ግርማ ካሣ

መግቢያ

ዲሞክራሲ «ዴሞክራቶስ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው። «ዴሞስ» በግሪክ ቋንቋ ሕዝብ ማለት ሲሆን፣ «ክራቶስ» ደግሞ ኃይል ወይም ስልጣን ማለት ነው። «ዴሞክራቶስ» የሕዝብ ኃይል ወይንም የሕዝብ ስልጣን እንደ ማለት ነው።

 

 

ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ ዴሞክራሲን ከሞናርኪ (የአንድ ንጉስ ፍቃድ ሕግ የሆነበት) እና ከኦሊጋርኪ (የጥቂት ሃብታሞች ፍቃድ ሕግ የሆነበት) ለይቶ ያስቀምጠዋል። ዴሞክራሲ የአንድ ግለሰብ ወይንም የጥቂት ሃብታሞች ፍቃድ የሚከበርበት ሳይሆን፣ የሕዝብ ፍቃድ የሚከበርበት እንደሆነ ያስረዳል።

 

ከ150 አመታት በፊት የአሜሪካን ፕሬዘዳንት የነበሩትና ባርነትን ያስቆሙት፣ አብርሃም ሊንከን፣ «ዴሞክራሲ ለሕዝብ፣ የሕዝብ፣ በሕዝብ የሆነ መንግስት ነው» በማለት ነበር የገለጹት።

 

ከሁለት ሺህ አመታት በፊት ዴሞክርሲን ሲለማመዱ ከነበሩት ከግሪኮች ዘመን ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ፣ በግልጽ እንደምናየው፣ ዴሞክራሲ በሕዝብ ፍላጎትና የሕዝብን ጥቅም በማስጠበቅ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት እንደሆነ ነው። በዴሞክራሲ «እግዚያብሄር ነው የሾማቸው» ተብለው፣ ወይንም ገንዘብ ስላላቸው፣ ወይንም ነፍጥ ስለጨበጡ ግለሰቦች የሚገዙበት ሁኔታ አይኖርም። ዴሞክራሲ ሕዝቡ የሚፈልገውን እየሾመ፣ የሚፈልገውን እየሻረ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ስርዓት ነው።

 

አንዳንዶች ዴሞክራሲ ለአፍሪካ አይሆንም ይላሉ። ከሁለት ሺህ አመታት በፊት ለግሪኮች ከሰራ፣ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ለምንኖር ሰዎች የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም። ዴሞክራሲ ሕዝብን፣ እያንዳንዱን ዜጋ የሚያከበር ነው። እንስሳ ካልሆነ በቀር «ምንድን ነው ፍቃድህ? የትኛው መሪ ቢገዛህ ትመርጣለህ?» ተብሎ ቢጠየቅና አማራጭ ቢቅርብለት፣ ማንም ሰው አይጠላም።

 

ብዙ ጊዜ ዴሞክራሲን ከነጻነት ጋር የማገናኘት ሁኔታ አለ። ዴሞክራሲ ነጻነት ማለት አይደለም። ዴሞክራሲ ነጻነት እንዲመጣ የሚረዳ መንገድ ነው። ዴሞክራሲ መሳሪያ ነው። ዴሞክራሲ ፖለቲካ ነው። ያለ ዴሞክራሲ፣ ያለ ፖለቲካ ትግል ነጻነት ሊኖር አይችልም።

 

ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት

ከዴሞክራሲ መገለጫዎች አንዱና ዋናው የሕግ የበለይነት ነው። አንድ በተባበሩት መንግስት የሕንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኛ የነበሩ፣ አቱል ካሬ፣ የተባሉ ሰው «ዴሞክራሲ ያለ ሕግ የበላያነት ሊኖር አይችልም። የዴሞክራሲን ባህል፣ እውነተኛ የዲሞክራሲን ስርዓት ለመገንባት የሚደረገው ሂደት፣ በሕግ የበላይነት ማእቀፍ ውስጥ መግባት አለበት» ሲሉ ያስረዳሉ።

