የአባይን ግድብ መገንባት እንችላለን!
ግርማ ካሣ
በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሰፊው እያነጋገረ ያለው ጉዳይ ቢኖር በቅርቡ የኢሕአዴግ መንግሥት ይፋ ያደረገው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ነው። አቶ መለስ ዜናዊ ምንም እንኳን የውጭ አገር መንግሥታትና ድርጅቶች እርዳታቸውን ለመዘርጋት ፍቃደኛ ባይሆኑም፣ ሰማኒያ ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በራሱ ገንዘብ ግድቡን መስራት እንደሚችል፣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነው በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊውንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ያነጋግሩ ዘንድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደሳለኝ ኃይለማሪያምንና በርካታ ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸውን ያካተተ የልኡካን ቡድን፣ በተለያዩ የአሜሪካንና የአውሮፓ አገራት ማሰማራታቸው ይታወቃል።
ትዝ ይለኛል ልጅ እያለሁ ከሃያ፣ ሃያ አምስት አመታት በፊት፣ ነፍሳቸውን ይማርና፣ አቶ ጳውሎስ ኞኞ በአባይ ዙሪያ ያቀረቡት የቴሌቭዥን ቅንብር። የአባይ ወንዝ ትልቅ የኢትዮጵያ ሲሳይ እንደሆነ፣ አባይን ለልማት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ነበር ጳውሎስ ኞኖ በመረጃ ሲያስረዱን የነበረው። የአባይን ግድብ የመገደቡና በወንዙም የመጠቀሙ ጉዳይ፣ በእኔም ሆነ በማንኛውም ኢትዮጵያ ልብ ውስጥ የተቀመጠ፣ “መቼ ይሆን የሚሆነው?“ ብለን የምንጓጓለት ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ነው።
“ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ለምን የአባይን አጀንዳ እንደ ትልቅ አጀንዳው አድርጎ ወሰደው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ብዙዎች የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ይደመጣሉ። በቺካጎ የኢኮኖሚ ፕሮፌሠር የሆኑ ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው፣ ኢሕአዴግ ስለዚህ ፕሮጀክት የሚያወራው ለአገር አስቦ፣ ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት ሳይሆን፣ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከተነሱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የሕዝቡን ትኩረት ለማዞር፣ ብሎም ከዳያስፖራው ገንዘብ ለመዝረፍ ፈልጎ እንደሆነ ይናገራሉ።[1]
የቀድሞ የቅንጅት ከፍተኛ አመራር የነበሩና የሰላማዊ ትግል ውጤት ሊያመጣ አይችልም በማለት አዲስ የዳያስፕራ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመው እንደሚንቀሳቀሱ የሚናገሩት ኢኮኖሚስቱ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፣ የኢሕአዴግን የአባይ እንገንባ እንቅሳሴ “ተራ ውንብድና” ሲሉ ያጣጥሉታል። “እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም መለስ ዜናዊ ካይሮ ድረስ ሄዶ ከሙባረክ ጋር “ኢትዮጵያም ሆነች ግብጽ የኣባይን