Yenesew Gebre መምህር የኔሰው ገብሬ - የዳውሮን ህዝብ የልማት ጥያቄ፤ የደፈቀው አለማየሁ አሰፋ ማነው?

- ለመ/ር የኔሰው ገብሬ ሞትስ፤ ማን ይጠየቅ?

ክፍል ሦስት

ዋካ (ከስዊድን) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በመጀመሪያው ክፍል ፅሁፌ የዳውሮ ዋካ የሚገኝበትን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም በተለያዩ የአስተዳደር ዘመኖች የነበረውን የዳውሮ ዋካ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርዘር አድርጌ መግለፄን አስታውሳለሁ።

 

 

በሁለተኛው ክፍል ደግሞ በዳውሮ ህዝብና በዳውሮ ላይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀደም ሲል የደቡብ ክልል ር/መስተዳድር በአሁኑ ሰዓት የውጭ ጉዳይ ሚ/ርና ም/ጠቅላይ ሚ/ር ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ያደረሱትን ግፍና በደል ዘርዘር አድርጌ አስረድቼ በዚህ የአገዛዝ ዘመናቸው ወላይታን ጨምሮ በተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የፈፀሙትን በደል በመድረክ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንዲያጋልጣቸው ጥሪ በማቅረብ በክፍል ሶስት ፅሁፌ እንድንገናኝ ቀጠሮ ሰጥቼ በይደር ተሰናብቼ ነበር።

 

ይሁን እንጂ ከደረሱኝ በርካታ የኢሜል መልዕክቶች እንደተረዳሁት በዳውሮ ህዝብ በተለይም በዋካና አካባቢው ህዝብ ላይ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተፈፀመውን ዘግናኝና ኢፍትሃዊ ደባ ከማጋለጥ ባሻገር በዳውሮ ህዝብ ስም ራሳቸውን ለአቶ ኃይለ ማርያም ታማኝ አገልጋይ በማድረግ ዳውሮና ህዝቡ እንዲረገጥና ከመንግሥት እንኳ ሊያገኛት የሚገባትን ጥቂት ልማት በማሳጣት ህዝብን አገርን በመዝረፍ ራሳቸውን በስልጣን ኮርቻ ላይ ለማስቀመጥ ብሎም ለማቆየት ከፍተኛ ደባ የፈፀሙትን የዳውሮ ህዝብ ነቀርሳ የሆኑ አመራሮችን የማጋለጡ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚፈለግ ተረድቻለሁ።

 

እኔም ከበርካታ አንባቢያን ለተሰጠኝ አስተያየት ከፍተኛ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በዳውሮ ዋካ ህዝብ ላይ ዘግናኝ በደል በመፈፀም ህዝቡንና አገሪቱን ለግለሰብ አሳልፈው በመስጠትና ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከለላ በማግኘት ህዝብን በማፈን በማስፈራራት በማሰር የመንግሥት ሰራተኛውን አላግባብ በማዛወርና ከሥራ በማገድ...ወዘተ ህዝብን እያሰቃዩ እያስነቡ የዘረፉ ሙሰኞችን፤ የሰረቁና ጠያቂ ያጡ ሌቦችን፤ አገር የሸጡ ከሃዲዎችን፤ እያስፈራሩ ያለብቃታቸው ሥልጣን ላይ የተቀመጡና ወደፊትም በሥልጣን ላይ ሊቆዩ የሚሰሩ ደካማዎችን በአሉባልታ ሳይሆን ብቃት ባለው መረጃ ተንተርሼ ለአንባብያን አንድ የዳውሮን ህዝብ ባላንጣና ጠላት አስተዋውቃችኋለሁለሁ።

 

ለአሁኑ የህዝብ አመፅ እንዲሁም ለሰማዕቱ መ/ር የኔሰው ገብሬ ሞትና ከህልፈቱም በኋላ የከፈለውን መስዋዕትነት ለማጣጣል በሃሰት ምስክሮችን በተለያየ ሁኔታ በማደራጀት ለማስዋሸት የሞከረ ጭምር ነው።

 

