የአቶ መለስ ዜናዊ ዘፈኖች - የጽንስ ማምከኛ ክኒኖች ናቸው
ተሻገር በላይ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
አቶ መለስ ዘፋኝ ወይም የሙዚቃ ሰው ባለመሆናቸው የጽሑፉን ርዕስ ስታዩ ትገረሙ ይሆናል። ነገሩ እንዲህ ነው። ሰው ሲደሰት ብቻ ሳይሆን ሲፈራ ወይም ብቸኝነት ሲሰማው ያቅራራል፣ ይፎክራል፣ ይዘፍናል። ይህን ሲያደርግም የሌሎችን ልቦና (attention) ይስባል። ለራሱም የተሻለ ስሜት ይሰማዋል።
አቶ መለስ ኢትዮጵያን መግዛት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ እርሳቸውና ድርጅታቸው የተለያዩ ውጣ ውረድን አይተዋል። አሁንም ቢሆን አገዛዛቸው ብልጣብልጥ አምባገነናዊ በመሆኑ በሕዝብ ይሁንታን አለማግኘታቸውንና ሁኔታውም እየከፋ መሄዱን ራሳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ያለፉትን አሥርት ዓመታት ብቻ ስናይ ብዙ ችግር ገጥሟቸዋል። ችግራቸውንም ነጠላ ዜማ በመልቀቅ በካድሬዎቻቸው አቀንቃኝነት ተቃዋሚያቸውን በማዘናጋት የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ሞክረዋል። እነዚህ ዘፈኖቻቸው በጎናቸው ሁነው የሚቃወሚትን ሆነ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያረገዘውን የዲሞክራሲ ጥያቄ እርግዝና ለማምከን የሚጠቀሙባቸው ክኒኖች ናቸው። የለቀቋቸውን ዜማዎችና የገጠሟቸውን ችግሮች በጥቂቱ እንደሚከተለው ለማስታዎስ እሞክራለሁ፦
1. ቦናፓርቲዝም: በኤርትራ ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከኤርትራ ወግነሃል የሚል አመለካከትና እርሳቸውን ከስልጣናቸው እንዲነሱ ከራሳቸው ወገን የሆኑት እንቅስቃሴ ባደረጉ ጊዜ፦
በሁኔታው ትኩሳታቸው በመጨመሩና ብቸኝነታቸው በመጉላቱ አንድ ነጠላ ዜማ ለቀቁ። እሱም “ቦናፓርቲዝም” የሚባል ነበር። ኢትዮጵያ በኤርትራ ጦርነት በተከፈተባት ወቅት “የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር ቦናፓርቲዝም ነው” ብለው ተነሱ። አቶ መለስ የደረሱትን ግጥምና ዜማ ሌላ ሰው በመጫዎቱ ቅሬታ ሳይሆን እንዲያውም ሽልማት ስለሚሸልሙ ካድሬዎቻቸው ለብዙ ወራት ዘፈኑት፣ ተቃዋሚዎቻቸውንም እስር ቤት ከተቱበት። በዚህም የተነሳ የ”ፀረ ሙስና” መሥሪያ ቤት አቋቋሙ። ይህ መሥሪያ ቤትም ይኸውና አገሪቱን ጥቅም የሚነካና በሕግ እንደተጠቀሰው ያለአግባብ በስልጣኑ የሚባልገውን ሳይሆን አቶ መለስንና ድርጅታቸውን የሚቃወመውን በወንጀል ጠልፎ የሚያስር ሆነ። ለዚህም ማስረጃው ከትንሽ አመታት በፊት በቴሌኮሙኑኬሽን መሥሪያ ቤት ከቻይናው የቴሎኮም ዕቃ ሻጪ ኩባንያ የእቃ ግዢውን ከግብ ለማድረስ የቴሎኮም የሥራ ኃላፊ የሆነው ግለሰብ ብዙ ገንዘብ ለመውሰድ ሲደራደር በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ በማስረጃነት ከቀረበ በኋላ ግለሰቡ ለቀናት ታስሮ በከፍተኛ ባለስልጣን ትዕዛዝ እንዲፈታ ተደርጓል።