ወንዝ የውሀ ፍሰት የሚቀንስ ምንም እርምጃ ኣይወስዱም” የሚል ስምምነት ተፈራረመ። ኧረ ይህ ስምምነት በጎ ኣይደለም የሚልን ኣገር ወዳድ ሁሉ ጦር ሰባቂ፤ ትምክህተኛ ተብሎ ሲዘለፍ ነበር። ታዲያ ዛሬ የኣባይ ወንዝ ግድብ ጉዳይ እንደ ትልቅ ኣገራዊ ኣጀንዳ በዚሁ ምንም ባልተቀየረ ሰው መነሳቱ ምንም እውነተኛ የልማት ኣላማ የሌለው ተራ ኣቅጣጫ ማስቀየሻ፣ ሲያልፍም ከህዝቡ ገንዘብ መዝረፊያ ተራ የውንብድና ስራ መሆኑን ለማሳየት በጣም ትልቅ ምርምር ኣይጠይቅም”[2] ሲሉ ነበር ዶ/ር ብርሃኑ ያላቸውን ጠንካራ ተቃውሞ የገልጹት።
አንተነህ ሽፈራው የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ኢንጂነር “ኢትዮጵያና ዓባይ፣ ግብጽና ወያኔ” በሚል ርዕስ ሥር ኢትዮሜዲያ ላይ ባወጡት ጽሁፋቸው፣ አቶ መለስ ዜናዊ በ1993 ከግብጽ ጋር የፈረሙትን ስምምነት እርሳቸው በማስታወስ፣ ኢሕአዴግ ሰፋፊ የመስኖ ሥራን ወደ ጎን በማድረግ፣ ሰብዓዊ መብትን በመርገጥ የሚገነባው ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ጥቅም እንደማይሰጥ ይናገራሉ። “መለስ ዜናዊ በ1993 ካይሮ ድረስ ሄዶ ኢትዮጵያ የአባይ የውሃ መጠንን ፍሰት ላለመቀነስ ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር እንደተሰማማ እየታወቀ የዛሬውን የእዳሴ ግድብ ድንፋታ ምን አመጣው?” ያሉት ኢንጂነር አንተነህ ““እኛ/የኢትዮጵያ ሕዝብ/ ግን አባይን የምንጠብቀው ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚሄደውን ለም አፈር/ደለል/ በሚባለው ግድብ ያለቦታው ገድቦ ለማስቀረት፣ አልያም ለመብራት ብቻ ሳይሆን ለሙ አፈር እንዳይሸረሸር ተገቢ እንክብካቤ አስቀድሞ በማድረግና በተገቢው ቦታ ግድቡን በመስራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ከመፍጠር በተጨማሪ ከግድቡ በታች በሚፈሰው ውኃ ሰፊ የመስኖ ሥራ-ሃብት ለሕዝባችን በአስተማማኝ ለመፍጠር ነው። እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ያላካተተ የአባይ ግድብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጋሎት ሰጠ ለማላት ጭራሽ አይቻልም”[3] በማለት ነበር ጽሁፋቸውን ያጠቃለሉት።
“ኢሕአዴግ ለምን የአባይን አጀንዳ አሁን አንግቦ መንቀሳቀስ ጀመረ? የኢትዮጵያን ሕዝብ ትኩረት በአረብ አገሮች ከታዩት አብዮቶች ለማዘናጋት ነውን?” ለሚሉት ጥያቄዎች ያሉኝን አስተያየቶች ከመስጠቴ በፊት፣ በ1993 ተፈረመ ስለተባለው ስምምነትና አባይን ለመስኖ በመጠቀሙ ዙሪያ ኢሕአዴግ ይኖረዋል ብዬ ስለማስበው አቋም ጥቂት ማለት እፈልጋልሁ።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ኢንጂነር አንተን ሽፈራው በ1993 ከግብጽ ጋር የተፈረመውን ስምምነት ሲጠቅሱ፣ የስምምነቱን አንቀጽ አምስትን ታሳቢ ያደረጉ ይመስለኛል። “እያንዳንዱ አገር የአባይን ውሃ በተመለከተ የሌላውን አገር ጥቅም ክፉኛ የሚጎዳ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይቆጠባሉ”(Each Party Shall refrain from engaging in any activity related to the nile waters that may cause appreciable harm to the interests of the other party) ይላል የ1993 ስምምነት አንቀጽ 5። በመርህ ደረጃ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ተጠቅማ ትልቅ ጉዳት ግብጽ ላይ እንደማታደርስ፣ ግብጽም እንደዚህ ኢትዮጵያን እንደማትጎዳ የሚገልጽ አንቀጽ ነው። ይህ አንቀጽ በምንም መስፈርትና ሚዛን ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ መጠቀም እንደማትችል የሚያሳይበት ሁኔታ የለም።
