ከሁዋላ የበቀለ ቀንድ ጆሮን ይቀድማል (መንግስቴ ደፋር)
ከአቶ/ሮ አዜብ ጌታቸው በጋ . . . "ኢሕአፓዎች ዛፍ ያጣ ጉሬዛ አትሁኑ" በሚል ርዕስ የተፃፈውን ጽሁፍ ተመለከትኩት። ከጽሁፍ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ ወደ ደጀሰላም ዝክር በአክብሮት የተጠራ ሰው፣ የሚገባውን ያህል ከተቋደሰ በሁዋላ፣ ሂሳብ ለማወራረድ እንደሚታገል ጀብራሬ የተወላገደ የነጠላ ዜማ ቅኝት መሆኑን ብቻ ነው። ብዕርዎ የገዛ ምስልዎን የሚቀርጹበት መሮ መሆኑን ደግሞ አይዘንጉት። “ አንድ አለብህ ይላል ያገር ቤት ዘፋኝ”
ትውልድ እንደ ጅረት ውሀ ነው ። በመተካካት ስሌት አንዱ ትውልድ ሲያልፍ ለሌላው ስፍራውን እየለቀቀ ይነጉዳል። ታዲያ በየዘመናቱ በየትውልዱ መሀል ጣልቃ እየገቡ እንደባቄላ ዘር ጠጥረው የሚፈጠሩ፣ የሀገርና የወገን ጥቅም የማይገዳቸው፣ ተደናብረው ሊያደናብሩ የሚሞክሩ፣ በፍልስፍና ድህነት የተመረዙ፣ አዋቂ ነን ባዮች በሀገራችን ሲበቅሉ፣ ሲያድጉና ሲከስሙ አስተውለናል።
ሰሞኑን እየተመለከትን ያለው የዘር ፖለቲካ ሙሽሮች የቃላት ቱማታም ይህንኑ እውነት በውል ያረጋግጥልናል። የድል አጥቢያ አርበኝነታቸውን ለማረጋገጥ፣ ከወዲሁ እየተሟሟቁ ያሉ የእናት ሀገር ጡት ነካሾች፣ ዛሬማ እንደወተወሮው ሁሉ በስፋት እየተበራከቱ መጥተዋል። እነዚህ ሰዎች ወትሮም ቢሆን በባህር ዳር የአሸዋ ግንብ እነደሚገነቡ፣ በመጨረሻም እየሳቁ መልሰው እራሳቸው እንደሚያፈርሷችው ህጻናት አይነት ናቸው። ምክንያቱም ሲገነቡ ባሀሩ አሸዋ ያቀርብላቸዋል፣ ሲያፈርሱ ደግሞ በተራው ባህሩ ይስቅባቸዋል።
ኢሕአፓ የሚያራምደው ኢትዮጵዊነትና ከዚያም የሚመነጨው የህዝብና የሀገር አንድነት አቋም ለእኛ ለደጋፊዎቹ ብቻ ሳይሆን ለማኝኛውም ኢትዮዽያዊ የአንድነት ደጋፊ ሁሉ ጽኑ መሰረት ነው ብዬ አምናለሁ። ኩራታችንም አርበኝነታችንም ከዚሁ አቋማችን ነው የመነጨው። ኢሕአፓ በታሪክ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎም ለሌላ ሰጥቶትም ሆነ ለድርድር አቅርቦት እንደማያውቅ፣ እርስዎ ለመመስከር ቢተናነቅዎ ህሊናዎ ይፈርድብዎታል። ትላንትም ዛሬም ቢሆን እያልን የለነው ነገር ቢኖር፣ ሀገር በምንደኝነት የሚዋዋሉበት የቅርጫ ገበያ አይደለም። ለስልጣን ጥም ሲባልም የሚደራደሩበት ጉዳይ ከቶ ሊሆን አይገባም። ለእኔና ለመሰሎቼ የኸ ጉዳይ የ90ሚሊዮን ህዝብ ሕልውናና ማንነትን የሚወስን ታሪካዊ ሐላፊነት ነው። ሰለሆነም