አንጀት የሚያርስ ጭውውት
ነፃነት ዘገዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ቢሯችን እስኪጸዳ ድረስ በር አካባቢ ቆም ብለን ብሶታችንን ማውራት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም የለመድነው ነገር ሆንዋል። እናም ዛሬ ጧት እንደልማዳችን ወደ አራት የምንጠጋ አለቃና ምንዝሮች ባንድነት ቆመን ስለኢትዮጵያና ስለዓለም ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ማውራት ያዝን።
የኔን ጫጫሪነት ማንም ያውቃል ብዬ አላስብም። ሁላችንም እየፎገላን በተለይ ስላገራችን አሳሳቢና አስጨናቂ ሁኔታ ማውራታችንን ቀጠልን። የሚገርመው ነገር ማንኛችንም ብንሆን ለፖለቲካና ኢኮኖሚ የብላኔ ትንተና የማንተናነስ ነበርን። እየቆየን ግን ከመካከላችን አንዱና በፊትም በአንባቢነቱና በጠቅላላ ዕውቀት ረገድ ባለው ልዩ ችሎታ እናደንቀው የነበረው ጓደኛችን መድረኩን በሞላ ተቆጣጠረውና አፋችንን አስከፈተን። ‘ጉባኤው’ እስኪበተንና ይህቺን መጣጥፍ እስክሞነጫጭር ቸኮልኩ። ግን ምን ዋጋ አለው - መብራት አልነበረምና እስኪመጣ መጠበቅ ነበረብኝ። አመሻሽ ላይ መጣ። ይሄውና አሁን መጻፍ ጀመርኩ። የኔን ሳይሆን የምጽፈው ያ ጎበዝ ጓደኛችን ‘ሌክቸር’ ያደረገልንን ነው። እናንተም ተከታተሉት። ‘የተማረ ይግደለኝ!’ ይሏል ይሄኔ ነው ታዲያ። መምሬ ‘አብራራው’ ቀጠለ፡-
ኢትዮጵያ ኤሊት የላትም። ካሏት ኤሊቶች ብዙዎቹ ለሆዳቸው ያደሩ ናቸው፤ ለሥልጣንና ለፍርፋሪ ኅሊናቸውን የሸጡ ናቸው ወይም በአድርባይነት አንገታቸውን ደፍተው ቀን እስኪያልፍ የሚጠባበቁ ናቸው። ለምሳሌ የማንኛውም ብሔርና ብሔረሰብ ኤሊቶች የነቁና ለእውነት ያደሩ ቢሆኑ ኖሮ የማህተመ ጋንዲንና የሮዛ ፓትሪክስ የሲቪክ ተቃውሞ መንገድ ተከትለው ሕዝቡን ለሰላማዊ ትግል በማነሳሳት የኢሕአዲግን ጠማማ የአስተዳደር መንገድ ሊያቃኑ በቻሉ ነበር። እኔ በበኩሌ ይሄን የ’እነሱ፣ እነኚያ’ የሚለውን አካሄድ አልደግፍም። አንድ ሰው ‘እነሱ’ ብሎ በመፈረጅ ተቃውሞ ማሰማት ከጀመረ የጤንነት ምልክት አይመስለኝም። መለየት ያስፈልጋል። በዘውግ የመደራጀት ጣጣ የመብከት ምልክት ነው። በዘውግ ወይም በጎሣ መሰባሰብ ማለት ‘ቢከፋም ቢለማም፣ ቢደድብም ቢማርም፣ ባይማርም ቢሰርቅም፣ ቢገድልም ቢዋሽም የራሴው የኔው ጎሣ ይሻለኛል’ እንደማለት ነው። በሰውነትና በ’ሜሪት’ የሚያምን ግን ከዚህ በሽታና ልክፍት ነፃ በመሆኑ በዘር አያምንም፤ በዕውቀትና በችሎታ፣ በትምህርትና በሥራ ልምድ ተመሥርቶ ነው የሥራ ምደባንና የኃላፊነት ቦታን የሚሰጠው። …
