የዳውሮ ዋካ ህዝብ ከእንባ ወደ አመፅ
የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ግልፅ ተፅዕኖና በደል
ከዳውሮ ዞን ምሥረታ እስከ ዛሬ
ክፍል ሁለት
ዋካ (ከስዊድን) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በመጀመሪያው ክፍል አንድ ፅሁፌ የዳውሮን ዞን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፤ የህዝቡን ኑሮ እንዲሁም የጀግናውን ህዝብ መሪር እንባ፤ እንባው የወለደውን ህዝባዊ አመፅ እንዲሁም ስለ አመፁና አጠቃላይ እንቅስቃሴው ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለመስጠት እንዲመቸኝ የዳውሮ ዋካን ቀደምት አከላለል ሁኔታ፤ የሰሜን ኦሞ ዞንን አመሰራረትና መክሰም አቅርቤ በአዲስ መልኩ የዳውሮ ዞን መመስረቱን ገልጬ ነው ያበቃሁት።
ቃል በገባሁት መሠረት በዚሁ በክፍል ሁለት ፅሁፌ ደግሞ የሰሜን ኦሞ ዞን ሲፈርስና የዳውሮ ዞን ሲመሠረት እንዲሁም ዞኑ ተመስርቶ አስተዳደራዊ ሥራውን ከጀመረ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ ከከፍተኛ የወያኔ መንግሥት አመራሮች፤ በተለይም ከአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀድሞው የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር፤ አሁን ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል ያረፈውን ጫና፤ የወረዳ ጥያቄው መነሻ መንሰኤ የሆኑ ነገሮች ለማንሳት እሞክራለሁ። ከዚያም ህዝቡ የደረሰበትን በደልና የወሰደውን እርምጃ እናያለን።
እንዲታወቅልኝ የምፈልገው በሥም የተጠቀሱትና በግልፅ የጠራኋቸው ግለሰቦች አሉ። ሃሳቤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግለሰቦቹን እንጅ እንወክለዋለን ብለው የሚያጭበረብሩትን ብሄረሰብ ወይም ህዝብ የማይመለከት መሆኑ ይታወቅልኝ። በግል እምነቴ ህዝብ የወከለው የፖለቲካ ፓርቲና አመራር በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ደረጃና አካባቢ በሥልጣን ላይ የለም። ወደ ዋናው ነገር ልመልሳችሁ።
የሰሜን ኦሞ ዞን እንዲፈርስ በወያኔ መንግሥት በ1993 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ተወሰነና ጉዳዩ ተቋጨ። መመሪያውን ወደ መተግበር ሥራ እንዲገባ ተዕዛዝ ተላለፈ። ሥራውን ለመጀመር እንቅስቃሴ ሲጀመር አንድ ከባድ ጥያቄ መጣ። ዞኑ እንዴት ይሸንሸን? እንዴት ይጣመር? አራት ዋና ዋና ትላልቅ ብሄረሰቦች /ዳውሮ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ/ እንዲሁም ሌሎች በርከት ያሉ አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ብሄረሰቦች/ኮንታ፣ ባስኬቶ፣ ዘይሲ፣ ... ወዘተ አሉ። እንዴት ይሁን? አጠያያቂ ሆነ።
