በወያኔዎች ተይዟል ከተባለው የኡጋንዳ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ያለው እውነታ
ዕለተ ሰንበት ነው፡፡ ቀኑ ጥቅምት 5 ቀን 2003 ዓ.ም (ኦክቶበር 16) ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እንደሚያደርጉት ሁሉ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፖላ የሚገኙ አማኞችም ራሳቸው ወዳስገነቡት ቤተክርስቲያን በማለዳ መትመም ይዘዋል፡፡ አብዛኛው ምዕመን የተለመደውን የቅዳሴ አገልግሎት ከመካፈል ባሻገር በሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫ የመሳተፍ እቅድ ይዞ ነው ወደ ቤተክርስቲያን የሄደው፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከምርጫው ዕለት አንድ ቀን ቀደም ብሎ በሞባይል አጭር የጽሁፍ መልዕክት (ኤስ.ኤም.ኤስ) በደረሳቸው መልዕክት ተደናግጠው እና ተቆጥተው ጉዳዩን ለማጣራት የመጡ ናቸው፡፡
ምዕመናኑ ቡንጋ ተብሎ በሚጠራው የካምፓላ ክፍል ከሚገኘው የመካነሰላም መድኃኔያለም ቤተክርስቲያን ሲደርሱ ግን የገጠማቸው ያልጠበቁት ነበር፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች ወደ ቤተክርስቲያኑ ግቢ የሚያስገባውን በብረት ፍርግርግ የተሰራ በር ዘግተው ወደ ውስጥ የሚገባውን በመምረጥ ስራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ቀደም ሲል ይፈቀድ የነበረው የግል መኪናን በቤተክርስቲያን ግቢ አቆሞ ማስቀደስም ዛሬ ተከልክሏል፡፡ ቤተክርስቲያኑን የተቆጣጠሩት ግለሰቦች የሚፈልጉትን እየመረጡ በዋናው በር መሃል በተቀደደች አነስተኛ በር ያስገባሉ፤ አይነ ውሃው ያላማራቸውን ደግሞ ይከለክላሉ፡፡
የክልከላው ምክንያት ካልገባቸው ምዕመናን አንዱ በድፍረት ወደ ግቢው በር ተጠግቶ ለመግባት ይጠይቃል፡፡ ከልካዮቹ አሻፈረኝ ይላሉ፡፡ ጠያቂው ግለሰብ እንደማንኛውም ምዕመን ወደ ቤተክርስቲያን የመግባት መብቱ እንዲጠበቅለት በጋለ ሁኔታ ይከራከራል፡፡ ከልካዮቹ በእምቢታቸው ጸኑ፡፡ ክርክሩም ኃይለ ቃል ወደ መለዋወጥ እና ጭቅጭቅ ተቀየረ፡፡ የግለሰቡ እና የሌሎች ምዕመናን ሁኔታ ያስደነገጣቸው ከልካዮች በቤተክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ አስቀድመው እንዲገኙ ያደረጓቸውን የኡጋንዳ ፖሊስ አባላት በመጥራት እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጓቸዋል፡፡
ፖሊሶቹ ግለሰቡን ጨምሮ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ የተከለከሉ ሌሎች ምዕመናን ይይዟቸዋል፡፡ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል እየጎተቱም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዷቸዋል፡፡ ከልካዮቹ “አሸባሪዎች” ናቸው በሚል ጥቆማ ባስያዟቸው ምዕመናን ብቻ አልቆሙም፡፡ ይልቅስ ከልካዮቹ ከጠሯቸው ፖሊሶች ጋር ቤተክርስቲያን ከመድረሳቸው ከንጋቱ 12 ሰዓት ቀደም ብሎ ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው የቅዳሴ አገልግሎት ላይ ይገኙ በነበሩ ሁለት ዲያቆናት ላይም እርምጃ እንዲወሰድ ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄውን የተቀበሉት የኡጋንዳ ፖሊስ አባላትም ጫማቸውን እንዳጠለቁ ወደ መቅደስ ሰተት ብለው ይገባሉ፡፡ በከልካዮቹ ጠቋሚነትም በቅዳሴ ላይ የነበሩ ሁለት ዲያቆናትን እየጎተቱ በማውጣት እየደበደቡ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ አስረዋቸዋል፡፡