ይህ ባለ ጊዜ እውነተኛ የዳውሮ ልጆችን በዕውቀትም ሆነ በብቃት እጅግ የሚበልጡትን ታማኝ አገልጋይ በመሆን ህሊናውን ሽጦ ምሁራንን ከሥልጣናቸው ያስባረረ፤ ዳውሮን አገሬ ብለው በሙያቸው ለማገልገል ከያሉበት አካባቢ ጓዛቸውን ጠቅልለው ዳውሮ ገብተው የአቅማቸውን እያገለገሉ የነበሩትን ከፍተኛ ባለሙያዎችን በተለያዩ ምክንያቶች በአይታዘዙልንም ስሜት በመነሳሳት በማባረር አካባቢውን የጎዳ ነው።

 

አሁን በዳውሮ ዋካ ህዝብ ባነሳው የልማትና የነፃነት ጥያቄ ዙርያ እጁን በቀጥታ በማስገባትና በማተራመስ የህዝብን ጥያቄ ወደ ግለሰቦች በማንሻፈፍ በርካታዎችን በእስራት በማስፈራራት ጥቂት የወረዳ አመራሮችን ገምግሞ ለማባረር ለማዳፈንና ጥፋትን ወደ ሌላ ሰው በማንሸራተት ለማምለጥ እየሰራ የሚገኝ ግለሰብ ነው።

 

ለነገሩ የዚህ የህዝብ እንባና ለቅሶ የመንግሥት ሰራተኞች ከሥራ መታገድና መወገድ በእስር የሚጉላሉት ወገኖቻችን በተለይም ወጣቶች ስቃይ በዋናነት ለሰማዕቱ መምህር የኔሰው ገብሬ ህይወት ብቻ ሳይሆን ከሞተም በኋላ ዓለምን ለማሳመን ይቻል ይሆናል በሚል ለተሰራው የአዕምሮ በሽተኛ ነበር ድራማው ዋና አዘጋጅ እርሱ ነበር።

 

አቶ አለማየሁ አሰፋ አሰሌ ይባላል። የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ነበር። በኋላም በትምህርት ዘርፍ ለሁለት ዓመት ተምሮ በዲፕሎማ ተመርቋል። በካድሬነት ህይወቱ ደግሞ እየተገመገመ ሲባረር ደጅ እየጠና ሲመለስ ሲባረር ብዙ ዘመን ደክሟል።ከዲፕሎማ ትምህርቱ ሲመለስ የዋካ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መ/ር የመሆን እድል አገኘ። እንዴት ያንን ቦታ በዚያች የትምህርት ደረጃ ሊያገኝ እንደቻለ አትጠይቁኝ አልነግራችሁም ብቻ በአጭሩ ርዕሰ መ/ር ሆነ። ከዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ጋር በሥራ ዘመናችን በሚገባ እንተዋወቃለን።

 

ከትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርነት ወደ የዳውሮ ዞን የማስታወቂያ መምሪያ ሃላፊነት ሹመት ተሰጠው። ሹመቱን የሰጠውን አስተዳዳሪ እግር ታቅፎ አመስግኖ ወደ ካብኔነት በአጭር ጊዜ ደረሰ። በርካታ ደጋፊዎች በየቦታው አደራጅቶ ሲያበቃ ያልሰራውንና ጭራሽ የማይችለውን ነገር ሁሉ ሳይቀር የእርሱ ግኝት አስመስለው ሊያቀርቡ የሚችሉትን ጥቂት ወሬኞችን ካድሬ አድርጎ አደራጅቶና የነገ ተስፋ ሰጥቶ የራሱን መሠረት በወሬ ብቻ አደላደለ።

 

ከዚያም ከወደታች ሰፋ አድርጌ በማቀርብላችሁ ምክንያቶች ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በዝግ ሁኔታ ተወያይቶ በዳውሮ የአቶ ኃይለማርያም ጉዳይ አስፈፃሚ ሆኖ ለማገልገልና በአመራር ላይ በወቅቱ የነበሩትንና አቶ ኃይለ ማርያም ባላጋራዎቼ ናቸው ብለው የያዙዋቸውን እውነተኛ የህዝብ አገልጋዮችንና ህዝብ የሚያምናቸውን ከማንኛውም የአመራር ቦታ ለማስወገድና ለማደባየት ቃል ገባ።

