የፈራ ይመለስ
ተመስገን ደሳለኝ
የፈራ ይመለስ። አዎ ይመለስ! ግን ከየት ነው የሚመለሰው? መችስ ወጣና ነው የሚመለሰው? እንዴት ነው ነገሩ ሁሉ እኮ፡-
መች ተዋጋና
ያስባል ገና
መሰለብንሳ። እውነት ግን በዛሬ ቀን ስለፍርሃት መወራት አለበት? ያውም በታላቁ የዐድዋ ድል ቀን፤ ለነገሩ ይሄ ድል ብቻ አይደለም-ከዐድዋ፤ የ‹‹ፍርሃት ኪኒን›› ፋርማሲስቱም ከዐድዋ ናቸው መሰለኝ፡፡ አይ ዐድዋ! ዋ አንቺ ዐድዋ…። ስለዐድዋ ብዙ ተበሎአል። ብዙም ተነግሮአል። ሆኖመ ከሁሉም ከሁሉም ለልብ የሚቀርበው ኢትዮጵያውያን አዝማሪዎች የገቡበትን የፍርሃት ጠርሙስ ፈንቅላ የወጣችው ጂኒ (ጂጂ)፣ ያች የጎበዝ ወዳጅ ‹‹ትናገር ዐድዋ›› ስትል በዛ በተስረቅራቂ ድምጿ ያቀነቀነችው ነው። አዎን! ትናገር ዐድዋ፡-
ዐድዋ ዛሬ ናት፣ ዕድዋ ትላት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት…
አየህ! ይህንን ነው እያልኩህ ያለሁት። የነፃነትህ ዋጋ ‹‹ሰው ተከፍሎበታል›› ያውም ከደምና አጥንት፡፡ መቼም ጀግናው ኢህአዴግ ‹‹እኔ ከሌለሁ አገሪቱ ትፈራርሳለች›› የሚለውን ‹‹ፖለቲካ›› እንደቧልት እንጂ እንደቁምነገር እንደማትወስደው ተስፋ አደርጋለሁ። ኃ/ስላሴ ነገሱ፣ ኃ/ስላሴ ወረዱ፤ ደርግ ገለበጠ፣ ደርግ ወደቀ፤ ኢህአዴግ ታገለ፣ ኢህአዴግ አቸነፈ ፖለቲካ ነው። በተቀረ ኢትዮጵያ ድሮም ነበረች፣ ዛሬም አለች፣ እመነኝ ነገም ትኖራለች፡፡ እናም አቦይ ስብሃት ነጋ ‹‹ከኢህአዴግ በቀር ይህችን ሀገር እያስተዳደረ ሊያኖራት የሚችል የለም›› የሚሉትን ፕሮፓጋንዳም እርሳው። ጂጂን (እጅጋየሁ ሽባባውን) ግን አድምጣት፡፡ እርሷ ብርቱ ሴት ናትና። ከወራት በፊትም በራሷ ድምፅ በለቀቀችው ግጥም ‹‹በቃኝ አትልም ወይ›› ብላህ እንደነበርም አስታውስ። ይህ ካልገባህም አብራርታ እንድትነግርህ ልትጠይቃት ትችላለህ ‹‹ምኑ ነው የሚበቃኝ?›› ብለህ። ለዚህ የሚሆን መልስ አላት። እንዲህ የሚል፡-
…በጣም በቃህ በሉት ዘራፊውን መንግስት
ክህደት ካልሆነ አያስተምር ሌላ
…መሪ ነው አትበሉት ይኽን ተሳዳቢ…
የእኛ ጂጂ እንዲህ ነች። መቼም እሷ ያአባቷ ልጅ ናት። ስለአንድነት ስትሰብክም አቻ የላትም። የምትዘፍነውም ‹‹አዝማሪ›› ለመባል እና ተያይዘው የሚመጡ ጥቅማ ጥቅሞችን አስልታ አይደለም። የምርም የጥበብ ሰው ስለሆነች ነው። በአናቱም ሀገሯን ስለምትወድ ነው።
ፍቅር ወዴት ወዴት ዘመም ዘመም
ሀገርም አለችኝ ሀገር የእኔ ህመም
ማለቷም ለዚሁ ነው። ቁርጥ የቴዲ አፍሮ ግልባጭ፣ ወይም ቴዲ የጂጂ ግልባጭ ይሉሀልም ይሄ ነው፣ ሌላ አይደለም። ሁለቱም ከግል ጥቅም በዘለለ ሄደዋልና።
የሆነ ሆኖ ዛሬ አርብ ነው፤ እለቱም የአድዋ በዓል ነው። እናም ዛሬ ሽብር በሽብር የሚሆኑት፣ ደርሶ ፍርሃት ፍርሃት የሚላቸው ይበዛሉ ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማይናወፅ አቋም የነበረው አንድ ንጉስ ነበር፤ ቴዎድሮስ የሚባል ። ይህ ሰው የኢትዮጵያ ዳር ድንበር እስከ ባድሜ ድረስ ነው የሚሉትን ብቻ ሳይሆን ቀይ ባህር ድረስ ነው የሚሉትንም አይቀበልም። ለምን መሰለህ? በቴዎድሮስ እሳቤ የኢትዮጵያ ግዛት እየሩሳሌምንም ስለሚያጠቃልል ነው።
