አስተሳሰብህ የሰፈር
አጨዋወትህ ለማፈር
ሁኔታህ ሁሉ ባዳ ነው
አንተን ማስቀመጥ ዕዳ ነው።
ተመስገን ተካ 1990 ዓ.ም.

ሰሞኑን የጌቶቻችንን የትጥቅ ትግል ታሪክ የሚዘግቡ መፃሕፍት ታትመው እየወጡ ነው፡፡ በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው። የተዋጋነው ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ ጭቆናን ለማስወገድ፣ ብሄረሰቦችን እኩያ ለማድረግ ስንል ነው የሚል ይዘት አላቸው። ማንም አንጋፋ ታጋይ፣ ያማረኝን ለመብላት፣ ጄት የሆነ መኪና ለመንዳት፣ የእሥር ቤት ቁልፍ በእጄ ለማስገባት ስል ነው የተዋጋሁት ብሎ እንዲተርክልን አንጠብቀውም።


የህወሓት ባለድርሳናት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትዝታን በመገረብ ላይ የተጠመዱት በምን ምክንያት ነው? ከዘመኑ ለማምለጥ ስለፈለጉ ይመስለኛል። የፈጠሩት ቡትቶና ሰንሰለት የለበሰ ዘመን ራሳቸውንም ሳያስደነግጣቸው አልቀረም። እናም በታሪክ ደን ውስጥ ገብቶ መደበቅ የመረጡ መሰለኝ።
ታሪክን እንደ አደጋ ጊዜ መውጫ መጠቀም ብዙ ጣጣ አለው። በሐቅና በሰመመን መካከል ያለውን ልዩነት ያስክዳል። በቅርቡ የታተመ እና በጎረቤቴ በአክሱም ሆቴል የተመረቀ አንድ ድርሳን ለዚህ ማሳያ ነው። የድርሳኑን ስምም ሆነ የደራሲውን ማንነት ማስተዋወቅ ለአንባቢ ጠቃሚ አልመሰለኝም። መጽሐፉ ከለመድነው ቤተመንግስታዊ ታሪክ የተለየ ነገር የለውም። ምናልባት እንደሰበር ዜና የወሰድኩለት የኢትዮጵያን እሴቶች (Values) የአክሱም እና የሸዋ ብሎ መክፈሉ ነው። ክፍፍሉ ምርጥ ምርጡ የአክሱም፤ ምራጭ ምራጩ የሸዋ የሚል የዋህ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል። የባለድርሳኑን አጠቃላይ ሀሳብ ይወከላል ብዬ ያሰብኩትን አንቀጽ ልጥቀስላችሁ።
.....የአክሱማውያን አርአያ ክርስትና ሃይማኖት የግዕዝ ስልጣኔ የትስስር ገመድ ከሰሜን ደገኛ ኢትዮጵያዊያን በተለይ የትግራይ እና የአሁንዋ ኤርትራ ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ እሴቶች ሌላውን ህዝብ የሚቃወሙ አልነበሩም። ወይም ማህበራዊ ስርዓት እና ዲሲፕሊን የሌላቸው ምልክቶች አልነበሩም። የክርስትና ሃይማኖትን ካወቁ ጊዜ ጀምሮ አክሱማውያን ባርነትን የተቃወሙና ሌሎቹን ያስተማሩ ህዝቦች መሆናቸውን ታሪክ ዘግቦታል። እውነተኛ ተከታዮች ይህንን አጥብቀው ተቀብለዋል። የሸዋ ገዥዎች ግን እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መዳረሻ ድረስ የባርያ ንግድ ወንጀል ውስጥ ተዘፍቀው የአክሱምን ሰለሞናዊ የዘር ሀረግ መናፈቃቸው ሌላው ቅዥትና ስህተት ነበር። አክሱምን ለመሆን ወይ መወለድ ወይ ባህሉን መከተል ወይ ሁለቱን መሆን ግድ ይላል.. በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ከቀረቡ ትንተናዎች መካከል በአስገራሚነቱ ይህንን አንቀፅ የሚወዳደር ያለ አይመስለኝም። ፀሐፊው አክሱም መወለዱን እንደ ብልጫ በመቁጠር ተወላጅነትን የአክሱማዊነት አንድ መስፈርት አድርጎ ወስዶታል። እዚህ ስህተት ውስጥ የገባው አክሱማዊ መንግስትን ከአክሱም ከተማ ጋር በማምታታት ይመስለኛል።
አክሱማዊ መንግስት ማለት የአክሱምን አውራጃ መዲናው ያደረገ ጥንታዊ የኢትዮጵያ መንግስት ማለት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም።
ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ይህንን ሲያረጋግጡ ..የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ከተማው ድሮ አክሱም ነበረ። አክሱም መሰረተ መንግስት የሆነው አባቶቻችን ስለመረጡት እንጂ ምናልባት ከሌሎቹ አውራጃዎች የተሻለ ሆኖ አይደለም.. መንግስትና የህዝብ አስተዳደር ገፅ 58)
ፀሐፊው ለአክሱም ነገስታት ልዩ የጎሳ መለዮ ሊያቀዳጃቸው ፈልጓል። ግን መሰረት የለውም። ጥንታዊ የአክሱም ነገስታት ብሄረሰባቸውን በግልፅ አልነገሩንም። በእርግጥ ትልቁ ኢዛና በአንድ የድንጋይ ብራናው ላይ ..ብእሴ ሐሌን.. (የሐሌን ተወላጅ) ብሎ ራሱን ያስተዋውቃል። ኢትዮጵያ ከ80 የማያንሱ ብሔረሰቦች አገር መሆኗን ባውቅም፣ የሐሌን ብሄረሰብ በዝርዝሩ ውስጥ እንደሌለ ርግጠኛ ነኝ። ምናልባት እንደ ጋፋት ወይም እንደ ማያ ከታሪካችን ባቡር ላይ ተንጠባጥቦ የቀረ ፉርጎ ይሆን? ኮንቲ ሮሲኒ ቢቸግረው አረብ ውስጥ ይፈልገዋል፡፡ በጥንታዊ አክሱም ዙሪያ ዝርዝር ጥናት ያካሄዱት ሊቃውንት አንዱ ሩሲያው ዩሪ ኮብስቻኖቭ የአክሱም ነገስታት ጎሳ ስም እና የሰራዊታቸውን ፍቺ ማግኘት የተሳካ እንዳልነበረ ፅፈዋል። “Attempts have been made to find translation for names of the armies and ethnic names of the kings, but they have not been very successful”
ተጨባጩ ታሪክ አክሱማውያን ነገስታት የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ውርስ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ አክሱም በፍርስራሾቿ ቅሪቶች ላይ ባህላዊ መልኳን እንጂ
የነገስታቷን DNA አልተወችልንም።
..ባርነት የሸዋ፣ አርነት የአክሱም..
ከዚህ እስከዚህ የኔ፣ ከዚህ እስከዚያ የእናንተ ብሎ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚከፍል ባለድርሳን ታሪክን ከአድልኦ ነፃ ሊያወጣት አይችልም። ፀሐፊው አክሱም የእኔ፣ ሸዋ የእነሱ ብሎ ከከፈለ በኋላ አክሱምን በተመለከተ ጭልጥ ያለ አለባባሽነት (Romanticism) ውስጥ ይገባል። ገብቶም ..ክርስትና ሃይማኖትን ካወቁ ጊዜ ጀምሮ አክሱማውያን ባርነትን የተቃወሙና ለሌሎች ያስተማሩ ህዝቦቹ መሆናቸውን ታሪክ ዘግቦታል.. እያለ ይኳሻል። ታሪክ ዘግቦታል ቢልም ዘገባውን አላቀረበልንም። በአረፍተ ነገሩ ላይ እንደሚታየው አክሱማውያንን ከባርያ ፍንገላ ባህል የሚያስጥላቸው የተቀበሉት ክርስትና ነው ብሎ የሚያስብ ይመስላል።
ክርስትና የቄሳርን ለቄሳር ብሎ፣ ነባሩ የፖለቲካ ስርዓት እንዲረጋ ከማፅደቅ በቀር ባርነትን የሚቃወም ህግ የለውም። ቢኖረው ኑሮ ለሸዋዎችም ይደርሳቸው ነበር። ታሪክ የሚነግረን አክሱማውያን አባቶቻችን፣ ባርነትን የኢኮኖሚ ዋልታ አድርገው ማየታቸው ነው። Slavery formed a necessary part of the ecomomic base of Axum and continued to exist in Ethiopia for more than thousand years (Yuri. M.Kobschanov: Axum) ኢዛና ከተጠመቀ በኋላ ባደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ..ፈጣሪ 214 ወንዶች፣ 415 ሴቶችን በምርኮ እንደሰጠው ራሱ ይነግረናል። (ዘወሀበኒ እግዚአ ሰማይ ፄዋ ዕድ 2)04 ፄዋ አንስት 4)05 (የኢዛና የድንጋይ ፅሁፍ)
ሌላው ቢቀር በአረብ ትረካ ከመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች አንዱ የሆነው ቢላል ቤተሰቦቹ በባርነት ተፈንግለው ወደ አረብ የወጡት በአክሱም ዘመነ መንግስት ነው።
