"ነጩ" መለስ - "ጥቁሩ" ፑቲን
ተመስገን ደሳለኝ
ሙሉ ስማቸው ቪላድሚር ቪላዲሮቪች ፑቲን (Vladimar Vladiraivouich Putin) ይባላሉ። የተወለዱት ከዋና ከተማዋ ሞስኮ በርቀት ላይ በምትገኘው በታሪካዊዋ የሌኒን ግራድ ከተማ ነው። ከኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አማኝ ቤተሰብ ነው የወጡት። የሁለት ልጆች አባት የሆኑት የ59 አመቱ ፑቲን። … መለስ ዜናዊ አስረስ ሙሉ ስማቸው ነው። የተወለዱት ከዋና ከተማው አዲስ አበባ በእርቀት ላይ በምትገኘው በታሪካዊዋ የአድዋ ከተማ ነው። እሳቸውም ልክ እንደ ”ሴራ አቻቸው” ፑቲን ከኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አማኝ ቤተሰብ ነው የተገኙት፣ የሶስት ልጆች አባት የሆኑት የ60 አመቱ መለስ።
ሁለቱም በወጣትነት እድሜያቸው ነው የፖለቲካ ፓርቲን የተቀላቀሉት። የሁለቱም ፓርቲዎች በኮሚዩኒስት ርዕዮተ-አለም የተቃኙ ናቸው። ሁለቱም ድንገት ነው ስልጣን የያዙት። ያውም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ፤ ፑቲንን ቦሪስ የልሲን የተባሉ አዛውንት ከፓርቲያቸው ፍቃድና ፍላጐት ውጭ በሆነ መልኩ ከግምጃ ቤት ሀላፊነት ጠርተው በእግራቸው እንዲተኩ ሲያደርጉ፤ የመለስም ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ነገሩም እንዲህ ነው አቦይ ስብሐት ነጋ የተባሉ አዛውንት ድንገት ፓርቲያቸው ህወሓት በያዘው አጀንዳ ላይ እየተወያዩ ሳለ፣ ከአጀንዳ ውጭየሆነ ጥያቄ አንስተው እንዲህ አሉ ”የእኔን ስልጣን ለመለስ መስጠት እፈልጋለሁ”።
እነሆም ሁለቱም ዛሬም በስልጣን ላይ ናቸው። ሁለቱም የሚሄዱበት መንገድም ተመሳሳይ ነው። ፖለቲካቸውም እንዲሁ። በብልጠትም የአንድ ሳንቲም ገፅታዎች ናቸው። ሁለቱም የፒኤ.ች.ዲ ዲግሪያቸውን የአገኙ ቢሆንም ”ዶክተር” ተብለው እንዲጠሩ ፍላጎት የላቸውም።
ጥቁሩ ፑቲን
ቪላድሚር ፑቲን በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ አካባቢ የኬጂቢ (KGB) ምክትል እንዲሁም ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። በቺቺኒያ ላይ የተደረገውንም ዘመቻ መርተዋል። በቀዝቃዛው ጦርነት አሜሪካ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ያስቻላትን የፕሬዘዳንት ሚካኤል ጎርቫቾቭ ግላስኖት (ግልፅነት) እና ፔሬስ ትሮይኪ (መልሶ ግንባታ) አዲስ ሃሳብ ታላቋ ሶቭየት ህብረትን እንድትከፋፈል ዳርጓታል። ከዚህ ክፍፍል በኋላ ‹ለዘብተኛ እና ደካማ› እየተባሉ የሚተቹት ፕሬዘዳንት ቦሪስ የልሲን ወደ ስልጣን መጡ። የኬጂቢው አለቃ ፑቲንም በአባታቸው እግር ተተክተው የክሬምሊን ቤተመንግስት ግምጃ ቤት ሀላፊ ሆኑ። ዲሴምበር 31/1999 እ.ኤ.አ ፑቲን በድንገት ልብ ድካማቸው የተነሳባቸውን የልሲንን ተክተው የሩሲያ ፕሬዘዳንት እንዲሆኑ በራሳቸው በየልሲን ተቀቡ። ይኽ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላም ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ተካሄደ፣ በከፍተኛ ድምፅም ቪላድሚር ፑቲን ተመረጡ። ፑቲን የተመረጡበት ጊዜም ሲያልቅ፤ ለሁለተኛ ዙር የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀመሩ። የአሠቡትም ተሳክቶ በድጋሚ ተመረጡ። ለ8 አመትም የሩሲያ ፕሬዘዳንት ሆነው አገለገሉ።