በተቀደሰው የእምነት ቦታ ከተፈጸመው ከዚህ አሳዛኝ ድርጊት ጀርባ ያለው መነሻ ታሪክ አመታትን ወደ ኋላ የሚጓዝ ነው፡፡ እስራቱ፣ ድብደባው እና የፖሊስ ጋጋታው በዕለቱ የነበረውን የሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫ እንዳይካሄድ ለማድረግ የታሰበ እንጂ ቀደም ብሎ በኢትዮ ሚዲያ ድረ ገጽ እንደተገለጸው ወያኔ ቤተክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር ሞክሮ ለማክሸፍ የተደረገ አይደለም፡፡ ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ ነውና እስቲ ወደ ኋላ መልስ ብለን የመድኃኒያለም ቤተክርስቲያን በካምፓላ መመሰርትን ተከትሎ ለአመታት ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች የተፈጠሩ ሁነቶችን እንመልከት፡፡
በተለያየ ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው ወደ ኡጋንዳ የመጡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን ለማነጽ ሲወያዩ ይቆዩና እ.ኤ.አ በ1997 በሚመለከተው የመንግስት አካል ህጋዊ እውቅና ያወጣሉ፡፡ የኡጋንዳ መንግስት ለቤተክርስቲያኑ የምዝገባ ምስክር ወረቀት የሰጠው እንደ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት (ኤን.ጂ.ኦ) በመወሰድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያኑ ከዓመት በኋላ ቤተክርስቲያን ለማነጽ የሚያስችላቸውን መሬት ይገዛሉ፡፡ ግዢው የተፈጸመው የቤተክርስቲያኑ አሰሪ ኮሚቴ አባል በሆኑ አንዲት ምዕመን ስም ነበር፡፡
ምዕመናኑ ቡንጋ ተብሎ በሚጠራው የካምፓላ ክፍል በተገዛው መሬት ላይ ቤተክርስቲያን እያነጹ ከአውሮፓና ምስራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ጋር መገናኘት እና መወያያት ያዙ፡፡ ብጹዕነታቸውም የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብለው እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ወደ ኡጋንዳ ካምፓላ መጡ፡፡ በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ በግለሰቦች ስም ተመዝግቦ የነበረው የቤተክርስቲያን ሰነዶች ለእርሳቸው እንዲተላለፍ የቀረበውን ጥያቄ የተቀበሉት፡፡ በወቅቱም ተቀማጭነታቸው ስዊድዲን ስቶክልሆም የሆነው ብጹዕ አቡነ ኤልያስ 14 የሚሆኑ ሰነዶች ተረክበዋል፡፡ ርክክቡንም 15 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ምዕመናን በምስክርነት ተገኝተው በፊርማቸው ያረጋገጡት ነው፡፡ ይህን የርክክብ ሰነድ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ በስተኋላ ላይ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ አካትተውታል (ይህንን ሰነድ ከጽሁፉ መጨረሻ ላይ ይመልከቱ)፡፡
እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2000 ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ታቦተ ሕግ ይዘው ከስዊድን ካምፓላ ገቡ፡፡ የሕጋዊው ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ መልከ ጻዴቅ ደግሞ ከሰሜን አሜሪካ መጡ፡፡ የኡጋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ምዕመናን በተገኙበትም የኡጋንዳ መካነ ሰላም መድኃኒያለም ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡ በዚያው ዓመትም ቤተክርስቲያኒቱን የሚያስተዳድሩ የቦርድ እና የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ይደረጋል፡፡
