መለስ፣ ሲአይኤ እና ኢትዮጵያ - ክፍል 3 (የመጨረሻ)
ፖል፦ ከኢቫንጀሊካን ቤተሰብ እንደወጣህ ተነግሮኛል እውነት ነው?
መለስ፦ የለም። ወላጆቼ ኦርቶዶክስ ነበሩ። ትግራይ ውስጥ ጥቂት የኢቫንጀሊካል ቤተሰብ ነው ያለን። በኤርትራ ውስጥ ካሉ ፕሮቴስታንቶች በጅጉ ያነሱ ናቸው። ትግራይ ውስጥ ያሉ ፕሮቴስታንቶች ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይን ይደግፋሉ። ግን ፕሮቴስታንቶች የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ያህል በወያኔ ውስጥ አስፈላጊ አይደሉም።
ፖል፦ ከሱዳን ድጋፍ ታገኛላችሁ?
መለስ፦ የሱዳን መንግስት ምን ጊዜም በሱዳን እንድንመላለስ፤ እንድንወጣ እንድንገባ ይፈቅዳል። ሕዝባችን እዚያ እንዲኖር ይፈቅዳሉ። ሌላ ድጋፍና እርዳታ ግን አያደርጉልንም። የበሺር መንግስት በማናቸውም ሁኔታ የጣለብን ገደብ የለም።
ፖል፦ የጉዞ ሰነድ ይሰጧችሁዋል?
መለስ፦ የጉዞ ሰነድ ሰተውን አያውቁም።
ፖል፦ እንዴት ነው ከሀገር ሀገር የምትጓጓዙት? ማናቸው የአረብ አገር የጉዞ ሰነድ ይሰጣችሗል?
መለስ፦ ሶማሌዎች ፓስፖርት ይሰጡናል። ብዙዎቻችን እንደሶማሊያዊ ሆነን ነው የምንጓዘው። ሌላ አይነት እርዳታ ግን አይሰጡንም። አንድም አይነት የእርዳታ ጥቅም ከማናቸውም አግኝተን አናውቅም። የትግራይ መልሶ ማቋቋም ህብረተሰብ መሰረቱን ለንደን ያደረገ፤ ለኛ በጣም አስፈላጊ እሱ ነው። አሁን በጣም በጣም ጥሩ ድጋፍ እያደረገልን ነው። መጀመሪያ ላይ ብዙም ማድረግ የሚያስችል አቅም አልነበረውም። እራሳችን ባለን ነገር ላይ ነው መተማመን ያለብን። አንድም አይነት እርዳታ ከአረብ ተቀብለን አናውቅም። ለኤርትራውያን እርዳታ ይሰጣሉ። ምክንያቱም ኤርትራውያኑ አረብ ነን ብለው እንዲያስቡ አረቦቹ ይፈልጋሉ። የኤርትራው ነጻ አውጭም ይህንኑ ስሜት ይዞ ለመቆየት ተስማምቷል። እኛ ግን ይህን አናደርግም። እኛ ከአረቦች ጋር አንስማማም።
ፖል፦ ወታደራዊ ድጋፍ ከየት ነው የምታገኙት?
መለስ፦ ከደርግ። ሁልግዜ ከነሱ በምንማርከው ነገር ላይ ነው የምንተማመነው። በቅርቡ በጣም ብዙ ማርከናል። በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ከመቀሌ ሲባረሩ ብዙ ወታደራዊ ትጥቅ ለማውደም ሞክረው ነበር። ነገር ግን እዚያ ብዙ ስናገኝ ተገርመናል። እንዳስላሴ ላይም በጣም ብዙ ማርከናል። በየጊዜው ብዙ እንማርካለን። ወታደሮችና መኮንኖች ወደኛ እየከዱ ብዙ መሳሪያና ፈንጂ ይዘውልን ይመጣሉ። በጦር መሳሪያ አቅርቦት እንኳ ተጨንቀን አናውቅም። ሕዝቡ ምግብ ያቀርብልናል። ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተሽከርካሪዎች ከደርግ ማርከናል። ችግራችን ነዳጅ ብቻ ነው። እርግጥ ከጅምር እስከጭርሱ ሁሉም ነገር ጥሩ ነበር ማለት አይደለም። ትግል በጀመርንበት ጥቂት አመታት ሰሞን ጥቂት ጠመንጃ ብቻ ነበረን። ንቅናቄአችን ሽሬ ውስጥ ነበር መሰረት ያደረገው።
ፖል፦ እንዴት ነበር ንቅናቄአችሁ የተጀመረው? ከራስ መንገሻ ስዩም ጋር ምንድ ነው ግንኙነታችሁ?
