ ብዬ ያቀረብኩት ጉዳይ እንዳልሆነ ተገንዘቡልኝ። ሃሳቡን መዝዤ ያቀረብኩበት ጉዳዩ ወዲህ ነው። እንደተባለውም የኢትዮጵያ ህዝብ - ህዝብ የምለው እኔ ነኝ። የመድረክ ቋንቋ አይደለም። - አደረገ በሚባለው የረጅም ጊዜ ትግል ከዚህ በላይ እንደተባለው በደርግ መንኮታኮት ላይ አቆመ ብሎ ከዚያ በኋላ ምንም ነገር እንዳልተደረገ፤ ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ፤ በማድረግ የሆነውን ሁሉ ወደጎን ትቶ ደርግ ተነኮታኮተ ከሚለው ተነስቶ ትግል እንቀይስ ማለት፤ ቢያንስ ባለፉት 18 ዓመታት በኢትዮጵያ መሬት ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አልነበረም/አልኖረም ከማለት ያነሰ ግምት የሚያሰጥ አይመሰልኝም።

 

ባገራችን የፖለቲካ ስርአት ህይወት ውስጥ በዕድሜያችን ካየናቸው የለውጥ ጊዜያቶች፤ የየካቲት 66 ለውጥ እሰከዚያ ጊዜ ድረስ የተመዘገቡ ተመሳሳይ ድርጊቶች ነበሩ ብለን በንንጽር የምናቀርብለት ያለ አይመስለኝም። ያ ለውጥ የሃገራችንና የህዝባችንን የፖለቲካ ህይወት 180 ዲግሪ ለውጦታል። ጥፋቱም ሆነ ልማቱ ተድምሮና ተቀንሶ ከሃገሪቱ የታሪክ መዝግብ በትልቅነቱ በቻ ሳይሆን በወሳኝነቱ ጭምር ተከብሮ ይቀመጣል። ምናልባትም ጊዜ ፈቅዶ በያመቱ የሚታሰብበት ሁኔታ መፈጠሩ ሩቅ ላይሆንም ይችላል። እሱን ተከትሎ የሚመጣው ግንቦት 7. 1997 ነው። ምንም እንኩዋን የአመጣጣቸው መንገዱም ሆነ ጊዜው የተለየ ይሁን እንጂ፤ ሁለቱም በኢትዮጵያና በህዝቧ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የፈጠሩት እምርታ በዓይነት ካልሆነ በስተቀር በታሪክ መዝገብ ውስጥ የሚኖራቸው ቦታ ቢያንስ በእኩልነት የሚጠበቅ ነው።

 

ስለሆነም ከላይ እንደ የደርግ መንኮታኮት በሚል የታሰረው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ውጤት ሁሉ፤ በግንቦት 7 .1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ህዝብ ያስመዘገበውን ድል፤ እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆኖ ለማለፍ መሞከር፤ ለህዝብ ጥቅምና ለህዝብ ጥያቄ ጆሮ አለኝ የሚልን ሁሉ አስቂኝ የሆነ ትዝብት ላይ ከመጣሉም በላይ፤ በታማኒነት ላይም ጥቁር ጥላ ይጥላል። ሕዝብ በ ግንቦት 7.1977 የሚፈልገውን አስረግጦ የተናገረበት፤ እኔ አውቅልሃለሁ ማለትን ይብቃ ያለበት፤ የምተዳደረው በመረጥኩት ነው ያለበት ዕለት ነው። ይህንንም ሲያደርግ፤ የሶስተኛ አለም ህዝብ ያልተማረ የማያነብ፤ የማይጽፍ፤ ስለሆነ የምርጫ መብቱን ሊጠቀም አይችልም እየተባለ የሚጋረድበትን የስነ-ልቡና አጥር ጥሶ፤ ለኢትዮጵያውያውን ብቻ ሳይሆን ለሌላም ህዝብ ምሳሌ የሆነ ምርጫ በማካሄድና እነዚሁ አይችልም ያሉት ሃይሎች አባባላቸውን እንዲቀለብሱ በማደረግ እንደሆነ የማይታብለ ነው። የዚህ አንጸባራቂ ድል ባለቤት እንደይሆን፤ የሰጠው ድምጹ ሲዘረፍበት አሜን ብሎ ሳይቀመጥ ድምጼ ይከበር ብሎ ወጥቶ ድምጹን ከፍ አድርጎ ጮኸ። ለጩኸቱ በተሰጠው ፋሺሽታዊ እርምጃ በመቶ የሚቆጠሩ ህጻናት፤ ወጣት፤ ሽማግሌ አሮጊት በአግአዚ ጥይት ተቆሉ። የመረጣቸው ወኪሎቹና ደጋፊዎች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በገፍ ታፍሰው ለስር ተዳረጉ። ከ30 ዓመት በፊት በቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ልጇ በግፍ ተገድሎባት እንዳለቀሰችው እናት ሁሉ፤ ሰኔ 8.1997 እና ጥቅምት 20. 1998 ባግአዚ ጥይት ልጇ በግፍ የተገደለባትም እናት አነባች።

 

