ሲሳይ አጌና

ከ2003 አዲስ ዓመት መግቢያ ጀምሮ ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ ቆመው በኢሕአዴግ የቅስቀሳ ስራ ተጠምደው መገኘታቸው ብዙዎችን ግር እያሰኘ ነው። 

 

ሕወሐት/ኢሕዴግ ዓለም የመዘገበውን የአዲስ አበባውን ጭፍጨፋ ሳይፈጽም፣ ሕዝቡን በዚህ መጠን ሳያስርብ በአንጻራዊ ደረጃ ሕዝብ በልቶ በሚያድርበት ከምርጫ 97 በፊት ያልደገፉትን ኢሕአዴግ ዛሬ እጁ ይበልጥ በደም ከጨቀየ በሁዋላ የሚደግፉት በምን መነሻ ነው? በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ስለተዓምራዊነቱ በነገሩን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የሌለ የህዳሴ ግድብ ሲወራ እሱ ደግሞ ከየት መጣ ብሎ ከመመርመርና ከመጠየቅ ይልቅ ለጨበጣ ፕሮጄክት ሕዝብ ደሞዙን እንዲገብር በአዝማችነት የተነሱት ለምን ይሆን? ... እኮ ለምን? ...

 

ዛሬ ኢትዮጵያ ከመቼውም ግዜ በላይ መከራ ውስጥ መውደቛ ሕዝቡ በኑሮ ፈተና መጠመዱ ለብዙዎቹ አርቲስቶች የተሰወረ አይደለም፤ ... እርግጥ ነው አንዳንዶቹ ... ሌሊት ሲዘፍኑ ያድራሉ፣ ቀን እስከ ቀትር ይተኛሉ፤ ከዚያ ጫት ላይ ይታደማሉ፤ ... ቀጥሎም ወደ ምሽት ክበባቸው ያመራሉ፤ ... የህይወት ኡደታቸው ይህ ነው።ስለምንም አይሰሙም፣ በሀገራቸው ስላለው ሁኔታም አያውቁም፤ ድንገት በኢሕአዴግ ስብሰባ ተጠርተው ኢትዮጵያ ከ5 ዓመት በሁዋላ በኢኮኖሚ አሜሪካንን ትቀድማለች፣ ቻይናንም ታስከትላለች ቢባሉ እንዴት ሆኖ የሚል ጥያቄ ቀርቶ ጥርጣሬም አይኖራቸውም፤ አቶ መለስ ያው በለመዱት መንገድ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ጨረቃ ላይ እንዲሰፍር ጥናቱን ጨርሰናል ቢሉ እነሱ የሚሉት ሰውየው ለየለት ሳይሆን ጥያቄያቸው የሚሆነው ጨረቃ ላይ ጫት አለ እንዴ? የሚል እንደሚሆንም ይታመናል።

 

አንዳንዶቹ አርቲስቶች ከዓለም ተነጥለው በምሽት ክበባቸው ዛቢያ ላይ ብቻ እንደሚሾሩ አንድ ማሳያ አብነት ላንሳ፤ በ1997 ዓ.ም. በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ አንዱ አርቲስት ቃለ ምልልስ ይሰጣል፤ ከጥያቄዎቹ አንዱ ስለ ዓለም ትከታተላለህ ወይ የሚል ነበር፤ አርቲስቱ በሚገባ ሲል ይመልሳል፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ማን ነው?የሚል ጥያቄ ሲከተል.. ውይ አፌ ላይ ነው ... እንዳለ ከአፉ ውስጥ ሳይወጣ ቃለ ምልልሱ ይታተማል፤ ... ኢዚህ ላይ በደንብ አላስቀመጥኩትም፤ ሳነበው ግን ስለገረመኝ ቃለምልልስ ያደረገውን ጋዜጠኛ አግኝቼ ሳነሳበት “እሱ ምን ይገርማል ... ሌሊት 7 ሰኣት ሞባይሌ ላይ ደውሎ ሰውየውን አገኘሁት አለኝ፤ በእንቅልፍ ልቤ የቱን ሰውዬ ስለው የተባበሩት መንግስታትን ጸሃፊ አለኝ፤ ተመልሼ ለመተኛት እየተጣደፍኩ እሺ ማነው ስለው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ አለኝና እንቅልፌን አጠፋው” .. ‘መረጃ” የሚከታተሉትን የርሱ ብጤዎችን ጠይቆ በርሱ ቤት መልሱን ማግኘቱ ነበር፤ ... በወቅቱ ቡትሮስ ጋሊ ስልጣን ከለቀቁ 8 ዓመታት አስቆጥረዋል፤ ኮፊ አናንም ሁለተኛ ዙራቸውን ጨርሰው ሊሰናበቱ የቀራቸው ከሁለት ዓመት ያነሰ ግዜ ነበር፤ ... አርቲስቱ አቶ መለስን እያየ፣ ኮሎኔል መንግስቱን እያስታወሰ አንዴ ስልጣን ከተያዘ ካልሞቱ ወይንም ካልተባረሩ ስልጣን አይለቀቅም ብሎ አምኖ ይሆናል፤ ... ሁሉም አርቲስት እንደዚህ ባይሆንም፣ ከአለም ተነጥለው በጫት ደሴት ላይ የሚኖሩ አርቲስቶች ቁጥር ግን ጥቂት አይደለም፤ ጫት እየቃሙ ከደሴቱ ባሻገር የሚያዩ ንቁ አዕምሮ ያላቸው፣ የሐገራቸው ሁኔታ የሚያስጨንቃቸው አርቲስቶች መኖራቸውም እርግጥ ነው።