መለስ፦ አዲስ አበባ ዊንጌት እማር ነበር። እና በ1973 ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ገባሁ። ዩኒቨርስቲ አልጨረስኩም። በ1974 ከኔ ጋር ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው የትግራይ ጓደኞቼ ጋር ተገናኛሁና የትጥቅ ትግል ለመጀመር ወደ ትግራይ ሄድን። ምክንያቱም ደርግ እኛን ተጠቃሚ ሊያደርገን የሚችል ስርዓት ይመሰርታል ብለን አናምንም ነበር። ሽሬ ውስጥ እኛን የሚደግፉ አርሶ አደሮች አገኘን። በተለይም አንድ አዛውንት አሁን በህይወት የሌሉ ይጠብቁን ነበር ያበረታቱን ነበር። የ1943 ን የወያኔ አመጽ እንደሞዴል ወሰድን። ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደነበር ተመልክተነዋል። መንገሻ ስዩም የመሬት ከበርቴዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመ ነበር። አንድም ነገር የምንጋራው የለም። የርሱ ንቅናቄ ተቀለበሰ። የኛ ተስፋፋ አደገ። ምክንያቱም እኛ በሕዝቡ እንተማመን ነበር።
ፖል፦ ከኢዲዩ ጋር ወይም እሱን ከተካው የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት ጋር ትተባበራላችሁ?
መለስ፦ ከነርሱ ጋር መተባበር የሚያስፈልግበት ነገር አይታየንም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንካሬ አላቸው ብለን አናስብም። ግን ባቀድነው የሽግግር መንግስት ውስጥ ቢሳተፉ ተቃውሞ የለንም። ማናቸውም አይነት አመለካከት በመንግስት ውስጥ እንዲወከል ግድ ይላል።
ፖል፦ ከሀያልነሽ ጋርስ ትተባበራላችሁ? በጎጃም ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በህዝብ ስሜት ላይ ተጽእኖ ያሳደረች ሴት። ባለፈው ዓመት አካባቢውን ስጎበኝ በተለይም በፓዌ የሰፈራ መንደር አካባቢ ሰው ምን ያህል እንደሚፈራትና እንደሚያከብራት አይቼ ደንቆኛል። እንደሰማሁት አንዳንድ ታሪክ ከሆነ ትግሬ ናት ይላሉ። እውነት ነው?
መለስ፦ ትግሬ ትሁን አትሁን አላውቅም። ከርሷ ጋር ግንኙነት የለንም። ግን ስለሷ እሰማለሁ። አንዳንድ ሰዎች ኢሕአፓ ናት ይላሉ። እኔ ግን እጠራጠራለሁ። ለምን ኢሕአፓ ትሆናለች? እኔ የአንድም ድርጅት ነች ብየ አላምንም። በራሷ ንቅናቄ ነች።
ፖል፦ በሰፈራ መንደሮች ምንድነው እየሆነ ያለው? ከሰፋሪዎቹ አብዛኛዎቹ ትግሬዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ወደ ትግራይ ተመልሰው ይመጣሉ?
መለስ፦ በየጊዜው ጥቂት ሰዎች እየተመለሱ ነው። ግን አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። በምእራብና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ተነጥለዋል። አደገኛ ጉዞ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እርግጥ እዚያ ቦታ ላይ መቅረት አይፈልጉም። ምክንያቱም በበጎ ፍቃዳቸው አልሰፈሩምና።
ፖል፦ ስለሰፈራ ያለህ አቋም ምንድነው? መልሶ ማስፈሩ ትክክል ነው ሊያስብል የሚያስችል መሰረታዊ ማሳመኛ ነበረው ብለህ ታስባለህ? ወሎና ትግራይ ተፈጥሮው የተጎዳ የተሟጠጠ ስለሆነ ህዝቡን ከዚያ ወደ ሌላ የሀገሪቱ ክፍል ከማንቀሳቀስ የተለየ አማራጭ የለም የሚለውን ማሳመኛ በተመለከተ አመለካከትህ ምንድነው?
መለስ፦ ሰዎች ሰፈራ ጣቢያው መኖር መቆየት ከፈለጉ መኖር አለባቸው። ለቀው መሄድ ከፈለጉ መሄድ አለባቸው። ምርጫ ከተሰጣቸው ብዙዎቹ ለቀው መሄድ ይፈልጋሉ ብየ እጠረጥራለሁ። ግን ትግሬዎች ሁል ጊዜም ለስራ ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ይሄዳሉ። ለመኖር፤ ለመነገድ ወደፊትም ይህንኑ መቀጠል ይፈልጉ ይሆናል። ከትግራይ ውስጥ በሀይል የሚደረገውን መልሶ የማስፈር ተግባር አጥብቀን እንቃወማለን።
ሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮው የከፋ ነው። ሰዎች ሊኖሩበት አይችሉም የሚለው ማሳመኛ የደርግ ፕሮፓጋንዳ ነው። ትግራይን አሁን ማየት አለብህ። በዚህ አመት ጥሩ የበልግ ዝናብ አለ። በጣም ቆንጆ ነው። የሚወራው የተፈጥሮ ድቀት ደርግ የሚቃወሙትን ሁሉ ካካባቢው ለማንቀሳቀስ የሚያቀርበው ምክንያት ነው። እናም ሁኔታውን ለማሻሻል አንድ ነገር ላለማድረግ። ወሎና በጌምድርም እንደዚያው ነው። መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ አንዳንዶች እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ይህንኑ የደርግ ወሬ ተቀብለው እየደጋገሙ መናገር መቀጠላቸው ነው። በአጠቃላይ ተሳስተዋል። ከአብዮቱ በፊት በትግራይ ደንን የማልማት ስራ ነበር። ሕዝቡ ዛፎቹን የሚያወድም ሞኝ አልነበረም። እኛም እንደገና ደን የማልማት ፕሮግራም ነበረን። በጣም የተሳካ ነበር። ሕዝቡ እንዴት እንደሚያሻሽለው እያስተማርነው ነው። እያደረጉትም ነው። ትልቅ የእርከን ስራ ፕሮግራም አለን። የእርሻውን ሁኔታ በጣም አሻሽሎታል። በመላው ትግራይ ገበሬዎች ኩሬና እርከን እየሰሩ ነው። በዚህ ዓመት ሁኔታዎች ጥሩ ይመስላሉ። ገበሬዎች እየዘሩ ነው። ጥሩ ምርት እንጠብቃለን። የበለጠ የልማት እርዳታ ሲደረግ ትግራይ የሚበቃትን ምግብ በሙሉ ታመርታለች። በእርሻው ለማይሰማሩ ወገኖች ስራ ለመፍጠር ኢንዱስትሪ እንገነባለን። የትግራይ ሰዎች እንዴት እራሳቸውን እንደሚረዱ ያውቁታል። እድሉን ማግኘት ብቻ ነው የሚያስፈልጋቸው።
ፖል፦ ሮም ውስጥ (ከደርግ ጋር ማለቱ ነው) በንግግራችሁ ወቅት ምን ሆነ? አንድ ውጤት ይኖረዋል ብለህ ትጠብቃለህ?
