ኢትዮጵያ በዊኪሊክስ ፋይሎች
(ሊያነቡት የሚገባ!) - ክፍል 3
አቢይ አፈወርቅ
መሐመድ አል-አሙዲ (ሼህ)
የዛሬው ምጥን ፍተሻችን ትኩረት መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ናቸው። እኝህ ሰው ባለፉት 20 ዓመታት ምናልባትም እጅግ አወዛጋቢ ሆነው ከቆዩ ሚና ያላቸው ጥቂት ሰዎች መሀል በአይነታነት መጠቀስ የሚችሉ ሰው ናቸው። በኢንቨስትመንቱ መስክ ወደፊት ከምንፈትሸው በትግራይ ህዝብ ስም በጥቂት የወያኔ ሹማምንት ከሚሽከረከረው ከኢፈርት ጋር ገዝፈው መውጣታቸው ይታወቃል። ከገዥዎቻችን ጋር ባላቸው የጠበቀ ትስስርም በተለያዩ ጊዜያት ስለፈጸሟቸው አጠያያቂ ተግባራት በህዝቡ መሀል በስፋት መነጋገሪያ ነበሩ። በፖለቲካው፣ በሰብአዊ መብቱና በኢንቫይሮመንት ዙሪያም እጃቸውን ምን ያህል እንዳስገቡ እነሆ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።
ሼህ አል-አሙዲ ወያኔ አራት ኪሎን ከመቆጣጠሩ ከዓመት በፊት ለንደን ውስጥ እነ አሰፋ ማሞ በኢህአዴግ ጠበል ጠመቁኝ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ለወያኔ ጥብቅና ቆመው ሲንቀሳቀሱ መኖራቸው ይታወቃል። ከጥቂት ቀናት በፊት እንኳን በአቶ በረከት መጽሐፍ ምረቃ ላይ ያሰሙትን ንግግር ማጤኑ አይከፋም። ቢያሳዝንዎትም ያስቅዎታል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ብዙ ሰዎች ድርጊታቸውን የሚያሰሉት ሀብት ለማጋበስ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት አንጻር የወቅቱ ንቅዝ መሪዎች ስለሚመቿቸው ነው በሚል ስሌት ነበር። እንዲህ በቅርቡ ይፋ የወጡ መረጃዎች ግን ከዚያም በላይ ስለሼኩ ትክክለኛ ዓላማ እንድንጠራጠር ቢያደርጉን አይደንቅም።
የሚቀርቡባቸው ምክንያታዊ ክሶች በርካታ ናቸውና ምናልባት በሌላ ጽሁፍ መዳሰሱ ይበጅ ይሆናል። ለአሁኑ ግን ርእሳችንን ተከትለን ዊኪሊክስ ይፋ ወደ አደረጋቸው ምስጢራዊ የኤምባሲ መልእክቶች እናመራለን። በዛሬው ምጥን ፍተሻችን በቀጥታ ሼኩን የሚመለከቱ፣ ከአሜሪካን ኤምባሲ የተላኩ ሶስት የተለያዩ ሪፖርቶችን መርጫለሁ። ኬብሎቹ የተላኩት በ2007፣ በ2008 እና በ2010 ዓ.ም ነበር። አብረን እናዝግም።
* * *
በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካን ኢምባሲ ስለ ሼህ አል-አሙዲ በ2007 ዓ.ም ያስተላለፈውን ሪፖርት የሚጀምረው ግለሰቡን እንደሚከተለው በማስተዋወቅ ነው።
“ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ በኢትዮጵያ የገዘፈ ስፍራ ያለው የቢዝነስ ሰው ነው። በእናቱ ኢትዮጵያዊ፤ በአባቱ የመናዊ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተወለደው። ወደ ሳውዲ አረቢያ ያቀናውም በ1963 ነበር።