በሰሜን ኦሞ ዞን ውስጥ በርከት ያሉ ብሄረሰቦች ያለፈቃዳቸው በግድ ለአስተድስደር ይመቻል በሚል የተሳሳተ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተጣምረዋል። ይህ ደግሞ አስከትሎት የነበረው የሥራ ጫና፤ እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው የሚነሱ የአስፈጻሚው አካላት የውስጥ አለመግባባቶች፤ ፍትህ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማግኘት አለመቻል ለሁሉም ትምህርት የሰጣቸው ይመስላል። በመሆኑም ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የወላይታ ተወካይ በስተቀር ሁሉም የየብሄረሰብ ተወካዮች ለየብቻቸው ያሰቡት ሁሉም ራሱን ችሎ በዞን ወይም በልዩ ወረዳ ደረጃ መዋቅር ለማግኘት ፈልጓል።
ታዲያ ክፍፍሉ የግድ ነውና ሰሜን ኦሞ በስንት ዞን ይደልደል? ሆነ ትልቁ ቁልፍ ጥያቄ። ከበድ ያለ ውዝግብ ነበር የነበረው። አርባ ምንጭ፤ ዋካ፤ ወላይታና ሳውላ ከተሞች በምጥ ተይዘው ሰነበቱ። አራቱን ትላልቆቹን ብሄረሰቦች ወክለው ጉዳዩን የሚያስፈፅሙ ባለሥልጣኖች ተሰየሙ። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወላይታን ወክለው፤ አቶ ዳሮታ ዶጃሞ ዳውሮን፤ አቶ ኢዮብ ኦዳ ጎፋን፤ አቶ ወንድሙ ገዛሃኝ ጋሞን፤ አቶ ታምሩ ግንበቶ ኮንታን እንዲሁም አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸውም ሌሎችም በጋራ ውይይት ጀመሩ ውይይቱ በዝግ ሁኔታ ነበር የቀጠለው። ከበድ ያለ ፈርጣማ ጡንቻ ያላቸው አመራሮች ለየራሳቸው ዞን ለመሆን ወደየራሳቸው ገመድ ጉተታውን ተያያዙት። ጉተታው በወቅቱ ተገቢ እንደነበር አምንበታለሁ። ጠንከር ያለ ፍልሚያ ሆነ።
እነዚህን ነጥቦች እዚህ ላይ ማንሳቱ ያስፈለገው ለዛሬው የህዝብ አመፅና የወረዳ ጥያቄ ያበረከተው ቀጥተኛ አስተዋጾኦ ስላለው ነው። ፍልሚያውን በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል። እስቲ ጎራዎችንና ፊልሚያውን እንየው።
የመጀመሪያው ጎራ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጊዜው የአርባምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ እንስቱቲዩት መምህርና ዲን፤ የዛሬው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሩት ሲሆን የጎራው አላማ የወላይታ ዞን ሲቋቋም ለብቻው ሳይሆን ዳውሮንና ኮንታን አጣምሮ ወላይታ ዳውሮ ኮንታ ዞንን መስርቶ የዞኑን ዋና ከተማ ወላይታ ሶዶ ላይ ማድረግ ነበር።
ጋሞና ጎፋዎች ሁለቱም ለየራሳቸው የዞን መዋቅር እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። ሆኖም ግን ተካዮቻቸው ለህዝባቸው ጥቅም ሲሉ የህዝቡን ጥያቄ አንግበው የሚመጣውን መስዋዕትነት መክፈል የፈለጉ አይመስሉኝም፤ በተለይም በጎፋ ተወካይ በኩል ቆራጥነት ቢኖር ሁኔታው ካሁኑ የተለየ ይሆን ነበር፤ ለአብሮነት ሳይስማሙ ተስማምተዋል ብሎ መገመት ይቻላል። የጎፋ ህዝብ ውሳኔውን አለመቀበሉን በከፍተኛ ተቃውሞ በመግለጽ በርካታዎች እየታሰሩና እየተፈቱ በዚያኔ ተወካያቸው እስከወዲያኛው እያዘኑ ይኖራሉ።
ዳውሮን ወክለው ድርድሩን የሚያካሂዱት ደግሞ አቋማቸው የነበረው ዳውሮ ቢቻል ለብቻው ዞን እንዲሆን ማስቻል ካልሆነ ደግሞ ቀድሞም ዳውሮና ኮንታ ለብዙ ዘመናት አብረው በአንድ የአስተዳደር መዋቅር የነበሩና የኖሩ ናቸውና ከኮንታ ጋር አብረን ዞን ብናገኝ አይከፋንም አሉ። ሁሉም ራስን በራስ ማስተዳደር ይሻላል ያሉ ይመስላል።
