ነፃነት ዘገዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

"… የምግብ ዘይት እንኩዋን በአቅሟ ሜርኩሪ ስትሆን ምን ይዋጠን? በደርግ ጊዜ በሊትር ሦስትና አራት ብር ትሸጥ የነበረች ከምን እንደተሠራች እንኳን በውል የማትታወቅ አንዲት ሊትር ተራ ዘይት ዛሬ በነፃ አውጫችን በጎብላላው ኢህአዴግ ዘመን ሰባ ብር ላይ ወጥታ ቂብ ስትል ምን ይባላል? በ‘ጨቁዋኙና ሰው በላው’ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሃያ ሣንቲም ይገዛ የነበረ ማለፊያ ጠረን ያለው አንድ የጣሊያን የልብስ ሣሙና ዛሬ በ28 ብር ሲገዛ የፀሐዩን መንግሥታችንን የኢሕአዲግን ዕድሜ ያርዝምልን ከማለት ውጪ ምን እንላለን? …" 

 

“የ… ዕድር አባላት የሆናችሁ ሁሉ እሁድ ግንቦት 14 (2003 ዓ.ም.) አስቸኳዋይ ስብሰባ ስላለ ከጥዋቱ 12፡00 ሰዓት ላይ በስብሰባው ሥፍራ እንድትገኙ የአመራር ኮሚቴው በጥብቅ ያሳስባል። ልጅ መላክ አይቻልም፤ የቀረ ሰው 10 ብር ይቀጣል።”

 

ይህ የስብሰባ ጥሪ የተደረገው ከሰዓታት በፊት ነው - ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል። የጥሪው ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ጥቂት አሰብኩ። የዕድር አመራር አባላት ምርጫ እንዳይባል ቅርብ ጊዜ ነው የነበሩትን አፅድቀን በጎደሉትም ተክተን የተለያየነው፤ የወር ክፍያ እንዳይባል ያለፈው ሣምንት እሁድ ከፍለናል - ሕጉ ወር በገባ የመጀመሪያው እሁድ ስለሚል። ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል? ሄዶ ማዳመጥ ነዋ!

 

ስብሰባ በተፈጥሮየ አልወድም፤ በጭራሽ! ለዕድር ክፍያም ከትንንሾቹ ልጆቼ አንዱን ነው የምልከው - ስብሰባ ከሆነም ሸዋርካብ ትሳተፋለች እንጂ እኔ ዝር አልልም። ልቅሶ ግን እደርሳለሁ፤ ሁዋላ እኔንስ ማን ይቀብረኛል? ‘ብድር በምድር አይደል?’

 

ለሌሎች ጉዳዮች በሌለኝ ያለወትሮነት ማለድ ብዬ ተነሳሁና ወደተባለው የስብሰባ ቦታ አመራሁ። ስብሰባው ተጀመረ። ነገሩ ስለአባይ የኅዳሴ ግድብና ስለግንቦት ሃያ በዓል አከባበር ሁኔታ ሆነና ዕድራችን የማኅበረሰባዊ አገልግሎት መስጫ መሆኑ ቀርቶ የኢህአዴግ ሥውርና ግልጽ ካድሬዎች መፈንጫ ሆኖ ዐረፈው። ዓይን ላለመግባት እኔ ብዙም አልተናገርኩም። ሌሎች አባላት ግን ስሜታቸውን እንደጉድ ያወርዱት ገቡ።

 

ክፍያውን በሚመለከት ሕዝቡ አለ፤ “በስንቱ አቅጣጫ ነው ገንዘብ የምንጠየቀው? በመሥሪያ ቤት ደምወዛችን እየተቆረጠ ነው፤ በትምህርት ቤት ልጆቻችን ‘ቦምብ’ ግዙ ተብለው በዚያም በኩል አዋጥተናል። በዕድር ግን በፍፁም ልናዋጣ አይገባም። በግድ አምጡ ተብለን ከተገደድንም ከኪሳችን ሳይሆን ከዕድር ተቀማጭ የተጠየቅነው ገንዘብ ወጪ ሆኖ ይከፈል። ኑሮውን አልቻልነውምና ለኛም ይታዘንልን። …” [በጥቅሱ ውስጥ በአርትዖት ችግር ነውና ‘ቦምብ’ የተባለው - እባካችሁ ‘ቦንድ’ በሚለው ተስተካክሎ ይነበብልኝ]

