ይነጋል በላቸው (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አንጀትን ሰርስሮ የሚገባ ግሩም አባባል። በርዕሴ ላይ የተመለከተውን ወርቃማ ንግግር የተናገረው ከደቂቃዎች በፊት ዚንታን በምትባል የምዕራብ ሊቢያ ትንሽ ከተማ ውስጥ አኒታ በምትባል የነውጠኛው አልጀዚራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የተጠየቀው አንድ በሙያዉ መሃንዲስ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ተገድዶ ግን የነፃነት ታጋይ ወታደር የሆነው መሀመድ የሚባል ሰው ነው።

አብሮ እንደዋለ ወይ እንዳደረ ሰው ያለሰላምታ ዘው ማለት ደግ ነው እንዴ? ባህላችንስ ይፈቅደዋል? አይ፣ ነውር ነው፤ በዚያ ላይ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተለያይተን ከርመናል። እናም ለብርሃነ ትንሣኤው እንኩዋን አደረሳችሁ ማለቱ ለጥቂት ቢያልፍብኝም እንዲሁ ግን እንደምን ሰነበታችሁ ብዬ ሰላምታ ማቅረቡ መጥፎ አይመስለኝም። ይህ ዓይነቱ ባህላችን ቢዳብር ጥሩ ነው። እኔን ጨምሮ በርካታ ባለመጣጥፎች እንዲያው ዝም ብለው - ከመሬት ተነስተው - ቁም ነገር ላይ ፊጥ ሲሉ ይገርመኛል። ቤት ሳይንኩዋኩዋ ዘው ተብሎ ይገባል? እናም እባካችሁ ይህን እንዴት ሰነበታችሁ የመባባልን ጉዳይ ችላ አንበለው። መጽሐፉስ ‹ተኣምሁ በበይናቲክሙ (እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ)› የሚለው በሰው ልጆች ኅልውና ሰላም ያላትን ማለፊያ ሚና ለማዘከር አይደል? እናም ሰላም መባባልን እንደነውር እየቆጠርን ጽሑፋዊም ሆነ ንግግራዊ ግንኙነታችንን ካለሰላምታ እየጀመርን ውጥናችንን ሁሉ ከውጥኑ ለሰይጣን አንዳርግ። ሰላምንና ፍቅርን ለሰዎች መመኘት ሁዋላቀርነትና የኢ-ሥልጡንነት ምልክት አይደለም፤ ሊታፈርበት የሚገባ መጥፎ ባህል የሰላም መጥፋት እንጂ ወገን ለወገን ሰላምን መመኘት ሊሆን አይገባም። … ለማንኛውም ‹ ነፃነት ከገንዘብ በላይ ናት› …

 

ነገሩ እንዲህ ነው። ይህች ከፍ ሲል የጠቀስኩዋት ጋዜጠኛ ያቀረበችው የዜና ጥንቅር እንደሌሎቹ የሊቢያ ግዛቶችና ከተሞች በሚዲያ ተገቢውን ሽፋን ካላገኙ የነፃነት ፍልሚያዎች መካከል አንዱን የሚያስቃኝ ነው። በምዕራቡ ጫፍ ስለምትገኘውና ዚንታን ስለምትባለው ከተማ የተቃዋሚ ኃይላት እንቅስቃሴ ነው ያቀረበቸው። ይህች ብዙም ሕዝብ የማይኖርባት አነስተኛ ከተማ በወፈፌው ጋዳፊ ወታደሮች ተከብባ በመድፍና በአዳፍኔ ከርቀት ያለርህራሄ እየተወገረች ናት። ተቃዋሚዎቹ ግን እስካሁን ቅጽሮችዋን በጋዳፊ የእግረኛ ጦር አላስደፈሩዋትም። ዙሪያዋን አጥረው ከዘመናችን ሂትለር ከጋዳፊ ጃዝ የተባሉ ያበዱ ውሾችን ወደከተማቸው እንዳይገቡ እየተከላከሉ ነው - በከባድ መሣሪያ ያለርህራሄ እየተጨፈጨፉ መሆናቸው እንደቀጠለ ቢሆንም። አኒታ ቃለ መጠይቅ ያደረገችላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና የነፃነት ታጋዮች እንደተናገሩት፣ ጎራቸውን ለውጠው ጋዳፊን የሚደግፉና ተቃውሞዋቸውን የሚተው ከሆነ ለእያንዳንዱ የከተማዋ (ነፍስ ያወቀ?)ነዋሪ በነሱ ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ዲናሬ (በጠጣሩ ምንዛሬ 750 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው ብላለች ጋዜጠኛዋ) ሊሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸውና የከተማዋ ነዋሪ ግን የሱ ገንዘብ ባፍንጫችን ይውጣ ብሎ ንቆ እንደተወው ይልቁንም በኅብረት ሆኖ የነፃነት ትግሉን አጠናክሮ እንደቀጠለ በስሜት ገልጸዋል። የዚያን ጊዜ ነበር መሀመድ የተባለው ሲቪል መሃንዲስ ጠበንጃውን እንዳገነደረ ይህችን ብዕሬን ከተቀመጠችበት ቦታ እንዳነሣ ያስገደደችኝን ዕንቁ ንግግር በቁጭት የተናገረው፤ ልድገማት ይሆን? አዎ - ምናለበት! - ‘Freedom is Priceless’ (ነፃነት ከገንዘብ በላይ ናት)። እውነቱን ነው - ነፃነት ከገንዘብ በላይ ብቻ ሳትሆን በገንዘብና በሀብት ብዛትም በጭራሽ ልትተመን አትችልም። አባባሉ ‹ቅንጭላቴ›ን ክፉኛ ነካኝ።

