ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም

የዶ/ር ዳኛቸው የጅብ እርሻ የኢትዮጵያን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ጽሑፍ ነበር፤ ብዙ ሰዎች እንዳነበቡት ተስፋ አደርጋለሁ፤ ካላነበቡት ፈልገው ቢያነብቡት ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ይጠቅማል፤ ዳኛቸው ከመንገድ ላይ ያገኛትን የአነጋገር ፈሊጥ ለቁም-ነገር አበቃት፤ ጅብ በተፈጥሮ ባሕርዩ አያርስም፤ ፍሬም አይለቅምም፤ ድንገት ተሳስቶ ቢያርስም እስቲበቅል ለመጠበቅ ትእግስቱ የለውም፤ ዳኛቸውም የጅቡን እርሻ ‹‹በአንድ በኩል የኢሕአዴግን አካሄድ በሌላ በኩል በተቃዋሚ ፓርቲዎች መሀከል የሚካሄደውን ሁኔታ ሊያስረዳልኝ/ሊገልፅልኝ የሚችል…›› ነው በማለት ይጠቀምበታል።

 

በኢትዮጵያ የነገሠው ለምንም ዓይነትና ለማናቸውም ጥያቄ ብቸኛ መልስ አለኝ የሚል አባዜ የተጠናወተው ሥርዓት ለቤት እጥረት ጥያቄ መልሱ ኮንዶሚኒየም ነው፤ ለመሬት ጥያቄ መልሱ ሊዝ ነው፤ ለብሔር የእኩልነት ጥያቄ መልሱ ፌዴራሊዝም ነው፤ ለክህሎት ጥያቄ መልሱ ሥልጠነና ነው፤ እያለ ሕዝቡን ያደነዝዘዋል፤ ስለዚህም በነፃነትና በእኩልነት፣ በሥልጠናና በትምህርት፣ በብዛትና በጥራት… መሀከል ያለውን ልዩነት ለመከራክር ወይም ለመሞገት ስለማይፈቅድ ዲሞክራሲያዊ ባሕርይ የለውም፤ይኸውም ባሕርዩ ለክርክርና ለሙግት ክፍት አለመሆኑ -- ለእውቀት እርምጃ የማይበጅ እንቅፋት ያደርገዋል፤ እንግዲህ አንድ ማኅበረሰብ በአንድ በኩል ለዴሞክራሲ ፋይዳዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለእውቀት ማስፋፋት ፋይዳዎች መንገዶቹና በሮቹ ሁሉ ከተዘጉበት የመታደስና የመሻሻል ዕድሉ ታፍኖአል ማለት ነው፤ አፈናውን የሚያጠነክረውና ይበልጥ አስከፊ የሚያደርገው የዴሞክራሲው መንገድ መዘጋት በዴሞክራሲ አስመሳይ ብልጠት፣ የእውቀቱም በር መዘጋት እንደዚሁ በአስመሳይ ብልጠት መሆኑ ነው።

 

በአጭር ጊዜ ውስጥ ዳኛቸው ያስተዋለው የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ምንጩ በሥልጣንና በእውቀት መሀከል የተፈጠረው የቁርባን ጋብቻ መሆኑን ነው፤ የሥልጣንና የፊደል እውቀት ዲቃላ ሥልጠና ይሆናል፤ ዲቃላው ሥልጠና እውቀትን ተክቶ ለማናቸውም ጥያቄ መልሱን የሚቀዳው ከአንድ የሥልጣን ምንጭ ብቻ መሆኑን ያውጃል፤ ዶር. ዳኛቸው ‹‹ሁሉንም በጠቅላላ ቋጠሮ ውስጥ ከ(ት)ቶ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ወጥ በሆነ ፖለቲካዊ አተያይ እንዲመራና መፍትሔውም ለሁሉም አንድ ወጥ የሆነ መልስ ብቻ እንዳላቸው አድርጎ የማቅረብ አባዜ ነው።›› (ፍትሕ የካቲት 2/2004) በማለት የገለጸው ይህንን ጸረ እውቀት የሆነ የሥልጠና ውጤት ነው፤ ሥልጡን አገልጋይ ወይም ሥልጡን አሽከር ትእዛዝ እየጠበቀ፣ ትእዛዝ እየተቀበለ በትእዛዝ የሚሠራና የሚያሠራ ነው፤ እንደዚህ ዓይነቱ ሥልጡን አባቱ ሥልጣን ሲሆን እናቱ ፊደልዋን ጨርሳ ንባብ የጀመረች ነች፣ ከመሃይምነት ለመውጣትዋ ዲፕሎማ ተሸልማለች፤ ስለዚህም ተምራለች፤ ስለዚህም ምሁር ነች፤ ስለዚህም የፊደል ችሎታዋን ለሥልጣን አገልጋይነት ማዋል ለሹመት ያበቃታል፤ እንዲህም እያለ ሥልጣንና ሥልጡን አገልጋይነት እየተደጋገፉና እየተባዙ ይቀጥላሉ።