እያንዳንዳቸውን የየራሳቸው ህዝብ በአንክሮ ይከታተላቸው ነበር። ፍጥጫና ትንቅንቅ ሆነ። የዛሬው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የያኔው የወጋጎዳ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን ለብቻቸው የተለየ አቋም ይዘዋል። ዳውሮን በሥራችን ከትተን የወላይታን ዞን እንመሰርታለን ብለው ተግተው ሰሩ፤ አልሆን አላቸው። ከበላያቸውም እስቲ ሞክረው ዓይነት ድጋፍ ያላቸው ይመስለኛል። ነገር ግን እሳቸው ለምንድነው ዳውሮ ጋር ወላይታን ማጣመር አለብኝ ብለው የወሰኑት? እስቲ መልሱን ወደ በኋላ እናገኘዋለን።
የተወካዮቹ የመከፋፈል ድርድር ምንም እንኳን ዝግ ውይይት ነው ቢባልም ከተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አንፃር አንዳንድ መረጃዎች እየሾለኩ ይወጡ ነበር። የውይይቱ አቅጣጫ እንደ ህዝቡ ፍላጎት ካልሄደ ህዝቡ ሌላ ከበድ ያለ ሁኔታ እንዳያነሳ ይፈራ ነበር። በዚህ ሳቢያ የአቶ ኃይለ ማርያም ሃሳብ ውድቅ ሆነ የሚአነሳውም አላገኘም። በዳውሮ በኩል የነበሩት ተወካይ ጠንካራ አቋም በመያዛቸውና ለሚመጣው ማንኛውም መስዋዕትነት ዋጋ ለመክፈል በመወሰናቸው የዳውሮን ዞን እውን ለማድረግ ታግለው በአሸናፊነት ተወጡ።
የዳውሮ ህዝብ ተወካይ ዳውሮ ከወላይታ ጋር እንዳይጣመር እጅግ ከፍተኛ ትግል በማድረግ የአቶ ኃይለ ማርያምንና የመንግሥትን ቀጥተኛ ያልሆነ ጫና በመቋቋም የዳውሮ ዞንን እውን እንዲሆን አድርገዋል። ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ ተወጥተዋል። በሃሳብ መሸነፍ ብዙን ጊዜ ወደበቀል የሚመራቸው አቶ ኃይለ ማርያም ሁኔታው ተስፋ አስቆረጣቸው። ሃሳባቸውን የተቃወሙትን ግን በቁጭት `ቆይ ግድ የለህም ` ብለው ከንፈራቸውን ነክሰው ሽንፈታቸውን ለመቀበል ተገደዱ።
እንግዲህ ሰሜን ኦሞ ዞን በሶስት ዞንና በሁለት ልዩ ወረዳዎች ተደልድሎ እጅግ አሳሳቢና አስቸጋሪ የነበረው የሰሜን ኦሞ ዞን የክፍፍል ጣጣ ፍፃሜ አገኘና በዚሁ ተቋጨ።
ይሁንና የዳውሮን ዞንነት ህዝባዊ ተልዕኮ ከግብ ያደረሱ ግለሰቦችና ዳውሮ በጋራ በአቶ ኃይለ ማርያም ጥርስ ውስጥ ገቡ። የሚገርመው ይሄ የዞን ድልድሉ ካበቃ በኋላ አቶ ኃይለ ማርያም ብዙም ሳይቆዩ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ከመምህነት ወደ ክልል አስተዳዳሪነት ተሾሙ። ከዚህ በሁዋላ ነው ግለሰቡ እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በግለሰቦችም ሆነ በዳውሮ ህዝብና ምድር ላይ ያለ የሌለ ኃይላቸውን መጠቀም የጀመሩት። እየጎዱ፣ እያደባዩና እየተበቀሉ እስከ እስከመጨረሻው ገፉበት። ሰው ሲሾም አይ በቃ ምህረት ላድርግ ብሎ ያስባል እሳቸው ግን እየባሰባቸው ሄደ።
የሚያሳዝነው፤ የዳውሮ ህዝብ ሰሜን ኦሞ ዞን በሚባል ፈርጀ ብዙ የሆነ ችግር የሞላበት ዞን ውስጥ አሳሩን ሲያይ ከርሞ፤ በመከራ ከዚያ ስቃይና ውጥረት ተላቆ ገና ሳያገግም፣ ቀደም ሲል በወረዳዎች መካከል የነበረውን የክለላና አዲስ የወረዳ ይሰጠኝ አቤቱታ እንዲሁም የወረዳ ርዕሰ ከተማው አያማክለኝም የሚል የህዝብ ጥያቄና የፈጠረው ውዝግብ ሳያንሰው በዳውሮ ህዝብ አናት ላይ አቶ ኃይለ ማርያም የሚባል ባላንጣ ተቀመጠበት። አይጣል እኮ ነው!
