እንደምን አላችሁልኝ ውድ አንባቢያን ወገኖቼ፦ ዛሬም አንደተለመደው ከሳይበሩ ዓለም ሰሞነኛ አክራሞት የቃረምኩት ጦምሬ ውድ ግዜያችሁን ልሻማ ብቅ ብያለሁ።

 

 

የዛሬው ጽሁፌ የተጠነሰሰው ከጥቂት ወራት በፊት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና መ/አ አያልሰው በኢሣት መስኮት ሙግት ወይስ ውይይት ? ባደረጉ ሰሞን ነበር። ይሁንና ጥንሡን አጥርቶ ለአንባቢ ለማቅረብ ብዙ ግዜ ወሰደብኝ። የግዜን ነገር ታውቁት የለ..!

 

የሆነው ሆኖ ይህ ጉዳይ አሁንም ድረስ “በላ-ልበልሃ” እያባባለ ያለ በመሆኑ ጽሁፌ እንደማይቆረፍድ ተስፋ አደርጋለሁ። አብይ መሆን ባይገባውም ለግዜው አብይ የመወያያ ጉዳይ የሆነው ይህው በአቶ አንዳርጋቸውና በመ/አ አያልሰው መካከል የተንጸባረቀው አይነት የአመለካከት ልዩነት ይመስለኛል።

 

የአመለካከት ልዩነቱ በአጭሩ ሲገለጽ “አንድነትን ተቀብሎ፤ ተማምሎ ወደ ውይይት መሄድ” የሚልና “በውይይት ወደ አንድነት መሄድ” የሚል ይመስለኛል፡፡ ማን የቱን እንደሚል ይጠፋችኋል አልልም።

 

ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ወይም በአጭሩ ከላይ የገለጽኩትን በዝርዝር ስንመለከተው፡፤ ራሳቸውን “የአንድነት ኃይሎች” ብለው የሚጠሩት(ስማቸውም ላይ ችግር ያለ ይመስለኛል! ዛሬም አንድነትን በሃይል ለማምጣት አስበው ከሆነ ማለቴ ነው) በኢትዮጵያ አንድነትን ከማያምንና ከማይቀበል ማንኛውም ወገን ጋር የሚደረግ ውይይትም ሆነ አብሮ የመስራት ስምምነት ሃገርን እንደመክዳት ይቆጠራል! ይላሉ። ለዚህም አባባላቸው ማእከል የሚያደርጉት ግንቦት7 ከኦነግና ከኦብነግ ጋር እያደረገ ያለውን አብሮ የመስራት ጅምር ነው።

 

ግንቦት7 ደግሞ በበኩሉ የኢትዮጵያ አንድነትን ተቀበሉ አትቀበሉ የሚለው ጥያቄ ከውይይት ሊያስቀረን አይገባም። ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር በውይይት ሊወለዱ የሚችሉ ስምምነቶችን ከወዲሁ ማጨናገፍ የለብንም። የኢትዮጵያ አንድነት እንደ ቅድመ ሁኔታ ባናስቀምጥም ከማንኛውም ወገን ጋር የምንወያየው ኢትዮጵያ በምትባለው አገር የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ መሆኑ በራሱ በቂ ገላጭ ነው። ቀሪው አንድነት ደግሞ በቅድሚያ ፊርማ ሳይሆን በቀና ውይይት ይወለዳል ብሎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በእንቅስቃሴውም ለውጥ እያየን ነው።

 

