ተመስገን ደሳለኝ

ይህ ርዕሰ ጉዳይ የተነሳው የዛሬ 15 ቀን ነበር፡፡ እናም ሳይደመደም በይደር ተላለፈ፡ ፡ ይደሩ በተቀጠረበት እለት የታተመው ደግሞ የህወሓትን 37ኛ የልደት በአል በማስመልከት የተዘጋጀ ልዩ እትም በመሆኑ ርዕሰ ጉዳዩ ተዘለለ። ሆኖም ተዘሎ አልቀረም ይኸው የዚህ እትም አጀንዳችን ሆነ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪዎች በጨረፍታ… ወደ አጀንዳችን ከመግባታችን በፊት አንድ አስደንጋጭ ወሬ የሳምንቱ ሰደድ እሳት በመሆኑ እሱን እናስቀድም።

 

አንዱአለም አራጌ ተደበደበ

 

አዎ! አንዱአለም አራጌ ተደበደበ። እናም የት ቦታ ተደበደበ? በማን ተደበደበ? ለምን ተደበደበ? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት የሚኖርብን ይመስለኛል። ደግሞም ማንሳት ብቻ አይደለም መመለስም አለባቸው። ለዚህም እንደመንደርደሪያ የሚሆነን ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ያወጣው መግለጫ ላይ ያለው መልስ ነው። መልሱም እንዲህ የሚል ነው፡-

 

‹‹አንዱአለም የተደበደበው በግዙፉ የቃሊቲ ወህኒ ቤት በታሰረበት ክፍል ውስጥ ሲሆን፤ ደብዳቢውም ኢባስ አስፋው የሚባል በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሶ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ በቅጣት ማሻሻያ ወደ እድሜ ልክ እስራት የተለወጠለት ወንጀለኛ ነው።›› አሳዛኙና ግራ አጋቢው ነገር ነፍሰ-ገዳዩ ኢባስ አንዱአለምን በምን ምክንያት እንደደበደበው አለመታወቁ ነው። የፓርቲው መግለጫም ስለዚህ ጉዳይ ያለው ነገር የለም። በደፈናው በእስረኛ አያያዝ ላይ የወጡትን አለም አቀፍ የህግ ድንጋጌዎች ጠቀሶ፤ ይሄ አንቀፅ ተጣሰ፣ ይሄ አንቀፅ ተበጠሰ፣ገለመሌ ከማለቱ ውጭ። መቼም ይኽ አይነቱ አመላለስ ‹‹ሾላ በድፍን›› አይነት መሆኑን ማንም አያጣውም። ‹‹ሾላ በድፍን›› ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ ሲሆን በፓርቲው ላይ የሚጣልን እምነት ይሸረሽራል፡፡ ወይም ገፅታን ያጠለሻል።

 

እናም የፓርቲው መግለጫ አይነ ግቡ አይደለም፡፡ አንዱአለም እንደደብዳቢው በጭካኔ የሰው ነፍስ አጥፍቶ የታሰረ አይደለም። ኪስ አውላቂ እና ቤት ሰርሳሪም አይደለም፡፡ ወይም እንደ አንዳንድ ባለስልጣናት በሙስና ተይዞ የታሰረ አይደለም። ይኽ ሰው የአንድ ትልቅ ፓርቲ አመራር አባል ነው፡፡ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮም በኢትዮጵያ ፖለቲካ አውድ ላይ ስብከት የጀመረ ካህን ነው። በምርጫ 97ም ቅንጅትን ወክሎ በፓርላማ ምርጫ ያሸነፈ ተመራጭ ነው። በምርጫው ጦስም ለ21 ወራት ታስሮ የተፈታ ፖለቲከኛ ነው።

 