በእርግጥ ሰውየው በዘመኑ ይኽን አላሳካም። ነገር ግን አንድ ቀን ያሳካዋል የሚል ትንግርት ነበረ፤ ወይም አለ። ያ ቀን እየሩሳሌምን ወደ ኢትዮጵያ የሚጠቀልልበት ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ይህ ንግርት እውን የሚሆንበት እለትም አርብ ቀን ነው ይባላል። እናም እንዲህ የሚል ግጥም ተገጠመ፡-
‹‹ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሣ ብሎ ስም
አርብ አርብ ይሸበራል እየሩሳሌም››
ዛሬ ደግሞ አርብ ብቻውን አልመጣም። ታላቁን የአድዋን ድልም አስከትሎ ነው የመጣው፡፡ ድርብ በዓል ይሉሃልም ይሄ ነው።
በዚህ እለትም ስለ‹‹ፍርሃት›› መፃፍ ፈራሁ፤ ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ምድር ለለውጥ ለመነሳት የሚፈራ ይኖራል ብሎ መጠርጠሩም በራሱ አስፈራኝ። ያውም የራስ አገር መንግስትን ስለመፍራት መፃፍ። ፍራቻዬ ሲፈታተነኝም ብዕሬን አስቀምጬ ላፕቶፔን መነካካት ቀጠልኩ። ኢሜል አካውንቴ አዲስ ነገር እንዳለው ለማረጋገጥም ከፈትኩ፤ አዲስ ነገርም አገኘሁበት። ከአንድ ሰው የተላከ አንድ መልዕክት አለው። መልእክቱንም ከፈትኩት። ‹‹ተመስገን እንደምን ከርመሃል? መቼስ ይህችን ፅሁፍ ስታነብ ይህ ደግሞ ማን ነው? ምንስ ፈልጎ ነው የሚነዘንዘኝ ብለህ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ›› ይልና ፀሀፊው የራሱን ስም ጠቅሶ የንግድ ስራ ኮሌጅ ተማሪ እና የ20 አመት ብላቴና እንደሆነ ነገረኝ። ይኽ የ20 አመት ወጣት የነብር ጣት (አሁን አሁን ወጣት የአብዮትም ጣት እየሆነ ነው) ‹‹የፍርሃት ካባችንን አውልቀን ልንጥለው ይገባናል!›› በሚል ርዕስ የፃፈውን አንድ ፅሁፍም እንዳነብ ጋበዘኝ። ሙሉውንም አንብቤ ጨረስኩት። የፅሁፉ መልእክት ከሞላ ጎደል ይኽ ነው ‹‹ፍርሃት ማለት በልባችን ተቀብሮ የሚገኝ አንዳች ነገር ሲሆን ያ ተቀብሮ የሚገኘው እና ሰላማችንን የሚነሳንን ነገር ለማውጣት በምንዳዳበት ጊዜ እንዳናወጣው የሚዳርገን አንዳች ሀይል ነው።… ፍርሃትን ማናችንም ቢሆን በር ልንከፍትለት አይገባም። በራችንን ከከፈትንለት ግን ልባችን ውስጥ ተሸንቅሮ ዘወትር ሰላማችንን ይነሳናል። ማናችንም ብንሆን የሚሰማንን ስሜት፣ በግልፅ ከመግለፅ መቆጠብ የለብንም። በጣም የሚገርመኝ እና የሚደንቀኝ ነገር ቢኖር መንግስትን የሚመለከት ነገር መናገርም ሆነ መንግስትን መተቸት በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ድፍረት ይቆጠራል። የምንናገረው ነገር እውነት እስከሆነ ድረስ ግን እንደ ድፍረት ሳይሆን እንደ ሃቅ ሊቆጠር ይገባል።
ነገር ግን በውስጣችን ተሸንቁሮ የሚገኘው ፍርሃት ጫና እያሳደረብን እንደ ሃቅ ሳይሆን እንደ ድፍረት እየተቆጠረ ይገኛል፡፡ እስከ መቼ ነው ግን ይህን ፍርሃታችንን በር የምንከፍትለት?›› ሲልም ይጠይቃል፤ ወጣቱ ፀሀፊ።