 

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለክልሉ ካብኔ የእሱ ሹመት እንዲፀድቅላቸው ሲያስተዋውቁ በዲግሪ የተመረቀ ብለው ዋሽተውና ሆነ ብለው ሌሎች አመራሮችን አታለው በማሳመን ሹመታቸው እንዲፀድቅ እንዳደረጉ ብነግራችሁ እንዳትገረሙ ከዚህ ከበድ ያለ ሌላ አለና። ሹመቱ የደቡብ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊነት ነበር ሰጡት። በኋላም ይሄ መዋቅር ወደ ፖለቲካ ቢሮ ሲቀየር የክልሉ ካቢኔና የፖለቲካ ሃላፊ ሆኖ ቀጠለ አሁንም እዚያው እየሰራ ነው።

 

አቶ ኃይለማርያም ለምን ይህን ያህል አለማየሁን አስናፈቃቸው አስወደዳቸው ይሆን? ወደሚያመልኩበት የሃዋርያት ቤተክርስቲያን ጎትተው ወስደው የእምነታቸው ተከታይም አደረጉት። በሥጋም በነፍስም ለአብሮነት ቃል ተገባ።እውነት ሊሰራ ቢሆን ምንም አልነበረም። አገርን ለማልማት ህዝብን በቅንነት ለማገልገል ቢሆን ባልከፋ ነበር።

 

ወገኖቼ ነገሩ የገባን ትንሽ ቆይቶ ነው።አቶ ኃይለማርያም ወደ ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት ዕድገት ተሰጥቷቸዋል ተብሎ ይዛወራሉ። ይህችን የፖለቲካ ክፍልዋን መዋቅር ለሌላው የወላይታ ተወላጅ እንዳይሰጧት ወላይታዎችን በክልል ሹመት ቦታ ላይ አብዝቷል ተብሎ አንድ ሰሞን ዋይታና ሁከት ታይቶ እንደነበር እስታውሳለሁ።

 

ስለዚህ ለሌላ ወላይታ ቦታዋን ሊሰጡ አልተመቻቸውም።ሲዳማዎች ደግሞ አስተዳደሩንና ፖለቲካውን አንድ ላይ ሁለቱን ከያዙት እሳቸው ወደ ላይ ያለመሰላል እንደወጡ ሁሉ ያለእርካብ ሊወርዱ ሆነ። ከክልል አስተዳዳሪነታቸው የተነሱትም በከፍተኛ የሲዳማ ህዝብ ተቃውሞ ነበር።ሌላ ታማኝ ሎሌ መፈለግና በርቀት መቆጣጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብቸኛ አማራጫቸው ሆኖ አገኙት። ዓይናቸውን ወደ ዳውሮ አማተሩ አንድ ሎሌ ፈለጉ ተሳካላቸው።

 

በመሆኑም የሳቸውን ባላጋራ እየመነጠረ በሳቸው ዣንጥላ ሥር ሆኖ በድፍረት የዳውሮ ወንድሞቹን ፈጅቶ ለዳውሮ ኮታ ብሎ ነገር ሳያነሳ የዳውሮ ህዝብ ልማት ብሎ የማያስብ ሆዱን እየሞላ ህዝብ እየዘረፈ እያሰረና እየገረፈ የሥልጣን መደላድሉን አስተካከለ። እስካሁን እሱን እያስተዋወቅሁ ነው።

 

አለማየሁ አሰፋ የህዝብ ነፃነትን ደሞክራሲን የልማት ጥያቄን ደፋቂው የኃይለ ማርያም ሎሌ በዳውሮ ዋካ ህዝብ ላይ ቀደም ሲል ወደ ክልል ተሹሞ ከመውጣቱ በፊት ያደረሰው በደል እጅግ ብዙ ሲሆን የአንባቢያንን ጊዜ ላለመሻማት በጥቂቱ ላሳያችሁ።ለእያንዳንዱ ለማነሳቸው ነጥቦች ማስረጃዎቼን እየጠቀስኩ ነው የማቀርብላችሁ።