የቤተክርስቲያኒቱ ቦርድ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴው ደግሞ ሰባት አባላትን በውስጡ ይይዛል፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ህገ ደንብ መሰረት የቦርዱ አባላት በየሶስት አመት መመረጥ ሲገባቸው የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴው አባላት ደግሞ በየሁለት አመቱ መመረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ቦርዱም ሆነ የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴው ቀጣዩን ምርጫ ያደረጉት እ.ኤ.አ በ2003 ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቦርዱ የአባላት ምርጫ እስካሁንም ድረስ አላካሄደም፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 የተካሄደው የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ ምርጫም ቢሆን ተቃውሞ አላጣውም፡፡ በምርጫው ቤተክርስቲያኑ ሲመሰረት በኮሚቴ አባልነት ያገለገሉ እና የመሬት ግዢ በስማቸው ተፈጽሞ የነበረ የአንዲት ምዕመን ፍላጎት አይሎ የታየበት ነበር፡፡ እኚሁ ምዕመን ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን የሚፈልጓቸውን ሰዎች ያስመርጡና የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡ የምርጫው አካሄድ ትክክል አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን ያሰሙ የነበሩ ምዕመናን “ጉዳያችንን የሚሰማ አላገኘንም” በሚል ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ጉዳያቸውን የተመለከተው ፍርድ ቤት ቤተክርስያኒቱ ጉዳዩን በራሷ እንድትፈታ፣ ተቃውሞ ያሰሙትም ድምጻቸው እንዲሰማ ትዕዛዝ ሰጥቶ ክሱን ውድቅ ያደርገዋል፡፡ በክሱ መሃል የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ሀብተኢየሱስ እየሆነ ያለው “ከአቅሜ በላይ” ነው በሚል ምክንያት ደብሩን ለቀው እ.ኤ.አ በ2005 ወደ ደቡብ አፍሪካ ይሄዳሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱም ለሁለት ወራት ያህል ያለ አስተዳዳሪ ካህን በቦርድ እየተዳደረች ትቆያለች፡፡
አባ ሀብተኢየሱስን ከአዲስ አበባ ወደ ካምፓላ ከአሉበት አፈላልገው ያመጧቸው ምዕመናን ነበሩ፡፡ እርሳቸው ካምፓላ ከደረሱ በኋላ ቡራኬ እንዲሰጡ እና የአስተዳዳሪውን ሹመት እንዲያጸድቁላቸው አቡነ ኤልያስን ይጠይቃሉ፡፡ ብጹዕነታቸውም ጥያቄውን ተቀብለው ያጸድቃሉ፡፡ አባ ሀብተኢየሱስ ደብሩን በለቀቁ ወቅት ምዕመናኑ እንደተለመደው አስተዳዳሪ ያፈላልጉ ገቡ፡፡ አሁን ቤተክርስቲያኑን እያስተዳደሩ የሚገኙትን ቆሞስ አባ ኃይለ እየሱስ እማኘውን በወቅቱ ተሰደው ይኖሩበት ከነበረው እና ኬንያ ከሚገኘው የካኩማ ስደተኞች ጣቢያ ያስመጣሉ፡፡ ብጹዕ አቡነ ኤልያስም የአባ ኃይለ እየሱስን ሹመት ያጸድቃሉ፡፡
በፍርድ ቤት የተያዘው ጉዳይ እልባት አግኝቶ አዲስ አስተዳዳሪ ተሹሞ ነገሮች በሰላም ቀጠሉ፡፡ አወዛጋቢ የነበረው የሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫም በየሁለት አመቱ ሲካሄድ ቆየ፡፡ ችግር መከሰት የጀመረው አሁን በስራ ላይ ያለው የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ በሕገ ደንቡ መሰረት ስልጣኑን እ.ኤ.አ በ2011 አስረክቦ ምርጫ እንዲደረግ ጥያቄ ሲቀርብ ነው፡፡ ምርጫው ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ይካሄዳል፡፡ በምርጫውም በቀድሞው ኮሚቴ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ አባላት ይመረጣሉ፡፡ ከተመራጮቹ መካከል በኮሚቴ አባልነት ሁለት ዙር ያገለገሉ ነበሩ፡፡ በሕገ ደንቡ መሰረት ደግሞ አንድ የኮሚቴ አባል ከሁለት ዙር በላይ መመረጥ አይችልም፡፡
