የኪነ-ጥበብና የከያኒ ፋይዳ በሃገር ጉዳይ (ከብርሃኑ ጃዝ)
ምንም እንኳን የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ የኪነጥበብ ሰዉ ቢሆንም በዚህ አጭር ጽሁፍ ሊያነሳ የፈለገዉ አጠቃላይ ስለ ኪነ-ጥበብና ስለከያኒዉ ሲሆን የኪነጥበብ ሰዎች በሃገራቸዉ ጉዳይ ላይ ስላላቸዉ ሚና በተለይም ገርና ህዝብ በከባድ ፈተናላይ እያለች ገሬ ወገኔ ብለዉ ስለሚያደርጉት ስላደረጉትና ማድረግ ስለሚገባቸዉ ከሞራልም/ከሰነ-ምግባርም/ ሆነ ከሙያ አኳያ አጭር ዳሰሳ ማድረግ ነዉ።
የኪነጥበብ ሰዎች ባሉበት ዘመናና ቦታ ያዩትን የሰሙትን የሚያልሙትን ከህብረተሰቡ ወስደዉ በሚታይ ፤በሚሰማ፤ በሚዳሰስ መልኩ በኪነጥበባዊ ቋንቋ ዉበትና ለዛ ሰጥተዉ መልሰዉ ለህብረተሰቡ ያቀርቡታል። ዛሬዛሬ በዓለም ላይ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ የኪነ-ጥበብ ሰዎች የህዝህብን ተቃዉሞና ብሶት አለማቀፋዊ በሆነ ቋንቋ ማለትም በስነ-ጽሁፍ፤ በስነ-ስእል (በፖስተር) ፤ በሙዚቃ ወዘተ መልኩ ያቀርቡታል፡ለዚህ ምስክሮቻችችን በመገናኛ ብዙሃን የምናያቸዉና የምንሰማቸዉ ይሆናሉ ።
ለምሳሌ:- የአየርንብረት መበከል፤ ስለግሎባላይዜሽን፤ ሰባዊ መብት፤ የሴቶች መብት እና እኩልነት የመሳሰሉትን ጉዳዮችን በማንሳት ፖለቲካዊ ተጽእኖ የፖለቲካ ሰዎች ላይ እያሳደሩ ነዉ። በኢትዮጲያ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ፍቅረ እንዳይኖር በሚደረግበት ገር ተቀምጠዉ ስለፍቅር/የጾታ/ ብቻ መዝፈን፣ የደከመና የሚበላዉን ያጣ በሞላበት ገር የተመቸዉና ገንዘብ ያለዉን ምስል መሳል፣ መንገድ ተዳዳሪና የፈራረሱ ቤቶች በሞሉባት ገር ፊልም ሰሪዎቻችን የሚያሳዩን ግን ከእዉነቱ የራቀ አስር ከመቶ ያልሞሉ ሰዎች የሚኖሩትን ኑሮ ቪላና ሊሙዚዬን መኪና ነዉ። ይህንን ስንመለከት የኪነ-ጥበብ ሰዎቻችን ለኢህአዲግ ፕሮፖጋንዳ እንደመሳሪያነት እያገለገሉ ነዉ ? ወይንስ ለጥበብ ፍቅር እየሰሩ ነዉ የሚሉን ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን ።
በአገራችን ኢትዮጲያ ዉስጥ ያሉም ሆነ በዉጪ የሚኖሩ የኪነጥበብ ሰዎቻችን የህዝብን ችግር ና ብሶት የሚያዩና የሚረዱ የራሳቸዉን አስተዋጽዎ የሚያበረክቱ ምንያህሉ ናቸዉ ብለን ስንጠይቅ ቁጥራቸወ እጅግ አናሳ ነዉ ። የኪነጥበብ ሰዎቻችንን ምን እያደረጋቹህ ነዉ ? የትናችሁ ? የጥበብ ሰዉ እኮ አነጋገር ለማሳመር ጸጉር ለማንጨባረር ህዝብ በበዛበት ብቻ ለመገኘት አይደለም፤ ጥበበኛ ለመሆን ቃል ሲገባ ፤ ያየሁትን የሰማሁትን በጥበቤ ህዝብን ላገለግል የማዉቀዉን ላካፍል የተደበቀዉን ልገልጽ ብሎ ቃሉን ሰጥቶ ነወ ጥበብን የሚቀበለዉ፤ የተቀበለዉን ሲጠቀምበት ክብርና ዝና ህዝብ ይለግሰዋል በህይወትና ህልፈቱም ዝንተአለም ስሙ ሲታወስ ይኖራል ሌላዉ ደግሞ አይንህ ላፈር ሲባል እንደተሸማቀቀና አሞሌ እንዳየች ላም ስምና ዝና ለማግኘት ሲባዝን ሆዱን ሲያስብ እንዲሁ ቋቱን ሳይሞላ ግባእተ መሬቱ ይፈጸማል ።
