ሉሉ ከበደ (ካናዳ)

      

ቀደምት የሐገራችን አንባገነኖች ሕዝባችንን ሲገሉና ሲያስሩ ሲያሰቃዩ የነበረው  ባብዛኛው ስልጣናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ መሆኑ ብዙም የሚያከራክረን አይደለም።  አሁን ያሉት ግን ለስልጣንም፤ ለገንዘብ፤ ለሐብትም ሖኗል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለፉት ሀያ ዓመታት መብቱ ተገፎ፤ ሰብእናው ተረግጦ፤ ተከፋፍሎ፤ ታስሮ፤ ተገሎ፤ ተዘርፎ፤ ለህይወቱና ለንብረቱ፤ ለስራው፤ ለኑሮው ዋስትና አጥቶ፣ ፈርቶ፤ ተጨንቆእንዲኖር የተደረገበት ዘመን ቢኖር አሁን ነው።

 

        ከአርሶ አደሩ እስከ ምሁሩ፤ ከነጋዴው እስከ መንግስት ሰራተኛው፤ መለዮለባሹን ጨምሮ፤ ኢትዮጵያውያን ከመቸውም ስርዓት በከፋ ሁኔታ ተነጣጥለው እየተጠቁ፤ ከወደቁበት እንዳይነሱ በሚል የጠላት እቅድ እየተመቱ ያሉበትና ተዋርደው  የኖሩበት ጊዜ ሀያ ዓመታትን አስቆጠረ።

      ገበሬው ለሚያርሳት ኩርማን መሬት፤ ለሚበትናት ዘር፤ መጀመሪያ የወያኔ ደጋፊ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። የወያኔ ነጋዴዎች አራሹ ቢያስፈልገውም  ባያስፈልገውም  ማዳብሪያ በእዳ እያራገፉበትየአዝመራ ወቅት ሲደርስ ከልጆቹ አፍ ነጥሎ፤ ሸጦ፤ እንዲከፍላቸው ያስገድዱታል። ከሌለውም የርሻ በሬ ሸጦ እንዲከፍላቸው ያደርጉታል። እንቢ ካለም ያስሩታል። ሰብሉን በእዳ ነጥቀውት ልጆቹን የሚመግበው ሲያጣ፤ የምግብ እርዳታ ለማግኘት መጀመሪያ የኢህአደግ ደጋፊ መሆኑ መረጋገጥ አለበት።  ተቃዋሚዎችን የሚደግፍ መሆኑ ከተመሰከረ የሚደግፋቸውን ወገኖች እርዳታ እንዲጠይቅ ተነግሮት ከረሀብተኛ ልጆቹ ጋር ወደመጣበት እንዲመለስ ይደረጋል። የምግቡን እርዳታ የሚያቀርቡት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ናቸው

     ነጋዴው፤ ከልጅነት እስከ እውቀት ጥሮ ግሮ ሰርቶ፤ አፈር ልሶ ተነስቶ፤ የደረጀ የከበረውን ጎበዝ ሁሉ የወያኔ ባለስልጣናት ንግዳቸውን የሚሻማ  የሚፎካከር መስሎ ከታያቸው የፈጠራ፣ የሀሰት ወንጀል እየደረደሩ፤ ፍቃድ እየነጠቁ፤ ድርጅቱን እያዘጉ፤ ስራውን ንብረቱን ይቀሙታል።

     የመንግስት ሰራተኛው እውቀቱ፤ የትምርት ደረጃው፤ አገልግሎቱ  የሚፈቅድለትን የስራ እድገት፤ የትምህርት እድልም ሆነ ጥቅማጥቅም የማግኘት መብት የለውም፤ የወያኔ ደጋፊ፤ ተላላኪ፤ ጆሮ ጠቢ ካድሬ፤ ካልሆነ በስተቀር። እንዳሁኑ በከፋ ሁኔታ ባይሆንም ይህን አሰራር ደርግም ሲጠቀምበት ነበር። በኢትዮጵያ የሚኖር ሰው ሁሉ ኢሰፓ እንዲሆን ተፈልጎ ነበረ። አሁን ደግሞ ኢህአደግ እንዲሆን።