ከሁለት ሺህ አመታት በፊት የግሪኩ አሪስቶትል «ሕግ ሊገዛ ይገባል» ሲሉ፣ የሮም ባለስልጣን የነበሩት ሲሰሮ «ሁላችንም የሕግ ተገዢ መሆን አለብን። አለበለዚያ ነጻነታችንን እናጣለን» ነበር ያሉት። በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዛዊው ሳሙዔል ሩተርፈርድ በተለምዶ በላቲን «ሬክስ ሌክስ» (ንጉስ ሕግ ነው) የሚባለውን አባባል ገልብጠው «ሌክስ ሬክስ»(ሕግ ንጉስ ነው) በማለት፣ ነገስታት ወይንም ግለሰቦች ሳይሆኑ ሕግ የበላይ መሆን እንዳለበት ነበር የጻፉት።

ለዴሞክራሲ መስፈን፣ የዴሞክራሲ መስፈንንም ተከትሎ ለሚመጣው የነጻነት መከበር፣ ሕግ የበለይ ሊሆን ይገባል። ይሄንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሕጉ አካል ከገዢዎችና ከሥራ አስፈጻሚው አካል የተለየና ገለልተኛ መሆን ይኖርበታል። ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሞቴንስኪዮ «የሕግ መንፈስ» (The Spirit of Laws) በሚል ርእስ ሥር፣ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1748 ባሳተመው መጽሃፍ፣ የግለሰቦችን ነጻነት ለማረጋገጥ ዴሞክራሲንም ለማስፈን የሕግ አውጭው (legislative) የሕግ አስፈጻማዊው (executive) እና የሕግ ተርጓሚው (judicial) አካላት የተለያዩ መሆን እንዳለባቸው አስቀምጧል።

 

በአገራችን ኢትዮጵያ ከዲሞክራሲ ጋር ትንሽ የሚቀራረብ ስርዓት የምናውቀው በኦሮሞዎች መካከል የነበረው የገዳ ስርዓት ነው። የኦሮሞ መኳንንቶች የተለያዩ ነገሳታትን በመፍጠር (የጊቤ መንግስታት ተብለው እንደሚታወቁት) ከገዳ ስርዓት ወደ አምባገነናዊ ንጉሳዊ ስርዓት እስከተሸጋገሩበት ጊዜ ድረስ፣ ከግሪኮች ባልተናነሰ መልኩ፣ በኢትዮዮጵያ ምድር ዴሞክራሲ ሲተገበር ነበር።

 

ከገዳ ስርአት ውጭ፣ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን አታውቅም። የምታውቁው በጉልበት በጠመንጃ ስልጣን የጨበጡ የግለሰቦች አምባገነንነትን ነው።

ዴሞክራሲን ቢያንስ ቢያንስ በወረቀት ላይ አስፍሮ፣ ለዴሞክራሲ መስፈን እንደሚሰራ በርግጥ፣ ኢሕአዴግ ይፋ አድርጓል። ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ለሕዝብ ቃል የገባቸው ነገሮች ቢኖሩ፣ ሕግ የበላይ እንደሚሆን፣ ዜጎችን እንደፈለጉ ማሰር፣ መግደል እንደሚያቆም፣ ሕዝቡ የፈለገውን የመሾምና የመሻር መብቱ እንደሚጠበቅ ነበር። አንድ የኢሕአዴግ ታጋይ የኢትዮጵያን ራድዮ በሚቆጣጠርበት ጊዜ የተናገረውን ማስታወሱ ብቻ ይበቃል። «ብሶት የወለደው የኢሕአዴግ ሰራዊት ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሬዲዮ ጣቢያውን ተቆጣጥሮታል” ነበር ያለው። ኢሕአዴግ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም እንደሚቆም ተስፋ መስጠቱ ነበር።

 

ነገር ግን «ፍየል ወዲህ ቅምዝም ወዲያ» እንደተባለው፣ ቃል የተጋበው ሌላ፣ እያየን ያለነው ሌላ እየሆነብን ነው። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ አስፈጻሚው፣ የሕግ አውጭውና የሕግ ተርጓሚው (ፍርድ ቤቶች) አካላት፣ በስምና በወረቀት የተለያዩ፣ በተግባር ግን በአንድ ላይ የተጨፈለቁ እንደሆኑ ነው የምናየው።