ለዚህም ነው የአንዱአለም መደብደብ እስር ቤት ውስጥ በተራ ምክንያት በእስረኞች መካከል በሚነሳ ፀብ ነው ለማለት የሚቸግረው። የፓርቲው መግለጫም እንዲህ ዙሪያ ጥምጥም መሄዱ አስገራሚ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ይታወቃል። የኢህአዴግ ጨዋታም እንዲሁ ግልፅ ነው፡፡ እናም በ1997 ዓ.ም. የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ እየጠቀሱ ‹‹ውሳኔ ያላገኙ እስረኞች ውሳኔ ካገኙ ሌሎች እስረኞች ጋር አይቀላቀሉም›› የሚለው አንቀፅ በአንዱአለም ላይ ተጥሶአል የሚል መከራከሪያ ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ የመሆን አቅም የለውም ወይም ውሃ አይቋጥርም። ምንአልባትም ይኽ መከራከሪያ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ›› ከሚል ግለሰብ የመጣ ቢሆን ኖሮ ውሃ በቋጠረ። ነገር ግን አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ያውም መሪው፣ መንግስት በሚቆጣጠረው እስር ቤት በታሰረበት መደብደቡን ተቃውሞ የሚያወጣው መግለጫ ይህንን በመሰለ ምክንያት ካውሸለሸለው ፖለቲካውን ደባሪ ያደርገዋል። አዎ! ከአንድነት ጠንካራ መከራከሪያ ይጠበቃል፡ የፖለቲካውን ባህሪ ተንተርሶም ከድብደባው ጀርባ ያለውን ፖለቲካ ማጋለጥ ይኖርበታል፡፡ በአናቱም የፖለቲካ ካርታ እንዲህ በመሳሰሉት ጉዳዮች ሊመዘዝ እንደሚችል ሊነቃ ይገባል። በተቀረ ‹‹ኢባስ›› የሚባል ፖለቲካ የለም፤ ሊኖር የሚችለው ፖለቲካ ከኢባስ ጀርባ ባሉ ሰዎች ላይ ነው።

 

የሆነ ሆኖ አንዱአለም አራጌ ራሱን መከላከል በማይችልበትና በህግ ጥበቃ ሥር በነበረበት ሁኔታ ህግ ተጥሶ አብሮት ሊታሰር የማይገባው፤ አብሮት እንዲታሰር ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመበት በመሆኑ ሊጠየቅ የሚገባው አካል ሊጠየቅበት ይገባል። ሀገር አቀፍም ሆኑ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጉዳዩን በቸልታ ያዩታል የሚል ግምት የለኝም፡፡ እንዲህ አይነቱን ውንብድና አቃሎ ማየቱም ሌላ አደጋ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ በተረፈ ክስተቱ ‹‹ደርግ እየተመለሰ ነውን?›› ያሰኛል። ኧረ እንዲያውም የደርግ የተሻለ ነው፡፡ ደርግ መደብደብ የፈለገውን እስረኛ ለመደብደብ ዙሪያ ጥምጥም አይሄድም። መታወቂያ ያለው ደሞዝተኛ ደብዳቢ (ገራፊ)ቀጥሮ ያሻውን ያደርጋል እንጂ፡፡ እናም እንዲህ አይነት ውንብድና፣ እንዲህ አይነት የማፊያ ስራ ለማንም እንደማይበጅ፣ እንዲሁም ከድብደባው ጀርባ ያላችሁ፣ ይኽ አይነቱ ጨዋታ ተራ ቁማር እንጂ ፖለቲካ ሊሆን እንደማይችል ልትረዱ ይገባል፡፡ ለነገሩ ማን ያውቃል ይኼ ክስተት ምን አይነት ቁጣ እንደሚቀሰቅስ?

 

አሁን ወደ አጀንዳችን እንመለስ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን አማካሪዎችን ወደ ማየቱ። ከ15 ቀን በፊት አማካሪ ዶ/ር ፋሲል ናሆምን ለናሙና ያህል ጨርፈን አይተናል። ተሸናፊውን ደርግ ባማከሩበት ማዕረግ፤ አሸናፊውን ኢህአዴግን ማማከራቸው፣ የምክራቸው አሳማኝነት የት ድረስ እንደሆነ ሊያሳይ እንደሚችልም ተነጋግረናል። እናም አማካሪ ሬድዋን ሁሴን እና አማካሪ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴን ጨርፎ ወደ ማየቱ እንለፍ። በቅድሚያም የወራቤው ፍሬ ክቡር አማካሪ ሬድዋን…

 