ለዚህ በቂ መገለጫው በቅርቡ በቴክሳስ ዳላስ ላይ በተደረገው ውይይት የኦነግ ዋና ጸሃፊ ከዚህ ቀደም ከየትኛውም የኦነግ አመራር አባል ባልሰማሁት መልክ ኦነግ ለዘመናት ይዞት ከቆየው አቋም እየተላቀቀ መሆኑን ያመላከተ ንግግር ማድረጋቸው ነው። የኦነግ ዋና ጸሃፊ ያደረጉት ንግግር እንዲሁ በአንድ ጀንበር የተገኘ ድንገታዊ የአቋም ለውጥ እንዳልሆነ ፤ የወቅቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እግር በእግር ለሚከታተለው ወገን የሚጠፋ አይመስለኝም። ከግንቦት7 ሰዎች ጋር በተደረገ በርካታ ዙር ውይይት የተወለደ መሆኑን ለማወቅ ቢያንስ ቢያንስ አቶ አንዳርጋቸው በዛው በቴክሳሱ ስብሰባ ያደረጉትን ንግግር ማድመጥ ይበቃ ይመስለኛል።

 

የፖለቲካ ሥራ ማለት ለኔ ይሄ ነው ። ልዩነትን ማጥበብ ማለትም ይህ ነው። የግንቦት7 ሰዎች ቅድመ ሁኔታን በመደርደር በውይይት የሚወለዱ ስምምነቶችን ከወዲሁ ማምከን አይገባም ማለታቸው ፤ እውነት አላቸው! እንድንል አድርገውናል። ይህችንስ ማን አየብን ያሰኘ መልካም ጅምር አሳይተውናል።

 

ይህን ስል በርግጥ ገና ጅምር ስራ መሆኑ አይጠፋኝም። ቢሆንም ጅምሩ ጥሩ ጅምር ነው ማለት ችኩልነት አይመስለኝም።

 

ኦነግ እንደ ድርጅት ለበርካታ አመታት ጂኦ ፖለቲካውን ያላገናዘበ የነጻነት ጥያቄ አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው። አሁንም ከዚሁ አመለካከት ያልተላቀቁ የድርጅቱ አካሎች ቢኖሩም፤ ቢያንስ ቢያንስ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ በመምከር የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት እንችላለን የሚል ራዕይ የያዘ ክፍል መኖሩ በራሱ እሰየው የሚያሰኝ ነው።

 

በሁለቱም በኩል አክራሪ፤ ወይም ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ወገኖች የግንቦት7ና የኦነግን አብሮ መስራት ሲቃወሙ ይሰማሉ። በተለይ የአንድነት ሃይሎች ነን የሚሉት፦ ግንቦት7ን የኢትዮጵያ አንድነትን ለድርድር እያቀረበ ነው ሲሉ ይከሳሉ፤ በኦነግም በኩል ተመሳሳይ ውንጀላ በነከማል ገልቹ ክንፍ ላይ እንደሚነሳ ግልጽ ነው፡፤

 

በኦነግ በኩል ያለውን የሃይል አሰላለፍ ባላውቅም ፤ በአንድነት ኃይሎች በኩል ያለው የሃይል አሰላለፍ ግን በኢህ.አ. ፓ “ቅሬተ-ግትርነት” ላይ ያማከለ፤ በሌለ ሃይልና በሌለ አንድነት ላይ ተመርኩዞ፤ አየር ላይ የሚንሳፈፍ፤ መሬት የማያርፍ “የቡሄ ዕለት የደነቆረ ሆያ ሆዬ ሲል ያረጃል” እንዲሉ አይነት ነው።

 

ኢ.ህ.አ.ፓ ከመከፈሉም በፊት ሆነ በኋላ (ሁለቱም ኢህአፓዎች) በኦነግ ላይ ያላቸው ውግዘትን ያማከለ አቋም አልተለወጠም ። በኦነግና በኢህአፓ መካከል የነበረው ተባብሮ የመስራት ችግር ዛሬም ከ(ዴ) ፊደል በስተቀር ምንም ለውጥ አላሳየም።

 

ኢ.ህ.አ.ፓ ከኦነግ ጋር ወይም ኦነግ ከኢ.ህ.አ.ፓዎች ጋር ያለው አብሮ ያለመስራት ችግር፤ ኢ.ህ.አ.ፓ “ለኢትዮጵያ አንድነት” ሲል ኦነግ “ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት” በሚል ከያዙት ተቃራኒ አላማዎች የሚመነጭ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ኢህአፓ “በኢትዮጵያ አንድነት ማመንን” ከውይይት በፊት አንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ እንደ ኦነግ ያለ ለነጻነት እታገላለሁ ብሎ ለ35 ረዥም አመታት ሲባዝን የኖረ ድርጅት ገና ለገና ከአንድ ተቃዋሚ ድርጅት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ለመወያየት ሲል ሊቀበለው የሚችል ቅድመ ሁኔታ አይደለም።

