PM Meles Zenawiአምባገነን የአፍሪቃ መሪዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

ስሜነህ ታምራት በቀለ

አፍሪቃ በዕድገት ሂደቷ የፈጠረቻቸው መልካም አስተዳዳሪና ምግባረ ሰናይ ሰብዕናን የተላበሱ በጣም ጥቂት መሪዎች አሏት። በአንፃሩም በስም ካልሆነ በቀር በተግባር ከጥንታዊያን አፄዎችና ፋሽስቶች የማይለዩ በርካታ መሪዎቿ አጠቃላይ ዕድገቷን ለጉመው ይዘውታል።

 

 

እነኝህኞቹ መሪዎች መልካም ሥራንና ንፁኅ ሰብዕናን ከጥቂቶቹ መማር ባለመቻላቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን መገመት አይከብድም። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ከአፍሪቃውያን ታሪክ ሊማሩ ያልቻሉ አምባገነን መሪዎች የመጨረሻ መውደቂያቸውን መተንበይ አይደለም። እንዳውም አፍሪቃን ወካይ የሆኑ መሪዎችን የመልካም አስተዳደር ምሣሌነት በማሳየት ዛሬ የህዝብን ጥያቄ መመለስ ወይም ሥልጣንን በሠላም መልቀቅ አፍሪቃውያን ይዘውት የተነሱ ወቅታዊ አማራጭ መሆኑን አበክሮ ለማሣየት እንጂ።

 

አፍሪቃችን ተዝቆ የማያልቅ የማዕድን ክምችት አላት። የተፈጥሮ ዕፅዋት፣ እንስሳትና የውሃ ሀብቷ ለጤና ተስማሚ ከሆነው የአየር ንብረት ጋር ሚሊዮን ቱሪስቶችንና የታሪክ ጠበብቶችን ይጋብዛል። የሰው ኃይልና አመቺ የገበያ ማዕከልነቷም የውጭዎችን ዓይን ይስባል። ሆኖም ግን አፍሪቃ በብዙ ነገሮች እንደመታደሏ በፈጣን የዕድገት ጎዳና እንዳልተራመደች ብዙዎቹ ይስማማሉ። መጀመሪያ ላይ ቅኝ ገዥዎች የተከሏቸው ሀገር በቀል አሻንጉሊት መሪዎች፣ በመቀጠልም ሥልጣንን በመፈንቅለ መንግሥትና በነፃ አውጭነት ስም የተቆናጠጡ መሪዎቿ ለዕድገቷ መጓተት የየራሳቸውን አፍራሽ ተፅዕኖ አሳድረዋል። በመሆኑም የትናንትናዋ ጨለማ አህጉር (The dark continent) ዛሬም ድረስ የመልካም አስተዳደር ብርሃን አልበራላትም። ጨለማውም አልተገፈፈላትም።

 

ይህንን ሁኔታ አጠንክሮ ያጤነ አንድ ዕውቅ አፍሪቃዊ ደራሲ ”የአፍሪቃ ቆንጆዎች ገና አልተወለዱም” በማለት ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ተቆርቋሪ መሪዎቿ ገና እንዳልተፈጠሩ ጽፏል። አዎ! አህጉሯ ባህር አቋርጠው፣ ድንበር ተሻግረው ከመጡ የባዕዳን ወራሪ የቅኝ ገዥዎች ብትላቀቅም መሠረታዊ የሆኑት ችግሮቿ ግን አብረው ሊወገዱ አልቻሉም። አህጉሪቷ በአፄዎችና ንጉሦች፣ በወታደራዊ አምባገነን አስተዳደሮች እንዲሁም በስመ-ዲሞክራት መሪዎች ስትረገጥና በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ብዙ ዓመታትን አስቆጥራለች። ከዚህ ጠባሳ ታሪኳ ጎን ለጎን ሁኔታዎችን አርቀው በማየትና ከጊዜያዊ ሥልጣን ይልቅ ዘለዓለማዊ የህዝብና የሀገር ፍቅርን መርጠው ሥልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁ መሪዎችም ብቅ ብቅ ብለዋል። በብቸኛው ቆራጭ ፈላጭ አኀዳዊ ፓርቲ ምትክ የብዙኀን ፓርቲ ጠቃሚነትን ተቀብለውና የህዝበ ድምፅ ሽንፈትን በፀጋ ተቀብለው በሠላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር ያደረጉም አሉ። በዚህ ረገድ የታንዛኒያውን ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የዛምቢያውን ኬነት ካውንዳ፣ የጋናውን ጄሪ ሮሊነግስ በምሣሌነት መጥቀስ ቢቻልም የዕውቁ ታጋይ የኒልሰን ማንዴላ አርኣያነት ግን በሁለት ታላላቅ ምክንያቶች ከሁሉም የላቀ አስተምህሮ አለው።