ሙሉ ስማቸው ሬድዋን ሁሴን ይባላል። በ1987ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በባይሎጂ ከተመረቁ በኋላ በጂንካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለጥቂት ጊዜ አስተምረዋል። ከጂንካም ለቀው በአዲስ አበባ አወሊያ ትምህርት ቤት ማስተማር እንደጀመሩ የህይወት ታሪካቸው ይነግረናል። አወሊያ ት/ቤት በነበሩበት ጊዜም ነው ፖለቲካን ከታች ሀ፣ ሁ፣ ሂ… ብለው መቁጠር የጀመሩት።

 

የሬድዋን የፖለቲካ ሀ፣ ሁ፣ ሂም የተመሰረተው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሳይሆን በስልጤ ህዝብ ማንነት ላይ ነበር፡፡ እናም ስልጤ በዞን ደረጃ ባለመዋቀሩ ከአካባቢው ተወላጆች ጋር ሲገናኙ ይቆጩና ይብሰከሰኩ ጀመር፡፡ በእርግጥ ጥያቄያቸው ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ይህችን ካርታ ብቻ መዞ ፖለቲካ ውስጥ መግባቱ ለትዝብት መዳረጉ አይቀሬ ነው።

 

የሆነ ሆኖ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ይኽን ቁጭታቸውን ወደ ተደራጀ የፖለቲካ ትግል በማሸጋገር የስልጤ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ስሕዴፓ) የተሰኘ የተቃዋሚ ድርጅት መሰረቱ፡ ፡ በፓርቲያቸው አስተባባሪነትም የተቃውሞ ሰልፍ እስከ ማድርግ ደረሱ፡፡ ምንአልባትም የዛሬው ድርጅታቸው ኢህአዴግ አርቆ አሳቢነት የፈጠረው ይሁን ወይም ሌላ፣ ድንገት የሬድዋንን ፓርቲ የሚቃወም አዲስ ፓርቲ ብቅ አለ፣ በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሚኒስትር በሆኑት ሲራጅ ፈርጌሳ አማካኝነት ይመራ የነበረው ይህ ፓርቲ የስልጤ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ስሕዴድ) ይሰኛል፡፡ …እሾን በእሾህ፣ ፓርቲን በፓርቲ።

 

እናም የሬድዋን ትግል ከኢህአዴግ ጋር ብቻ መሆኑ ቀርቶ ከሌላኛው የስልጤ ህዝብ ድርጅት ጋርም ሆነ፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከልም የከረረ የውክልና ፉክክር ተፈጠረ። በሽግግር መንግስቱ ዘመን ‹‹የኦሮሞን ህዝብ በትክክል የምወክለው እኔ ነኝ›› በሚል በኦነግ እና በኦህዴድ መካከል የነበረው ፉክክር አይነት ወራቤ ላይም ተደገመ፡፡ ቃላቶችን እያሰካኩ ያለማቋረጥ የመናገር ተሰጥኦ ያላቸው ሬድዋንም በአገኙት አጋጣሚ በሲራጅ ፈርጌሳ የሚመራውን ስሕዴድ ‹‹የኢህአዴግ ተላላኪ፣ ተለጣፊ፣ አሻንጉሊት…›› እያሉ ይተቹት እንደነበር የትላንት ትውስታ ነው።

 

ትውስታችንንም በማስረጃ ለማስደገፍ ያህል ሬድዋን የተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር በነበሩበት ዘመን በ1993 ዓ.ም. ታህሳስ ወር ከታተመው ከጎህ መጽሔት ጋር ከአደረጉት ቃለ መጠይቅ ጥቂቱን እንቀንጭብ፡፡ መጽሔቱም የሳቸውን ድርጅት የማይደግፉ የስልጤ ተወላጆች መኖራቸውን ጠቅሶ ይኼ ከምን የመነጨ እንደሆነ እንዲያብራሩለት ጠየቃቸው። ሬድዋንም ሲመልሱ እንዲህ አሉ፡-

 

‹‹…የስልጤን ብሔረሰብ በተለያየ ስያሜ ፈርጀው የተንቀሳቀሱት የብሔረሰቡ ተወላጆች የኋላ ኋላ እውነቱን ቢረዱም ጥቅም ፍለጋ በዚያው ሰክረው ቀሩ እንጂ የተፈጠረው ምስቅልቅል በመጀመሪያ የራሱ የሆኑ መነሻዎች አሉት።››