      የዩኒቨርስቲ ተማሪው ትምሕርቱን ጨርሶ የደከሙ ወላጆቹን ለመርዳት ለመጦር በሚጓጓበትና በሚዘጋጅበት ሰዓት  ለወያኔ ታማኝነቱና አገልግሎቱ እምን ድረስ እንደነበረና እንደሚሆን እየታየ ስራ እንዳይቀጠር ይደረጋል ።

     መለዮ ለባሹ የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉአላዊነት ለመጠበቅ ሳይሆን፤ የሌላ ሀገር መንግስት ትእዛዝ ለመፈጸም፤እንደግል አሽከር የትም ለጦርነት እየተላከ ሲሞት፤ ላገልግሎቱ የሚከፈለውን ገንዘብ ወያኔ እየተቀበለ ወደካዝናው ይከታል። “መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም “ እንደተባለው ጦሩም ዝም።

     በሀገራችን የሰፈነው የሀይል አገዛዝ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፤ በህውሀት የኢኮኖሚ ክንፍ የበላይነት በሶስት ሀይሎች ቁጥጥር ስር አውሎታል። የመጀመሪያው የራሱ የወያኔ ንግድ ድርጅት የሆነው የትግራይ ኢንዶውመንት ፈንድ የተባለው ክንፍ ፤ በስሩ ልዩ ልዩ ክፍሎችን አደራጅቶ፤ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ ግንባታና ኢንጅነሪንግ፣ ፋብሪካ፣ ማዕድን፣ በትራንስፖርት መስክ፤ ሆቴልና ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶች፤ በሀገር ውስጥ ገቢና ወጪ ንግድ፤ ባጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የተቆጣጠረ ሲሆን ሁለተኛው ሀይል የሼክ መሀመድ አላሙዲን ሜድሮክ ኩባንያ እንደ ወያኔው ድርጅቶች እስከ ሽሮና በርበሬ ችርቻሮ ወርዶ የህብረተሰቡን ስራ ባይቀማም ከወያኔ ጋር በመደጋገፍ በሁሉም የኢኮኖሚ መስክ ተሰማርቷል። ሌሎቹ በወያኔ ራዳር ስር እየተንቀሳቀሱ እየተጠቀሙ የሚጠቅሙ የቻይናና የሌሎች ሐገር ኩባንያዎች እንዳሉ ሆነው ሶስተኛውና አስፈሪው ሐይል ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት፤ ለሀገር ውስጥ ፖለቲካ፤ ለዜጎች መብትና ደህንነት፤ ለኢትዮጵያ ተፈጥሮ ጥበቃ፤ ለአፈሩ፤ ለውሀው፤ ለኢኮሎጂው፤ ለደኑ  ለአራዊቱ ጭርም ሆነ የረጅም ጊዜ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ በወያኔ ፍቃድ የኢትዮጵያን የእርሻ መሬት በክፍለ ዘመን ኮንትራት እየተቀራመቱ ያሉት ሀይሎች ናቸው።

     አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፖለቲካውም  ከኢኮኖሚውም ጨዋታ ውጭ ተደርጎ፤ የበይ ተመልካች በመሆን ላይ ይገኛል። ከንግዲህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የሀብት ባለቤቶች ወያኔና ይጠቅሙናል ብለው ከውጭ የሚያሰገቧቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ናቸው ።

    ይህ ግልጽነት የሌለውና ጥድፊያ የተሞላበት የእርሻ መሬት ሽያጭ፤ የክልሉን ነዋሪዎች፣ የኢትዮጵያን ህዝብ፣ ሐገር ወዳድ ምሁራንን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ሀገራችን ነች፤ ይመለከተናል  የሚሉ ወገኖች አንዳቸውም ያልተጋበዙበት፤ ያልመከሩበት፤ አንድ ሺ ስድስት መቶ ኪሎ ሜትር የሀገር ዳር ድንበር ግዛት ተቆርሶ ለሱዳን ሲሰጥ ወያኔ ማንንም እንዳልፈራና ምንምም እንዳልደረሰበት ሁሉ ይህንንም ወንጀል በማናለብኝነት ብቻውን እየፈጸመው ይገኛል።

