የኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ሞት
እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)
የደርግ የቀድሞ የደህንነት ሚኒስትር፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም.፣ በእስር ላይ በነበሩበት ቃሊቲ ወህኒ ቤት አርፈዋል። ወንዳወንድ ገፅታና ደንዳና ሰውነት የነበራቸው ኮ/ል ተስፋዬ፣ በሕይወት ዘመናቸው ብዙ ከመናገር ይልቅ ማዳመጥን የሚወዱ ሰው እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገሩላቸዋል። የደርግ አባል አልነበሩም። ሆኖም፣ አብዮቱ የመጣላቸው እንጂ የመጣባቸው እንዳልነበር ነጋሪ አላስፈለጋቸውም። ተስፋዬ የጭቁኖች ልጅ ነበሩ። ወዲያው ነበር ታማኝ የሆኑት።
በመጀመሪያዎቹ የአብዮት ዓመታት ከደርግ አባሉ ተካ ቱሉ ስር ሆነው ሰርተዋል። በማዕረግ ግን ተስፋዬ ይበልጡ ነበር። በስልጠናም የሰማይና የምድር ያህል ይራራቁ ነበር ማለት ያስደፍራል። ተስፋዬ እስራኤል ድረስ ሄደው ተምረዋል። ከሞሳድ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተጋፍተዋል። አክራሪ አብዮተኞች የእስራኤል ቆይታቸው ሁልጊዜ ይቆጠቁጣቸው ነበር። ብዙም ሲያሟቸው ኖረዋል። የመንግሥቱ ኃይለማርያም ልብ ግን በተስፋዬ ብቃት በጠዋቱ ማልሏል። ተስፋዬ ሰለቸኝ ሳይሉ ጧት ማታ ይሰራሉ። አለቃቸው እንደዚያ ዓይነት ሰው አልነበሩም። ብዙም ሳይቆይ፣ ተካ ተነስተው ሜዳውም ፈረሱም የተስፋዬ ሆነ።
ተስፋዬ፣ ሚኒስትርነት ወዲያው ነበር የተመቻቸው። ሰውነታቸው እንደፊኛ ተለጠጠ። ከጭንቅላታቸው እስከእግር ጣታቸው ወፈሩ። ዝምታቸውም በዚያው ልክ ጨመረ። ብዙ ሚስጢሮችን እየዋጡ አስቀሩ። አንደበታቸው ቢከፈት አፈትልከው የሚያመልጧቸው ሳይመስላቸው አልቀረም። ሚስጢሮቹም ከቀን ወደ ቀን ተደራርበውባቸዋል። ለምሳሌ፣ ስለ በዓሉ ግርማ አሟሟት ያውቁ ነበር። ብርቅየው ደራሲ በሞቱ ጊዜ የመንግሥት «የጓዳ ሚስጢር» በእሳቸው መስሪያ ቤት ውስጥ ተማክሎ ነበር። ቅዳሜ እለት ወደመቃብራቸው ይዘውት ሄደዋል። ከመንግሥቱ ሌላ፣ ይሄን ሚስጢር የሚያውቅ አሁን ከቶ በነፍስ ይኖር ይሆን?
ደርግ፣ እረፍትን ሳያውቅ የሞተ መንግሥት ነበር። ከ1971 እስከ 1978 ዓ.ም. የነበሩት ሰባት ዓመታት አንፃራዊ ሰላም ነበራቸው። ሻዕቢያ ተዳክሞ ነበ።፡ ሕወኃት ገና በዳዴ ላይ ነበረች። የዚያድ ባሬ መንግሥትም ተንፍሷል። ደርግ የማይገፋ ተራራ ነው ተብሎ የተነገረለት በእነዚህ ዓመታት ነበር።
በ1978 ግን፣ የአልጌና ግምባር በሻዕቢያ እንደ ድንገት ተደመሰሰ። ከዚህ በኋላ፣ ደርግ ከማጥቃት ወደ መከላከል ተሸጋገረ። ከሁለት ዓመት በኋላ አፍአበትን ተቀማ። መንገዳገድ የጀመረው ከዚህ ግዜ አንስቶ ነበር ማለት ይቻላል። ከሶስት ዓመት በኋላ፣ በግንቦት 1983 ዓ.ም.፣ ሙሉ ለሙሉ ተሸነፈ።
በደርግ ተቀዋሚዎች ላይ መረጃ የማሰባሰብ ኃላፊነት የተጣለው በኮሎኔል ተስፋዬ መሥሪያ ቤት ላይ ነበር። ኃላፊነቱ ሁለት ገፅታዎች ነበሩት። አንደኛው፣ አማጺያኑ በከተማ የነበራቸው መዋቅር መበጣጠስ ሲሆን፣ ሁለተኛው አማጺያኑ እምብርት ድረስ ዘልቆ በመግባት መረጃ ማሰባሰብ ነበር። ይህንን ተልዕኮ ለማስፈፀም፣ ሙያዊ ስልጠና የተሰጣቸው በርካታ የመረጃ ሰራተኞች በኮሎኔል ተስፋዬ ስር ነበሩ።
የመጀመሪያውን ኃላፊነት እነ ኮሎኔል ተስፋዬ በብቃት ተወጥተዋል። አንድም አማፂ፣ በከተማ የረባ መዋቅር አልነበረውም፤ እስከመጨረሻው እለት ድረስ። ውድቀታቸው፣ ሁለተኛው ተልዕኮ ላይ ነበር። አንድንም አማጺ ሰርገው በመግባት መረጃ መቃረም ሳይችሉ ቀርተዋል። ያ ሁሉ የተማረ ኃይል አንዲትም ቁም ነገር መስራት አልቻለም። የአልጌና፣ የአፍአቤት፣ የምፅዋና የሽሬ ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃት የዚህ ክፍተት ውጤት ነበር። አማጺያኑ ድል የተጎናፀፉት ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘር በመቻላቸው ነበር።
ስለዚህም፣ የኮሎኔሉን አጠቃላይ ውጤት ሃምሳ ከመቶ ነበር ማለት ይቻላል። ችግሩ፣ በሞትና ሽረት ትግል የ50 ከመቶ ውጤት ሽንፈት መሆኑ ላይ ነው።