 

ሬድዋን ወደ ኢህአዴግ ያዘነበሉትን የስልጤ ተወላጆችን ነው ‹‹ጥቅም ፍለጋ በዚያው ሰክረው ቀሩ›› ሲሉ የወነጅሉት፡፡ በዛ በደጉ ዘመን። በእርግጥ ዛሬ ሬድዋን እንዲህ ሊሉ አይችሉ። በብራሃን ፍጥነት ራሳቸውም ከዋነኞቹ ኢህአዴጎች አንዱ ሆነዋልና። ሆኖም ሬድዋን ከኢህአዴግ ተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግ አመራርነት የተሸጋገሩበት ምክንያት ‹‹ጥቅም ፍለጋ በዚያው ሰክረው ቀሩ›› ሲሉ የወነጀሏቸውን ሰዎች ፈለግ ተከትለው ይሁን ወይም የግንባሩ ፖለቲካ አዋጭነት ገብቷቸው ከሳቸው ሌላ የሚያውቅ የለም። ለነገሩ ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ይባል የለ።

 

ሌላው ሬድዋን በወቅቱ ኢህአዴግ ሰላማዊ ትግልን እንደሚያፍን እና ፓርቲያቸውም በሰላማዊ መንገድ መታገል እንዳልቻለ ተቃውሟቸውን እንዲህ ሲሉ ገልፀው ነበር፡-

 

‹‹ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እያጣን የከተማው እንቅስቃሴያችን ለሌሎች መታየት የሚገባውን ያህል አልታየም…. ሰላማዊ ሰልፍንም በተመለከተ በተለይ ባለፈው ዓመት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስልጤ ሕዝብ የመብት ጥያቄ በሕዝብ ውሳኔ እንዲፈታ ከመወሰኑ በፊት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው የፓርቲው ደጋፊ ትዕይንት ሕዝብ እንዲካሄድ በወሰነው መሰረት ሁለት ጊዜ ጠይቀን መከልከላችንን በተለያዩ መድረኮች ገልፀናል።››

 

ይኽ እንግዲህ የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ እና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር፣ ከ10 ዓመት በፊት ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት የሬድዋን ሁሴን ድምጽ ነው፡፡ ‹‹ኢህአዴግ ያፍናል››፤ አማካሪ ሬድዋን ልክ ነዎት! ኢህአዴግ ያፍናል። አጠያያቂው ጉዳይ ግን የባይሎጂ መምህሩ ሬድዋን ለመሆኑ ኢህአዴግን የተቀላቀሉት አፈናው ቆሞ ነው ወይስ የአፈናው ተባባሪ ለመሆን? የሚለው ነው። መቼም አፈናው ቆሞ ነው እንዳንል ያን ጊዜም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ናቸው፣ ዛሬም ጠቅላይ ሚንስትሩ መለስ ናቸው። ያን ጊዜም የኢህአዴግ ሊቀመንበር መለስ ናቸው፤ዛሬም የኢህአዴግ ሊቀመንበር መለስ ቸው፡፡ የተለወጠ ነገር የለም።

 

በነገራችን ላይ በ2002ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ሬድዋን ሰፋ ያለ የሚዲያ ሽፋን የማግኘት ህልማቸው ተሳክቶላቸዋል። ስለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ‹‹ከእኔ´በላይ ላሳር…›› ሲሉም ነበር፡፡ የኢህአዴግ መስመር አሻሚ አይደለም፤ ግልፅ ነው፡፡ለአብዮታዊ ዲሞክራሲው ቅኔ መወድስ ማቅረብ ለፈለገ ሁሉ በእጁ፤ ሁሉ በደጁ እንዲሆን ያደርጋል። ለሬድዋንም የገጠማቸው ይኸው ነው። ተቃዋሚ በነበሩበት ጊዜ በየደረሱበት ‹‹የሚዲያ ያለህ፣ ድምፃችን ይሰማ…›› ሲሉ የምድረበዳ ጩኸት ጮኹ። ሆኖም በንስሃ ወደ ኢህአዴግ በተመለሱ ጊዜ እንኳን ድምፃቸው፣ ሳቃቸውም የሚዲያ ሽፋን አገኘ። ነገር ግን ሌሎች የታፈኑ ድምፆች ዛሬም የምድረበዳ ጩኸታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሬድዋንም ከአፋኙ አንዱ ሆነዋል። ያውም ክፉ አፋኝ። ድክመትን እና ስልትን አብጠርጥሮ የሚያውቅ። እዚህች ጋር ልትገባ የምትችል የፕሮፌሰር ስፍን ወልደማሪያም አንዲት ግጥም ትዝ አለችኝ። እርሷ ‹‹መሰላል መውጣት›› ትሰኛለች፡-

