እንደጠላት ለሚታይ ሕዝብ ድጎማ ለምን?
ይነጋል በላቸው
የፕ/ር እንድርያስ እሸቴን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንትነት መሰናበት ልዩ የሚያደርጉ ሁለት ሰሞነኛ ክስተቶች አሉ። ቀዳሚውና ከዚሁ ግለሰብ ጋር በቀጥታ የሚገናኘው የወያኔ መንግሥት ቅሌትን እንደ ክብርና ሞገስ የሚቆጥር መሆኑን የገለጸበት መንገድ ነው። እንድርያስ እሸቴ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ድራሹን ማጥፋቱ በመለስ ዜናዊ አድናቆትና ከፍተኛ ዋጋ ተሰጥቶት ለማን ደስ ይበለው በሚል ይመስላል ሰውዬው በሚኒስትርነት ማእረግ የጠ/ሚንስትሩ የአቶ መለስ ‹አማካሪ› እንዲሆን ተሹሟል።
እኔን አማካሪ ያድርገኝና እንድርያስ እንኩዋንስ ሌላ ሰው ሊያማክር ይቅርና ራሱን መክሮ ከአንዲት አህያው ጋር ወደሚኖርበት የመኖሪያ ቤቱ መሄድ የማይችል አንቱ የተባለና የመኢጠማን ሊቀመንበርነትን ያለተቀናቃኝ ሊጨብጥ የሚገባው ጣጤ ሰካራም መሆኑን ማንም ያውቃል። ነገሩ ሁሉ ቀልድ ነው። መለስ እንኳንስ እንድርያስን ሊሰማ እግዜሩ በሰው አምሳል ወርዶ ቢመክረውም የሚያዳምጥበት ጆሮ የለውም። ለጥፋት የተሠለፈ ሰው ደግሞ መካሪው የውስጥ ጂኒው እንጂ ሰው ሊሆን አይችልም። ሊጠቅማቸው ወይም አጠገቡ አስቀምጦ ሊቆጣጠራቸው የሚፈልጋቸውን ሰዎች ለይምሰል ‹አማካሪ› እያለ በሀገር ሀብት ይቀልዳል።
እዚህ ላይ እንድርያስ ለምን ያሀል ጊዜ ‹እንደሚያማክር› ፈጣሪ ይወቀው ዋና መልእክቱ ግን ልቡንና አእምሮውን ለወያኔ ሸጦ - ትምህርት ኖረውም አልኖረውም - ሀገርን ያጠፋ ሰው ሁሉ በወቅቱ መንግሥት ‹ትልቅ› ቦታ አለው ለማለት የተፈለገ ይመስላል - ያቺ ዮዲት ጉዲትስ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆና የለም? እንጂ እንደጥፋቱ ከሆነና ትክክለኛና ፍትሃዊ ሥርዓት ቢኖርማ ኖሮ ምንም እንካእን ሰውዬው የተመደበበት የ‹ሥልጣን ቦታ› እዚህ ግባ የሚባል አገልግሎት የማይሰጥበት ከጡረታ ቦታነትም የማይተናነስ ቢሆንም የሚኒስትርነት ሳይሆን ከርቸሌም ሲያንሰው ነበር። ግን ምን ይደረግ? ማንስ ለማን አቤት ይላል?