የሆነ ሆኖ በሩሲያ ህግ መሰረት አንድ ፕሬዘዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ በስልጣን መቆየት ስለማይችል ፑቲን ለሶስተኛ ጊዜ የመወዳደር ሃሳባቸውን እንቅፋት ገጠመባቸው። እናም ለፕሬዘዳንቱ ወንበር ሳይወዳደሩ ቀሩ። ይህ ማለት ግን ፑቲን ከመንበሩ የሉም ማለት አይደለም። እንዲህማ ሊሆን አይችልም! በቤተመንግስቱ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን አስመርጠው ሲያበቁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር ላይም እርሳቸው ተቀመጠው ልክ እንደ ራስ ሚካኤል ስሁል አንጋሽ ሆኑ እንጂ። ማንም ያለፉትን አራት አመታት የሩሲያ ፖለቲካን የተከታተለ ሁሉ እንደሚረዳው ሚድቬዲቭ ”ፕሬዘዳንት” ከሚለው መጠሪያ በስተቀር የፖለቲካው ስልጣን የነበረው በፑቲን መዳፍ ውስጥ ነው። ለዚህም እንደ ዋነኛ ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀሰው ሩሲያ ጆርጂያን ስትወር የነበረው ሁኔታ ነው። እናም ሩሲያውያኖች ከመጋረጃው ጀርባ ፑቲን እንዳሉ ያውቃሉ። ዛሬ ደግሞ እስከ አሁን ድረስም እያወዛገበ ባለው ምርጫ ፑቲን ”አሸንፌአለሁ” ስላሉ መጋረጃው ተገልጧል። ወደ አደባባይም ወጥተዋል። ”ፕሬዝዳንት” የሚለውንም ማዕረግ መልሰው ተረክበዋል።
ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በፓርቲያቸው ”ዩናይትድ ሩሲያ” አይነግቡ ተተኪ እንዳይኖራቸው ያልፈነቀሉት ጉድጓድ የለም። በእርግጥም ፍንቀላው በሚገባ ሰምሮላቸዋል። በዚህም ስልት የፓርቲያቸውን አባላት እና ደጋፊዎች ”ከፑቲን ውጭ ማን ሊወክለን ይችላል?” የሚል አማራጭ አልባ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል። ይህ ብቻም አይደለም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ደካማና የተከፋፈሉ ይሆኑ ዘንድ በጂዶ ትምህርት ጥቁር ቀበቶ ያላቸው ፑቲን ያደሩት ድር አድርቶላቸዋል። የተሳካ የፖለቲካ ሴራም ይሉሀል ይህ ነው።
የፑቲን ስልት ይህ ብቻ አይደለም፤ ምርጫ ማጭበርበር፣ ደጋፊዎቻቸው በተለያዩ ጣቢያዎች ደጋግመው ድምፅ እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም ተቃዋሚዎች እንዲከፋፈሉና ድምፃቸው እንዲበታተንም ማድረግን ያካትታል። ለዚህም በዋናነት የተጠቀሙት ዝነኛውን ሩሲያዊ ቢሊየነር ነው።
ሚካኤል ፕሮኮሮቭ (Michael Prokhorov) ይሰኛል-ቢሊየነሩ። እኒህ ሰው ከስድስት ወር በፊት ነው የፑቲን ተቀናቃኝ ሆነው ወደ ምርጫው እንደሚገቡ ይፋ ያደረጉት። ሆኖም ሰውየው በመንግስት ጀርባ ተንጠላጥለው ሀብት ያካበቱ፤ እንዲሁም አብላጫው ሀብታቸው በሩሲያ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያ በተቃውሞ ጎራ ያሉ ፖለቲከኞች አላመኗቸውም። በግልፅም የሰውየውን ጨዋታ ”የክሬምሊን ቁማር” እንደሆነ ተችተዋል። March 5, 2012 በታተመው “TIME” መጽሔት ሚካኤል ኢዶቭ (Michael Idov) የተባለ ተንታኝ “Prokhorov’s role in right