ዲሞክራሲን ያያችሁ? (ክፍል 1)
ሉሉ ከበደ
‘’ንስሀዬ’’ በሚለው ያለፈ ጽሁፌ መለስ ዜናዊ ስልጣኑን ለሽግግር መንግስት እንደሚያስረክብ ቃል ገብቶልናል። ምኞት አይከለከልም፤ የቢሆን ተስፋም ተዘግኖ አያልቅም። ቀጥሎ እንደግዲህ የኛ ተግባር የሚሆነው ከመለስ በሗላ መልሶ እዚያው ጭቃ ውስጥ ይዞን የሚሰጥም ወፈፌ ቡድን መልሰን ስልጣን ላይ እንዳናወጣ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። እንዴት?.. በሽግግሩ መንግስት በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን አጠናክረውና አደራጅተው፤ ለምርጫ እንዲወዳደሩ የሚፈቀድላቸው ህብረብሄር ፓርቲዎች መጀመሪያ በራሳቸው ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለ ወይ? መደማመጥ መቻቻል አለ ወይ? ብለን መመርመር መጠየቅ ይጠበቅብናል።
የሚያቀርቡልንን መተዳደሪያ ደንብና ቢመረጡ እንዴት ሀገሪቱን ሊያስተዳድሩ እንደተዘጋጁ የነደፉትን መርሀግብር ቃል በቃል እያጠናን፤ እየተወያየንበት፤ እየመረመርን በምንተዳደርበት ሰነድ ላይ የሚሰማንን ቅሬታም ሆነ ድጋፍ ከማሻሻያ ሀሳቡ ጋር እያቀረብን ወደፊት የምንገዛበትን ህግና ስርዓት ፖለቲካውን ኢኮኖሚውን ማህበራዊውን ጉዳይ ሁሉ እናዳብረዋለን ማለት ነው።
አሁን በዚህ ጽሁፌ የማቀርበው እንደ አንድ ዜጋ የሚኖረኝን የዲሞክራሲ ሀሳብ አስተዋጾ ነው። እንዲህ አይነት ዲሞክራሲ ቢኖረን ብየ ሀሳብ አቀርባለሁ። ዜጎች ሁላችሁም የየራሳችሁን ታቀርባላችሁ። የሀሳብ ማከማቻ ባንክ ውስጥ እንሰበስባለን። ከዚያ የሀሳብ ባንካችን ሲሞላ ከክምችቱ ውስጥ አበጥረው አንጠርጥረው ለኛ የሚስማማ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ይህ ነው ብለው ለመጨረሻ ውይይት የሚያቀርቡልንን ኮሚቴዎች መልምለን ሀላፊነት እንሰጣቸዋለን ማለት ነው።
ውድ አንባቢያን ልብ ይሏል፤ መለስ ዜናዊ ደደቢት ጫካ ውስጥ ለብቻው ቁጭ ብሎ የለቀለቀው አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ የኮሙሚዝም አስተሳሰብ ውራጅ ስለሆነ ያንን ለራሱ አዝሎ ይዙር። ወደሚሄድበት ይዞ የሂድ። ብቻ ከፊታችን ገለል ይበል።
አሁን ወደ ቁም ነገሩ ልመለስና ዲሞክራሲ ምንድነው?
