ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰላይዎችዎን ይሰብስቡልን
ተመስገን ደሳለኝ
ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፡- በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታዬን እንደጻፍኩልዎ ይታወቃል። በተደጋጋሚ ጊዜም ስልጣንዎን ይለቁ ዘንድ ተማፅኝዎታለሁ። በተደጋጋሚ ጊዜም አምባገነናዊ አስተዳደርዎን ነቅፌአለሁ። በተደጋጋሚ ጊዜም የሀገሪቱን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጠቅልለው መያዝዎን፣ ለሀገራችን የማይበጅ ስለመሆኑ ምክንያታዊ ትችት ፅፌአለሁ። በተደጋጋሚ ጊዜም…
ታዲያ ይህን ሁሉ ደፍሬ ስፅፍልዎ በማንም ተመክቼ አይደለም። አስተዳደርዎ ዴሞክራሲያዊ ሆኖም ‹‹የሚነካኝ የለም›› በሚል መንፈስም አይደለም። እንዲህማ ልል አልችልም። ከእኔ በፊት በዚህ መልኩ ይተችዎት የነበሩ ጋዜጠኞችን እንዴት ከጨዋታ ውጪ እንዳደረጓቸው የአደባባይ ሚስጥር ነውና። ከሌላው ኢትዮጵያዊም የተለየ ደፋር ሆኜም አይደለም። እርዳታ እና ብድር ሰጪ ሀገራትንም ተማምኜ አይደለም። ይመኑኝም አይመኑኝም ስራዬን እየሰራሁ ያለሁት የሀገሬን ህገ-መንግስት ተማምኜ እንደሆነና እርስዎም ከእለታት አንድቀን ህገ-መንግስቱን ያከብራሉ በሚል ተስፋ እንደሆነ ደግሜ ደጋግሜ የነፍሴን ያህል በምወዳት (በአድዋ ድል ላይ በተውለበለበችው) ባንዲራ ስም እነግርዎታለሁ።
እናም ዛሬ በምቾት እና በድሎት ላይ በመሆንዎ ብቻ ለእዚህ ያበቃዎትን የእልፍ አእላፋት የገበሬ ልጆች መስዋዕትነት ይረሱታል ብዬ አላስብም። በተለይም የትግራይ ገበሬን። ምንም እንኳ አማራውም፣ ኦሮሞውም፣ ከምባታውም… የተሰዋ ቢሆንም የትግራይ ልጆች መስዋዕትነት በቁጥር ከፍተኛው ነበር። በእርግጥ ይሄ ቁጥር እርስዎ በሚመሩት ድርጅት ስር የተሰባሰቡትን ብቻ የሚመለከት ነው። በተቀረ ከደርግ አስተዳደር ጋር በኢህአፓ፣ በመኢሶን፣ በኦነግ… ስር ተደራጅተው የተሰዉትን እንቁጠር ካልን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመጣጣኝ ሊባል በሚችል መልኩ ሞቷል፡፡ ደምቷል። ቆስሏል። ተገርፏል። ተሰዷል።
የሆነ ሆኖ ከዚህ ሁሉ መስዋዕትነት በኋላ እርስዎ እና ድርጅትዎ ስልጣን ያዙ፣ ይህንንም ተከትሎ ‹‹ከዚህ በኋላ በሀገራችን አፈና እና ጭቆና ለአንዴ እና ለዘላለሙ ተቀበረ። ድህነትም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ጎረቤት ሀገር ፈረጠጠ። የአንድ ሰው እና የአንድ ፓርቲ አገዛዝም አከተመለት….›› ወዘተ ሲሉ አስረግጠው ነገሩን። ለዚህም ዋስትና ይሆን ዘንድ ‹‹ህገ-መንግስት›› የተባለ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ተብሎ ፀደቀ። እናም ይህንን ህገ-መንግስት የሚፃረር ብቻ ሳይሆን ለመፃረር ወይም ላለማመን በሆዱ ያሰበ ሁሉ ሳይቀር ድራሹ እንደሚጠፋ አስጠነቀቁን። በእርግጥም ምክንያትዎ ህገ-መንግስት ይሁን ፖለቲካ ባይታወቅም ድራሻቸውን ያጠፏቸው ሰዎች አሉ።
እኔ እና ባልደረቦቼ ምንም እንኳ እርምጃዎን ባንደግፍም፣ የዚህን ያህል የተቆረቆሩለትን ህገ-መንግስት፣ ሌላው ቢቀር ቢያንስ እርስዎ እንኳ ያከብሩታል ብለን አምነን የጋዜጠኝነትን ሙያ መረጥን። መርጠን ስናበቃም ህግ አክብረን በእውነት ለመስራት ለራሳችን ቃል ገባን፡፡ እነሆ ዛሬም ድረስ እኛ ቃላችንን አላጠፍንም። እርስዎ ግን…