 

የሕግ አውጭ አካል (ፓርላማው)

የሕግ አውጭውን አካል፣ ፓርላማውን ብንወስድ፣ በደርግ ጊዜ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ከነበራቸው ሸንጎ ጋራ የሚለይበት ሁኔታ አይታይም። አንድ የሚታይ ልዩነት ቢኖር ኮሎኔል መንግስቱ በከፍታ ቦታ ነበር የሚቀመጡት። በፓርላማ አቶ መለስ ደግሞ ወረድ ብለው፣ ከተቀሩት የፓርላማ አባላት ጋር ከፊት ነው የሚቀመጡት።

 

የመጀመሪያ የፌዴራል ምርጫ የተደረገው በ1987 ዓ.ም ነበር። በዚህ ወቅት ኢሕአዴግና አጋሮቹ ከ547 መቀመጫዎች 480 መቀመጫዎችን (82.9 %) አሸነፍን አሉ። በ1992 ዓ.ም. ቁጥራቸውን አሻሽለው ወደ 534 አወጡት። በ1997 ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ፉክክር የተደረገበት እንደሆነ በሚነገርለት ምርጫ፣ ብዙዎች ቅንጅት እንዳሸነፈ ቢናገሩም፣ የድምጽ ቆጠራውን በማስቆም፣ ኮሮጆ በመቀየር፣ ኢሕአዴግና አጋሮቹ 386 መቀመጫዎች (ከሰባ በመቶ በላይ) አሸነፍን ብለው አወጁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተነሳው ውዝግብ በሰላም የሚታገሉ የሰላማዊ የፖለቲካ ታጋዮች ወደ ወህኒ ተወረወሩ። በንጹሃን ዜግች ግንባር ላይ ጥይት ተርከፈከፈ። እነ ሽብሬ ደሳለኝ ወደቁ። ለሕዝቡ ጥቅም እንደቆሙ ሲናገሩ የነበሩት ኢሕአዴጎች፣ የኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ዜጎችን ደም በየመንገዱ አፈሰሱ። በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከየቤታቸውና ከይቅያቸው እየታፈሱ በደዴሳ፣ ዝዋይ፣ ሸዋሮቢት በመሳሰሉ ዘግናኝ እሥር ቤቶች በጅማላ ታሰሩ። በአንድ ምላጭ መቶዎች ጸጉራቸው ተላጨ።

 

ከጥቂት አመታት በፊት የተደረገው የ2002 አራተኛ ምርጫ ደግሞ ከዚያ በፊት ከተደረጉት ሶስቱ ምርጫዎች በባሰና በሚያሳፍር ሁኔታ ተጠናቀቀ። በከዚህ በፊቶቹ ምርጫ ኢሕአዴግ፣ በውስጡ አምባገነን ባህሪ ቢኖረውም፣ ላይ ላዩን የዴሞክራሲ መልክ ይታይበት ነበር። የ2002 ምርጫ ግን የኢሕአዴግን የዴሞክርሲ ሽፋን ሙሉ ለሙሉ ገፈፈው። ኢሕአዴግ ከ547 መቀመጫዎች 547ቱን አሸነፍኩ ብሎ 99.6 በመቶ ፓርላማውን ተቆጣጠረ።

የቀድሞ የኢራቅ ፕሬዘዳንት ሳዳም ሁሴን ለብቻቸው ተወዳድረው ያሸነፉት መቶ በመቶ ነበር። በአለማችን ካሉ በርካታ አምባገነኖች ከነ ቬኑዙዌላው ሁጎ ቻቬዝ፣ ከኢራኑ አህማዲኒጃን፣ ከሱዳኑ አልባሽር፣ ከዚምባቤው ሙጋቤ ብሰው፣ ከሳዳም ሁሴን ቀጥሎ በሁለተኛነት የተቀመጡት፣ 99.6 በመቶ አሸነፍኩ ያሉት የእኛው ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኑ። በ2002ቱ ምርጫ በማያሻማ መልኩ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ርዝራዥ እንኳን እንደሌለ በግልጽ ተረጋገጠ።