 

ስለዚህ በኢህአፓና በኦነግ መካከል ያለው ልዩነት አስከ ዛሬ ሊዘልቅ ችሏል።

 

ግንቦት7 ደግሞ ከኢህአፓና ኦነግ የቆየ ቅራኔ ልምድ በመቅሰም ይመስላል። “የኢትዮጵያ አንድነትን መቀበል” አንደ ቅድመ ሁኔታ ከማስቀመጥ ይልቅ ለውይይት መቀመጥ በማስቀደም መስራትን መርጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህም በመጠኑም ቢሆን ለውጥ አያሳየ ይመስለኛል።

 

ይሁንና ግንቦት7 ለውይይት ቅድሚያ በመስጠት በኦነግና በኢህአፓ መካከል ያልነበረውን አብሮ የመስራት ጅምር አያየ ባለበት በአሁኑ ወቅት በኢህአፓና በኦነግ መካከል የነበረውና ያለው የዘመናት ቅራኔ መልኩን ለውጦ በኢህአፓና ከኦነግ ጋር ለመስራት በፈቀዱ ድርጅቶች ላይ እየታየ ነው።ይህ እንግዲህ ችግሩ ጠቅለል ባለ መልክ፦ ነገር ግን ግልጽ በሆነ መንገድ ሲቀርብ ነው።

 

በኢህአፓ በኩል ከኦነግ ጋር ያለን ቅራኔ ለኢትዮጵያ አንድነት ካለን ቁርጠኝነት የሚመነጭ ነው የሚል ምክንያት ሲሰጠው ኖሯል። ይሁንና በቁርጠኝነት የቆሙለትን “የኢትዮጵያ አንድነት” እውን ለማድረግ ለዘመናት የተከተሉት አቅጣጫ እንዳልጠቀመ ተመልክተው፤ የአላማ ሳይሆን የስትራተጂ ለውጥ ለማድረግ አለመቻላቸው አስካሁንም የዘለቀ ትልቁ ችግራቸው ነው።

 

ባንድ ወቅት እኔም በኢ.ህ.አ ፓ ስር ለተሰዉት እውነተኛ የህዝብ ልጆች ስል ኢ.ህ.አ.ፓን እደገፍ ነበር። ሽንጤን ገትሬም እከራከር ነበር። ውሎ ሲያድር ግን ኢ.ህ.አ.ፓ የሚባል ድርጅት ከስም በስተቀር ምንም የሌለው አቅሙና ሃይሉ መግለጫ በማውጣት ላይ የተወሰነ ባዶ ድርጅት መሆኑን ልረዳ ችያለሁ፡፡ ጉድለቱን ለመሙላት ጥረቱ ቢኖር፤ ባዶነቱ በራሱ ባልከፋ ነበር። ቀስ በቀስ …. ሊደረስበት በቻለ ነበር። ነገር ግን የኢህአፓ አካሄድ ራስን በሚያጎለብት እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ ሊጎለብት ወይ ሊያድግ ይችላል ብለው ያሰቡትን ተቃዋሚ ድርጅት ማጥፋት ላይ ያታኮረ በመሆኑ እንሆ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

 

ኢ ህ አ ፓ ከሁለት እንደተከፈለ አንደኛው ወገን ማለትም ዴን ፊደል ጨምሮ የተገነጠለው ክፍል ለክፍፍሉ ምክንያት ብሎ የገለጸው ፦ በድርጅቱ ውስጥ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሆኑ አሰራሮች እየነገሱ በመሄዳቸው ይህንኑ ለማረም ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ነው። ሲል፦ ሌላው በአቶ እያሱ የሚመራው ወገን ደግሞ አንጃው ከወያኔ ጋር ለመስራት ይቻላል ብሎ አቋም በመውሰዱ ነው ብሎናል።

 

የሚገርመው ግን ሁለቱም ወገኖች ከክፍፍሉ በኋላ ምንም የአቋምም ሆነ የአመለካከት ለውጥ ያለማሳየታቸው ነው፡፤ እንደ ድርጅት ዛሬም ሁለቱም ከጽንፈኛና እኛ እናውቅልሃለን አካሄድ የወጡ አይመስሉም። በተለይ የብሄር ድርጅቶችን አስመልክተው ያላቸው አቋም አጥፍቶ መጥፋት አይነት በጠላትነት የመፈረጅ እንጂ የጎሳ ፖለቲካ የሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ “እውነታ” መሆኑን ለመቀበል የተዘጋጁ አይመስሉም። ከጥቂት ወራት በፊትም ከወደ ካናዳ በተደረገ አንድ የኢ.ሃ.አ.ፓ መራሽ ስብሰባም የብሄር ድርጅቶችን እንዋጋቸዋለን የሚል መፈከር ማድመጣችን ይታወሳል። ይህ ደግሞ ወቅታዊውን የፖለቲካ እውነታ ያላገናዘበ መፈክር ይመስለኛል። ዛሬ ወደድንም ጠላንም የጎሳ ድርጅቶች የሚታዩ የሚዳሰሱ ህያው ሕዝብ ያቀፉ እውነታዎች ናቸው። ስለዚህ ልንዋጋው የሚገባን የጎሳ ፖለቲካን እንጂ የጎሳ ድርጅቶችን አይደለም። የጎሳ ፖለቲካን ለመዋጋት የሚቻለው ደግሞ ሰራዊት አሰልፎ ነጋሪት ጎሽሞ ሳይሆን ፦ በጎሳ ፖለቲካ አምነው ከሚንቀሳቀሱ ወገኖች ጋር ሰፊና ተከታታይ ውይይት በማድረግ ነው።

 

ባጠቃላይ ኢ ህ አ ፓ ወያኔን ማስወገድ የሚቻለው በአመጽ ወይም ሃይልን ባማከለ ትግል ነው ከሚሉ ተቃዋሚዎች ጎራ ቢሆንም እያካሄደ ያለው ዘመቻ ግን በዚሁ ጎራ ያሉትን ወገኖችን ማብጠልጠል ነው። ይህ ደግሞ የ ኢ. ህ. አ.ፓ የተለመደ ባህሪ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል።

 