መለስ፦ ንግግሩ ባጠቃላይ የሚያስከፋ ነበር። ጣሊያኖቹ የአሻግሬ ይግለጡና የደርግን አቋም ነበር የደገፉት። በሂደቱ ላይ ግልጽ ነበር። በተለይም አደራዳሪ የነበረው የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባለስለጣን። የደርግን አቋም እንድንቀበል ከጣሊያኖች ሙግት ገጥሞን ነበር። ያን ልናደርግ አንችልም። ስለዚህ ጥለን ወጣን። በንዲህ ያለ ሁኔታ ተመልሰን ለንግግር አንቀመጥም።
ፖል፦ በንግግሩ ወቅት ምን ቋንቋ ነበር የተጠቀማችሁት?
መለስ፦ አማርኛና እንግሊዝኛ
ፖል፦ ከደርግ ጋር የመነጋገሩ ነገር ከንግዲህ አይታሰብም ማለት ነው?
መለስ፦ ደርግ ጠንካራ ተደራዳሪ መሆን የማይችል እጅግ ደካማ ነው። ከኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባርም ጋር እንደዚያው። ደርግ መጥፋት ነው ያለበት። ከደርግ ጋር ስምምነት ልናደርግ አንችልም። አገሪቱን ነጻ ለማውጣት ውጊያችንን መቀጠል አለብን። ለዚህም የምዕራቡ አለም በሰፊው እንዲረዳን እንፈልጋለን። እናም የዋናዋና ምእራባውያን እርዳታና ድጋፍ እንሻለን። አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላም በማምጣቱ ረገድ ትልቅ ሚና ስትጫወት ማየት እንፈልጋለን። ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምንድነው የአሜሪካ አቋም?
ፖል፦ አሜሪካ ምንጊዜም የኢትዮጵያን የግዛት ሉአላዊነት ትደግፋለች። እናም ሀገሪቱ እንድታድግና እንድትሰለጥን ትፈልጋለች። ይህ አቋሟ መቸም ተለውጦ አያውቅም። አሜሪካ ሶቬት ህብረት ለመንግስቱ የጦር መሳሪያ መላኳን አቁማ ማየት ትፈልጋለች። እኔ በግሌ አሜሪካ ከሶቬት ህብረት ጋር ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጠንከር ብላ ተነጋግራለች ብየ አላስብም። ምናልባትም እንዳነበብከው በምክር ቤት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ክፍል አፍሪካ ንኡስ ኮሚቴ ፊት ቀርቤ ይህን አመለካከት ገልጫለሁ። ጠቅሻለሁ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት። ሶቬት ህብረት በምስራቅ አውሮፓ አገሮች ብዙ ለውጦችን ተቀብላለች። በሞንጎሊያ እንኳ ግላስኖስት እና ፔሪስትሮይካ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖር ፈቅዳለች። ግን በብዙዎቹ የሶስተኛ ዓለም ሀገሮች ራሽያ ያንኑ አሮጌ ፖሊሲ መከተል ቀጥላለች። አፍጋኒስታን ውስጥ የጦር መሳሪያ ያፈሳሉ። ለመንግስቱ ኃይለማሪያም ያቀርባሉ። የጦር መሳሪያ በገፍ እየጫኑ የአንጎላው ጦርነት እንዲቀጥል ማድረግ ይዘዋል። ካስትሮን መደገፋቸውን ቀጥለዋል። እኔ በግሌ የማስበው አሜሪካ ይህን ጉዳይ በተመለከት በሶቬት ህብረት ላይ ግፊት በማሳደሩ ረገድ የምእራብ ሀገሮችን መምራት አለባት። ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ሁሉ በሚጫነው የጦር መሳሪያ ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ተስፋ አደርጋለሁ።
መለስ፦ እናንተ (አሜሪካን ማለቱ ነው) አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ጥሩ እድል አላችሁ። ደርግ ብዙም ሊቆይ አይችልም። የቀዳሚነቱን ስፍራ ወስዳችሁ በኢትዮጵያ የተሻለ መንግስት እንዲኖረን መርዳት ትችላላችሁ። በዋሺንግተን የመንግስት አካላት ለምንድ ነው የበለጠ ነገር የማያደርጉት?