ማህተመ ጋንዲ ሕንድን ከእንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ነፃ ያወጣው አንድም ጥይት ሳይተኩስ ነው። ሕዝቡን ጨው አትግዙ ብሎ ሰበከ። ‘ምግባችንን በምን እናጣፍጥ?’ ብለው ጠየቁት። ከባሕሩ ጨዋማ ውኃ እንዴት ተደርጎ ጨው እንደሚገኝ አሳያቸውና በዚያ ጥበብ ተመርተው የእንግሊዝ ጨው ነጋዴዎች እንዲከስሩ አደረገ። የእንግሊዞችን ልብስ አትግዙ አላቸው። ‘ምን እንልበስ?’ ብለው ጠየቁት። ‘ልክ እንደኔ አቡጀዲ ልበሱ’ አላቸው። ያን አቡጀዲ እያጣፉ እንደሱ ለበሱ። የእንግሊዝ የልብስ ማምረቻ ኩባንያዎችም ከስረው ሱቃቸውን ዘጉ። በዚህ መልክ ዒላማውን አረጋግጦ ባወቀ አድማ የእንግሊዝን የቅኝ ገዢ ኩባንያዎች በማክሰር ሕንዳውያን በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በመጨረሻም ካለደም መፋሰስ ለድል በቁ። ይህ ሲሆን እርግጥ ነው ግርማ ሞገስ ያለውና ሕዝብ በአመኔታ ተቀብሎ ወደመራው የሚሄድለት አመራር ሰጪ ፋና ወጊ ሰው ያስፈልጋል፤ ልክ እንደ ማህተመ ጋንዲ። ይህን ዓይነቱን ትግል ካለ ሁነኛ መሪ ማሰብ ከባድ ነው። የንብ ቀፎ ካለ ንግሥት ዋጋ እንደሌለው ሁሉ ሕዝብም ያለ ሁነኛ አታጋይ አመርቂ ውጤት ማስገኘት ሊከብደው ይችላል።
ሮዛ ፓትሪክስ ጥቁር አሜሪካዊት ናት። በ1950 እና 60ዎቹ በአሜሪካን ሀገር ከፍተኛ ጥቁሮችን የማግለል ድርጊት ይፈጸም ነበር። በመጠጥ ቤት፣ በምግብ ቤት፣ በትራንስፖርት፣ በሥራ ቦታ፣ … ጥቁሮች ከነጮች እንዳይቀላቀሉ ይገለሉ ነበር። ይህች ቆራጥ ሴት በአንድ አውቶቡስ ስትሄድ ወደዚያ አውቶቡስ አንድ ነጭ ይገባል። እንደደንቡ ከሆነ ነጭ ቆሞ ጥቁር መቀመጥ አልነበረበትምና ለነጩ ሰው ወንበር እንድትለቅ ስትጠየቅ ‘እምቢዬው፣ እኔም እንዳንተው ሰው ነኝና በነጭነትህ አልነሳልህም’ ከሚል ትክክለኛ እሳቤ በመነሳት በጥቁርነቷ ምክንያት ወንበር እንደማትለቅ ትገልጻለች። ግርግርና ትርምስ ይነሳል። መኪናው ወደፖሊስ ጣቢያ ይሄዳል። ይሄም ኹከት በወቅቱ የጥቁሮች መብት ተሟጋች ወደነበረው ኪንግ ማርቲን ሉተር ጆሮ ይደርሳል።
በ’ህልም አለኝ’ መፈክሩ የሚታወቀውና ህልሙም ከአርባ ዓመታት በኋላ እውን ሆኖለት ገሚስ አፍሪካዊ ጥቁር ፕሬዝዳንት በመንበረ ዋይት ሀውስ ሊቀመጥ መቻሉን ቀድሞ የተነበየው ያ ሰው፤ ከዚያን ጊዜ በኋላ ጥቁሮች በነጮች አውቶቡሶች እንዳይሄዱ የነፃነትን ዐዋጅ ማስተጋባት በተጠማው ጭቁን አንደበቱ ይገዝታል። ጥቁሮች በእግራቸው መጓዝ ይጀምራሉ። ጥቁር ባለመኪኖችም በእግሩ የሚሄድን ጥቁር በነፃ በማጓጓዝ ትግሉን እንዲያስተባብሩና እንዲያቀጣጥሉ ይደረጋል። በውጤቱም ነጭ ባለአውቶቡሶች ይከስሩና ያን ነባር የአፓርታይድ ሕግ እንዲቀይሩ ይገደዳሉ። ድል በአንድ ቀን አይጠናቀቅምና ዛሬ ይሄውና ጥቁሮች ከዛን ጊዜው በተሻለ ሀኔታ ላይ ሊገኙ ችለዋል።
