እስክንድር ነጋ አዲስ አበባ


በዚህ ሳምንት የማካፍላችኹ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2ዐዐ3 . አዲስ አበባ ውስጥ ከሚታተመው መሰናዘሪያ ጋዜጣ ጋር ያደረግኹትን ቃለምልልስ ነው፡፡ በዋናነት የሚያጠነጥነው በፀረ ሽብር ሕጉና ባስከተለው የፍርሃት ድባብ ዙሪያ ነው፡፡

 

 

መሰናዘሪያ፡- የፀረ ሽብር ህጉን እንዴት ታየዋለህ? ከፕሬስ አንፃርስ?

 

አቶ እስክንድር፡-  የፀረ ሽብር ህጉ ሰላማዊ ተቃውሞን ጭምር ለማዳከም ሆነ ተብሎ የወጣ ነው፡፡ ህጉ የወጣው ከምርጫ 97 በኋላ ነው፡፡ ሲረቅም፣ ሲፀድቅም ምርጫ 97 እንዳይደገም እየታሰበ ነው፡፡ በህጉ ምንም ነገር «ሽብር» ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ ህጉን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እናድርገው ብለው ከተነሱ፣ ኢህአዴግን በሀሳብ ደረጃ መቃወሙ በራሱ ሽብር ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ፓርላማው አልቃይዳን የሽብር ድርጅት ብሎ ባለፈው ሰሞን ፈርጆታል፡፡ ይሄ ድርጅት ከአሁን በኋላ በየትኛውም ሀገር የሚፈፅመውን ጥቃት መዘገብ በፀረ ሽብር ህጉ ያስጠይቃል፡፡ የሽብርን ተግባር ማስተዋወቅ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ ደግሞ አንድን ጋዜጠኛ ቢያንስ አስር ዐመታት ያስቀጣዋል፡፡ በምን መለኪያ ነው ይሄ ፍትሃዊ የሚሆነው? በኦጋዴን፣ በመንግስትና በኦብነግ መካከል ውጊያ አለ፡፡ ኦብነግ የሽብር ድርጅት ስለተባለ ስለዚህ ውጊያ እንዳትዘግብ ህጉ ይከለክላል፡፡

 

ታዲያ እንዴት ነው ስለሀገራችን የምንነጋገረው? እንዳደርግ ግዜ በየጓዳችን እንድንወያይ እያስገደደን ነው የፀረ ሽብር ህጉ፡፡ ይሄ ለሀገር የሚጠቅም ህግ አይደለም፡፡ ሀገርን የሚጎዳ ህግ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያስፈልጓቸው የሚያቀራርባቸው ህግ እንጂ የሚያራርቃቸው  ህግ አይደለም፡፡

 

ይህ ማለት ኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ህግ አያስፈልጋትም ማለት አይደለም፡፡ ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ህግ ግን በሰላማዊ ተቃውሞና በሽብር መካከል ሆን ብሎ ብዥታን  የሚፈጥር ህግ መሆን የለበትም፡፡ ህጉ ችግር እንዳለበት በዐለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የጋጠመው ተቃውሞ አይነተኛ ማስረጃ ነው፡፡ ብዙ ሀገሮች የፀረ ሽብር ህጎች አላቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያው ግን አላከራከሩም፣ አላጨቃጨቁም፣ አልተወገዙም፡፡ የኢትዮጵያው ገና ከመነሻው ነበር ችግሩ፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዱ ባለሙያዎች ነበሩ ሊያረቁት የሚገባው፡፡ በተግባር የረቀቁት ግን በፖለቲካ የተነከሩና ለሹመት የቋመጡ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ኢህአዴግን እንጂ ሀገራቸውን አያሰቡ አላረቀቁትም፡፡ ሁላችንም ሊያስማማን የሚችል ህግን በጥልቀት እንዲከፋፍለን አድርገዋል፡፡ እነሱ የፈለጉትን ሹመት አግኝተዋል፡፡ ሀገራችን ግን የሚያስከብራት የፀረ ሽብር ህግ የላትም፡፡ የህሊና ሸክም እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡

 

መሰናዘሪያ፡- በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በሀገራችን የፕሬስ ነፃነት ምን ይመስላል? መሻሻልስ አሳይቷል? ካላሳየስ ለምን?