 

መሰላል ለመውጣት፤

አለው ትልቅ ብልሃት።

የላዩን ጨብጦ፤

የታቹን ረግጦ፤

ወደላይ መመልከት…

…ብልሆች የማይጣደፉ፤

ሞልተዋል በያፋፉ!

ዘርግተው የጨበጡትን መርገጥ፤

የመውጣት ህግ ነው የማይለወጥ!

ሲወርዱ ግን ያስፈራል፤

የረገጡትን ያስጨብጣል።

 

ዛሬ ሬድዋን የጨበጡትን እርግጠውታል። የረገጡትንም ጨብጠውታል፡፡ ማጠፊያው የሚያጠረው ግን ለሁለተኛ ጊዜ የረገጡትን ጨብጠው ‹‹ውረዱ›› የተባሉ እለት ነው፡፡ ሆኖም የማታ ማታ የሬድዋን ትግልየምርም ለስልጤ ህዝብ ሳይሆን ወደ ስልጣን ለመውጣት እንደሆነ ታወቀ። እናም የወራቤ ወጣቶች ‹‹ሬድዋን የስልጤን ህዝብ መሰላል አደረጉት›› ሲሉ ተሳለቁ።

 

እንቀጥል፣ በወቅቱ ሬድዋን ተቃዋሚ ፓርቲን ወክለው ፓርላማ የገቡ ቢሆንም፤ በፓርላማውም ተገቢ ውክልና ፍትሀዊ አመዳደብ የለም ሲሉ ለመጽሔቱ ገልፀው ነበር።

 

‹‹በምክር ቤቱ አንድ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች ፓርቲዎች የተወከሉ በመሆኑ የድርጅታችንን አለመወከል በመቃወም ድምፄንአሰምቻለሁ… የሆነ ሆኖ የተወከሉትን ድርጅቶች የአወካከል ሁኔታ ስንመለከት ላንወከል የቻልንበት አላማና ምክንያት አልገባንም፡፡ በስሜት እንጂ በበቂ ምክንያት የተደገፉ አይመስልም። በወቅቱበምክር ቤቱ ቅሬታዬን ከማሰማቴም በላይ ቅሬታውንም ከመድረክ ውጭ ለማስረዳት ሞክሬአለሁ።››

 

ይህ ነው ዛሬም ያለው ትልቁ ችግር። ፓርላማው ፍትሃዊ አይደለም የሚል ማለቴ ነው፡፡ በፓርላማው የሚወጡ አዋጆች ሁሉ ስሜት በፈነቀለው ጭብጨባ እና ሳቅ የሚደገፉ እንጂ በምክንያት የሚደገፉ አይደሉም፡፡ሬድዋንም ይኽንኑ ነው ያረጋገጡልን፡፡ መምህሩ ያን ጊዜ የዚህ ሀሳብ አቀንቃኝ ነበሩ፤ ዛሬ ግን ለፓርላማው ፍትሃዊነት መስካሪ ሆነዋል። እኒህናቸው እንግዲህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ።

 

ስለኢህአዴግ የምርጫ አጭበርባሪነትም ሬድዋን የሀቅ መስክረው ነበር ‹‹….በተቀሩት ምርጫ ክልሎች በተለይ በጉራጌ ዞን በተፈጠሩብን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መራጩ ህዝብ ከጐናችን የነበረ ቢሆንም ውጤታም ልንሆን አልቻልንም።… አዲስ አበባ በሚካሄደው ምርጫ ለመሳተፍ የነበረንን እቅድም በአንዳንድ ምክንያቶች መሰረዝን መርጠናል።››

 