   ወያኔ እነዚህን ባለሀብቶች በከፍለ ዘመን ኮንትራት እየጠራ ሀገር ውስጥ ሲያቆናጥጣቸው የራሱ የሆነ የረጅምና  የአጭር ጊዜ ግብ አለው። በአጭር ጊዜ ግ ፤ መሬቱን ቶሎ ቶሎ በርካሽ እየሸጠ በሚያገኘው ቢሊዮን ብር ራሱን በስልጣን ላይ ያጠናክራል። ሕዝቡን ለማፈን ይጠቀምበታል። በረጅም ጊዜ ግቡ ከነዚህ ሀብታም ሀገሮች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፤ የወታደራዊ ድጋፍ ይገዛበታል። ወያኔ ለራሱ ወዳጅ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት እያፈራ ነው ።

     ለሀገሩ የቆመ መንግስት ባለበት፤ የእርሻ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ወደ ሀገር ሲገቡ፤ ብሄራዊ ጥቅምን በተመለከተ ህዝብና መንግስት የሚነጋገሩባቸው ዋና ዋና ነገሮች፤ እነዚህ ባለሀብቶች ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ ጥቅም ያለው ምን አዳዲስ ቴክኖሎጂ ይዘውልን ይመጣሉ? ለዜጎች ምን ያህል የስራ እድል መፍጠር ይችላሉ? ከሚያመርቱት ምርት ምን ያህሉን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ያቀርባሉ? በምን አይነት ዋጋ?፣ ምን ያህል የሰለጠነ የሰው ሀይል ሊያፈሩልን ይችላሉ? ምን ያህል መንገዶችንና ክሊኒኮችን፤ ትምህርት ቤቶችን በአጠቃላይ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በምን ያህል ፍጥነት ሊያስፋፉ ይችላሉ? በተፈጥሮ ጥበቃ፤ ደንና ዱርአራዊት፤ በውሀ አጠቃቀም፤ ለተባይና ለማዳበሪያ፣  ለአረም ማጥፊያ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች መሬቱን እንዳይመርዙ፤ እንዳይበክሉ፤ የሚሰጣቸው ግዴታና መመሪያ ምን መሆን አለበት? መመሪያ ካልተከተሉ፣ ውል ከጣሱ ሕብረተሰቡም ሆነ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ምን መሆን አለበት? ያካባቢው ዜጎች ባለሀብት የሆኑትን በማደራጀትም ሆነ በሌላ መልኩ ከባለሀብቶቹ ጋር በባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸውና አብረው እንዲስሩ ምን መደረግ አለበት? በጥቂቱ እነዚህ ጉዳዮች በግልጽ ባደባባይ ከዜጎች ጋር ሊመከርባቸው የሚገባ ነበር። ወያኔ ግን እንዱንም አላደረገውም።

  ገዢው ቡድን ሐገሪቱ በምግብ እህል እራሷን እንድትችል፤ የስራ እድል ለመፍጠር መፍትሄው ይህ ነው እያለ ነው የሚያስወራው። በዘመናዊ መሳሪያ የሚከናወን የንግድ እርሻ ድርጅት በየትም ዓለም ታች ላለው ድሀ አርሶ አደር የስራ እድል የፈጠረበት ሐገር ታይቶ ተሰምቶ አይታወቅም። አርሶ አደሩ ራሱን እንዲችል ለማድረግ ቅን ልቦና ካለ  አቋራጭ መንገድ  መሬቱን በባለቤትነት ለአራሹ መስጠት። ከዚያ በሗላ እርዳታና ድጋፍ እያደረጉ፤ ባነስተኛ ወለድ ብድር የተሻሻለ የርሻ መሳሪያ የሚያገኝበትን መንገድ እየፈለጉ ዘመናዊ ያስተራረስ ዘዴ እያስተማሩ፤ እዚያው መሬቱ ላይ ያለውን ዜጋ ማሳደግ ነው እንጂ ድሀውን እያፈናቀሉ መሬቱን በመሸጥ አይደለም ገበሬው እራሱን የሚችለው። ገበሬው አንዲት ሄክታር መሬት ብትኖረው የበለጠ ስራና ሕይወት ይኖረዋል። ከ 1966 ጀምሮ ስንጮህለት የነበረው መሬት ለአራሹ ጥያቄ እስከ አሁን አልተፈታም ። እነዚህ አሁን በዝርፊያ ላይ የተሰማሩትም ሰዎች እኮ መሬት ላራሹ ይሉ ነበር።

