ብርቱካን “ቁርጣችንን ንገሪን” - ግልጽ ደብዳቤ ለብርቱካን ሚደቅሳ
አጋፋሪ ተክሌ (ኦታዋ - ካናዳ)
1- ፖለቲከኛ የህዝብ ነው፦ ብርቱካን ፖለቲከኛ ነች። ወይም ነበረች። ስለዚህ ብርቱካን የህዝብ ነች። ብርቱካንን ጠምጃታለሁ። ምክንያቱም፡ በትንሹ፡ በአስራምናምን አመት የተገነባን ዝናና ሰብእና እንዲህ በዋዛ እንድናጣው አልፈቀድኩም። ይሄንን የግል ደብዳቤ አርቅቄ እንዴት እንደማደርሳት ግራ ቢገባኝ፡ የለም ፖለቲከኛ ምን የግል ነገር አለው ብዬ በድረገጾች ልሰቅለው ወደድኩ።
2- ብርቱካንና ተስፋ፡ ብርቱካንና ቃሏ፦ ብርቱካን በተፈታች በወሯ፡ ኪሩቤል ታደሰ የተባለ የካፒታል ኢትዮጵያ ጸሀፊ፡ ስለብርቱካን ቀጣይ የፖለቲካ ሕይወት የሚንሸራሸሩትን ሀሳቦች መሰረት አድርጎ የሚማርክ ነገር ጻፈ። “ብርቱካን፡” ደቡብ አፍሪካዊው መጋቢ፡ ዴዝመንድ ቱቱ እንዳሉት ከተስፋ ነዳይነት ይልቅ፡ “የተስፋ እስረኛ ሆኖ መቅረት ይሻልል።” ስለዚህ፡ እንኩዋንስ ሁለት አመት፡ በእስር 27 አመታት ብትቆዪም፡ ብርቱካንና ተስፋ መፋታት የለባቸውም አለ። ቀጠለናም፡ “እስር በህሊናና በአካል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ማወቅ የሚችሉት በእስር ቤት ያለፉ ብቻ ናቸው።” ይሁን እንጂ፡ “ብርቱካን ቀድሞውንም በእስር ለሚደርስባት ነገር ካልተዘጋጀችበት፡ ደጋፊዎቿ (እኛን ማለቱ ነው) ስለብርቱካን ይሉ የነበሩት ሁሉ ሀሰት ነበር ማለት ነው” አለ። እኔ ተክሌ ደግሞ እጨምራለሁ፡ ብርቱካን በዚያው ከጠፋች፡ ስለራሷ ያለችን፡ “የህግ የበላይነት የምታሰርለት የምሞትለት ነገር ነው፡” ብላ የነገረችን ሁሉ፡ ውሀ በላው ማለት ነው።
3- ግልጽ ደብዳቤ ወይስ የግል ደብዳቤ? ለተከበርሽው ውድ እህቴ፡ ብርቱካን ሚደቅሳ ደሜ፡ እንደምን ሰንብተሻል? እኔ ከዚህ በፊት የጻፍኳቸው አሁንም የምጽፈው ሀሳብ ጤንነቴን ካላጠራጠfረሽ በስተቀር፡ እጅጉን ደህና ነኝ። ከዚህ በድሎት ከምሰቃይበት አገር ሆኜ፡ ይሄንን “ቁርጣችንን ትንገረን፤ ስለብርቱካን የማወቅ መብት አለን” የሚል ጽሁፍ አዘጋጅቼ ከመለጠፌ በፊት ዘወትር እንደማደርገው፡ ያይልኝና አስተያየት ይለግሰኝ ዘንድ ለወዳጄ ላኩለት። እሱም፡ አብዛኛውን ጊዜ ሀሳቦቼን ከመጋፋት ይልቅ፡ የቋንቋ ግድፈት በማረም ላይ ቢያተኩርም፡ አንዳንዴ እንደሚያደርገው፡ “የለም ይሄንን ጽሁፍ አታውጣ። የምትፈልገው መፍትሄ መጠቆም ከሆነና እሷ ርምጃ እንድትወስድ ለመምከር ከሆነ፡ ይሄንን ለራሷ እንዲደርሳት አድርግ እንጂ፡ አደባባይ አውጥቶ መለጠፍ እሷን ከማሳጣት ውጪ ምንም አዎንታዊ ፋይዳ የለውም” አለኝ። እነሆ ሀሳቡን ሰማሁትና አደባባይ ከመለጠፍ ይልቅ ለራስሽ ልልክልሽ ሞከርኩ። ነገር ግን ይድረስሽ አይድረስሽ ስላላወቅኩና ቀኑም እየገፋ ስለሄደ፡ እነሆ ባደባባይ ደግሞ መጣሁ።