 

ወደ ነጥባችን እንመለስ፤ በኢትዮጵያ ምድር በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ኢሕአዴግ መሆን እንደ አንድ ማህበራዊ ነውር የሚቆጠር በመሆኑ ለአንድ አርቲስት በኢህአዴግ ዙሪያ መታየት በጣም ከባድ እና አስቸጋሪ ስለሆነ የሚታሰብ ነገር አልነበረም፤ ዛሬ ይህ እንዴት ተሰበረ? በአንድ በኩል በሀገሪቱ በግልጽ አፍጥጦ በመጣው አፈና በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አርቲስቶች ጉዳዩ ከስራ ዋስትና ጋር የተያያዘ ስለሆነባቸው በዚህ ኑሮ ውድነት እንኩዋን ያለ ደሞዝ ችግሩ በደሞዝም የሚገፋ ባለመሆኑ በአማራጭ እጦት የተባሉትን ይፈጽማሉ፤ በግል የሚንቀሳቀሱትም ፊልም ጽፈውም ሆነ ቲያትር ደርሰው ለማሳየት ብዙዎቹ አዳራሾች የመንግስት በመሆናቸው የተባሉትን ማድረግ ግዴታ እንደሆነባቸው ይታመናል፤ በተፈጥሮ የአደርባይነት ዝንባሌ ያላቸው ደግሞ በአህያዋ ፍልስፍና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚመሩ በመሆናቸው ሃይ የሚል ገሳጭ ሲጠፋ በእኔ በልጥ ታማኝነት ፉክክሩን ያከሩታል፤ሌላው በዋናነት የሚነሳው እና አርቲስቶቹ ለኢህአዴግ በደንብ ገብረው ዓቢይ ሚና እንዲጫወቱ የሚገፋቸው የብላክሜል (በግለሰቡ ማህበራዊ ነውር፣ ወንጀል ወዘተ ለህዝብ አጋልጥሃለሁ በሚል ማሸማቀቅ እና አከስሃለሁ ወዘተ በማለት ማስፈራራት) ውጤት እንደሆነ ለአንዳንዶች እንግዳ ነገር አይደለም፤ ... ጥቂት ዓመታት ወደሁዋላ ልውሰዳችሁ፤ ...

 

በ1995 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ የመንደሩን ሰው ያስጨነቀ ጠንቐይ ነበር ”ሰላም ነሳን፣ ለህግ አካል ብናመለክትም ጉቦ እየከፈለ የሚደፍረው ጠፋ” በማለት የአካባቢው ነዋሪ ተወካዮች እቢሮዋችን ይመጣሉ፤ የኢሕአዴግ ሬዲዮ ጣቢያ ወደ ሆነው ፋናም የመራሉ፤ ደረሰብን ያሉትን ለማየት፣የሚመጣውንም ሰው ብዛት ለመጎብኘት አንድ ቅዳሜ ቀን ለሊት 12 ሰዓት (ሲነጋ) ከእኛጋ የተመደበው ጋዜጠኛ በተባለው ሰዓት እስፍራው ደረሰ፤ በኋላ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛም ቀድሞት ደርሱዋል፤ ... እንደተባለው ብዙ ሰው ነበር፤ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉትም በኣካባቢው ለመጠጥ ጭምር የሚጠቀሙበት ውሃ በሚያስመልሱ የሰውየው በሽተኞች የመበከል እድሉም የሰፋ ነው፤ ጋዜጠኛው የሄደው ይህንን ለማየት ቢሆንም ይዞት የተመለሰው ዜና ግን በጣም የሚያስደነግጥ፣ሊናገሩትም የሚቀፍ፣ቢፅፉትም የሚያስጸይፍ ነበር፤ ...