 

የደርግ ሥልጡን አገልጋዮች እውቀትን በትክክለኛው መንገድ የማካበቱን የተመሰከረለት መንገድ ለመለወጥ ተወራጭተው ነበር፤ መጀመሪያ ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያውን መመዘኛ በትምህርት መሆኑ ቀርቶ በ‹‹መደብ ጀርባ›› እንዲሆን አደረጉ፤ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨበርስቲ ከገቡ በኋላ ፈተናው የሚሰጠው የመደብ ጀርባ እየታየ ባለመሆኑ ብዙዎቹ በመደብ ጀርባቸው የገቡት ለገና ወደየቤታቸው ይመለሱ ጀመር፣ ተማሪዎቹ Charismas Graduates ይሏቸው ነበር፤ በኋላም ሥልጡን አገልጋዮች ትምህርትን ለሰፊው ሕዝብ በአጭር ጊዜ ለማዳረስ በነበራቸው ጉጉት የዩኒቨርስቲውን የትምህርት ጊዜ ከአራት ዓመታት ወደ ሦስት ለወጡት፤ የሦስት ዓመቱ ተመራቂዎች ሊጨርሱ ስድስት ወር ሲቀራቸው ተማሪዎች አጉረመረሙና ጥናት ተደረገ፤ ካልተሳሳትሁ ወደዘጠና ከመቶ የሚጠጉት ተማሪዎች መመረቁ እንዲተላለፍላቸውና አንድ ዓመት እንዲጨመርላቸው ጠየቁ፤ ጉዳዩ ወደ ዩኒቨርስቲው የአመራር ጉባኤ ቀረበና የጦፈ ክርክር ተደረገ፤ በዶር. ዱሪ የሚመራው የዩኒቨርስቲው አመራር የተማሪዎቹን ጥያቄ በመደገፍ አንድ ዓመት እነዲጨመር አጥብቆ ተከራከረ፤ ሌሎቻችን ደግሞ ቀደም ሲል ወደ ሦስት ዓመት ሲለወጥ በጣም ተቃውመን የነበርነው አንድ ዓመት ይጨመር የሚለውን በጣም ተቃወምን፤ ምክንያቱም አንደኛ ተማሪዎቹ በሦስት ዓመት እንደሚመረቁ ተነግሮአቸው የገቡ ናቸውና ውሉ መፈጸም ነበረበት፤ ሁለተኛ የሦስት ዓመቱ ትምህርት ከአራት ዓመቱ የተሻለ መሆኑንና አለመሆኑን ማወቅ የሚቻለው እነዚህ ‹‹በለብ-ለብ›› የተመረቁት በሥራ ሲፈተኑ ነው፤ በማለት ተከራክረን አሸነፍን፤ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ተንጫጩ።

 

የዛሬውን የ32 ዩኒቨርስቲዎች ጥራት ዳኛቸው በአጠቃላይ ነካክቶታል፤ (አዲስ ጉዳይ፣ የካቲት 2004)፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ተሽሮ ስልጠና የሚሰበክበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤›› ይላል ዳኛቸው፤ ከዚያ በላይ ለማለት በበኩሌ አልችልም፤ ግን የምሰማው ሁሉ ለብ-ለብ በጣም የተሻለ እንደነበረ ነው፤ ዓላማቸው ሥልጠና በመሆኑ ለድኅረ-ምረቃ የኢሕአዴግ አባል ያለሆነ አለመቀበላቸው ዩኒቨርሲቲ የሚለውን ስያሜ ያዋርደዋል፤ ነገሩ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ትምህርት ያልነገራቸው ሰዎች ስለትምህርት አመራር ሲሰጡ ከባዱንና ውስብስቡን ጉዳይ በቀላል እንደሚመለከቱት ሳይታለም የተፈታ ነው።

 

በጣም ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸውን ሠላሳ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ወደስማቸው ለማስጠጋት ምን ማድረግ ያስፈልጋል? እንደምንም ብሎ እያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ የሚባለው በምርጥ አስተማሪዎች፣ በተሙዋላ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-ሙከራ፣ በተሙዋላ የኮምፒዩተር አገልግሎት የተደገፈ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መታጀብ አለበት፤ ሠላሳ ሁለት ጥሩ ጥሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው።

 

ምንጭ፦ ፍትህ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