 

1ኛ) ኒልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት የስቃይ እስር በኋላ በነፃ ተለቀው የሀገራቸው የመጀመሪያው ጥቁር መሪ በሆኑበት ጊዜ ሀገሪቱን በአፓርታይድ ሥርዓት በፕሬዝዳንትነት ይመሩ የነበሩትን ፍሬድሪክ ዴክላርክን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ሾመዋል። በዚህ አድራጎታቸው የዘርና የቀለም ጥላቻን በአብሮነትና በፍቅር ለሀገር በጋራ በመሥራት ድል ማድረግ እንደሚቻል በተጨባጭ አስተምረዋል።

2ኛ) በደቡብ አፍሪቃ የነፃነት ትግል ውስጥ ከእርሳቸው የላቀ ከፍተኛ መስዋዕትነትን የከፈለ የለም። ይህንን መላው የዓለም ህዝብ እና መናገር ባይፈልጉም ራሳቸውም ያውቁታል። ሆኖም ግን ትናንትናም ሆነ ዛሬ ብዙዎች እንደሚያስቡት እስከ ዕድሜልካቸው መሪ ሆነው መቆየትን አልመረጡም። እናም ሥልጣንን በራሳቸው ፈቃድ በመልቀቅ ዳግም ታላቅ ምሣሌነታቸውን አስመሰከሩ።

 

በዚህ ታላቅ ርምጃቸው ኒልሰን ማንዴላ የነፃነት አርበኛ ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲ አስተማሪነታቸውንም አሳይተዋል። የዓለም ሠላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ክቡር ኒልሰን ማንዴላ ዛሬ በመላው ዓለም እንደታላቅ መሪ በክብር ቦታ፣ እንደተራ ሰው በየትኛውም ስፍራ ያለጠባቂና አጃቢ በነፃነት መንቀሳቀስ የመቻል ምክንያቱ ይኸው የሥልጣን ቁራኛና የሥልጣን ሱሰኛ ያለመሆናቸው ፋይዳ ነው። ያለምንም ማጋነን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያለጠባቂ ከቤተሰባቸው ጋር የትም ቦታ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የታደሉት ብቸኛው አፍሪቃዊ መሪ ክቡር ኒልሰን ማንዴላ ብቻ ናቸው። በየትም ስፍራ በነፃነት የመንቀሳቀስ ምክንያቱ ለነፃነት መታገልና መታሰራቸው ሳይሆን፤ በሥልጣን ዘመናቸው ከሙስና የፀዳ ሰብዕና መላበሳቸውም ነው።

 

PM Meles Zenawiለነፃነት መታገል ብቻውን ነፃነትን የሚሰጥ በሆንማ የዚምባቡዌው ሙጋቤ፣ የሊቢያው ጋዳፊ፣ የኤርትራው ኢሣያስ፣ የኢትዮጵያው መለስ፣ የኡጋንዳው ሙሴቪኒ፣ ... በነፃነት ትግል አልፈው የመጡ ነበሩ። ነገር ግን ከላይ ከጠቀስኳቸው መሪዎች አንዳቸውም ቢሆን የትኛውም ቦታ ያለ ቀጥተኛ አጃቢና ያለ ስውር ጠባቂ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ አይንቀሳቀሱም። እንግዲህ መማር የማይችሉት መሪዎች ነፃነት የሚሉት ይህን አይነት አኗኗር ይሆን? ክቡር ኒልሰን ማንዴላ መንግሥት ለጡረታ ከሚሰጣቸው ገቢ ሌላ የገቢ ምንጭ የላቸውም። ምክንያቱም የሀገርና የህዝብ ንብረት አልዘረፉምና። ቢፈልጉማ ወርቅና አልማዝ አምራች ሀገራቸው በግላቸው በዓለም ታዋቂ ቱጃር ለመሆን ባስቻለቻቸው ነበር።

 