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ አቶ ተፈራ መስቀሌ ይባሉ የነበሩት የደቡብ ክልል ፀሃፊ ወያኔ ወደ መንግስትነት ከመጣ በኋላ በዳውሮ ውስጥ ባሉት አምስት ወረዳዎች ሁሉ የዋካ ከተማን ጨምሮ የወረዳ አስተዳዳሪዎችን / መጀመሪያ ክፍለ ህዝብ ይባሉ ነበር/ በሙሉ ከወላይታ ሹመው ይልካሉ። እሳቸውም ለካስ ከዚያው ብሄረሰብ ነበሩ። እነዚሁ ቢያንስ ከአምስት አመት ያላነሰ ገዝተዋል። ሁሉም በብሄረሰብ ወላይታዎች ነበሩ። አልፎ አልፎ በየመድረኩም ሲቆጡ በትግርኛ ነበር። ዋይ ዋይ፣ አታ፣ ... ይሉ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ይህ ሳይታሰብበት አይመስለኝም። የሥነ ልቡና ጉዳይ መሆኑ ነው። አንዳቸውም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ስለማጠናቀቃቸው እርግጠኛ አይደለሁም።
ለፈገግታ እንዲሆናችሁ ያህል ከነርሱ አንዱ ዜና ኮላሶ የሚባል ካድሬ ዶክተር አስራት ወልደየስን አንስቶና ስለ ኤርትራ ነፃነት ጉዳይ በስብሰባ ላይ ማብራሪያ ይሰጥ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችን እያናሳ ብዙ ያወራል። በዚህ አድራጎቱ በርካታ መምህራን ተናደውበት ኑሯል። በዚያ ስብሰባ ላይ የነበረና ተበሳጭቶበት የነበረ አንድ መ/ር የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እንዲሰጥ ከተላከበት ት/ቤት ሲሄድ ያንን ካድሬ እዛው ፈተና ጣቢያ ያገኘዋል። ደግሞ የፈተና ታዛቢ አድርገው ላኩት ... መቼም የማትገቡበት የለም ብሎ መምህሩ በውስጡ ይናደዳል። ጉዳዩ ግን እንደዛ አልነበረም። አየወረዳ ገዢው ካድሬ የመጣው የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ሊፈተን ነው። መምህሩ ወንበር ይዞ ተቀምጦ ያገኘዋል።
ምነው ተቀመጥክሳ መምህሩ ይጠይቃል አይ ተፈታኝ ነኝ ... እንዴት? ... በቃ ተፈታኝ ነኛ ... ይሄኮ የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ነው ... መሆኑማ አውቄ ነው ልፈተን የመጣሁት ... ይህ ዶክተር አሥራትን ሲወነጅል ሲአንኳስስና ሲተች የነበረ ካድሬ ለካስ ስምንተኛ ክፍል እንኳን ያላጠናቀቀ ነበር።
መ/ር አወቀ አባተ ነገሩ ተገርሞ ወንድሜ ሆይ ይህንን ፈተና ባለፈው የምትሰድባቸው ሰዎች በሙሉ ለብቻቸው ተቀምጠው በመፈተን ያለፉ ናቸው። በል ዛሬ አንተም ለብቻህ ተቀመጥና ሞክረው! ይለውና ፊትለፊት ወንበር አዘጋጅቶለት አስቀምጦ ፈተነው። ውጤቱ ሲመጣ ከመቶ ከአንድ ፐርሰንት በታች እንደሆነ ሰምቻለሁ።
አቶ አወቀ የሰራው ሥራ አንድ ሰሞን ብዙ እንድናስብ አድርጎናል። ልብ በሉ! አቶ ተፈራ የላኩልንን አስተዳዳሪዎች፤ በርካታ ምሁራን ከሞሉበት ወላይታ ነው አቶ ዜና ኮላሶና ጓደኞቹ ለዳውሮ የተላኩልን፤ የትምህርት ደረጃቸውን አስተውሉ። ይህን ያነሳሁት ዳውሮን ለመዋጥ ይሰራ የነበረውን ደባ ለማሳየት ብቻ እንጂ ለአስተዳዳሪነትም ሆነ ለማንኛውም የሥልጣን እርከን ብቃት ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የየትኛውም ብሄረሰብ አባል የሆነ ህዝቡን ማገልገል እንደሚችል የማምን ዜጋ ነኝ። ወደ ዋናው ጉዳይ ላምራ።