ክቡርነትዎ፡- ወጣትነቴን አሳለፍኩበት፣ ጓደኞቼን አጣሁበት፣ ጀርባዬን በእሳት አለንጋ ተገረፍኩበት… ባሉት መራራ የትጥቅ ትግል የተገኘውን ህገ-መንግስት እየናዱት ነው። ጥፋትዎ ይበልጥ ግልፅ እንዲሆንልዎ የጣሱትን አንቀጽ ልጥቀስልዎ። የአንቀፁ መጠሪያ ቁጥሩ 29 ሲሆን፤ ሙሉ ሀሳቡ እንደሚከተለው ነው፡-
‹‹የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝ እና የመግለጽ መብት፤
1. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፤
2. ማንኛውም ሰው ያለማንም ሰው ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለፅ ነፃነት አለው። ይህን ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሁፍ ወይም በህትመት፣ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም አይነት መረጃ እና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል።
3. የፕሬስ እና የሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የስነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት መብቶች፡- የፕሬስ ነፃነት የሚከተሉትን መብቶች ያጠቃልላል።
ሀ) የቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ) የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት እድልን፣
4. ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሀሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል በተቋምነት የአሰራር ነፃነት እና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎት እንዲኖረው የህግ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡…›› የሚል ነው።
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፡- እነዚህ መብቶቻችን ከዚህ ቀድሞ ከእኔ እና ከባልደረቦቼ ላይ እየተሸራረፈ እንደነበረ እርስዎም ያውቁታል። (ዳሩ አዛዥ ናዛዡ ማን ሆነና!) ሆኖም በተቻለን አቅም ታግሰን እያለፍን ሀገራችንን እና ህዝባችንን ከማገልገል ግዴታችን አልቦዘንም ነበር። ነገር ግን ምን ዋጋ አለው፡፡ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ (11/04/04) ማምሻውን ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት መብቶቻችን ተጠቅመን በሰራነው ስራ ምክንያት በደህንነት ሰራተኞች ጫና፣ ክትትል፣ ተፅዕኖ… የመሳሰሉት ስር ወድቀናል።
ይህን እየፃፍኩልዎ ሳለም ጊዜው ከምሽቱ 4 ሰዓት ቢሆንም የራስ ፀጉራቸውን በሹራብ ኮፍያና ባርኔጣ የሸፈኑ ሰላዮች መኖሪያ ቤቴን በቅርብ እርቀት በአይነ ቁራኛ እየጠበቁ ነው። ጨለማው አልፎ ብርሃን ሲተካም፤ እንዲሁ በመንገዳችን ሁሉ ይከተሉናል። ከቢሮአችንም አካባቢ ቀድመው ደርሰው በተለያየ መንገድ ያስፈራሩናል።
ክቡርነቶ፡- እመኑኝ ምንም እንኳ ቤቴ አንድ ክፍል ብትሆንም ክትትሉ ከተጀመረበት እለት ጀምሮ ሁላችንም የጋዜጣው አዘጋጆች በዚህች ቤት በመሆን የሚመጣውን ነገር በሙሉ በፀጋ ለመቀበል፤ በጋራ ተጨናንቀን እየኖርንባት ነው። እኔን ካላመኑ ይህን ኢ-ህገመንግስታዊ ድርጊት ይፈፅሙብን ዘንድ የላኳቸውን ሰላዮችዎን ሊጠይቁ ይችላሉ። ነግረዎትም ሊሆን ይችላል።