የኪነጥበብ ሰዎቻችን እንዴት ናችሁ ወዴት ናቹህ እጃቹህ ከምን ስትሉአቸዉ ፖቲካና ኮረንቲ በሩቁ ቴዲን ያየ ከኢህአዲግ ጋር አይቀልድም የልጆች አባት ነኝ የሚሉ መልሶችን ልትሰሙም ትችላላቸህ አንዳነዶቹ እንደዉም የሃገር ጉዳይ የጋዤጠኞች ስራ ብቻ አድርገዉ የሚገምቱ አይጠፉም:: አንዳንድ የጥበብ ሰዎቻችን ትላንት ከደርግ ጋር ሆነዉ የደርግን ዲሞክራሲያዉነት ሲነግሩን የነበሩ ስራዎቻቸዉን ለደረግ ቅስቀሳ መጠቀየሚያ ሲያገለግል እንዳልነበረ ዛሬ ደግሞ የተገላቢጦሽ ደርግን በመኮነን በደርግ ጊዜ ተቃዋሚነታቸዉን በሰምና በወርቅ በአብስታራክት የአሳሳል ዘዬ የህዝብን ብሶት ስገልጽ በማለት እራሳቸዉን አታለዉ ህብረተሰቡን ያታለሉ የሚመስላቸዉ ለነገዉ ደግሞ ራሳቸዉን ለሞመረድ የሚዘጋጁትን ስንመለከት ማዘናችን አይቀሬ ነዉ። ከምናደንቃቸዉ አንዳንዶቹ እናንሳ ለጫዋታችን ማጣፈጫነት እናድርጋቸዉ።
በጃንሆይ ጊዜ አንዱ የጃንሆይ አፍቃሪ ጃንሆይን አክሊል ሲየደርግላቸዉ ስሎ ነበር ታዲያ ደርግ መጣና አንተ የአድሃሪ ደጋፊ ነህ እንደዚህ አይነት ስእል የምትሰራዉ አክሊል የምትደፋላቸዉ ሲለዉ አይ አኪሊሉን እያነሳሁባቸዉ ወይም እየነጠቅኳቸዉ ነዉ አለ ይባላል:: አሁንም ከሰአሊዎቹ ዙርያ ፈቀቅ ሳልል የማስታዉሰዉን ላዉጋቹህ ፡ በደርግ ጊዜ ወሎ ላይ ማደጉን ወለየነቱን ሲያጎላ የነበረ ሰአሊ ኢህአዲግ እንደገባ ወለየነቱን ዘንጋ አደረገና ትግሬነቱን ጎላ ማድረግ መረ፤ ዘረኛዉ ኢህአዲግም ለአንድ ሰሞን ከበሮ ሰጥቶት እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። አንዳንዶቹ ደግሞ አቋማቸዉ ከምን እንደሆነ እንኳን አያቁትም የጥበብ አላማና ምግባራን ለማወቅም አልታደሉም፤ ሳር በተጎዘጎዘበት ሁሉ እጅ በማስታጠብ ላይ እናገኛቸዋለን።
ስልጣን ተቀብለዉ ገርና ወገንን ለሚያጠፋዉ የኢህአዲግ የጥፋት ዘመቻ አስፈጻሚ አካላት የሆኑ ቤት ይቁጠራቸዉ። አዉቀዉ እንዳላወቁ በመሆን ከማጋር ትጋፋለህ በሚል የሰጧቸዉን ተቀብለዉ በሃገር በወገን መርዝ የሚነሰንሱት አንሶ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ሰዉ በመግደል ህብረተሰብን በመናቅ ያለማዳመጥ በትእቢትና በማን አለብኝነት በክፋት የጨከነ እና የሰለጠነ አይምሮ በማድነቅና ወደኪነጥበብ ጎራ እንዲቀላቀል በመጋበዝና በማደፋፈር የነገዉን ተስፋችንን የሚያጨልሙ ብቅ እያሉ ነዉ :: የኪነ-ጥበብ ሰዉ ዉሸታም ለሆዱ የተገዛ ፈሪ ታዠዥ ገሩን ባህሉን ማንነቱን ና ቋንቋዉን የማያውቅ አደርጎ ለማፍራት ለሚታገለዉ የኢህአዲግ ሰራዊት መንገድ ከፋች እንዳይሆኑ።
የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለሌሎች አርያዉች ናቸዉና የሚሄዱበትን የሚያደንቁትን የሚናገሩትን ኢትዮጰያዊነት ጨዋነትና ምግባር የተላበሰ መሆኑ አግባብ ነዉ አለበለዚያ “ መጥፎ አድናቂና መጥፎ የኪነጥበብ ሰዉ ራሱ ተሳስቶ ህብረተሰቡን ያሳስታል እና” መተንቀቅ ይበጃል እላለሁ ::