ይህንን ክፍተት ያገናዘቡት አንድ ተመራጩ አባል ምርጫው ህገ ወጥ ነው እንደምሳሌም የእኔን ጉዳይ መውሰድ ይቻላል በሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ የሰበካ ጉባኤው አባል ያልሆኑ ጭራሽ ለኮሚቴ አባልነት መመረጣቸው እና አንዳንዶቹም በሌሉበት የተመረጡ መሆኑን በተጨማሪነት ያነሳሉ፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስልጣኑን ለመልቀቅ ሲያንገራግር የነበረው ነባሩ ኮሚቴም ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የስነ ስርዓት ጥያቄ ያነሳል፡፡
ምርጫውን እንዲያካሄድ በምዕመናን ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጦ የነበረው አስመራጭ ኮሚቴ እና የቤተክርስቲያኒቱ ቦርድ “የማቻቻያ ሀሳብ” ያሉትን ያመጣሉ፡፡ ማቻቻያ ሀሳቡ “ሌላ ምርጫ አይደረግም፤ ነባሩ እና አዲስ የተመረጡት ኮሚቴዎች አንድ ላይ ይቀየጡ” የሚል ነበር፡፡ ከነባሩ ኮሚቴ አባላት መካከል ወደ ውጭ የሄዱ፣ ድጋሚ የተመረጡ እና አዲሶቹ ተጨምረው የተመራጮቹ ቁጥር ዘጠኝ ይመጣል፡፡ ይህ ደግሞ ህግ ደንቡ ከሚያዘው ሰባት በላይ ነበርና አጣብቂኝ ይፈጠራል፡፡ “ከኮሚቴ አባላት ቅነሳ ከማካሄድ ይልቅ አዲስ ከተመረጡት ውስጥ ሁለቱን ወደ ቦርዱ የልማት ኮሚቴ በማዛወር ችግሩን መፍታት ይቻላል” የሚል አስታራቂ ሀሳብ ይመጣል፡፡ በዚህ ስምምነት ላይ ይደረሳል፡፡
አሁን ችግሩ የተፈታ መሰለ፡፡ የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴው የሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እና ጸሀፊ ድልድል ማድረግ ሲጀምር ግን እንደገና አለመግባባት ተከሰተ፡፡ በሕገ ደንቡ መሰረት የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴው የሊቀመንበርነት ቦታ ለቤተከርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ የሚሰጥ ነበርና እዚህ ላይ አለመግባባት አልተፈጠረም፡፡ የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታውም ቢሆን ከአዲስ ተመራጮች ውስጥ ለአንዱ በመሰጡ በእርሱ ላይ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ ምንም እንኳ የምክትል ሊቀመንበርነቱን የተመረጡት ግለሰብ ከዚህ ቀደም ሁለት ዙር የተመረጡ በመሆናቸው ድጋሚ መመረጥ ባይገባቸውም ተጨማሪ ጭቅጭቅ ላለመፍጠር በሚል ታለፈ፡፡ ለጸሀፊነት ቦታ ድልድል ሲደረግ ግን በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ እና በነባሩ ኮሚቴ መካከል ስምምነት ጠፋ፡፡
የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪው “የጸሀፊነቱ ቦታ መሰጠት ያለበት ከዚህ ቀደምም እንደሚደረገው የክህነት ስልጣን ላለው ሰው ነው” ሲሉ ሞገቱ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ “ጸሀፊው ቤተመቅደስ ድረስ ያሉትን ንብረቶች መቆጣጠር ያለበት ስለሆነ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት የሚፈቀድለት የክህነት ስልጣን ያለው በመሆኑ ነው” የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ይህንን ቦታ ይዘው የቆዩት ዲያቆናት እንደነበሩ በምሳሌ በማንሳት “አሁንም ሲሰራበት በቆየው አሰራር መቀጠል አለብን” ይላሉ፡፡