4- አንቺ የኛ ነሽ፦ ብርቱካን ሆይ፡ ይሄንን ጽሁፍ የምጽፍልሽ፡ አንቺ የራስሽ ወይንም የቤተሰቦችሽ ብቻ ሳትሆኚ የኔም የኛም ነሽ ከሚል ግምት ተነስቼ ነው። ልክ እኔ የኔ ብቻ እንደሆንኩት፡ አንቺም የራስሽና የልጅሽ ብቻ ብትሆኜ፡ በግለሰቦች ሕይወት ስለማያገባኝ ምንም አላደርቅሽም ነበር። አንቺ ግን አውቀሽም ይሁን ሳታውቂው የሕዝብ ስለሆንሽና፡ ሕዝብ ደግሞ በመሪዎቹ ላይ ስልጣንና መብት አለው ብየ ስለማምን፡ እነሆ ከሕዝብ እንዳንዱ ሆኜ፡ ይሄንን ልጽፍ ፈቀድኩ።
5- ትንሽ ፍልስፍና፦ ሁልግዜም ቢሆን በህይወት ውስጥ፡ የምንመኘውን ነገር ሁሉ ማግኘት አንችልም። ለኔ የሰውን ልጅ የሚያኖረው የሚመኘውን ነገር ማግኘት አለመቻሉ ነው። ሰው የሚመኘውን ቢያገኝም እንኩዋን ሌላ የሚመኘው ነገር ስለሚፈጠር፡ የሰው ልጅ እየተመኘ እድሜዉን ይገፋዋል ባይ ነኝ። ከብርቱካን ጋር በተያያዘ፡ የኔ ምኞት፡ ባትፈታ እንደነበር ከዚህ ቀደም ጽፌያለሁ። ከተፈታችም ደግሞ፡ ምኞቴ የታሰሩትን የማስፈታቷን፡ የሞቱትንም የማስነሳቷን፡ ትግላችንን ወደፊት የማስኬድ ተጋድሎዋን እንድትቀጥልና የነጻነት ሀሳባችንን ከግብ እንድታደርስ ነው። አንዴ የነበር ጭራ ይዛለችና ወደፊት ብትገሰግስ ነው ምኞቴ። ምኞቴ፡ ፖለቲካ ውስጥ ቆይታ ይሄንን መላ የጠፋው ያገር ፖለቲካ አጥርታ፡ በጥርጥርና በጭንቀት እንዲሁም በአመራር እጦት ውስጥ ያለውን ሕዝብ ይዛ ወደፊት ትመራናለች ነው። ያም ባይሆን ደግሞ፡ ድምጿን ሳታጠፋ፡ በጊዜ ቁርጣችንን አሳውቃን ሌላ ብርቱካን እየፈለግን ወደፊት እንጓዛለን ነበር።
6- የሰቀቀን ኑሮ፦ ይሁን እንጂ፡ ከተፈታሽ ሶስት ወር ቢያልፍሽም፡ በተፋታሽ በመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ከሰጠሽው ቀጣይ ፖለቲካዊ አስተዋጽኦዬን አስቤ እንድመለስና ከቤተሰቦቼ ጋር ትንሽ ግዜ እንዳሳልፍ ትንሽ ጊዜ እወስዳለሁ ከሚለው መግለጫ ውጪ[1] ስለቀጣይ ፖለቲካዊ ሕይወትሽ እስካሁን ካንቺ፡ ከብርቱካን የሰማነው ይፋዊ መግለጫ የለም። ቀጣይ የፖለቲካ ሁኔታሽን የሚያስመረምር ምን አዲስ ነገር ተገኘ? ይሄንን ያህል ጊዜስ ያስፈልግ ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፡ ቢያንስ ከዚህ በኋላ ግን ብዙ በሰቀቀንና በልብ መንጠልጠል መጎሳቆል የለብንም ብዬ ይሄን ብርቱካን ለምን ቁርጣችንን ልትነግረን እንደሚገባ የሚያትት ጽሁፍ ጻፍኩልሽ።
7- ልክ እንደ ሳንሱ ቺ፡ ልክ እንደማንዴላ፦ እንዳጋጣሚ ሆኖ፡ ይሄንን ጽሁፍ በማጠናቅርበት ሰሞን፡ የበርማዋ ታጋይ፡ ኦንግ ሳን ሲኪም ተፈታች። በተፈታች ማግስት ሰለቀጣይ ፖለቲካዊ ጉዞዋ መግለጫ ሰጠች። ማንዴላም ያደረገው ይሄንኑ ነው። በተፈታ ማግስት ቀጥታ ስራው ያደረገው፡ የጀመረውን ትግል ከግብ ማድረስ ነው። የደቡብ አፍሪካና የበርማ ተሞክሮf ለኛ ይሰራል ማለቴ አይደለም። ማንዴላ የተፈታበት ሂደትና ሁሌታም አንቺ ከተፈታሽበት ሁኔታ ይለያል። ነገር ግን መሪዎች፡ በፍጥነት እርምጃ ካልወሰዱ፡ የአመራር ክፍተት ይፈጠራል። የመሪዎች ደረጃና ተሰሚነትም እየቀነሰ ይመጣል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለው ሁኔታና እንደ አንድነት ያለ ርስ በርሱ የሚናከስ አመራር ባለበት ድርጅት፡ የሞራል የበላይነት ያለው መሪ ካልመጣና አመራር ካልሰጠ፡ ጥርጣሬ ይሰፍናል። አንቺን የመጠበቅ አዝማሚያም ሰፍኖ ስራ መስራት ይቀራል። ስለዚህ ቶሎ አመራር መስጠት አለብሽ። የፖለቲካ ሕይወትሽን ከቀጠልሽ ማለቴ ነው።
8- ተስፈኛዋ ብርቱካንና ተስፋ የቆረጠችው ብርቱካን፦ ከላይ የገለጽኩት ኪሩቤል ታደሰ የተባለ፡ ከጽሁፉ እንደተረዳሁት ላነቺ ለብርቱካን ጥሩ ስሜት ያለውና ለመመጀመሪያው ግዜ በ2007 ላይ ያገኘሽ ጸሀፊ እንዲህ ይላል። ብርቱካንን ባገኘኋት ግዜ፡ በዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እንዲሁም በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነትን ለማግኘትና መሪ መሆን እንደምትችል ተስፋ የፈነጠቀች ነበረች።[2] እንደ ኪሩቤል ምስክርነት፡ እኛም ብርቱካንን በሰሜን አሜሪካ ስትንቀሳቀስ እንደመሰከርነው፡ የብርቱካን የፖለቲካ ህይወት በተስፋ የተሞላ ነበር። የ70 አመት አረጋዊ እናቷን ምክር አሻፈረኝ ብላ ወደ ፖለቲካ ገባች። የአንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ መሪ ሆና ስትመረጥ፡ የመጀመሪያው ስራዋ ምን እንደሆነ ስትጠየቅ፡ “በመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት ትኩረት የምትሰጠው ሚሊዮን የኢህአዴግ ካድሬዎችን የሚቋቋም ድርጅታዊ አቅም መገንባት” እንደሆነ ነበር የተናገረችው። ያ ሳይሆን ቀረና፡ ብርቱካን ለእስር የሷ ጥፋት ባልሆነ ሰንካላ ምክንያት ለእስር በቃች። ግን ከ21 ወራት እስራት በኋላ ተፈታች። ብርቱካን ከእስር ስትወጣ፡ እኔም ምናልባትም ሌሎችም ማየት የፈለግነው የድሮዋን፡ ተስፈኛዋን፡ ጠንካራዋን፡ ልበሙሉዋን፡ ቀጥተኛዋን፡ ብርቱካን ነበር። ነግር ግን የአሁኗ ብርቱካን የድሮው ጥንካሬዋ የከዳት፡ የራሷም የአገሯም ፖለቲካዊ መጻኢ እድል የጨለመ የመሰላት ብርቱካን ሆነችብኝ ይላል ኪሩቤል። እኔም ተጋራሁት።
9- ሲሆን ሲሆን መኖርሽን፡ ያለበለዚያም …፦ ብርቱካን ከተፈታሽ ጀምሮ ስለመጪው ፖለቲካዊ ጉዞሽ ያለሽው ነገር አለመኖሩ፡ ከላይ እንደገለጽኩልሽ ያንቺ ብቻ ጉዳይ አይደለም። ፖለቲከኛነትሽን ክደሽ አደባባይ እስካልወጣሽ ድረስ፡ እኛ የምናምነው የምናውቅሽም በፖለቲካ መሪነትሽ ነውና፡ ያንቺ ጉዳይ የኛ ነው። ስትታሰሪ ብቻ ሳይሆን ስትፈቺም ያንቺ ጉዳይ የኛ ጉዳይ ነው። ከእስር የተፈታችው ብርቱካን፡ ከቃሊቲ እስከ ፈረንሳይ፡ ከአዲስ አበባ እስከ አዋሳ የተናገረችውን የሰማን እነደሆነ፡ በንግግሯ ጠንቃቃና ቁጥብ፡ በተቻለ መጠን ፖለቲካን የምታስወግድ ትመስላለች። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ንግግሯን ወይንም ፈረመች የተባለውን ንግግሯን ነጻ በሆነችበት ሰዓት የተናገረችው አይደለምና ከግምትም አናስገባውም። ልክ እንደኪሩቤል እኔም፡ ከልጅሽ፡ ከእናትሽና ከቤተሰቦችሽ ጋር ጊዜ እንዲኖርሽ መፈለግሽን እቀበለዋለሁ። ግን ቀድሞውንስ ነገር የፖለቲካ አቅጣጫሽን እንደገና መመርመር ለምን አስፈለገ? ይሄ ምርመራስ እስከመቼ ይዘልቃል? እስከዚያውስ እኛ በድፍንፍን ውስጥ መቆየት አለብን? እኔና ጓደኞቼ፡ ብርቱካንን ቀስ በቀስ ከእጃችን ልናጣት ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ያሰቃየናል። ሲሆን ሲሆን “አለሁ ብለሽ መልሺልን። ከሌለሽም ቁርጣችንን እንወቀው።
10- የመላምትና የግምት ቁርጠት ገደለን፦ ብርቱካን ከእስር ስትወጪ፡ ልጅሽ ሀሌ፡ እናትሽና ባጠቃላይ ቤተሰብሽ የመጀመሪያ ቀዳሚ ነገሮች መሆናቸውን ተናግረሻል። በርግጥ አገር ይበልጣል ቤተሰብ የሚል ተራ ክርክር ውስጥ አንገባም። ነገር ግን አገርም ትልቁ ቤተሰብ ነው። ያ ብቻም አይደለም፡ አንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ (አፍዴ) ችግር ውስጥ ነው። መሪዎቹም ርስ በርሳቸው