    በቅርቡ ወደ ጋምቤላ ሄዶ የነበረ የቢቢሲ ጋዜጠኛ የመለስ ዜናዊ መንግስት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በሊዝ ለመሸጥ ተዘጋጅቷል። የዚህም መሬት ልክ ቤልጅየም የምተባለውን አገር የቆዳ ስፋት ያህላል ሲል ጽፎ ኪራዩም  በአመት አስር ዶላር ብቻ እንደሆነ አትቶ ነበር። የዚያው አካባቢ ነዋሪ ለጋዜጠኛው ሲናገሩ “ስለመሬት ጉዳይ ባሁኑ ጊዜ እንደፈለክ መናገር አትችልም። ወይ ትገደላለህ ወይ ትታሰራለህ።” ብለው ነበር። በርግጥም በዚሁ ምክንያት በጋምቤላ ውስጥ አስር ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መታሰራቸውን የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ማመልከታቸው ይታወሳል ።

     መሬትን የመቸብቸቡ ፖሊሲ ዒላማ ያደረገው በአፋር የአዋሽን ሸለቆ፤ በምዕራብና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ ቆላማ መሬት፣ እንዲሁም በኦሮሞ ክልሎች ያሉ ለም መሬቶችን ያጠቃልላል። በክልሉ በርካታ ክፍለ ህዝቦች ይኖራሉ። የወያኔ መንግስት በተለመደ ውሸቱ በህዝቡ ላይ አንዳችም ጫናና ጭቆና አላደረስኩም ባይ ነው። ነዋሪዎቹ ደግሞ ለዓለም መገናኛ ብዙሀን ብሶታቸውን ሲያሰሙ፤  የአርቢነት ባህላዊ ልምዳቸውና የአኗኗር ዘዴያቸው ከትውልድ ትውልድ እየተወራረስ የመጣው የኑሮ ወግ በሀይል ሊያከትም መሆኑ ያስፈራቸዋል። አንድ አዛውንት እንዳሉት “ልምዳችንንና ባህላችንን ልናጣ ነው። ለተተኪው ትውልድ የምናስተላልፈው ነገር አይኖርም። የዛሬው ሕይወት ለልጆቻችን በወሬ ብቻ የምንነገረው ታሪክ ይሆናል ብየ እፈራለሁ”  ማለታቸው ተጽፏል።

    ጋምቤላን የወረሩት ባለሀብቶች አብዛኛዎቹ ቻይናውያን፤ ሕንዶች እና የሳውዲ አረቢያ ቱጃሮች ናቸው:፡ የሳውዲ ሀብታሞች እንደሚሉት በዓመት በሚሊዮን ቶን የሚገመት ሩዝ ለራሳቸው የውስጥ ፍጆታ የሚውል እንደሚያመርቱ ተስፋ አላቸው። ሳውዲ ስታር የተባለው የእርሻ ድርጅት በሚቀጥሉት አምስት አመታት 100 000 ሔክታር የሚሆን መሬት ባለቤት እንደሚሆን አረጋግጧል።

    ሌላው ወደ ጋምቤላ ሄዶ የነበረ ዘ ጋርዲያን የተባለ በንግሊዝ አገር የሚታተም ጋዜጣ ዘጋቢ ካራቱሬ የተባለው የሕንድ የርሻ ድርጅት ተወካይን ሲያናገር ሰውየው፤  “የክፍለ ዘመኑ ርካሽ የስምምነት ዋጋ ነው” በማለት ነበር እየተኩራራ የመለሰለት። “150 ፓውንድ በሳምንት ከፍለህ 2500 ስኩየር ኪሎሜትር በላይ ወይም 1000 ስኩየር ማይልስ ስፋት ያለው ለምና ድንግል የርሻ መሬት፤ መሬቱ ከታክስ ቅናሽ ጋር ሲሰጠኝ የት ቦታ እንዳለም አላየሁት ብሎ ተናግሯል። “በህንድ አገር እንደዚህ አይነት መሬት የለንም። አንድ ፐርሰንት የተፈጥሮ ለምነት ያለው መሬት ካገኘህ እድለኛ ነህ። እዚህ መሬቱ ካምስት በመቶ የበለጠ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አለው ።ማዳበሪያም ሆነ የተባይ ማጥፊያ መጠቀም አያሻንም። በመሬቱ ላይ አንድም የማይበቅልበት ነገር የለም።” እያለ በኩራት ይናገር ነበር።

አነስተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ጋምቤላ ርካሽና ለም መሬት ለማግኘት የሚሽቀዳደሙ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ትኩረት ሆናለች። በ 2007/2008 ባልተጠበቀ ሁኔታ ድንገት የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ በርካታ ሐገሮች በምግብ እጥረት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። ህንድ ህዝቧን መመገብ የማትችልበት ደረጃ ላይ ተቃርባለች። ቻይናም ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ሳውዲ አረቢያና የመካከለኛው ምስራቅ ቱጃር አረቦች የእርሻ መሬትና የውሀ ችግራቸው እንዳለ ሆኖ ምግባቸውን ከሕንድና ከሌሎች የእስያ ሀገሮች ነበር የሚያስገቡት፤ እነዚያ ሀገሮች አሁን ለራሳቸው ተጨማሪ ምግብ ፈላጊ በመሆናቸው የሁሉም ትኩረት “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል “ እንደተባለው ሩጫው ወያኔ እንደፈለገ መሬቱን እየሸነሸነ ወደሚሸጥበት ሀገር ኢትዮጵያ ሆኗል ።

    መንግስት እንደሚለው 36 የሚሆኑ ሐገሮች ከኢትዮጵያ የእርሻ መሬት ገዝተዋል። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ግን አንዲት ጋት መሬት የለውም። መሬት የሚኖርበት ሕዝብ ንብረት ነው መሆን ያለበት።

    የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባለሙያዎችንና ያካባቢውን ነዋሪዎች በሚያሳዝን ሁኔታ ደኖች በብዙ መቶ ሰኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት እየተጨፈጨፉ፤ እየተቃጠሉ ነው። ብዛት ያላቸው የዱር አራዊት እና አእዋፍ መድረሻ እያጡ ወደ ጎረቤት አገሮች በመሸሽ ላይ ናቸው። የሁሉም እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፤ በማይረዱት ሁኔታ መኖሪያ ቦታቸውን የማይከላከሉት ባላንጣ ሲያወድምባቸው፤ አእላፍ የኢትዮጲያ ዱር አራዊት ጠባቂም ባለቤትም አልባ ሆነዋል።

   የመንግስቱ ባለስልጣናት የአካባቢውን ነዋሪዎች እያስገደዱ እንደሚያስለቅቁ ለውጭ መገናኛ ብዙሀን ውሸት ይናገራሉ። ይክዳሉ። አቶ ካሳሁን ዘርፉ የተባለ የወያኔ ሹመኛ ዘጋርዲያን ለተባለው ጋዜጣ ሲናገር “መሬቱን ለባለሀብቶች ለመስጠት አይደለም ነዋሪዎቹን ወደ ሌላ የምናሰፍራቸው፤ በአካባቢው ምንም የመሰረተ ልማት አውታር የለም፤ ስለዚህ በፍቃደኝነት ነው ወደ ሌላ አካባቢ የምናሰፍራቸው። ትምህርት ቤት፣ ንጹህ ውሃ፣ ሕክምና፣ የመኪና መንገድ  አገልግሎት ሊያገኙ ወደሚችሉበት አካባቢ ነው የምናንቀሳቅሳቸው። የነዋሪዎቹ መልሶ መስፈርና የባለሀብቶቹ ወደ ክልሉ መምጣት ሳይታሰብ የተገጣጠመ ነው ” በማለት ዓለምን በሀሰት ወሬ ለማወር ሞክሯል ።