አቶ ኃይለማርያም በሥልጣን ዘመናቸው ያገኙትን ጉልበትና የደቡብ ክልል ር/መስተዳደርነት ሥልጣን ተሞርኩዘው በዳውሮ ህዝብና ቀደም ሲል በሥልጣን ላይ በነበሩት አመራሮች ላይ ከወሰዱት ጠንካራ እርምጃዎች ሳቢያ ካደረሱት ጉዳት ውስጥ ጥቂቱን እንመልከት፦
1. ከላይ እንደገለጽኩት በዞን ክፍፍሉ ወቅት ከወላይታ ጋር መጣመር ሳያስፈልገን የዳውሮን የዞን አስተዳደር መዋቅር በቀጥታ ማግኘት አለብን ብለው ተከራክረው የአቶ ኃይለ ማርያምን ዕቅድ ያደናቀፉዋቸውን የዳውሮን ህዝብ ተወካዮች በተለያየ ሰበብና አስባብ ገመገምኩ ብለው አላማቸውን አስፈፃሚ ካድሬዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አደራጅተው ከሥልጣን ጠራርገው አስወገዱ።
2. በዳውሮ ውስጥ የሳቸውን ፍላጎት ያለምንም ጥያቄ፤ ቅድመ ሁኔታና የህዝብ ፍላጎት በቀጥታ ሊያስፈፅሙ የሚችሉ አዳዲስ ታዛዥ አገልጋዮችን በመመልመልና ቃል በማስገባት፤ ከካድሬነት ወደ ዞንና የክልል አመራርነት ሾሟቸው። የዳውሮን ህዝብ ጥቅም የማያነሳና የማይጠይቅ፤ እሳቸው ያሉትን ሁሉ የሚቀበል ማለት ነው።
እሳቸው ያሉትን ሁሉ የሚቀበልና በቀላሉ መንግሥት ነው ያለው፣እኛ ምን እናድርግ እያለ መንግሥትንም እያማ፣ ልማት ይመጣላችኋል እያለ ህዝብን እያታለለ፣ በወንበርና በህዝብ ጫንቃ ላይ ለመኖር የሚሻ አመራር በዞንና በክልል ደረጃ ከዳውሮ በዳውሮ ውስጥ ፈጠሩ።
ከዚያም በኋላ ፈረሱም ሜዳውም የሳቸው ሆነ። ዕስቲ ከሰሩዋቸው ሥራዎች ጥቂቱን ለማንሳት ያህል፦
2.1. በግልገል ግቤ ቁ.3/የኦሞ ወንዝ/ ግድብ ሥራ ፕሮጄክት ላይ የሠራተኛ ቅጥርን በሚመለከት በቀጥታ እጃቸውን አርዝመው የፈለጉትን ሲያስቀጥሩና እሳቸው ከወጡበት አካባቢ ብቻ ሠራተኛ በብዛት እንዲቀጠር በማድረግ የዳውሮን ወጣቶች ጎድተዋቸዋል፤ አሁንም እየጎዱዋቸው ነው። በዚህ የተነሳ ከዕለታት አንድ ቀን የአካባቢው ወጣቶቹ በመቆጣት አሁን እንደምናየው ዓይነት የህዝብ አመፅ አነሱና ፈረንጅ ሳይቀር በዱላ ደብድበው አንድ ቀን ከፍተኛ ረብሻ ፈጥረውና ሥራ አስቁመው ከፍተኛ ችግር ፈጥረው ከአዲስ አበባ የወያኔ ባለስልጣኖች ሄደው እንዳረጋጉት አውቃለሁ።
2.2 በዳውሮ ውስጥ ለሠፈራ የሚሆን ቦታ አስከልለው ከወላይታ በርካታ ህዝብ አምጥተው አስፍረዋል። በዚህ የተከለለ ሥፍራ የዳውሮ ወጣቶች በስግሰጋ ለመስፈርና አካባቢያቸውን ለማልማት ቀደም ሲል ጠይቀው ተከልክለው ነበር። የዳውሮ ወጣቶችን በዳውሮ ውስጥ ሰግስጎ ማስፈር የተከለከለበት ምክንያቱ በኋላ ላይ ገሃድ ወጣ። ለወጣቶቹ የውስጥ ስግሰጋ ለማካሄድ በጀት የለም ተብሎ ነበር አይቻልም የተባለው፤ በኋላ በጀት ከየት መጣ? አላማው ግልጽ ወጣ።
መጀመሪያ የተወገዱት የዳውሮ አመራሮች የተወገዱበት አንዱና ትልቁ ምክንያት ይሄ ነበር። መጀመሪያ የውስጥ ስግሰጋ እናደርጋለን ከዚያ በኋላ ከወላይታ ብቻ ሳይሆን ከሌላም ብሄረሰብ ባለን ባዶ ስፍራ ወደፊት እናሰፍራለን ነበር ብለው የዘጉት። እንዲህ ማለታቸው ነበር ለመወገዳቸው ዋና ምክንያት የነበረው።