ወደ ላይ ከፍ ብለን በአንቀጽ 4 ደግሞ፣ ሁለቱ አገሮች፣ የአባይ ውሃን አጠቃቀምን በተመለከተ በአለም ቀፍ ሕግ መሰረት፣ ውይይት ለማድረግ እንደተስማሙ ይገልጻል። ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላት በገሃድ እንድታረጋግጥ የተደረገበት ስምምነት እንጂ በምንም መልኩ የኢትዮጵያን ጥቅም የሸጠ ስምምነት አይደለም። ይህ ስምምነት የሁለቱንም አገሮች ጥቅም ባሰጠበቀና የአለም አቀፍ ሕግን ባልጣሰ መልኩ የአባይን ውሃ በጋራ መጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመነጋገር መወሰናቸውን የሚገልጽ ስምምነት ነው። በኔ አስተሳሰብ የ1993 ስምምነት ለኢትዮጵያ ድል ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል ባይ ነኝ። አቶ መለስ ዜናዊም ይህንን ስምምነት በመፈረማቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል እንጂ ሊያስወቅሳቸው አይገባም። (የአባይ ፖለቲካ በሚል ርዕስ፣ አውራምባ ታይምስ ታህሳስ 2 ቀን 2003 ባወጣው ጽሁፌ ላይ ይህ የ1993 ስምምነት በሰፊው ተተንትኗል።[4])
አባይን ለመስኖ በመጠቀሙ ዙሪያ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት የአባይን ውሃ ለመስኖ እንደማይጠቀም የገለጸበት ሁኔታ እስከ አሁን አላነበብኩም። ምናልባት ለህዝብ ግልጽ ያልሆኑ መረጃዎች ካሉ ይፋ ቢሆኑ መልካም ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል ለማመንጨት ብቻ ሳይሆን ለመስኖ ስራዎችም አባይን የመጠቀም ሙሉ መብት አላት። የአለም አቀፍ ሕግ ግብጽ፣ ኢትዮጵያም የውሃ ተጠቃሚ እንደሆኑ ነው የሚደነግገው። ግብጽ ብቻዋን ውሃውን እንድትጠቀም የሚያዝ አንዳች አይነት አለም አቀፍ ሕግ የለም።
አብዛኞቻችን አሁን በስልጣን ላይ ካለው የኢሕአዴግ መንግሥት ጋር የሰፋ ምናልባትም የከረረ ልዩነቶች ይኖሩናል። ብዙዎቻችን በኢትዮጵያ ፍትህና መልካም አስተዳደር እንዲኖር ካለን ጠንካራ አቋም የተነሳ፣ በብዙ አጋጣሚዎች ኢሕአዴግ በሚያራምዳቸው አንዳንድ ጠቃሚ ያልሆኑና ጎጂ ፖሊሲዎቹ ላይ ያሉንን ትችቶችና ጠንካራ ተቃውሞዎች አሰምተናል፤ ወደፊትም ማሰማታችንን እንቀጥላለን።
ነገር ግን ኢሕአዴግን ስንቃወም ግልጽና የተጨበጡ ምክንያቶች ሊኖሩን ይገባል ባይ ነኝ። እንደው ለመቃወም ያህል መቃወም እንደ አገር ርቀን እንድንሄድ አያደርግም። ኢሕአዴግን ለመቃወም “መስኖን መጠቀም አንችልም፤ የ1993 ስምምነት የአገርን ጥቅም ሽጧል ወዘተረፈ” በማለት ከእውነት የራቀ ክሶች ማሰማት ያለብን አይመስለኝም። ኢሕአዴግን ለመቃወም ከተፈለገ በቂ የሆኑ፣ የማያከራክሩ፣ እራሳቸው የኢሕአዴግ ደጋፊዎችን ሳይቀር አሳምኖ በአመራሩ ላይ ጫና ሊያስፈጥሩ የሚችሉ በርካታ የመቃወሚያ ነጥቦች አሉ።
የአባይ ወንዝ መገንባቱ ለአገራችን ኢትዮጵያን ለሕዝቡ ትልቅ ጥቅም አለው ብለን ከተማመን ሊኖሩን የሚችሉ ሌሎች ቅሬታዎች የሚስተካከሉበት ሁኔታ ማመቻቸትና በዚያ ላይ መሥራቱ ይበጀናል።