ነው ለዘመናት መተኪያ የሌላቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ክቡር ህይወታቸውን ሲገብሩለት የኖሩት። ለእኛም በአጋጣሚ ተርፈን በህይወት ላለንና የኢሕአፓ ደጋፊዎች በሙሉ የትግልና የመስዋእትነት ትሩፋታችን ነው። የሀገር ሉዓላዊነትና በህዝብ አንድነት ጥያቄን እንደ እርስዎ ድርጅት ለድርድር ቀዳሚ አዠንዳ አድርጎ ኢሕአፓ አለማቅረቡ በራሱ የጥንካሬው አይነተኛ መግለጫ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በአንድ ወቅት እርስዎ የኢሕአፓ ብርቱ ደጋፊ እንደነበሩ ነግረውናል። ዛሬ ደግሞ ለግንቦት 7 ጥብቅና ቆመው እኛን ከዛኛው ጎራ ይሞግቱናል። እዚህ ላይ ተለዋዋጭ ባህሪዎን እያደነቅን፣ ወትሮም ቢሆን የሰው ልጅ ልቡ እንጅ አካሉ አይደለም የሚሸፍተው። ልብዎ ሳይሆን አካልዎ ነበር ኢሕአፓ ቤት ሲውረገረግ የከረመው። መጀመሪያውኑ በዚህ በሰንካላ መንፈስ ወደ ኢሕአፓ ጎራ መምጣት አልነበረብዎት። ትግል ቁርጠኝነትን፣ የዓላም ጽናትንና ግልጸኝነትን ይጠይቃል። በአላመኑበት መስመር ለመታገል መሰለፍ ተደናብሮ ማደናበር ነው ትርፉ። በድርጅት ጥላ ስር ሲያርፉ በቅድሚያ ሊያስተውሉት የሚገባው ነገር፣ ድረጅቱ አንግቦት የተነሳውን መሰረታዊ የትግል አላማና ግብ ህዝባዊነት፣ የትግል ቁርጠኝነት፣ የአመራር ብቃትና ተመክሮ፣ ድርጅታዊ ጥንካሬና የእስትራቴጂ አወንታዊነት፣ የፖለቲካ ብስለት፣ የሃይል አሰላለፍ ግምገማ ብቃትና የጊዜ አጠቃቀሙ ወ.ዘ.ተ እንጅ፣ የሰው ብዛትና ማነስን አይደለም። የኢሕአፓን በእርሶ አባባል "ባዶነት" እያወቁ ለምን ወደ ወና መንደር መጥተው በባዶ ቤት ላይ መጮህ እንዳስፈለገዎት አልገባኝም። ደግሞም የዓላማ (አይዲያ)ትልቅነት እንጅ የሰው ትልቅ ለምድር ይክበድ እንደሁ እንጅ ሌላ ምን ትርፍ አለው ብለው ነው። እርስዎም ቢሆኑ የተሰሳቱት ሰው አይተው በመምጣትዎ ነው። ምክንያቱም ሰው አይተው ነው የተመለሱትና። በቃ የታሪክዎ መነሻውም መድረሻውም እንደነገሩን ከሆነ ይኸው ነው።
ልዩ ለተልእኮ ኖሮዎት ከሆነ ግዳጅዎን በአግባቡ እየተወጡ ስለሆነ ሽልማትዎን በኢሳት ቴሌቪዥን መስኮት አንድ ቀን እንደሚያስቃኙን ተስፋ እደርጋለሁ። እርስዎን እንዳሉት በአንድ ወቅት ኢሕአፓ በአክብሮት ሰለአስተናገደዎት ሊያመሰግኑንት ይገባዎታል። ምክንያቱም ሌላው ቢቀር ቢያንስ ቢያንስ አውቄዋለሁ ያሉትን አቅሙንና የፖለቲካ ድክመታቶቹን ሸምተው ተመልሰዋል (በእርግጥ አውቀውት ከሆነ)። እድሜ ደግሞ ዘልዛላ ነው ነገ ምን እንደሚፈጠር ማን ያውቃል? ወትሮም ቢሆን ድንበር ተሻጋሪ ቃላቶች እንጅ ድንበር ተሻጋሪ ማንነት አልነበረዎትም ማለት ይቻላል። ትችትዎትን ሰው በሌለበት ወሀኒ ቤት እንደጣሉት ይቁጠሩት።
ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በታሪክ እስከ ዛሬ አልነበረችም። አዲሲቱን ኢትዮዽያ እኛ አዲስ የምንገነባናት ናት እያሉ በአገርና በህዝብ መሳለቅ ታሪክም ህዝብም ይቅር የማይለው ስህተት ነው። ይህንንማ ቀድሞ ወያኔ ሲያራግብልን ኖሯል። ምን አዲስ ነገር አለውና ነው? የኮፒ ራይት ህግ ስለሌለበት እርስዎም ሆኑ ግንቦት 7 ደግመው ቢያዜሙት ቅር አይለንም። ልነግርዎት የምፈልገው ቁም ነገር፣ እንኳን ደስታ መከራም ቢሆን በሀገር ነው የሚያምረው። ይህን ፈጽሞ ልንክደው ማንችለው ሀቅ ነው። የድል አጥቢያ አርበኝነትም ቢሆን እንደ አንዳንዶች የምንናፈቀው ጉዳይ አይደለም፡፡ በደንብ የሚያውቁት ከሆነ ኢሕአፓም ሆነ እኛ ደጋፊዎቹ፣ በእንዲህ አይነት ቅሌት አንታማም። ለኢትዮዽያ አንድነት በጽናት የምንታገል መሆናችንን እርስዎም በጽሁፍዎ አስፍረውታል። ሐሰት በባህሪዋ ብዙ ስለሆነች፣ በየቦታው እንደልብ ትናኛለች፣ አድናቂዎቿም እንዲሁ በርካታ ናቸውና። እውነት ግን ተከታዮቿ ጥቂት እንደመሆናቸው መጠን፣ ከእነሱው ጋር ተቆራኝታ አንሳ ትኖራለች፡፡ ከዚህም የተነሳ በእውነት ስም ለማመን የሚያዳግት ታሪካዊ ግድፈት፣ በግል፣ በድርጅትና በሀገር ደረጃ ጭምር ሲሰራ የሚስተዋለው። በዚህ ዘመን እውነቱን ከሀሰት፣ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለመለየት እያስቸገረ ያለው በዚህ ሳቢያ ይመስለኛል።
ኢሕአፓ ከወያኔ ጋር ለመተባበር አይመለስም ያሉት ፈር የለቀቀ ስም ማጥፋት ነው። የገላባ ሸክም ያህል የቀለለ ስም ማጥፋት ነው የሚሆነው። በሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ጉዳይ በታሪክ ኢሕአፓ ከማንም ጋር ሲደራደር ተሰምቶ አይታውቅም። ወደፊትም ፈጽሞ የሚታሰብ ጉዳይ መስሎ አይታየኝም። ደግሞም መዋሸት ሲገደዱ እንጅ ስራ ሲፈቱ አይደለም።
እርሶን የሚያህል ምሁር የኢትዮጵያን ታሪክና ፖለቲካ በሚገባ የገመገመ፣ ቢንስ ለሚተኩዎት ልጆች በታሪክም ይሁን በአካል ሊያስረክቧት የሚያስቧት ኢትዮድያ የቷ እንደሆነች ለማየት እናፍቃለሁ። ያባትዎና የአያትዎ አደራስ ምን ይሆን? በዚህ ረገድ ተሸውደዋል አለያም ከድጡ ወደማጡ እየሄዱ ይመስለናል። በሀገር ክብርና በግል ጥቅም መካከል መቃቃር ከተፈጠረ ሰንበትበት ብሏል። ህገወጥና ኢርቱእ ሥራ ህግ እየተረቀቀለት ሀገር ሳይቀር ለባእዳን እየተቸበቸበ እያን፣ እየሰማን ባለንበት በዚህ አይን አውጣ ዘመን፣ እርስዎ አዲስ ካባ ለብሰው ቢመጡ አይደንቀንም።
ኢሕአፓ የሚባል ድርጅት በስም ያለና መግለጫ ከማውጣት በስተቀር፣ ሃይልም ብቃትም እንደሌለው፣ ባዶ እንደሆነ አበክረው በማያሻማ ቃል ነግረውናል፡፤ እኛስ እሽ ነው እንበል፣ እርስዎ በባዶ ድርጅት ላይ ይህን ያህል የፖለቲካ ግምገማና ትችት ሲያባዝንዎ መክረምዎ የበለጠ ባዶ የሆኑ አይመስልዎትም? ያልተረዱት ነገር ቢኖር፣ ሌላውን ከዙፋን ለማውረድ ሲያስቡ፣ በራስዎ ልብ ውስጥ የነገሰብዎት የጥላቻ ዙፋን ማንሳትዎን ማረጋገጥ ያስፈልግዎታል። ይኸ አእርሶም ለሚሟገቱላቸው ድርጅቶችም ጭምር ይጠቅማችሁዋል። አለበለዚያ ጭነቷ እንደአጋደለች አህያ በተንሻፈፈ ሀሳብ አግድም ስትጉብጡ መክረማችሁ ነው። ደግሞም ራሱን የማይችል አንገት ይኖራል ብለው አሰበው ከሆነ፣ የተሳሳተ ግምት ውስጥ ወድቀዋል። “ቢራቢሮ ቂጧን የምትሸፍነው የላት ምድር ታለብሳለች” እንዳይሆንብዎ፣ እየተጓዙበት ያለውን መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ እንደ ዜጋ ከወዲሁ ልናሳስብዎ እንወዳለን። ሰው ብዙ የሚናገረው ከሀሳቡ ጋር ሰላም መፍጠር ሲያቅተው ነውና። ሰላምዎ እንዲመለስልዎ ምኞታችን ነው። ቢንስ ቢያንስ የህሊና ሚዛን እንዲስተካከል ይረዳዎታል።
እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ኢሕአፓ በበኩሉ ሌሎች ታዳጊና ተቃዋሚ ድርጅቶችን ሲረዳ፣ ሲያበረታታ፣ ሲያጠናክር የኖረ ስለ መሆኑ ቀደምት ስራዎቻቹ ምስክር ናቸው። ዛሬም ቢሆን ተጨባጭ የጋራ የትግል መድረክ በሀገር ውስጥ ለመፍጠር ጥሪው እንዳልተቋረጠ ይታወቃል። ይህን ማድረግ ያልቻሉ እዚህ በሞቀ ቤት ተቀምጠው ሌላውን በሀሰት ፕሮፓ ጋንዳ እያወናበዱ የወያኔ ሰለባ ማድረግ፣ በዜጎች ህይወት መቀለድና ብቻ ሳይሆን፣ ሐላፊነት የጎደለው እኩይ ተግባርም ጭምር ነው። ሀገር ወዳድ የሆነ የአንድነት ደጋፊ ሁሉ ቸል ሊለው አይገባም። ጽሁፍዎ ለሚያስተውል ሁሉ፣ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት፣ አንዲሁም የጥፋት ሃይሎችን የሃይል አሰላለፍና እንዲሁም እየተከተሉት ያለው እስትራቴጂ ገመና የሚያመለክት ነው።
