የፓርላማው አባላት ያጨበጨቡት ለምንድነው?
ታደሰ ብሩ
ይህንን ዜና ምን ትሉታላችሁ?
ዋናው ኦዲተር የፓርላማ አባላትን ያስጨበጨበ ሪፖርት አቀረበ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የፌዴራል መንግሥት መሥርያ ቤቶች የ2002 በጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲት ሪፖርት የፓርላማ አባላትን አስጨበጨበ። በርካታ የመንግሥት መ/ቤቶች የአፈጻጸም ጉድለቶችን ፈጽመዋል። ሪፖርተር ጋዜጣ ሰኔ 1 ቀን 2003 ዓ.ም.
ለምንድነው የፓርላማ አባላቱ ያጨበጨቡት? የኦዲተሩ ሪፖርቱ ምን አስደናቂ ነገር ይዟል? ቀጥለን ያለውን አንቀጽ እናንብብ።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ቢሮ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ባቀረቡት በዚህ ሪፖርት እንደገለጹት፣ ቢሮው ባካሔደው የኦዲት ምርመራ በ16 መ/ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 1.45 ቢሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል።
እና ...
የፓርላማው አባላት ያጨበጨቡት
- አንድ ቢሊዮን አራት መቶ አምሳ ሚሊዮን ብር (ብር 1, 450, 000, 000.00) ስለተመዘበረ ደስ ብሎዓቸው ነው?
ወይስ
- “አንበሳው” የፌደራል ዋና ኦዲተር ይህን ጉድ “ፈልፍሎ” አግኝቶ አደባባይ ስላወጣው?
እንደኔ እንደኔ የመጀመሪያውን እንጃ እንጂ ሁለተኛው ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። በግድ የጭብጨባው ምክንያት ሁለተኛው ነው ከተባለም ተቀባይነት የለውም። መከራከሪያዎቼ ሁለት ነጥቦች ናቸው
- ይኸው ጽ/ቤት ከዚህ በፊት ከዚህ የላቁ የአሠራር ግድፈቶችን አጋልጧል። አሁን በቀረበው ሪፖርት የተጠቀሰው ገንዘብ ብዙ ቢሆንም ተራ ሙስና (Petty Corruptions) ነው፤ የቀድሞዎቹ ግን በመርህ ላይ የተደረጉ ግዙፍ ሙስናዎች (Grand Corruptions) ነበሩ። ሆኖም ግን ለአንዳቸውም አልተጨበጨበም።
- አሁን የቀረበው የናሙና ጥናት ብቻ ነው። ጭንቅላት ያለው ሰው “በናሙና ጥናት ብቻ ይህን ያህል ጉድለት ከተገኘ ሙሉ ምርመራ ቢደረግ ምን ይገኛል?” ብሎ በማሰብ ይሳቀቃል እንጂ አያጨበጭብም።
መከራከሪያዎቼን ትንሽ ላብራራ።
1. ከዚህ በፊት ለምክር ቤቱ ቀርበው ያልተጨበጨበላቸው ሪፖርቶች
1.1. የክልል መንግሥታት ከፌደራል መንግሥት የሚሰጣቸውን የድጎማ ሂሳብ እንደማያስመረምሩና ይህም ተገቢ አስራር እንዳልሆነ ዋናው ኦዲተር በአንድ ወቅት ሪፓርት አቅርቦ ነበር። በወቅቱ በሪፓርቱ የተናደደው አቶ መለስ ዋናው ኦዲተር የክልል መንግሥታትን “ሉዓላዊነት” ተዳፍሯል ማለቱን አንረሳም። እንዲያውም “ከፈለጉ፣ የክልል መንግሥታት ከፌደራል መንግሥት የሚሰጣቸውን ድጎማ ተቀብለው ሰብስበው ማቃጠል ይችላሉ” ብሎ ነበር።
እንኳንስ ለክልል ለሌላ አገር እንኳን ቢሆን የተሰጠ ድጎማ፤ ተቀባዩ አገር የተሰጠውን ገንዘብ በምን በምን ተግባራት ላይ እንዳዋለው የማስረዳት ግዴታ ያለበት መሆኑን የሚጠራጠር የሂሳብም ሆነ የፋይናንስ ባለሙያ ይኖራል ብዬ አላስብም። ነፃነት ያለበት አገር መንግሥት ከአገሩ ግብር ከፋዮች የሰበሰበውን ገንዘብ ተቀብሎ ለሚያቃጥል እብድ ሰጥቶ በሰላም ውሎ ያድራል ማለት ዘበት ነው።