ነባሩ ኮሚቴ በበኩሉ ምርጫው እስኪደረግ ጊዜ ድረስ በጸሀፊነት ሲያገለግል የቆየው የነባሩ ኮሚቴ አባል በቦታው ላይ መቀጠል አለበት የሚል አቋም ያዘ፡፡ ይህ ግለሰብ የነባሩ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር የነበረ ሲሆን የጸሀፊነቱን ቦታ እንዲይዝ የተደረገው ቀድሞ በቦታው የነበረው ዲያቆን ወደ ሌላ ሀገር በድንገት በመሄዱ ምክንያት ነበር፡፡ ግለሰቡ በተተኪነት ቦታውን እንዲይዝ መደረጉን በማስታወስ አስተዳዳሪው በቀድሞ አቋማቸው ይጸናሉ፡፡ ለዚህ ውዝግብ መፍትሄ እንዲሰጥ የሚጠበቀው የቤተክርስቲያኑ ቦርድ ነበር፡፡ አባላቱ በየጊዜው ባገኙት እድል ወደ ውጭ ሀገር በመሄዳቸው እና በፍቃዳቸው ከስልጣናቸው በመልቀቃቸው ቁጥሩ የተመናመነው ቦርዱ የሚመራው በአንድ ግለሰብ ነው፡፡
እኚህ ግለሰብ ቦርዱን ወክለው መፍትሄ ያሉትን ይዘው መጡ፡፡ የቤተክርስቲያኑ ተጠሪ ለሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤልያስ በጻፉት ደብዳቤም ሁለቱ ወገኖች መካከል መግባባት ባለመቻላቸው የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት እንዳይጓደል እና በእንጥልጥል ያሉ ጉዳዮች እንዲፈቱ ጊዜያዊ ኮሚቴ መመደብ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ይህ ጊዜያዊ ኮሚቴ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ኃይለ እየሱስ እማኘውን፣ የቤተክርስቲያኒቱ የስብከተ ወንጌል ሊቀመንበር ቀሲስ ፀሐይ ደስታ እና አንድ ምዕመን ያሉበት እንደሆነ ደብዳቤው ያሳውቃል፡፡ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ይህንን ጊዜያዊ ኮሚቴ “አልቀበልም” ይላሉ፡፡
ይህንን ምላሽ የሰማው አንድ አባል ብቻ የቀሩት የቤተክርስቲያኒቱ ቦርድ ከነባሩ የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ ጋር በመሆን ለብጹዕ አቡነ ኤልያስ በድጋሚ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ የደብዳቤው ጠቅላላ ሐሳብ ነባሩ ኮሚቴ በጊዜያዊነት ስራውን ይቀጥል የሚል ነው፡፡ ይህ ውሳኔ የተወሰነው “ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር” እንደሆነ ደብዳቤው ይጠቅሳል፡፡ ይህ አባባል የቤተክርስቲያኒቱን ሕግ ደንብ የሚጥስ ነበር፡፡ በሕገ ደንቡ አንቀጽ ሰባት መሰረት ማንኛውም የዲሲፕሊን ጉዳዮችን ሰምቶ የመወሰን ስልጣን የተሰጠው ጠቅላላ ጉባኤው ነበር፡፡ በደብዳቤው የተጠቀሰው “የሚመለከተው አካል” ጠቅላላ ጉባኤ መሆን ነበረበት፡፡ ይህ ችግር ለጠቅላላ ጉባኤው አልቀረበምም፤ በደብዳቤው የተጠቀሰው ውሳኔም አልተላለፈም፡፡
በቦርዱ እና በነባሩ የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ ትብብር የተጻፈው ደብዳቤ ለአቡነ ኤልያስ የተላከው እ.ኤ.አ ኤፕሪል 1 ቀን 2011 ነበር፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን አቡነ ኤልያስ ጉዳዩን ሰምተው በተመሳሳይ ቀን ከስዊድን ስቶክሆልም በተመሳሳይ ቀን ለቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የጻፉት ደብዳቤ መድረሱ ነው፡፡ የተጻፈው ደብዳቤ ሳይደርስ አቡነ ኤልያስ ችግር እንዳለ “በተለያየ አቅጣጫ” እንደደረሳቸው በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡ “ቀድሞ ሲሰራበት በነበረው ሕግ መሠረት እየተሰራ እንዲቆይ” የሚል ውሳኔም አስተላልፈዋል፡፡
ይህም ብጹዕነታቸው ውሳኔያቸውን ያስተላለፉት ከአንድ ወገን በሰሚ ሰሚ በደረሳቸው መረጃ ላይ በመመስረት እንደሆነ ያሳያል፡፡ በቤተክርስያኒቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታየውን ችግር ወደ ካምፓላ በመምጣት እና ምዕመናን በማነጋገር እንዲፈቱ በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ልመናም እንዳልተቀበሉ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የአቡነ ኤልያስ ውሳኔ ነባሩ ኮሜቴ “ቀድሞ ሲሰራበት በነበረው ይቀጥል ሲሉ እኛን ማለታቸው ነው” እንዲል አድርጎታል፡፡