እንግዲህ ይኽ የ20 አመት ወጣት መልእክት ነው፡፡ እናም እንዲህ አሰብኩ ‹‹ቀኑ ምንም እንኳ የፍርሃት ሳይሆን የአባቶቻችንና የእናቶቻችን የጀግንነት ታሪክ የሚወሳበት እለተ ዐድዋ ቢሆንም ስለፍርሃት መወራት አለበት።›› አስቤም ስጨርስ ላፕቶፔን ከድኜ የጀመርኩትን ርዕስ ለመጨረስ ተበረታታሁ። በሰራ አከላቴም የደስታ ስሜት ሰረፀ፤ በሀገሬ ወጣቶች ሁልም እንደኮራው ነው። ቢያንስ በያሉበት ሆነው በአገር ጉዳይ ላይ መፍራት እንዳሌለባቸው ያውቃሉ። የወጣቱም ፁሁፍ የብዙ ወጣቶች አቋም እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁ። ስለዐድዋ ብዙ እናውቃለን። ዐድዋ ትውልድና ዘመን ተሻጋሪም እንደሆነ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም፣ አንድ እንኳ። በእርግጥ ለጭቆና እጅ ያለመስጠት ታሪካችን በዐድዋ ብቻ የተገደበ አይደለም። የ66ቱ አብዮት፣በሶማሊያ ወረራ፣ በባድሜው ጦርነት፣ በ1997ቱ ህዝባዊ አብዮት…ዓመት አውደዓመት ድገምና የተባለለት ነው፡፡ የዐድዋ መንፈስ።
አዎ! ‹‹ፍርሃት››ን እና ‹‹ኑሮ››ን ግራና ቀኝ አድርጎ መመዘን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹ሞት የማይፈሩ ወጣቶች›› በሚል ርዕስ በፃፍኩት ፅሁፍ ላይ ስለሀገሬ ወጣቶች፣ ስለእድሜ አቻዎቼ ታሪክ ሰሪነት እና ትዕግስታቸው ባለቀ ጊዜም ለለውጥ ‹‹ሆ›› ካሉ ማንንም፣ ምንንም እንደማይፈሩ አስታውሼ ነበር፡፡ ይህ ወጣትም ከእነዛ ከ‹‹ተስፋዎቻችን››አንዱ ነው። ገና ተማሪ ነው። የዘመኑን ወጣትም ይወክላል።
ደግሞም በአሁኑ ወቅት ያለው የሀገራችን ሁኔታ ከመፍራት ይልቅ እንድትቆጣ የሚገፋፋህ ነው። እንደምታውቀው የሀገሬ ገበሬ እህሉን (ምርቱን) በጎተራው የሚከተው በትህሳስ እና በጥር ነው። ለ3 ሺ አመትም ጥር ወር የጥጋብ በመሆኑ የሰርግ እና የድግስ ወር እንደሆነ ቆይቷል። በጥር፣ በየካቲት… ኑሮ የሚረክስበት ነው። የእህል ዋጋ የሚወርድበት ነው። ሌላው ቀርቶ በጨካኙ ኮለኔል መንግስቱ ዘመንም ይህ ልማድ አልተፋለሰም። በእነዚህ ወቅቶች ኑሮ ረክሷልና። አሁን ግን ይሄ ታሪክ ሆኖአል። በጥርም በየካቲትም የእህል ዋጋ ከሐምሌና ነሐሴም በላይ ጨምሮአል። ምንአልባት በዚህ መረጃ ካልተስማማህ የሰሞኑን የእህል ዋጋ ከገበያው ጠይቀህ ማረጋገጥ ትችላለህ።
ሌላም ‹‹አስቆጪ›› ነገር ልጨምርልህ። በእርግጥ አንተም ታውቀዋለህ፡፡ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሆነህ የህብረተሰብ (Geography) ትምህርት አስተማሪህ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ (Tower) ነች›› ሲሉ ሰምተሀቸዋል። ነገር ግን እመነኝ ይሄ ድሮ እንጂ ዛሬ ታሪክ ሆኖአል። ታሪከ የሆነው ግን ኢትዮጵያ የውሃ ማማ መሆኑዋ አይደለም። ውሃ እያላት ዜጎቹዋ ውሃ የሚጠሙባት ሀገር መሆንዋ እንጂ። መቼም ለዚህ ተጠያቂው ከመንግስት በቀር ማንም ሊሆን አይችልም። እናም ዙሪያህን ተመልከት ወጣት አዛውንቱ፣ ሴት ወንዱ፣ ህፃን አዋቂው ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላው ቀበሌ፣ ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው መንደር ውሃ ፍለጋ እየተንከራተተ ነው። በደንብ አድምጠኝ እያወራሁ ያለሁት ስለነዳጅ መጥፋት አይደለም፤ ስለውሃ መጥፋት ነው። የእግዜሩ ውሃ እንኳ በአቅሙ ኢትዮጵያውያን በቀላሉ የማያገኙት የቅንጦት መጠጥ ሆኖአል። የመብራትን ነገር ባናነሳው ይሻላል። ደጋግመን የተነጋገርነው ነውና። አምባገነኑ መንግስቱ ኃ/ማርያም እንኳ መብራት በፈረቃ መሆኑን በሰማ ጊዜ ‹‹ያን ሁሉ ግድብ የት አድርገውት ነው፣ መብራት በፈረቃ የሆነው?›› ሲል ተሳልቋል። ይህችን ፅሁፍ እየፃፍኩ ሳለም መብራት ስንቴ ጠፍቶ እንደመጣ አልነግርህም፡፡ የፍትህ እና የመልካም አስተዳደሩን ነገር ተወው። በዚህ ጉዳይ ተቺዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሱ መንግስትም እንዳልሆነለት ይስማማልና።