ቃሉ ከግሪክ የተወረሰ ነው።’’ የሕዝብ ስልጣን ” ማለት ሲሆን “ዲሞስ’’ ‘’ሕዝብ’’ ‘’ክራቶስ’’ ‘’ስልጣን’’ ማለት ናቸው:: ዊኪፒዲያ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚፈታው።
ዲሞክራሲ ዜጎች ህይወታቸውን በሚነካ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ እኩል ድምጽ እንዲኖራቸው የሚደደረግበት መንግስታዊ አሰራር ነው ። ይህም የሚያጠቃልለው ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮችን በሙሉ ሲሆን ለምሳሌ ህግ ሲረቀቅ፤ ሲሻሻልና ሲጸድቅ፤ ዜጎች ሁሉ እኩል በቀጥታ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መፍቀድ ማለት ነው።
ዊኪፒዲያ እንደሚለው ምንም እንኳ ሁሉንም በጋራ የሚያግባባ የዲሞክራሲ ትርጉም ባይኖርም፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ እኩልነትና ነጻነት እንደ መለያ መስፈርት የሚታዩ የዲሞክራሲ ቱሩፋቶች ናቸው። ይህም መርህ በዜጎች ሁሉ የሚንጸባረቀው ሕግን በማውጣት ሂደትና በህግፊት እኩል መሆናቸውን በማረጋገጡ ልምድ ላይ ነው። የዜጎች ሁሉ ድምጽ እኩል ዋጋ አለው። የቡድን ወይም የግለሰብ ነጻነታቸውም በህግ እውቅና ባለው መብት ይረጋገጣል። ያም በህገመንግስት ዋስትናና ጥበቃ ይኖረዋል።
የሆነው ሆኖ ማናቸውም ዲሞክራሲ ዜጎች ህይወታቸውን በተመለከተ በሚወጡ ህጎች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የሚያደርግን መንግስት እንዲገታ ተደርጎ ካልተዋቀረ፤ ወይም ደግሞ አንድ የመንግስት አካል ስልጣንን በብዛት ለራሱ የማድረግን አሰራር መግታት ካልቻለ፤ የመንግስት ስልጣን ባንድ ወገን እጅ ይበዛና አንባገነንነት ተከትሎ ዲሞክራሲ የሚባለውን ስርዓት ትርጉም የለሽ ያደርገዋል።
ባብዛኛው አለም ‘’ዲሞክራሲ’’ ሲባል ‘’ሊበራል ዲሞክራሲ’’ የሚባለውን አይነት ለመጥቀስ መሆኑ የተለመደ ነው። ሊበራል ዲሞክራሲ የሚባለው ልዩ ልዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የሚስተናገዱበት፤ በህግፊት እኩልነት የሚረጋገጥበት፤ በመንግስትም ሆነ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጥያቄና ቅሬታ የማቅረብ መብት የሚረጋገጥበት፤ ፍትህ ቢጓደል የሚጠየቅበት፤ የግለሰብ ነጻነት የሚከበርበት፤ የሰብዓዊ መብት የሚጠበቅበት አናም በሲቢል ሕይወት እንደመደራጀት መሰብሰብ የመሳሰሉት ሁሉ የሚከበሩበት ዲሞክራሲ ማለት ነው።
ዲሞክራሲ እንደየመንግስታቱ ባህሪና የስልጣኔ ደረጃ የተለያየ ትርጓሜና አካሄድ ቢኖረውም፤ መርሁ ጠቀሜታ ላይ ሊውል የሚችለው በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም የማህበረሰብ ስብስብ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በሙያ ማህበራት፤ በንግድ ድርጅት አስተዳደር ቦርዶች በቀበሌ ፍርድ ሸንጎ በጽዋና በሰንበቴ ማህበራት ሳይቀር ሀሳብን በነጻነት መግለጽና መምረጥ መመረጥን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ይቻላል። ይህ ማለት የብሁሀን ምርጫ የሚከበርበት የህዳጣንም መብት የሚጠበቅበት ሂደት ማለት ነው።
በአሜሪካ የሚገኝው ሒላ ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊነት ምህርት ክፍል በድረገጽ ላይ ያስቀመጠው ጥናታዊ ጽሁፍ ሰብሰብ አድርጎ እንደሚያስረዳው፤