2. BPR: ሠራተኛው በየመሥሪያ ቤቱ የወያኔን አሠራር በመቃዎም የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳት ሲጀምር አካሄዱና ውጤቱ ላያምር ይችላል ብለው ያሰቡት አቶ መለስ BPR (Business Process Re-engineering) የሚል ዘፈን ለቀቁ። ሠራተኛውም ይህች BPR ምንድናት እያለ በማሰላሰል በህብረት ማሰቡን ትቶ በግል “እኔን የት ታደርሰኝ ይሆን?” ብሎ መጨነቅ ጀመረ። አሁንም ብዙው ሠራተኛ BPR የሚለውን ትርጉሙን ሳያውቀው ሲዘፍነው ይውላል። ይህ ዘፈንም “ትምክህተኛ” ናቸው የሚላቸውን ውድ ባለሙያዎች ወያኔ ለፖለቲካው ስላልተመቹት ብቻ ለማባረር አስችሎታል። አሁንም ይህ ዘፈን ከመዘፈን አላቆመም። ዓላማውም በአቶ መለስ አዲሱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፍልስፍናቸው የተካኑትን ወያኔዎች በማሰባሰብ ቀደም ሲል የነበሩትን ሠራተኞች ማባረር ነው።
3. ኢንተርሀሞይ እና አደገኛ ቦዘኔ: የ1997 ዓም ታሪካዊ ብሔራው ምርጫ ወቅት አካሄዱ ያላማራቸው አቶ መለስ ኢንተርሀሞይ የሚል ሌላ ዜማ ደርሰው ለቀቁ። ይህንንም ዘፈናቸው ሌትተቀን ሲያዘፈኑ ምርጫውንም በጉልበት አሸንፌአለሁ ካሉ በኋላ እራሳቸው ሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረጋቸው በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎች ደማቸው በከንቱ እንዲፈስ ተደረገ። ሟቾቹንም ሆነ ሌሎች የሥርዓቱ ተቃማሚ የዲሞክራሲ ደጋፊ ወጣቶችን “አደገኛ ቦዘኔ” የሚል ስም በመስጠት ካድሬዎቻቸው እንዲዘምሩትና ሕዝባዊ እንቅስቃሴው እንዲቀጭጭ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አደረጉ።
4. ህዳሴ: ይህ ደግሞ አርቲስቱ መለስ በሦስተኛው ሺህ ዘመን መጀመሪያ ላይ የለቀቁት ነጠላ ዜማቸው ነው። የሚገርመው ነገር እርሳቸው የተናገሩትን ቃል ከላይ እስከታች ድረስ መዘመሩ ነው። ይህም የሆነው የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት፥ የኢኮኖሚ ነጻነት ይከበር፣ ዜጎች ያለምንም ገደብ ተንቀሳቅሰው ከድህነት ነጻ የመውጣት መብት ይከበርላቸው፣ ከድህነት ነጻ ለመውጣት የወያኔን ፈቃድ አያስፈልግንም በማለት ሰፊ እንቅስቃሴ በአገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በሚንፀባረቅበት ጊዜ ነው። ልብ በመለስ ወያኔ ዘመን አንድ ሰው ከድህነት ጋር ግብግብ ገጥሞ ያለ ወያኔ ፈቃድ ሊያሸንፍ አይችልም። በድል ላይ ድል ተቀዳጅተዋል እየተባሉ የሚሸለሙት ገበሬዎችም ሆነ ሌሎች በወያኔ ፈቃድ የተንቀሳቀሱና በወያኔ መተንፈሻ የሚተነፍሱ ናቸው። ይህንን የወያኔ ሥርዓት የሚቃወሙ ሰዎችን ደጋፊ ለማሳጣት መንግሥት ዘመኑ የህዳሴ ነው በወያኔ ዘመን “ድህነት ወሬ ሆኖ ይቀራል” ብለው ዋሽተው ካድሬዎቻቸውንም አስዋሽተው በማዘፈን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሸብበው ያዙ።