“ይህ ሰው ንብረቶቹ ሰፊና በየአገራቱ ያሉ ናቸው። በሰሜን አውሮፓ ካሉት ሁለቱ ትልልቅ የነዳጅ ማጣሪያዎች ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ በኡጋንዳና በጅቡቲ እስካሉት ሸራተን ሆቴሎች ድረስ ኢንቨስትመንቶቹ ተዘርግተዋል።
“በ2007 ዓ.ም የወጣው ፎርበስ መጽሔት 8 ቢሊየን ዶላር ያለው የዓለማችን 80ኛው ሀብታም ብሎታል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሚድሮክ ኢትዮጵያ የተሰኘው ግዙፍ ድርጅቱ ደግሞ በስሩ ቢያንስ አስራ አንድ ካምፓኒዎችን የያዘ ነው። እነዚህም የወርቅ ማውጫ ጉድጓዶችን፣ የኪራይ አየር መንገድ ንግድን፣ የሰፋፊ እርሻ ኢንተርፕራይዞችንና የተለያዩ አምራችና የግንባታ ካምፓኒዎችን የሚያጠቃልሉ ናቸው።” ይላል የኤምባሲው የ2007 ዓ.ም መልእክት።
የተለያዩ የኤምባሲው መልእክቶች ባለሀብቱ ከወቅቱ ገዥዎቻችን ጋር የተሳሰሩ ስለመሆናቸውና ከሌሎች ኢንቨስተሮች ይልቅ መሰናክሉ የተነሳላቸው፣ ጎዳናውም የተጠረገላቸው ስለመሆናቸው በስፋት ይጠቃቅሳሉ። ከዚያም በላይ ግለሰቡ በአገሪቱ ውስጥ እየተጫወቱ ያለው ሚና ምን ያህል የሞራል ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉ ስለመሆናቸውም የተለያዩ ሪፖርቶች አቅርበዋል። የመንግስት ከፍተኛ ሹማምንትም የሼኩን ጥቅም ለማስጠበቅ ታጣቂዎቻቸውን ሰላማዊ ህዝብ ላይ እስከማዝመት የሚዘልቁ መሆናቸውን ከኤምባሲው የምርመራ ውጤቶች መረዳት አይገድም።
እኛም በረድፍ በረድፉ ለማየት እንዲመቸን የባለ ሀብቱን የሞራል ደረጃ በሚፈትሸውና በወቅቱ ገዥዎች የተሰጣቸውን ከለላ ልክ በሚያሳየው የኤምባሲው የ2010 ዓ.ም የምርመራ ሪፖርት ቅኝታችንን እንጀምር።
አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ!
“ከዲሴምበር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የሻኪሶ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ያለ ወንዝ በመርዛማ ዝቃጭ በመበከሉ ሰዎችና እንስሳት እየታመሙ ነው። የሚል ክስ ማሰማት ጀመሩ። ነዋሪዎቹ ለዚህ የጤና ብክለት ተጠያቂው የሼህ አል-አሙዲ ንብረት የሆነው የላጋዳንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስለመሆኑ ከሰዋል። የፓርላማ አባል የሆኑት ደምባቦ ቦኩም ይህንኑ ከሼሁ የማዕድን ማውጫ ወደ ወንዙ የተደፋውን ዝቃጭ በተመለከተ ‘የተለያዩ አገር በቀል ኤክስፐርቶች ባደረጉት ምርመራ በውሃው ውስጥ በአደገኛ መጠን የተከማቸ ሜሪኩሪ መገኘቱን አረጋግጠዋል’ ብለውናል።
“ዲሴምበር 3 ቀን የሻኪሶ ተማሪዎች ይህንኑ ብሶታቸውን ለወረዳው ኃላፊዎች አመለከቱ። የሼክ አል-አሙዲ ካምፓኒ በወንዛቸው ላይ በረጨው መርዛማ ዝቃጭ ሳቢያ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ልክም ዘረዘሩ። በተጨማሪም ባለሀብቱ ከመሬታችን ወርቅ እያወጡ ለአካባቢው ማህበረሰብ እድገት ግን አንዳችም አይነት አስተዋጽኦ አያደርጉም ሲሉም ከሰሷቸው። በአካባቢው የስራ አጡ ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ሼሁ ግን አብዛኛውን ሰራተኛ የሚያስመጡት ከሌላ ስፍራ በመሆኑም ኮነኗቸው።
“የጉጂ ዞንና የሻኪሶ ወረዳ ሹማምንት ሁኔታውን አጥንተው መልሱን በዲሴምበር 16 እንሰጣችኋለን ነበር ያሏቸው። ይሁንና በተቀጠረው ቀን መልሱን ለመስማት የሄዱ ነዋሪዎችን የጠበቃቸው በክልልና በፌደራል ፖሊስ መከበብ ነበር። ብዙ ሰዎችም ታሰሩ።” ይላል የኤምባሲው ሪፖርት።
ይህ የአካባቢው ህዝብ ብሶት መሰማት የጀመረው ሼክ መሀመድ አል አሙዲ ከለጋደምቢው የወርቅ ማውጫቸው በተጨማሪ በሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሳካሮ በሚባለው አካባቢ አዲስ የወርቅ ማውጣት ፍቃድ እንዲሰጣቸው ካመለከቱበት ወቅት ጀምሮ ነበር። ህዝቡ ይህን የነዋሪውን ጤና እየነሳ ያለውን መርዛማ ዝቃጭ ሳያጸዱ ሌላ ፈቃድ ሊሰጣቸው አይገባም ባይ ሆነ። ይህንኑ አስመልክቶ የኤምባሲው ሪፖርት የሚለውን እንመልከት።
“ለጋዳምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ንብረትነቱ የመሀመድ ኢንተርናሽናል ዲቨሎፕመንት፣ ሪሰርች ካምፓኒስ ወይንም በምህጻረ ቃል የሚድሮክ ኢትዮጵያ ነው። ባለቤቱ ሼህ መሀመድ አል-አሙዲ ሲሆን ይህ ካምፓኒው በሀገሪቱ ብቸኛው በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚሰራ የወርቅ አውጭ ድርጅት ነው። ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ከላጋዳምቢ ብቻ 466 ሚሊየን ዶላር አግኝቷል።
“በኖቬምበር 24-2009 ዓ.ም ደግሞ ከላጋዳምቢ የወርቅ ማዕድን ቀበቶ 3ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ባለው በሳካሮ አካባቢ 20ሺህ 48 ኪሎ ግራም ወርቅ እንዲያወጣ ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የ10 ዓመት ውል ተዋዉሏል። ይሁንና ይህ ሁሉ የአካባቢው ብክለትንና በዚህም የተከሰተውን የጤና ቀውስ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በሂደቱ ተጠቃሚ ያለመሆኑ ክስ እያለ ተጨማሪው ኮንትራት መሰጠቱ ነዋሪውን አበሳጭቷል።” ይላል ሪፖርቱ።
ሼህ መሀመድ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር እያጋበሱበት ያለው ካምፓኒ የሚያፈሰው መርዛማ ዝቃጭ የህብረተሰቡን ጤና እየበከለ መሆኑ ያሳሰባቸው አይመስሉም። የአካባቢው ባለስልጣናት የህዝቡን የተቀናጀ ስሞታና ጩኸት ተቀብለው ጉዳዩን ለመመርመር ቃል ሲገቡ እንኳን እጅግ አጠያያቂ በሆነ ሁኔታ የፌደራሉ ባለስልጣናት ጣልቃ ገብተው ችግሩን ከመመርመር ይልቅ ተቃውሞው እንዲታፈን የኃይል ርምጃ መውሰዱን ነው የመረጡት። ሼሁም የካምፓኒያቸውን መርዛማ ዝቃጭ ከማጽዳት ይልቅ ይብሱኑ አዳዲስ ጉድጓዶችን ለመቆፈር ነበር የወሰኑት።
ይህንኑ በመቃወም ብሶታቸውን በማሰማታቸው የታሰሩት ሰዎች ከ100 በላይ መሆናቸውን ግራ ቀኙን እያነጋገረ የመረመረው የአሜሪካ ኤምባሲ በሪፖርቱ አመልክቷል። 8ቱ ብቻ ፍርድ ቤት ቀርበው ከተደጋጋሚ ቀጠሮ በኋላ በነጻ ሲሰናበቱ እንኳን ፖሊስ ግን ሳይፈታቸው መቅረቱን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ሁለት የተለያዩ የፓርላማ አባላት ምስክርነታቸውን ለኤምባሲው ኦፊሰር አሰምተዋል።
ሌላው ቀርቶ በሻኪሶ ህዝባዊ ተቃውሞው ቅርጽ ይዞ በተነሳበት ወቅት በስፍራው ያልነበሩ 3 የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ በዚሁ ሳቢያ ተይዘው ያቤሎ እስር ቤት ተወርውረው ነበር። በወቅቱ ሁለት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጀት አባላትም የደረሱበት ሳይታወቅ መቅረቱ ተነግሯል።
የህዝቡን ችግር ችላ ብሎ የሼሁን ጥቅም ለማስጠበቅ የተወሰደው እርምጃ በከፍተኛ የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት የታዘዘ ስለመሆኑ የቀረበውን ህዝባዊ ክስ ከሚያጠናክሩ ክስተቶች አንዱ የጅምላ እስሩን የፈጸመው ተልእኮ የመጣ የፌደራል ፖሊስ ኃይል መሆኑ ሲሆን ‘አፈሳው ህጋዊ ነው።’ የሚል መከራከሪያ ለመስጠት የሞከሩትም የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ሽመልስ ከማል ናቸው።
ይህ ህዝባዊ ቁጣ እየጋለ ሲመጣ ደግሞ ሼክ ሙሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ አንድ የለመዷትን መደለያ ነበር ለመጠቀም የሞከሩት። ልክ ለአንዳንድ ታዋቂ አርቲስቶች ገንዘብ ወርወር እያደረጉ በጎ ስም ለማትረፍ እንደሚያስወሩት ሁሉ በሻኪሶም በርካታ ሰዎች የአልጋ ቁራኛ ከሆኑና ከ100 በላይ ዜጎች ህጋዊ ተቃውሞ በማሰማታቸው ምክንያት ዘብጥያ ከተወረወሩ በኋላ ሼኩ በአካል ወደ ሻኪሶ ብቅ ብለው ህዝቡን በፍርፋሪ ሊገዙት ሞከሩ። እስቲ ከኤምባሲው መልእክት ላይ የፓርላማ አባሉን፤ ደምቦባ ቦኩን ያጣቀሰውን ዘገባ እንመልከት፦
“ጃንዋሪ 20 ቀን ሼህ አል-አሙዲ ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴሩ ከአለማየሁ ተገኑና ከኦሮሚያ ክልል ፕ/ት ከአባ ዱላ ገመዳ ጋር ሻኪሶ ድረስ መጡ። የተወሰኑ ተመርጠው የተጠሩ ሰዎች ብቻ በተገኙበት መድረክ ላይም በጉጂ ዞን ላሉ 15 ወረዳዎች ልማት የሚውል በድምሩ 15 ሚሊዮን ብር ረድቻለሁ አሉ። ይህ ግን ለአብዛኛው የአካባቢው ነዋሪ ትርጉም የሚሰጥ አልነበረም። ህዝቡ እጅግ የዘገየ፤ እጅግም ያነሰ ነው ሲል አጣጣለው። ይልቅስ የታሰሩት ወገኖች በአስቸካይ እንዲፈቱና የአካባቢውን ወንዝ የበከለው መርዛማ ኬሚካል እንዲጸዳለት መጠየቁን ቀጠለ።”
ይህ ግራ ቀኙን መርምሮ የቀረበ የኤምባሲው ኬብል ሪፖርቱን የሚያጠናቅቀው በሚከተለው አስተያየት ነበር።
“ከዚህ መርዘኛ ብክለት ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ኃያል የሆኑትን ኢንቨስተር የሚቃወም ትክክለኛ የሆነ ‘ግራስ ሩት’ እንቅስቃሴ በሻኪሶ ወረዳ ቅርጽ ይዞ ወጥቷል። የአካባቢው ሹማምንት ጉዳዩን ለመመርመር የነበራቸው ፈቃደኝነት ግን ወዲያውኑ ተንኗል። ይህም የሆነው የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት በማናቸውም መንገድ ተቃውሞውን አዳፍኑ! የሚል ትእዛዝ በማስተላለፋቸው ነው የሚለው የደምቦባ ክስ ከመሰረቱ የሚታመን ነው።
“በአኳያው ይህንን ችግር አጉልቶ ለማውጣት ደምቦባም ሆኑ የማህበረሰቡ መሪዎች የነደፉት ስትራቴጂ ያለ አይመስልም። የአካባቢው ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ በተወሰደው የጅምላ እስር ሳቢያ ፍርሀት ቢያድርባቸው እውነት አላቸው። ስለዚህ ችግሩ ጎልቶ ወጥቶ የበለጠ ትኩረት ማግኘት የሚችለው የፓርላማ ተመራጩ ደምቦባ ወይንም ሌላ በከፍተኛ ደረጃ ያለ ሹም ችግሩን የራሱ አድርጎ ወስዶ ከተንቀሳቀሰ ብቻ ነው።” ይላል የኤምባሲው ግምገማ።
ይህንን መሰሉን የባለ ሀብቱን የሼህ መሀመድ አል-አሙዲን የሞራል ደረጃ የሚያስጠይቁ ሌሎች ተግባራትም ከኤምባሲው ሾልከው በወጡ ሪፖርቶች ላይ ተፈትሸዋል። በተለይ ይህች ሀገር ምን ዓይነት ሞራል ያጣ ትውልድ እንድታፈራ እንደሚመኙላት የሚያሳብቀውን በሼሁና በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር በሆኑት በዶናልድ ያማማቶ መሀል የተደረገውን ውይይት ስንቃኝ ‘እውን እኚህ ሰው አላማቸው ሀብት ማጋበስ ብቻ ነውን?’ ሊያሰኘን ሁሉ ይችል ይሆናል። ለማንኛውም ፍሬ ነገሩን ከምንጩ ለመቅዳት ይመቸን ዘንድ ሴፕቴምበር 4 ቀን 2007 ዓ.ም በሼሁና በአምባሳደሩ መሀል የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ ከ2 ቀናት በኋላ የተላላፈውን ኬብል እንደሚከተለው እንቃኝ።
“ከፈቀዳችሁልኝ… ለፖለቲካ አላማ እሰራለሁ” ሼህ ሙሀመድ አል-አሙዲ
“በኢትዮጵያ ትልቁ ኢንቨስተር የሆነው ሼህ መሀመድ ሁሴን አል አሙዲ በሀገሪቱ ስላለው የቢዝነስ ሁኔታ፤ ስለ ኢንቨስትመንቶቹና እቅዶቹ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንዴት መስራት አንደሚቻል ያለውን ሀሳብ ባደረግነው ውይይት ላይ አካፍሎናል።” ሲል የሚጀምረው ይህ የአምባሳደር ያማማቶ መልእክት መንደርደሪያውን ያዋለው ሼኩ ስለኢንቨስትመንታቸው በሰጡት ዝርዝር ላይ ነው።
ሼህ መሀመድ በፔትሮሊየም መስክ ሚና ካላቸው አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎታቸውን እየጠቀሱ አሁንም በናይጀሪያና በአንጎላ እንደ ኤክሶን እና ቶታል ካሉ ኩባንያዎች ጋር እየሰሩ ስለመሆናቸው ያወሳሉ። በሞሮኮ፣ በቦትስዋናና በኮትዲቯር ስላላቸው ኢንቨስትመንትም ይዘረዝራሉ።
እጅግ የሚያስገርመው ግን በሶማሌ ላንድ የበርበራ ወደብን በወጉ ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት የሚተርኩት ዓላማቸው የቢዝነስ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆኑን በመናዘዝ መሆኑ ነው።
(ካሁን ቀደም በአንዳንድ የምዕራቡ አለም የፕሬስ ውጤቶች ላይ እንደተዘገበው ሁሉ) አሜሪካኖቹ በሼሁ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ ከግምት በማስገባት ይመስላል፦ ‘ያለ እናንተ ፈቃድ አንዳች አላደርግም’ እያሉ ሲማጸኑ ይታያሉ። እስቲ ከአምባሳደሩ መልእክት የሚከተለውን እንጨልፍ።
“ሼህ አል-አሙዲ የበርበራ ወደብን መገንባት እንደሚፈልግ ቢገልጽም ‘የአሜሪካን መንግስት በጎ ፈቃዱን ካልቸረኝ በቀር እቅዴን በምንም ተአምር አልተረጉመውም’ ብሎናል። ምክንያቱን ሲገልጽ ‘እኔ ከማገኘው የቢዝነስ ዲል ይልቅ ዋናው አስፈላጊ ነገር የአሜሪካን መንግስትን ፖለቲካዊ ስሜት መጠበቄ ነው።’ ነው ያለን። እንዲያውም በሶማሌ ላንድ መስራት የሚፈልገው ለቢዝነስ ሳይሆን ለፖለቲካ ዓላማ እንደሆነም ነግሮናል።”
አምባሳደር ያማማቶ በዚሁ መልእክታቸው መዝጊያ ላይ የበርበራ ወደብን በተመለከተ ለሼሁ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ መስሪያቤታቸውን ጠይቀዋል።
አል-አሙዲ ግን በዚህም አያቆሙም። ራሳቸውን የአሜሪካኖቹ ፍላጎት አስፈጻሚ አስመስለው ለማቅረብ የሚደክሙ ይመስላሉ። ለዚህም በዓመት 90ሺህ ሰማያዊ ጅንስ የሚያመርት ፋብሪካ ትግራይ ውስጥ መክፈታቸውን ከመጥቀስ ጀምረው የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ የአሜሪካ ፖፕ አርቲስቶችን አርአያው እንዲያደርጋቸው ያላቸውን ህልምና እያደረጉ ያሉትን ጥረት ይዘረዝራሉ። እስቲ አገራችን ምን አይነት ራዕይ የለሽ ወጣቶች እንድታፈራ እንደሚጓጉላት ከሪፖርቱ ውስጥ እንመልከት፦
“ሼህ አል-አሙዲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንዲቀየር ወጣቶቹ መቀየር አለባቸው የሚለው እምነቱን እየደጋገመ ገልጾልናል። በዚህም የኢትዮጵያን የሚሊኒየም በዓል አከባበርን በተመለከተ የተንቀሳቀሰው በተለይ ወጣቱ ትውልድ ላይ በማተኮርና ወጣቶቹ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ በማለም መሆኑን ነግሮናል። ለዚህ አላማው ስኬትም የአሜሪካኖቹን ሙዚቀኞች ብላክ አይድ ፒስ፣ ጃኔት ጃክሰን፣ ቢዮንሴ ኖዌል እና 50ሴንትን ከሴፕቴምበር እስከ ጃንዋሪ ባለው ጊዜ ኮንሰርታቸውን እንዲያቀርቡ ማድረጉን አውርቶናል። ዝግጅቶቹ በቀጥታ እንዲተላለፉም ከኤች.ፒ.ኦ ጋር እየተደራደረ ነበር። ለበዓሉ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከቢዝነስ ይልቅ አገሪቱ በአለም ፊት ያላትን መልክ ለመቀየርም ነው ባይ ነው።” ይላሉ ያማማቶ።
‘ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት የማደርገው ከአይምሮዬ ይልቅ ልቤን ተከትዬ ነው’ የሚሉት እኚህ ባለ ሀብት የወያኔን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በተመለከተም ከአምባሳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት አንስተዋል።
“ምንም እንኳን ህዝቡ “ ይላሉ አል-አሙዲ “የአሜሪካ ሸቀጦች ወደ ሀገሪቱ መግባትን በተመለከተ ጥሩ ስሜት ቢኖረውም መንግስት ግን አመለካከቱን ከሶሻሊስት ወደ ካፒታሊስት መር እድገት ለመቀየር ጊዜ ወስዶበታል።” ብለዋል።
አምባሳደር ያማማቶ በዚሁ ውይይታቸው ወቅት አሁንም አንዳንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መቀየር እንደሚያስፈልጋቸው ሼኩ መናገራቸውን ያስታውሱና፦
“ይበልጥ የትኞቹ ፖሊሲዎች አስፈላጊ እንደሆኑ ወይም በቅርብ ጊዜ ለመተግበር የላቀ እድል ያላቸው የትኞቹ እንደሆኑ ያቀረብንለትን ጥያቄ ግን አድበስብሶ አልፎታል።” ሲሉ በሪፖርታቸው አካተዋል።
እንግዲህ ሼህ መሀመድ አል-አሙዲ ከገዥው የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት ጋር እራሳቸውን አቆራኝተዋል። ካምፓኒያቸው ባገሪቱ ዜጎች ጤና ላይ ትልቅ ችግር የፈጠረ አደጋ ሲጋረጥ እንኳ የተፈጠረውን ጥፋት ለማረም አልደከሙም። የህዝቡን አንገብጋቢ የሆኑ የህልውና ጥያቄዎች ከማድመጥና ካምፓኒያቸው የደፋውን መርዛማ ኬሚካል በማጽዳት አካባቢውን ከብክለት ከመጠበቅ ይልቅ ተበዳዩ ሰላማዊው ህዝብ ይብሱኑ ለጅምላ አፈሳ እንዲዳረግ ነው የተውት።
የአገሪቷ ተረካቢ ትውልድን አመለካከት ለመቅረጽም አላማዬ ብለው መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል። ችግሩ ይህ አላማቸው እጅግ አስፈሪ መሆኑ ላይ ነው። 50ሴንትን ወይ ጃኔት ጃክሰንን አርአያው ያደረገ ፤ ብልክ አይድ ፒስ ወይንም ቢዮንሴ ኖዌልን ‘ዩኒቨርሲቲዎቼ’ ያለ ትውልድ ለመጭዋ ኢትዮጵያ ምን አይነት ተስፋ እንደሚሆናት ማሰቡ ይከብድ ይሆናል። ባለ ሀብቱ ሼህ ግን የተመኙላት ይሄንኑ ነው።
በህዝብ መሀል በስፋት ሲታመን እንደቆየው ሁሉ የአሜሪካ ኤምባሲም እኚህ ሰው ከገዥዎቻችን ጋር ምን ያህል እንደተሳሰሩ እና የሚሰጣቸውን ልዩ ከለላም እየደጋገመ ገልጿል። እኛም ይህችን አጭር ምጥን ፍተሻ ከመቋጨታችን በፊት ቀድሞ የህዝብ ሀብት የነበሩ ተቋማትን እንዴት እኚህ ባለ ሀብት እየተቆጣጠሯቸው እንደመጡ በተወሰነ ደረጃ የሚያሳየውንና ከኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ጋር የተገናኘውን የኤምባሲውን መልእክት ጨምቀን በአጭሩ እንይ ፦ (በነገራችን ላይ ኤምባሲው ለዚህ በ2008 ዓ.ም ላስተላለፈው ምስጢራዊ ኬብል የሰጠው ርእስ “ፕራይቬታይዜሽን ኦር ሞኖፖላይዜሽን ኢን ኢትዮጵያ? “ የሚል ነበር።
“የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ግል ሀብት ማዛወር የጀመረው በ1994 ዓ.ም ነበር። ኤጀንሲው ያከናወናቸውን ዝውውሮች በተመለከተ የተማላ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባይሆንም ልናሰባስባቸው የቻልናቸው መረጃዎች የሚያሳዩት ግን የኢትዮ ሳውዲው ሚሊዮነር የሼህ ሙሀመድ አላሙዲ ንብረት የሆኑ ወይንም ግንኙነት ያላቸው ካምፓኒዎች በዋጋ ደረጃ ከፍተኛውን ድርሻ መውሰዳቸውን ነው። ከመንግስት ወደ ግል ከተዛወሩት ድርጅቶች መሀል ይህ ነው የሚባል የገንዘብም ሆነ የስትራቴጂክ ዋጋ ያላቸውን ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ የአል-አሙዲ ካምፓኒዎች ናቸው የጠቀለሏቸው።
በቁጥር ደረጃ ምንም እንኳን ኤጀንሲው ከሸጣቸው 254 ካምፓኒዎች 233 ያህሉ ለሌሎች ግለሰቦች ወይም በሴፍትኔት ለተደራጁ ሰራተኞች የተሸጡ ቢሆንም እነዚህ ግን ጥቃቅን ሱቆችና ሆቴሎች ብቻ ናቸው። ሼህ አል-አሙዲ ግን እየመረጠ የወሰዳቸው ካምፓኒዎች በቁጥር 21 ብቻ ይሁኑ እንጂ በገንዘብ ደረጃ ከአጠቃላይ 60 በመቶውን ወይንም በወቅቱ ምንዛሪ 2.34 ቢሊየን ብር የሚያወጡትን ነው የሸፈነው።” ይላል የኤምባሴው ሪፖርት።
የእነዚህ 21 ካምፓኒዎች ስም፣ የተሸጡበት የገንዘብ መጠንና የገዟቸው የሼኩ ካምፓኒዎች ዝርዝርም በሪፖርቱ ውስጥ ተካቷል። ይህን መሰሉ ዋና ዋና የተባሉትን እና ለሽያጭ የቀረቡትን የህዝብ ሀብቶች ሙሉ ለሙሉ አንድ ግለሰብ ብቻ እንዲቆጣጠራቸው የተደረገበት ሁኔታ ምን ያህል አጠያያቂ እንደሆነ ደግሞ የአሜሪካ ኤምባሲ የሚለው አለው፦
“ከሼሁ ጋር የተያያዘ ኩባንያዎች ኤጀንሲው ለገበያ ካቀረባቸው መሀል ምርጥ ምርጡን እየለቀሙ ወስደዋል። ለምሳሌ፦ ላጋዳምቢ በአገሪቱ በስፋት የተዘረጋ ብቸኛ የወርቅ ማውጫ ነው። ውሽ ውሽ ደግሞ በአገሪቱ ብቸኛው በእርሻ ደረጃ የተቋቋመ ሻይ ቅጠል አምራች ነው።
“ሼህ አል-አሙዲ ከወቅቱ ገዥ ፓርቲ ከህወሐት/ኢህአዴግ መሪዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው መሆኑ ይታወቃል። የተለየ መጠቃቀም እንዳላቸውም በስፋት ይነገራል። ምንም እንኳን ጨረታን በተመለከተ ገጥጦ የወጣ አድሎ ባይታይም አንድ ግለሰብ ይህን ያህል ዋና ዋናዎቹን በገንዘብ ዋጋቸውም 60 በመቶ የሆኑትን ለብቻው ጠቅልሎ መያዙ ግን ሂደቱ በእርግጥ ውድድር ያለበት ነው ወይ?’ ያሰኛል።” ይላል ዊኪሊክስ ይፋ ያወጣው የኤምባሲው ሪፖርት አስተያየቱን ሲያጠቃልል።
(በሚቀጥለው ክፍል በሌላ ርእሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት)
www.ethiopiazare.com