   ተፈናቃዮቹ ደግሞ ለዚያው ጋዜጣ ተጨባጩን ነገር ሲናገሩ፤ ለንብረታቸው ማካካሻ ይሰጣችሗል ጠብቁ እንደተባሉና ባዲሱ ሰፈራ እየጠበቁ እንዳሉ ይመሰክራ ። “ትምህርት ቤት እንደሚሰራልን ቃል ተገብቶልን ነበ ። ክሊኒክ፣ ንጹህ ውሃ፣ ይኖራችኋል ተብለን ነበር። ከስምንት ወር በፊት። እስካሁን አንድ የውሀ ፓምፕ ብቻ ነው ያለን “  250 ነዋሪዎች ያሉት አዲስ የሰፈራ መንደር ነዋሪዎች ተወካይ ነበር ይህን ለጋዜጠኛ የተናገረው።

  ሌሎችም እንደዚሁ ለባለሀብት ከተሰጠ መሬት ላይ የተፈናቀሉ ስለ ድርጊቱ ቅሬታቸውን ቢገልጹ ለህይወታቸው እንደሚፈሩ ያመለከቱ ሲሆን ማብቂያ ከሌለው የወያኔ ባለስልጣናት ውሸት የግብርና ሚኒስትሩ “ህዝብን ከቦታ ቦታ የማዘዋወር ተግባር የለም። መሰረታዊ አገልግሎት ማግኘት ምርጫቸው  ነው። ግን ቀደም ሲል የነበራቸውን አኗኗር መተው አለባቸው “ እያሉ ሀሰት ይነዛሉ።

       በሌላ በኩል ስለነዋሪው የወደፊት እድልና መብት ሲጠየቁ  በሚሰጡት መልስ የሚሸጡት መሬት ስራ ላይ የማይውልና ሰው ያልሰፈረበት እንደሆነ ያወራሉ። መሬቱ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ነው ሕዝቡ የሚናገረው። በአብዛኛው የሚጠቀሙበት የክልሉ ከብት አርቢዎች ናቸው። በአካባቢው በአራት ሚሊዮን የሚገመት ቁጥር ያላቸው አርብቶ አደሮች ይኖራሉ። በብዙ ሺ ማይልስ አገር እያቋረጡ ለከብቶቻቸው ግጦሽና ውሃ ባገኙበት ይሰፍራሉ። መሬቱን ለልዩ ልዩ አገልግሎት ይጠቀሙበታል። ለእርሻ ፣ ለአደን፣ አንዳንዴም ረሀብ ሲከሰት ፍራፍሬ ይለቅማሉ። አንድ ነዋሪ እንዳሉት ስራና ታሪክ የሌለው መሬት በጋምቤላ የለም። በሁኔታው የተቆጡ ሌላ አዛውንት “መሬት መሸጥ አይችሉም። የነርሱ መሬት አይደለም። መሬቱ ያያት የቅድም አያቶቻችን ነው። “ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

    በጋምቤላ አብዛኛው የሊዝ እርሻ የታቀደው ለሩዝና ለሸንኮራ አገዳ ተክል ሲሆን ሁለቱም አዝርእት ውሃ ከሚገባው በላይ የሚፈልጉ ናቸው። ክልሉ የዝናብ እጥረት እንደሚያጋጥመው እየታወቀ ባለሀብቶቹ ከየወንዞቹ መጠቀም የሚችሉት የውሀ ልክ አለመገደቡን ይናገራሉ።

    በአፋር ክልል በቅርቡ ወያኔ 88 ያፋር ሽማግሎችን ሰብስቦ መላውን የአዋሽ ሸለቆ የሸንኮራ አገዳ ተክል ለሚያለሙ የውጭ ሰዎች ሊሸጠው ስለሆነ መልቀቅ እንዳለባቸው ሲያስጠነቅቅ፤ አፋር ኑሮው የተመሰረተው በከብት እርባታ ላይ ስለሆነ መሬታችን ከተያዘ እንዴት እንሆናለን በማለታቸው በአሳይታና በዱብቲ 200 ዜጎች ታስረዋል። በገዋኔ አካባቢ ይህንኑ በመቃወማቸው 60 የሀገር ሽማግሌዎች ታስረው በመሰቃየት ላይ ናቸው። የአፋር ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጩኸቱን ለዓለም ሰብዓዊ መብት፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅቶች እያሰማ ይገኛል።