 

ሕዝቡ ተራ በተራ ምሬቱን ሲገልጽ የአድማጭን ቀልብ የሚስብ ነበር። በርግጥም በተለይ የሰሞኑ ኑሮ በጣም ይዘገንናል። የምግብ ዘይት እንኩዋን በአቅሟ ሜርኩሪ ስትሆን ምን ይዋጠን? በደርግ ጊዜ በሊትር ሦስትና አራት ብር ትሸጥ የነበረች ከምን እንደተሠራች እንኳን በውል የማትታወቅ አንዲት ሊትር ተራ ዘይት ዛሬ በነፃ አውጫችን በጎብላላው ኢህአዴግ ዘመን ሰባ ብር ላይ ወጥታ ቂብ ስትል ምን ይባላል? በ‘ጨቁዋኙና ሰው በላው’ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሃያ ሣንቲም ይገዛ የነበረ ማለፊያ ጠረን ያለው አንድ የጣሊያን የልብስ ሣሙና ዛሬ በ28 ብር ሲገዛ የፀሐዩን መንግሥታችንን የኢሕአዲግን ዕድሜ ያርዝምልን ከማለት ውጪ ምን እንላለን?

 

ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት እንኳን እነሸዋርካብሽ ኪሎውን በሁለትና ሦስት ብር ይገዙት የነበረው የባቄላና የአተር ድብልቅ የሽሮ እህል ዛሬ 30 ብር ሲገባ፤ “መለስን ለዘላለም ያኑርልን!” ከማለት በስተቀር ሌላ ምን አማራጭ አለን? የወያኔያዊ ድሎቻችን ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም። ይህን ድል ያመጣልንን ወያኔ ስንመርጥ ታዲያ ይታያችሁ ውድ ምዕመናን - ሊያውም በ99.57% የ‘ሕዝብ’ ድምፅ! ዓለም የቀልድ ምድር ናት፤ እንደተቀለደ መኖር ሱሚ መሆኑ በነጋዳፊና ሙባረክ ለሚሊዮንኛ ጊዜ መረጋገጡ ለነመለስ አስደንጋጭ የወቅቱ ዜና መሆኑ ከፋ እንጂ። አዎ! በሰፈሩት ቁና መሠፈር ዛሬ አልተጀመረም። መለስና ቢጤዎቹ - በተቃዋሚነት ተሰልፈናል የሚሉትንም ወገኖች ጨምሮ - በየትኛውም ጎራ የሚገኙ ሕዝብን አስለቃሽ የታሪክ ዝቃጮች ፍርዳቸውን የሚያገኙበት ወቅት ሩቅ አይደለም። የማይነጋ መስሎኣቸው ሌት ከቀን በሚያወርዱብን መብረቃዊ የመቅሰፍት ውርጅብኝ ለጊዜው የተሰባበርን ብንመስልም የመዳኛችን ዘመን በቅርብ ሲብት እነሱም በተራቸው የመክሊታቸውን ጽዋ አለውድ በግዳቸው ይጎነጫሉ።

 

ወደ ስብሰባችን ልመለስ። ካድሬዎቹ በዕድራችን መድረክ ማዘዝ መናዘዛቸውን ቀጥለዋል። አንዱ ቀጠለ፤ “የፊታችን ቅዳሜ ለኅዳሴ ግድባችን መሠረት የሆነው የግንቦት 20 ቀን ለ20ኛ ጊዜ በደመቀ ሁኔታ የሚከበርበት ዕለት ነው። ለዚህ በዓል ስኬት በሕዝብና በመንግሥት ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው። እናንተም የበዓሉ አካል እንደመሆናችሁ በዕለቱ ግንቦት ሃያን በማስመልከት ለታላቁ የሚሌኒየም ግድብ ድጋፋችንን የምንገልጽበት አጋጣሚ በመሆኑ በመስቀል አደባባይ ሠልፍ እንድትወጡ ከዕድር አመራሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል። …”

 