 

1ኛ. አቶ አለማየሁ አሰፋ በ1997 ዓ.ም. የዳውሮ ዞን የማስተወቂያ መምሪያ ሃላፊ ነበረ። የዞኑ አስተዳዳሪ ጋር በመሆን የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቁ የተወሰኑ ነገሮች ላይ ተወያይተው ይስማማሉ። በጥቅም ጉዳይ ላይ ግን አለማየሁ ቀልድ አያውቅም።

 

የዞኑ አስተዳዳሪ ብዙውን ጊዜ የመማር ፍላጎት እንዳለው ሲወራ እሰማለሁ። በተለይ ውጭ አገር ካልሆነም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ። ምክንያቱን ባይናገሩም ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ተመረቅን የሚሉ አብዛኛዎቹ ጓደኞቼም ይህንን ኅሳብ ሲጋሩት እሰማለሁ። ት/ቤት እያለን ድሮ 1ኛ ዓመት 2ና ዓመት ... ምናምን የሚል ጨዋታ ብዙዎቹ ምቾት አይሰጣቸውም። ምክንያቱን አላውቅም።

 

ከዕለታት አንድ ቀን የዞናችን አስተዳዳሪ ለመማር በጣም መፈለጉን ለአለማየሁ አበክሮ ይነግረዋል። መፍትሄ ፈልግልኝ ብጤ ንግግር ይመስላል። ሲያወጣና ሲያወርድ መፍትሄ ሲፈልግ ሰንብቷል። አንድ አጋጣሚ ነገር ተገነ።

 

የዳውሮ ዞን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በዳውሮ ዞን ዋና ከተማ ለትምህርት ቤት መገንቢያ የሚሆን አማካይ ሥፍራ ሰፋ ያለ ምቹ ቦታ እንዲሰጣቸው አመለከቱ። ቀኑን በውል ባላውቀውም በ1998 ዓ.ም. ውስጥ ነው። ት/ቤት ለመሥራት የቦታ ጥያቄ ቀረበ። መቼም ማንም ኢትዮጵያዊ ያለውን መመሪያ ተንተርሶ የቦታ ጥያቄውን ከልማት ማስፋፋትና ከትምህርት ጥቅም ጋር በማያያዝ ለመፍቀድ ብዙ ጊዜ ሊወስድበት የሚገባው አይመስለኝም።ባለ ጉዳዩ እንዲያውም የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ባለሥልጣን ነው መሆን የነበረበት።

 

የካቶሊክ ቤተክርስቲያኑ ተወካይ ቀጠሮ ተሰጠውና ሄዶ በቀጠሮው ዳግም ሲመለስ ቢሮ ገብቶ ለተርጫ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ቦታ ይሰጣቸው ተብሎ የተፃፈ ደብዳቤ ይጠይቃል። የምን ደብዳቤ? እንዴ ባለፈው መጥተን ... ቀጠሮ ይዘን አልነበር እንዴ? አሃ ... በዚያ ላይ ውሳኔ ሰጥተንበታል። አይ ጥሩ እናስ ... ምላሽ ተሰጠ።

 

ለትምህርት ቤት ግንባታ የያዛችሁትን በጀት አውቀናል። ብር 200 000 /ሁለት መቶ ሺህ/ ነው። የባጀቱ አላማ ትምህርት ቤት ለመሥራት ነው። የዞናችን አስተዳዳሪ ሁለተኛ ዲግሪውን ውጭ አገር ሄዶ ለመማር ይፈልጋል! ያው ይህም ትምህርት ነውና ገንዘቡ ለትምህርት ቤት ግንባታ የተያዘው በሙሉ ለአስተዳዳሪው የትምህርት ክፍያና ወጪ እንዲሆን ተወስኗል ተብሎ ተነገራቸው። ጭካኔ የተሞላው ውሳኔ ነበር። እንዲህ ተባልን ብላችሁ ብታወሩ ደግሞ ... ማስጠንቀቂያ ብጤ ተሰጠ።