cause was to divide the opposition vote and thus help the ruling united Russia party in the parliamentary elections. (የፕሮኮሮቭ ትክክለኛው ሚና ለፓርላማ አባልነት በሚካሄደው ምርጫ የተቃዋሚዎችን ድምፅ በመከፋፈል ገዥውን ዩናይትድ ፓርቲ ማገዝ ነው) ሲል ሩሲያውያን ጋዜጠኞችን እና አክቲቪስቶችን ጠቅሶ ገልጿል። በአናቱም የመለስ መንግስት አንደበት የሆነው ትላንት የታተመው ”ኢትዮጵያን ሄራልድ” ጋዜጣ እንዳስነበበን ፑቲን በዚህ መልክ ላሸነፉት ምርጫ አምሳያቸው መለስ ዜናዊም የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት አስተላልፈዋል። አምባገነን-ለአምባገነንም ይሉሀል እንዲህ ነው።
ነጩ ፑቲን
በእርግጥ መለስ በአይን ቀለም ነጭ አይደሉም፤ ሀበሻ ናቸው። ሆኖም በፖለቲካ ዘይቤአቸው ፍፁም የፑቲን ግልባጭ ለመሆናቸው አያከራክርም። ምክንያቱም በሩሲያ የተደረገው እያንዳንዱ የምርጫ ቅስቀሳም ሆነ የምርጫ ቅልበሳ ዘዴ በኢትዮጵያም ተደርጓልና። ለምሳሌ መለስ በምርጫ 2002 ዋዜማ ድንገት በፓርላማ ተገኙ። ተገኝተው ሲያበቁም እንዲህ ሲሉ በምርጫው ዋነኛ ተገዳዳሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቅ ለነበረው መድረክ መልእክት አስተላለፉ።
”የመድረክ አመራር የሻዕቢያ ተላላኪ ነው። በሽብር ተግባርም እንደሚሳተፍ እናውቃለን። የኒዮ ሌበራሊስቶችም ተላላኪ ነው። እናም ከምርጫው በኋላ እርምጃ እንወስድበታለን” አሉ። በዚህም በአብዛኛው የመድረክ አመራር እና መድረክን ሊመርጥ በተዘጋጀ ህዝብ ላይ የፍርሃት ሽብር ነዙ። ምርጫውንም ”ከፖለቲካ ስልጣን መያዝ እና ያለመያዝ” ፉክክር አውርደው የሉአላዊነት ጉዳይ አደረጉት። ፑቲንም እንዲሁ ናቸው። በምርጫው ዋዜማም እንዲህ አሉ
“I am the only one who can guarantee stability and all those people protesting against me are part of an American plot to overthrow the government” (ለሀገሪቱ መረጋጋት ብቸኛው ዋስትናቸው እኔ ነኝ። እናም እኔን የሚቃወሙኝ በሙሉ መንግስታችንን በሴራ ለመበታተን የምትሞክረው የአሜሪካ ተላላኪዎች ናቸው)
እናሳ! መለስን ከፑቲን በምን ትለያቸዋለህ? በቀለም ወይም በፓስፖርት እንዳትለኝ። እየነገርኩ ያለሁት ቀጣዩ የመለስ እስትራቴጂ የፑቲን ግልባጭ ስለመሆኑ ነውና። ቪላድሚር ፑቲን ቢሊየነሩ ሚካኤል ፕሮከሮቭ በሚባል ቱጃር የሩሲያውያን ድምፅ በተፅእኖ ስር ሊያውሉ እንደሞከሩት ሁሉ፣ መለስ ዜናዊም አላሙዲን በሚባል ሲራራ ነጋዴ ድምፅ ለመግዛት ሞክረዋል። ያውም የውጭ ሀገር ዜጋ ሆኖ። ፕሮኮሮቭ እንኳ ቢያንስ ፓስፖርታቸው ላይ ያለው ዜግነት ”ሩሲያዊ” የሚል ነው። እናም አላሙዲ የመለስ ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ አርማ የሆነውን ”ንብ” ምልክት ያለበትን ቲሸርት ለብሰው ከመቀስቀስም አልፎ የተቃዋሚ ፓርቲ የሆነውን የ”ሁለት ጣት” የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ለተቃዋሚዎች እንደማይገባ ጠቅሶ በአደባባይ አውግዟል። …