ዲሞክራሲ አራት ዋና ዋና ፈርጆችን የሚያካትት የዘመናዊ አስተዳደር ስርዓት ነው
1. ነጻና አግባብነት ባለው መንገድ ምርጫ አካሂዶ መንግስትን በሰላም የመቀየር ሂደት።
2. ሕዝብ እንደዜጋ በፖለቲካና በሲቪል ህይወቱ በነጻነት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግበት።
3. የዜጎች ሁሉ ሰብአዊ መብት የሚጠበቅበት፤ የሚከበርበት።
4. ፍትህ ለሁሉም እኩል የሚዳረስበት፤ የሕግ የበላይነት የሚከበርበት።
ዲሞክራሲ ሰላማዊ የመንግስት ለውጥ ስለመሆኑ
ዲሞክራሲ አንድ ህዝብ መሪዎቹን በነጻነት የሚመርጥበት ፤ የሰጣቸውንም ሀላፊነት በተጠያቂነት እንዲወጡ፤ በፖሊሲያቸውና ባጠቃላይ ያመራር ክንዋኔያቸው ሀላፊነት ኢንዲወስዱ አድርጎ የሚቆጣጠርበት ስልት ነው።
አስተዳዳሪ የሚሾመው በተዳዳሪው ፍላጎት፤ ስምምነትና ፍቃድ ብቻ ነው። በፓርላማ ውስጥ ማን እንደሚወክለው ሕዝቡ ይወስናል። በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማን መንግስትን እንደሚመራ ሕዝብ ይወስናል። ሕዝብ ይህንንም የሚያደርገው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በነጻነት አወዳድሮ፤ እርሱም በንቃት በምርጫው በመሳተፍ ነው። ህግና ፖሊሲ ሲወጣ፤ ሕዝቡ ከያካባቢው ወክሎ ፓርላማውስጥ ባስቀመጣቸው አባላት አብላጫ ድምጽ ይወሰናል። እንደዚያም ሆኖ የህዳጣን መብት እራሱን የቻለ ጥበቃ ይደረግለታል።
በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ህዝብ ሉዓላዊ ነው። ከፍተኛው የፖለቲካ ስልጣን ያለው በህዝብ እጅ ነው። ሕዝብ ይበጀኛል ያለውን ይሾማል። አልበጀም ያለውን ይሽራል። የፖለቲካ ስልጣን ከሕዝብ ወደ ተመራጭ መሪዎች ይፈሳል። መሪዎችም ጊዜያዊ ናቸው። ሕዝብ የሰጣቸውን ስልጣን በሀላፊነት፤ በተጠያቂነት በተፈቀደላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከውነው ከመድረክ ይወጣሉ።
ህዝብ መርጦ ስልጣን ላይ ያስቀመጣቸውን ተወካዮችና መሪዎች የመተቸት፤ የመንቀፍ፤ በእንዴት ያለ ሁኔታ ስራቸውን እያከናወኑ እንዳለ የመከታተል፤ የመቆጣጠር፤ ሙሉ መብት እና ስልጣን አለው።
ስልጣንን ከሕዝብ የተቀበሉ በብሄራዊ ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ ባለስልጣናት የህዝብን ጥያቄና ቅሬታ የማዳመጥና ባስቸኳይ መልስ የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
ምርጫ በህግ ተወስኖ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ ይካሄዳል። ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ያለ ሕዝብ ፈቃድ የስልጣን ዘመናቸውን ሊያራዝሙ የሚችሉበት አንዳችም መንገድ አይኖርም። ደግመው ለመመረጥም የሕዝብን ፍቃድ ይሻሉ።
ምርጫ ነጻና ሚዛናዊ እንዲሆን፤ ሙያው ያላቸው፤ ከአድሎ የጸዱ፤ ወገንተኝነት የሌላቸው፤ ገለልተኛ የሆኑ፤ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች በ እኩል አይን ማየት የሚችሉ ወገኖች የሚመሩት ቦርድ የምርጫ ቦርድ ይሆናል።
በወያኔ ዲሞክራሲ የምርጫ ቦርድ አባላት የሚመለመሉት አሁን መንግስት ነኝ በሚለው ፓርቲ ነው። በያምስት ዓመቱ መንግስት መሆን ያለበት አሱ ስለሆነ ባያሸንፍም አሸንፏል የሚሉ የራሱ ሰዎች ምርጫ ቦርድ መሆን አለባቸው።
ሁሉም እጩ ተወዳዳሪዎችና ፓርቲዎች፤ በነጻ የምርጫ ዘመቻ የማካሄድ