 

ይህማ ከድርጅታችን መመሪያ ውጭ ነው አሉ ካቶሊኮቹ። ይህን ካላደረጋችሁ ዳውሮ ዞን ውስጥ ያለውን ድርጅታችሁን ዘግታችሁ ከዞናችን በአስቸኳይ እንድትወጡ! አጭርና ግልጽ ነገር ተነገራቸው። ወዲያ የለ ወዲህ። አንባቢያን ስትሰሙት ቀልድ ይመስላል ግን እውነት ነው። ከአንድ አንደኛ ት/ቤት ግንባታና ሙሉ የትምህርት ሥራ ወጪ ይልቅ የአንድ ግለሰብ መማር ይበልጣል ተብሎ በጉልበት የህዝብ ጥቅም ልማት ትምህርት ተዘጋ። ገንዘቡ ወደ አስተዳዳሪውና ወደ አስገድዶ ጉዳይ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ እጅ 200 000 ሁለት መቶ ሺህ ብር ገባ።

 

ስንት ስንት እንደተካፈሉና አለማየሁ ያገኘውን ድርሻ ባይታውቅም የተጠቀሰውን ገንዘብ ስለመቀበላቸው እኔም እራሱ አቶ አለማየሁም የዳውሮ ዋካ ህዝብም ያውቀዋል፡ በኋላም የካቶሊኮቹ ሀላፊዎች በህዝብ ተጠይቀው አስተዳዳሪዎቻችሁ በግድ ወሰዱብን ብለው አስረድተዋል። ልማት አሳጡን! ሙሰኞች ይውደሙ! እያለ ህዝቡ እያለቀሰና እያነባ ያመፀው አንዱ ለዚህ አይነት ዝርፊያ ነበር። ማስረጃ የዳውሮ ዞን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን/ ኃልፊ አባ ሬንዞ ይባሉ ነበር/ ወይም ዋና ጽ/ቤት አዲስ አበባ ቀርቦ ወይም ደውሎ ለእውነት የቆመ ማረጋገጥ ይችላል። ጠያቂ የለም እንጂ አቶ አለማየሁ አስፋም የሚክዱት አይደለም። ህዝብ ከሚለማ እኔ ልልማ ብለው የዘረፉ ሌቦች ልማት ለምን ጠየቅህ ወደ ላይ ለምን አቤት አልክ አጋለጥከን ብለው የተዘረፈውን ህዝብ መልሰው ያስሩታል። ያንገላቱታል።

 

2ኛ. ዊብስ የሚባል ፕሮግራም በዩ ኤን ባለቤትነት የሚተዳደርና የሚረዳ በአንድ አካባቢ ለሚኖር ህብረተሰብ የውሃ ልማት የሚሰራ ፕሮጀክት ነበር። በዋካ ከተማና ዙርያው ለሚኖር ህዝብ በጀት ተፈቅዶለት በተለያዩ በተጠኑ ሥፍራዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ሥራ እንዲከናወን በጀት ይላካል። እጅግ ከፍተና መጠን ያለው ገንዘብ ነበር።

 

የሥራው አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ከተለያዩ ሴክተር መ/ቤቶች የተውጣጡ ግለሰቦች ነበሩ። አቶ አለማየሁ አሰፋ ትምህርትን ወክለው ወደ ኮሚቴው እንዲገባ ተመቻቸለት። በኮሚቴው ውስጥ ሂሳብ ሹም እንዲሆን ተደረገ። አለማየሁ የሚባል ሰው ሂሳብ ሹም ሆኖ ኮሚቴውን ሊያገለግል ተሰየመ። ለግንባታ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች እንዲገዙ ከሚሰሩት ባለሙያዎች ጥያቄ ቀረበ። ኮሚቴው ተነጋግሮ የገንዘቡን መጠን ወስኖ ሲያበቃ ዕቃውን ለመግዛት እሳቸው ለመሄድ እንደሚፈልጉና ለሌላ የሥራ ጉዳይ ስለምሄድ ወጪ ለመቀነስ ይመቻል ብለው አታለው ሲያበቁ በርካታ ገንዘብ ይሰጣቸውና ለግዢ ሄዱ።