 

ኢሕአዴግ «አብዮታዊ ዴሞክራሲ» የሚለውን ከዴሞክራሲና ለሕዝብ ከመገዛት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ማእከላዊነት ላይ ያተኮረ፣ የማርክሲስት ግራ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ አሰራር እንደሚያራምድ ይታወቃል። ለዚህም ነው የኢሕአዴግ አባላት እርስ በርሳቸው እንደ ኢሰፓዎች «ጓዶች» የሚባባሉት።

 

ሕገ መንግስቱ የፓርላማ አባላት ተጠሪነታቸውን ለሕገ መንግስቱ፣ ለመረጣቸው ሕዝብና ለሕሊናቸው እንደሆነ በአንቀጽ 54 ንኡስ አንቀጽ 4 ይገልጻል። ነገር ግን በኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካ መሰረት፣ አንድ የኢሕአዴግ አባል ወደደም ጠላም፣ ድርጅቱ የሚወስደውን የፖለቲካ ውሳኔ የማስፈጸም ግዴታ አለበት። በመሆኑም የኢሕአዴግ የፓርላማ አባላት፣ የመረጣቸውን ሕዝብ ጥቅም፣ ከኢሕአዴግ ፍላጎት ጋር ከተጻረረ፣ ነጻ ሆነው ድርጅታቸውን ተቃውመው ድምጽ መስጠት አይችሉም። በመሆኑም 99.6 በመቶው የኢሕአዴግ የፓርላማ አባል የሚገዛው መርጦናል ላሉት ሕዝብ ሳይሆን ኢሕአዴግን በበላይነት ለሚመሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ ነው። አቶ መለስ ዜናዊ ከፈለጉ በ24 ሰዓት ውስጥ ፓርላማው ሕግ እንዲያወጣ ማስደረግ ይችላሉ።

 

አቶ መለስ ዜናዊ ሜዲያውን የሚያፍን ሕግ ለማውጣት ሲነሱ ፓርላማው ሆ ብሎ አጸደቀላቸው። አቶ መለስ ጠንካራ የሚሏቸውን የተቃዋሚ መሪዎች ለማንበርከክ መሰረት የሌለው «የፀረ-ሽብርተኛ» ሕግ እንዲወጣ ሲያዙ ፓርላማው ሳያቅማማ ፍቃዳቸውን ፈጸመላቸው። በአሁን ጊዜ ሕግ አውጭውም፣ ሕግ አስፈጻሚውም አቶ መለስ እንደሆኑ በግልጽ እየታየ ነው።

 

የፍርድ ሥርዓቱ

የሕግ አስፈጻሚው አካል የሕግ አውጭውን አካል ብቻ አይደለም እየተቆጣጠረ ያለው። የሕግ ተርጓሚውንም አካል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ይቆጣጠራል። ፍርድ ቤቶች ከአቶ መለስ ፍቃድ ውጭ የመወሰን ፍላጎቱ የላቸውም። ፍላጎት ቢኖራቸውም እንኳን፣ አቅሙና ስልጣኑ ይጎድላቸዋል።

 

እርግጥ ነው ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው ሕገ መንግስቱ ይደነግጋል። አንቀጽ 79 ንኡስ አንቀጽ 2 «በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግስት አካል፣ ከማንኛውም ባለስልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽእኖ ነጻ ነው» ይላል።

 

ነገር ግን ሕግ መንግስቱ እራሱ በሌሎች አንቀጽ እራሱን ተቃርኖ፣ የፍርድ ቤቶችን የበላይነት በማያሻማ መልኩ የሚሸረሽረበት ሁኔታ አለ።

 

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 81 መሰረት፣ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርጠው፣ በጠቅላይ ሚኒስተሩ አቅራቢነት፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሚቆጣጠሩት ፓርላማ ይጸድቃሉ። ሌሎች የፌዴራል ዳኞች (የፌዴራል የአንደኛ ደርጃ፣ የፌዴራል ከፍተኛ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች) በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተመርጠው፣ በጠቅላይ ሚኒስተሩ አቅራቢነት በፓርላማ ይጸድቃሉ።