አንባቢ እንዲረዳልኝ የምሻው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ተዟዙሮ እንደልቡ መሥፈር መቻል፤ ያሻውን በየትኛውም አካባቢ መሥራትና በነፃነት መኖር መቻል እንደሚገባው አጥብቀው ክሚደግፉትና ከሚያምኑት ወገን ነኝ። ይህን ያነሳሁት ግን አቶ ኃይለ ማርያም የራሱን ብሄርረሰብ እየጠቀመ ነው ይሰራልናል የሚል ወገንን በመፍጠር ይፖለቲካ ግባአት ለማግኘት በሚል የተሳሳተና አደገኛ ግምት ሌላውን የመጉዳትና የማፈን ሥራውን ገሃድ ለማሳየትና የሃገሪቱ በጀት ለሁሉም ብሄሮች እኩል የሚጠቅም አለመሆኑን ለማሳየት ፈልጌ ብቻ ነው። የሚሠራው በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን ወንበር ላይ ባለው ባለጊዜ ፍላጎት መሆኑንና የህዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው ደግሞ በስልጣን ላይ ላለው አካልም ሆነ ግለሰብ ጥቅም ሲሉ ህዝባቸውን በድለው ለመሰንበት እንደሚሰሩ ለማሳየት ነው።
2.3 በ1997 ዓ.ም. ለተካሄደው የህዝብና የቤት ቆጠራ ማካሄጃ በተዘጋጀው ይስራና የስልጠና ማንዋል ውስጥ ዳውሮን የወላይታን ብሄረሰብ በሚለው ሥር አስገብቶታል። ሆን ተብሎ ለመሆኑ በግሌ ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለኝም። እየተሰራ ያለው ደባ ያልገባቸው የምርጫው ተቆጣጣሪዎችና ቆጣሪዎች በስልጠና ላይ ሳሉ ለምን እንዲህ ሆነ?ማንዋሉ ምነው ወላይታ ሥር አስገባን? የሚል ጥያቄ አነሱ። በመጀመሪያው ቀን የአፃፃፍ ስህተት ነው ተባለና ሊታለፍ ተሞከረ። ጥያቄው አድሮ ያላየው ሁሉ አይቶት አድሮ በማግስቱ ጠንከር ብሎ ቀረበ። ተዋሽቶና በቢ.ፒ.አር ጥቂቶችን በማስፈራራት ተገታ። ጥያቄውን ያነሱት በጣም አዝነው እንዴ ካድሬዎቻችን ዳውሮ መስለውኝ ነበር ለካስ ... አሉ። ይሄ ዳውሮን የመቆጣጠርና ብሎም ወደፊት የመዋጥ አላማ ያረገዘ መሆኑ ስላሰጋቸው ነበር ሰልጣኞቹ ያነሱት። በኋላም የዞኑ አንድ ባለስልጣን እስከ ስታቲስቲክስ መ/ቤት ሄዶ ቢጠይቅም ወይድ ተባለ።
2.4 የኋላ ቀር አበል በደቡብ ክልል ደረጃ ለተመረጡ ወረዳዎች ሲፈቀድ በዳውሮ ዞን የማረቃ ወረዳ ምሁራን እንዳያገኙ ይደረጋል። በመጀመሪያ ከወረዳው ለጥናቱ የሚረዳ የተሟላ መረጃ ባለመላኩ በጥናቱ ሳይካተት ቀርቷል በሚል የኋላቀር አበል ክፍያው ውሳኔ እንዲዘለው ተደረገ። ከዚያም ስለሁኔታው ለሚነሱ ተደጋጋሚና በርካታ ጥያቄዎች ለመምህራን የተሟላ መልስ መስጠት አቃተኝ። በተለይ የዋካ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ጥቅሙን እንዳያገኙ ነው የሆነው። ፀሃፊው በወቅቱ እዚያ የትምህርት ሥራ ሃላፊ ሆኜ እሰራ ነበር። የተሟላ መልስ መስጠት አዳጋች ሆነ። ሁኔታው ግራ ያጋባል። መምህራን ጥያቄያቸውን አጠናከሩት። እኔና በወቅቱ የማረቃ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት ግለሰብ ወደ ክልሉ ሰራተኛ ማስተዳደሪያ ቢሮ /ሲ.ፔ.ኤ. ቀርብን ሁኔታውን አስረድተን ወረዳው በጥናቱ ያለመካተቱን ተረዳን። ማን እንደዚህ እንዳደረገ ማወቅ አልቻልኩም። ሁሉም አመራር ትግሬዎች ከደሙ ንጹህ መሆናቸውን ነበር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚያወሩት።