በርግጥ የኢሕአዴግ መንግሥት ለዘመናት የኢትዮጵያውያንን የልብ ትርታ የሆነውን የአባይን አጀንዳ ይዞ መነሳቱ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በሙሉ ልብም ሊደገፍ የሚገባው ጉዳይ ነው እላለሁ። ይህንን የሕዳሴ ግድብ የምንቃወምበት ምክንያት አለ ብዬ አላምንም። በተለይም ኢሕአዴግን ስንቃወም የነበረን ወገኖች ቆም ብለን እራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። ኢሕአዴግ የሚያራምዳቸውን ጠቃሚ ያልሆኑ ፖሊሶውች መቃወማችንን እየቀጠልን፣ በተለይም ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለዲሞክራሲ መስፈን የሚደረገውን ትግል እያፋፋምን፣ ገዢው ፓርቲ የሚያደርጋቸውን የልማት እንቅስቃሴዎችንም መደገፍ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። ዴሞክራሲ ስለሌለ ልማት አትደግፉ ማለት ምግብ ስለሌለ ልብስ አትልበሱ ማለት ነው።
አውራምባ ታይምስ የአባይን ግድብ ስኬት እንደግፋለን በሚል ርዕስ አንቀጹ ሥር፣ ሚያዚያ 1 ቀን 2003 ባወጣው እትሙ “አንዳንድ ወገኖች እንደሚሟገቱት ይህ ፕሮጀክት (የአባይ ግድብ) ዜጎች ሁለንተናዊ ጥያቄዎቻቸውን ለገዢው ፓርቲ እንዲያቀርቡ በሚል የተቀመረ የሃሳብ ማስቀየሻ አጀንዳ ሆነም አልሆነም ለዲሞክራሲ መብቶች መከበር ከሚደረገው ትግል ጎን ለጎን፣ ፕሮጀክቱን የመንፈሳዊና ስነ-ልቦናዊ ጥብቅ ትስስር፣ እንዲሁም የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነ አደሮ መቀበልና መደገፍ ይቻላል” በማለት ፕሮጀክቱን መደገፍ ሊኖረው የሚችለው የጎላ ጥቅም በግልጽ አስቀምጧል።
“ኢሕአዴግ ለምን ይህን የአባይን አጀንዳ አሁን አነሳ?” ወደሚለው ጥያቄ ስንመለስ አንዱ የሚሰጠው መልስ “የሕዝቡን ትኩረት በአረብ አገሮች ከሚደረጉት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማዞር ነው” የሚል ነው። ይህን አይነት አስተያየት የሚያቀርቡ ወገኖች እንዲሁ ስሜታቸውን ከመግለጽ ውጭ ብዙ አሳማኝ መረጃዎች ሲያስቀምጡልን አላየሁም።
ያም ሆነ ይህ ጥያቄዎቹ መሆን ያለባቸው “ኢሕአዴግ ለምን ይህንን ፕሮጀክት ጀመረ? ምንድን ነው ያነሳሳው “የሚሉት ሳይሆን “ይሄ ፕሮጀክት እንዴት ነው ተግባራዊ የሚሆነው? እንዴት ነው በፕሮጀክቱ ሂደት ተጠያቂነትና ግልጽነት የሚረጋገጠው? እንዴት ነው ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ማሳተፍ የሚቻለው? ፕሮጀክቱ ከተገነባ በኋላ እንዴት ነው የሚጠበቀው …?” የሚሉት ናቸው።
ለዚህ ፕሮጀክት ያለኝ ድጋፍና ለፕሮጀክቱ መሳካትም የድርሻዬን ለማበርከት ያለኝ ቁርጠኝነት እየገለጽኩ አንድ በጣም የሚያሳስበኝን ነጥብ ለማንሳት እፈልጋለሁ። ቀድም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ኢሕአዴግ ይህንን ታላቅ ተልእኮ ይዞ መነሳቱ በእጅጉ አስደስቶኛል። ነገር ግን ምን ያህል ተግባራዊ ሊያደርገው ይችላል የሚለው ላይ ግን ትልቅ ጥርጣሬ አለብኝ።
ከላይ እንደጠቀስኩት አቶ መለስ ዜናዊ ይህንን የአባይ ግድብ ሰማኒያ ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ሊገነባው እንደሚችል ገልጸዋል። በርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ይህንን ማድረግ ይችላል። በሕዝቡ አቅም ላይ ጥርጣሬ የለኝም። ነገር ግን ይህንን የሕዝብ አቅም በተገቢው ሁኔታ ማሰባሰቡና ማሰማራቱ ላይ ችግር ይኖራል ብዬ ግን እፈራለሁ።