 

በሃይማኖቴ የሃይማኖቴ የማዕዘን ራስ የሆነው ጌታየና መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሳም ተላልፎ የተሸጠው በ30 አላድ ነበር - ይህ የገንዘብ መጠን 750 ሺህ ዶላርን ግን አይጠጋም - ምንም እንኩዋን ጊዜው ቢርቅምና የዚያን ጊዜውና የአሁኑ ምንዛሬ ሊያጠራጥረን ቢችልም።(በነገራን ላይ ከአንባቢያን መካከል እምነቴን የምትጋሩ ብትኖሩ ተውላጠ ስምን የማስተካከል መብታችሁ የተጠበቀ ነው - የሰዎችን የእምነት መብት ለማክበር ከ‹ጨዋነት› አንጻር እንጂ ይበልጥ ክርስቶሳዊ ሆኜ ሞቼ አንደኛ መደብ ነጠላ ቁጥር መጠቀሜ እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ)። እነዚህ ወንዶች(ሴቶችም ጭምር!) ሊቢያውያን ግን ‹ችግራችንና ጥማታችን ምግብና መጠጥ ሳይሆን ነፃነት ነው› አሉና ባንድ ድምፅ ‹ ከነገንዘብህ ጀሃነብ ወይም ገደል - እንደምርጫህ - ግባ እንጂ በኛው ገንዘብ - ከኛው ቀምተህና ዘርፈህ ለዘመናት ባከማቸኸው ዓለማዊ አላፊና ጠፊ አዱኛ ልታታልለን ልታነሆልለንም አትችልም!› ብለው እቅጩን ነገሩት - ሌባው ቀጣፊን። ትዝታ - በደርግ ዘመነ መንግሥት ‹የሌባው መሪ ኮሎኔል ቀጣፊ ነገ ስለሚመጣ አብዮት አደባባይ ተገኝታችሁ በሠልፍ እንድትቀበሉ፤ ፍየል ታስሮ ከኩባ ስለሚመጣ ሠልፍ እንድትወጡ…› የሚል የጡሩንባ ለፋፊ ቀልድ ትዝ አይላችሁም?

 

ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰይጣን ተፈትኖኣል። ሦስት ተራራ ተራራ እሚያህሉ ጥያቄዎችን ተጠይቆ በሚያኮራ ሁኔታ ዲያቢሎስን አሳፍሮ ፈተናውን አልፎኣል። ከሦስቱ ጥያቄዎች አንዱና የመጀመሪያው በአሁኑ ወቅት ዓለምን እየተፈታተናትና ወደመጨረሻዋ የጥፋት አዘቅትም በብርሃን ፍጥነት እያምዘገዘጋት የሚገኘው የሆድ ነገር ነው፤ ‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል› መባሉ ለዚህ ይሆን? ይሄ ሆድ የሚሉት ነገር ከበስተሁዋላችን ቢሆን ምን ይውጠን ነበር እባካችሁ? እንኩዋን አልሆነ! ብዙዎቻችንን ገደል ይከተን ነበራ!