ከዚያም መረጃውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርተን እንድናቅርብ ተነጋግረን መረጃውን አዘጋጅተን አቀረብን። የክልሉ ሰራተኖች ማስተዳደርያና የአቅም ግንባታ ቢሮዎች መረጃውን ተቀብለው በስህተት እንደሆነ አምነውበት ወስነው ለክልሉ ረዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ክፍያው በቶሎ እንዲፈፀም ለውሳኔ አቀረቡ። ለካስ ነገሩን አቶ ኃይለማርያም ያለ ደብዳቤ በስልክ አግደውት ኑሯል። በኋላም አንድ ለነፍሱ ያደረ ከፍተኛ የክልል አመራር አትድከሙ። በደህዴን በኩል ክፍያው ለወረዳው እንዳይፈፀም ተወስኗል ብሎ ነገረን። ይህንን ለዞኑ አስተዳዳሪ አስጠንቅቀው ጉዳዩን ይዘጋሉ። በዚህ የተነሳ በርካታ ምሁራን ሥራቸውን ለቀው ሄደዋል። እዚያ ቆይተው የሰሩትም የሥራ ሞራላቸው ላሽቆ ለመኖር ሲሉ ብቻ ይሰሩ እንደነበር አውቃለሁ። አቶ ኃይለ ማርያም የዋካና ዙርያው ህዝብ ጠላት ናቸው። ከፍተኛ የትምህርትና የጠና ባለሙያዎች በዚህ የተነሳ ወረዳ ቀይረዋል አካባቢውን ለቀው ሄደዋል። ለዚሁ በደላቸው አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ጥቂት የዳውሮ ዞንና የክልል አመራሮች ረድተዋቸዋል።
2.5 ሰሞኑን ህዝቡ በአገሪቱ አለ የሚባለውን ልማት ተቋዳሽ አድርጉኝ የወረዳ ማዕከል ስጡኝ፤ አዲስ ነገር መስጠት እንደማትፈልጉና እንደማትችሉ እናውቃለን። የነበረንና የቀማችሁብንን የወረዳ ማዕከልነት መልሱልን የሚል የተለመደውንና የሚሰቃይበትን አቶ መለስ ዜናዊን እንኳን መመለስ ያልቻሉትን /መቼም አቃታቸው እንበልና/ ጥያቄ ዳግም በተጠናከረ ሁኔታ ለመንግስት አቀረበ። መልሱ እስር ሆነ። እስሩ ህዝቡን አበሳጨው አስመረረው። ከዚያም ጥያቄውን በአግባቡ እንደመመለስ ነፃነትን መንፈግና ማፈን ማሰር ማሰቃየት ሆነ። ይህ ብሶት እያደር ግፉ በዝቶ ይህንን ለመሸከም ባለመቻል ራሱን በእሳት የሚያቃጥል ዜጋ ፈጠረ። መ/ር የኔሰው ገብሬን።
ይህን የዳውሮ ዋካና የሌሎች የዞኑ ወረዳዎች የወረዳ ማዕከል ጥያቄን ያፈኑት የህዝቡን ነፃነትና ልማት የገረሰሱት የዘመኑ የዳውሮ ህዝብ ባላንጣና ጠላት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው። ራቅ ያለ ጊዜ የተደረገው ይቅርና የማውቀውንና በቦታው የነበርኩበትን አፈና ላውጋችሁ።
በግምት 1999 ዓ.ም. መግቢያ አካባቢ ይመስለኛል። የክልሉ አስተዳደር 29 ተጨማሪ ወረዳዎችን በክልሉ ውስጥ ላሉት ዞኖች ለማከፋፈል ይወስናል። የክልሉ መስተዳድር ባለሥልጣናት የዞን አስተዳዳሪዎችን ጨምረው ለየዞኑ ተሰብስበው ደለደሉ ተባለ። ለሲዳማ ለቤንች ማጂና ለወላይታ ዞኖች ከሃያ ዘጠኙ ግማሽ ያህሉ ደረሳቸው። የወላይታ ዞን አምስት ተጨማሪ ወረዳዎችን አገኘ። የወላይታ ህዝብ መልካም አስተዳደርንና ልማትን በቅርቡ እንዲያገኝ ተጨማሪ ወረዳዎችን እንዲያገኝ በመደረጉ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለምን አገኘ አልልም።
በእርግጠኛነት ግን ማለት የምችለው ለተጨማሪ ወረዳ ጥያቄና የወረዳ ማዕከል ጥያቄ ወላይታ ውስጥ እንደዳውሮ በህዝብ አቤቱታና እንባ ይቀርብ የነበረ አቤቱታ አለመኖሩን ነው። በዚህ ከፍተኛ የክልል አመራሮች ለራሳቸው ህዝብ ወረዳ ደለደልን ብለው ለመስጠት የዘየዱት እንደነበር መገመቱ ቀላል ነበር። እንደዳውሮ ተጨባጭ ችግር እያለባቸው ተጨማሪ ወረዳ ያላገኙ ብሄረሰቦች አሉ። በክልል ከፍተኛ አመራር ላይ ተቀምጠው እንኳ የህዝባቸውን እውነተኛ ጭንቅ አስረድተው መፍትሄ ያላመጡ አመራር ነኝ ባዮችም አይጠፉም።