በቅርቡ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት በውጭ አገር ያለውን ኢትዮጵያዊ አነጋግረው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ተልእኳቸው በተሳካ ሁኔታ እንደተጠናቀቀም የሚገልጹ መግለጫዎችን አውጥተዋል። ነገር ግን ለግድቡ መሥሪያ ከሚያስፍልገው ገንዘብ አንጻር ሲታይ በቂ ድጋፍ ከዳያስፖራው መገኘቱ ግን አጠራጣሪ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት በዋሺንግተን ዲስና በለንደን ስብሰባዎች እንደተበተኑ፣ የልኡካን ቡድኑ ተቃዎሞ አጋጥሞትም እንደነበረም በአንዳንድ ቦታ በሰፊው ተዘግቧል።
አብዛኞቻችን ቦንድ ለመግዛት ለግድቡ መሰራት የሚያስፈለገውን የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁዎች ነን። ተከዜን፣ ግለገል ጊቤንና በለስን እንዲገነባ ያደረገው ኢሕአዴግ፣ አቅሙ ቢኖረው አባይንም የማይገነባበት ምክንያት የለም። በዚያ ላይ ብዝይ ጥራጣሬ የለኝም። በአባይ ጉዳይ ከኢሕአዴግ ጎን ለመሰለፍ እንፈልጋለን። በርግጥ ኢሕአዴግ ይህንን ፕሮጀክት አጠናቆ ባራክ ኦባማ ቢን ላዲንን በመግደላቸው ካገኙት የፖለቲካ ትርፍ አሥር እጥፍ በላይ፣ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ትርፍ ቢያገኝ ግድ የለንም።
ነገር ግን የዚህ ታላቅ አገራዊ አጀንዳ ተባባሪዎች እንድንሆን፣ የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ኢሕአዴግ ሁኔታዎችን ያመቻችልን፣ በሩን ይክፈትለን እንላለን። አብሮ ለመስራት መተማማን ያስፈልጋል። አብሮ ለመስራት መከባበር ይጠያቃል። አብሮ ለመስራት እንደ ወንድማማች መተያየት ይጠያቃል። ኢሕአዴግ ያክብረን፣ እኛም ኢትዮጵያዊያን እንደሆንን ይረዳልን፣ አያስፈራራን፣ አይዛትብን፣ አያዋርደን፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድሞቹ ይቁጠረን እንላለን።
አንድ አባቶቻችን የሚናገሩት መልካም ተረት አለ። “ከፍትፍቱ ፊቱ” ይላሉ። ኢሕአዴግ “የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እየሰራው ነው። አሁን ደግም አባይን ልገነባ ነው” እያለን ነው። በፊታችን የሚያስቆረጥም ፍትፍት አቅርቦልናል። ነገር ግን አብዛኞቻችን ከፍትፍቱ ፊቱ እንላለን። መልካም ፊት፣ መልካምና ጨዋነት የተሞላበት ንግግር የሰውን ልብ በቀላሉ ማሸነፍ ይችላል። የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ትህትና የተሞሉ፣ ከአንደበታቸው መልካም ንግግር የሚወጣቸው፣ ሕዝብን የሚያከብሩ፣ የሚቃወሟቸውን ማሳደድና ማጥፋት፣ በነርሱም ላይ መዛት ሳይሆን፣ የሚቃወሟቸውን ከጎናቸው ለማሰለፍ የሚችሉበትን አቅም ማጎልበት ይኖርባቸዋል።
በመጨረሻ ለአባይ ግድብ ግንባታ መሳካት ካለኝ የጸና ፍላጎት የተነሳ የሚከተሉትን ጠቃሚ የምላቸውን ሃሳቦች በአክብሮት አቀርባለሁ፡
1. ምርጫ ቦርድ በድህረ ገጹ ባስቀመጠው አሃዝ መሰረት፣ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ብዙ ድምጽ ያገኘው፣ አብይ የተቃዋሚ ድርጅት የሚባለውና ብዙ ድጋፍ ያለው ድርጅት የአንድነት ፓርቲ ነው። በሁለተኛነትም ኢዴፓ ይቀጥላል። የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ድርጅታቸው ያለውን ድጋፍ በግልጽ አስቀምጠዋል። የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ስዬ አብርሃም ፓርቲያቸው በምንም መልኩ የአባይ ግድብን እንደማይቃወም ለጀርመርን ድምጽ ራዲዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አብራርተዋል።