ሁለተኛውና በኢትዮጵያ ሕዝብ የሬሣ ሳጥን ላይ ምናልባትም የመጨረሻዋን ምሥማር የሚቀረቅበው የትናንት ማታው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ነው። ብዙዎቻችን ራሳችንን ታምመን ነው ያደርን። ጭማሪው ታይቶ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ እስካሁን እንደምንም በመከራ ስንገፋው የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ሕይወታችንን እስከወዲያኛው እስትንፋሱን የሚያጠፋ ይመስለኛል። የጥሎ ማለፉ የኑሮ ትግል ዓይኑን አፍጥጦ መጥቷል። በእስካሁኑ ሁኔታ ወያኔዎችና አጎንባሾቻቸው ናቸው እንደተቀማጠሉ እየኖሩ ያሉት። የተወሰነው ሕዝብ እንደነገሩ እየተንጠራወዘ ይኖር ነበር። ከአሁኑ በኋላ ግን ያስፈራል። በእጅጉም ያሳስባል።
የአንድ ሊትር ቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ አዲስ አበባ ላይ ብር 18.30 ሆኖ እንዴት ሊኖር እንደሚቻል ሲታስብ ይዘገንናል፤ ያስጨንቃልም። ሁሉም ነገር ከነዳጅ ጋር የተያያዘ ነው። ጫካው ተቃጥሎና ተመንጥሮ አልቋል - በእንጨት እንዳንገለገል። እህልም ከሀገር ቤት ነው ወደከተሞች የሚመጣው። የነዳጁ ዋጋ ሲሰቀል የእህሉ ዋጋም ከአሁኑ በበለጠ አብሮ ይሰቀላል። ምን ሊውጠን ነው? ምንስ ይብቃን? የት ሄደን እንኑር? እግዚአብሔርንስ ማን አገተብን? ወያኔ እኛን ሕዝቡን እንደጠላት ስለሚያይ ነዳጅን በመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ ለማድረግ በፍጹም አይፈልግም። እናስ ምን ይበጀን? የ1966ቱና የ1997ቱ የኢትዮጵያ እሳት ወጣትስ የት ገባ? - ምንስ ዋጠው? ሞትስ የት ያለው ይሆን?
የወያኔና የኛ ነገር ‹የበላችው ያስገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል› ዓይነት ከሆነብን ሃያ ዓመታትን አስቆጠርን። ወያኔ በእሳት አኮርባጅ ለመግረፍ እኛ ደግሞ ጀርባችንን አመቻችተን ለመስጠት በግንቦት 20/1983 ውል የተፈራረምን ነው የምንመስል። አሁንስ ሁሉም ነገር አንገሸገሸኝ። ምነው ሸዋ! አንነሳም እንዴ ጎበዝ? ፈረንጆቹ “Death by installment” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው። በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ በሥልትና በዘዴ እንዲሞት የሚደረግን ሕዝብ ወይም አንድን ሟች ፍጡር ለማጣቀስ የሚጠቀሙበት አነጋገር ነው። እኛም የቁጥ ቁጥ ሞት እየሞትን እንደሆነ ይሰማኛል። በአንዴ ለመፍጀት የሚያስቸግርን ሟች ልክ እንደወያኔ ልዩ ሥልትን በመጠቀም መፍጀት ይቻላል። ዓለም እንዳይታዘብና በዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይጠይቅ በርሃብና በችጋር እየቆሉ ሕዝብን ቀስ በቀስ መጨረስ የወያኔ ዘውጋዊ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው - የ21ኛው መ/ክ/ዘመን ልዩ ቴክኒክና ስትራቴጂ። ወይ ወያኔዎች ለካንስ ይህን ያህል ብልጦች ናቸው!
ዛሬ አንድ የሳዑዲ ዐረብያ ዙፋናዊ መንግሥት ተቃዋሚ ግለሰብ በፕረስ ቲቪ ሲናገር ያዳመጥኩት ነገር የኛኑ መሰለኝ። እንዲህ አለ፤ ‹እንዴ! የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን የሚሉት ከማን ጋር ሊደራደሩ ፈልገው ነው? ማንን ሊያሞኙ ነው? የሀገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ አንቀሳቃሽ ዜጎች እኮ አንድም በስደት ነው የሚገኙት፤ አንድም በእሥር ላይ ናቸው፤ አንድም በሀገር ውስጥ እንዳይናገሩ እንዳይጋገሩ አፋቸውና ኅሊናቸው ተቆልፎባቸው በከፍተኛ እመቃና ጭቆኛ ውስጥ ናቸው። ታዲያ ‘እንነጋገራለን፣ እንደራደራለን’ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ከማንስ ጋር?› ... ወይ የነገር መመሳሰል? አሁን እዚህ ላይ ለምን ትዝ አለኝና ጨመርኩት?