በምርጫ 97 ዋዜማ ሚያዚያ 29 ቀን የገዥው ፓርቲ በጠራው በድጋፍ ሰልፍ ላይም ጥቂት የማይባሉ የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች የፋብሪካና የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤቶች የድርጅታቸውን ሰራተኞች በመስቀል አደባባይ እንዲገኙ ያስገደዱበት ሁኔታም ነበር። ፑቲንም ይህንኑ አድርገዋል። አንድ የመንግስት ደጋፊ የሆነ የአንድ ፋብሪካ ባለቤት ሰራተኞቹ የፑቲንን ፓርቲ ”ዩናይትድ ሩሲያ”ን መምረጥ ትተው የኮሚኒስት ፓርቲን በመምረጣቸው ኦፊሰሮቹን ሰብስቦ የተሰማውን ንዴት እንዲህ ሲል ገልጾላቸዋል፡-
“I tell them, folks, when I needed you, you voted for the communists. so let the communists help you. let them lay your sewer pipes, put in your fire extinguishers, patch the walls in your houses”
(ነግሬችኋለሁ፤ በፈለግኋችሁ ጊዜ፣ እናንተ ግን ኮሚኒስቶቹን መረጣችሁ። ስለዚህም እነሱ ይርዷችሁ። የውሃ ቧንቧዎችን ያስገቡላችሁ፣ የእሳት መከላከያም ያኑሩላችሁ፣ ቤታችሁንም ያድሱላችሁ)
ይሄ ሁኔታ በአንድ ወቅት ሳይቀነስ ሳይጨመር በኢትዮጵያ ተተግብሮ ነበር። ቅንጅት ሙሉ በሙሉ ባሸነፈባቸው አካባቢዎች ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ”ቅንጅት ያድርግልህ፣ ቅንጅት ይስራልህ፣ ቅንጅት ይፍረድልህ…።” ይሄንን ነው የፑቲን ሀበሻነት እና የመለስ ሩሲያዊነት ተነጣጥሎ ሊታይ አይችልም የምለው። ከላይ እንዳየነው በሩሲያ “I am the only one who can guarantee stability” የሚል የፖለቲካ አጀንዳ እንዳለው ሁሉ በኢትዮጵያም ”ኢህአዴግ ከሌለ ሀገሪቷ ትበታተናለች” የሚል የዚህ ግልባጭ የፖለቲካ ጨዋታ አለ። ከዚህም ባለፈ አቶ መለስ ከምዕራባውያን ዲፒሎማቶች ጋር ሲወያዩ ከእርሳቸው ውጭ የሀገሪቱን ሰላም አስጠብቆ የሚቆይ መሪ እንደሌለ ከመናገር እንደማይቦዝኑ ይሰማል።
እነዚህ ሁለት አምባገነን መሪዎች ተመሳሳይ ቃላት በመጠቀምም አቻ ናቸው። ለምሳሌ በትላልቆቹ የሩሲያ ከተሞች ፑቲን በዚህ ምርጫ መሳተፍ እንደሌለባቸው እና ራሳቸውንም ከምርጫው እንዲያገሉ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ በተደረገ ጊዜ፤ ከምክትሎቻቸው አንዱ ተቃዋሚዎቹን እንዲህ ሲሉ ዘለፋቸው ”የተበሳጩ የከተማ ቦዘኔዎች”፤ በምርጫ 97 ዋዜማም ከተፎካካሪዎቹ ዋነኛ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በጠራው ግዙፉ የሚያዝያ 30 ሰልፍ ላይ ድፍን የአዲስ አበባ ህዝብ ተገኘ፤ የመለስ ፓርቲም ሰልፈኛውን ”የአደገኛ ቦዘኔ ስብስብ” ሲል ተቸ። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የፑቲን የቃላት አጠቃቀም ብሂል አማርኛ የሚመስልህ፤ ወይም የመለስ የቃላት አጠቃቀም ብሂል ሩስኪ የሚሆንብህ።
የሁለቱ ብልጥ አምባገነኖች መመሳሰል በዚህ ብቻ አያበቃም። ለምሳሌ ከምርጫ 97 ወዲህ በኢትየጵያ ገዥው ፓርቲን ከሚደግፍ ሰልፍ በቀር የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎ አያውቅም። ወይም እንዲደረግ አይፈቀድም። በሩሲያም ይሄው ነው ያለው። በእርግጥ የሩሲያ ህዝብ አንዳንዴ ፈንቅሎ ይወጣል። ሆኖም በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ጣት እንደሚያስቆርጠው ሁሉ፣ በሞስኮም ተመሳሳይ ዋጋ ያስከፍላል።