 

የወሰዱት የገንዘብ መጠን ላይ ሌላ ጊዜም በተመሳሳይ ሁኔታ ጨማምረውበታል ሲለሚባል ትክክለኛ ቁጥሩን እሳቸውም የሚያውቁት አይመስለኝም። ገንዘቡን ወስደው ሲያበቁ ዕቃ የለ የገዙት ባዶ እጃቸውን ተመለሱ። ዕቃውስ? ችግር የለም ይመጣል። በጣም ጥሩ ዋጋና ግዢ አከናወንኩ...ዕቃው የታለ ታዲያ? ይመጣል እኔ ቸኩዬ ነው ነገ ከዚያ ወዲያ ሲሉ ቆዩ። ሂሳብ አወራርዳችሁ ሰነዳችሁን አውጡ ተብሎ ይታዘዛል። እንቢ አለ። አለማየሁ ሂሳብ አወራርድና ሰነዱ አዲስ አበባ በአስቸኳይ ይላካል ተባሎ ደብዳቤ ተፃፈለት።አሁን ነገሩ መረር እያለ መጣ።

 

ምነው ሂሳብ አወራርድ እንጂ! የሚል ጫን ያለ ግፊት ሲመጣ ሌሊት ሮጠና አዋሳ ገባ። ሲፈለግ በማግስቱ የለም።ምነው ሂሳብ ማወራረድ ትቶ ለምን ሄደ? ሰላም አይደለም እንዴ ምን ገጠመው ይሆን እያሉ ጓደኞቹ ሲያስቡ ይቆያሉ ... ለካስ እሱ አዋሳ የሄደበት ጉዳይ ሌላ ኑሯል።

 

ህዝብን ይሰርቁና ወይም ያጭበረብሩና ሲያበቁ ቀድመው በሩጫ ፀረ ሙስና ግቢ ገብተው ሌባ አግኝቻለሁ! አጭጭበርባሪ ይኸውላችሁ! በማለት በቅድሚያ የሚጠቁሙ እንደ ሌባ የማይታዩና ህግም ሽፋን የሚሰጣቸው መሆኑን በማመን ሂሳብ አወራርድ ተብሎ የተጠየቀው ግለሰብ ያልሰረቁትንና ሂሳብ አወራርድ ያሉትን አሳስሮ እሱ አይኑን አፍጦ በመመለስ ከወጀል ነጻ ሆነ ተብሎ በሹመት ላይ ሹመት እየደረበ አሁን ካለበት የአመራር እርከን ላይ ደርሷል።

 

በዚህ በሰሩት ደባ ያለአግባብ የታሰሩ ወገኖቻችን ከብዙ እስርና ድካም በኋላ በነፃ ወጥተው የሰረቀው ሌባ ተሹሞባቸው እነርሱም ህዝቡም በመንግሥት ሥራ አዝኖ አንገቱን ደፍቶ ይኸው እስከዛሬ ይኖራል። ሌባ አገር ይመራል። ሰርቀኸኛል ያለውን ሁሉ ያስራል ከሥራ ያባርራል።

 

የሚያሳዝነው በውቅቱ እሱ ያልተገዛና ያላቀረበውን ዕቃ ሂሳብ ለማወራረድ የማቅረቡን ምስጢር የሚያውቁትን የዚያኔ የወረዳው የፋይናንስ የቁጥጥር ባለሙያዎችና ሂሳብ ሠራተኞችን የቂም መወጣጫ ጊዜዬ አሁን ነው ብለው መሰለኝ ሰሞኑን የቀረበውን የህዝብ የልማትና የወረዳ ማዕከል ጥያቄ በምስጢር ህዝቡን አነሳስታችኋል በሚል ቅጥፈት ቀጥታ መመሪያ ለወረዳዎች እየሰጠ ከሥራቸው እያሳገዳቸው ይገኛል።

 