ብዙ ልጆች ያሉዋት አንዲት ሴት 200 ብር ይዛ በዚያኛው ሰሞን ገበያ ወጣች። ጤፉን ስትጠይቅ ግማሹን ኩንታል 500 ብር ይሉዋታል። ስንዴ ስትጠይቅ እንደዚያው ውድ ይሆንና የማይቀመስ ይሆንባታል። ዘይት ብትጠይቅ ሊትሩን 36 ብር ይሉዋታል። ከሰል ስትጠይቅ አንድ ፍሬ የማዳበሪያ ከሰል 140 ብር ይሉዋታል። ቡና ብትጠይቅ 3ኛ ደረጃውን 80 ብር በኪሎ ይሉዋታል። ሁሉን ገበያ አዳረሰች። በያዘችው 200 ብር ግን ምንም ነገር መግዛት ሳትችል ትቀራለች። ልብ አድርጉ 200 ብር መያዙዋም እሱዋው ሆና ነው። ቤሣ ቤስቲን የሌለውም አለና። በመጨረሻ ምንም ነገር ሳትገዛ ወደቤትዋ ትመለስና የልጆችዋን በርሀብ ማለቅ በሕይወትዋ ቆማ ከምታይ ኤሌክትሪክ ጨብጣ መሞትን ፈልጋ የተላጠ ገመድ ትይዛለች - ምኞት አይከለከልም መቼም ልትሞት አሰኝቷት። ያኔ ለካንስ የመንደሩ የመብራት ፈረቃ ዕለት ኖሮ በጉጉት የጠበቀችው ሞት እንዳማራት ይቀራል። ስታስበው ተራቸው ስለሆነ መብራት የለም። እሱዋም አለች - ‹ምን ዓይነት ሀገር ነው? መኖር አይቻል፤ መሞት አይቻል›። እውነትዋን ነው፤ ኢትዮጵያዊ መሆን በተለይ በአሁኑ ዘመን ከእርግማኖች ሁሉ የተለየ ትልቅ እርግማን ነው።
ነገስ እንዴት ትሆን? ዕድሜ የሰጠው አድሮ ማየት ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ግን ዕድሜ ለመለስ ዜናዊ የለየላት ሲዖል ሆናለች። እንዲያውም ሲዖል ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም። ቢያንስ እሁድ እሁድ እረፍት አለ ይባላል። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ወያኔ ሕዝብን የማሰቃየት ሥነ ልቦናዊ አባዜው እየቀነሰ ሳይሆን እየታደሰና እየገነነ ስለሚሄድ እንኩዋንስ የአንድ ቀን የአፍታ እረፍትም የለም። እሳት - እሳት - እሳት አሁንም እሳት፤ ሁልጊዜ እሳት፤ ያውም ቆስቋሾቹ ለቅጽበት እንኳን የማያርፉበት የገሃነም እሳት። መጥኔ ለኛ! እግዚአብሔር ሳይቀር ከአጋንንት ጋር ተደርቦ ዓይናችሁን ላፈር ላለን።
ሰሚ ከተገኘ አሁን ያለን ብቸኛ አማራጭ በየአካባቢያችን በጎበዝ አለቃ እየተደራጀንና የወያኔ አገዛዝ ያንገፈገፋቸውን የሠራዊትና የፀጥታ አባላት ከጎናችን እንዲሠለፉ ችግራችን ችግራቸው እንደሆነ በመግለጥ እያግባባን ይህን የወያኔ መንጋ ከነሰንኮፉ መነቃቀል ብቻ ነው። ወያኔዎች ዘመድ ላይሆኑን ከእንግዲህ እነሱን ማባበል ወይም ጊዜ ይለውጣቸው ይሆናል ብለን በከንቱ መጠበቅ የዋህነት ነው። በየክፍለ ሀገራቱ መቆሚያ መቀመጫ ካሳጣናቸው ሳይወዱ በግዳቸው ከጫንቃችን ይወርዳሉ። ማወቅ ያለብን ዋና ነገር ተቃውሟችንን በኅብረት ከጀመርን እነሱ በቁጥር እጅግ ጥቂት በመሆናቸው በፍፁም የማይችሉት ሕዝባዊ ማዕበል እንደሚገጥማቸውና ሊቋቋሙትም እንደማይቻላቸው ነው።
ይነጋል በላቸው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