ይሄም ሆኖ ዝምታን መርጠሀል። በእርግጥ ፈርተህ ነው አልልም፡፡ እንደማትፈራ አውቃለሁና። ዳሩ ለምንስ ትፈራለህ? ህግ እስካልጣስክ ድረስ፣ ህገ- መንግስቱ ላይ የተቀመጡትን መብቶችህን ተጠቅመህ ያሻህን ማድረግ ትችላለህ። አንተ ህግ አክብረህ ስትቆጣ፣ እነሱ ህግ ጥሰው ቁጣህን ለማፈን ከሞከሩ ስጋት አይግባህ፣ አንድ እንጂ ዘጠኝ ሞት አይመጣብህም! ብትታሰርም አትሟሟም።
የሆነ ሆኖ ከላይ ያየናቸው የ‹‹ደካማ መንግስት መገለጫዎች›› ቁጣ ለመቀስቀስ በቂ ናቸው። ነገር ግን ታግሰሃል። በእርግጥ ትዕግስት ጥሩ ነው። ‹‹ትዕግስትህ እስከመቼ ነው?›› ብዬ አልጠይቅህም። ጥፋታቸውን የማያምኑት ትላልቆቹ ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም ኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ፣ ፖለቲካ አያገባኝም የሚሉትም ናቸው። ለምሳሌ ከወራት በፊት በተካሄደው በአለም የሩጫ ሻምፒዮን ውድድር ላይ ውጤት ያጡ አሰልጣኞች የተናገሩትን ሰምተሀል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ዛሬም በዛው ሀላፊነት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ማለትም ይህች ናት፡፡ ተጠያቂ ያሌለባት ሀገር። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መንግስትና በቁጥጥሩ ስር ያሉት ሚዲያዎች ይህንን ሁሉ ጥፋት እና ክስረት ከማመን ይልቅ ገልብጠው ይነግሩሀል፡፡ እናም ኢኮኖሚያችን አደገ፣ ተመነደገ፣ ኢትዮጵያ አበበች… ሲሉ መስማቱ በራሱ ደም ያፈላል። ደግሞ ደም ማፍላት ብቻ አይደለም…
እንዲህ አይነት ተጠያቂነት የሌለበት መንግስት በየትም አለም የለም፡፡ ህዝብ የሚለው ሌላ፣ እነሱ የሚሉት ሌላ። አዎ! እደግመዋለሁ ይህ አይነቱ መንግስት ከባቢሎን (የቋንቋ መደበላለቅ) በስተቀር በየትም ተከስቶ አያውቅም። ዛሬ ኢትዮጵያዊ ‹‹ኑሮ እንዴት ነው?›› ተብሎ ሲጠየቅ የሚመልሰው መልስ ግልፅ ነው። ‹‹ከነገ ዛሬ ይሻላል፡፡›› የሚል ነው። እኔም ይሄንን ነው እያልኩ ያለሁት።
በእርግጥም አሁን አሁን ገናና በነበረችው ኢትዮጵያ ከኢህአዴግ አመራር በቀር ማንም ነገን ተስፋ አያደርግም። ለ20 አመት ያየነውም ይህንኑ ነው። ኢህአዴግ የዛሬን እዳ በነገ ተስፋ እያንጠለጠለ 40 እና 50 አመት በስልጣን ላይ ሆኖ መጓዝ ይፈልጋል። ነገን በጣም ይወዳታል። ነገን በጣም ያፈቅራታል። ነገን አጥብቆ ያመልካታል። ነገን የመና ቀን አድርጎ ይነግርሃል። እናም ሲያሻው ‹‹የ5 አመት እቅድ›› ይልሃል። ያ የተባለው አምስት አመት እንደዋዛ ሲያልፍ ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የሚባል ሌላ የ5 አመት ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥሃል። ይህም አማኝ ሲያጣ ‹‹የአባይ ግድብ ተደፈረ፣ ቦንድ፣ ቦርድ፣…›› ገለመሌ ሲል ይደልልሃል። መቼም ይህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳ ከ‹‹ፀብ አጫሪነት›› ተለይቶ አይታይም። ወይም የዚህ ግልባጭ፡-