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወደ አስራ አምስት የሚጠጉ ምዕመናን በራስ አነሳሽነት የቦርዱ ብቸኛ አባል የሆኑትን ግለሰብ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ለማነጋገር ይሞክራሉ፡፡ ጥረታቸው ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ በስተመጨረሻ ይሳካላቸዋል፡፡ ምዕመናኑ “ይህ ነገር በእርጋታ ይፈታ፤ ስብሰባ ይጠራ” የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ ቦርዱ በአሁኑ ወቅት ስብሰባ መጥራት “ችግር ያመጣል” በሚል ያዘገየዋል፡፡
ስብሰባው ሳይካሄድ ከአቡነ ኤልያስ ሌላ ደብዳቤ ወደ ካምፓላ ይላካል፡፡ ደብዳቤው የቤተክርስቲያኔ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ኃይለ እየሱስ እማኘው ከቦታቸው ተነስተው የቤተክርስቲያኒቱ የስብከተ ወንጌል ሊቀመንበር እና ቀዳሽ ቄስ የሆኑት ቀሲስ ፀሐይ ደስታ በምትካቸው መተካታቸውን የሚገልጽ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ለአብዛኛው ምዕመን የሚዋጥ አልነበረም፡፡
ቀሲስ ፀሐይ ደስታ በበኩላቸው በአቡነ ኤልያስ የተሾሞበትን ደብዳቤ በመያዝ በጠበቃ አማካይነት ለአባ ኃይለ እየሱስ እና ለሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች ደብዳቤ መጻፍ ይጀምራሉ፡፡ ለአባ ኃይለ እየሱስ በአምስት የተለያየ ጊዜ እንዲደርሳቸው የተደረገው ደብዳቤ በአስቸኳይ ከቤተክርስቲያን ለቀው እንዲወጡ እና በእጃቸው ያለውን ንብረት እንዲያስረክቡ የሚያዝ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር አልቆሞም ላሏቸውን መዘምራን ደግሞ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በራስ ተነሳሽነት የተሰባሰቡት ምዕመናን የስልጣን ሽግግሩ ቆሞ ስብሰባ እንዲጠራ የሚያደርጉትን ግፊት ይቀጥላሉ፡፡ ቦርዱ በስተመጨረሻ ስብሰባ ለመጥራት ይስማማል፡፡ በመጀመሪያው የስብሰባ ጥሪ የነባር ኮሚቴ አባላት ባለመገኘታቸው ለሌላ ቀን ይተላለፋል፡፡ በሁለተኛው የስብሰባ ጥሪ ደግሞ “ኮረም አልተሟላም” የሚል ምክንያት ከነባር ኮሚቴ አባላት ይቀርባል፡፡ “ኮረም አልተሟላም” የተባለው ከዚህ ቀደም የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ መዘምራን እና ዲያቆናት አባላት አይደሉም የሚል መከራከሪያ ከነባር ኮሚቴው በመቅረቡ ነው፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ያቀረቡት መዘምራን እና ዲያቆናቱ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ክፍያ የማይከፍሉ መሆናቸውን ነው፡፡
የመዘምራን እና ዲያቆናት ክፍያ ከዚህ ቀደም ጥያቄ ሆኖ አያውቅም፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ህገ ደንብ አንቀጽ 14 ቁጥር 2 መሰረት በቂ በሆነ ምክንያት መዋጮ ለመክፈል ያልቻለ አባል ለካህናት አባቶች አመልክቶ እንዳይከፍል ይደረጋል፡፡ በዚህም መሰረት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንዳይከፍሉ ተወስኖ ላለፉት 10 ዓመታት ይኸው ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ ዲያቆናት እና መዘምራን በጠቅላላ ጉባኤው ያለችግር ይሳተፉ ነበር፡፡ ሲመርጡም ሆነ ሲመረጡ ቆይተዋል፡፡