በረከት መጽሃፍ ጻፈ ያዉም በሚጠላዉ ህዝብና ቋንቛ በአማርኛ ። ለምን በሚወደዉና በሚኮራበት እንግሊዘኟ አልጻፈም ? ምክንያቱም እዚያዉ በሚጠላዉ ህዝብ ላይ መርዙን ለመርጨት አመቺዉ መንገድ እሱ ብቻ ስለሆነ ነዉ ። ዛሬ ዛሬ አቶ በረከትና ፓርትያቸዉ ያላቸዉን የህዝብ ንቀትና ክፋት አጥፊመሆናቸዉን ሁሉ ፊት ለፊት የሚናገሩበትን አጋጣም እየተገኘ ነዉ ለዚህ ምሳሌ በመጻህፋቸዉ ምረቃ በሸራተን አዲስ የተናገሩት” ኢህአዲግ የታህድሶ እንቅስቃሴ ባካሄደባቸዉ 10 አመታት የቀድመዋ ኢትዮጲያ እተናደች አዲሷ ኢትዮጴአ እተገነባች መሆኑን ተናገሮ የነበረዉ።” ባህል ታረክ የራስመግለጫ ማንነት እና ቋንቋን በረከትና ፓርቲዉ እያፈረሱና እየናዱት ነዉ ። በማያቁት ሁሉ የኢህአዲግ አባላት እናዉቃለን በሚል እየገቡ ራሳቸዉን እንደ ታሪክ ጸሃፍትና የኪነ-ጥበብ ሰው በመቁጠር እድሉ ስላላቸዉ ብቻ ዉሸትን ጽፈዉ አሳትመዉ ሲያሰራጩ ለህሊናቸዉ ለትዉልድ ምንም አይነት ገራዊ ሃላፊነት አይሰማቸዉም። በርግጥ ኪነ-ጥበብ እንዳስፈላጊነቱ ቅስቀሳን ታካሂዳለች ሆኖም የኪነ-ጥበብ ሰዎች ከሌላዉ የሚለዩት ለስሜታቸዉ አለመገዛታቸዉ ላመኑበት ሃይልና ጉልበታቸዉን መስጠታቸዉ (ማዋላቸው) ብቻ ሳይሆን ወገንተኟ ሳይሆኑ ለሁኔታወች የማያደሉ መሆናቸዉ ነዉ፤ ከዚህ በተቃራኒ ኢትዮጲያ ወስጥ የኪነ-ጥበብ የታሪከ ጥላሸት ቀቢዎች ዉሸት ፋብራኪዎች እየተስፋፉ ነዉ።
ኢትዮጵያ አድርባይ የሆኑ የኪነጥበብ ሰዎች እንዳፈራች ሁሉ ቆራጥ ከህብረተሰቡ ጋር የቆሙ የኪነጥበብ ግኖችን አፍርታለች ለምሳሌ ጸጋዬ ገብረመድህን ፤ በአሉ ግርማ፤ አቤጉበኛ፤ ገሞራዉ፤ ሰአሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ፤ ሻምበል በላይነህ ፤ ጂጂ (እጅጋየሁ ሽባባዉ) ና ታማኝ በየነን አፍርታለች:: ከዚህ በተቃራኒ የዘቀጡና የወረዱ ከህብረተሰቡ ወይም ከኪነ-ጥበብ ጎራ ሳይሆኑ ሆድ አደሮችን እናገኛለን:: ለምሳሌ እንዉሰድና ሰለሞን ተካልኝ፣ ንዋይ ደበበና ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ የመሳሰሉ ይገኛሉ።
አነዳንዶቹ ደግሞ ከኢህአዲግ ባለስልጣናት ጋር ጭራ መቁላት ኢህአዲግን ማስፈራርያ ጋሻ ና መከታ አድርጎ መጠቀም በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችን የሚጠበቅ አልነበረም ; አንዳንዶቹማ እጅ መንሻ ሎቲ ወይንም እስኪሪቢቶ ማቅረብ ምረዋል:: በህብረተሰቡ ግብር ወይም ታክስ ገንዘብ የተማሩት ህብረተሰቡን ይጠቅማሉ ሲባል እንጂ እነሱ ለወንበዴ እጅ መንሻ የሚሰጡ ይሆናሉ ተብሎ አልነበረም :: ጥበብ ዝምብላ የምትገኝ አልነበረችም አይደለችምም ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎች ዝም ብለዉ እንደ ጓሮ ጎመን አልተቀጠፉም ለነገሩ የጓሮ ጎመን ዛሬ የት አለና።