የኢ.ህ.አ.ፓ ትልቁ ትኩረት ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ መታየት እንጂ ዋናውን ጠላት ወያኔን ማስወገድ አይመስለኝም። ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ ለመውጣት ደግሞ ጠንካራ ተቃዋሚዎችን ማስወገድ ስለሚያስፈልግ ይህን እውን ለማድረግ ሲል ከወያኔም ጋር ለመተባበር የመይመለስ ድርጅት መሆኑን በቅንጅት ምስረታ ማግስት በወያኔ የፓልቶክ ሩሞች ገብተው ያደርጉት የነበረውን የምናስታውስ እናስታውሰዋለን። ዛሬም ይህነኑ እየደገሙ ነው። ዛሬ ለ ኢ. ህ. አ.ፓ ድጋፍ እየሰጡ ያሉት በግንቦት7ና ኦነግ ትብብር ስጋት የያዛቸው፤ በአንድና አንድ ምክንያት የአመጽና የትጥቅ ትግሉን አምርረው የሚቃወሙ፤ በሰላማዊ ትግል ስም ወያኔን ለይስሙላ የሚቃወሙ ነገር ግን የወያኔ ፍጻሜን ተከትሎ የሚሆነው ነገር የሚያሰጋቸው የውስጥ አርበኞች ናቸው፡፤ ኢህ.አ.ፓ ግንቦት7 ከኦነግ ጋር የሚያደርገውን አብሮ የመስራት እንቅስቃሴ የሚቃወመው ለምንድነው? እውን የኢትዮጵያ አንድነት አስግቶት ነውን? እውን በግንቦት7 ውስጥ ያሉ ወገኖች የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ስራ ይሰራሉ ብሎ አምኖ ነውን? ይህ ቢሆን ኖሮ ከግንቦት7 ጋር አብሮ ለመስራት ጥሪ ባልቀረበ ነበር። ስለዚህ ኢህ.አ.ፓ የግንቦት7ና የኦነግን አብሮ መስራት የሚቃወመው እነሱ ለዘመናት ሊፈጥሩት ያልቻሉትን አብሮ የመስራት ድባብ በኦነግና በግንቦት7 መካከል ሲፈጠር ለማየት ባለመፈለጋቸው ብቻ ነው። አለቀ። እንጂ የኢትዮጵያ አንድነት ስጋት ላይ ሲወድቅ ከማንም በተለየ ለነሱ ብቻ በራዕይ የሚታያቸው ልዩ ዜጎች ሆነው አይደለም። እኔም አቶ እያሱም ሆኑ አቶ መርሻ ወይም የግንቦት ሰባት ሰዎች በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያለን ወይም ሊኖረን የሚችለው አቋም የአንዳችን ከአንዳችን የሚለይበት የሚበልጥበት ምንም ምክንያት የለም። እንደ ዜጋ ሁላችንም አንድነቷን እንሻለን። ልዩነቱ ያለው፤ ይህን እንፈልገዋለን የምንለውን አንድነት ለማምጣት የምንሞክርበት መንገድ ላይ ነው። አንዱ በፉከራ፤ ሌላው በስራ፤ …ይሀው ነው።

 

በመንፈሳዊው አለም የእምነት ጽናት ብቻ መንግስተ ሰማያትን እንደሚያወርስ የህይወት ቃል ይነግረናል ። በፖለቲካው አለም ግን የአላማ(እምነት) ጽናት ብቻ በቂ አይደለም። በፖለቲከው አለም ከአላማ ጽናት ባሻገር ፤ አላማውን ከግብ ለማድረስ አካሄድንና እንቅስቃሴን ከወቅቱ የሕዝብ ልብ ትርታና የተቃራኒ ወገን ስነ፥ልቦና አንጻር የመቃኘትን ልዩ ዘዴ ይጠይቃል። ኢህ.አ.ፓ ግን ትናትም ዛሬም ከአፋዊና መግለጫዊ ቁርጠኝነት ባሻገር አላማውን ለማሳካት ወቅቱን የዋጀ የስታራተጂ ለውጥ ለመድረግ አልቻለም ብቻ ሳይሆን ሲሞክርም አልታየም። አሁን ግልጽ እንደሆነው ደግሞ አቅምም የለውም።

 

“ባምባሰል ቅኝት ባቲ አይመታም” እንዲሉ ዛሬ “የወዛደሩን አምባገነንነት እንመሰርታለን ! በሚል መፈክር ይታጀብ በነበረው በ1960ዎቹ አመታት የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ሪትም መዝፈን አይቻልም፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር በውይይት ሊፈታ እንደሚችል ከሊቅ እስከ ደቂቅ እምነት ያሳደረበት የሰለጠነ ግዜ ነው። የኢ.ህ.አ.ፓ አካሄድ ደግሞ ዛሬም አንድነት ወይም ሞት! በሚል መፈክር የታጀበ በ60ዎቹ ላይ ፖዝ ያደረገ ይመስላል። ግንቦት7 ደግሞ አንድነት በሞት ሳይሆን በውይይት እያለ ነው …..! ልዩነቱም በአጭሩ ይህ ነው።

 

በኔ እምነት ግንቦት7 ከኦነግ ጋር አብሮ ለመስራት ይቻላል በሚል እምነት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን መሞከሩ ምንም ጉዳት የሚያስከትል ይመስለኝም።

 