ትንታጉ ወጣት ካድሬ የአባላትን ይሁንታና ድጋፍ ለማግኘት ተፍጨረጨረ። ነገር ግን ከዝምታ ውጪ ያገኘው ነገር አልነበረም። ማን ሠልፍ እንደሚወጣና እንደማይወጣ ገና ከስድስት ቀናት በኋላ የምናየው ይሆናል። እስከዚያው በደህና ያሰንብተን። ፈጣሪያችን በመንግሥቱ ያስበንና በጉጉት የምንጠብቃቸው፤ ነገር ግን እንደተረገዙ ውሳጤያዊ መንፈሣችን የሚነግረን ሕዝባዊ አርበኞች በአፋጣኝ እንዲወለዱ፣ የተጠማነውንም የነፃነት ጠበል እንዲያጠጡን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። እኛም የየድርሻችንን ለማበርከት ዝግጁ ሆነን እንጠብቃቸው። ማመን ካለማመን የበለጠ ዋጋ አለውና ተስፋ ቆርጣችሁ በየሥርጉዋጉጡ ተደብቃችሁ የምትኖሩ ወገኖች በፈጣሪ ሥራ አትጠራጠሩ። የነፃነታችን ጊዜ ቀርባለች። ለመድረስ የሚፈጅባት ጊዜ እኛ እኛን ለማስተካከልና በኀሊዮም በገቢርም ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የሚፈጅብንን ጊዜ ያህል ነው። ያንን ጊዜ ደግሞ ከፈለግን ዛሬና አሁን ልናደርገው እንችላለን። ከየገባንበት የራሳችን ሥሪት የሆኑ ትንንሽ ዓለማት ወጥተን ሰፊ አደባባይ ላይ መገናኘት ነው ዋናው አብነት። ከሰውነት ተራ ያወጡንን አጉል ባሕርያት ረግመን ሰው መሆን ነው መፍትሔው።

 

ኢትዮጵያ ሰው አጥታለች እሚባለው በአካለ ሰው የሚንቀሳቀስ ግዑዝ ሰው መሳይ በሸንጎ ሳይሆን ራሱን በመልካም ምግባር አስገዝቶ ለሌሎች አርኣያ የሚሆን የሕዝብ አመኔታን ሊያተርፍ የሚችል ሰው (Iconic Figure) አጥታለች ማለታችን ነው። (የጭፈራ ቤቶችንና ‘መዝናኛ’ ሥፍራዎችን ስናይ በርግጥም የኢትዮጵያ ማኅፀን እንደመከነ እያለቀስን እንረዳለን፤ ዝርዝር ውስጥ መግባት አይገባም እንጂ - የንዋይ ብዛት እያነሆለላቸው ዕድሜያቸውን ፍፁም በመርሳት ስንትና ስንት ‘ታዋቂ’ዎቻችን የገቡበትን የውርደት አዘቅት ስናይ እንደሀገርና እንደሕዝብ ያልታደልን መሆናችንን እናስታውሳለን፤ ‘ሁሉም በኃጢያት ሥር ወድቋል’ የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል በገሃድ እየታየ ነው። ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከኃይማኖት ቁንጮው እስከ ተራው ዲያቆን፣ ከሀገር መሪው ትልቁ ባለሥልጣን እስከተራው ካድሬ ሁላችንም በመለስኛ ቋንቋ ‘በስብሰናል’። ፈጣሪ በፀጋው እንዲጎበኘን እባካችሁ እግዚኦ እንበል።)

 

እንግዲያው ለሰው ለሰውማ እንደሚባለው ከሆነ ከ85 ሚሊዮን በልጠን የለም? እናም በጎሣና በጎጥ መከፋፈልን፣ በኃይማኖት ሰበብ መናቆርን፣ በሞራል መዝቀጥን፣ በአፍቅሮተ ንዋይ መታወርን፣ መረን በለቀቀ የወሲብ ድርጊት መሰማራትን፣ ከጋራ ብልጽግና ይልቅ በግለኝነት የራስ ወዳድነት ልክፍት መጠመድን፣ … በተውን ማግሥት በፈጣሪ ጥላ ሥር ሆነው የእርሱን ትዕዛዝ ብቻ እየተጠባበቁ ያሉት የነፃነት ቀንዲል አብሪ አርበኞቻችን ባልተጠበቀ ወቅት ካልጠበቅነው አቅጣጫ ወደኛ ይመጣሉ። ራሳችንን በማስተካከሉ ሂደትም የሚሳነው ነገር የሌለው እግዚአብሔር/አላህ ይርዳን። አሜን!!


ነፃነት ዘገዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!