 

ክርስቶስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ያለ ምግብ ቆይቶኣል ። ኢየሱስ ሰውም አምላክም ነውና - ይቅርታ ለስብከት አይደለም - በጣም ተራበ፤ ተጠማም። ይህን ያስተዋለው ወያኔው ሰይጣን በመጀመሪያ ጥያቄው፤ ‹አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ› አለው። ኢየሱስም አለው፤ “‘ሰው የሚኖረው እግዚአብሔር በሚናገረው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም’ ተብሎ ተጽፎኣል“።

 

ሊቢያውያን ሰይጣኑ ጋዳፊ - ውሉደ ዲያቢሎስ ብቻ ሳይሆን ራሱ ዲያቢሎስ በሰው አምሳል ተከስቶ ማለት ይቻላል - ‹ብዙ እንጀራ - ዕድሜ ልካችሁን የማትጨርሱት እንጀራ ልስጣችሁና ነፃነታችሁን ግን ለኔ ተውልኝ፤ እንዳሻኝም ልረጋግጣችሁ፤ልረማመድባችሁም› አላቸው - ጅብ ‹አነ አአምር ግብሮሙ ለቆራዕብት(የቆዳዎችን ነገር ለኔ ተውልኝ)› እንዳለው ቢጤ መሆኑ ነው። እነሱ ግን አይሻንም አሉት። የሚኮፈስበት ገንዘብ ከእናቱ ማኀጸን ይዞት የወጣው ወይም ከእናት አባቱ በኑዛዜ የወረሰው - (ፈረንጆቹ - to be born with a silver spoon in one’s mouth - እንደሚሉት) ሳይሆን እነሱን መዝብሮ ያገኘው መሆኑንና በነፃነታቸው ማግስት ሁሉም ነገር የእነሱና የእነሱ ብቻ እንደሚሆን ዕቅጩን በመንገር አሳፍረው መለሱት። እንዲህ ነው የነቃ ዜጋ ማለት። ከ42 ዓመታት በሁዋላ አዚሙ ለቀቃቸው። እኛስ ከስንት ቀን ወይ ሣምንት ወይ ወር ወይ ዓመት በሁዋላ ይሆን የወያኔ አፍዝ አደንግዝ የሚለቀንና ወግ ማዕረጉ የሚደርሰን?

 

እስከመቼ ከእህህ ጋር ተጎራብተን በንዴትና በብስጭት ቁና ቁና እዬተነፈስን ቆሽታችንና በተወደደ ውስጥ ዕቃ ጨጉዋራችን እዬጨሰ እንኖራለን? እስከመቼ ከቁጭታችንና ከነዳማችን ጋር በልቅሶና በዋይታ እየተንሰቀሰቅን ዕድሜያችንን ወበከንቱ እንፈጃለን? ወያኔ ጋር ለማይረባ ሻጋታ እንጀራ ሀገራችንንና ሰፊውን ወገናችንን እንደይሁዳ አንጀት በማያጠረቃ ድርጎ እየሸጥን የምንኖር ግማሽ ዜጎች እስከመቼ ነው በዚህ መልክ በሆድና በኀሊና አጣብቂኝ ውስጥ ገብተን ነፍስና ስጋችን እዬተሙዋገቱብን በስቃይ የምንኖር?

 

የይሁዳንና የኛን አንዳንድ የወያኔ ተለጣፊ ወገኖቻችንን ሁኔታ ስታዘብ የሚገርመኝ ነገር አለ። ይሁዳ በ30 አላድ ክርስቶስን እንደሸጠውና ያችንም ገንዘብ ሳይጠቀምባት ላይጠቅመው ተልከስክሶ በጸጸት ምክንያት አንጎሉ ዞሮ ተሰቅሎ እንደሞተ እናውቃለን። እኒያው ፈሪሳውያኑ ያን ገንዘብ ወስደው የደም መሬት ብለው የሰየሙትን ቦታ እንደገዙበት መጽሐፉ ያትታል። የሱ ጉዳይ ረቀቅ ያለና ከሥነ መለኮታዊ እሳቤ አንጻር ሊታዩ የሚገባቸው ነጥቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ እዚህ ላይ አንገፋበትም።

 