5. ትራንስፎርሜሽን: የ2002 ምርጫን ብ99% አሸንፌአለሁ ብለው የዓለምን ሕዝብ ባስደነቁበት ማግሥት፣ የወያኔ ሥርዓት ተቃዋሚዎችም ይህ የወያኔ መንግሥት እስከመቸ ነው እንዲህ የማፍያ ሥራ እየሠራ የሚቀጥለው? ብለው ራሳቸውን ጠይቀው ሁኔታውን ለመለወጥ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውንና የዓለም አቀፍ ህብረተሰብም እንዲሁ በሁኔታው አለመደሰታቸውን ሲያውቁ፣ ዞሮ ዞሮ በአገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ሲቃወመኝ፣ ሲያምጽብኝ ነው ጉዴ የሚፈላው ብለው ስለሚያምኑ አዲስ “ትራንስፎርሜሽን” ዘፈን ለቀቁለት። ያወቀውም ያላወቀውም ይህንኑ ዘፈን እያሰበና እየዘፈነ የትስፋ ዳቦ እየበላ አቶ መለስና የድርጅታቸው ሰዎች ግን የእውነቱን ዳቦ እየበሉ ይዝናናሉ። ለነገሩ ዳቦ እቤታቸውም አይገባም። ሌላ ስንት ምግብ ሞልቶ እንዴት ዳቦ ከቤታቸው ይገባል?
6. ህዳሴ ግድብ: ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ የሚወዱት ዜማቸው ሳይሆን አይቀርም። የሰሜን አፍሪካ ሀገራት አምባ ገነን መንግሥታቸውን በሰላማዊ የሕዝብ አመጽ በሚቀይሩበት ወቅት፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በታላቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በሚናጡበት ወቅት ነገ ባለ ተራ እኔ ነኝ ብለው ያሰቡት አቶ መለስ በሕዝቡ ልቦና ውስጥ ሌላ ትክ ሀሳብ ማምጣት አስፈላጊ ነው ብለው የተረዱት “የስን ልቦና ጠበብቱና አርቲስቱ” መለስ ዜናዊ የሚልንየሙን የመጀመሪያ አሥርት ዓመት ታላቅ ዜማ ሊባልለት የሚችለውን “ህዳሴ ግድብ” የሚለውን መዝሙር ለቅቀዋል። ይህ ዘፈን የተለቀቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሰሜን አፍሪካ አገሮች መሰል የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ አቅጣጫ ለማስቀየር ታስቦ ነው። ልብ በሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ አባይ ኢትዮጵያዊነት ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ ምንም አገልግሎት አለመስጠቱን በተለያዬ መልኩ ሲገልፀው ቆይቷል።
የመገደብ ሀሳብም ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ እቅዶች እንደነበሩ እንሰማለን። የአባይን መገደብ እና ለኢትዮ ጵያ ሕዝብ እና ኢኮኖሚ እድገት አገልግሎ ት መዋሉን የሚቃዎም ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ ማሰብ ያስቸግረኛል። የተቃውሞው እንቅስቃሴ የተነሳው አቶ መለስ ይህንን ዘፈናቸውን የለቀቁት በእጅ የተያዘን ሀሳብና የተረገዘ እንቅስቃሴን ለማስንጨገፍ አስበው ነው። ኢትዮጵያውያን የአቶ መለስ ደጋፊዎችን ጨምሮ ሊያስተውሉት የሚገባ ነገር በተለያዩ አስተያዬቶች እንደተገለጸው ቀደም ሲል በአቶ መለስ የተለቀቀዉ የ5ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ይህንን