መብት ሊኖራቸው ይገባል። በአካልም ሆነ በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት፤ እቅዳቸውንና የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለመራጮቻቸው የማስረዳት ሙሉ ነጻነት አላቸው ።
ድምጽ ሰጪዎች በሚስጢር ድምጻቸውን ይሰጣሉ። ፍጹም ከአመጽና ከማስፈራራት በጸዳ መልኩ ።
ገለልተኛ ታዛቢዎች ድምጽ አሰጣጡና የቆጠራው ሂደት፤ ከማጭበርበር፤ ከማስፈራራትና ከማዋከብ፤ ከአሻጥር የጸዳ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በነጻነት የታዛቢነት ተግባራቸውን ሊያከናውኑ ይገባል ።
ምርጫ ፍጹም ነጻና ዲሞክራሲያዊ ሚዛናዊ እንዲሆን በርካታ ድርጅታዊ ዝግጅቶች ያስፈልጉታል። የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች ስልጠና፤ ያስመራጭ ባለስልጣናት ምልመላና ስልጠና፤ ምርጫውን የሚሳተፍበትና የሚቆጣጠረው ህዝብና የሙያ ማህበራት ሁሉ በቂ ልምምድና ቅድመ ስልጠና ትምህርት ያስፈልጋቸዋል ።
በዲሞክራሲያዊ ስርዓት የዜጎች ሚናና ተሳትፎ
በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ቁልፍ የዜጎች ሚና በሀገራቸው የፖለቲካ ተውኔት ሙሉና የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ነው። ‘’ እኔ ፖለቲካ አልወድም ፤ ፖለቲካና እሳትን በሩቁ ” የሚሉ የተለምዶ አባባሎችን አስወግዶ “ ማን እንዴት ያስተዳድረን?‘’ የሚለውን የሕይወት ጉዳይ ዘርዘር አድርጎ ማወቅ፤ መነጋገር፤ መከራከር ያስፈልጋል ።
ዜጎች ሕዝባዊ ጉዳዮችን ማለትም ጉዳያቸውን የመስማት የማወቅ ግዴታ አለባቸው። የመረጧቸው መሪዎችና የፖለቲካ ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ሀላፊነት በምን መልኩ እየተወጡ እንዳለ ሕዝብ በጥንቃቄ ማጤን፤ መከታተል፤ ማወቅ ይጠበቅበታል። ባለስልጣናት ስልጣናውን እንዴት እየተጠቀሙበት እንዳለ መከታተል፤ ኢንፎርሜሽን መለዋወጥ፤ ቅሬታቸውን፤ ፍላጎታቸውን፤ አመለካከታቸውን መግለጽ የዜጎች መብት ነው ።
በምርጫ ወቅት ድምጽ መስጠት ዋናውና አስፈላጊው የዜጎች ተግባር ነው ። የሚመርጡትን ግለሰብ ወይም ቡድን ከመወሰን በፊት ሕዝቡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራምና አፈጻጸም፤ ቢመረጡ እንዴት ለማስተዳደር እንደተዘጋጁ፤ ልብ ብሎ ማዳመጥ መመርመርና ማወዳደር፤ ከዚያ የዚህኛው እቅድና አሰራር ከዚሀኛው ይሻላል እያሉ በማወዳደር ለሚመርጡት ድምጽ መስጠት ነው ።
ተሳትፎ፤ ለሚደግፉት ተፎካካሪ ወይም የፖለቲካ ቡድን የድጋፍ ዘመቻ ማካሄድንም ያካትታል። ለምርጫ መወዳደርም ተሳትፎ ነው። በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ክርክር ማድረግ፤ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማደራጀትና ስለ ምርጫ መነጋገር፤ መንግስትን ጥያቄ መጠየቅም ሆነ መቃወም ነጻ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት ነው።
ሌላው አቢይ የተሳትፎ መንገድ መንግስታዊ ባልሆነ ነጻና ገለልተኛ የሲቢል ማህበራት በመታቀፍ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ነው። እነዚህም ማህበራት የሙያ ማህበራት ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የመምህራን ማህበር፡ የገበሬዎች ማህበር፤ የነጋዴዎች፤ የሀኪሞች፤ የሴቶች፤ የወጣቶች ወዘተ….