   መሬትን በሊዝ የማከራየት ጉዳይ ውስብስብ ያለና አፈጻጸሙም ላይ አለመግባባቶችን እንደሚያስከትል የዓለም ባንክ ማስጠናቱ ተጽፏል። በጥናቱ መሰረት አሉታዊም አዎንታዊ ጎኖችም አሉ። የሊዝ ሽያጭ ላቲን አሜሪካ ውስጥ መልካም ስኬት አሳይቷል። በአፍሪካ ውስጥ ግን የሚያሳየው በጎ ነገር ትንሽ ነው። ብዙ የሊዝ ፕሮጀክቶች ያቀነጃጀትና ያደረጃጀት ችግር ስላለባቸው የታሰበውን ያህል ጥቅም አያመጡም:: መንግስትና የሲቢል ተቋማት ትክክለኛውን አሰራር ግልጽ ባለ ሁኔታ ማስቀመጥ አለባቸው። እድገትና ምርታማነት እንጂ ጉዳት እንዳይከተል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ወያኔ ግን ይህን እያደረገ አይደለም ያለው። አሁን እንደሚታየው ባለሀብቶቹ ናቸው በመንግስቱ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚያስችል አጋጣሚ ያላቸው። ምክንያቱም እየተፈለጉ እየተጠሩ ነው አንዳንዶቹም በሌሉበት መሬቱ እየተሰጣቸው ያለው። እንደጤናማ መንግስት ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚችል መንገድ ተጨንቆና ተጠቦ ፖሊሲውን ቀርጾ ድሀውን አትራፊ ለማድረግ አይደለም ወያኔ እየሰራ ያለው። ለራሱ ነው። ከድሀው የኢትዮጵያ ህዝብ መብት ጋር የተቃረነ ስራ እየተሰራ ነው። የነገውን የህዘብ ኑሮና ሕይወት ሳይሖን ወያኔ ዛሬ ለራሱ የሚያገኘውን ጥቅምና ገቢ ነው በማስላት ላይ ያለው።

    በመጪዎቹ ሃያና ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በየዓመቱ 3.1 % እንደሚጨምር ይጠበቃል። በ 2040 የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 160 ሚሊዮን እንደሚደርስ ጥናቶቸ አረጋግጠዋል። ዛሬ ካለንበት እጥፍ ማለት ነው። ወያኔ ዘንድሮን ካለፈና ትንሽ ስልጣን ላይ ከቆየ  በ 2040 የኢትዮጵያ መሬት በሙሉ በባዕዳን ተይዟል። መጪው ትውልድ የት አርሶ እንደሚበላ፣ የት ሄዶ ጎጆውን እንደሚቀልስ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እራሱን እየጠየቀ መልሱን መሻት አለበት።

   የወያኔ መንግስትና ይህ ህገወጥ ተግባሩ ዛሬ እዚህ ላይ ካልተገታ ስልጣን ላይ የሚዘልቅ ከሆነ የልጅ ልጆቻችንን ሳይቀር መከራ ውስጥ የሚጥል እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሱዳን 1600 ኪሎ ሜትር ርዘመት ያለው የኢትዮጵያን መሬት ይዟል። ምናልባትም በትጥቅ ትግሉ ወቅት ሱዳን ለወያኔ ላደረገው እርዳታና ድጋፍ እንደ ክፍያ የተዋዋለው ሊሆን ይችላል። እነዚህ መሬት እየተቀራመቱ በገፍ አገር ውስጥ መስፈር የያዙ ሀብታሞች ከጀርባቸው ጠባቂና ተንከባካቢ መንግስት አላቸው። ነገ የስርዓት ለውጥ ቢመጣና የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እርምጃ እንውሰድ ብንል ፤ እንዲለቁ ወይም አዳዲስ ግዴታ እንዲገቡ ቢጠየቁ ጥቅማቸውን የሚነካ ከሆነ፤ ተባብረው ሊወጉን አይሞክሩም  ወይም በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ አይገቡም ብሎ የሚያስብ ካለ ስህተት ነው። ወያኔ ሕዝቡን ከፋፍሎ አቃቅሮ ስለሚያዘጋጅላቸው ከሲዳንም ከግብጽም ጋር እየተባበሩ የጦር መሳሪያ በገፍ በማስገባት ለተቃቃረው ሕዝብ ማደል የሚያውካችው እንዳይመስላችሁ።