ታዲያ ከግንቦት 7. 1997 በኋላ የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ብሎ የሚነሳ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ መነሻው መሆን ያለበት የግንቦት ድሎችን ለማስመለስ - ድምጼ ይከበር ሲል ህዝብ የጠየቀውን - ካልሆነ በስተቀር ወደሁዋላ ሄዶ ከ 30 ዓመት በፊት የሆንን ነገር መጎተትና ያንን መነሻ ማድረግ አስፈላጊነቱ የቱ ላይ ነው? ወይስ በእርግጥ ዛሬ መድረክን የፈጠሩት የጎሳ ድርጅቶች ይሉ የነበረው፤ እነዚያ የግንቦት 7 ድሎች የአንድ ጎሳ ድል እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ተብሎ ሊመዘገብ አይችልም የሚለው አቋም በመድረክ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ወጥቶ ነው? የግንቦት 7 የህዝብ ድሎች ከቁጥር ሳይገቡ እንዳልባሌ የታለፉት? የመድረክ መለስተኛ ፐሮግራም ባለቤቶች መልስ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ወደ መለስተኛ ፕሮግራሙ ዝርዝር ልተላለፍ፤

 

መለስተኛ ፐሮግራም ምንድነው? ለምንሰ ያስፈልጋል? በመድረክ ውስጥ የተሰባሰቡት ድርጅቶች የሚከተሉት ናቸው፡ 1ኛ. የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፤ 2ኛ. የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴ. ህብረት፤ 3ኛ. የ ኦሮሞ ህዝቦች ኮነግረስ፤ 4ኛ. ያኦሮሞ ፌደራሊስት ዴ.ፓረቲ፤ 5ኛ አረና ትግራይ 6ኛ. ሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች፤ 7ኛ. የኢትዮጵያ ዴ. አንድነት ንቅናቄ፤ 8ኛ. አነድነት ዩዲጄ ናቸው። በነገራችን ላይ ከ 1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር ያሉት መድረክ የሚባለው እስከሚፈጠር ድረስ ይታወቁ የነበረው በህብረትነት ነበር። ለምን፤ እንዴት፤ ከመቼ ጀምሮ እንደተበታተኑ የተሰጠ መግለጫ እንዳለ መረጃ የለኝም። ሆኖም የመድረኩን አባላት ቁጥር ከ 6 ወደ 8 ከፍ አድርጎታል። ይሁን። እነዚህን ድረጅቶች ቢያንስ በሁለት ታላላቅ ምድብ ባስቀምጣቸው፤ የጎሳ ድርጅቶች በአንድ ወገን፤ የህብረ-ጎሳ ድረጅቶች በሌላው ወገን ነው የሚሆኑት። ብሎም እነዚህ በሁለት የከፈልኳቸው ቡድኖች ስማቸው እንደሚያመለክተው በመጀመሪያው ምድብ ያሉት የተወሰኑ የህብረተ-ሰብ ከፍሎችን ጥቅም በማስቀደም የጋራ ጥቅሙን በሁለተኛ ደረጃ የማየት አዝማሚያ ሲኖራቸው፤ በሁለተኛው ምድብ ያለው ደግሞ ተቃረኒውን የሚያይ ነው። ከማለት በተሻለ ማስቀመጥ ነገር ማንዛዛት ነው። ይህ ሲባል ግን በሁለቱም መደብ ውስጥም ቢሆን በየራሳቸው ጥቃቅን ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም። መሰረታዊነቱ ግን ይሄን ያሀል አይደለም።

 

ስለሆንም የአንድ መለስተኛ ፐሮግራም ተግባር በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች ፐሮገራም መካከል ያለውን ልዩነት አጥብቦ፤ ይህም ማለት የየድረጅተሎቹን የየግል ፐሮግራሞ እሰከወዲያኛው ከአገልግሎት ውጭ ሳያደርግ፤ በሁሉም ወገን፤ ለሁሉም ወገን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ብቻ ለይቶ በማስቀመጥ በአንድ በተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደሚቀጥለው ከፍተኛ ፐሮግራም ማሸጋገር ነው። ይህ ሁኔታ የተለያዩ ልምዶችና አስራሮች የሳዩት የመለስተኛ ፐሮግራም ተግባር ነው።

 

መለስተኛ ፐሮግራም ለምን አስፈለገ? ለሚለውም ጥያቄ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የስርዓት ለውጥ መደረግ አለበት የሚል አጠቀላይ ግንዛቤ ስላለና፤ ይህንን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ደግሞ የግድ ዛሬ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ሊወገድ የሚፈለገፈውን ስርዓት የሚዘውረውን ሓይል ማስወገድ ስለሚያስፈልግና ይህ ተግባር ደግሞ፤ ሊከናወን የሚችለው በተባበረ ሃይል በሚደረግ ትገል ካልሆነ በስተቀር ሌላ አማራጭ አለመኖሩ በመረጋገጡ ነው። የዚህ ዓይነቱ የህብረት ትግል ጥያቄ ግንባር ቀደም አራማጁ ደግሞ ከማንም በላይ ህዝብ እራሱ ሆኖ መገኘቱ ድርጅቶችን እንዲተባበሩ አድርጓቸዋል፤ ለተባበረው ትግልም የጋራ መለስተኛ ፕሮግራምን አስፈላጊ አድርጎታል ብለን እንደምድምና ታድያ የመድረክ መለስተኛ ፐሮገራም ከዚህ በላይ ባስቀመጥኳቸው የመለስተኛ ፕሮግራም ተግባርና አስፈላጊነት አቅጣጫ የተቃኘ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሴን ይዤ በሚቀጥለው ጊዜ ልመለስ የዚያው ሰው ይበለን።


አሸብር ከጀርመን

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