 

አዎን አንድ አገር ያወቀው ሰው … ከጠንቋዩ ዕድምተኞች አንዱ ነበር፤ በእውነት ለማመን ተቸገርን፤ ሁሉም በዝርዝር ተነገረን፤ በሗላ ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደተረዳነውም ይህ ትንሽ ቦታ የተገኘው ትልቁ ሰው ቐሚ ተሰላፊ ነው፤ ... ዛሬ ይህ ሰው ስለ ኢሕአዴግ ልማት አውርቶ የማይጠግብ፣ በአጭር ግዜ ጃፓንን ጥለን እንደምንሔድ የሚሰብክ ሆኑዋል፤ ነፍሱን ይማረውና የሬዲዮ ፋናው ጋዜጠኛ ያየውን ለአለቆቹ የኢህአዴግ ሰዎች መናገሩ የሚጠበቅ ነው፤ ከዚያ በሁዋላ በራሱ በጠንቛዩ አማከይነት በምስል የተደገፈ መረጃ በመያዝ በዚያ እያሸማቀቁ የፈለጉትን መጫን፤ የፈቀዱትን ማናገር ነው፤ ... በኢትዮጵያ ከሕወሐት/ኢሕአዴግ በላይ የሚጠላ ምንም ነገር አለ ብዬ ባላምንም ከጠንቁዋይ እና አስጠንቁዋይ በላይ የሚጠላ አይመሰለኝም፤ ...

 

በ2001 ዓ.ም. በኢትየጵያ ትልቁ ዜና ታምራት የተባለው ጠንቋይ መያዝ ነበር፤ እድምተኞቹ “አባባ ታምራት” ይሉታል፤ በርካታ አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች የሰውየው ደንበኞች እንደነበሩም ተገለጠ፤ የአንዳንዶቹም ስም ፍርድ ቤት ውስጥ በምስክሮች ተነገረ፤ቤቱ ሲበረበር በተገኘ ቪዲዮ ውስጥ ስለጠንቋዩ አዋቂነት ምስክርነት ከሰጡ ሰዎች ውስጥ አንዳንድ ባለስልጣናት እና አንዳንድ አርቲስቶች እንዳሉበት በስፋት ተወራ፤ እንደ ጋዜጠኛ ለወሬ ባለኝ ቅርበት የባለ ስልጣናቱንም የአርቲስቶቹንም ማንነት በወሬ ደራጃ ደረስኩበት፤ በሬዲዮ ፋና ላይ የባለስልጣናቱን ስም በመደበቅ የአርቲስቶቹ ሊነገር መሆኑ ከቅርብ ምንጮች ተሰማ፤ ... ሰዎቹን ስማቸውን አደባባይ በማውጣት እና በቲቪ ስክሪን ምስላቸውን እያሳዩ ምስክርነታቸውን ማሰማት ለኢህአዴግ የሚያመጣው ትርፍ የለምና በዚህ ቪዲዮ ኣማካኝነት ሰዎቹ ብላክሜይል ተደረጉ፤ እናም አድርጉ የተባሉትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ኢህአዴግን ምን ያስደስተዋል እያሉ መባከን ይዘዋል፤ እሱን በማስደሰት ሐጢያታችንን እንሸፍናለን እያሉ ይበልጥ እየዘቀጡ የሐጢያተኞች አሳለፊ ሆነዋል፤ ... ሕዝባዊ ፍቅርና ድጋፍን ለማግኘት የሚያስችል አቐምና አቅም የሌለው ይህ ቡድን ሰዎችን በዙሪያው የሚያሰባስበው በዕምነት ሳይሆን በጥቅም እና የሰዎችን ነውር በመያዣነት በመጠቀም መሆኑን ሌሎች አብነቶችንም መጥቀስ ይቻላል።

 