የዳውሮ ተጨማሪ ወረዳ ማግኘት ዳውሮ ራሱን ችሎ ወደፊት በሌላ እንዳይዋጥ ዋስትና ይሰጠዋልና በምንም መንገድ ተጨማሪ ወረዳ ሊሰጠው አይገባም ብለው በአፅኖት የሚያምኑት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የዳውሮን ህዝብና ነፃነት እየረገጡት ይገኛሉ። የሚተባበራቸው እንጂ ተው ይህን በደል በህዝቡ ላይ ለምን ታደርሳለህ የሚል አንድም አመራር በዳውሮ ውስጥ አላየሁም።
የአሁኑ የወረዳ ይገባኛልና የወረዳ ማዕከል አላግባብ ተወስዶብኛል ይመለስልኝ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በአግባቡ እንዳላገኝ ተደርጓል ልማት ያስፈልገኛል የሚለውን የህዝቡን ጥያቄ አፍነው ረግጠውና አስረው ህዝቡ ላይ የገዛ ልጆቹ ይጫወቱበታል። ከህዝባቸው ይልቅ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አገልጋይ መሆንን መምረጣቸው ደግሞ በጣም ያሳዝናል። እውን የህዝቡ ጥያቄ ተገቢ አይደለም? የዋካን፤ ቶጫን፤ ሎማባሌንና የወልደሃኔን ህዝብ የዳውሮ ህዝብ ወገን እንዳልሆነ ነጥሎ መብት ማሳጣት ተገቢ አይደለም።
ወረዳ ካልጠቀመ አቶ ኃይለማርያም ለምንድነው በአንድ ጊዜ አምስት ወረዳ ቀምተው ለሌላ የሰጡት ወረዳ ባይጠቅም ይሆን? አንዳንዶቹ እኔ የተወከልኩት ከሌላ ወረዳ ነውና የዋካ ህዝብ ምን ያመጣብኛል ብለው ማሰባቸው አሳዛኝ ነው። የዚህ ሰለባ የሆነ የህዝብ እንባ ነገ ተጠያቂነት ማስከተሉ አይቀሬ ነው። መሳሪያ ሆኖ አገልግሎ ነገ መሸሸግ ያስቸግራል። ከህዝብ መሸሽ አይቻልምና፤ እንግዲህ በዳውሮ ዋካ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግፍና በደል በተለይ አቶ ኃይለማያም ደሳለኝ የተፈፀመበትን ግፍ አሳይቻለሁ።
አንድ ነገር ብዬ ላብቃ። ለመሆኑ ባገራችን ሰው የሚሾምበት መስፈርቱ ገብቷችኋል? ዘበኛም ቢሆን ... ፖለቲካችንን ካስፈጸመልን ልንሾም እንችላለን የተባለውን ረስቼ ነው ለካ ... ለመሆኑ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ህዝብን የበደሉ ዘረኛ ሰው መሆናቸው እውን አይታወቅምን? ዳውሮን የበደለ ለዛሬው ህዝብ አመፅና ለሞቱት ወገኖቻችን ህይወት ህልፈት ተጠያቂነት የሚጠብቀው ግለሰብ ለኢትዮጵያ ይበጃል ተብሎ ነው ያ ስልጣን የተሰጠው ? የወላይታ ሶዶ ህዝብስ በሳቸው በደል አልደረሰበትምን ይገርማል።
ወላይታና ሲዳማ መካከል በተለያዩ ሥፍራዎች የተካሄደውን ግጭት ለመከላከል ብለው ራሳቸው የሚመሩትን ጦር አዘው የጠፋው ህይወት፤ በጎፋ በወረዳና በዞን ጥያቄ የተነሳ ያደረሱት በደልና ግፍ፤ በተለያዩ ዞኖች ያደረሱትን በደሎች የሚያውቁ ወገኖች በሰፊው እያጋለጡ ወደ ህዝብ ጆሮ እንዲደርስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ተስፋ አደርጋለሁ።
በአቶ መለስ ዜናዊ ጥላ ሥር ሆነው ህዝባችንን የሚያስነቡትን ለሆዳቸው ያደሩትን የህዝብ ጠላቶች የማጋለጡ ሥራ በሰፊው መቀጠል አለበት።
በሚቀጥለው ክፍል ሶስት ፅሁፌ በቅርቡ የተጀመረውን የዳውሮ ዋካን ህዝብ አመፅ አጀማመር ሂደትና አሁን ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ፤ የሰማዕቱ መ/ር የኔሰው ገብሬን ህይወት የሚዳስስ የመጨረሻውን ክፍል ለማቅረብ አስባለሁ በቸር ያቆየን! - አሜን!