እንደዚሁም አንዳንድ ጠንካራ የሆኑ ግለሰቦችን ይተቹኛል ይንቁኛል ድሮ ሊስትሮና ዕቃ ተሸካሚ አልነበርክም እንዴ ዛሬ ቀን ወጥቶልህ ይሉኛል በሚል ጥርጣሬና ደካማ ምክንያት ከሥራ እስከማገድ ድረስ እርምጃ እየወሰደ ነው። ለምን የሚል ነፃ የሆነ የሲቪል ሰርቪስ በሌለበት ወገኖቻችንን ከሥራ እያፈናቀለ ቤተሰቦቻቸውን እያስራበ ለመንግሥትና ለገዢው ፓርቲም ጭምር ባላጋራ እያደራጀ ገፍቶበታል።ሰው በልጅነቱ እንደ እድሉ ምንም ሆኖ ሰርቶ ያድጋል። አድጎና ራሱን ችሎ ሲያበቃ ግን ያንን የልጅነት ምስጢሬን ታውቃለህ ብሎ ሰው አይገድልም። አሱ ግን ሰው ብቻ ሳይሆን ህዝብ እየገደለ ነው።ያባረራቸውን ለመጥቀስ አልፈለኩም

 

3ኛ. በ1997ና በ2002 ዓ.ም የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ በዋናነት አለማየሁ አሰፋ በተወዳደረበት በዳውሮ ዞን ቶጫ ወረዳም ሆነ በማረቃ ዋካ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የምርጫ መቀስቀሻ ዋናው የገዢው ፓርቲ የመቀስቀሻ አጀንዳ የወረዳ ማዕከልና የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ነበር የለፈፉት። ለህዝቡ ተጨማሪ ወረዳ ይሰጣል አይዟችሁ ብለው የቀሰቀሱት የመንደር ካድሬዎች አሳፈራችሁን አስዋሻችሁን እያሉ በግልፅ መውቀስ መጀመራቸውን አውቃለሁ።

 

እጅግ በጣም የሚያሳዝን ለአሁኑ የዳውሮ ዋካና ለሌሎችም ወረዳዎች የህዝብ አመፅ መሠረት ጥሎ የበለጠ አጠናክሮ ያለፈና በአካል የነበርኩበትን አሳዛኝ እውነት ልንገራችሁ። አንድ ትልቅ በክልል ደረጃ የተከናወነ የመልካም የአስተዳደር የትምህርትና የልማት ጉባኤ በሚል የወረዳ የዞን የአስተዳደርና የፖለቲካ ኃላፊዎች እንዲሁም የየሴክተር መ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ ባሉበት ውይይት ላይ በነበርንበት ጊዜ ነው። በ1999 ዓ.ም ሲሆን በ2ኛው ሩብ ዓመት የሥራ ጊዜ ሲሆን ቀኑን አላስታውስም። የዚያኔ የዳውሮ ዞን የፖለቲካ ሃላፊ የነበረ አቶ ካሳሁን ገበየሁ የሚባል ግለሰብ አንድ የሚገርም ሁኔታ ፈጠረ። እጅግ አሳዛኝ ነገር ነበር።

 

በውይይቱ ላይ የተጨማሪ ወረዳ አስፈላጊነት ጉዳይ ላይ እንወያይ ነበርና ጠንከር ያሉ የባለሙያ ትንታኔዎች ጭምር እየተነሱ በዳውሮ በወረዳ የቆዳ ስፋትና የወረዳ ማዕከል ችግር ሳቢያ ሥራ ለመስራት አለመቻሉን በማስረዳት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቀርቦ ሃሳቡ ከፍተኛ ትኩረት ሳበ። ወዲያው ከላይ የጠቀስኩት ግለሰብ እጁን አወጣና እኛ በዞን ደረጃ ወስነን ተጨማሪ ወረዳ እንዲሰጠን ክልሉን ጠይቀን ነበር ነገር ግን ያለበቂ ምክንያት የክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ወረዳ ከለከለን አለን።

 