ፖል፦ እኔ ለአሜሪካ መንግስት አልናገርም። ይህን መረዳት አለብህ። ለአስር ዓመታት ገደማ በዚያ ውስጥ አይደለም ያለሁት። እንደባለስልጣን ሆኘ ይህን ጥያቁ አልመልሰውም። ለኔ እንዴት እንደሚመስለኝ ብቻ ነው የምነግርህ። መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ከፍተኛ ቅድሚያ የምትሰጣት አይደለችም። በዓለም ላይ በጣም ብዙ ትኩረት የሚጠይቁ ሁኔታዎች አሉ። ምስራቅ አውሮፓ፤ ቻይና፤ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ያለች ሀገር ሶቬት ህብረት፤ በላቲን አሜሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ችግሮች ከአፍሪካ ከፍተኛ ቅድሚያ አላቸው። አፍሪካ በአሜሪካ የቅድሚያ ሰንጠረዥ ታች ወለሉ ላይ ነው የምትገኘው።
መለስ፦ የኢትዮጵያ ሁኔታ የአፍሪካ ጉዳይ ብቻም አይደለም። የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይም ነው። በዚያ ያለውን የዓለም ክፍል ስልታዊ ሁኔታዎች ሁሉ ይነካል። እንዲሁም ሰብዓዊ ጉዳይም ነው። የሰብዓዊ መብት ጉዳይ። በሉቲኒያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ሁሉ እናነባለን። ነፃነታቸውን መልሰው እንዲያገኙ የሉቲኒያውያን ምኞታቸውን እንመኝላቸዋለን። ግን በሉቲኒያ ውስጥ ጦርነት የለም። ረሀብ የለም። ከኛ ህዝብ ጋር ሲነጻጸር በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው። ሉቲኒያውያን ሶስት ሚሊዮን ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ሀምሳ ሚሊዮን ናቸው። ከትኩረቱ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል። አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ በእጅጉ ትከበራለች ትደነቃለች። እና የአፍሪካ ቀንድ ህዝብ አሜሪካን ብቸኛ ተስፋው አድርጎ ነው የሚመለከተው። አሜሪካውያን አሁን ስለረሀብ በጣም ያሳስባቸዋል። ግን ረሀብ ዳግም እንዳይከሰት ፖለቲካውን በተመለከት ለምን አንድ ነገር አያደርጉም?
ፖል፦ እያልከው ያለኸው ነገር በትክክል እኔ የልኩትን ነገር ነው። ይህንን ነገር ደግሜ ደግሜ ጽፌው ይህንኑ አመለካከት ሁለት ኮንግሬሽናል ኮሚቴ ፊት በፌብሩዋሪ መጨረሻ ላይ ጠቅሸዋለሁ። የጻፍኩትን ነገር ብታነበው ያልኩትን ነገር ታየዋለህ። አፍሪካ በቅድሚያ ደረጃ ለአሜሪካ ዝቅተኛ ተርታ ላይ ነች ብየ ስነግርህ እውነትነቱን ላረጋግጥልህ አይደለም። ሁኔታውን ላንተ ለመግለጽ እንጂ። ነገሮችን እንዴት እንዳሉ ለይተህ ማወቅ አለብህ። እዚህ ተጽእኖ ማሳደር የምትችልበት ሁኔታ በትክክል አለህ። ሉቲኒያውያንና ሌሎች የቦልቲክ አገሮች እዚህ አሜሪካ ውስጥ ጠንካራ ሎቢዎች አሏቸው። እነዚህ ሰዎች ድምጽ አላቸው። በኮንግረስ ሰዎቻቸው ላይ ግፊት ማሳደር ይችላሉ። ይህንን ለማድረግ የሚችሉ በቂ ኢትዮጵያውያን እስካሁን እዚህ የሉም። እናም የአሜሪካ ፖለቲካ እንዴት እንደሚሰራ ባግባቡ የተረዱም አይደሉም። የሆነው ይሁንና ኢትዮጵያ በአሜሪካ ውስጥ ብዙ ወዳጆች አሏት። ከቸልተኝነትና ሌሎች ቅድሚያ ለማግኘት ከሚፎካከሯት በቀር ጠላት የላትም። ከኮንግረስ ሰዎች ጋር ስትነጋገር ህይወትን ከማዳን ቀጥሎ ያለው በጣም አስፈላጊ ነገር ለረሀብ መከሰት ምክንያት የሚሆኑ ሁኔታዎችን በትክክል ለማሻሻል እርምጃ መውሰድ እንሆነ ንገራቸው።
መለስ፦ ዘወትር ሰዎች ለረሀብ ስለሚሰጥ እርዳታ ብቻ ሲያወሩ እኛ እንረበሻለን። ረሀቡ እንዲከሰት ስለሚያደርገው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ግን ሊወያዩበት አይፈልጉም። ወደ ተቆጣጠርናቸው አካባቢዎች ምግብ እንዲደርስ ለማድረግ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ይህንን ለሁሉም የኮንግረስ ሰዎች እናረጋግጥላቸዋለን። ደርግ ላደረገው ነገር ግን እኛ ሀላፊነት የለብንም። እኛን ወደሚደግፉ አካባቢዎች የሚመጣውን የምግብ እርዳታ ያግዳሉ። እዚህ ዋሺንግተን ውስጥ ያለው ሕዝብ ለምንድነው ያን የማይረዳው? ረሀብ በተከሰተበት አካባቢ ለሚኖረው ህዝብ እርዳታ ለማድረስ ያለው መንገድ በደርግ ላይ ግፊት ፡ ተጽእኖ ማሳደር ነው። እናም የደርግ ስርዓት ተለውጦ በሌላ ተተክቶ ማየት። ከዚያ በኢትዮጵያ ውስጥ መላው ህዝብ የሚደግፈው መንግስት ይኖራል። ከዚያ በሗላ ሌላ ረሀብ ጨርሶ አይኖርም።
ፖል፦ በአሜሪካ መንግስት ውስጥ ጥቂት ሰዎች ያንን ይረዳሉ። ከኮንግረስ አባላትም እንደዚሁ። ሴናተር ጎርም በጥሩ ሁኔታ ተረድተዋል የሚል አስተሳሰብ አለኝ። አናግረው። የቻልከውን ያህል የኮንግረስ አባላትንም አናግራቸው። አሁን ለኔ እያልከው ያለኸውን ነገር ንገራቸው።
መለስ፦ ዩናይትድ እስቴትስ እስራኤል ደርግን ለመርዳት እያደረገች ያለችውን ነገር ተደግፋለች?