አማካሪ ሬድዋን ጥሩ ብለዋል። እጅግ በጣም ጥሩ። የእርስዎ ፓርቲ በምርጫ 97ም ሆኑ በምርጫ 2002 ሙሉ በሙሉ አሸነፍኩ ያለው ተቃዋሚዎች ልክ ያኔ እርስዎ እንደጮኹት ጩኸት አይነት ‹‹ውጤቱንአጣነው እንጂ መራጩ ህዝብ ከጎናችን ነበር›› እያሉ እየጩኹ ነው። እናሳ! አማካሪ ይኽን ነገር እንዴት ያዩታል? ማለቴ መራጩ ከጎኖት ቆሞኮረጀው ባዶ ሆኖ ሲገኝ?

 

ሬድዋን ‹‹መራጩ ሕዝብ ከጎናችን የነበረ ቢሆንም ውጤታማ ልንሆን አልቻልንም›› የሚለው ወቀሳቸው ‹‹ኢህአዴግ ምርጫን እያጭበረበረ ነው የሚያሸንፈው›› ለሚሉ ተከራካሪዎች አንድ ማስረጃ ነው። ምክንያቱም ሬድዋን ‹‹አጭበረበረኝ›› የሚሉት ኢህአዴግን ነውና። ሆኖም ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው ‹‹አጭበርባሪ›› ሲሉ የወነጀሉትን ድርጅት መቀላቀላቸው ብቻ ሳይሆን ስለፃድቅነቱ ልሳናቸው እስኪዘጋ ድረስ መስበካቸው ነው። ማን ነበረ‹‹በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌላ ሰው ላይ አታድርግ›› ያለው?

 

የሆነ ሆኖ ሬድዋን አና ኢህአዴግ ፍቅርየጀመሩት ከቀጣዩ አጋጣሚ በኋላ ነው፡፡ በ1992 የስልጤ ህዝብ የራስን እድል በራስ እንዲወስን በመደረጉ፣ ከጉራጌ ህዝብ የተለየ ማንነት እንዳለው በሪፈረንደም አስወሰነ፡፡ በዛው አመትበተደረገው የፓርላማ ምርጫም ሬድዋን እና የፓርቲያቸው አመራሮች ኢህአዴግን አሸንፈው ፓርላማ ገቡ፡፡ እናም የዛሬው የኢህአዴግ አመራርእና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማ የገቡት ተቃዋሚ ሆነው ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በፓርላማውብዙም ሳይቆዩ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጳጳሳት የትኛው እንደሰበካቸው ተለይቶ ባይታወቅም፣ የመረጣቸውን ህዝብ አውላላ ሜዳ ላይ ትተውበአብዮታዊ ዲሞክራሲ አምነው ተጠመቁ፡፡ ፓርቲያቸውንም አፍርሰው ወደ እነሲራጅ ፓርቲ ዝውውር አደረጉ። በ1997 ዓ.ም. ከስልጤ ዞን ለደቡብ ክልል ም/ቤት ተወዳድረው አሸናፉ፤የደኢሕዴንም የስራ አስፈፃሚ አባል ሆኑ።

 

ሬድዋን ሁሴን ሲጀምር የስልጤ ተወላጆችን ችግር ከፊት አስቀደሙ፡፡ ኋላምለችግሮቹ ገና መፍትሄ ሳያገኙ ‹‹ችግር ፈጠረብን›› ያሉትን ገዥውን ፓርቲ ተቀላቀሉ። እንዲህ አይነቶቹን ፖለቲከኞች ደግሞተንታኞች ‹‹የፖለቲካ መንገደኞች›› ሲሉ ይተቿቸዋል፡፡ ጠቅለል አድርገውም የወል ስም ሲሰጧቸው ‹‹የብሄረ ኢንተርፕርነሮች (Ethnic entrepreneur)›› ይሏቸዋል፡፡ የፖለቲካ ስልጣን እና ስልጣኑ የሚያመጣውን ጥቅም በማስላት የተወለዱበትን ብሔር ቅሬታዎች በማግለብለብራሳቸውን ጉምቱ ፖለቲከኛ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይነቀንቁት ቋጥኝ የሌላቸው ሬድዋንም ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡ በመቃወም ያገኟቸው ጥቅሞች አነሱባቸው፤ እናም ወደ ተቃወሙት ስርዓት ተቀላቀሉ፡፡ በምክንያት አነሳነው ያሉት የብሔራቸው ጥያቄም ስልጣን ባገኙበት አፍታ ሞቶ ተቀበረ።

