የኢፈዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ሰኔ ፲፬ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. (June 21’2011)

ክቡር ሆይ!

ቅዳሜ ሰኔ ፲፩ (The Saudi - June 18) የሳዑዲው የተባለው ጋዜጣ ባወጣው እትም የሳዑዲ መንግሥት ፴ ሺሕ ሠራተኞች (ሹፌሮች፣ የቤት አገልጋዮች፣ በልዩ-ልዩ ቴክኒክም የሰለጠኑ) ከኢትዮጵያ ለመውሰድ የምትሻ መሆኗን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም እነዚህ ሠራተኞች ተገቢ ስልጠና እንዲያገኙ ሙሉ ትብብር ለማደረግ ዝግጁ እንደሆነች መናገርዎን አስፍሯል።[1]

 

አስቀድሜ መንግሥት በሃገር ያለውን የኢትዮጵያውያን የሥራ አጥነት ችግር መፍትሔ ለማግኘት የሚያደርገው ያለሰሰ ጥረት እጅግ የሚደነቅና የሚደገፍ፣ የተቀደስም ተግባር ነው እያልኩ፤ በአኳያው ግን ከሳዑዲ መንግሥትና ሕዝብ ለኢትዮጵውያን ወገኖቻችን ስላለው የባርያ ስርዓት አያያዝ ምንም ሳያነሱ በመቅረትዎ፣ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲና በሌሎችም የዓረብ አገሮች ዘወትር የሚደርስባቸው ያለ ግፍ ጠቅሰውም ተቃውሞ ባለማቅረብዎ ቅር የተሰኘሁ መሆኔን ለመግለጽ እፈልጋለሁ።

 

በዓረብ አገሮች በልዩ-ልዩ ሥራ የተሰማሩ ብዙ ሠራተኞች፣ ከህንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከባንግላዴሽ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከማሌዥያ፣ ከተለያዩም የአፍሪካ አህጉሮች የሄዱ ሲሆኑ የሚደርስባቸው ያለ ግፍና በደል ዘወትር በየጋዜጣውና በየድረ-ገጹ የምናነበው ጉዳይ ነው። በብዙ የዓረብ አገሮች ለዝቅተኛ ሠራተኞች ያለው አያያዝ የባርያ ስርዓት፣ ወይም ከባርያ ስርዓት ብዙም ያልራቀ እንደሆነ አያጠራጥርም። ይህ ሁኔታ መንግሥት ተቃውሞውን ካልገለጸና በደሉ እንዲቆም ካልጠየቀ መቸም የሚለወጥ አይደለም።

 

የዛሬን አያድርገውና ኢትዮጵያ ለራሷ ወገኖች ጥቃት ቀርቶ ለሌላ ሕዝብም በመቆርቆር ባሕር አቋርጣ ትዘምት እንደነበረች በሃጼ ካሌብ ዘመን የተፈጸመው ሁኔታ በመጽሓፈ ናግራንና በሌላ የታሪክ መጽሐፎችም ይገኛል። ከዚህ ትንሸ ለመጥቀስ፤ ፊንሃስ የተባለ አንድ ክፉ አይሁዳዊ ንጉሥ በየመን አገር ነግሦ በክርስትያኖች ላይ ጥቃት በማድረሱ፣ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ተሻግራ መዝመቷና ፍትሕ ማውረዷ በታሪክ የሰፈረ ሐቅ ነው።

 

በአኳያው ደግሞ ለብዙ ዘመናት ዓረቦች ወደ ሃገራችን እየመጡ በአሽከርነትና በኩሊነት ሲያገለግሉ፣ ሱቅ ሲከፍቱና ሲነግዱ፣ ሲያገቡ፣ ሲወልዱና-ሲዋለዱም እንደቆዩ ለማንም ግልጽ ነው። (ለኩሊነታቸው ማስረጃም እስከዛሬ ድረስ በእጅ የሚገፋው ጋሪ በትግርኛ ‘ዓረብያ’ ተብሎ ይጠራል!) በዓረብ ሃገር በንዚን ወጥቶ በብዛት እየለቀቁ እስከሄዱበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የአሽከርና የኩሊ አገልግሎች ሲሰጡ አንደቆዩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

 

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዓረቦች ሙሉ ሕጋዊ መብታቸው ተጠብቆ፣ ምንም ግፍ ሳይደርስባቸው እንጂ ይህ ተበደሉ፣ አንዲትም ግፍ ተፈጸመችባቸው የሚባል ፍጹም ተሰምቶ አይታወቅም። ለዚህም ነብዩ መሓመድ፤ “ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ፣ የፍትሕ አገር ነው፣ ከዚያ አንድም ግፍ አይደርስባችሁም!” ብለው ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ መላካቸው ምስክር ነው። ኢትዮጵያም ከዓረቦች በፊት ነው እስልምና ነፃ እንዲሰበክ፣ ያለምንም ውጊያና ጦርነት እንዲስፋፋ በዓለም የመጀመሪያዋ ሃገር ሆና የፈቀደችው።

 

ዛሬ ግን ለሥራ የሄዱት ወገኖቻችን በዓረብ አገር መብታቸው ሲገፈፍና ብዙ አሰቃቂ ፍዳዎች ሲፈጸሙባቸው፣ እህቶቻችን ክብራቸው ሲገፈፍ፣ ሲደፈሩና ሲዋረዱ፣ ይህ ብሎ ለመዘርዘር የማይቻል በደልም ሲደርስባቸው ስንሰማና፣ ስናነብብ፣ ባሕር አቋርጦ መዋጋትም ቢቀር፤ “አረ ተው!” ብሎ መናገር እንዴት ይቀራል? ለመሆኑ ይህን ነገር አንስተው ለምን አልገለጹም?

 

አሁንም ጥያቄው በዚህ ጉዳይ መንግሥት ያደረገው ነገር አለን? ለወደፊትስ የሚወሰደው እርምጃ ይኖራል ወይ? በእርስዎ ቢሮም የሚወሰድ እርምጃ ካለ እንደሚገልጹልኝ በተስፋ እጠባበቃለሁ።

አክባሪዎ - ገ/ኢ. ጐርፉ

[1] http://www.saudigazette.com.sa/index.cfm?method=home.regcon&contentID=20110613102928 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!