ፖል፦ በአስተዳደርም ሆነ በኮንግረስ ውስጥ ለዚህ ምንም ድጋፍ እያየሁ አይደለሁም። የዩኤስ መንግስት እስራዔል በአሁኑ ሰዓት ከደርግ ጋር የመሰረተችውን ግንኙነት በመጻረር ምክር መለገሱን ሰምቻለሁ። እናም ማናቸውንም ወታደራዊ እርዳታ ተቃውማለች። አንድም የኮንግረስ አባል እስራዔልን መደገፉን አልሰማሁም። ብዙ አይሁዳውያን የኮንግረስ ሰዎች ተቺዎች ናቸው። ድርጊቱ በእስራዔል በራሷ ውስጥ አወዛጋቢ ነው። ያለጥርጥር እንደምታውቀው መንግስቱ ኃይለማሪያም ከእንግዲህ ጥቂት ወራት እንዲቆይ የሚአስችለውን ነገር ማየት ማንም አይፈልግም። የእስራዔልም ድጋፍ ውጤቱ ያችው ነች። በግሌ አመለካከት እስራዔሎች ባይኖሩ ኖሮ በአሁኑ ሰዓት መንግስቱ ወድቆ ነበር።
መለስ፦ በጣም አናዶናል፤ ከልብም አስቀይሞናል። ለዚህ ውሳኔ ሀላፊነት ያለባቸው እስራዔላውያን ምንድነው የሚያስቡት? እኛ አረቦች እንደሆን አድርገው ያስባሉ? እኛ አረቦች አይደለንም። ከአረቦች ጋር የተሳሰርንም አይደለንም። የኤርትራው ነፃነት ግንባርም አረብ ነው ብለው ሊያስቡ አይገባቸውም። ከኢትዮጵያ አንጻር ኢፒልፍ የት እንደሚቆም ግልጽ ላይሆን ይችላል። ግን ኤርትራን ወይም ኢትዮጵያን ለአረብ አይሸጥም። እኛ ኢትዮጵያን እንዳለች ለማቆየት ነው። እስራኤሎች መንግስቱ ኢትዮጵያን እንዲያወድማት እየረዱት ነው። የኢትዮጵያን የግዛት ሉአላዊነት ለማቆየት ከፈለጉ እስራኤሎች እኛን ነው መርዳት ያለባቸው። መንግስቱንና የተናጋውን ደርግ አይደለም። ለምንድነው እነሱ ይህን መረዳት የማይችሉት?
ፖል፦ ብዙ እስራኤሎች ይረዳሉ። ለዚያም ነው ይመስለኛል ጠንካራ ትችቶች በ እስራኤል ጋዜጦች የሚወጡት።
መለስ፦ እስራኤላዊው ምሁር ሐጊ ኤርሊችስ ስለ ኤርትራና ስለ ትግራይ በጣም ጥሩ ጽፏል። ታሪካችንን የተረዳ ነው። እንዴት እሱ ይህን አይነት ድርጊት ይደግፋል?
ፖል፦ እንደማይደግፍ እጠረጥራለሁ። ሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያ ወዳጅ እስራኤላውያን አይደግፉም። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች መንግስታቸው ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን አዲስ አቋም መንግስቱ ኃይለማሪያም ስልጧኑን እንዲለቅ ለማግባባት እንዲጠቀምበት ለማሳመን ይቻላቸው ይሆናል። ወይም በሀይል ለማስወገድ።
መለስ፦ በፍቃዱ ስልጣኑን የሚለቅ አይመስለኝም። በሂደት ብዙ ሰው መግደል የሚፈልግ ይመስለኛል። እስራኤሎች የሰጡት መሳሪያና ምክር እስካሁንም ብዙ አገር ወዳዶችን ገድሏል።
ፖል፦ መስክ ላይ የእስራኤልን ድጋፍ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ታያለህ? የእስራኤልን አማካሪዎች መኖር ሪፖርት አግኝተሀል? የምትማርኳቸው ወይም እጃቸውን ለናንተ የሚሰጡት የመንግስቱ ወታደሮችና መኮንኖች ምንድነው የሚሉት?
መለስ፦ የእስራኤሎችን መኖር የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎችን እናያለን። በፍጥነት ነው የተንቀሳቀሱት። ጦር ሜዳ ካሉ ክፍሎች ጋር የእስራኤል አማካሪዎች አገልግሎት ሲሰጡ ሪፖርት እናገኛለን። ወደኛ የሚመጡት ወታደሮች እስራኤሎች ስለ ሰጡት መሳሪያ ሪፖርት ይሰጡናል። በኢትዮጵያ ጦር ሀይል ውስጥ 200 የሚደርሱ እስራኤላውያን አማካሪዎች እንዳሉ እናምናለን። ብዙ መሳሪያና የሚያስፈልገውን ነገር ይሰጡታል። ኢትዮጵያውያን መኮንኖችንም ለስልጠና ወደ እስራኤል እንደሚወስዷቸው እናውቃለን።
ፖል፦ ግን የናንተ ሀይል እየተቀዳጀ ካለው ድል አኳያ ብንመለከተው የእስራኤላውያን መሳሪያና ምክር ብዙም ውጤት ያለው አይደለም። የመንግስቱ ጦር በጥሩ ሁኔታ እየተዋጋ አይደለም። ወደ ሗላ እየተገፋም ነው
መለስ፦ ልክ ነህ። እስራኤላውያን በመንግስቱ ጦር ውስጥ ጥሩ ሞራል እየፈጠሩ አይደለም። ግን ሊሆን የሚችለውን ነገር ሊያዘገዩት ይችላሉ። በመንግስቱና በዙሪያው ላሉ ሰዎች የበለጠ መተማመንን ሊሰጧቸው ይችላሉ። ስለዚህ የበለጠ ብዙ ሰዎችን ወደ ጦር ሰራዊቱ ሊያመጡ ይችላሉ። ብዙም ሰራዊት ሊያዘምቱብን ይችላሉ። በረጅም ጊዜ ግን ተስፋ ያለው ነገር አይደለም። ብዙ ብዙ አማሮች አሁን ወደኛ እየመጡ ነው። ስንይዛቸው እኛ ዘንድ ልናቆያቸው አንችልም። ወደ ቤታቸው ተመልሰው መሄድ ይፈልጋሉ። እንደገና ይያዙና ወደ ጦሩ ይመለሳሉ። ስለዚህ ወደእኛ ያመልጣሉ። ከኛ ጋር ለመዋጋት ዝግጁ በሚሆኑበት ጊዜ እንቀበላቸዋለን። ከኛ ጋር እናኖራቸዋለን።
ፖል፦ አሁን ነገሮች እየተጓዙበት ባለው መንገድ የሚመስለው በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንጦጦ አናት ላይ ቆመህ ይታየኛል። ቁልቁል አዲስ አበባን ስትመለከት፤ እና በሰልፍ ወደ መሀል አዲስ አበባ ለመንጎድ ስትዘጋጁ። የዚያን ጊዜ ለህዝቡ ምንድነው የምትለው? ስልጣኑንስ እንዴት አድርገህ ነው የምትለማመደው?
መለስ፦ ይህ በጣም አሳስቦናል። ስለዚህ ጉዳይ ማሰብና ንቅናቄአችንን ሁሉ ማደራጀት፤ ከዚያ የምናደርገውን እናውቃለን። ምእራባውያን እንዲረዱንና ለምናደርገው ነገር ሁሉ ድጋፋቸው እንዲኖረን እንፈልጋለን። እዚህ የመጣንበትም ዋና ምክንያት ይኸው ነው። ስልጣኑን ለመረከብ ስንዘጋጅ የአሜሪካ ድጋፍ እንዳይለየን እርግጠኞች መሆን እንፈልጋለን። እና ምክርና እርዳታም እንፈልጋለን። ማርች 10/1990 የፕሮገራማችንን ሰነድ አቅርበናል። በዚያ እናምንበታለን። ለኢትዮጵያ ነጻነትና ዲሞክራሲን ማምጣት እንፈልጋለን። አንባገነንነትን መመስረት አንፈልግም። ፕሮግራማችን ማርክሳዊ ሌኒናዊ አይደለም። የሽግግር መንግስት እናዋቅራለን። ያም አዲስ መንግስታዊ ስርዓት ይፈጥራል። ከዚያ ስልጣኑን ወደ ሕዝቡ እንመልሰዋለን። በመላ አካባቢው ሰላም እንዲኖር የተቻለውን ሁሉ እናደርጋለን። በኢትዮጵያ፤ በሱዳን በሲማሊያ መካከል ያሉትን የውጥረት ምንጮች ሁሉ መፍትሔ እንሰጣቸዋለን። የኤርትራ ጥያቄ በስርዓት ምላሽ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማየት እንሻለን። ዓለም እንዲረዳንና እንዲረዳን እንፈልጋለን። የ አሜሪካ ሀሳብ ከሁሉም በላይ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን። ዩናይትድ ስቴትስ ከባድ ሀላፊነት አለባት።
ፖል፦ ወደ መሀል አዲስ አበባ እየገፋችሁ ስትሄዱ ሕግና ስርዓት ማስከበር እንደምትችል ትገምታለህ? ደርግ ሲወድቅ አዲስ አበባ ውስጥ ምን የሚሆን ይመስልሀል?