ስለዚህ አክሱማውያን አባቶቻችንን ባርነት አይመለከታቸውም ማለት ጭው ያለ ሰመመን እንጂ ታሪክ አይሆንም። የሸዋ ገዢዎች የአክሱማዊያን ወራሾች ናቸውና እንደ ዘመናቸው ጠባይ ባርያ ቢያሳድሩ አይገርምም፡፡ ባርያ ማሳደራቸውን የአካባቢያቸው ልዩ ጠባይ አድርጎ መውሰድ ግን ሐቅም ፋይዳም የለውም። በሸዋ ባርነትን ለማስወገድ ተግባራዊ ጥረት ነበር።
ባለድርሳኑ አፄ ምኒልክን ባርያ በማሳደራቸው ሲዘልፋቸው ባርያን ነፃ ለማውጣት ያደረጉትን ጥረት ረስቶ ወይም ቸል ብሎ ሊሆን ይቻላልና ላስታውሰው። ንጉስ ምኒልክ ለንጉስ ሊዎፖልድ በ1840ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ሰራዊታቸው የማረካቸውን አንዴ ሃያ ሺህ ሌላ ጊዜ አምሳ ሺህ የሚገመቱ ምርኮኞች ወደ ወላጆቻቸው መልሰው መላካቸውን ካስታወሱ በኋላ ይህንን ያደረጉበትን ምክንያት ሲገልፁ ..የክርስትያን ስራአት ባላቸው ነገስታት አገር ሁሉ ባርያ አይሸጥም እሚሉ ትዛዝ ብሰማ.. ብለው ከባርያ ነፃነት ህግ ጋር መስማማታቸውን ይገልፃሉ፡፡ (ዝርዝሩን ለማግኘት ከፈለጉ ሩቢንሰን ያዘጋጀውን Internal rivalies and foreign threats ይመልከቱ)
አጤ ሚኒልክን መርገም ለህወሓት ልሂቃን አዲስ አይደለም። እስካሁን ድረስ የነበረው ትችት በድህረ አድዋ ..ጉድለት.. ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡ ሚዛናዊነት እስካለው ድረስ እንዲህ አይነት ትችት አይጠላም። አባ ዳኘው ባንድ አዋጃቸው ..ንጉስህን መርቅ ንጉስህን ርገም.. በማለት ለሚዛናዊ ትችት ሆደ ሰፊ መሆናቸውን ይነግሩናል። አሁን ግን የምንሰማው ትችት አጤ ሚኒልክ አክሱማዊ ሳይሆኑ ሰለሞናዊ ነኝ አሉ የሚል ይዘት አለው። የዘመናችን የዴሞክራሲ ጥያቄ በባላባትነት ጥያቄ የተተካ መሰለኝ። ባለድርሳኑ ያሉትን ላስታውሳችሁ .....የሸዋ ነገስታት የአክሱምን ሰለሞናዊ የዘር ሀረግ መናፈቃቸው ቅዠትና ስህተት ነበር..
በባለድርሳኑ ቤት አክሱማዊና ሰለሞናዊ አንድ ናቸው። በየት በኩል? የክብረ ነገስትን ትረካ ለስምምነት ያክል እውነት ነው ብለን ብንወስደው እንኳ ሰለሞን ከሳባ ጋር አንሶላ የተጋፈፈው አክሱም ሳትቆረቆር መቶ አመታት አስቀድሞ መሆን አለበት። ..የአክሱም የዘር ሐረግ.. የሚለው ትርጉም እንደሌላው አሳይቻለሁ፡፡ ትርጉም ያለው አክሱማዊ ባህል የሚለው ነው። እሱን እንመልከት።
አጤ ምኒልክ የሰለሞን ልጅ ነኝ የሚሉት ልቦለድ ከሆነ፣ አክሱማዊውን ባህል ተከትለው ነው ማለት እንችላለን፡፡ ንጉስ ኢዛና በቅድመ ክርስትና ራሱን ወልደ መሐረም ብሎ ይጠራ ነበር፡፡ መሐረም የጦር አምላክ ሲሆን ለዘመናዊ ሰው ልቦለድ ነው።
አጤ ሚኒልክ እንደ አክሱም ነገስታት በኃይል ተስፋፊ ነበሩ። እንደ አክሱም ነገስታት የውጭ አገር ትምህርትን የማይጠየፉ ነበሩ። እንደ አክሱም ነገስታት ስልጣናቸውን ለሚስታቸው የሚያካፍሉ ነበሩ። እንደ አክሱም ነገስታት በስማቸው ሳንቲም ያስቀረፁ ነበሩ። ይህን ሁሉ ሲታይ፣ አጤ ሚኒልክን ለአክሱም ባዕድ ማድረግ ቅዠትና ስህተት መሆኑ ይገባሃል። በደንብ ከመረመርነው ሸዋም ሆነ ትግራይ የማይበላለጡ የኢትዮጵያ ጣቶች ናቸው። ባንዱ ታሪክና በሌላው ታሪክ መሃል እንደ ቼዝ ሰሌዳ ፍንትው ብሎ የሚታይ ድንበር የለም። ደሞኮ ታሪካችን የግጭቶችና የጭቆና ብቻ አይደለም። ግጭቶችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችም የታሪካችን አንድ አካል ናቸው። አፄ ዮሐንስና በንጉስ ምኒልክ መካከል የተከሰተው የግጭት ታሪክ ጋብ ብሎ በሁለቱ ሃያላን መካከል የተደረጉ የስጦታ ቅብብሎች፣ ሽምግልናዎች እና የጋብቻ ዝምድናዎች ይታወሱ። ያንድነት መንፈስን ማደስ የምንችለው በዚህ መንገድ ይመስለኛል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