ይሄ ማለት ግን፣ ለደርግ ውድቀት ተስፋዬ ብቸኛና ዋነኛ ተጠያቂ ነበሩ ማለት አይደለም። ተጠያቂዎቹ ብዙዎች ናቸው፤ የሚጀምረውም ከአናቱ ከእራሳቸው ከኮሎኔል መንግሥቱ ነው። ቁምነገሩ፣ በዋናነት ከሚፈረጁት መካከል አንዱ ኮሎኔል ተስፋዬ መሆናቸው ነው። ከደርግ ስልጣን ባሻገር ሃገርን የመጠበቅ ኃላፊነት ነበረባቸው። ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ውጤቱ ኤርትራን አስከፍሏል።
ኮሎኔሉ ያለፉትን 20 ዓመታት በእስር አሳልፈዋል። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ታስረው፣ ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። 7307 ቀናትን በአንዲት ጠባብ ግቢ ውስጥ ተወስነው አሳልፈዋል። በእስር ላይ የነበራቸው ቆይታ ከመደበኛ እስረኛ የተለየ እንደነበር አውቃለሁ። የደርግ ባለሥልጣናት ከብዙሃኑ እስረኛ ጋር አልተቀላቀሉም። ለብቻቸው ተከልለው ነው የኖሩት። እስር ቤታቸው ንፁህ ነው። ጥበቱም የሚጋነን ሆኖ አያውቅም። ዓመታት በገፉ ቁጥር፣ ብዙ እስረኞች ወይ በሞት፣ ወይ በፍቺ፣ እየተቀናነሱ አሁን አሁን እንዲያውም ሰፍቷቸው እንደሚኖሩ ሰምቻለሁ። ቴሌቪዥንና ቤተመጻሕፍት አላቸው። የመዝናኛ እና የስፖርት ጊዜም አመቻችተዋል፤ ቢንጎ የዘወትር ጊዜ ማሳለፊያ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም፣ አረብ ሳት ገብቶላቸዋል። የሚከታተሉትን ጣቢያ የሚወስንላቸው ግን ወህኒ ቤቱ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ቤተሰቦቻቸውን ቶሎ ቶሎ ያገኛሉ። በኢትዮጵያ ደረጃ፣ አያያዛቸው የሚያስከፋ አይደለም። ብዙዎቻችን በኢሕአዴግ ገሃነማዊ እስር ቤቶች ያየነውን መከራ እነሱ አላዩም። ከዚህ አኳያ፣ እድለኞች ናቸው ማለት ይቻላል።
በአንድ ወቅት፣ ተስፋዬ ወልደሥላሴ፣ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ለገሠ አስፋውና ስለሺ መንገሻ አንድ ክፍል ውስጥ እንደነበሩ ሰምቻለሁ። የተረጋገጠ ግን አይደለም። እነዚህ የደርግ አባላት ተስፋዬን አኩርፈዋቸው እንደነበረም ከእነዚያው ሰዎች አጫውተውኛል። እንደገና ግን፣ የተረጋገጠ አይደለም፤ ወሬ ነው። እውነት ቢሆን ግን አልገረምም። ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ለመያዝ በተቃረበበት ጊዜ፣ ባለሥልጣናት እንዳይጠፉ ኬላ እንዲዘጋ ተስፋዬ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበርና። በትዕዛዛቸው መሰረት፣ አዲስ አበባ የነበሩት የደርግ ባሥልጣናት በኢሕአዴግ እጅ ወድቀዋል። (የተረፉት 4 ብቻ ነበሩ። እነሱም በወቅቱ ጣሊያን ኢምባሲ ገብተዋል።) እስር ቤት ሲገናኙ፣ ትዕዛዙ መንግሥቱን የተኩት የጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን እንጂ የእሳቸው እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ ምን ያህል እንደታመኑ አላውቅም።
ከኮሎኔል ተስፋዬ በፊት፣ ተካ ቱሉ እዚያው እስር ቤት አርፈዋል። ከደርግ አባላት መካከል፣ ካሣዬ አራጋውና ካሣሁን ታፈሰም የመጨረሻ እስትንፋሳቸው የወጣችው በእስር ላይ ሆነው ነበር። ሌሎች የማላቃቸው የደርግ አባላትም እዚያው እንደሞቱም እገምታለኹ። በነፍስ ያሉት አርጅተዋል። የእድሜያቸውን 1/3ኛ በእስር አሳልፈዋል። ቅስማቸው ያልተሰበረው ጥቂቶች ናቸው። ሁሉም ተፀፅተዋል። ጥፋታቸው የማይረሳ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚታዘንላቸው እንጂ የሚጠሉ ሰዎች መሆናቸው አብቅቷል። ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች ሆነው ያለፉትን 20 ዓመታት አሳልፈዋልና።
ስለዚህም፣ ከአሁን በኋላ ከእስር ቤት ወደ ቤታቸው የሚመለሰው ሬሳቸው መሆኑ ትርጉም የለውም። መሞት የሚገባቸው ከእስር ተፈትተው በየቤታቸው ነው። እነሱ ያላሳዩትን ርኅራሄ ለእነሱ በመቸር፣ ለታሪክ የማይረሳ ትምህርት ትቶ ማለፉ ለቀጣዩ ትውልድ ይጠቅማል።
ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.