መለስ፦ እናውቃለን እዚያ ያሉት ዜጎች ተጨንቀዋል። እኛም ተጨንቀናል። ሕዝቡ ጭንቅ ውስጥ እንዳይገባና መዋጋቱን እንዲተው ስርዓት እንዲጠብቅ እንማጸነዋለን። በተቆጣጠርናቸው አካባቢዎች ያንን አድርገናል። ተሳክቶልናልም። ከደርግ ነጻ ስላወጣነው ሕዝቡ በደስታ ነው የተቀበለን። ከውጭ ድጋፍ እንዳለንና የምናደርገውን ነገር ተቀባይነት አሜሪካ እንዳረጋገጠች ሕዝቡ ቢያውቅ በስርዓት እንደሚኖር እናምናለን። ስራቸውን ይቀጥላሉ።
ፖል፦ አሁን ከህዝቡ ጋር የምትገናኙት እንዴት ነው?
መለስ፦ የራሳችን ራዲዮ አለን። ወደ አካባቢው እንደመጣን ወዲያውኑ አቋማችንን እናውጃለን። በየከተማው ደጋፊዎችና ጓደኞችም አሉን። አቋማችንን ያውቃሉ። የትም ቦታ።
ፖል፦ አንዳንድ በሬዲዮአችሁ የምትሰጧቸው መግለጫዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ሳነባቸው ፖሊሲያችሁንና ሀሳባችሁን እንቆቅልሽ አድርገውብኛል። ሬዲዮአችሁ በሰው የሚያሳድረው አስተሳሰብ ንቅናቄአችሁ ማርክሲስት ሌኒኒስት መሆኑንና ደርግ ተቀንሶ ያንኑ ስርዓት በተመመሳሳይ ስርዓት ተክታችሁ የምትቀጥሉ ነው የሚመስለው።
መለስ፦ ይህን ነገር ሬዲዮአችን ይል ነበር። በቅርቡ ግን በጣም ጥንቁቅ እየሆን ነው። ሬዲዎአችንን የመቆጣጠር ችግር እንዳለብን ማመን አለብን። በዚህ ጉዳይ ላይ እየሰራን እንገኛለን። በቀጥታ በቁጥጥራችን ስር ማድረግ አለብን። ይህ ግን አስቸጋሪ ነው። አንተም ትረዳዋለህ። በአሜሪካ ሬዲዮ የአማርኛ አገልግሎት እናንተም ተመሳሳይ ችግር ያለባችሁ ይመስላል። ብዙ ጊዜ በዚያ ሬዲዮ መስመር ላይ በምንሰማው የአማራ ትምክተኝነት አስተሳሰብ ደስተኞች አይደለንም። የአሜሪካ ድምጽ ሀላፊዎች ክቡር የሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ መስደብና ማናደድን ለማስቀት ሬዲዮውን በተሻለ ቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸው አይረዱም እንዴ? ከአሜሪካ ድምጽነት ይልቅ የአማራ ድምጽነት አንድምታ አለው። አንዳንድ ጊዜ ስንቀልድ የደርግ ሌላው ድምጽ ብለን እንጠራዋለን።
ፖል፦ እጅግ የከፋ ነው አስተያየትህ እዚህ ላይ። በካርተር አስተዳደር ውስጥ በነበርኩ ጊዜ ስርጭቱን ለማደራጀት እርምጃዎች እስከወሰድኩ ድረስ ለኢትዮጵያ ልዩ የሆነ ስርጭት የለም። በ1980 ዎቹ መባቻ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት አየር ላይ ሲውል በቅጽበት ነበር በጣም ተወዳጅ የሆነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህዝብ የደርግ ሌላው ድምጽ አድርጎ ቢመለከተው ኖሮ አያዳምጠውም ነበር። እና የጋዜጠኞቹን የስራ ጥራት በማድነቅ ደብዳቤ አይጽፍም ነበር። ሰራተኞቹ በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ውስጥ ይሰሩ የነበሩ እስከሆነና በአማርኛ እስከተላለፈ ድረስ የኢትዮጵያውያንን የተማከለ አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። ሌላ አይነት ምልከታ ሊኖረው ይቸገራል። ጠፍንጎ የሚያስተዳድረውን ማዕከላዊ መንግስት ግን አይደግፍም። የስርጭት አገልግሎት እስከሆነ ድረስ። የማንንም የፖለቲካ አቋም የመደገፍ ስልጣን የለውም። ዜናና የተመረጡ አስተያየቶችን ብቻ ነው የሚያስተናግደው እንዴት የእያንዳንዱን የአመጽ ንቅናቄ ያረካል? ግን ልቀበለው የምችል አተያይህ አለ። አንዳንዴ በሚያቀርቡት ስርጭት እጅግ እርቀው የሄዱ ይመስላል። እናም እረዳለሁ። ለምን እንደምትናደድ። አንዳንድ ጊዜ እዚህ ዋሽንግተን ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስለሚያደርጉት ስብሰባ አንዳንድ ዘገባ ሲያቀርቡ። አሁን እዚህ እስካለህ ድረስ ለምን ሔደህ ስርጭቱን ከሚሰሩት ሰዎች ጋር አትነጋገርምና አመለካከትህ አየር ላይ እንዲውል አትጠይቅም። ለምን እራስህን ብቻ ታዳምጣለህ? የትግራይ ሕዝብ ለውጭ ዜና ጥገኝነቱ በምንላይ ነው?