ሌላው የሁለቱ መሪዎች የፖለቲካ መመሳሰል ጎልቶ የሚወጣው ሁለቱም በሚከተሉት የሽብር ፖለቲካ ነው። ለምሳሌ በዘንድሮ ምርጫ ፑቲን ኩርገን ከተማ ሄደው ቀስቅሰዋል። ነገር ግን ከዚህ ቅስቀሳ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የመንግስት ቴሌቪዥን ያሳየውን ፕሮግራም ከTIME መጽሔት እንደወረደ አውርደን ስናየው እንዲህ የሚል ሆኖ ታገኘዋለህ፡-
“The day before Putin’s arrival in kurgan, state TV aired a program arguing that the west is trying to overthrow the government through proxies. As proof it showed footage of anti-putin activists visiting the U.S. embassy in Moscow and quoted U.S. senator john McCain’s Twitter jab at putin on Dec. 5 ‘Dear Vlad. The Arab spring is coming to a neighborhood near you’
(ፑቲን ኩርገን ከተማ ከመድረሳቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የመንግስት ቴሌቪዥን ምዕራባውያን በእጅ አዙር መንግስትን ለመጣል እያሴሩ እና ህዝቡን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ለማሳየት ተቃዋሚዎች ሞስኮ የሚገኘውን የአሜሪካንን ኢምባሲ ሲጎበኙ የሚያሳይ ምስል አሳይቷል። እንዲሁም የአሜሪካው ሴናተር ጆን ማይኬ Dec. 5 በቲውተር ገፃቸው ላይ ”ውድ ፑቲን የአረቦች አመፅ የቅርብ ጎረቤቶችህን እየጎበኘ ነው”) ማለታቸውን ያስነብበናል።
ምናአልባትም ይህንን የራሺያ ፖለቲካ ወደ አዲስ አበባ ፖለቲካ ስንመልሰው በተከታታይ እያየናቸው ያሉትን የኢቲቪ የሽብር ፊልሞች ግልባጭ ሆኖ እናገኘዋለን። ”አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ፣ አኬልዳማ፣ የሽብር አባት፣ እመቤት ፍትህ …”
የሰዎቹ መመሳሰል ማለቂያ የለውም። በአሌክሳንደር ፑሽኪን ምንጅላትነት የተያያዘ ገመድ ይሁን ወይም ሌላ ተለይቶ ባይታወቅም፤ የፑቲን ፖለቲካ ከመለስ ፖለቲካ የሚለይበት የስልትም የአፈጻጸምም ነጥብ የለውም። ሊቲያኮቭ Iityakove የተባለ አሳማ አርቢ ገበሬ ፑቲን በስልጣን ላይ የቆዩበት ጊዜ በጣም አጭር እንደሆነ ሲገልፅ እንዲህ አለ፡-
“Moses walked with the Jews in the desert for 40 years to free them of their slave mentality. Putin has only been our leader for a decade.”
(ሙሴ አይሁዶችን ከባርነት አስተሳሰባቸው ነፃ ለማውጣት 40 አመት ያህል በበረሃ አብሯቸው ተጉዟል፣ ፑቲን ግን መሪያችን ከሆነ ገና አስር አመቱ ነው) ደ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመፃሀፋቸው እንደገለፁት ”መለስ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እስክትሰለፍ በስልጣን መቆየት ይፈልጋል” ያሉትን ስናስታውሰው በሩሲያ እየሰማን ካለው ጋር ልዩነት አናገኝበትም። ሆኖም ጥያቅ ግን ማንሳት ይኖርብሀል፤ ”ያ የመካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ ለመድረስ ምን ያህል አመት ይፈጅባታል? ሀምሳ አመት ወይስ መቶ አመት?” ብለህ ማለቴ ነው፤ መልሱ እንጃ! ሊሆን እንደሚችል መገመት አለብህ።
