በኢትዮጵያ ከ1966 ዓ.ም. ወዲህ በርካታ ድርጅቶች ተፈጥረው የፖለቲካ ትግል ሲያካሄዱ እንደነበረ ይታወቃል። ከእነዚህም አንዱ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ /ህወሓት/ ነው። ይህ ድርጅት ከነገ በስቲያ የተመሰረተበትን ሰላሳ ሰባተኛ አመት ያከብራል።


ህወሓት የደርግ ስርዓትን ለመጣል በተደረገው ትግል የግንባር ቀደሙን ሚና መጫወቱ የሚካድ አይደለም። እናም የደርግ ስርዓት ወድቆ የኢህአዴግ መንግስት ቢተካም አሁንም በኢህአዴግ ውስጥ የግንባር ቀደሙን ሚና እየተጫወተ ያለው ህወሓት መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው።


ከ1983ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ለተከሰቱ በጎም ሆነ መጥፎ ሁነቶችም በግንባር ቀደምነት ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው ህወሓት ነው። ፍትህ በአጠቃላይ ሲገመገም በሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ላይ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ህወሓት ያበረከተው ጥቂት በጎ ነገር ቢኖርም እንደ ሀገር ሲታይ ግን ያጠፋው ይበዛል ብላ ታምናለች።


በፍትህ እምነት ሀገሪቱ ወደብ አልባ ልትሆን የቻለችው በህወሓት አመራር ፍላጐት ወይም ድክመት ነው። በቋንቋ ላይ ከተመሰረተው ፌደራሊዝምም ምንጩ ህወሓት ነው። ምክንያቱም ህወሓት የብሔር ጭቆና አለ ብሎ ብረት፣ አንስቶ በሚታገልበት ዘመን፤ ሌላኛው አጋር ድርጅት በወቅቱ ኢህዴን ይባል የነበረው፣ ዛሬ ብአዴን የሚል የአንድ ብሄር መጠሪያ የያዘው የብሔር ድርጅት አልነበረም። ነፍጥ ያነሳውም አምባነንነትን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እቀይራለሁ ብሎ እንጂ ቀዳሚው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄ የብሔር ጭቆና ነው በሚል እምነት አልነበረም።


በደርግ ውድቀት ዋዜማ የተቋቋመው ኦህዴድ በትጥቅ ትግሉ ላይ የነበረው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል ስላልነበረ፣ ደርግ ከወደቀ በኋላም በግንባሩ ውስጥ የተሰጠው ቦታ በትክክል ድርጅቱ ከወከለው ብሔር ህዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን እንዳይሆን አድርጐታል። ደኢህዴን ጭራሽ በትግሉ ላይ ያልነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ የተቋቋመውም በ1985ዓ.ም እንደሆነ አይዘነጋም። እናም በዚህ የተነሳ አራቱ ድርጅቶች በመሰረቱት ኢህአዴግ ውስጥ የህወሓት ሚና እና ተፅዕኖ ፍፁም የበዛ ሊሆን ችሎአል። ለዚህም ነው ፍትህ የህወሓት ስህተቶች የመንግስት ስህተቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል የምትለው።


የኢትዮጵያ ታሪክ የ3000ሺ አመት ሳይሆን የ100 ነው የሚለው የታሪክ ብረዛም ምንጭ ህወሓት ነው። ህወሓት በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳሳየው ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ተቃርኖ ውስጥ በመግባት ‹‹ነፃ ላወጣው›› ተመሰረትኩለት ከሚለው ህዝብ አቋም እና ፍላጐት በእጅጉ ያፈነገጠ እና የራቀ የታሪክ አመለካከት አንፀባርቋል፡፡ ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ በሩ የዘጋ ወይም እጅግ ምስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ለታሪክ ተመራማሪዎችም ሆነ ለጋዜጠኞች ዝግ የሆነበት ሁኔታ ይስተዋላል።


ከላይ እንዳልነው ሀገራዊ ተፅእኖው እጅግ የበዛ የሆነውን ፓርቲ ስለውስጣዊ አወቃቀሩ ተመራማሪዎች ማጥናታቸው ፋይዳው የላቀ ነውና ፓርቲው ይህንን ጉዳይም እንዲያስብበት ፍትህ ታሳስባለች።


በቅርቡ የቀድሞ የህወሓት ሊቀመንበር አቦይ ስብሓት ነጋ በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያ በሚተላለፈው የትግርኛ ፕሮግራም ላይ ቀርበው የአክሱም ታሪክ የኢትዮጵያ አይደለም፤ የትግራይም አይደለም፤ ከትግራይም የአጋሜ አውራጃን እና ተንቤንን አይመለከትም በሚል ያቀረቡት ትንተና ህወሓት ከታሪክ ጋር ያለውን ታሪካዊ ፀብ ሊያመላክት የሚችል በመሆኑ በዚህ በምስረታ በአሉ ላይ ይህ አቋም የግለሰቡ ወይም የፓርቲው ለመሆኑ ይፋ ይሆን ዘንድ ፍትህ ትጠይቃለች።


ከዚህ ባሻገርም ህወሓት በትግሉ ዘመን ያፈራሁት ነው በሚል በኤፈርት ስም ያቋቋመው የንግድ ድርጅት ገቢ እና ወጪው፣ እስከ ዛሬ ድረስ ከንግዱ ያተረፈው፣ እንዲሁም በሀገሪቱ የንግድ ስርዓት ላይ እያደረሰ ያለው በጎም ይሁን መጥፎ ገፅታ ይፋ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የኤፈርት ገቢ የት እንደገባ፣ ከኤፈርት በሚገኘው ትርፍ ምን እንደተሰራ፣ ማን እንደተጠቀመም የመጠየቂያው ጊዜ አሁን እንደሆነ ፍትህ ታስገነዝባለች።


ከላይ እንደተገለፀው በትግሉ ዘመን ዋነኛው ባለድርሻ ህወሓት ነው። በዚህም የተነሳ በርካታ አካል ጉዳተኛ ታጋዮች እና ልጆቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው የተሰዉባቸው ዜጎች ከኤፈርት ገቢ መጠቀም ያለመጠቀማቸውም በግልፅ ሊነገር ይገባል እንላለን።


ሌላው ጉዳይ ተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚነገረው ህወሓትን ለመመስረት ወደ ደደቢት በረሃ የገቡት አስራ አንድ ሰዎች እንደሆኑ ነው። በፍትህ የምርመራ ዘገባ መሰረትም ከአስራ አንዱ አንዱ የአማራ ተወላጅ ሲሆን አብተው ታከለ ይባላል። ይህ ሰው ፎቶው በሰማዕታት ሀውልት ላይ አለመቀመጡ እና በህወሓት ታሪክ ውስጥም የሚገባውን ስፍራ አለማግኘቱ በፍትህ እምነት ተገቢ አይደለም፤ እናም ቢያንስ ህወሓት በሰላሳ ሰባተኛ በዓሉ ላይ ለታጋዩ የሚገባውን ክብር ይሰጥ ዘንድ ፍትህ አጥብቃ ትጠይቃለች።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