ታላቅና ታሪካዊ ግድብ በውስጡ አለማያዙ ነው። ታዲያ ከ4.7 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ያወጣል የተባለ ታላቅ ፕሮጀክት እንዴት የበጀት ዓመቱ ከተጀመረና የ5ዓመቱም እቅድ ከታወቀ በኋላ በአጣዳፊ እንዲወጣ ተደረገ። ለመለስ ደጋፊዎች የምጠይቀው ይህንን ነገር ህሊናችሁ የመለስ ማደናገሪያ አይደለም ብሎ እንዴት ሊቀበለው ቻለ? የ4.7 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት በረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ ሳይታቀድ ይሠራል ወይ? እስቲ ለአፍታ ያህል በጭፍን ከመደገፍ ወጣ ብላችሁ ጥያቄ ጠይቁ።
የሚገርመው “ደራሲው” አቶ መለስ ሰሞኑን ከአልሃያት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠየቅ የሕዝብን ጥያቄ አለመስማትን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲገልጹ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደሚሰሙና አባይን የመገደቡ ፕሮጀክትም ሕዝቡ በጠየቀው መሰረት ነው ብለው ሲመልሱ ተደምጠዋል። እኚህ ሰው ምን ያህል ጨካኝ መሆናቸውንና የሕዝቡን ዋና ዋና ጥያቄዎች አልሰማም ለማለት የተዘጋጁ መሆናቸውን ያሳያል።
አቶ መለስ ሰው በመሆናቸው ወደዱም ጠሉም መሞታቸው አይቀርም። ከሞት በኋላ ባለ ሕይዎት እንደማያምኑ አውቃለሁ። ይህንን የሚያምን ሰው ደግ መሥራት ለራሱ መሆኑን ስለሚያውቅ ደግ ሥራ ለመሥራት ጥረት ያደርጋል። እርሳቸውና ባልደርቦቻቸው ግን በተጠናዎታቸው ኮሚንስታዊ አስተሳሰብ በተመሠረተ እድገታቸው ምክንያት ሕይዎት ይህች አሁን የያዟት ብቻ በመሆኗ የራሳቸውን በልተውና ጠጥተው የሚጠሏቸውን ተበቅለው መሄድ ነው የሚፈልጉት። ሆኖም ግን የሠሩት ሥራና አብሮአቸው ስለማይሞት ሲታወሱበት ይኖራሉ። ለመለስ የምጠይቀው “መለስ በምን እንዲታወስ ይፈልጋሉ?” መቸም የሰይጣንን መስመር የተከተለ ሰው እንዲታወስ የሚፈልገው በሰይጣንነቱ ስለሆነ መልሳቸው ምን ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።
ውድ ኢትዮጵያውያን መለስ ዜናዊ በሚለቋቸው ዘፈኖች ተዘናግተን ከዲሞክራሲ ጥማት የተነሳ የተጠነሰሰውን ትግል አላስፈላጊ ጊዜ በመስጠት ትግሉን እንዳናዳክም አደራ እላለሁ። የመለስ ዘፈኖች የጽንስ ማምከኛ ክኒኖች ናቸውና አንዎስድም እንበለው። ጽንሳችን ስንት ጊዜ ያስወርዱናል? ስንት ጊዜ ያሞኙናል? አዎ አባይ መገደብ አለበት። በአባይ መገደብ ላይ ወያኔ ተቃዋሚዎች ፍላጎት የላቸውም ብሎ እንደሚያወራው አይደለም። አባይን የኢትዮጵያ ሕዝብ በባለቤትነት ይገድበዋል። የወርቅ ማምረቻ ቦታዎቻችን በማን እንደተያዙና ለማን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠንቅቀን እናውቃለን።
በቃ የመለስ ወያኔ አገዛዝ በቃ!
ተሻገር በላይ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
May 04, 2011