 

ከዚህ በተጨማሪም ሬድዋን የኢህአዴግመስመር በትክክል ገብቷቸው ነው የተቀላቀሉት ብለን እንዳናስብ በምርጫ 2002 የሰነዘሯቸው ሀሳቦች ገትረው መያዛቸው ነው፡፡ ኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስለቡድን መብት እንጂ በተናጠል ስለግለሰብ መብት እንደማይጨነቅ ለ20 አመት የተናገረው ነው። በቅርቡ መቀሌላይ በተከበረው የከተሞች ቀንም ከህወሓት የ‹‹ሀሳብ መሀንዲሶች›› አንዱ አባይ ፀሐዬ ‹‹የግለሰብ መብት ጥያቄ የተሸነፈ፤ ግን ያልሞተእይታ ነው›› ሲሉ የግለሰብ መብት ጥያቄ የሚያነሱ ለቲከኞችን በግልፅ ተችተዋል። አዲሱ ኢህአዴግ ሬድዋን ግን በምርጫ 2002 ክርክር ላይ እንዲህ አሉ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲየግለሰብ መብትንም ያከብራል፡፡›› …አቤት ይኽን ጊዜ ነበራ የኢህአዴግ አመራሮች ምን ያህል ተሸማቀው ይሆን? አንድዬ ነው የሚያውቀው።

 

የሬድዋን እና የኢህአዴግ ስመር አልተግባብቶ የሆነው በዚህ ብቻ አይደለም። ስለአፄ ሚኒሊክ ኢህአዴግ የሚለው እና ሬድዋን የሚሉት አራባና ቆቦም ነው፡፡ ኢህአዴግ ‹‹ለኤርትራ መገንጠል የመጀመሪያም የመጨረሻም ተጠያቂ አፄ ሚኒልክ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ጣሊያንን አደዋ ላይ ከአሸነፉ በኋላእስከ ኤርትራ ዘመተው፤ ከኤርትራም ቢያባሩት ኖሮ ኤርትራውያኖች የእንገንጠል ጥያቄ አንስተው አይታገሉም፤ ምንሊክ ግን ከመረብበኋላ አያገባኝም ብለው አደዋ ላይ ቆሙ›› ሲል ተደጋጋሚ ጊዜ ሚኒሊክን ይከሳል። በዛ ምርጫ ደግሞ ሬድዋን ለተቃዋሚዎች ሳይሆን ለኢህአዴግ ክስ በቂ መልስ ሰጡ፡፡እንዲህ ሲሉ፡-

 

‹‹…ምንሊክ አድዋ ላይ አሸንፈው፣ መረብን አልሻገርም ያሉት ኤርትራን ለማስገንጠል ስለፈለጉ፤ አገር ለማስካድ ስለፈለጉ አልነበረም። ከዚያ በላይ ቢሄዱ ኖሮ የአድዋ ድል አብሮ ይከስም ነበር፡፡ መላው ኢትዮጵያም በጣሊያን እጅ እንደምትወድቅ አይተው ቤቴ ተመልሼ ውስጤን አጠናክሬ፣ ትንፋሽ ወስጄ ልመለስብለው ያደረጉት ብልህነት መሆኑን ሊገባን ይገባል።››

 

ለምን ይዋሻል በወቅቱ ለሬድዋን መልስ ከመቀመጫዬ ተነስቼ አጨብጭቤላቸው ነበር። ወዲያውም በቃ እኒህ ሰው ኢህአዴግ አይደሉም ብዬ አሰብኩ። ግን ምን ዋጋ አለው…

 