ደግሞም እርስዎ ጥብቅና የቆሙላቸው ድርጅቶች ኢትዮዽያዊነታቸውን ገና ያልተቀበሉና በድርድር ዜግነት ሊያሰጧቸው የሚሟገቱላቸው መሆናቸውን አጥተውት ነውን? ማን ዜግነት ሰጭ ማን ተቀባይ እንደሆነ ወደፊት በሂደት የሚታይ ቢሆንም፣ በእኔ በኩል ግን “የት ይደርሳል ያሉት ጥጃ ልኳንዳ ቤት ደጃፍ ተገኘ” አይነት እየሆነብኝ ተቸግሬአለሁ። ይህንን በግልጽ መናገር ደግሞ ወንጀለኛ አያሰብልም። ደግሞም “ሳይቃጠል በቅጠል” ነውና። እንደነገሩን ከሆነ ድርጅትዎ ታዳጊ ነው ብለዋል። ታደጊ እኮ ሲሳሳት ይመከራል፣ ይወቀሳል፣ እንዲያም ሲል ካልተመለሰ ይኮረኩማል። በፖለቲካ ዓለም የፋፋ ትውልድ ነኝ አትንኩኝ አይሰራም። ጨዋታው ሎሚ ተራተራ ነው። ሞፈር በለጋው ካልታረቀ ለማረሻነት አያገለግልም አይደል። በባህላችንም ቢሆን፣ ታደጊው ሽማግሌውን ሊሰድበው ሊያዋርደው አይገባም። ሽማግሌውም ቢሆን ታዳጊውን መርግም እንዲሁ የለበትም። ቁምነገር ካለው በሃሳብ መፋጨትና መጫወት እሰየው ነው፣ ነገር ግን ድብቅ አዠንዳ ይዞ በሀገርና በወገን ህይወት እየቀለዱ አይደለም። እዚህ የጨዋታው ህግ ሌላ ነው። የማትረፍ እንጅ የማክሰር አይደለም።
መዋጋት የሚገባን የጎሳ ፖለቲካን እንጅ የጎሳ ድርጅትን አይደለም ማለትስ ምን ማለት ነው። እረስዎ ደግሞ የትኛው የጎሳ ፖለቲካ ሊቀመኳስ ነዎት? የወያኔው መሪ መለስ ተሳክቶላቸዋል እንበላ። የጎሳን ፖለቲካ ከመሪ ድርጅቱ እንዴት ነው ነጥለው ሊዋጉ የሚችሉት? የጎሳ ድርጅት እያጠናከሩ የጎሳን ፖለቲካ እንዴት ሊዋጉ እንሚችሉ እስኪ ይተንትኑልና? “ ልናይ ገና አሉ እማማ ደበሬ!” የጎሳ ፖለቲካ እንኳን ለእኛ ለቆሚሳሩ ለራሱ ለወያኔም ቢሆን ሞክሮት አላዋጣ ስላው፣ በኢትዮዽያ ባንዲራ ውስጥ ራሱን ለመደበቅ ጥረት እያረገ መሆኑን አላስተዋሉም እንዴ? ስለ አንድነት መሪጌታ ለመሆን በአስመሳይ ፖለቲካው ሲሯሯጥ የምናየው ወያኔ አይደለምን? እናንተ እሱ እሰከሚጥልላችሁ ነበር እንዴ የጠበቃችሁት ልበል። በኢትዮዽያ ጉዳይ የጎሳ ፖለቲካማ የተበላ እቁብ ማለት ነው።
አለው አለውና በጎንደር ሲዘፈን
ንቅሳት ጌጥ እንጅ መች መለያ ነበር። ነው ዘፈኑ በሀገራችን።