ይሄ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የኢህአዴግ ፖሊሲ ሊሳካ የሚችለው ኢህአዴግ 40 እና 50 አመት በስልጣን ሲቆይ ነው የሚለውን ትርጓሜ እናገኛለን። በአናቱም መለስና ኢህአዴግ 20 አመት በስልጣን መቆየታቸው የሚያሳስብ አይደለም ”በጣም አጭር ጊዜ ነውና” እየተባለ የሚሰበክልህን የ”ድርሳነ አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ግልባጭ ታገኛለህ። በረከት ስምኦን የተባሉ የመለስ አጋርም ”ናዳን የገታ እሩጫ” በሚለው መጽሐፋቸው 40 እና 50 አመት በስልጣን መቆየት እንዳለባቸው የነገሩህን እዚህ ላይ አስታውሰው።
የሚገርመው ነገር የመለስም የፑቲንም ደጋፊዎች ፍፁም ተመሳሳይ መሆናቸው ነው። እንደተለመደው መለስም ደጋግመው እንደነገሩን የድጋፋቸው መሰረት ያለው በከተማ የሚኖረው እና የተማረው ህዝብ ሳይሆን አርሶ አደሩ ጋር እንደሆነ ነው። በፑቲን ሀገርም እንዲሁ ነው። የፑቲን ደጋፊ ላባአደሩና የገጠር ነዋሪው ነው። የራሻይ ፖለቲካ ተንታኞች የፑቲን አገዛዝ ወደ ወደቀው ንጉሳዊ (ግለሰባዊ) የዛሩ መንግስት አይነት እየሄደ ነው ሲሉ ይተቻሉ፤ በኢትዮጵያም በመለስ ላይ እየቀረበ ያለው ትችት ያለው ይህ ነው። የመለስ አገዛዝ የአንድ ሰው እየሆነ ነው። ወደ ንጉሳዊና ንግስታዊ ስርዓትም እያመራ ነው የሚል።
ሌላው የሚያመሳስላቸው ሁለቱም የድጋፍ ሰልፍ ሲፈልጉ ህዝባቸውን አስገድደው ማስወጣታቸው ነው። ነገር ግን ሁለቱም ህዝቡ ”ተገድጄ ወጣሁ” እንዲል አይፈቅዱለትም። በግልባጩ ”ፈልጌ፣ አምኜበት፣ ወድጄ… እንዲል ያደርጉታል እንጂ። ከምርጫው አንድ ወር ቀደም ብሎ በኩርግ ከተማ ፑቲንን የሚደግፍ ሰልፍ ተካሄዶ ነበር። አንድ የሰልፉ ተሳታፊና አስተባባሪም ሰልፉ የግዴታ ሰልፍ እንደሆነ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲያስተባብል
“We didn’t force anyone to go. We just suggested it was a good idea.” (መሰለፍ ጥሩ ነገር እንደሆነ ከመናገር በዘለለ ማንንም እንዲሰለፍ አላስገደድንም) ሲል በፈገግታ መልሷል። እዚህ ሰው መልስ ውስጥ ግን ”ተገዶ” መሆኑ በግልፅ ይታያል። እናም ሁሌም የኢህአዴግና የኢቲቪ መስካሪና ተንታኝ የሆኑት የአዲስ አበባ ”አንዳንድ ነዋሪዎችም” ተገደው ለወጡበት ሰልፍ እንዲሁ እንደሚመልሱልህ ትዝ ይልሀል፡
የሆነ ሆኖ ምንአልባትም ፑቲን አምባገነን ናቸው፤ መለስም አምባገነን ናቸው። ሁለቱም በማደራጀት ያምናሉ። ነፃ ተቋሞች እንዳይኖሩ ማድረግም መለያቸው ነው። የሃይማኖት ተቋማትንም ”የስርዓቱ አፍ ጠባቂ” በማድረግ ይታወቃሉ፤ ህዝቡ በሀገሪቱና በፖለቲካ ጉዳይ እንዲገባ አይፈልጉም፤ ”ይመለከተኛል” ማለቱንም አይወዱም። የምንጊዜም መርሀቸው ”የሞትንም እኛ ያለንም እኛ” የሚል ነው። ሁለቱም የሀይል አማራጭን የስርዓታቸው ዋነኛ መጠበቂያ አድርገው ያዩታል፤ የሩሲያ ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ማሻ ጌሴህ (Masha Gesseh) የተባለ ሩሲያዊ ኤክስፐርት ስለፑቲን ጉልበተኝነት ለቢቢሲ ሲያስረዳ