‹‹አትነሳም ወይ
አትነሳም ወይ…››
የሚል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም እንዲህ አይነት ስሜት ቢሰማህ እንኳ አሁንም ጥፋቱ የአንተ አይደለም። ተጠያቂው ራሱ ሰላማዊ ተቃውሞህን የገለጽክበት መንግስት እና ፕሮፓጋንዳው ነው።
የመንግስት ዋነኛ የስራ ድርሻ ከህዝብ ላይ በኮንትራት በወሰደው ስልጣን ሀገር ማስተዳደር ነው። ሀገር ማስተዳደር ሲባል ደግሞ ተራራ እና ወንዙን ወይም ወሰን መጠበቅ አይደለም። ህዝብን የፍትህ ርትዕ ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ግብርን ጨምሮ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ገቢ እና ሀብት ህዝብን መመገብ ነው። ይህን ማድረግ ከተሳነው ኮንትራቱ ተቋረጠ ማለት ነው። ኮንትራት የሚቋረጠው ደግሞ በተቀባይ ፍላጎት ሳይሆን በሰጪው ነው። ሰጪው ደግሞ አንተ ነህ። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚንስትሩ “ህዝቡ እንደአረብ ሀገራት ሊያምጽብን ይችል ይሆናል ብለው አልሰጉም ወይ” ተብለው ሲጠየቁ (ምንም እንኳ የሰጉ ቢሆንም) “ህዝቡ የአምስት አመት ኮንትራት የሰጠን በቅርቡ ነው ስለዚህም ሊያምጽብን አይችልም” ሲሉ የመሰሉት ለዚህ ነው፡፡ በእርግጥ በእንዲህ አይነት ጊዜ (መንግስት ቃል የገባውን ማሳካት ባልቻለ ጊዜ) በሌሎች ሀገራት ራሱ መንግስት ነው ይቅርታ ጠይቆ በፍቃዱ ስልጣን የሚለቀው። ይሄ በየትኛውም አለም ያለ እውነታ ነው። ይህን በምንም ብትተረጉመው ኢትዮጵያ ሲደርስ ‹‹ሽብር›› ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ሽብር የሚሆነው የኮንትራት ውሉ እንደ ውርስ ሲታይ ነው። ‹‹የሞትኩለት ነው፣ የተዋጋሁለት ነው፣ የታገልኩለት ነው…›› ቅብርጥሶ የሚለው የታሪክ ትርክትም የአንተ ጉዳይ አይደለም። በየትም ሀገር የተጨቆነ የሚታገለው ጨቋኝ ለመሆን አይደለም፤ ጭቆናን ለማስወገድ እንጂ። ጨቋኝን መጣልም ባለታሪክ ያደርጋል እንጂ መልከፀዲቅ (የዘለአለም ካህን) አያደርግም።
እናም በዚህ የ‹‹ዜሮ ብዜት›› ፖለቲካ ሊያደናግሩህ ሲሞክሩ አትፍቀድላቸው። በእርግጥ እልፍ አእላፍት ደንገጡሮች፣ እልፍ አእላፍት ነጭ ለባሾች፣ እልፍ አእላፍት ፊርማቶሪዎች፣ እልፍ አእላፍት…አሏቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹ጉልቤ እስረኞች››ም ያሏቸው መሰለኝ። በዚህም መዋቅር ሊያስበረግጉህ፣ ሊያስደነብሩህ፣ ይፈልጋሉ። ይህ ግን ሊያስጨንቅህ አይገባም። ሊያስጨንቅህ የሚገባው ጥያቄህ ህጋዊ መሆን ያለመሆኑን ማረጋገጡ ላይ ብቻ ነው። በነገራችን ላይ ሆስኒ ሙባረክም ሚሊዮን ነጭ ለባሾች፣ ሚሊዮን ፊርማቶሪ …ነበረው። ነገር ግን እነዚህ ሚሊዮናት ከ18 ቀን በላይ ሊከላከሉለት አልቻሉም። እነዚህን ቀናት ለሙባረክ የመጨረሻዎቹ እንዲሆኑ ያደረጓቸው በአንተ ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ያሉ ወጣቶች ናቸው። ለዕምቢባይነቱ እንደውም አንተ ከእነርሱ የተሻለ የኋላ ታሪክ አለህ-አድዋ!