21ኛው ከፍለዘመን እንኳን የአንድነት ኃይሎችን ስንት ባንዶችን ችሎ እየኖረ ነው። የፖለቲካውን ሽፍጥ ለእርስዎና መሰሎችዎ እተወዋለሁ። በአቋም ጸንቶ መኖር የጥንካሬ መገለጫ እንጅ ተንበርካኪነት አይደለም። የኢሕአፓን ሥራ በተመለከተ ስላነሱት ጉዳይ፣ እርስዎ መስፈርት ሊያወጡለት የሚያስችልዎት የሞራል ብቃት የአለዎት አይመስለኝም። ኢሕአፓ በረዥም ዓመታት በእሳት ተፈትኖ፣ በጽናት እዚህ የደረስ ድርጅት እንጅ፣ እንደ እርስዎ አባባል ውርዴ ፖለቲካ የሚያራምድ እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህ ጉዳይ ጨለምተኝነት እንዳለብዎት እረዳለሁ፡፡ ባልገባዎት ነገር ደፍረው አደባባይ ሙግት በመውጣትዎ እደንቀዎታለሁ። በዚህ ረገድ ሌሎች በርካታ አጃቢዎች ሊያገኙ እንደሚችሉ እገምታለሁ። በየመንደሩ ገባቸውም ባልገባቸውም ነገር አድናቂዎች ሞልተዋልና አድማጭ አያጡም። “ወፈፌ መች አጃቢ አጥቶ ያውቃል።
ጠላዋ እንደአማረላት ሴት ሽር ጉድ ማለትዎ አለቆችዎን ለማስደሰት ካልሆነ በስተቀር፣ ኢሕአፓን ለመስደብ ብዙ ርቀት መሄድ ባላስፈለገዎት ነበር። እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ኢሕአፓ የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ አያውቅም። እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ ወያኔም ባልቀደመው ነበር። በዚህ ስም ቢጣሩ አቤት ባዮቹ ሌሎች ናቸው። ብዙ ማውራት ያፍ መንሸራት ያመጣል። የምረጫ 97ን ትንግርታዊ ድራማ መለስ ብለው ቢቃኙ ማን ጥሩ ተዋናይ እነደነበረ መልሱን ከዛው ያገኙታል። ደብቆ የሚያፋልግ ወያኔ ብቻ ነው።
“አንድነት ወይም ሞት” ነው የኢሕአፓ መፈክር ያሉት እውነት ብለዋል። ኢሕአፓ የዛ ትውልድ ቅሪቶች ሰብስብ እንጅ የዘመኑ ፖለቲካ ፍርፋሪ ለመልቀም የተሰባሰቡ ምንደኞች ባለመሆኑ፣ መነሻውም መድረሻውም ይህንኑ ሐላፊነት ማእከል ያደረገ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። ወያኔ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ፣ ሀገርን ያህል ነገር ከመጋረጃ ጀርባ በተደረገ ድርድር ሲሸጥ፣ ሲለወጥ በተደጋጋሚ አይተናል። በዚህ ረገድ ወያኔና ሻእቢያ እስኪበቃን አስተምረውናል። “ ሞኝን እባብ ሁለት ጊዜ ይነድፈዋል እንዲሉ” ከአንዴዬም ሁለቴዬ ተነድፈናል እርሰዎ ደግሞ ለሌላ ለሶስተኛ ጊዜ ሊያስነድፉን ይታገላሉ። ይህ ደግሞ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነት ነው።
የትግል ስልት አነዳደፍ ለኢሕአፓ ለማስተማር ብረቱ ጥረት አድርገዋል። “ከእኛ መዲያ ፉጨት አፍን ማሞጥሞጥ ነው” ሲባል አልሰሙ ልበል?