 

እስክንድር፡- ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አኳያ፣ ምስራቅ አፍሪቃ ሰፋ ያለ አካባቢ ነው፡፡ በውስጡ ያሉት ሀገሮች ከሚመሳሰሉባቸው ይልቅ የማይመሳሰሉባቸው ያመዝናሉ፡፡ ከፖለቲካ፣ ከታሪክ፣ ከሥነልቦና አኳያ ጠበብ አድርገን ስለአፍሪቃ ቀንድ ነው መነጋገር የምንችለው፡፡ ይህ ማለት ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሱማሊያን ነው፡፡ ቀሪዎቹን የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳን ነጥለን ማውጣቱ የግድ ይላል፡፡ እነዚህ ከሌሎቹ የአፍሪቃ ሀገራት ጋር እየተራመዱ ናቸው፡፡ ታንዛኒያ የአፍሪቃ ዲሞክራሲ አይነተኛ ምሳሌ ናት፡፡ ኬኒያ ውስጥም ጭቆና የለም፡፡ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የኖረው ካኑ (KANU) በምርጫ ተሸንፎ ስልጣኑን ለተቃዋሚዎች ካስረከበ ቆይቷል፡፡ የኬኒያ ዋነኛ ችግር የሙስና ችግር ነው፡፡ ከካኑ አምባገነናዊ አገዛዝ የተወረሰ ችግር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የምንወርሰው የሙስና ችግር ይኖራል፡፡ በዩጋንዳ ዲሞክራሲ የለም፡፡ በማንኛቸውም መለኪያ ግን ከአፍሪቃ ቀንድ ትሻላለች፡፡ በተለይ የፕሬስ ነፃነትን በሚመለከት በርካታ ነፃ ጋዜጦችና ሬዲዮኖች አሉባት፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ተቋማትም የተሻለ ነፃነት አላቸው፡፡

 

የአፍሪቃ ቀንድን የተመለከትከው እንደሆነ ግን ዴሞክራሲ የታመመበት ቀጠና ነው፡፡ የአምባገኖች መጨረሻው የአፍሪቃ ቀጠና ነው፡፡ 6 ወራት በፊት ሰሜን አፍሪቃም እንዲሁ ዲሞክራሲ የታመመበት አካባቢ ነበር፡፡ በቱኒዚያ የተነሳው ሕዝባዊ ቁጣ ግን በቀጠናው ያሉትን አምባገነኖች ጠራርጎ  ወስዷቸዋል፡፡ በግብፅና በሊቢያ የሆነውን ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ሞሮኮ በሰላማዊ መንገድ ዲሞክራሲያዊ እየሆነች ነው፡፡ የቀረችው አልጄሪያ ብቻ ናት፡፡

 

ለአምባገነኖች ምሽግ በመሆን የአፍሪቃ ቀንድ ብቸኛው ቀጠና ነው፡፡ አንድም ዲሞክራሲያዊ ሀገር የለበትም፡፡ በሌላኛው ጫፍ ግን በደቡብ አፍሪካ ካሉት ሰባት ሀገራት መካከል ዚምባብዌ ብቻ ናት ዲሞክራሲነቷ የሚያጠራጥረው፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የምትወዳደር አይደለችም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የተቃዋሚዎችና የሙጋቤ ጥምር መንግስት ያለባት ሀገር ናት፡፡

 