በፖለቲካው መስክም ሆነ በሲቢል ሕይወት የሴቶች ተሳትፎ እጅግ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ሴቶችን ስለ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውና ማህበራዊ አገራዊ ሀላፊነታቸው ብሎም የፖለቲካ ልምዳቸውን ለማዳበር የማስተማርና የማንቃት ሀላፊነትና ግዴታ አለ። ሴቶች በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ መብታቸውንና ፍላጎተቸውን ወክለው መቆም አለባቸው።
በዲሞክራሲያዊ አሰራር ውስጥ ዜጎች የሙያ ማህበርም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት አባልነትና ተሳትፎአቸው በራሳቸው በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ነው የሚሆነው ። ማንም ዜጋ ያንዱ ወይም የሌላው ቡድን አባል ወይም ደጋፊ እንዲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንዳችም ተጽእኖ ሊደረግበት አይገባም ።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአደግ ያልሆነ ሰው አናም በትግራይ ውስጥ ህውሀት ያልሆነ ሰው እንደዜጋ በሰላምና በነጻነት የመኖር ዋስትና የለውም ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ዋና ድርጅቶች ናቸው። ዲሞክራሲም ሕያውና ጠንካራ የሚሆነው፤ ዜጎች በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነው። የሆነው ይሁንና ማንም ዜጋ በማስፈራራትና በሀይል በማስገደድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ ሊሆን አይችልም። በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ዜጎች የተሻለ ነው ብለው የመረጡትን የፖለቲካ ቡድን የመቀላቀል ወይም የመደገፍ ነጻነትና መብት አላቸው። ይህ መብት በመንግስትም ዘንድ ሆነ በህዝብ መከበርና መጠበቅ ያለበት ነው።
እንደወያኔ ዲሞክራሲ ኢህአደግ ያልሆንክ አይማረኝ ብምርህ ማለት፤ ዘርም እርዳታም አልሰፍርልህ፤ ስራም አልሰጥህ፤ እንደሰው አይደለም እንደውሻም አልቆጥርህ ማለት፤ እስላም ያልሆንክ ወዮልህ እንደሚለው ታሊባን ወይም እንደ አልቃይዳ መሆን ማለት ነው።
ዲሞክራሲ በየፈርጁ በሚደረግ ንቁ የህዝብ ተሳትፎ ላይ ጥገኛ የሆነ ነገር ነው። የፖለቲካ ተሳትፎ ከአመጽ፤ ከደባ፤ ከሽብር፤ ከህገወጥ ድርጊትና ወንጀሎች በጸዳ መልኩ ነው መካሄድ ያለበት። ሕግን ማክበር፤ የተለያዩ አመለካከቶችን ማቻቻል፤ መቻቻል፤ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ መገለጫ ተግባሮች ናቸው ።
ይቀጥላል….
በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ግምት ከስድስት ሚሊዮን የማያንስ ኢትዮጵያዊ ባለም ላይ ተበትኖ ይገኛል ። ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ይጠፋ ይሆን? ይህ አንድ ሚሊዮን ሰው በየወሩ አስር አስር ብር ብቻ ቢያዋጣ የወያኔን አፈና ተቋቁሞ ሀያ አራት ሰዓት ለኢትዮጵያ ህዝብ አውነትን የሚያስተላልፍ ቴሌቭዢን ይኖራል። አስር ብር ማለት ደግሞ አንድ ቅዳሜ መሸታ ቤት ጎራ ብለን ከምናቀልጠው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ምንም ማለት አይደለም። እባካችሁ እባካችሁ ይህን ጽሁፍ አንብባችሁ እንደጨረሳችሁ ESAT የሚለውን በማውስ ጠቁሙና አንድ ነገር አድርጉ። እንደ አኬልዳማ አይነቶቹን የወያኔ ውሸቶች ፤ እውነቱን በማቅረብ ነው ህዝቡን መታደግ የሚቻለው። ጸሀፍትም ሁሉ በየጽሁፎቻችሁ መጨረሻ ላይ ይህንን ልመና አቅርቡ ።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር



