ለልጅ ልጆቻችን ስንል - የአዲስ ዘመን መልዕክት
ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
የአሥራ ሰባት ዓመት ወጣት ነው። ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ በእጁ ይዟል። እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፣ ንግግር አድርገው ወደ ጨረሱ አንድ የእድሜ ባለጸጋ ሰውዬ ቀስ በቀስ ይጠጋል። ሳያስቡት የያዘውን ሽጉጥ ወደ እርሳቸው ደቅኖ ይተኩሳል። ሰውየው ይወድቃሉ። አካባቢው ተረበሸ። ተናወጠ። አምቡላንስ ተጠርቶ በአፋጣኝ በስፍራው ደረሰ። የወደቁትን አባት በአምቡላንሱ የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች አነሷቸው። የፍጥነት ጉዞ ወደ ሆስፒታል ጀመሩ። ሆስፒታል ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የኝህ ሰው ሕይወት አለፈች።
ይህ ወጣት ይጋል አሚር ይባላል። ተኩሶ የገደላቸውም ሰው፣ የቀድሞ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይሳቅ ራቢን ነበሩ።
ይሳቅ ራቢን እድሜ ዘመናቸውን በሙሉ የጥይትና የመድፍ ድምጽ በመስማት ያሳለፉ ጦረኛ ወታደር ነበሩ። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1941 ከታዋቂው ሞሼ ዳያን ጋር የፓልማክ ግብረኃይል አባል ሆነው፣ ያኔ በፍረሳንዮች ቅኝ ግዛት ስር በነበረችው በሊባኖስ የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረው የፈረንሳይ ቪቺ መንግስት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል። በዚያ ጦርነት ጊዜ ነበር ሞሼ ዳያን አንድ አይናቸውን ያጡት።
ከዚያ በኋላ ከአረቦች ጋር በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ትልቅ ጀግንነትና የውትድርና ብቃት ያሳዩ፣ በእሥራኤል ታሪክ አሉ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የጦሩ የኢታ ማጆር ሹም ሆነውም አገልግለዋል።
ይሳቅ ራቢን ”እኔ ሰላም ሳላይ እድሜዬን ጨርሻለሁ። ለልጆቻችን ሰላም ማምጣት አለብን” በሚል እምነት፣ ድፍረት የተሞላበት የሰላም እርምጃ ወሰዱ። የእሥራኤል ጠላቶች ከሚባሉ ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ኢሳቅ ራቢን ከመገደላቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገሩት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንና ለመሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አስደናቂ አባባል ነበር ። ”የሰላም መንገድ ከጦርነት ይሻላል። ይሄን የምለው እንደ አንድ ወታደር ነው። መከላከያ ሚኒስቴር ሆኜ የእስራኤል ወታደሮች ቤተሰቦች ስቃይ ይሰማኛል። ለነርሱ፣ ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ስንል መንግስታችን ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ማንኛውንም ቀዳዳ፣ ማንኛውንም እድል መጠቀም አለበት። ሰላም አንድ ጸሎት ብቻ አይደለም። ሰላም የጸሎታችን መጀመሪያ ነው” ነበር ያሉት።
የጦርነትን፣ የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ አደገኛነቱን ያወቁታልና፣ አብረዋቸው የነበሩ ጓደኞቻቸው ሲረግፉ፣ አካለ ስንኩል ሲሆን፣ ንብረት ሲወድም፣ ሰው በሰው ላይ ሲጨክንና አውሬ ሲሆን አይተዋልና፣ እርሳቸው የኖሩበትን በጦርነት የተበከለን አየር ለልጅ ልጆቻቸው ማውረስ አልፈለጉም። እርሳቸው ይመኙትና ይናፍቁት የነበረውን ሰላም፣ እርሳቸው ባያገኙትም እንኳን፣ የልጅ ልጆቻቸው እንዲያገኙ መደረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው ተገነዘቡ። ”ለልጅ ልጆቻችን ስንል ሰላም እንዲመጣ የተገኘችዋን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም አለብን” በሚል ጽኑ አምነት፣ በጦርነት ያልሆነ፣ የወስጥና የልብ ጀግንነት ለማሳየት ተንቀሳቀሱ። የእሥራኤል ጠላት ከተባሉት ከነያሲር አራፋት ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ብዙ ተቃውሞ መጣባቸው። እነ ናታንያሁ ተነሱባቸው። ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በጭንቅላት ሳይሆን በጠመንጃ የሚያምኑ፣ እነርሱ ብቻ ከሌላው እንደተሻሉ አድርገው በመቆጠር በትእቢት የተወጠሩ፣ ከነርሱ ዘር ውጫ ለሌላው ግድ የማይሰጣቸው ሰዎች በርሳቸው ላይ ማንጎራጎር ጀመሩ።
ኢሳቅ ራቢን ግን ወደ ኋላ አላሉም። ”የሰላም ጠላቶች አሉ። ሊጎዱን፣ የሰላሙን መንገድ ሊያጨናግፉን የሚፈልጉ። በድፍረት እናገራለሁ። ከፍልስጤማውያን መካከል የወጣው፣ በፊት ጠላታችን የነበረው የፍልስጤም ነጻ አውጭ ግንባር አሁን የሰላም አጋራችን ሆኗል” ሲሉ ከቀድሞ ጠላቶቻቸው መካከል ወዳጆችን እንዳፈሩ ተናገሩ። ከያሲር አራፋት ጋር በአንድ ላይ ለሰላም ቆሙ። ኢሳቅ ራቢን በጦርነት ሊያጠፉት ያልቻሉትን የያሲር አራፋትን ቡድን በሰላም አሸነፉት።
ታዲያ ለዘመናት በጦር ሜዳ ሲዋጉ በጥይት ያልተመቱት እኝህ ታላቅ ሰው፣ በሰላሙ ሜዳ በቴላቪቭ ከተማ ጥይት አገኘቻቸው። ለሰላም ለፍቅር ለወንድማማችነት ሲሉ ወደቁ። እጅግ ታሪካዊ፣ ተወዳጅ የሰላም ሰው!!!!
የይሳቅ ራቢንን ታሪክ ያለምክንያት አላመጣሁትም። አንዳንዶችን ተቃዋሚዎችን መጨፍለቅ ጀግንነት ይመስለናል። አንዳንዶች ኃይልን የምንመዝነው በያዝነው ብረትና በዘረጋነው የሥለላ አውታር ነው። መነጋገር፣ መወያየት፣ ፍቅርና መግባባት፣ በጦርነትም ሆነ በጉልበት ከሚገኝ ጊዚያዊ መፍትሄ የበለጠ ዘለቄታ ያለው ጥቅም ሊያመጣ እንዲሚችል አናስብም። የሩቁን፣ እኛ ካለፍን በኋላ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን ዘመን ሊፈጠር የሚችለውን፣ ለሁላችንም የሚበጀውን አንመለከትም። ጊዚያዊ ጥቅማችንንና ስልጣናችን ላይ ብቻ በማተኮር ግትር ፖለቲካ እናራምዳለን።
እንደ ኢሳቅ ራቢን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ከወጣትነታቸው ጀምሮ ጦርነትን ያዩ፣ በጦርነት የኖሩ ሰዎች ናቸው። በታሪክ ስለሚኖራቸው ቦታ፣ ስለ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ማሰባ አለባቸው እላለሁኝ።
ጸረ-ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ተብሎ የወጣው አዋጅ፣ በዚህ አዋጅ መሰረትም፣ ለሰላማዊና ለሕጋዊ ትግል ጠንካራ አቋም ያላቸው እነ እስክንደር ነጋን አንዱዋለም አራጌ እንዲሁም ሌሎች በርካታ በሽብር ወንጀል ተከሰው ወደ ወህኒ መውረዳቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቃዋሚዎች ላይ በየወረዳውና በየክልሉ የሚደርሰው ወከባ … ኢሕአዴግን ከሕዝብ ጋር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን እንዲሰፋ የሚያደርጉ፣ ዜጎች የበለጠ ወደ ከረረ አቋም እንዲሄዱ የሚገፋፉ እንጂ፣ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት እንደ አጀንዳ እንደግፈዋለን ያሉትን የመግባባትንና የእርቅን መንፈስ የሚያመጡ አይደለም።
ተናዶ የኃይል እርምጃ መወሰድ፣ በበቀል መነሳሳት፣ ሰውን ማዋረድ፣ ሰውን መስደብ፣ ሰውን መክሰስ በጣም ቀላል ነው። በአይናችን ላይ ትልቅ ምሰሶ እያለ የሌላውን ጉዳፍ ማየት፣ የተገነባውን ማፍረስ፣ አገርን ከድህነት ወደ ድህነት ማውረድ፣ ጠላቶችን ማፍራት፣ ሕዝብን ከሕዝብ መከፋፈል፣ ወንድምን ከወንድም ማጣላት አስቸጋሪ አይደለም።
ይሳቅ ራቢን እንዳደረጉት ጠላት የነበሩትን ወዳጅ ማድረግ፣ የፈረሰውን መገንባት፣ አገርን ከድህነት ማውጣት፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ትችትና ወቀሳን በትህትና ተቀብሎ ስድብና አሉባልታን ደግሞ ንቆ ነገሮችን በትእግስት ማሳለፍ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው።
ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊንና ጓደኞቻቸውን፣ አሁንም የቀናውን መንገድ እንዲይዙና ለእርቅና ለብሄራዊ መግባባት መዘጋጀታቸውን ለማሳየት ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲነሱ ጥሪ እንደወትሮው በደጋሜ አቀርባለሁ። ከነዚህ በነአቶ መለስ መወሰድ አለባቸው ከምላቸው አበይት ተግባራት መካከል የሚከተሉት ሶስቱን በዋናነት እዘረዝራለሁ፡
1. በአገራችን ዋና ከሚባለው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ከሆነው፣ ከመድረክ ጋር፣ ቅንነትና መከባበር ባለመብት መልኩ ቀጥተኛ ውይይት መጀመር፤
2. በሽብርተኝነት ክስ፣ የተከሰሱ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደረጉ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ መሪዎችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፍታት (እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ርዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ እንዲሁም ሌሎች …)
3. ሽብርተኛ ተብለው የተሰየሙ ድርጅቶች በሙሉ (ከአልሻባብና ከአልካይዳ በስተቀር) ከሽብርተኝነት መዝገብ ተሰርዘው እነርሱን ወደ ድርድርና ወደ ሰላም ለማምጣት ስትራቴጂዎችን መንደፍ፣ በዚያም ዙሪያ መንቀስቀስ