ይህ እውነታ ግን በነባር የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ አባላት ተቀባይነት አላገኘም፡፡ “ኮረም አልተሟላም” የሚል ምክንያትን ለመጠቀም የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥር መቀነስ ነበረበትና ዲያቆናት እና መዘምራን አባላት አይደሉም ተባሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ጭቅጭቅ ተፈጠሮ ነበር፡፡ ስብሰባውም እንዲበተን ተደረገ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ለአራት ጊዜ ያህል የተሸጋገረ ስብሰባ ጉዳይ ያሳሰባቸው ምዕመናን በጠበቃ አማካይነት የቦርዱ ብቸኛ አባል የሆኑት ግለሰብ ሌላ ስብሰባ እንዲጠሩ ደብዳቤ ይጽፋሉ፡፡
በምዕመናኑ ግፊት የቦርዱ ብቸኛ አባል የሆኑት ግለሰብ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሌላ ስብሰባ ለመጥራት ተገደዱ፡፡ ከዚህ ስብሰባ የሚጠበቀው የመተዳደሪያ ሕገ ደንቡን ለማሻሻል እና የአዲስ ሰበካ ጉባኤ ምርጫ ለማካሄድ አስመራጭ ኮሚቴ ማስመረጥ ነበር፡፡ “የመተዳደሪያ ሕገ ደንቡን ማሻሻል” የሚለው አጀንዳ በሌላ ጊዜ እንዲታይ ተወስኖ አስመራጭ ኮሚቴ ይመረጥ አይመረጥ በሚለው ድምጽ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው ሁለት ሶስተኛ ድምጽም አስመራጭ ኮሚቴ እንዲመረጥ ተወስኖ ምርጫ ተካሄደ፡፡ ነባሩ ኮሚቴ ግን የአስመራጭ ኮሚቴውን ምርጫ ተቃውሞ ልዩነቱን አስመዝግቦ ነበር፡፡ በዕለቱ የተመረጠው አስመራጭ ኮሚቴ የአዲስ ሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ አባላትን ለማስመረጥ ጥቅምት 5 ቀን 2003 ዓ.ም (ኦክቶበር 16) ቀን ቆርጦ ስብሰባው ተጠናቀቀ፡፡
ከዚህ ቀደም የታዩ አለመስማማቶች ላይ ተመስርቶ ችግር እንዳይፈጠር በመስጋት አስመራጭ ኮሚቴው ጉዳዩን ቤተክርስቲያኑ ለሚገኝበት አካባቢ ፖሊስ ያሳውቃል፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴውን ስጋት የሚያጠናክሩ እና ምርጫውን ለማደናቀፍ ያሰቡ ሰዎች እንዳሉ በካምፓላ ጭምጭምታዎች መሰማት ጀመሩ፡፡ ከምርጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የተከሰተው ግን ጉዳዩ የደረሰበትን አሳሳቢ ደረጃ አመላካች ነበር፡፡
በጥቅምት 5 (ኦክቶበር 16) ዋዜማ በቤተክርስቲያኒቱ ግቢ የሚገኘው የሰንበት ትምህርት ቤት እንዲታሸግ ተደረገ፡፡ በግቢው ውስጥ የሚገኘው የዲያቆናት መኖሪያም ተመሳሳይ ዕጣ ገጠመው፡፡ በምርጫው ዕለት ምዕመናን እንዲጠቀሙባቸው ታስበው የተደረደሩ ወንበሮች ተሰብሰበው በአዳራሽ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ተቆለፈባቸው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ የግቢ በር እንዲዘጋ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ሰምተዋል፡፡
በምርጫው ዋዜማ ምሽት የተከሰተው ግን ማንም ያልገመተው ነበር፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ግድም ሲቪል የለበሱ ነገር ግን ከኡጋንዳ ፖሊስ መምጣታቸውን የሚናገሩ ግለሰቦች በፖሊስ መኪና በመሆን ወደ ቤተክርስቲያኑ ይመጣሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ተልከው መምጣታቸውንም ይናገራሉ፡፡ የኤምባሲው ባልደረባ የሆነ አንድ ሰው ስልክ ቁጥርም ለጠያቂዎቻቸው ያሳያሉ፡፡