በአንፃሩም ሥልጣንን መልቀቅ አለርጂክ የሆነባቸው፣ በሙስና መዘፈቅ የተዋሃዳቸው፣ የንፁኀንን ደም ማፍሰስ የተጠናወታቸው እንዲሁም የደም ስሮቻቸውና ህዋሳቶቻቸው የታጠቀ ጦር ብቻ የሆነባቸው አምባገነኖች ትምክህትና ትዕቢት ዓይናቸውን ስለጨፈነው አርኣያነት ካላቸው የአፍሪቃ መሪዎች መልካም ተግባርን ሊማሩ አልቻሉም። እናም የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ግልፅ ነው። በቅደም ተከተል ለማሳየት ግን መጀመሪያ ይወገዛሉ። በዚህም ውርደትን ይከናነባሉ። አማራጭ ሲጠፋም ከሀገር ይሰደዳሉ። በመጨረሻም ለፈፀሟቸው ብሔራዊ ጥፋቶች ተጠያቂ ይሆናሉ። ለዚህ ነው ርዕሱ ”ውግዘት፣ ውርደት፣ ስደትና ተጠያቂነት፤ ቀጣዩ የምባገነን መሪዎች ዕጣ ፈንታ” ነው የሚለው።

 

ጥቂት የማይባሉ መሪዎች ጥቁር አሜሪካዊው የነፃነት ተሟጋች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ከብዙ ዓመታት በፊት ስለጥቁሮች ነፃነትና እኩልነት የተናገሩትን ሲጠቅሱ ይሰማሉ። የርሳቸውን ወርቃማ ህልም (ራዕይ) በምድረ አፍሪቃ ከተገበሩት ከታላቁ ሰው ከኒልሰን ማንዴላ ግን ተግባራዊነትን አልተማሩም። ”አባቱን አያውቅ አያቱን ይናፍቃል” የሚባለው እዚህ ላይ ነው። ጥቅሳቸውና ራዕያቸው እንደማርቲን ሉተር እንዲያም ሲል የሰው ፍቅራቸው እንደ ጌታ ኢየሱስና ነቢዩ መሐመድ መሆኑን ቢደሰኩሩልንም ከባዶ ቃሉ የዘለለ ተግባር ግን የላቸውም። ለምን ቢባል አምባገነን ሆኖ የሰው ፍቅር ያለው በምድር ላይ አልታየምና። አንዳንድ ዘረኛ መሪዎችማ ልጆቻቸውንና ጎሣዎቻቸውን ዘለዓለማዊ ገዥና መሪ ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ቀመር እየቀመሩ ይገኛሉ። ስለአፍሪቃ የአየር መበከል ሊቀሊቃውንት ሆነው ሊነግሩን የሚፈልጉና ስለሠለጠነ ፖለቲካ እየለፈለፉ ሥልጣን ግን በገዥዎች የዘር ቧንቧ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው ዘመን እየተላለፈ እንዲቀጥል ዘረኛ ተግባራቸውን እየዘሩና እያስፋፉ ይገኛሉ።

 

ከብዙ አልፎ ሁሉም ለማለት በሚያስችል መጠን የአፍሪቃ መሪዎች የኒልሰን ማንዴላን የእስርና የስቃይ ታሪክ ያስተጋባሉ። በየሀገራቸው በየጊዜው የሚገነቡትንና የሚያስፋፉትን የእስርና የማሰቃያ ቦታ ለመዝጋት ወይም ለመቀነስ ግን የሞራል ጥንካሬ የላቸውም።

 

አሁንም ጥቂት የማይባሉት መሪዎች ለሀገርና ለህዝብ ንብረት ተቆርቋሪ ለመምሰል የሙስና ተከላካይ ኮሚሽን አቋቁመናል ይሉናል። የዜጎችን አንጡራ ሀብት አሟጠው በውጭ ሀገር ባንኮች ከማከማቸትና በውጭ የመኖሪያ ቤቶችን ከመግዛት ግን አልተቆጠቡም። በአንድ በኩል ዕድሜ ልክ ሥልጣን እየተመኙ በሌላ በኩል በውጭ የመኖሪያ ቤት መግዛት እንቆቅልሹ አይገባንም። መቼ ነው የሚኖሩበት? ለሚለው ጥያቄም መልስ የላቸውም። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉና የሚሊዮኖች የዕለት ምግብ በውጭ ዕርዳታ ላይ ያለው ሳይቀር በረሃብተኛው የስቃይ ምስል የሚለምኑትንና የሚያጋብሱትን እጅግ መጠነ ሠፊ መዋዕለ ንዋይ መልሰው ወደ አውሮፓና አሜሪካ በማከማቸት ኢ-ሰብዓዊና ኢ-ሞራላዊ ታሪካቸውን መልሰው ይደግሙታል።