በነገራችን ላይ ያለንበት ሁኔታ በእጅጉ አስፈሪ ቢሆንም በአደባባይ ህገ-መንግስቱ ላይ የተጠቀሰው አንቀጽ 29 መሻሩ እስካልታወጀ ድረስ ከስራችንም ሆነ ከቆምንበት አላማ አንድ ኢንች እንደማናፈገፍግ እገልፅልዎታለሁ። ወደየትም አንሰደድምም። እውነትን ከመፃፍም አንቦዝንም፡፡ ምክንያቱም ህግ ይከበር ዘንድ ዋነኛው ነገር ወንጀል አለመስራት ብቻ ሳይሆን፤ ህግ አውጪው ራሱ ያወጣውን ህግ ያከብር ዘንድ ግድ በመሆኑም ነው።
አቶ መለስ እስቲ አስቡት! በየደረሱበት እግር እግርዎን እየተከታተሉ የገቡበት የሚገቡ፣ አሁን የሉም ሲሉ ከፊትዎ ቀድመው የሚገኙ፣ ምሳ ሲበሉ የሚያፈጡብዎ… በአጠቃላይ መውጫ መግቢያዋን በመኪና እና በእግር አጥረው በቁጣ የሚጉረጠረጡ አይኖቻቸውን እንደ መቀናጢ ከወዲህ ወዲያ እያራወጡብዎ፣ እንዴት ብለው ስራዎን መስራት ይችላሉ? እንኳን ስራዎን ሊሰሩ ቀርቶ በቅጡም መተንፈስ አይችሉም። እነዚህ የስለላ ሰራተኞችዎ የባልደረባዬን ስልክ ነጥቀው፣ ሲም ካርዱን ከውስጡ አውጥተው፣ ባዶ ቀፎ መልሰው፣ ክብረ-ነክ ስድብ ሰድበው፣ ከዛቱበት ደቂቃ እና ሰዓት ጀምሮ በጣም ዘመናዊ በሆኑ መኪናዎች ሳይቀር እየተከታተሉ የማስጨነቅን ስራ ስራዬ ብለው ይዘውታል።
ክቡርነትዎ፡- ይሄ ሁኔታ ምን እንዳስታወሰኝ ልንገርዎማ። …ከሁለት ወር በፊት (ቀዳማይ እመቤት አዜብ መስፍንን የሚመለከት ፅሁፍ በፃፈኩ ማግስት) ከምሽቱ ስድስት ሰአት አካባቢ በብቸኝነት በምኖርበት፤ ያውም በመንገድ ዳር፤ ያውም አዋሳኝ አጥሩ የፀጥታው መስሪያ ቤት በሆነው ቤቴ ውስጥ ሆኜ፤ በፀጥታ ስራዬን እየሰራው ሳለ ፊታቸውን የሸፈኑ ሁለት ወጣቶች፣ የቤቱን መስታወት በድንጋይ አረገፉት። በሁኔታው ተደናግጬ ከፍቼ ብወጣም እነዚህ ወጣቶች ‹‹አይነኬ›› ናቸውና፤ በተዝናና እና ‹‹ናና ሞክረን›› በሚል ሁኔታ እየተጎማለሉ ሄዱ፡፡ በእርግጥ መልእክቱ ገብቶኛል። ለዚህም ነው በማግስቱ ቤቱን ያከራዩኝ ግለሰብ ‹‹ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እናመልክት?›› ሲሉኝ የተሰበረውን መስታወት እንደማሰራላቸው ገልጬ፣ ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ ያልተስማማሁት።
እንግዲህ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ እየሰራን ሳለ ነው በሰላዮች ተወረን ሳምንቱን ለማሳለፍ የተገደድነው። መቼም ‹‹ይሄን አላውቅም›› እንደማይሉ እርግጠኛ ነኝ። በሚገባ ያውቃሉና። እንደው በቅንነት የእርስዎ ‹‹ጥቅሻ›› የለበትም ብለን እንዳናስብ እንኳ፣ ድርጊቱ ፍትህ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ ድህረ ገፆች ከተዘገበ በኋላም ያው ሁኔታ ቀጥሏል። እናም በህገ መንግስቱ ላይ ለፕሬሱ የህግ ጥበቃ ይደርግለታል የሚለውን አንቀጽ እንዴት ያዩታል? መቼም ከዚህ በኋላ ስለእዚህ አንቀፅ አስፈላጊነት የማውራቱ ሞራል የሚኖሮት አይመስለኝም። ‹‹ፅድቁ ቀርቶብኝ…›› አለ ሰውየው፤ እውነቱን ነው። ጥበቃው ይቅርና ማዋከቡ እና ማስፈራራቱን ቢያስታግሱልን መልካም ነው።