በአፍሪካ ቀንድ እንኳን የጥምር መንግስት ይቅርና አንድ ነፃ ሬዲዮ የለም፡፡ ቴሌቪዥንማ አይታሰብም፡፡ ጋዜጦች ትንሽ ይሻላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከምርጫ 97 በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ተጉዛለች፡፡ ነፃ ጋዜጦች በሙሉ ተዘግተዋል፡፡ እንደገና ብሎ መጀመር አስፈልጓል፡፡ ምርጫ 97 የነበሩበት ቦታ ለመመለስ ገና ብዙ ጊዜ፣  ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ይልቅ የሱዳንና የጅቡቲ ጋዜጦች የተሻለ ነፃነት አላቸው፡፡ በጥቅሉ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ኢትዮጵያ ከጅቡቲና ከሱዳን እኩል መራመድ አልቻለችም፡፡ ይሄ ማለት የአፍሪካ ጭራ ሆናለች ማለት ነው፡፡ እኛ ለነፃነት ባበቃናቸው የአፍሪካ ሀገራት ተቀድመናል፡፡ እኛ ባዋለድናቸው ሀገራት፡፡ በግሌ ይሄ ሁኔታ እንደ እግር እሳት ሆኖ ያንገበግበኛል፡፡ እኛ ለእነሱ አርአያ መሆን እንጂ እነሱ ለእኛ አርአያ መሆን አይገባቸውም፡፡ ለስልጣኔ እኮ እኛ እንቀድማለን፡፡

 

ለማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን የመገለፅ መብት አልተከበረም፡፡ ለዚህም ደግሞ የእኔና የሌሎች ሰዎች ጋዜጣ ፈቃድ መከልከል ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡ የአንድ ሰው መብት ሲገደብ የሁሉም መብት ተገድቧል ማለት ነው፡፡ መብት የሁሉም መሆኑ ቀርቶ በስጣታ የሚታደል ውለታ ሆኗል ማለት ነው፡፡

መሰናዘሪያ፡-  የሀገራችን ሚዲያዎች በተለይ ነፃው ፕሬስ በብዙ መንገድ አደጋ ተጋርጦበታል? ለምሳሌ የህትመት መቀነስ፣ በተለያዩ ህጎች መገደብና የመሳሰሉት ምክንያቱ ምንድነው ትላለህ? ምንስ መደረግ አለበት?

 

አቶ እስክንድር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት በተቃራኒ በአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ አገዛዝ ዙሪያ ስርዓት የመገንባት ምኞትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለ፡፡ በተለሳለሰ ቋንቋ ሲገለፅ የአውራ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ማለት ነው፡፡ ይህ ስርዓት ለነፃ ፕሬስ ቦታ የለውም፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው የሚያስፈለገው ተብሏል፡፡ በአንፃሩ ነፃ ፕሬስ የሊብራል ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አንድ መገለጫ ነው፡፡ እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሆነ ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊያን እንደሌሎቹ የአፍሪካ ህዝቦች የሊብራል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ብቁ አይደለም፡፡ ምን እንደሚጎድለን ግን ገና አልተገለፀልንም፡፡ በደፈናው ግን ሀሳባችንን እንዳንገልፅ ተከልክለናል፡፡ የፈለግነውን መንግስት በምርጫ ካርዳችን እንዳንሾም ተከልክለናል፡፡ የሙያ ማህበራትን በነፃነት እንዳናደራጅ ገደብ ተጥሎብናል፡፡ ስለልማት ወይም በሌላ አነጋገር ስለሆዳችን እንጂ ስለመብቶቻችን እንዳናስብ መመሪያ ተሰጥቶናል፡፡ ፈጣን እድገትና ዲሞክራሲ እንደእሳትና ውሃ አይጣጣሙም ነው የሚሉት የኢህአዴግ መሪዎች፡፡ ሀሳብን በነፃ በመግለፅ መብት የተገደበውና ነፃ ምርጫ የተከለከልነው ህዝብ ጠግቦ በልቶ እንዲያድር ነው የሚሉት፡፡ ችግሩ፣ መብታችንም ታፍኖ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በረሀብ አለንጋ የሚጠበሱባት ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ ችግሩ፣ ኢትዮጵያ ረሀብ ከገጠር ወደ ከተማም እየተዛመተባት የምትገኝ ሀገር መሆኗ ነው፡፡ ችግሩ፣ ኢትዮጵያ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው 2ዐ ዓመታት በሙሉ አንድ ጊዜ ረሀብ ያልጠፋባት ሀገር መሆኗ ነው፡፡ ረሀብን 2 ዓመታት ውስጥ ማጥፋት ያቃተው መንግስት ረሀብን ለማጥፋት ያልተፈጠረ መንግስት ነው፡፡

 

ፀሐፊውን ለማግኘት፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