ይበጣበጣሉ። ብርቱካን እንዲህ ያለው የብጥብጥ ድርጅት ውስጥ መልሶ መሄድ ጠቀሜታው ላይታያት ይችላል። ያም ብቻ አይደለም፡ ጭራሹንም ፖለቲካ ሊደብርሽ ይችለል። ለዚህ ሁሉ ስቃይ የዳረገሽ ፖለቲካ መሆኑን ስትገነዘቢ፡ ፖለቲካ ሊሰለችሽ ይችላል። ግን ደግሞ ይሄ ሁሉ ግምት ነው እንጂ፡ በርግጥም ያጠፋሽ ምን እንደሆነ አላወቅንም። ስለዚህ በመላ ምትና በግምት ቁርጠት እንድንሰቃይ ከምትጠይን፡ ቁርጣችንን ንገሪን።
11- አንድ ወቅት እንዲህ ብዬ አሰብኩ፦ “ይህቺ ብርቱካን እኮ በእስር በቆየችበት ወቅት ከእስራት የላቀ፡ ለምሳሌ እዚህ የሚነገርም የማይነገርም ሰቆቃ ፈጽመውባት ሊሆን ይችላል”። የሆነ ሆኖ፡ የደረሰብሽን ነገር እስካልነገርሽንና፡ የደረሰብሽ ነገር የደረሰብሽን ነገር ለኛ መንገር የማያስችል እስከሆነ ድረስ፡ ተደብቅሽ ከቀረሽ፡ ሀያ አንድ ወራት ታስረሽ ስትፈቺ ብዙ ታደርጊልናለሽ ብለን ስንጠብቅሽ፡ በማናውቀው ምክንያት፡ ድክመታችንንና ጉድለታችን እያወቅሽ፡ አውላላ ሜዳ ላይ፡ የመሪ እጦት የአታጋይ ረሀብ፡ የድርጅት በረሀ ላይ ጥለሽን ከፖለቲካ ከሸሸሽ፡ ኪሳራችን አሰቃቂ ነው። የሆነ ሆኖ ይሄ ደብዳቤ፡ እባክሽ ያለፍላጎትሽ፡ ያለእምነትሽም ቢሆን ፖለቲካ ውስጥ ኑሪልን የሚል ሳይሆን፡ “እባክሽ ቁርጣችንን ንገሪን” የሚል ነው። ቢያንስ በጊዜ ውሳኔሽን ማወቅ፡ ኪሳራችንን በግማሽ ይቀንሰዋልና። ግን ለምን?
12- የመፈታትሽ የምስራች፦ ብርቱካን፡ የሕወሀት ኢህአዴግ መገናኛ ብዙሀን በተፈታች እለት እንደገዘገቡት ፖለቲካ አቁማ ወደ ህግ ሙያዋ ብቻ የምትመለስ ከሆነ፡ የመፈታቷ የምስራች ለቤተሰቦቿ ብቻ ነው። መታሰሯም መፈታቷም ለኛ የትግል ወንጌል አይደለም ማለት ነው። የብዙሀን ፓርቲ ስርአት ለሚያስፈልጋት፡ ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግልና በንግግር የህዝቡን አመኔታ ለማግኘት እንዲታገሉ ለሚያስልጋት ኢትዮጵያ፡ ብርቱካን ነጻ ነግር ግን እንደ አማራጭ የማታገለግል ሴት ሆነች ማለት ነው። ከምንም በላይ የማረከኝና ከዚህ ደብዳቤ አንቺም አንባቢዎችም እንድትወስዱልኝ የምፈልገው ነገር የሚቀጥለው እኔም የምስማማበት የኪሩቤል ታደሰ አባባል ነው።