እንደዚህ ዓይነት ትግል የሚደረገው ግን በጅምላ ሳይሆን አጥፊው እዬተለዬ በአጥፊው ላይ ብቻ ነው። በሀገራችን የዚህን ዓይነት ትግል ማካሄድ ቢፈለግ በስመ ትግሬ ወይም አማራ ወይም ኦሮሞ ሳይሆን፤ ከወያኔ ጋር የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ የጥቅምና የዓላማ አንድነት ያላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች ለይቶ በመነጠል ሊሆን ይገባል። የሀገራችን ኤሊቶች ብዙዎቹ በዕውቀትም በምግባርም ድሆች ናቸው ብዬ የማምነው ይህን አነስተኛ የትግል ሥልት እንኳን በሕዝቡ ዘንድ ለማስረጽ ባለመቻላቸው ነው። ከወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በንግድ የሚበለጽግን ሰው ከዘውግ ጋር ፍጹም ባልተገናኘ ፍረጃ በማህተመ ጋንዲያዊ ትግል ሥልት ቢገስጹት አንድም ራሱን በማስተካከል ተጸጽቶ ወደ ሕዝቡ ይመለሳል፤ አለዚያም ከስሮ ንግዱን ይዘጋና እንደልቡ ከመፏነን ይቆጠባል። መሳሳቱን በሕዝባዊ ቁጣና አድማ ሊረዳ ካልቻለ እየባለገ ይቀጥላል።
ለምሳሌ እኔ አንድ ወቅት አንድን ሰው ልጋብዘው ብዬ ወደ አንድ በራሱ ጥረት ተፍጨርጭሮ ትልቅ ሆቴል ወዳቋቋመ ግለሰብ ቤት ልወስደው ብል የራሱ ምርጫ ወደሆነ ሌላ ቤት ሊወስደኝ ፈለገ። እኔ ግን እምቢ አልኩ። ለምን ብሎ ጠየቀኝ። ‘የምትወስደኝ ቤት ከወያኔ ጋር በመነካካቱ ነው አለአግባብ የከበረው፤ ያኛው ግን በጥረቱና የወያኔን መሠሪ ሸርና ተንኮል ተቋቁሞ ነው እዚህ ደረጃ የደረሰው፤ ስለዚህ ተቃውሞየን እንዳቅሜ የምገልጸው እዚያ ቤት ውስጥ ባለመጠቀም ነው’ አልኩት። እሱም ተገርሞ ‘ለካንስ እንዲህም አለ? እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር መኖሩን ራሱ ዛሬ መስማቴ ነው።’ በማለት ተገርሞ መለሰልኝ።
እኔም ‘አዎ፣ ይህ ዓይነቱ ሰላማዊ የተቃውሞ ትግል ዛሬ የተጀመረ አይደለም። የጥንት ነው። ነገር ግን በስሜትና በግልፍተኝነት ሳይሆን በአስተዋይነት መሆን አለበት። የወያኔዎች መነሻ ትግራይ በመሆንዋ ሳቢያ በስመ ትግሬ ከወሰድክ ስንትና ስንት በዚህ አገዛዝ አንጀታቸው የሚቃጠል ትግሬዎች አሉ፤ በብአዴንም ሆነ በሌሎች ወዶገብ አማራዎችና ኦሮሞዎች ምክንያት በስመ አማራም ሆነ ኦሮሞ ወይም ሌላ ብሔርና ብሔረሰብ ከወሰድክ እጅግ ብዙ የነዚህና የሌሎች ዘውጎች አባላት በብዙው የሚበግኑ አሉ። ስለዚህ ሰላማዊ ትግልን በማካሄድ ወቅት አጥፊውን ከንጹሑ በመለየት የጥቃት ዒላማን ማስተካከል ይገባል እንጂ፤ ‘ከሰሊጥ ጋር የተገኘሽ ጎመን ዘር አብረሽ ተወቀጭ’ ዓይነት ሁሉንም በጅምላ በጠላትነት መፈረጅ ነውር ነው፤ ትልቅ ስህተት ላይም ይጥላል። በዘውግ ትስስር ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሰውን መጥላትም ሆነ መውደድ ወይም ማፍቀር የጤንነት ምልክት አይደለም። መጥላትም ሆነ መውደድ በመሠረቱ ሰውን ሳይሆን ድርጊትንና አስተሳሰብን ነው። መሾም መሸለምም ሆነ ተገቢውን ሥራ ለተገቢው ሰው መስጠት አግባብ የሚሆነው በ’ሜሪት’ (በዕውቀትና ችሎታ) እንጂ በዘርና በትውውቅ መሆን የለበትም። ሁሉም ሰው የአዳምና የሔዋን ትውልደ ሐረግ በመሆኑ ከጊዜ በኋላ በመጣ የሰዎች ልዩነት ተመሥርቶ አድልዖና ክፍፍል መፍጠር ኢሰብዓዊ መሆን ነው። ሰው የመሆንን ትርጉምም ማጣት ነው። …
ይህ ከዚህ በላይ የተቀመጠው ሃሳብ የኔ አይደለም። እርግጥ ነው ቃል በቃልና የተነጋገርነውን ሁሉንም አስቀምጨዋለሁ ለማለት በፍጹም አልደፍርም። ይሁንና የውይይታችን አጠቃላይ አንኳር ጭብጥ ጠቃሚ ነው ብየ ስላሰብኩ እንደነገሩ ከብዙው በጥቂቱ ለማስፈር ሞክሬያለሁ። በዚህ አጋጣሚ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በአሁኑ ወቅት የሚያወራው ስለአስጨናቂው የወቅቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሀገራዊ ሕይወታችን መሆኑን በተለይ በአዲስ አበባ በተለያዩ ሥፍራዎች ዘወር ዘወር በማለት ሰዎች ከሚያደርጓቸው ውይይቶችና ንግግሮች መረዳት እንደሚቻል መግለጽ እወዳለሁ።
ዘመናችን በጣም አስጨናቂ ሆንዋል። የኑሮ ውድነቱ በተለይ ሊገለጽ በማይችል ሁኔታ የቁም ስቅላችንን እያሳየን ነው። ለመጮህ ብንፈልግም እንኳ የምንጮህበት ቦታና ሰሚ የለንም። በዚያ ላይ ታግለው ያታግሉናል ብለን ተስፋ የጣልንባቸውን የሕዝብ ልጆች በዚህ ለሰሚ ግራ በሆነ የአሸባሪነት ወንጀል ክስ የወያኔው መንግሥት እያግበሰበሰ እሥር ቤት እያጎራቸው ነው። አሸባሪነታቸው ግን ለሕዝብ መበደል መቆርቆራቸው እንጂ ወያኔ እንደሚለው እነዚህ ከብዕርና ከርቱዕ አንደበት ሌላ ምንም ዓይነት መሣሪያ የሌላቸው ምሥኪን ዜጎች በርግጥ ጥፋተኞች ሆነው ተገኝተው አይደለም። አህያ ‘አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ’ እንዳለችው ነው ነገሩ ሁሉ። ብቻ መቅሰፍት በዝቷል። የዝምታውም ድባብ ነግሷል። ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ምን እንደሚውጠን እንጃልን። … ያልፍ ይሆን ግን??? …
ነፃነት ዘገዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