 

ይህ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚባለው አካል፣ በሕገ መንግስቱ ላይ ቢያንስ ከአራት ጊዜ በላይ በአንቀጽ 79 እና 81 ላይ ተጠቅሷል። ነገር ግን ሕገ መንግስቱ ስለዚህ አካል አመሰራረትና ስልጣን የሚዘረዝርበት አንድም ቦታ የለም። (ይሄ የሕገ መንግስቱን ግድፈት የሚያሳይ ነው)

 

ይህ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚሾሙት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት እና ምክትል ፕሬዘዳናት በአባልነት የሚገኙበት አካል ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ካልሆነም ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የሚታዘዝ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አይከብድም።

 

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 4፡ ለ፣ መሰረት፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አንድን ዳኛ «ብቃት የለውም» በሚል ከዳኝነት ከሃላፊነት ሊያነሳው ይችላል። በአንቀጽ 79 ንዑስ 4፡ሐ መሰረት፣ ፓርላማውም በሶስት አራተኛ ወይንም ሁለት ሶስተኛ ሳይሆን በአንድ ድምጽ አብላጫ ድምጽ ተስማምቶ አንድ ዳኛ የማንሳት ስልጣን አለው። በአጭሩ አባባል ማንኛውም ዳኛ በሕግ አሳፋጻሚውና የሕግ አሳፈጻሚው በሚቆጣጥረው የሕግ አውጭ አካል በቀላሉ ሊነሳ ይችላል ማለት ነው። ፈረንጆች እንደሚሉት “The Judiciary is at the mercy of the Executive”።

 

ያ ብቻ አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ዜጎቿ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ያሉባት አገር ናት። ዳኞች የሕግ አስፈጻሚውን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ውሳኔ የማይወስኑ ከሆነ፣ በዳኝነት ሞያቸው የማገልገል እድላቸው የመነመነ ነው የሚሆነው። ከሥራቸው ይባረራሉ። ጥቅም ይቀርባቸዋል። የተለያዩ ሰበቦች እየተፈለገ፣ በግምገማ «ሙስና ውስጥ ተዘፍቀል» በሚል ወደ ወህኒ ሊወርዱም ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ይፈራሉ። እንኳን የሕዝብን መብት ሊያረጋግጡ፣ ጭራሹኑ ለአገዛዙ በሕግ ስም ዜጎችን የመጨፍለቂያ መሳሪያ እየሆኑ ነው።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአቶ ስዬ አብርሃ ጉዳይ ላይ በወሰኑት ውሳኔ ከዳኝነት እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል። እንደ ዳኛ መሸሻ ወልደሚካኤል፣ ዳኛ ፍሬህይወት የመሳሰሉ፣ ለሕሊናቸው የተገዙ ዳኞች አድራሻቸው በውጭ አገር ሆኗል።

 

ኢሕአዴግ ሕግን እንደ ዱላ በመጠቀም፣ ፍርድ ቤቶችን እያዘዘ፣ ሕግን መሳቂያና መቀለጃ ነው ያደረገው። በብዙ የዴሞክራሲ አገሮች ዳኛ ይከበራል። ፍርድ ቤት ይከበራል። በኛ አገር ግን ፍርድ ቤት የተናቀ ሆኗል። በፍርድ ቤቶች እውነተኛ የሕግ ሂደትን ሳይሆን ተራ የፖለቲካ ዳንኪራና ቀልድ ነው እየተፈጸመ ያለው።

 

