ፍፁም ከእስራኤል

ኢትዮጵያ ሀገራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰብ መኖሪያ ቤት መሆንዋ ይታወቃል። ሆኖም ግን እስካሁን ያሳለፍናቸውን ዘመናት ከታሪክ እንደተረዳነው በርካታ ጦርነት ተካሂደውባታል። የተደረጉት ጦርነቶች ጎሣን መሰረት ያደረጉ አልነበሩም፤ የግዛት አድማስን ለማስፋት ወይም ያለተቀናቃኝ ብቸኛው ንጉሥ ለመሆን እንጂ።

 

ለምሳሌ ብንጠቅስ የቅርብ ታሪክን ማየት እንችላለን። በእቴጌ ምንትዋብ እንዲሁም ከርሳቸው ከቀደሙትም በከፍተኛ ደረጃ የኦሮሞዎችን ድጋፍ ይሹ ነበር ይባላል። በጋብቻም ሳይቀር ትብብር እና ትሥሥር እንዲኖር ተደርጎ ነበር። ጂኦግራፊና ጎሣን ማዕከል አላደረገም።

 

በአጼ ቴዎድሮስ ጊዜም በሚስታቸው አባት ላይ ነበር ያመጹት። ባለቤታቸውም እቴጌ ተዋበች አባታቸው በባለቤታቸው ሲጠቁ ድጋፋቸው ከባለቤታቸው ጎን መቆም ነበር። ቴዎድሮስም ለዘመናት በመሣፍንቶች ተከፋፍላ ትገዛ የነበረችውን ኢትዮጵያን አንድ ወጥ የማዕከላዊ መንግሥት ለመመስረት ከነበራቸው አቋም ቀጠሉና ወደመሃል እስከሸዋ ወደሰሜን እስከ ትግራይ ሰፊ የአስተዳደር መዋቅር ዘረጉ።

 

በአጼ ዮሐንስም የቴዎድሮስን አርማ አንግበው ቆሙ እንጂ፤ የራሳቸውን ብሔር ወክለው አልነበረም። የተቀረው የሀገሪቱ ብሔረሰብም እኒሁን መሪው አድርጎ ተቀበለ እንጂ አይወክሉንም አላለም። አጼ ቴዎድሮስ ደብረ ታቦርን እና መቅደላን ማዕከል ቢያደርጉም፤ አጼ ዮሐንስም መቀሌን ማዕከል አደረጉ። ዋናው ቁም ነገሩ ይህ ሳይሆን ኃላፊነቱ ላይ ነበር።

 

አጼ ዮሐንስ ጎንደር በደርቡሾች ተወረረች ቢባል ወደመሃል ሀገር ለመዝመት የነበራቸውን እቅድ በመሰረዝ በመጀመሪያ ጎንደርን ነፃ ለማውጣት ወሰኑ። ከዛም በጎንደር በኩል የመጣውን የግብጾችን ወራሪ በመመለስና ተከትለው እስከመተማ ድረስ በማሳደድ ላይ እንዳሉ ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ ለሀገርና ለወገን በመተማ ጦርነት በክብር ወደቁ።

 

ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ከጥንት የቆየውን ልንክደው የማንችለው ሐቅ ነው። ትግራይና አማራ የሚለው ቋንቋ እንጂ የዘር መለያ አልነበረም።

 

ምሳሌ ልጥቀስ፤ ራስ ወልደ ሥላሴ ቤተሰቦቻቸው ከጎንደር ሲሆን፣ የመቀሌን ከተማ የቆረቆሩት እኒሁ ሰው ናቸው። እቴጌ ጣይቱም ቢሆኑ ከጎንደር ተነስተው ሸዋ ላይ የኢትዮጵያን ዋና ከተማ አዲስ አበባን ሲመሰርቱ ጎንደር ላይ ይሁን አላሉም።

 

የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ግን ምን እንደሚፈልግ በትክክል አይታወቅም። ዓለማችን እጅግ በሥልጣኔ ወደፊት ቀድሞን ከሔደ ቆይቶአል። እኛ ግን ወደኋላ ተመልሰን በመውረድ ላይ እንገኛለን።

 