    ዛሬ እነዚህ በመሬት ነጠቃ ላይ የተሰማሩ ባዕዳን ቶሎ ቶሎ በርካሽ ዋጋ አገር እየተሽጠላቸው ያሉ፤ ከወያኔ ላይ የሌባ እቃ እየገዙ እንዳሉ ሊገነዘቡ ይገባል። የሌባ ተቀባዮች ናቸው። የኢትዮጲያ ህዝብ ነገ በሀገሩ የባለቤትነት መብቱን ሲያረጋግጥ ሌላ ግዴታና ውል እነደሚጠብቃቸው ከወዲሁ ማስገንዘብ መልካም ነው። ወያኔ በወረራ ሀገሪቱን ተቆጣጠረ እንጂ የተመረጠ የሕዝብ መንግስት አይደለም።

    ሀገሪቱን በሀይል እየገዛ ያለው በመለስ ዜናዊ የሚመራ ጥቂት የወያኔ አመራር ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ የማንም ወዳጅ አይደለም ። ባለፉት ሀያ ዓመታት የወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም የሚወክልና የሚጠብቅ  አይደለም። ከራሱም ከህዝብም የተጣላ፤ ሕዝብንም እያጣላ የሚኖር መሰሪ የዘረኞች ስብስብ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ 81 ብሄረሰቦች ይኖራሉ። አብዛኛዎቹ ተሰባጥረው ክፉ ደጉን ተጋርተው፤ ተጋብተው፤ ተዋልደውም፤ በደም በስጋ በባሕልም በልምድም ተዋህደው፤ ለዘመናት በሰላም እየኖሩ ነበር። ባለፉት ሀያ ዓመታት ወያኔ ባዘጋጀው አስራ አራት የዘር ክልል ሰማንያው ብሄሮች በዘር መድሎ፤ በዜግነት መብት ገፈፋ፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ  እየተሰቃዩ መኖር ይዘዋል። ወደ ኦሮሞው ክልል ብትሄዱ ኦሮሞ ያልሆነው 80 ብሄረሰብ በሙሉ እንደ ሁለተኛ ዜጋ፤ እዚያችው ተወልዶ ባደገባት ቀዬ ውስጥ የዜግነትና የሰብዓዊ መብቱ ተገፎ፤ ስራ አይቀጠር፣ ለሀብቱ ለንብረቱ ዋስትና አጥቶ እየፈራ እየተሸማቀቀ በመኖር ላይ ይገኛል። ወደ አማራው ክልል ብትሄዱ እስከ ቅድም አያቱ ዘሩን ከአማራ ያላስቆጠረ ተወልዶ ባደገባት ቀዩ ባይተዋር ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን፤ ተወልጄ አደኩባት የሚላት ሰፈር ውስጥ ሳይሆን ሌላ የማያውቀው አገር ውስጥ መኖር እንደያዘ እየተሰማው መቷል። ወደ ትግሬውም ክልል ብትሄዱ እንደዛው። ወደሱማሌው፣ አፋር፣ ሐረር ሁሉም። ታዲያ ይህን ሁሉ በደል በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመው ሕዝቡ ሳይሆን ወያኔና ወያኔ የፈጠራቸው፣ የቀጠራቸው ጉዳይ አስፈጻሚ ዘረኛ ባለስልጣናት ናቸው።

    ዛሬ በአስራ አራቱም የዘር ክልል ተፈርቶና ተጠልቶ ግን የፈለገውን አድርጎና እንደፈለገው ሆኖ መኖር የያዘ የመለስ ዜናዊን ቋንቋ የሚናገረው ታማኝ ወገን ብቻ ነው። የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ስርዓቱን ማስወገድና በኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነትና አንድነት ላይ የተመሰረተ በእውነተኛ ዲሞክራሲ ላይ የቆመ ስርአት ለመገንባት የመለስ ዜናዊን ጽንፈኛ ዘረኛ ቡድን በቃ ብሎ መነሳት ቀጠሮ የማያስፈልገው ጉዳይ ነው።          

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