ወያኔ አሁን አሁን አሻሽሎላቸው እንደሆነ አላውቅም እንጂ በግድም በውድም እያባበለ ለሠልፍ ወይም ለስብሰባ አደባባይ ለሚያወጣቸው ዜጎች የሚከፍለው ገንዘብ 30 ብር መሆኑ ግን በጣም ይከነክነኝ ነበር። ይህም መመሳሰል በይሁንታ የሚደረግም ይመስለኝ ነበር። ሚያዚያ 29/1997ዓ.ም በአብዮት አደባባይ የተናዳፊዋን ንብ ከናቲራ በግድ አልብሶ ላሠለፋቸው ወገኖቻችን ለእያንዳንዳቸው የከፈላቸው 30 ብር ነበር። በ2002ዓ.ም ለታዬው ቁጩ የምርጫ ቲያትር ለተሠለፉለት እጅግ ችግረኛ - በምርኩዝና በእንፉቅቂት ሳይቀር የሚጉዋዙ ነዳያን ነበሩበት - ወገኖቻችን የከፈላቸው ለእያንዳንዳቸው 30 ብር ነበር፤ የሚያስደንቀው ነገር ብዙዎቹ ድሃና የኔ ቢጤ በመሆናቸው ገንዘቡ ሲሰጣቸው ሠልፉ ላይ ተማገዱ እንጂ ለምን እንደተሠለፉ እንኩዋን አያውቁም ነበር። ከአንድ ዓመት በፊት የወንድሜ ልጅ በትምህርት ቤትዋ ለሁለት ቀናት በተካሄደ የንቃት ማዳበሪያ ስብሰባ ስትካፈል በቀን 30 ብር በድምሩ 60 ብር ይዛ ስትመጣ ታናሽ ወንድሙዋ ‹እንደይሁዳ ሀገርሽን ለወያኔ በ30 ብር ሸጥሽ አይደል?› ብሎ የተረባትንና በትረባው መላ ቤተሰቡን ያስደመመንን ድማሜ መቼም ቢሆን ዕድሜ ልኬን አልረሳውም።

 

ድህነት ዓይነቱ ብዙ ነው። ነገር ግን እንደአስተሳሰብ ድህነት ያለ አስቀያሚና አዋራጅ ድህነት የለም። በአስተሳሰብ ድሃ የሆነ ሰው የሁሉም ነገር ድሃ ነው። በገንዘብ ድሃ የሆነ ሰው ግን አንድ ቀን ሊያልፍለት ስለሚችል ከታገሰ ከብዙ ውጣ ውረድና አዋራጅ ሁኔታ ተጠብቆ ለቁም ነገር ደረጃ ሊደርስ ይችላል። በአሁኑ ወቅትም ሆነ ቀደም ሲል የንዋይ ፍቅርና የሥልጣን ሱስ አስተሳሰባቸውን እንደዖዞን ንጣፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳሳባቸው መጥቶ ከነጭርሱ የሚቦጫጭቅባቸው ዜጎቻችን መጨረሻቸው ሳያምር ለብስጭትና ያንንም ተከትሎ ለሚመጣ የመጠጥና የሌላ ሱሶች ተገዢ እንደሚሆኑ፣ ወደፊትም ከዚሁ ሥነ ልቦናዊ አዙሪት ሳይወጡ ለውርደትና ለቀጣዩ ኅልፈት እንደሚዳረጉ እናውቃለን። በልቶ ለማይጠረቃ ሆድ ብለው ውድ ሀገራቸውን ለጠላት አሳልፈው የሚሸጡ ዜጎች መዳረሻቸው የማያምርና ጸጸት የተሞላበት መሆኑ ባይካድም ለጊዜው ግን በከፍተኛ ደረጃ እዬጎዱን መሆናቸው ግልጽ ነው። እነዚህን ሳይወለዱ ቢቀሩ የሚሻላቸውን ወይም የክርስቶስን አማርኛ በጨረፍታ በመዋስ ‹እናታቸውን በ30 ብር የሚሸጡ ጭንጋፍ ዜጎች የወፍጮ መጅ ባንገታቸው ታስሮ ወደ ጥልቁ ውቅያኖስ ቢወረወሩ ይሻላቸዋል።› ብዬ ሳልወድ በግዴ ባጭሩ ልገልጻቸው የምፈልጋቸውን ወገኖቼን፣ እኔ በበኩሌ በአሁኑ ፈታኝ ወቅት ሌላ የምላቸው ምንም ነገር የለኝም። ለማንኛውም ፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለምና ፊቱን መልሶልን ራሳችንን እንድንመረምርና እውነቱን በቶሎ ተረድተን ሁላችንን ሊጠቅመን ወደሚችል የተሻለ አማራጭ እንድንዞር ያደርገን ዘንድ በጋራ በመጸለይ እንለምነው። ፈቃዱ ከሆነ እኮ ባንድ ቀን አዳር ሚሊዮን ጀግኖች እንዲወለዱ ሳይሆን እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል። ዋናው እምነት ነው። እንመን እንጂ ከገባንበት አረንቁዋ ለመውጣት ሣምንትም ላይፈጅ ይችላል።

  