እንዲህ እንዲህ እያለ ምርጫ 2002 መድረሴ ነው ይል ጀመረ፡፡ ይኼን ጊዜም ነው ሬድዋን ሁሴን የአዲስ አበባውን የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊነት የተቀላቀሉት፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ኢህአዴግ ከምርጫ 97 ሽንፈቱሁለት ነገር መማሩ ነው። አንዱ ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች ምህዳር ማጥበብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የራሱን አባላት ማብዛት ላይ ማተኮርእንዳለበት ነው። ይህም ትምህርት እውን ይሆን ዘንድ ግዳጁ በሬድዋን ሁሴን ላይ ተጣለ። መመልመል፣ መመልመል፣ መመልመል…. የተመለመሉትንም ማጥመቅ፣ ማጥመቅ፣ ማጥመቅ… የቀን ተቀን ስራቸው ሆነ። ፊቼ እና አላጌም ዋናው ምኩራባቸው ሆኑ።

 

ምርጫ 2002ም ደረሰ። በዋዜማውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ተካሄደ፡፡ በአብዛኛው የክርክር መድረኮችም ሬድዋን ሁሴን ቋሚ ተሰላፊ ሆኑ። በየመድረኩም የተቃዋሚዎቹን የፖለቲካ ፕሮግራም ሳይሆን የተከራካሪዎቹ ማንነት ላይበማተኮር የማጣጣል እና የማጠቋቆር ዘመቻ ከፈቱ። የበርካታ ሰዎችም መነጋገሪያ ለመሆንበቁ-አማካሪ ሬድዋን ሁሴን።

 

እንግዲህ አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ከአማካሪ ፋሲል ናሆም በምን ይለያሉ? ፋሲል ከደርግ ጋር ወግነው ኢህአዴግ በበረሃው ትግልተደምስሶ ይጠፋ ዘንድ የሚያውቁትን ሁሉ መከሩ፣ ዘከሩ፡፡ ሆኖም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆነና ደርግ ተሸንፎ ኢህአዴግ አሸናፊ ሆነ። ፋሲል ናሆምም ሠልፋቸውን ከኢህአዴግ ጋር አስተካከሉ። …ሬድዋን ሁሴንም ከተቃዋሚው ድርጅታቸው ‹‹ስሕዴፓ›› ጋር ሆነው ኢህአዴግ ይወድቅ ዘንድ የቻሉትን ያህል ጣሩ፤ አልፎ ተርፎም በስልጤ ዞን በተደረገው ሁለተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ኢህአዴግን አሸንፈው ፓርላማ ገቡ።

 

ከለታት አንድ ቀንም በፓርላማው ሳሉ ከኢህአዴግ ጋር በአይን ፍቅር ወደቁ፡፡ እነሆም ከዚህ አለት ጀምሮ አሰላለፋቸውን ቀየሩ፡፡ ፋሲል ናሆም መንግስቱ ኃ/ማሪያምን በመከሩበት አንደበት መለስ ዜናዊን እንደመከሩትሁሉ፤ ሬድዋን ሁሴንም ኢህአዴግን ሲቃወሙና ሲተቹበት በነበረው አንደበታቸው ጠቅላይ ሚንስትሩን እየመከሩ ነው። ‹‹በቃክ፣ ውረድ››ያሉትን ኢህአዴግንም እየመሩ ነው። (እንዴት ነው ነገሩ ማሊያ መቀያየሩ ለጠቅላይ ሚንስትሩአማካሪነት ለመታጨት እንደ አንድ መስፈርት ይወሰድ ይሆን እንዴ?)

 

መቼም አንድ ሰው ምልዑ ሊባል የሚችለው ወይ የህግ ትምህርት አሊያም ባይሎጂበመማሩ ብቻ አይደለም። ለራሱ ህሊና ተገዥ ሲሆን ነው። በእምነቱም ሳይናወፅ ሲቀር ነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ መለስ ‹‹ትክክለኛ ባይሆንም የራሱ አቋም ያለውን ሰው አከብራለሁ›› ብለው ነበር። እናሳ! እንዲህ ጀንበር በሰረቀችቁጥር አቋማቸውን እንደሸሚዝ የሚቀያይሩ አማካሪዎቻቸውንስ ያከብሯቸው ይሆን?

 

የሆነ ሆኖ ለስርአቱ ብልሹነት የአማካሪዎቹም አቋመ ፅኑ አልባነት እና የመርህ ሰው አለመሆን አንዱ ምክንያት ይመስለኛል።

 

ምንጭ፦ ፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