ዋናው ኦዲተር ይህንን የመሰለ መሰረታዊ ህፀፅ አግኝቶ ሪፓርት ሲያደርግ ሊጨበጨብለት ቀርቶ ከመለስ ተረብና ውረፋ የታደገው አልነበረም። መለስ “ከፈለጉ ክልሎች የተሰጣቸውን ገንዘብ ማቃጠል ይችላሉ” ሲልም “ኧረ ይኸ ነገር መስማት እንኳን ይቀፋል” ያለ አልነበረም።
1.2. የመለስ ዜናው መንግሥት ህግ ከሚፈቅድለት እጅግ በላይ የሆነ ገንዘብ ከብሄራዊ ባንክ መበደሩን ዋናው ኦዲተር ባጋለጠበት ወቅት ደግሞ ሌላ እጅግ አስገራሚና አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል።
አቶ መለስ ዋና ኦዲተር እንኳንስ የሃገር፤ የሱቅ ሂሳብ እንኳን መመርመር የማይችል እንደሆነ በፓርላማው ውስጥ በንዴትና በቁጭት እየተናገረ አረዳን። ያኔ አቶ መለስ የተናገረው ለግለሰቡም ለተቋሙም ነበር፤ ወይም እንዲያ እንዲመስል ፈልጓል።
በዚህ ሪፓርት እና በአቶ መለስ ንዴት መነሻነት “አጣሪ ኮሚሽን” ተቋቋመ። ኮሚሽኑም ለማንም ግልጽ ያልሆነ “መንግሥት የፈፀመው ብድር በአንድ በኩል ትክክል ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስህተት ነው” በማለት አንባቢው የፈለገውን እንዲመርጥ እድል የሚሰጥ አስገራሚ ሪፓርት አቀረበ። መለስ “ትክክል ነው” የሚለውን አነበበ። በጊዜው የነበሩት ተቃዋሚዎች “ስህተት ነው” የሚለውን አነበቡ። ድምጽ ሲሰጥ ያው የወያኔ ሰዎች እጅ ሲያወጡ አብረው ነውና “ትክክል ነው” የሚለው አሸነፈ። የአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፓርት የፃፉት የመለስ የደህንነት ሰዎች ናቸው ተብሎ በወቅቱ ሲወራ እንደነበር ማስታወስ ይጠቅም ይሆናል።
ከዚህ ክስተት መለስ ተማረ። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ጭቅጭቅ ውስጥ እንዳይገይባ መንግሥት ከብሄራዊ ባንክ ያለምንም ማዕቀብ እንደፈለገ እንዲበደር የሚፈቅድ አዋጅ እንዲወጣ አደረገ፤ ያው በድምጽ ብልጫ አልፎ አዋጅ ሆኖ ወጣ። ከአዋጁ ጋርም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይወደስበት የነበረው ብቸኛው ነጥብ - የተረጋጋ ገንዘብ - ተሸኘ።
ከዚያ ጊዜ ወዲህ የመለስ መንግሥት ከብሄራዊ ባንክ ሳይቀር እንዳሻው እየተበደረ ለሚመጣው የዋጋ ንረት “በስግብግብ” ነጋዴ ሲመካኝ ይኸው አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። መንግሥት ከብሄራዊ ባንክ ተበደረ ማለት ደግሞ አዲስ የገንዘብ ወረቀት ኢኮኖሚ ውስጥ ተበተነ ማለት እንደሆነ ጥቂት የኢኮኖሚክስ ኮርሶችን የወሰደ ሁሉ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
በነገራችን ላይ ያ ሪፓርት በቀረበ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ዋናው ኦዲተር ሥራ እንዲለቁ ተደርጓል። አሁን ያሉት ዋናው ኦዲተር ሌላ ናቸው። ለዋናው ኦዲተር መጨብጨብ ከነበረበት እነዚህ ሁለት ሪፖርቶች በቀረቡበት ወቅት ሊሆን ይገባው ነበር። ምክንያቱም በእነዚህ ሪፓርቶች ነው የዋና ኦዲተር ጽ/ቤት የመርህና የህግ ሙስናዎችን ለማጋለጥ ድፍረት አግኝቶ የነበረው።
2. የናሙና ጥናት የመሆኑ ሃቅእርግጥ ነው 1.45 ቢሊዮን ብር ቀላል ገንዘብ አይደለም - ለድሃው። ለወያኔ ግን ትንሽ ገንዘብ ናት።