አቶ ኃይለማርያም የዚያን ሰሞን ወረዳ ያድሉ ነበር።ለህዝባቸው መብትና ልማት የቆሙ አመራሮች የነበሩት ዞን ሁሉ ወረዳ ተሰጥቶታል። ታማኝና ደካማ ተወካዮች የነበሩዋቸው ዞኖች ዳውሮን ጨምሮ ወረዳ አላገኙም። መስፈርቱ ነባራዊ ሁኔታንና እውነታን መሰረት ያደረገ አልነበረም። እኛን ያስረዳን እሱ ለዳውሮ ህዝብ የማያስብ ደንታ ቢስ መንግስትና ፓርቲ በክልሉ መኖሩን ነበር። ሁላችንንም እረፉ በመንግሥት ተስፋ ቁረጡ ነበር ያለን። ይህን ያለን እሱ ጥዋት አራት ሰዓት አካባቢ ነው። ከምሳ በፊት መሆኑ ነው።

 

አቶ ካሳሁን ከምሳ በኋላ የለበሰውን ጃኬት እንኳን ሳይቀይር እጁን አውጥቶ እኛ የዳውሮ ዞን አመራሮች ለዳውሮ ህዝብ ተጨማሪ ወረዳ ይሰጥ ብለን ክልሉን አልጠየቅንም አለና ቁጭ አለ። አጋጣሚ ለእኔ ቀረብ ብሎ ነበር የተቀመጠውና ትኩር ብዬ አየሁት።ተሳታፊው በሙሉ ቢያዝንም ከማቀርቀር በስተቀር አንድም ሰው ምነው ብሎ የወረዳ ጥያቄው እንኩዋ ቢቀር ስለግለሰቡ ጤንነት እንኳ የሚጠይቅ ሰው አጣሁና በግሌ በሁኔታው በጣም አዝኜ እድል በግድ አግኝቼ የወረዳ ማዕከል ጥያቄና የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ የልማት ጥያቄ መሆኑን የዳውሮ ህዝብ የወረዳ ጥያቄ ያለው መሆኑን እንደማውቅ አስረድቼ ይህ አመራር ወደፊት ተጠያቂነት እንዳለበት መግለፄን አስታውሳለሁ። ከስብሰባ ስንወጣ ትቀልዳለህ እንዴ እንዳንተ የህዝብ ጉዳይና ፍላጎት እያወራንማ መቼ እንቆይ ነበር ብሎኝ እንደገና አቁስሎኝ ሄደ።

 

ለምሳ የወጣውን ካድሬ አለማየሁ ሆዬ ምሳውን አስጥሎት ሲያበቃ ጆሮውን ጠምዝዞት ሃሳብህን ገልብጠህ ተቃራኒውን ተናገር ብሎ ሊያናግረው መቻሉን ማየቴ እንደው አቶ ኃይለማርያምና ሎሌው የመለመሉትን የዳውሮ ዞን ካድሬዎችና ያላቸውን የህሊና ባዶነት እንዳረጋግጥ ረድቶኛል። አቅም አጡ እንጂ አንዳንድ ጠንካራ ካድሬዎችም እወረዳ ላይ ነበሩ። አይ አለማየሁ አሰፋ ህሊናህን ለጥቅምህ ብለህ ትተህ ስታበቃ በተራህ አንተ ደግሞ የሌላውን ህሊና ሰልበህ ያሻህን ታናግራለህ ።

 

የአለማየሁ አሰፋ ሥራና ወንጀል እንዲህ በአጭሩ የሚቋጭ አይደለም። በሚቀጥለው ክፍል አራት ጽሁፌ የዚህን ቀጣይ ክፍል አቀርባለሁ። ለመምህር የኔሰው ገብሬ ህዝባዊ ጥያቄና ለመስዋዕትነቱ መነሻ የሆነውን በደል ከመፈፀም ባሻገር ከመምህሩ መስዋዕትነት በኋላ ክብር ሞቱን ጥላሸት ለመቀባት የተጫወተውን ሚናና ድራማ ይዤላችሁ ብቅ እላለሁ በቸር ያቆየን!


ዋካ (ከስዊድን) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