13- የወላጅን የቤት ስራ ለልጅ፦ብርቱካን ልጇ ሃሌ ሚደቅሳን ለማሳደግ ስትል ፖለቲካ ካቆመች፡ ብርቱካን ከነዚያ ልጆቻቸውን ከሚወዱና ከሚጠነቀቁላቸው፡ ነገር ግን ልጆቻቸውን ከሚጎዱ መጥፎ ወላጆች አንዷ ነች ማለት ነው። ምክንያቱም፡ ዛሬ ብርቱካን ሸሽታ የምትወጣው ትግል፡ ብርቱካን ድሮ ትል እንደነበረው፡ ወደፊት እንደሀሌ ያሉትን ህጻናት ይጠብቃቸዋልና። ለልጆቻችን የቤት ስራ ቆልሎ እንደማስቀመጥ ማለት ነው። ነገሩ ልክ ነው እኮ። ሀይለስላሴ ያስቀመጡት ችግር ደርግ ላይ የተወለድነውን ጠበቀን። ደርግ ላይ የተጠራቀመው ችግር ደግሞ ኢህአዴግ ላይ ተቆልሎ ጠበቀን። ኢህአዴግም ጥሩ እቆለለልን ነው። እኛ ዛሬ ያልፈታነው ችግር ለልጆቻችን ይጠራቀማል እንደማለት ነው። ልክ ነው እኮ። ከአሜሪካን እስከ ቻይና፡ ከሊበን ወረዳ እስከ ራስ ቃሳር ድረስ ብትሄዱ ከአያቶቻችንና ከአባቶቻችን የተጠራቀመ ችግር ነው ዛሬ ፍዳችንን የሚያሳየን። እነሆ ማን ሞኝ አለ ብቻውን የሚሰቃይ እኛም ለልጆቻችን እናካፍላቸዋለና።
14- ስለዚህ ወደ ብርቱካን ስንመለስ፡ ኪሩቤል እንዳለው፡ “ይህቺ ልጇን የምትወድ እናት ትግሉን፡ ማለትም ጭቆናውን ለልጇ አቆየችላት ማለት ነው። ስለዚህ “ትግሉን ራሷ መጨረስ ተስኗት፡ ነጻነትን ሳይሆን ጭቆናና ለልጇ የምታቆይ እናት ልጇን ትወዳለች ማለት ይቸግራል። ማንም እናት ያንን ለልጁ ማውረስ ይፈልጋል ማለት ይቸግራል።” ኪሩቤል ታደሰ ሲደመድም፡ ብርቱካን ልጇን ለማሳደግና ለመንከባከብ ብላ ፖለቲካ ከተወች፡ ጥሩ እናት አትሆንም ይላል።
15- ብርቱካን አንቺ እንደ ታንካችን እንደ ሚሳይላችንም ነበርሽ። ከላይ እንደገለጽኩት፡ እዚያ እስር ቤት ሞራልሽን የሚደግል ነገር አድርገውሽ ይሆናል። ያንን አንቺና መድሀኔዓለም እንዲሁም ሕወሀት/ኢህአዴግ ናችሁ የምታውቁት። ግን ከምናውቀው በላይ ምንም አላደረጓትም ከሚል ግምት ተነስተን ካየነው፡ ባንቺ የደረሰው በሌሎች አለማቀፍ ታጋዮች ከደረሰው የከፋ አይደለም። ለምሳሌ ኔልሰን ማንዴላ ወይንም በቅርቡ የተፈታችውን ኦንግ ሳን ሱቺን ውሰጃቸው። እንደውም ዛሬ ነገ ስል አስር አመት ሳላነብ የገፋሁትን የአቶ ኔልሰን ማንዴላን መጽሀፍ በዚህ ሰሞን አነበብኩት። በደቡብ አፍሪካዊያን ላይ የደረሰውን ትተን፡ በሱ በማንዴላ ብቻ የደረሰበት መከራና ግፍ የትየለሌ ነው። አስራስምንት አመት ሚስቱን እንዳይነካ፡ በመስታወት ብቻ እያያት፡ ለዚያውም በሁለት አመት ባምስት አመት አንዴ ማለት ነው፤ ሙሉ ሱሪ እንዳማረው፡ ጥብስና ቅቅል፡ ጭማቂና ፍራፍሬማ የማይታሰብ ነው። የነማንዴላ ምግባቸው ምግብ አይባልም ነበር። አንድ ቦታ ላይ፡ ማንዴላን ከረባ ምግብ ተለያይቶ ከመቆየቱ የተነሳ፡ አንድ ቀን በዚያ በእስር ቤት ደረጃ ታይቶ የማይታወቅ ምግብ ሲሰጡት፡ ያ ትልቁ ማንዴላ እንደህጻን እያደረገው ስልቅጥ አድርጎ ሲመገብ ታይዋለሽ። ያን ያህል የከፋ ነበር በደላቸው። ወዳጅሽ አብይ ተክለማሪያም ጽሁፍ ላይ የኔልሰን ማንዴላ መጽሀፍ ቤትሽ እንደነበር አንብቤያለሁ። ስለዚህ የማንዴላን መጽሀፍ አልደግምልሽም።