መጥፎ የሆነ ከፊውዳሉ የተወረሰ ሁኖ፤ ነገር ግን ከዛም በከፋ መልኩ በንቀት ላይ የተመረኮዘ፤ የተማረው ያልተማረውን፣ ከተሜው ገጠሬውን፣ ከዛም አልፎ ወደብሔር ብሔረሰብ፣ … ወዘተ እያለ ይቀጥላል። ይህ ደግሞ የትም አያደርስም። አንዱ ሌላውን ከነልዩነቱ በመከባበር ካልኖረ አንድነታችን ጠንክሮ ሊቀጥል አይችልም።

 

በዚህ አስቀያሚ ልማዳችንም እኛ ኢትዮጵያውያን በሌሎች አፍሪካውያን እንታወቃለን። ለምሳሌ ያክል ልጥቀስ፤ ባለፈው በደቡብ ሱዳን የሪፈረንደም ድምፅ በተሰጠበት ቀን የቪኦኤ (የአሜሪካን ሬዲዮ ጣቢያ) የአማርኛው ክፍል ለአንዲት በአዲስ አበባ የምትኖር ደቡብ ሱዳናዊ ወጣት ቃለመጠይቅ ሲያረግላት አዳምጬ ነበር። ይህች ወጣት አማርኛውን አቀላጥፋ ትናገራለች። የአዲስ አበባ ኑሮዋን ስትገልጽ፤ ሁሉም ጥሩ ነበር ካለች በኋዋላ፤ በት/ቤት ልጆች እንደሚሰድቧት፤ ይህ ደግሞ ብዙ እንደጎዳት፣ እንዲሁ በአጠገባቸው ስታልፍ ጥቁር ባሪያ እያሉ እንደሚያስቸግሯት ገልፃለች። እኛው ራሳችን ጥቁር ሁነን ሌላውን ጥቁር ማለታችን አሳፋሪም ከመሆኑም በላይ የኋላ ቀርነታችን ተምሳሌት ነው እላለሁ።

 

ይህ ደግሞ የዘመኑ ፖለቲከኞች ይጠቀሙበታል። ከቀድሞ ኢትዮጵያውያን ብዙ መማር ይቻላል። ሌላው ቢቀር ራሳቸውን መርተው የመንግሥት ድጋፍ ሳይሰጣቸው፣ ባካባቢው የፀጥታ አስከባሪ ፖሊስና ፍርድ ሳያሻቸው ለዘመናት የተለያዩ ጎሣዎችና የተለያዩ እምነት ያላቸው ህዝቦች በኢትዮጵያ ተከባብረው ኑረዋል።

 

ዓለማችን በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ብትሆንም ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደተሻለ አመለካከትና አስተሳሰብ ልታመራ ሲገባት ወደ ጠበበና የጋርዮሽ አመለካከት እያመራች ትገኛለች። የተማረው ያልተማረውን ቢንቀው፣ ያልተማረው ራሱን አላወቀም ለማለት አያስደፍርም። “ተምሬአለሁ”፣ “ምሁር ነኝ” የሚለው ወገን ያላወቁትን የማስተማር ግዴታውና ኃላፊነቱ ነው። ይህ ደግሞ ከባድ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ አይደለም። ሁላችንም እርስ በእርስ መናናቃችንን ትተን የዜግነት ግዴታችንን ብንወጣ የተሻለ ኅብረተሰብና የተሻለች ሀገር መገንባት ይቻላል።

 

ይህች ሀገር የተገነባችውና ለዘመናት የዘለቀችው አያሌ ኢትዮጵያውያን እኮ ለናት ሃገር ክብር ሲባል እንዲሁም ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ብለው ደማቸውን አፍሰውላትና አጽማቸውን ከስክሰውላት መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

 

ይህ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ያንን ውድ ዋጋ የቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን ቢከፍሉም፣ የወደቁለት ዓላማ ባይሳካም፤ ሥም ለዘላለም ይኖራል እንደሚባለው ሁሉ የታጋይ ድምጽ አይጠፋም፣ ከመቃብር ሆኖም ይጮሃል። ለጩኸቱ ተገቢውን ምላሽ የመስጠት የሁላችን ግዴታም ነው።

 

ይህችን መጣጥፍ ሳቀርብ ከሌሎች የተሻለ ዕውቀት ኑሮኝ ሳይሆን፤ ሁሌም በሃሳቤና በአዕምሮየ የሚመላለሰውን ለመተንፈስ ስል ነው። ምናልባትም የኔው አይነት ካለም ብቻውን አለመሆኑን ስገልጽለት በታላቅ አክብሮት ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!


ፍፁም ከእስራኤል

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