ስለተረቱ ምስጋናዬ የላቀ ነው። ኢትዮጵያዊነቴ ደግሞ በዚህ አያሳፍረኝም። ምላሼን የተሟላ እንዲሆንልዎ አንድ ልበልና ነገሬን ልደምድም። የአሳማና የፍየል መንጋ ማዶ ለማዶ፣ ጎራ ለጎራ ሆነው ሲበሉ ይውላሉ። ከሰዓት በሁዋላ ሲሆን ፍየል ሞቅ ያደርገውና መንጋውን ማንቧቧት ይጀምራል። በጩኸት ጎራውን ያተራምሰዋል። ሁኔታው ያበሳጨው አሳማ ባልደረባውን ለመሆኑ እዛ ማዶ እንዲህ የሚጮኸው ምንድነው ብሎ ይጠይቀዋል። እሱም ፍየል ነው ብሎ ይመልስለታል። በመቀጠልም ታዲያ እነደዚህ ምን ያስጮኸዋል ይለዋል። መልሶም አይ ልጅ መውለድ ፈልጎ ነው ብሎ ይመልስለታል። ለመሆኑ እንዲህ ለፍልፎ ስንት ነው የሚወልደው በማለት ይጠይቀዋል። አንድ ወይም ሁለት በማለት ይመልስለታል። እኛ ታዲያ ድምጻችን ሳይሰማ 8 እና 9 እንወለድ የለም እንዴ እሱ ለአንድና ለሁለት ነው እነዲህ ሀገር ይያዝልኝ የሚለው አለ ይባላል።
ምናልባት የውጭ ሃገር ህይወት ያሰፈነብዎት ጭንቀት አይምሮዎን ብቸኛ አድርጎዎት፣ እርቃኑን የቀረውን ማንነትዎን አጋልጦ ባሳዬዎት ጊዜ ባንነው፣ ከዚህ አባዜ ለመሸሽ ሲሉ ያደረጉት ይመስለኛል። ይህ ደግሞ በእርስዎ የተጀመረ ሳይሆን ሌሎችም በርካቶች እርስዎን መሰል የሄዱበት ጎዳና እንደመሆኑ መጠን እርሶም ሌላ አዲስ ነገር ከቶ አላሳዩንም።
ቀጥ ብለው መሄድ የሚያውቁትን ያህል፣ ለምን እያነከሱ ወደ ኢሕአፓ እንደተመለሱ በውል ባይገባንም፣ አጋዘኖች ኤሊዎችን ፍጥነት እናስተምራችሁ ያሉትን አይነት ጥያቄ አዘል ሀሳብ ለማቅረብ ከሆነ፣ ጸብ ያለሽ በዳቦ መሆኑ ነው። ከኢሕአፓ ጋር የቆዬ ተደጋጋሚ ቂም ሊኖርዎት እንደሚችል ከጽሁፍዎ መረዳት ይቻላል። ያ ደግሞ የሚያምርው ራስዎትን ችለው በሚጫወቱ ጨዋታ ነበር። አመች ሸፋን የሚሆንልዎ አጋጣሚ ጠብቀው ከድርጅቶች ጀርባና በሌላ ስም ሽፋን ኢሕአፓን ለማሳጣት አልመው ከሆነ፣ ለዛሬ አልተሳካልዎትም። ሌላ እድል እንዲሞክሩ አበረታታዎታለሁ። ከዚህ ውጭ የነገር ድር በማድራትና በመሸመን፣ የድርጅቶችን ቅራኔ በማራገብ ያንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ነው የሚሆነው። ድርጅቶቹ የየራሳቸው ልሳን አሏችው። ቀላጤ ካልተላኩ በስተቀር ራሳቸውን ችለው ለመሟገት ብቃት አላቸው። ተለጣፊ አቡካቶ ለመሆን ከፈለጉ ደግሞ፣ ይህን ብቃትዎን ለግብረሰናይ ድርጅት ቢያውሉት ምንኛ በታደሉ ነበር። እንደእርስዎ ላለ አዛውንት(በግብሩም በአካሉም) የሚበጀውና የሚጠቅመው ሥራ አሱ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ለንስሀ ሞት ሊበቃዎት ይችል ይሆናል።
በዚህ በዝንጉርጉር ባህሪ (አንዴ ከእዚህ ሌላ ጊዜ ከእዚያ)፣ ጣፋጭ ዜማ እቀኝበበታለሁ ብለው የሚማስኑ ከሆኑ፣ በእርግጥ ሊታዘንልዎት የሚገባ ምስኪን ኢትዮዽያዊ (ፀሐፊ) ነዎት። ይህ የፖለቲካ ትንተና መስጫ መድረክ ባለመሆኑ ወደ ፖለቲካው መስመር ገብቼ ያለ ቦታው መቀላቀል አልፈልግም፡፤ አላማዬ እርስዎ ላነሱት ነጥብ ምላሽ ይሆን ዘንድ ብቻ ነው። ለዛሬ በዚህ ላብቃ።
በቀጣይ እስከምንገናኝ፣ ቸር ይግጠመን።