እንግዲህ እነዚህ ሁለቱ ድርጅቶች ይህንን ታላቅ ፕሮጀከት የሚደግፉት ከሆነ፣ እነርሱም ኢሕአዴግም ከዚህ በፊት የነበራቸውን የከረረ ልዩነቶች ወደ ጎን አድርገው፣ በጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠው፣ በጋራ እንዴት በዚህ ጉዳይ መስራት እንደሚችሉ በአስቸኳይ መመካከር ያለባቸው ይመስለኛል።ለዚህም ኢሕአዴግ በር ከፋች መሆን አለበት እላለሁኝ።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የአንድነት አመራሮች ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመነጋገር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እነርሱም በፊናቸው መሃከል መንገድ መምጣት ያለባቸው ይመስለኛል። ከኢሕአዴግ ጋር መነጋገር፣ ኢሕአዴግን የሚሰራቸው አንዳንድ ጠቃሚ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በይፋ የመደገፍ ልምምድ ሊኖራቸው ይገባል።
2. ይህ የአባይ ግድብ ግንባታ ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። ኢሕአዴግ በደጋፊዎቹ ብቻ ሊሰራው አይችልም። የሚቃወሙትን ከጎኑ ማሳለፍ አለበት። ለዚህም እንዲረዳ ፕሮጀክቱን የሚመራና የሚያንቀሳቀስ፣ ከኢሕአዴግም ከተቃዋሚዎች የመጡ ባለሞያዎች ያሉበት አንድ ገለልተኛ ኮሞሽን ቢቋቋም በጣም መልካም ሊሆን ይችላል። ይህ ኮሚሽን ጉዳዩ የኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን የአገር ጉዳይ እንደሆነ ከማመላከት ባሻገር በብዙዎች ዘንድ ያለውን የአመኔታ ችግር ሊቀርፍ ይችላል።
3. የሕዝብ በአንድ ላይ መሰባሰብ አስፈላጊነቱን ኢሕአዴግ ተረድቶ፣ ዜጎች በኢሕአዴግ ላይ ካላቸው ቅሬታ አንጻር ከዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ፊታቸውን እንዳያዞሩ፣ በተቻለ መጠን በሰብዓዊ መብትና በዲሞክራሲ ግንባታ አንጻር አስቸኳይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይኖርበታል። የፖለቲካ ተሃድሶ ቁም ሳጥን ውስጥ ተቆልፎበት ብዙ ወደፊት መሄድ የምንችል አይመስለኝም። ሪፖርተር እሑድ ሚያዚያ 9 ቀን 2003 ዓ.ም ባወጣው ርዕስ አንቀጹ ግሩም በሆነ መልኩ እንዳስቀመተው “ በመገደብ(አባይን) ልንሰራ ያሰብነውን ታሪክ ባለመገደብ (ዴሞክራሲን) ታሪክ ሰርተን አናጅበው”[5]
ማን ያውቃል … በዚህ የአባይ ፕሮጀክት ምክንያት የሚፈጠረው መቀራረብ የአገራችን ኢትዮጵያን ትንሳዔ ሊያፋጥን ይችላል።
[1] http://www.ethiomedia.com/andnen/2466.html
[2] http://www.ginbot7.org/pdf/Dr_Berhanu_Nega_Speech__Atlanta_April_2011.pdf
[3] http://www.ethiomedia.com/andnen/blue_nile_vs_egypt.pdf
[4] http://ethioforum.org/wp-content/uploads/2010/12/Awramba_Times_Issue_145.pdf
[5] http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/1731-2011-04-17-07-25-46.html
ግርማ ካሣ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ግንቦት 4 ቀን 2003 ዓ.ም.