በቅርቡ ይፋ በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሃግብር (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ሪፓርት መሠረት በወያኔ ከሃገር ከወጣው 8.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማለትም ወደ 150 ቢሊዮን ብር (በቁጥር ሲፃፍ 150, 000, 000, 000.00 ብር) ጋር ሲነፃር 1.45 ቢሊዮን ብር ለሻይ በኪስ የምትያዝ ዝርዝር ናት። ለዚያውም ዋናው ኦዲተር ማስረጃው አልተሟላም እያለ ዳር ዳር አለ እንጂ ይህን ያህል ተዘርፏል አላለም። የዩ.ኤን.ዲ.ፒ ሪፓርት ግን ተዘርፏል ብቻ አይደለም ከአገር ወጥቷል ነው ያለው።
ብሄራዊ ባንክ ባሌስትራ በሚያስቀምጥበት አገር የኮንትራት አለመሟላት፤ ያለጨረታ ሥራ መስጠት እጅግም የሚገርም አይደለም።
በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት ያሉት መሥሪያ ቤቶች 16 ብቻ አይደሉም። መከላከያ፣ ውጭ ጉዳይ፣ የማዕድንና ኃይል ምንጭ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በናሙናው ውስጥ ነበሩ? ዜናው ስለዚህ ጉዳይ የሚለው የለውም።
ላጠቃልል። መቸም የፓርላማው አባላት ዋናውን ኦዲተር “እሰይ አበጀህ!፣ እንኳንም አጋለጥካቸው!” ለማለት እንዳላጨበጭቡ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ፓርላማው ይህን የማለት ድፍረት የለውም። ፓርላማው ድፍረት ቢኖረው ኖሮ ገና ድሮዉኑ (ለዚያው ያኔ ጥቂትም ቢሆን ተቃዋሚዎች ነበሩበት) ሊያደርገው ይችል ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ የፓርላማው አባላት 1.45 ቢሊዮን ብር (ብር 1, 450, 000, 000.00) ስለተመዘበረ ደስ ብሎዓቸው አጨበጨቡ ለማለትም ይከብዳል።
እናንተም እንደኔ ታዝባችሁ ከሆነ የወያኔ የፓርላማ አባላት እንደ በግ መንጋ ናቸው። አንዷን በግ ብቻ እየጎተቱ በመቅደም መንጋው እንዲከተል ማድረግ እንደሚቻል ሁሉ ቀድሞ በማጨብጨብ ሁሉም የፓርላማ አባላት እንዲያጨበጭቡ፤ ቀድሞ ጮክ ብሎ በመሳቅ ደግሞ ሁሉም እንዲስቁ ማድረግ ይቻላል። የወያኔ ፓርላማ አንዱ መታወቂያው ይህ ነው። [በነገራችን ላይ በቀድሞው ፓርላማ ውስጥ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን በአንድ ደቂቃ በጣም ትልቅ መልዕክት ጥሎ የማለፍ ብቃትን ማድነቅ የቻለ አንድ ሰው እንኳን መኖሩን እጠራጠራለሁ። እሳቸው መናገር ሲጀምሩ መሳቅ ለሁሉም “የተከበሩት የወያኔ የፓርላማ አባላት” የተላለፈ ቋሚ ትዕዛዝ ይመስል ነበር።]
ስለዚህም የወያኔን የፓርላማ አባላት “ለምን አጨበጨባችሁ?” ብሎ መጠየቅ ዋጋ የለውም። ምክንያቱን እነሱም አያውቁትም። ምናልባት ምክንያቱን የሚያውቀው - ያውም ምናልባት - በመጀመሪያ ያጨበጨበው ሰው ነው።
እናም ጥያቄዬን አሻሽዬ ላቅርበው።
የዋናው ኦዲተር ሪፓርት ከቀረበ በኋላ በመጀመሪያ ያጨበጨበው ማነው?
ለምንስ ያጨበጨበ ይመስላችኋል?
በመጨረሻ አንድ ነገር ጣል አድርጌ ልሰናበት። የዋና ኦዲተር ጽ/ቤት የመለስ ዜናዊ መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ መፍጨርጨሩ የሚያስመሰግነው ነው። ሆኖም ግን እሱ ራሱ ከግዙፍ ሙስና የፀዳ አይደለም። ለዚህ አባባሌ የሚከተለው የአዲስ አበባ አስተዳደር ዋናው ኦዲተር ጽ/ቤትን በተመለከተ ሰሞኑን የወጣ ሌላ የዜና አርዕስት በበቂ በላይ ማስረጃ ነው።
ግንቦት 20 ሠልፍ ያልወጡ የከተማው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘዙ
ሪፖርተር ግንቦት 28 ቀን 2003 ዓ.ም.
ይህ በመርህ ላይ የተደረገ ግዙፍ ሙስና (Grand Corruption) ነው።