16- ብርቱካን ያለፍትህ መታሰርሽ፡ በራሱ ትልቅ በደል ነው፦ ብርቱካን የምጽፈው እንደ ሰው ነው። እንደመላእክትም ተጽፎ ከትችትና ከንትርክ ማምለጥ አይቻልም። የኛ ፖለቲካ ባንድ በኩል ግልጽነት ይጎድለዋል። የፖለቲከኞቻችንና የታዋቂ ሰዎቻችንን ውሎና ታሪክ መስማትና ማየት እንደራበን፡ በጭምጭምታና በአሉ ብቻ፡ አንዳንዴም ከራሳችን ሰዎች ሳይሆን ከጠላች እየሰማን እንኖራለን። ስለዚህ የሰማነውንና ያየነውን ያህል ብቻ ነው የተናገርኩት። ስለዚህ ብርቱካን የደረሰባት እጅግ የከፋ አይደለም ስል፡ በደረሰባት ልክ የከፈለችው መስዋእትነትና እኛ ያገኘነው ትርፍ የትየለሌ ነው፤፡ በትንሽ መስዋእትነት፡ ትልቅ ትርፍ አጋበስን ለማለት ነው እንጂ፡ የብርቱካንን መስዋእትነት ለመቀነስ አይደለም። ይብዛም ይነስም አንቺ የበኩልሽን ተወጥተሻል።
17- ብርቱካን የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መዋእለ ነዋያችንን ያፈሰስንብሽ ሴት ነሽ፦ ብርቱካን ኢ”ንቨስትመንታችን” ነች። ትርፍ እንፈልጋለን። ባናተርፍም እነኳን፡ ኪሳራችንን መቀነስ እንፈልጋለን። ኪሳራችንን የምንቀንሰው ደግሞ በማወቅ ነው። ማወቅ እንድንዘጋጅ ይረዳናል። ብርቱካን ላይ ኢንተረስት አለን። ስለዚህ ውሳኔዋን የማወቅ መብት አለን። አንደኛውን ተስፋ ቆርጠን ሌላ አማራጭ እንድናዘጋጅ ይረዳናል። ድርጅቷ አንድነትና መድረክም፡ ቁርጣቸውን አውቀው ሌላ ሰው እንዲፈልጉ ወይንም ቦታቸውን በጽናት ይዘው እንዲታገሉ ይረዳል። በአመራር ላይ ክፍተት አይፈጠርም። ከዛሬ ነገ ትመጣለች ተብሎ የሚባክን ጊዜ አይኖርም። ምንም ይሁን ምንም ብርቱካን በእስር በመቆየቷ፡ ሌሎችን ሊያስከትል የሚችል የሞራል የበላይነት ገንብታለች። እሷን አክብረው እንኩዋን ባይሆን አገር ምን ይለናል ብለው እንዲከተሏት የሆነች መሪ ሆናለች። ስለዚህ እነዚህ መሪዎች ቁርጣቸውን አውቀው ስራቸውን እንዲሰሩ፡ ያንቺን የብርቱካንን ውሳኔ ማወቅ አለባቸው። ያለበለዚያ ክፍተትና መጠባበቅ ይፈጠራል።