ሃምሌ 5/1995 ሌሊት በአዲስ አበባ በተለይም በወረዳ 17 እና 18 ማለትም በቦሌ እና በ22 አካባቢ ከፍተኛ አሰሳ ተደረገ፤ አሰሳው የጦር መሳሪያ ፍለጋ ሳይሆን፤ ጨለማን ለብሰው ለጋ ሕጻናትን እርቃን በሚያስደንሱ መሸታ ቤቶች ላይ ሲሆን፣ ወረዳ 17 በቪርሊ፣ ዞሮ ፐብ ... በተባሉ መሸታቤቶች ላይ በተደረገው ፍተሻ ርቃን ደናሾቹን፣ የመሸታ ቤት ባለቤቶቹን እና ታዳሚዎቹን ጨምሮ 105 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፤ በወረዳ 18 በደንበል ሕንጻ ላይ በነበረው ኢን ኤንድ አውት እንዲሁም ወሎ ሰፈር በነበረው ሉካ ፐብ ራቁታቸውን ሚደንሱትን ጨምሮ 91 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፤ ከነዚህ ውስጥ 36ቱ ከደንበል ኢን ኤንድ አውት የተያዙ ናቸው። ... በአጠቃላይ በአንድ ምሽት ከታፈሱት 196 ሰዎች ውስጥ የጦር ጄኔራሎች፣ በከፍተኛ መንግስታዊ ስልጣን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቐም ባለስልጣናት ዲፕሎማቶች ነበሩበት፤ ስለግለሰቦቹ ማንነት ባይነገርም አሰሳ መካሄዱና ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው በመንግስታዊዎቹ ሚዲያዎች ተዘግቡዋል፤ ...

 

ያኔ በዚያ ሂደት ታስረው ወዲያውኑ ከተፈቱት ውስጥ ዛሬም በሚንስተርነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሁለት ሰዎች አሉ፤ ... አንዱ ጄኔራልም ስራ ላይ ናቸው ... 6 ወርም ይሁን 6 ቀን የሚያሳስራቸው ክስ ተንጠልጥሎ ስለሚገኝ ከእስሩ በላይ ውርደቱና ቤተሰባዊ ቀውሱ እያስጨነቃቸው ታማኝነታቸው እስከመቃብር እንዲሆን የቆረቡ ይመስላሉ፤ ... የሌሊት ርቃን ዳንሱ ዛሬም በከተማዋ የቀጠለ ቢሆንም፣ ድጋሚ አሰሳ ሲደረግ አልታየም፤ በቅንነት ከታየ አሁንም እነዚያኑ ሰዎች ማሳፈር ይሆናል በሚል የተተወ እንደሆነ ይገመታል፤ በሌላ በኩል ግን የኢህአዴግ መንግስት ለማህበረሰቡ የሞራል እሴቶች ተጨንቆ የወሰደው ርምጃ ሳይሆን የዚህን ሱሰኞች እጅ ከፍንጅ ይዞ ብላክሜይል ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ይታመናል፤ ... ኢህአዴግ ስላጣኑን በአንድ ሰዓት የሚያራዝም መስሎ ከታየው ይህ በምዕራቡ ዓለም ያለውንና ኡጋንዳ ላይ ሙግት የቀሰቀሰውን ቆሻሻ ነገር በህግ ለመፍቀድ ወደሁዋላ የሚል አይመስለኝም፤ ...

 

የሕወሐት ቡድን ደካሞችን እና የጎደፈ ታሪክ ያላቸውን በመሰብሰብ በድክመታቸው እያስፈራራ፣ ሌሎችን ደግሞ በሌብነት ውስጥ እንዲገቡ በማደፋፈር እና መውጫ በመንሳት ለዘረፉት ገንዘብ ሰስተው ገብረው እንዲኖሩ እያደረጋቸው ነው፤ ... ኢህአዴግ ሰዎችን በድክመታቸው ከሚጠቀምባቸው ማሳያዎች አንዱ የሕወሀትን ክፍፍል ተከትሎ የታየ ነው፤ የኢሕአዴግ አስኳል በሆነው ሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል በዕምነት ሳይሆን በጥቅም በተቧደኑት የሕወህት አጋሮችም ዘንድ የስኒ ማዕበል ቀሰቀሰ፤ በዚህም ወቅት አንዲት ባለስልጣን ይከዱና የስርዓቱን ጉድፍ በአደባባይ ተናገሩ፤ ይህንንም ተከትሎ የተደበቀው እና በመያዣነት የተከደነው ገመናቸው ይገለጥና ከትዳር ጋር የተያያዘው የፍርድ ቤት ፋይል በጋዜጣ ላይ እን ዲዝረከረክ ተደረገ፤ ...