እየታዩ ካሉት አበረታች ውጤቶች አኳያ እንዲያውም እሰየው የሚያሰኝ እንጂ የተቃውሞ ዘመቻ ሊከፈትበት የሚገባ አይደለም ባይ ነኝ ።የአንድነት ሃይሎች ነን የሚሉትም በርግጥ ሃይሉ ካለ የሌላውን ጉዞ ከማደናቀፍ ተቆጥበው በአመኑበት ይቀጥሉ ።

 

ማንም ቢሆን የሚለካው በስራው ባስመዘገባቸው ውጤቶች በመሆኑ ሕዝብ ውጤት ያየበትን ይደግፋል። ውጤት ያላየበትንም ጥሎ ያልፋል። አይቶ የመፍረዱን፤ መርጦ የመደገፉን መብት ለህዝብ ትቶ፤ ሁሉም ባመነበት ከመንቀሳቀስ ውጭ ምንም አማራጭ በሌለበት 21 ክፍለ ዘመን ላይ አንደምንገኝ ማወቅ ይገባል።

 

ግንቦት7 በሌሎች ድርጅቶች አካሄድ ላይ ምንም አይነት ተቃውሞና ትችት ሲያቀርብ ባለመስማቴ እርምት ይገባዋል ብዬ ላነሳው የምችለው ጉዳይ የለም። ነገር ግን ከጎሳ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ሁሉም አብሮ ሊሰራበት የሚችልበትን መንገድም ግዜ ሰጥቶ ቢያስብበት መልካም ይመስለኛል።

 

ኢህአፓም ዛፍ ያጣ ጉሬዛ የመሆን ስጋት ከፈጠረው አሉታዊ እንቅስቃሴ እራሱን ሊገታ ይገባዋል።

 

በነገራችን ላይ ዛፍ ያጣ ጉሬዛ የሚለው ተረት ስርዎ መነሻን አስመልክተው አንድ አባት ስለ ጉሬዛ ባህሪ ያወጉኝን እኔም ላውጋችሁና የዛሬውን ጽሁፌን ልቋጭ።

 

በጸሎተኝነቱ የሚታወቀው ጉሬዛ፡ ልቡም ተራራ ነው አሉ። ዛፍ ላይ ሆኖ በአናቱ ሰማይ ላይ አውሮፕላን ሲያልፍ ዘፉን እየነቀነቀ ብስጭቱን ይገልጻል። ያለኔ ፈቃድ እንዴት በግዛቴ ያልፋል ነው…አሉ ብስጭቱ። እናም በልቡ፤ ያረፈበት ዛፍም ሆነ የአካባቢው አዛዥ እሱ ነው፡፤ አደን ሲያበረው እንክዋ ለራሱ የሚያዝበት ዛፍ ካላገኘ በስተቀር ከሌሎች ጋር አንድ ዛፍ ላይ ተጠግቶ ለማምለጥ ስለማይፈቅድ፤ የብቻው የሆነ ዛፍ እስኪያገኝ መቁነጥነጥና መረበሽ ነው፡፤ ሲሉ ከረዥም ግዜ በፊት አንድ አባት አውግተውኛል። “ዛፍ ያጣ ጉሬዛ ….” የሚለው ተረትም መውደቂያ ፤ መከለያያ፡ መጠጊያ ማጣት፤ ለሚፈጥረው ጭንቀት እንደ ተምሳሌ የሚጠቀሰው ለዚሁ ነው።

 

እናም የኢ.ህ.አ.ፓም ጭንቀት የጉሬዛው አይነት መጠጊያ አጣን ካልሆነ በስተቀር ለሌላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የማይታየው ለነሱ ብቻ የሚታይ “ኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያንዣበበ፤የተደቀነ ስጋት የለም። ሊኖርም አይችልም። ስጋት ካለ አብረን እናየዋለን ለግዜው ግን የለም። ከዋናው ጠላት ከወያኔ በስተቀር ማለቴ ነው።

 

ለዛሬው ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ…….በማለት በዚሁ እሰናበታለሁ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