ፖሊሶቹን አናግረዋል የተባሉ ሰዎች ከሌሎች ጋር በመሆን ለተለያዩ የካምፓላ ነዋሪዎች በየሞባይሎቻቸው የአጭር ጽሁፍ መልዕክት (ኤስ.ኤም.ኤስ) ይልካሉ፡፡ መልዕክቱ “የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለሊቱን ቤተክርስቲያኒቱን ሊወር ነው” የሚል ሲሆን ፖሊሶቹ ሰጡ የተባለው የሞባይል ስልክ ቁጥርም ተጠቅሷል፡፡ ያንን ቁጥር ለማጣራት የሞከሩ በእርግጥም የኤምባሲው ባልደረባ የሆነ ሰው ስልክ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ይህ ጉዳዩን በገለልተኝነት ሲመለከቱ የነበሩትን ሁሉ ያስደነግጥ እና በበነጋታው ወደ ቤተክርስቲያን ጉዳዩን ለማጣራት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል፡፡
በበነጋታው የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ ዲያቆናት፣ ምዕመናን ታሰሩ፡፡ በኢትዮ ሚዲያ ድረ-ገጽ ላይ እንደወጣው ወያኔ ቤተክርስቲያኑን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት የከሸፈበት ሳይሆን አወዛጋቢ የሆነው የሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫ እንዳይካሄድ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ድራማ ነው፡፡ በእርግጥ ወያኔ የተፈጠረውን ክፍተት አይጠቀምበትም አንልም፡፡ እንደ እኛ ቤተክርስቲያን የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚራኮቱ ግለሰቦች በሚፈጥሩት ክፍተት ተጠቅሞ ወያኔ የፈለገውን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ እንዳይከሰት ግን መሰረታዊው የቤተክርስቲያኒቱ ችግር በአስቸኳይ መፈታት ይኖርበታል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ወደ ካምፓላ መምጣት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ ያሳሰባቸው ምዕመናን በቤተክርስቲያኒቱ ቦርድ በኩል መፍትሄ እንዲገኝ የጣሩትን ያህል ብጹዕ አቡነ ኤልያስም እየሆነ ያለውን እንዲያውቁት ለማስረዳት ጥረዋል፡፡ የምዕመናኑ ፊርማ የሰፈሩባቸው እና ሰፋ ያሉ ሀሳቦችን ያያዙ ከእንድም ሶስት ደብዳቤዎች ለብጹዕነታቸው ተልኳል፡፡ ምዕመናኑ ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት በማሰብ ለሕጋዊው ሲኖዶስ ሁለት ጊዜ ያህል ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
ምዕመናኑ ተስፋ ሳይቆርጡ የብጹዕ አቡነ ኤልያስን መልስ በመጠባበቅ ላይ እያሉ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ክስተት ተፈጸመ፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በሳምንቱ ጥቀምት 12 (ኦክቶበር 23) ሌላ አሳዛኝ ድርጊት ተከናወነ፡፡ በዕለተ ሰንበት ቅዳሴ ሊሳተፉ የመጡ አስራ ስምንት የሚሆኑ መዘምራን ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ እንዳይገቡ በፖሊስ አማካኝነት ተከልክለዋል፡፡ ለአንዳንዶቹም ከዚህ በኋላ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ ድርሽ እንዳይሉ የእገዳ ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በየጊዜው እንግልት እየደረሰባቸው የሚገኘው መዘምራን ምዕመናኑ ከቅዳሴ ሲወጡ ጠብቀው እግዚያብሔርን በመዝሙር አመሰግነዋል፡፡
በየጊዜው እየተባበሰ የመጣውን ይህ ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ወደ ካምፓላ መጥተው ምዕመናንን፣ አገልጋዮችን፣ የቦርድ እና የሰበካ ጉባኤ ኮሚቴ አባላትን ማነጋገር የቻሉ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ሕገ ደንብ አንቀጽ 29 ላይ ሊቀ ጳጳሱ የሚቀርቡለትን ቤተክርስቲያኒቱን የሚመለከቱ ጉዳዩችን መርምሮ የመጨረሻውን ገላጋይ ውሳኔ የመስጠት ውሳኔ ይኖረዋል ይላል፡፡ በርካታ ምዕመናንም የሚፈልጉት ይህንን ነው፡፡ ቁልፉ ያለው ብጹዕ አቡነ ኤልያስ ጋር ነው፡፡