 

በተቀዋሚ ፓርቲ አባላት ውስጥም በመጠጥ ሃይል ደክመው ነውራቸው ተቀርጾ ብላክ ሜይል ተደርገው የአፍራሽነት ሚና ተሰጥቱዋቸው ሙከራ አድርገው በዚያው የመጨረሻ ስንብት የወሰዱ መኖራቸው ብዙም እንግዳ ነገር አይደለም፤ ... በጽላት ሽያጭ ምርመራ ተካሄደባቸው በበላይ አካል ትዕዛዝ ክሱ እንዳይንቀሳቀስ የታገደለቸው እና በምላሹ በተቃዋሚዎች ውስጥ አፍራሽ ሚና እንዲጫወቱ ተልዕኮ የተሰጣቸውና ዛሬ የለየላቸው ስለመኖራቸው ብዙዎች ባይሆኑም ጥቂቶች ያውቃሉ፤ ይህንን ፋይል በገንዘብ ሃይል ለማስወጣትና ለህዝብ ለማድረስ በተደረገ ሙከራ ብዙ ርቀት ቢኬድም ለነገሩ በመንግስት በተሰጠ ከፍተኛ ክብደት መረጃው ሊወጣ አልቻለም፤ ... የተቀጠሩበትን መስሪያ ቤት ገንዘብ ዘርፈው የተሰወሩ ይህም በአደባባይ የተገለጠባቸው ከተቃዋሚነት ወደ ታማኝ ተቃዋሚነት ገብተው የክስ ፋይላቸውን ዘግተዋል፤ አረ ዝርዝሩ ብዙ ነው፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ አጨብጭበውበት ሲፈለጉ ሸሽተው ጫካ የገቡ ዛሬም ከነዕዳቸው የአንድ ባንክ የቦርድ ሃላፊ ሆነው የተቀመጡ መኖራቸውን በእጄ ላይ የሚገኘው መረጃ ይመሰክራል፤ መቼ ተበደሩ? ምን ያህል ተበደሩ? ሰውየው ማን ናቸው? ተገቢውን ርዕስ መርጬ ከነሰነዱ በዝርዝር እመለስበታለሁ። እኛ ዓለም ያወቃቸው ሰውየስ ቢሆን ከሕዝብ ጋር እልህ የተጋቡት በጤና ነው?

 

ሕወሓት/ኢሕአዴግን በጥቅም እንጂ በዕምነት የሚጠጋው አለመኖሩ ለሕወሓት ሰዎች ግልጽ ነው፤ አቶ ስየ አብርሃ ለእህል ውሃ ሲሉ አባል የሆኑ በማለት ይገልጹዋቸዋል፤ አባል ሳይሆኑም በተለያዩ አጋጣሚዎች በስርኣቱ ዙሪያ የሚያንዣብቡትም ተልዕኮዋቸውን ሲጨርሱና ወደ ጉዳያቸው ሲመለሱ በጸረ ሕወሐትነት አፋቸውን እንዳይከፍቱ እያንዳንዱዋ ጥቃቅን ነገር ትያዛለች፤ የኢትዮጵያን ሚሊኒየም ለማክበር በሚል የተቐቐመውን ሴክሬታርያት እንዲመሩ ከለንደን ወደ ኢትዮጵያ ከሄዱት አንዱ ለአሜሪካዊቱዋ ታዋቂ አቀንቃኝ ቢዮንሴ አጎንብሶ ጫማ ሲያደርግላት የሚያሳይ ፎቶ በአንዲት ጋዜጠኛ ከተነሳ በሁዋላ አቶ በረከት ስምዖን እጅ ገብቷል፤ ሰውየው ዝቅ ብሎ ለቢዮንሴ ጫማ ሲያጠልቅላት ፎቶ የተነሳው ርሱዋ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ ገብታ ስትመለስ ነበር። ... ምን ዓይነት ሞራል አልባ ሰዎች በኢህአዴግ ዙሪያ እነደሚሰበሰቡም ይህ በራሱ የሚፈነጥቀው አለ፤ ... ዛሬ ስለ ተኣምራዊው ዕድገት የሚነግሩን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለፈለት የሚሰብኩን ስለህዳሴው ግድብ መዋጮ የሚጠይቁን ... አዎን እነዚህ ናቸው፤ ... አዎን እነሱ ብላክሜይል የተደረጉት፤ ሀጢያት ባህር ውስጥ የሚዋኙቱ።


ሲሳይ አጌና

እነሆ ኢሜይል፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ግንቦት 27/2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