እርስዎም ቢሆኑ ሁለት ወዶ ስለማይሆንልዎ አንዱን መምረጥ አለብዎ፡፡ ወይ ስልጣንዎን፤ አሊያም ስልጣን ጠቅልለው በመያዝ በሚነሱ ትችቶችን መቀበል። ምክንያቱም ትችት ካልፈለጉ፣ ያለዎት ብቸኛ አማራጭ ለእውነት የሚሰሩ ጋዜጠኞችን እንደእባብ አናት፣ አናታቸውን ማለት ሳይሆን፤ ስልጣንዎን መልቀቅ ብቻ ነውና። በተረፈ ሀገር እመራለሁ እስካሉ ድረስ በሚሰሩት ስህተት እና በተንሸዋረረ ፖሊስዎ የሚሰነዘርብዎን ምክንያታዊ ትችት በፀጋ ሊቀበሉ ግድ ይልዎታል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- እርስዎም ሆኑ የደህንነት ሹምዎ መስሪያ ቤቱን ዜጎችን ለማስፈራራት እና ለማዋከብ የመጠቀም መብት እንደሌላችው ልታውቁት ይገባል። በእንዲህ አይነት ሁኔታም ማፈኑ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። ዛሬ አንድ ‹‹ፍትህ››ን ቢያፍኑ ነገ፤ ብዙ ፍትሆች እኛ እየጠየቅን ያለውን ጥያቄ መጠየቃቸው፤ እኛ እየሰራን ያለውን መስራታቸው አይቀሬ ነው። በተረፈ በቅርቡ ወደ አማርኛ የተተረጎመውን ‹‹የሀበሻ ጀብዱ›› መጽሐፍ ካነበቡት መልካም፤ ካላነበቡትም እንዲያነቡት እጋብዝዎታለሁ። የፋሽስት ጣሊያን ወታደሮች አሮጌ ምንሽር፣ ዱላና በባዶ እጅ ከፊታቸው የተሰለፈውን ኢትዮጵያዊ አርበኛ በታንክ፣ በመትረየስ እና በአውሮፕላን በአንድ ጊዜ ሺውን ሲፈጁት፤ ሌሎች ሺዎች በሟቾቹ ሬሳ ላይ ተረማምደው ‹‹በጦር በጎራዴ››፣ አንዳንዴም በባዶ እጅ ታንክ መማረካቸውን ይተርካልና።
አዩ! አቶ መለስ፡- እኛ ኢትዮጵያውያኖች እንዲህ ነን፤ ሲይዙን የምናይል፣ ሲገፋን ይበልጥ የምንጋፋ፣ ሲያጠፉን የምንበዛ፣ ሲያፍኑን ደፋርና ጢስ… ብቻ ከእኔ ይበልጥ በተግባርም እርስዎ ስለሚያውቁት ለማስታወስ ያህል ካልሆነ መዘርዘሩ ዋጋ የለውም።
እናም አሁን እየተከተሉት ያለው የአፈና መንገድ የትም እያደርስዎትም። ምናልባትም በእኛ ላይ ከዚህም የከፋ ነገር ቢፈፅሙ እንኳ፣ ሚሊዮኖች ጥያቄያችንን መጠየቃቸው፣ ጩኸታችንን መጮኻቸው አይቀሬ ነው። ዳሩ ከነተረቱስ፡-‹‹ምንም የማያውቀውን በሬ ነካክተው ነካክተው አደረጉት አውሬ›› አይደል የሚባለው። በተረፈ ሚሊዮን ሰላይ፣ ሚሊዮን ፖሊስ፣ሚሊዮን ወታደር፣ ሚሊዮን ካድሬ፤ አንድ ሙባረክን እና ጫጩቶቹን እንኳ ከምንም አላዳነም።
እናም አቶ መለስ እውነቴን ነው የምለው፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሬ አንዳች የማምነውም ሆነ የምተማመንበት ተቋም የለም፡፡ በተከበረው የፍትህ ወንበር የሚቀመጡት ካድሬዎች በሆኑበት፣ ህግ አስፈፃሚዎች የአንድ ፓርቲ ሰዎች ከሆኑ፣ ህገ አስከባሪዎቹ ከገለልተኝንት ይልቅ ወገናዊነትን ከመረጡ… ከቶስ በማን መተማመን ይቻላል?
ይሄ ሁሉ አፈናና ጫና እየተደረገ ያለው ምን አልባት በፍትህ ባልደረቦች ላይ ብቻ ነው ብለው እንዳይሳሳቱ። ሀገሩን የሚወድ እና ስለእውነት የሚቆረቆርን በሙሉ የሚነካ እንደሆነ ግልፅ ነው። ምክንያቱም ይሄ ወሬ በሚዲያ ይፋ ከሆነ ጀምሮ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከወጪ፤ የኢህአዴግ ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች ይህንን የውንብድና ተግባር አውግዘው ከጎናችን እንደሚቆሙ በተለያየ መንገድ መግለፃቸው ምስክር ነውና። ይሄ የሚያሳየውም ህዝብ አቅም በማጣቱ ዝም ማለቱን እንጂ ድርጊቱ ኢ-ፍትሀዊ፣ ኢ-መንግስታዊ መሆኑን ሳይረዳ ቀርቶ አለመሆኑን ነው።
የሆነ ሆኖ ክቡር ጠ/ሚንስትር፡- እነዚህ ሰላዮቾን ከለያችን ላይ ያንሱልን። ከመኖሪያ ቤቴም ሆነ ከቢሯችን ይሰብስቡልን። ይሄ ሁኔታ ምናአልባትም ዛሬ እኛን የሚጎዳ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ውሎ አድሮ ዋነኛ ተጎጂ እርስዎ እና እንዲህ የሚንሰፈሰፉለት ስልጣንዎ ለመሆኑ ጥርጣሬ አይግባዎ።
ምንጭ፦ ፍትሕ ጋዜጣ