“When he feels it’s not possible, he will use force” (ምንም ማድረግ እንደማይቻል ሲሰማው ሀይል ይጠቀማል) ያለውንም ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ምክንቱም መለስም እንዲሁ ናቸው። ምንግዜም ቢሆን ከአቅሜ በላይ ነው ብለው ካሰቡ ህግን ሳይሆን ሀይልን ለመጠቀም አያመነቱም። እናም ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች አሏቸው። ለምሳሌ ሰሞኑን የሞስኮ አደባባዮችን ያጥለቀለቁትን መፈክሮች እያቸው። የሁሉም ይዘት “Putin our president”, “We believe in Putin”… የመሳሰሉት ናቸው። በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶችም ተሽከርከር ደግሞ ብዙ የመለስ ዜናዊን ምስል የተሸከሙ ቢልቦርዶች ስር እንዲህ የሚል መፈክር ታያለህ ”ለልማት የተጋ አፍሪካዊ መሪ”፣ ”አባይን የደፈረ መሪ … እና የመሳሰሉት።
ከዚህ በተጨማሪም ፕ/ር ፓል ኮልየር የተባሉ ፀሐፊ ስለአምባገነኖች እና ዴሞክራክራቲክ መሪዎች የአደባባይ ፎቶዎች የሰጡት አስተያየት ለመለስ እና ፑቲን በሚገባ ይሰራል። ፕ/ሩ እንደሚሉት ዴሞክራቲክ መሪዎች እንዲሰቀሉላቸው የሚፈልጓቸው ፎቶዎች ቁጥር ከማነሱ በተጨማሪ ፎቶዎቻቸው በሙሉ በፈገግታ የታጀቡ ናቸው። ከዚህ በግልባጩ ፎቷቸውን በየአደባባዩ፣ በየተቋማቱ እና በየትምህርት ቤቶቹ የሚሰቀሉት አምባገነኖች “እጅግ የተኮሳተሩ፣ አተኩረው የሚያዩ ዓይኖችን የያዙ አስጨናቂ ፊቶች ናቸው። ሲሉ Wars, Guns & Votes በሚለው መፀሀፋቸው የገለፁት በጣም ትክክል የሚሆነው በየአደባበዩና በየመንግስት መስሪያ ቤቱ የተሰቀሉትን የመለስን ፎቶዎች በአይነ ህሊናችን ስናስተውለው ነው። ለነገሩ የመንግስቱ ኃ/ማሪያምም፣ የፊደል ካስትሮም፣ የመሀመድ ጋዳፊም፣ የሳዳም ሁሴንም፣ የሆስኒ ሙባረክም፣ የቪላድሚር ፑቲንም… ፎቶ ከፈገግታ ጋር የተፋታ ነው። በግልባጩ የቶኒ ብሌር፣ የቢል ክሊንተን፣ የባራክ ኦባማን…ፎቶ ስናይ ”አስፈሪ” ነገር አናይበትም። እንዲያውም ተመልካችን ዘና ሊያደርግ በሚችል ፎልፏላ ፈገግታ የተሞላ ነው።
ሌላም ተመሳሳይ ነገር እንጥቀስ፣ በኢህአዴግ ካድሬዎች የሚነገር አንድ አሳሳች ተረት አለ። እንዲህ የምትል ”መለስ ስልጣን ለመልቀቅ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ለማን ይልቀቁ? ብቃት ያለው ሰው ማን አለ?”። እኔ ግን በዚህ አልስማማም፤ እልሃለሁም መለስ ስልጣን በጣም ይወዳሉ። መልቀቅም አይፈልጉም። ይህ ለቦታው የሚመጥን የለም የሚለው የፑቲን እና የእሳቸው የፖለቲካ ቧልት ካልሆነ በቀር ጉንጭ አልፋ ክርክር ነው።
ሌላው ማሳሳቻ ደግሞ ”መለስ በጣም አዋቂ ናቸው” የሚለው ፕሮፓጋንዳ ነው። መቼም ይሄ ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የዘለለ አይደለም። ምክንያቱም መለስ አዋቂ አይደሉም የሚል አይደለምና ክርክሩ። ክርክሩ የአምባገነንነት ጉዳይ ነው፤ ክርክሩ የህግ የበላይነት ነው። በቅርቡ በምርጫ ተሸንፈው ስልጣን አለቅም ብለው እስር ቤት የገቡት የሴራሊዮኑ ፕሬዝዳንት የታሪክ ፕሮፌሰር መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። እናም መለስ ያወቁ፣ የበቁ፣ የመነጠቁ አልፎም ፈላስፋም ይሁኑ የአንድ ትውልድ እድሜን ያህል በስልጣን ቢቆዩም ጠብ የሚል ነገር አላመጡም። ክፋቱ ደግሞ እንደገና የሌላ አንድ ትውልድ እድሜን ያህልም በስልጣን የመቆየት ፍላጐታቸው ነው። ይሄ ነው የሚያምው።
የነጩ ፑቲን መተካካት
እስከአሁን እንዳየነው በመለስና በፑቲን መካከል ያለው ልዩነት የቆዳ ቀለምና ቋንቋ ብቻ ነው። በሌላው በሌላው ፍፁም አንድ ናቸው። ፑቲን ለሁለት ጊዜ ያህል በፕሬዘዳንትነት ካገለገሉ በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር ስለማይችሉ አሻንጉሊታቸውን ሜዴቬዴቭን አስቀምጠው እሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፖለቲካ ስልጣኑን ጨብጠው ቆዩ፤ አሁን ደግሞ ወደ ክሬምሊን ቤተ መንግስት ተመልሰዋል።
… መለስ እስከአሁን በዚህ በኩል የገጠማቸው ችግር የለም። ህገ-መንግስቱም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ገደብ አላስቀመጠም። እስካልሰለቻቸው ድረስ እየተመረጡ እንዲቀጥሉ ይፈቅዳልና። ከዚህ በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥ መለስን ”በቃህ” ብለው ሊገዳደሩ የሚችሉ የትግል አቻዎቻቸው ከአውዱ ላይ ተነስተዋል። በሌሎችም ተተክተዋል። የመተካካት እስትራቴጂም አስፈላጊነት እዚሁ ጋር ግቡን መቶ ተቋጭቷል።
አሁን ምን አልባት ከመለስ ባሻገር በትልቅ ስልጣን ላይ ከሚገኙት ውስጥ በፊት መስመር ጥርሰ ፍንጭቱ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ደርበው የያዙት ሀይለማርያም ደሳለኝን ልናገኝ እንችል ይሆናል። በእርግጥ እኒህ ሰው እንደ መለስ፣ በረከት፣ ብርሃነ ክርስቶስ፣ አባይ ፀሐዬ፣ ስብሐት ነጋ… ታግያለሁ፣ ደምቻለሁ፣ ቆስያለሁ እናም ”በደም ያገኘሁትን በካርድ አልሰጥም” የሚሉ አይደሉም። ምክንያቱም ታጋዮቹ በሚታገሉበት በዛ የትግል ዘመን ሀይለማርያም ፊንላድ ነበሩ። ታጋዮቹ አዲስ አበባ ሲደርሱም ቢሆን ከፊንላድ አልተመለሱም። ስለዚህም ኃ/ ማሪያም ሊሉ የሚችሉት ነገር ቢኖር ከዚህ ቀደም ለአንድ ጋዜጣ የገለፁትን ”አባቴና ጓደኞቹ እኛ እቤት ውስጥ ስለኢህአፓ ሲያወሩ እሰማ ነበር” የሚለውን የፖለቲካ ትግል ልምዳቸውን ነው። ይህ ደግሞ ”ለተራራ አንቀጥቃጮቹ” መሪ ተጨማሪ ቀልድ ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም። እናም ምንአልባት እነዚህ እነዚህ መስፈርቶች ተደራርበው በሚቀጥለው ምርጫ ሀይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንበር፣ ለቀጣዩ አምስት አመት በአደራ ሊረከቡ ይችላሉ። መለስም እንደ አምሳያቸው ቪላድሚር ፑቲን ለአምስት አመት ያህል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦታ ላይ ሆነው፤ አዛዥ ናዛዥ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ካልሆነ ግን ሌላው ሊሆን የሚችለው የመለስ ስልት ከመንግሰታዊ ሃላፊነት ራሳቸውን አግለው የፓርቲውን የሊቀመንበርነት ቦታ ብቻ እንደያዙ ”ሿሚና ሻሪ” ሆነው የሚካኤል ስሁልን ታሪክ የሚደግም ነው። በእርግጥ ይሄ ትንተና እንጂ መረጃ አይደለም። ትንተናው ግን ምክንያታዊ ነው።
ምንጭ፦ ፍትህ ጋዜጣ