አንጋፋው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ታስረው በነበረ ጊዜ «ፍርድ ቤቱ ከአገዛዙ ነጻ ሆኖ መፍርድ አይችልም» በሚል «አልከላከልም» ብለው ነበረ። ከምርጫ ዘጣና ሰባት በኋላ፣ የቅንጅት መሪዎች ለፍርድ ቤቱ እውቅና ሳይሰጡ፣ ሳይከላከሉ፣ በአስቂኝ ሁኔት ከአራት ኪሎ በመጣ ቀጭን ትእዛዝ የእድሜ ልክ እሥራት ተወስኖባቸው ነበር። አሁንም በነ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ የምናየው፣ ይሄንኑ ሕግን የማርከስ ተግባራትን ነው። አቃቢ ሕግ ያቀረባቸው መረጃዎች እራሳቸው የአቃቢ ሕግን ክስ የሚያፈርሱ እንደሆነ ዳኞቹ እያወቁ፣ ተከሳሾቹ ፍጹም ሰላማዊና ሕግን አክብረው የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ መረጃ ቀርቦላቸው፣ ፊታቸውን ከእውነት አዙረው፣ ፍርድን ሲያዛቡ ተመልክተናል።

 

የሕግ አስፈጻሚው አካል መሪ፣ የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው። አቶ መለስ ስልጣን ከጨበጡ ሃያ አንድ አመታት ሊሆናቸው ጥቂት ወራት ነው የቀራቸው። ላለፉት 21 አመታት ፓርላማው ከርሳቸው ፍቃድ ውጭ የወሰነው አንዳችም ውሳኔ የለም። የፌዴራል ዳኞች በሙሉ የተሾሙት በርሳቸው አቅራቢነት፣ እርሳቸው በሚቆጣጠሩት ፓርላማ ውሳኔ ነው። ከእርሳቸው ፍቃድ ውጭ ፍርድ የሚሰጡ፣ ሕሊናቸው ያሸነፋቸው ዳኞች አሊያም ከስራቸው ተባረዋል፣ ወይ አገር ለቀው ወጥተዋል። በአሁኑ ወቅት ያሉት ዳኞች፣ ቀኝ ግራውን መዝነው ፍርድ የሚሰጡ ሳይሆን፣ ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው፣ አይናቸውን በጨው አጥበው፣ ከሕሊናቸውና ከእግዚአብሄር ተጣልተው፣ ከአራት ኪሎ የመጣውን መመሪያ የሚያነቡ ናቸው።

 

መለስ ሌክስ

 

እንግዲህ በአገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢሕአዴግ ከሃያ አንድ አመታት ስልጣን ሲጨብጥ ተስፋ እንደተገባው ሳይሆን፣ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማሪያም አስተዳደር ወቅት እንደነበረው አይነት፣ መልኩን የቀየረና ከጊዜው ሁኔታ ጋር የተመሳሰለ፣ ፍጹም አምባገነንነት ነው። ሃይ ቴክ (High Tech) አምባገነንነት ብዬዋለሁ።

 

ከባድመ ጦርነት በፊት ቢያንስ ቢያንስ በኢሕአዴግ፣ በተለይም በሕወሃት አመራር አባላት መካከል አንጻራዊ የውስጥ ዴሞክራሲ እንደነበረ የሚናገሩ አሉ። የሕወሃት አመራር አባላት እንደ ቡድን በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ አምባገነን ሆነው ነበር እንጂ፣ እርስ በርሳቸው እንደ እኩል ነበር የሚተያዩት። አሁን ግን እድሜ ለቦናፓርቲዝምና «ስልጣንን ለወጣቶች እናስረክብ» የሚል መፈከር፣ አንጋፋ የቀድሞ የሕወሃት አመራር አባላት ተወግደው፣ ግማሾቹ አምባሳደሮች፣ ግማሾቹ የስኳር ለቃሚዎች ሆነዋል። ግማሾቹ ቤት ተለግሰው አርፈው አርፈው ተቀምጠዋል።

 

አሁን የጥቂት የሕወሃት አመራር አባላት አምባገነንነት ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው፣ የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት ነው ። አብርሃም ሊንከን ዴሞክራሲን «ለሕዝብ የሕዝብ በሕዝብ የሆነ መንግስት ነው» ነበር ያሉት። በኢትዮጵያ እንጅሩ ዴሞክራሲ። ዴሞክራሲ የለም። ያለው ለመለስ የመለስ በመለስ የሆነ መንግስት ነው። የእንግሊዛዊውን ሳሙዔል ሩተርፈርድ የላቲን አባባል ልዋስና ሌክስ ሬክስ (ሕግ ንጉስ ነው) ሳይሆን «መለስ ሌክስ» (መለስ ሕግ ነው) ነው ማለት የሚቻለው።