 

ዛሬ በሰሜን አፍሪቃና በመካከለኛው ምስራቅ ከዳር እስከዳር እያስተጋባ ያለ አንድ ከፍተኛ ህዝባዊ ጥያቄ አለ። ይህም የዘመናት የህዝብ ብሶት ተሸክሞት የኖረው የአፈና እና የጭቆና ቀንበር ከላያችን ላይ ይውረድ፤ ግፍ በቃን ይላል። ነገድና ጎሣ፣ ዘርና ኃይማኖት፣ ዕድሜና ፆታ ሳይለያዩት፣ የአምባገነኖች የድለላ ሸፍጥና የያዙኝ ልቀቁኝ ድንፋታ ሳይበግረው ሁሉም አደባባይ ወጥቶ ብሶቱን አሰማ። ሥልጣን ልቀቁ፣ ከሀገር ውጡ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት፣ ... ወዘተ እያለ ትዕግስቱ ተሟጦ ማለቁን በቁጣ ገልጿል።

 

ህዝባዊ ማዕበሉ የሚፈጥረውን ቅራኔ መፍታትና ሥልጣንን ለቀውም በሀገራቸው በሠላም መቀመጥ እንደማይችሉ የተረዱት የቱኒዚያና የግብፅ መሪዎች በውግዘትና በውርደት ሀገር ለቀው ኮብልለዋል። ዛሬ የአፍሪቃ መሪ የተባለ ሁሉ መውጫ ቀዳዳውን እያዘጋጀ ነው። እነዚህን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። በአንድ በኩል በሠላም ሥልጣንን ለማስረከብ ወስነው ጊዜውን የሚጠባበቁ ይኖራሉ። በሌላ በኩል የሚሄዱበትን ሀገር ወስኖና አመቻችቶ ህዝባዊ ደወሉን የሚጠባበቁ ይኖራሉ።

 

ገና ከአሁኑ የቱኒዝያው መሪ በስዊዝ ባንክ ያስቀመጡት መጠነ ሠፊ ገንዘብ በግል ሊጠቀሙበት እንደማይችሉና መታገዱን በይፋ በባለሥልጣናቱ ተገልጿል። እንግዲህ መማር የሚችል ይማር። በማናቸውም መልኩ የድኀ ሀገርና የህዝብን ንብረት እንደፈለጉ አከማችቶ በውጭ ተንደላቅቆ መኖር ጊዜው ያለፈበት ሌብነት ሆኗል። አሁን አሁንማ ችግሩ ገንዘቡን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለማረፊያ ሀገር የማግኘቱ ጉዳይም ነው። በዚህ ህዝባዊ ትይንታቸው የቱኒዝያና የግብፅ ህዝቦች፤ ህዝባዊ ኃይልን የጦር መሣሪያ ሊያቆመው እንደማይችል ለተጨቋኝ አፍሪቃውያን አሳይተዋል። ሣይንስና ቴክኖሎጂም የህዝብን ወሳኝነት ለዓለም በማዳረስ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እናም ወቅቱ ለአምባገነኖች ብርሃኑ እያጨለመባቸው፤ ለህዝቦች ደግሞ ጨለማው እየበራላቸው መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል።

 

ይህን አይነት ህዝባዊ ትግል መቀጠል አለመቀጠል የአፍሪቃውያን ጉዳይና የየራሳቸው ብሔራዊ የቤት ሥራ ነው። ትናንት ሀገር ጥለው የተሰደዱትንና ወደፊት ደግሞ የሚሸሹትን ቁጭ ብሎ በመጠበቅ ብቻ የሚገኝ ነፃነት የለም። ያለ ህዝባዊ አንድነትና ያለመስዋዕትነት የሰሜን አፍሪቃ አኩሪ የጀግንነት ሥራ ምስራቅ አፍሪቃ ሊመጣ አይችልም።

 