በአገራችን እርቅና ሰላም እንዲመጣ ማድረጉ የኢሕአዴግ ብቻ ሃላፊነት አይደለም። ኢሕአዴግን እንቃወማለን በምንልም ወገኖች በኩል መደረግ ያለበት ቁልፍ ጉዳዮች አሉ ብዬ አምናለሁ። ሰላም በአንድ በኩል ብቻ አይደለም። እኛ ”ኢሕአዴጎች ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደሉም” ብለን እንደምንከሳቸው ሁሉ እነርሱም በበኩላቸው ”ስልጣን ብንለቅ አይለቁንም፣ በሰላም መኖር አንችልም” የሚል ፍርሃት ሊኖርባቸው ይችላል ብዬ አምናልሁ። በዚህም ምክንያት እርቅ ለመመስረት ፍላጎቱ ቢኖራቸውም፣ ከፍራቻ የተነሳ፣ በሰላም ስልጣን ከለቀቅን መገደላችን ካልቀረ፣ እስከተቻለን ድረስ ስልጣናችንን ማቆየት አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ይህ እንግዲህ እርቅ እንዳይመጣ ሁላችንም ወደ ባሰ ደረጃ እንድንደርስ የሚያደርገን ነው።
እንግዲህ በዚህ ረገድ የተቃዋሚ ጎራው፣ የሰለጠነ፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ (ኢሕአዴጎችን ጨምሮ) የሚያቀራርብ፣ በበቀልና በጥላቻ ላይ ሳይሆን በፍቅርና በይቅርታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዎች ማራመድ ይጠበቅበታል።
በቅርቡ ቃሌ በተሰኘው የኢትዮጵያውያን መወያያ መድረክ፣ የፓል ቶክ ስሟ አላማዬ የተባለች አንዲት የተከበረች እህት፣ አንዲት ጥያቄ አቀረበችልኝ። ”ወያኔን የኢትዮጵያ ጠላት ነው ብለህ ትቀበላለህ ወይ?” አለችኝ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አትላንታ በተደረገው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ውድድር ወቅት፣ የተናገረቸውን ጠቀስኩላት። ስላሰሯት፣ ለወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ስላስቀመጧት ስለ ኢሕአዴጎች ወ/ት ብርቱካን ስትናገር ”ወንድሜ ስመ ጥፉ፣ ግብረ ጥፉ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምንም ማድረግ አልችልም ወንድሜ ነው” ነበር ያላችው።
አንጋፋው አርቲስትስ ቴዲ አፍሮ እንዲህ ሲል ከሰባት አመታት በፊት ያቀነቀነው ልጥቀስ፡
“ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ፣
ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ
ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ፣
ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳዔ፣
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ
ፍቅር አጥተን እንጅ በረሃብ የተቀጣን፣
አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን
ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ፣
ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ
በተስፋዋ መሬት እንዲፈጸም ቃሉ፣
ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ …”
እንግዲህ በፊታችን የፈረንጆች የ2012 ዓ.ም. የወንድማማችነት መንፈስ የሚወርሰን፣ የገዢው ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎቻቸው የሚቃወሟቸውን ሁሉ እንደ ጠላት ማየቱን አቁመው ዜጎችን በሙሉ እንደ ወንድም የሚያከብሩበት፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭም በተቃዋሚ ጎራ ያለን ሁሉ በይቅርታ መንፈስ ተሞልተን፣ ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳለቸው፣ ኢሕአዴጎችን እንደ ወንድሞቻችን የምናይበት ዘመን ያደርግልን። አገራችን ኢትዮጵያ የምትፈወሰው በፍቅር ብቻ ነውና መድህኔ አለም ፍቅሩን ያብዛልን
መልካም አዲስ ዓመት!
ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