 

መደምደሚያ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ ነጻነትህና፣ መብት እንዲከበር፣ በየወረዳው አቶ መለስን የሚያገለግሉ ካድሬዎችና የደህንነት አባላት የሚያደርሱብህ ግፍ እንዲያበቃ፣ በአገርህ፣ በማንነትህና በኢትዮጵያዊነትህ ተከብረህ፣ ቀና ብለህ፣ ሰርተህ፣ ተምረህ፣ ነግደህ፣ በሰላምና በፍቅር መኖር፣ የፈለከውን መሾም፣ የፈለከውን መሻር ትፈልጋለህን? መልስህ «አዎን» ከሆነ እንግዲህ፣ በያለህበት የድርሻህን ለመወጣት ተነሳ። በያልህበት ተደራጅ። ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምጽህን አሰማ።

 

ታላቁ የሳይንስ ሰው አልበርት አነስታይን ስለ ዲሞራሲና የሕግ የበላይነት ሲናገር «ምርጫ እስካለኝ ድረስ፣ የፖለቲካ ነጻነት፣ መቻቻል እና ዜጎች ሁሉ እኩል በሚታዩበት፣ የሕግ ስርዓት ባለበት አገር ብቻ ነው መኖር የምፈልገው” ነበር ያለው።

 

አነስታይን ከናዚ ጀርመን ሸሽቶ፣ መብቱ በተከበረበት በአሜሪካ የስደት ኑሮውን ጀመረ። መቼም ሰማኒያ ሚሊዮን ኢትዮያውያዊ ኢትዮጵያን ለቆ ሊሰደድ አይችልም። ዴሞክራሲን ፍለጋ ዴሞክራሲ ወዳለበት መሸሹ ጥቂቶችን ለጥቂቶች አጋጣሚውን ላገኙ እፎይታ ሊሰጥ ይችላል። ነገር ግን ዴሞክራሲን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ከሰራን ግን፣ መፍትሄው ለሚሊዮኖች ይሆናል። የተሰደዱም ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።

 

ዴሞክራሲ አቶ መለስ ዜናዊ የሚሰጡት ስጦታ አይደለም። አቶ መለስማ የፈለጉትን እያፈረሱ፣ የፈለጉት እየገነቡ፣ የፈለጉትን እያከበሩ፣ የፈለጉትን እያዋረዱ ይኸው በስልጣን ላይ ሃያ አንድ አመት ሊሆናቸው ነው።

 

ዴሞክራሲ ባራክ ኦባማ ወይም የምእራባውያን አገሮች አይሰጡንም። ምናልባት «ጥቁር ሕዝቦች ረግጦ የሚገዛቸው አምባገነን ነው የሚሻላቸው» በሚል ከዝንጀሮ በላይ ከሰው በታች ይቆጥሩን ይሆናል።

 

ዴሞክራሲ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚያመጡት ነገር አይደለም። በውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ሰልፎች፣ የተለያዩ ዝግጅቶች በራሳቸው ዋጋ አይኖራቸውም። በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ከመስጠት በስተቀረ ወሳኝ ሚና አይኖረውም። ሊኖረውም አይችላም። በውጭ አገር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ ተስፋ አደርጎ ለውጥ የሚጠብቅ ኢትዮጵያዊ ወገን ካለ፣ በርግጥ አዝንለታለሁ። ለምን እውነታውን ሲረዳ ማዘኑ አይቀርምና።

 

ዴሞክራሲን እያንዳንዱ አገር ቤት የሚኖር ኢትዮጵያዊ ታግሎ፣ መስዋእትነትን ከፍሎ የሚያመጣው በረከት ነው። ሕዝብ ካልተነሳ፣ ሕዝብ ከፍርሃቱ ካልተላቀቀ፣ ሕዝብ ካልተደራጀ፣ ሕዝብ አምባገነንነትን በቃ ካላላ፣ በአገርችን ኢትዮጵያ የአምባገነንነት ዘመን ለአመታት ይቀጥላል።


ግርማ ካሣ (

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