ማጠቃለያ - ከዚህም ከዚያም

ዓለም ግልብጥብጡዋ እዬወጣ ባለችበት በአሁኑ የሀዘንና የሰቆቃ ዘመን ትርጉሙ በማይገባ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የሚመስል ሠርግ የሚያሠርጉትን ወግአጥባቂ ቅንጡዎች ፈጣሪ ልብ ይስጥልንና ወደኀሊና ጉዋዳቸው ይመልስልን። በቢሊዮን የሚገመት የዓለም ሕዝብ ይልሰውንና ይቀምሰውን አጥቶ በርሀብና በእርዛት፣ በመሬት መናወትና በሱናሚ፣ በጦርነትና በስደት፣ በደን ቃጠሎና በንፋስ ንፅውፅውታ፣ በጎርፍና በናዳ … እየተቆራመደና ይገባበትን እያጣ ባለበት ሁኔታ በሠርግም ሆነ በሌላ አላስፈላጊ ወጭ የዓለማችንን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብት(Resource) በከንቱ ከሚያባክኑ ትናንሽ አንጎል ያላቸው ግን ‹ሀብታም› ዜጎቻችን ይጠብቀን። በቀለምና በዘር ወይም በሀብትና በሥልጣኔ ልዩነት ሰበብ በተለይ በአፍሪካ ስንትና ስንት ዜና ሊሠራባቸው ለሚችሉ አንገብጋቢና አሳሳቢ ጉዳዮች የሴከንዶችን ያህል እንኩዋን የዘገባ ሽፋን ሳይሠጡ ከቱሪዝም መስህብነት እምብዝም ያለፈ ጠቀሜታ በሌለው የሁለት ሰዎች ጋብቻ ላይ ያተኮረ የሙሉቀን የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን የሚሰጡ የሚዲያ ተቁዋማትን አሁንም ልብ ይስጥልን። መለስ ዜናዊ ከሚባል ጋንጩር ኢትዮጵያንና ልጆችዋን እግዚአብሔር ልዩ ዘዴና ይበብን ተጠቅሞ ነፃ ያውጣልን፤ እኛንም ወኔ ሰጥቶን የዚህ ዘረኛና ግፈኛ የዋልጌዎች ጥርቃሞ ‹መንግሥት› ዕድሜ ከፊታችን ግንቦት እንዳያልፍ ያድርግልን። በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዕብድ ውሾችን እግዜር በብልኃቱ ጉልበታቸውን ቀጤማ ዐይናቸውን ጨለማ አድርጎ ክራንቻቸውን ሰባብሮልን የየሀገሮች ሕዝቦች በሰላምና በመፈቃቀር እንዲኖሩ ያድርግልን - ለግንዛቤ ያህል እነዚህ ዕብድ ውሾች በዋናነት የሚገኙት በኢትዮጵያ፣ በሊቢያ፣በየመን፣ በዩጋንዳ፣ በሩዋንዳ፣ በዚምባብዌ፣ በባሕሬን፣ በሳዑዲ፣ በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ፣በእስራኤል፣ በኢራንና በፍልስጥኤም … ኦ! ኦ! ኦ! ዝርዝሩ ከቀጠለ አሜሪካና አውሮፓም ሳይገባብኝ አይቀርምና እዚሁ ላቁመው። በነገራችን ላይ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ዋናው ነገር በአንድ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ በአግባቡ መኖሩ ወይ አለመኖሩ ብቻ አይደለም የዚያ ሀገር ሕዝብ እንደተመቸው ወይም እንዳልተመቸው ለመረዳት የሚያስችለን። በጉልበት ሥልጣን ላይ የወጣ ጥሩ አምባገነን መሪ ሊገኝ እንደሚችለው ሁሉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደሥልጣን የመጣ መጥፎ መሪም የሚያጋጥምበት ጊዜ ይኖራል ብቻ ሳይሆን አለ - በተለይ ቡድናዊና ምሥጢራዊ ፍላጎት ያላቸው ሥውር ‹መንግሥታት› በግልጥ መንግሥታት ጀርባና ጉያ ተፈኛጥጠውና ተወትፈው ብዙ ደባ የሚሠሩበት አጋጣሚ ሞልቶኣል። ስለዚህ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባንድ ሀገር መስፈን ብቻውን ምንም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሉዋል። የዛሬን አያድርገውና የአሁኑ ሆድ አምላኩ ሶሎሞን ተካልኝ ‹ዕድል ነው› በሚል አዝማች ‹ሚስትና ሎተሪ አንድ ነው› ብሎ ያቀነቀነውን ‹ዕድል ነው፤ መለስና ሰይጣን አንድ ነው› ብዬ ልሰናበት።


ይነጋል በላቸው(

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