18- ሊያጡሽ የማትገቢ ፖለቲከኛ፦ ብርቱካን፡ መቼም በሁለት አመት እስራትሽ በተሰሩት ድልድዮችና ህንጻዎች ተማርከሽ የለም ኢህአዴግ መልካም መንግስት ነው ልትይ የምትችይ ሴት አይደለሽም። የጀመረሽውን ኢትዮጵያን በህግ የበላይነት ባህር ላይ የማንሳፈፍ ተልእኮ እንዳላገባደድሽም የታወቀ ነው። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ክንፍ አውጥቶ ሊበር ሲል፡ የዛሬ አምስት አመት ክነፉን ተመታ። ተከሰከሰ። ክቡሩ ሰው በገፍ ተገደለ። ክቡሩ ሰው፡ አንቺን ጨምሮ ታሰረ። እነሁ ለሞቱት የገዳያቸው፡ ለታሰሩትም የእስራታቸው ፍትህ ገና አልተገለገለም። አንቺ ደግሞ፡ ያ “ቤታችን በሰማይ ነው” የሚለው መጋቢ ነገሩን ሁሉ በጌታ እንድትጥይው የሚያሳምንሽ አይነት ሰው አይደለሽም። ስለዚህ ምን ይሆን ሀሳቧ ብለን እንዳንሰቃይና አንደኛውን አንዴ እንዲወጣልን፡ ቁርጣችንን በጊዜ ብታሳውቂን መልካም ነው። ብርቱካን ሊያጡሽ የማትገቢ ታላቅ ፖለቲከኛና ታጋይ ነሽ። በተለይ ያሳለፍሽው የእስር ህይወት፡ ሴትነትሽ፤ ወጣትነትሽ፡ እንዲሁም የህግ ባለሙያነትሽ፡ ውድ እንድትሆኚ ያደርግሻል። ያንቺን አይነት ሰው ለመተካት አይቻልም ባልልም፤ ያንቺን አይነት ሰው ለማግኘት፡ እንደገና ብዙ አመት ብዙ መስዋእትነት ሊከፈል ነው። ጊዜና እድልም ያስፈልጋል። እድል ደግሞ ሁሌ በተመሳሳይ መልኩ አይደገምም። ስለዚህ ወደፖለቲካ ቶሎ ተመለሺልን። ካልተመለስሽም ቁርጣችንን ንገሪን።
19- ድምጽሽን እንስማ፦ ብርቱካን፡ ይሄንን ደብዳበ እየጻፍኩልሽ ሳለ፡ የበርማዋ ታጋይ ኦንግ ሳን ሱቺ በካናዳ ሬድዮ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉላት ሰማሁ። በንግግሯ ላይ ሁሉ እሷም እንዳንቺ ጠንቃቃ ነበረች። ስለዚህም ከተናገረቸው ሁሉ የማረከኝ፡ በግርድፉ፡ ቀጣይ እርምጃዬን “ህዝብ ምን ይለኛል” የሚለው ስሜት ሊቆጣጠረው አይገባም ያለችው ነው። አንቺም በምትወስኚው ውሳኔ የኛ ፍላጎት እስረኛ መሆን የለብሽም። ግን ደግሞ እኛም ያንቺ ቀጣይ ውሳኔ ታጋቾች መሆን የለብንም። የማወቅ መብት አለን። መብት ብቻ አይደለም፡ የፖለቲካች ደዌያችን ለማከም ያንቺም ምትሀታዊ እጅ ያስፈልገናል። ድምጽሽን ተራብን። ስለዚህም ስለቀጣይ የፖለቲካ እርምጃሽ ቁርጣችንን ንገሪን። ሶስት ወር ለኢትዮጵያ ብዙ ነው።
[1] http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-11712802
[2] http://capitalethiopia.com/index.php?option=com_content&view=article&id=13595:birtukan-midekssa-a-prisoner-of-hope&catid=6:society&Itemid=17