የሆነ ሆኖ መንግስቱ ኃ/ማሪያምም በአፍሪካ ተወዳዳሪ የለውም የሚባል ኃይል ነበረው ይባላል። እኛ ግን ነፍስ አውቀን ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ መረዳት ስንጀምር መለስ የሚባል እንጂ መንግስቱ የሚባል አምባገነን በቦታው የለም።
ለዚህም ነው ህዝባዊ ቁጣን፣ የወጣቶች ቁጣን ማንም ሊያቆመው አይችልም የምልህ። ደግሞም ኢትዮጵያውያን ይህንን አይነት ቁጣ የሚቆጡት ጭቆና ሲበረታባቸው ብቻ ነው። ለሀበሻ ጭቆና ያው ጭቆና ነው። የውስጥ ሆነ የውጭ ለውጥ የለውም። ከትዕግስት ባሻገር ጭቆናን የሚሸከም ጫንቃ የለውም። ይህ ደግሞ ፆታ አይለይም።
ዛሬ የአድዋ የድል ቀን ነው። ስለዐድዋ ስናነሳ ከንጉስ ምኒልክ በተጨማሪ መነሳት ያለባቸው አንዲት እንስት አሉ፤ እቴጌ ጣይቱ የተባሉ። እቴጌ ጣይቱ የዛሬውን ትውልድም ወካይ ናቸው።
እናም ጣይቱ ለዐድዋ ጦርነት እንደምክንያት የሚጠቀሰው የ‹‹ውጫሌ ውል›› በፈረሰበት ወቅት የጣሊያኑ ቆንስላ ጣሊያን በጦር ኃይል ፍላጎቷን እንደምታሳካ በዛቻ በነገራቸው ጊዜ እንዲህ አሉት፡-
‹‹ እኔ ሴት ነኝ ጦርነትን አልወድም፤ በሀገሬ ሲመጣ ግን… የዛሬ ሳምንት አድርገው። በዚህ የሚደነግጥልህ የለም። ሂድ የፎከርክበትን አድርግ። እኛም የመጣውን እናነሳዋለን። እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ሀገሩን የማያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ። የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ ሀገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይባልም። አሁንም ሂድ፣ አይምሽብህ፣ የፈከርክበትን በፈቀደ ጊዜ አድርገው፣ እኛም ከዚህ እንቆይሃለን።››
ዛሬ ደንዳና ልብ ያላቸው፣ ብርታታቸውና ባርነትን ያለመቀበል ጥንካሬያቸው ከጣይቱ ክቡድ መንፈስ የሚናጠቅ ሴት ወጣቶችም እንዳሉ አውቃለሁ። ጂጂን የእነዚህ የብርቱ ሴት እህቶቻችን ወካይ አድርገን ብንቀበላት አግባብ እንደሆነም እነግርሃለሁ። ማን ያውቃል ነገ ምን እንደሚሆን? መቼም ሀበሻ ታሪክ ከመስራት አያፈገፍግም። የዐድዋ የአልገዛም ባይነት መንፈስ አሁንም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አለ። በእኔንና አንተ ልብ ውስጥም አለ። አዎን! ጊዜ ይህን መንፈስ በአደባባዮቻችን ይገልጠዋል። ያን ጊዜም አምባገነኖችም…