ፒካሶን ትልቅ ያደረገዉ ቁመቱ፣ ዉፍረቱ ከፖለቲከኛ ሰዎች ጋር መታየቱ ወይም ጭራ መቁላቱ አልነበረም ከዚህ ይልቅ ስራዉ ነዉ ትልቅ ያደረገዉ:: ፒካሶ ቢሞትም ስሙ በየእለቱ በተለያዩ ሰዎች ይነሳል የቻሉ ስራዉን ይሰበስባሉ ያልቻሉ ፖስት ካርዶቹን ብሎም በየሙዚየሙ ስራዉን ይመለከታሉ ከነኚህ ስራዎቹ መካከል አለም የሚዉቀዉ ማድሪድ በሚገኘዉ ሬና ሶፊያ ሙዚየም ዉስጥ የሚገኘዉ ገርኒካ ነዉ :: ገርኒካ ከዚህ ሙዚየም በተጨማሪ በምንጣፍ ስረ በተባበሩት መንግስታት ህንጻ ዉስጥ በኒዎርክ ከተማ ይገኛል:: ይህ ስእል የሚያሳየዉ የ ርመን ጦር በንጸሃን ዜጎች ላይ ያደረገዉን ግፍና ስቃይ ነዉ:: በወቅቱ ፒካሶን አንድ የ ርመን ወታደር ገርኒካ ስእል ላይ አትኩሮ እየተምለከተ ይህ የአንተስራ ነዉን ብሎ ቢጠይቀዉ፤ ኮምጨጭባለና ኮስተር ባለ ሁኔታ ይህ የኔ ስራ ሳይሆን ያንተስራ ነዉ ብሎ መልሶለታ። ዛሬ የሰላም ምልክት የምናደርጋት ነጭ እርግብ ከምናዉቀዉ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ዉጭ የፒካሶ ሰራ ዉጤት ነች። ይህም የሆነዉ ፒካሶ የስእል ስቲዲዮ ሆኖ ወደዉጭ ሲመለከት አንድ የ ርመን ወታደር ሰላመዊ የሆንችን እርግብን በጥይት ተኩሶ ይመታታል ሰላማዊዋ እርግብ ላባ በአየር ላይ ይበተናል ይህንን የተመለከተዉ ፒካሶ የየዋህዋን እርግብ በስእሉ ወይንም በሸራው ላይ የናዚን ጭካኔ በሸራዉ ላይ ለህዝብ አቀረበ።
ዛሬ በኢትዮጲያ ምድር የሰዉ ልጅ በዘሩ በጥይት ሲቆላ ወደ እስርቤት ሲታጎር በርሃብ ሲታመስ አይቶ እንዳላየ የሆነ የኪነ-ጥብበ ባለሙያ ቤት ይቁጠረዉ።ሌሎች ደግሞ ኢህአዲግ አይደለሁም ብለዉ ስልጣን እስከሰጡኝድረስ መስራት አለበኝ በሚል የኢህአዲግን የጥፋት ዘመቻ የሚተገብሩ አስፈጻሚ አካላት ሆነዋል።
ጥበብ በርግጥ ግላዊ ነች ነጻነትን ዲሞክራሲን ስትፈልግ አድርባይነትን ወገንተኝነትን ዘረኝነትን ትኮንናለች፤ ጥበብ የሰለጠነ አይምሮ ማስተዋል ማድመጥ በአጠቃላይ የኪነጥበብ ሰዉ አምስቱ የስሜት ህዋሳት ከሌላዉ በተሻለ ሁኔታ መጠቀም ይጠበቅበታል ፡በተጨማሪም ስድስተኛ ህዋስ ሲሜት አዳብሮ ሚዛናዊ የሆነ ቅን የተመረኮዘ ስራ እንዲሰራ ያደርገዋል ወይም ይገፋፍዋል ፡እንጂ ሰዉ በመግደል ህብረተሰቡን በመናቅ ባለማዳመጥ በትእቢትና በማን አለብኝነት በክፋት የጨከነ የሰለጠነ አይምሮ እንዴት እንደሚደነቅና ወደኪነ-ጥበብ ጎራ እንዲገባ አያበረታታም፡፡ ይህ ከሆነ ግን ያላዋቂ ሳሚ -- ይለቀልቃል እንደሚባልው ሁሉ ። የሚደነከውን እና የሚበረታታውን መለየት መቻአል አልብን፣አንባቢም የሚገዛውን እና ገዝቶ የሚየበረታታውን ለይቶ ማወቅ አልበት እላለሁ። ይህ ጽሁፍ ጸ ፊውንም ይመለከታል| ለአጻጻፍ እንዲያመች በሚል ነው የኪነ-ጥበብ ሰዎች የሚለውን የተጠቀመው። በሚቀጥለው ጽሁፍ ለመገናኘት የእግዚአብሔር ፍቃድ ይታከልበት።
berhanujazz@ hotmail.com