ከግብፃውያን፣ ቱኒዝያውያን፣ ሊቢያውያን በበለጠ የድኅነት ቀንበር ስር የሚገኙ የምስራቅ አፍሪቃ ህዝቦች አምባገነን መሪዎቻቸው በሠላም ሥልጣን እንዲለቁ ወይም ከሀገር እንዲወጡ የማይጠየቁበት አንድም ምክንያት የለም። ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ሱዳናውያን፣ ኬንያውያን፣ ኡጋንዳውያንና የጅቡቲ ህዝቦች በጠብመንጃ ኃይል ድምፃቸውን ዘርፈው በሙስና ከሚጨማለቁ ትናንሽ ሂትለሮች የመገላገያ ጊዜው ዛሬ ነው። የአንድ ሀገር ህዝብ ሌላውን አነሳሽ ሆኖ የአፍሪቃን ትንሣዔ እያቃረበ ይገኛል። እንግዲህ ለራስ ነፃነት በራስ መነሳት እንጂ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ነፃ ያወጣኛል ብሎ መጠበቅ የቀረ አካሄድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምስራቅ ህዝቦች በመካከላቸው እጅግ በርካታ ልዩነቶችና መናቆሮች አሉ። ጭቆናንና ግፍን ለመቃወም አደባባይ ወጥቶ ለነፃነትና ለህልውና በመታገል ግን አንዱ ሌላውን አልጠበቀም። ልዩነት በአንድነት የሚለውን መፈክርም በተግባር አሳይቷል።

 

ማጠቃለያ

ውሾች ይጮሃሉ ግመሎችም ያልፋሉ፤ ይህ የተለመደ ነው በማለት ዛሬ እየተቀጣጠለ የመጣውን የህዝብ ብሶት በንቀትና በትዕቢት መመልከት አወዳደቅን ያበላሻል። አህጉራዊ እሳቱ መቀጣጠል ጀምሯል። ትናንት የጥቂት ባለሥልጣኖች የዕድሜ ማቆያ የነበረው የጦር ኃይል ዛሬ ፊቱን ወደ ወገኑ እያዞረ ፀጥታ እንዳይደፈርስ በመቆጣጠር ላይ ብቻ ተወስኗል። የጦር መሣሪያ ብቻውን የህዝብ ብሶትን መግታት እንዳልቻለ ከቆየው ታሪካችን ብንረዳም ዛሬ ደግሞ የቱኒዝያና የግብፅ ህዝብ በድጋሚ አሳይቶናል። ህዝባዊ ማዕበሉን ጊዜ ገዝቶና አረሳስቶ ለማኮላሸት የሚደረግ ሽንገላና መማፀን ኋላቀርነታቸው ታይቷል። ማንም አይደለልም፤ ምክንያቱም ህዝቡ በአንድ ቃል ”በቃን!” ብቻ ሳይሆን፤ ”ኧረ! በቃን!” ብሎ ቆርጧልና። እናም ለህዝባዊ ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ መልስ መስጠት አላስፈላጊ መስዋዕትነትን ይከላከላል።

 

በአፍሪቃ በአንድ በኩል ምሳሌነት ያላቸው ዲሞክራት መንግሥታት መታየታቸው በሌላ በኩል በሰሜን አፍሪቃ የህዝብ ቅምጥ ብሶት የወለደው የመሠረታዊ ለውጥ ጥያቄ አህጉሪቷን ወደ አዲስ የለውጥ ዘመን ለማሸጋገር አዲስ ምዕራፍ (new era) ከፍቷል። ያለህዝብ አመኔታ በጠብመንጃና በኃይል በሥልጣን መኖር ጊዜው አልቀበል ያለበት ተግባር ነው። ስለሆነም ህዝብ ያልፈለጋችሁ የአፍሪቃ መሪዎች የመልካም አስተዳደርና የመሪነት ሰብዕና ምሣሌነት ካላቸው አቻዎቻችሁ መማር ወቅቱ ያቀረበላችሁ አማራጭ ነው። ይህን ባታደርጉ መሰሎቻችሁ በግትርነትና በማንአለብኝነት የገጠማቸው ውግዘትና ውርደትን ተቀብሎ በጊዜ መሸሽና አንገትን ደብቆ ተጠያቂነትን መጠባበቅ ይሆናል። የየሀገራችሁን ህዝብና አፍሪቃን በአዲስ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማሸጋገር ኳሱም ሜዳውም ዛሬ በእጃችሁ ነው። ’ነገ’ ግን የእናንተ አይደለችም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