መለስ፦ ቪኦኤ የአማርናውን ክፍል ዘወትር አዳምጣለሁ። ብዙ ሕዝብ ትግራይ ውስጥ ያዳምጠዋል። ቪኦኤ የእንግሊዝኛውን ክፍል አዳምጣለሁ። የጀርመን ድምጽና የሞስኮ ራዲዮ አዳምጣለሁ። ከሁሉም የበለጠ ግን ለቢቢሲ አክብሮት አለኝ። በአለም ላይ ምን እየተካሄደ እንዳለ በቅርበት እከታተላለሁ። ማንበብ እወዳለሁ። የማገኛቸውን የሚነበቡ ነገሮች በሙሉ እጠቀምባቸዋለሁ። ከአሜሪካና ከአውሮፓ የሚላኩ ነገሮችም አሉኝ። ያመጣህልኝንም ነገሮች በጣም አደንቃለሁ። ወስጃቸውም በጥንቃቄ እንደማነባቸውም እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
በጣም ከሚያስጨንቁን ነገሮች አንዱ ዓለም ስለኛ አያውቅም። በአሜሪካና በአውሮፓ ጋዜጦች ስለ እኛ በጣም ጥቂት ታሪኮችን ነው የሚጽፉት። ብዙ ግዜም ስለ አቋማችን ፍጹም የተዛባ ነው የሚጽፉት። ብዙ ዚዜ ጋዜጠኞችና እስፔሻሊስቶች ወደ ትግራይ መተው እያደረግን ያለነውን ነገር እንዲመለከቱ እንሻለን። ሁሉንም ነገር ልናሳያቸው አንፈራም። ያጣጥሉታል ብለን አናስብም። ምን ምክር ነው በዚህ ጉዳይ ላይ የምተሰጠን። ልትረዳን ትችላለህ?
ፖል፦ ግልጽ ባለሁኔታ የህዝብ ግንኙነት ችግር አለባችሁ። አቋምህንና የምታስበውን ስታብራራልኝ ተማርኬ አለሁ። ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ያለህ ራዕይ ከደርግ ይልቅ ያንተ ስሜት ይሰጣል። የህዝብ ግንኙነት ስራ ስኬት ኖሮትም አያውቅም። ደርግ ውድቅ ነው ብለህ የውጭውን ዓለም ለማሳመን ጊዜህን ልታጠፋ አይገባም። አንተ መረዳት ያለብህ እውነታ ኢትዮጵያ ላለባት ችግር የበለጠ ገንቢ አቀራረብ ያለው መፍትሔ ማቀድህን ነው። ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ መተው እንዲጎበኙ እንድትጋብዝ ሀሳብ እሰጥሀለሁ። የአካዳሚ ስፔሻሊስቶችንም ጋብዝ። ብዙ በትግራይ ጉዳይ እስፔሻላይዝ ያደረጉ ምሁራን አሉ። ወደትግራይ እንዲመጡና አስተዳደርህን እንዲታዘቡ አድርግ።
መለስ፦ ሐጊ ኤርሊችን አግኝተን ወደ ትግራይ ለጉብኝት እንዲመጣ ማድረግ የምንችል ይመስልሀል? ሁሉንም ነገር ልናሳየው እንሻለን። የራስ አሉላ የትውልድ ስፍራ ሳይቀር እንወስደዋለን። ክርስቶፈር ክላፎንትንም ልንጋብዘው እንፈልጋለን። ስለ ኢትዮጵያ በጣም የተረዳ ሰው ነው። አዲስ አበባ ዊንጌት ትምህርት ቤት እማር የነበረ ጊዜ ሌክቸር ሲሰጥ ማድመጤን አስታውሳለሁ። ንገረው። የሱን ጉብኝት እንደምናደንቅ እንደምናከብር። የሚያውቀውን ቲዎሪ በተግባር ለመፈተን ያስችለዋል።
ፖል፦ ለሁለቱም ግብዣህን ለማስተላለፍ ደስተኛ ነኝ። ዋናው ችግር እስራኤላውያንን በሱዳን በኩል ወደ ትግራይ ማምጣት አስቸጋሪ መሆኑ ነው። አይቻልም። ግን ምናልባትም አንድ መንገድ ይገኝ ይሆናል።
መለስ፦ አንድ ነገር አደርጋለሁ። አንተስ ለምን መተህ አትጎበኘንም? እስከፈለክ ድረስ ቆይተህ ሁሉንም ነገር ታያለህ። መቀሌ አብርሀ ህንጻ ውስጥ መቆያ እናዘጋጅልሀለን። የእንግዳ መቀበያችን አድርገን እየተጠቀምንበት ነው።
ፖል፦ አመሰግናለሁ ስለግብዣህ አስብበትና አሳውቅሀለሁ።



