የአቶ አንዷለም አራጌ ግልጽ ደብዳቤ (ከቃሊቲ እስር ቤት)
ለተከበሩ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ
ወንድማዊ የአክብሮት ሰላምታዬ ይድረስዎ!
በዚህ በቃሊቲ ወህኒ ቤት በእኔ ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ በተከበረው ጋዜጣዎ መዘገቡን ሰማሁ። በቅድሚያ ጋዜጣዎ እውነትን ለማሳወቅ ስላደረገችው ጥረት ከልብ እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ። በጣም አመሰግናለሁ!
በዚህ ለኑሮም ሆነ ለማሰብ ፍጹም በማይመች ሁኔታ፣ ለዚያውም ከተፈጸመብኝ አሰቃቂ ድብደባ ሳላገግም፣ ብእርና ወረቀት እንዳገኝ የጎተጎተኝን ጉዳይ፣ ከዚህ እንደሚከተለው እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ። (አቶ አንዷለም አራጌ በእጃቸው የጻፉትን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
ባለሁበት ወህኒ ቤት ጋዜጦችን ቀርቶ መጻህፍትንም ማስገባት ባለመቻሌ፣ እናንተ በምትኖሩባት ”አለም” ከሚቀርበው የመረጃ ማእጽ መቋደስ አልችልም። እንደሌላው እስረኛ ሁሉ በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንዳልጠየቅ አሳሪዎቼ ቢከለክሉም፣ እንዲጠይቁኝ ከተፈቀደላቸው ሁለት ሦስት ቅርብ የቤተሰብ አባሎች አልፎ አልፎ ወሬ መቃመሴ ግን አልቀረም።
ይህን በመሰለ ሁኔታ ውስጥ፣ ወህኒ ቤቱ በእኔ የደረሰውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ፣ የሰጠውን ምላሽ ይዘት በመስማቴ፣ ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ የመናገር ፍላጎት ባይኖረኝም፣ በቀጥታና በዝርዝር ማስረዳት እንደሚገባኝ ከራሴ ጋር ስምምነት ላይ ደረስኩ።
አሁን ካለሁበት የእሥር ሁኔታና ከገጠመኝ የጤና መቃወስ አንጻር ሃሳቤን በወጉ ለማደራጀት መቸገሬን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው፣ ሃሳቤን በሚከተለው አኳኋን እንዳቀርብ መልካም ፍቃድዎ እንዲሆን በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ለሁለት ወራት ገደማ በማእከላዊ እሥር ቤት ከቆየው በኋላ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት መዛወሬ ይታወሳል። በቃሊቲም ከሌሎች፣ በአንድ መዝገብ ከተከሰስን ሰዎች ተነጥዬ፣ አሰቃቂ ወንጀል ፈጽመው ያታሰሩና በተደጋጋሚ እያመለጡ ያስቸገሩ እስረኞች ወደሚታሰሩበት (የቅጣት ቤት) ተወሰድኩ። ገና እግሬ የወህኒ ቤቱን ቅጥር ከመርገጡ ለምን ወደዚህ አይነት ቦታ እንደተወሰድኩ ለሰሚው ግራ እንደሚሆን እገምታለሁ። በወህኒ ቤቱ ውስጥ ግማሽ ቀን እንኳን ባልቆየሁበት ሁኔታ ”ለአያያዝ አስቸግሮን፣ ልዩ ጥበቃ (Maximum Security Zone) ውስጥ አስገባነው” ሊባል አይችልም። ውሳኔው ቀደም ሲል መከሰስ እንዳለብኝ ከወሰኑት አሳሪዎች እንደተላለፈ መገመት የሚከብድ ጉዳይ አይደለም።
አሳዛኙ ጉዳይ በዚች እጅግ ጠባብና አራት ማእዘን ሰማይ ብቻ በሚታይባት እሥር ቤት ተወርውሬ የአሳሪዎቼ የበቀል በትር ያልተለየኝ መሆኑ ነው።
በዚች የጭንቅ ማማ ሁለት ወራት እያገባደድኩ በነበርኩበት አንድ ምሽት፣ ድብደባውን የፈጸሙብኝ አቶ ይብሳ አስፋው እንዲቀላቀሉኝ ተደረገ። አብረውኝ ከነበሩት ከኦፌዴኑ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ጋር በመሆን፣ ጎናቸውን ያሳርፉበት ዘንድ ወለሉን ካመቻቸንላቸው በኋላ፣ የእሥር ሕይወታችንን ቀጠልን። የተከሰስንበትን ሁኔታ፣ ቀደም ሲል ያለንን የእስር ተመክሮዎችና እንዳዴም ግለታሪካችንን መጨዋወታችንን አልቀረም።
ካንደበታቸው በተደጋጋሚ እንደሰማነው በበርካታ የነፍስ ማጥፋትና ከባድ የዘረፋ ወንጀል ምክንያት እንደታሰሩ ገለጹልን። አክለውም ከዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ ከአቶ ታምራት ላይኔና ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር እንደታሰሩ አጫወቱን። ”ለምን እኝህ ሰው ተለይተው ከእነዚህ ፖለቲከኞች ጋር ታሰሩ?” የሚለውን ጥያቄ ግን መመለስ አልቻልንም።
በሂደት ለረጅም ጊዜ የሚያውቋቸው እስረኞች፣ የማረሚያ ቤቱ ሰላይ፣ በእነርሱ አገላለጽ ”ወሬ አቀባይ” መሆናቸውን አስረዱን። እርሳቸው ግን ሌላውን ታሪክ ባይነግሩንም አሁን ያለንባት ጠባብ ክፍል ውስጥ ከታሰሩ የመጀመሪያው እስረኞች አንዱ ስለመሆናቸው ገለጹልን።
ቃሊቲ ውስጥም ሆነ ውጭ፣ ፊት ለፊት መናገር ወይንም መተግበር፣ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል ብዬ አምናለሁ። ለ1998-1999 ባለው ጊዜ በአብዛኛዎቹ የቃሊቲ ወህኒ ቤት ዞኖችና በከርቸሌ ጨለማ ቤት ድረስም ስታሰር፣ የተከተልኩት ዘይቤ ይሄንኑ ነው። በሂደቱም ከአንድም እስረኛ ጋር የኃይል ነገር ይቅርና ሃይለ ቃልም ተለዋውጬ አላወቅም። ”ቦዘኔ” ክልል ተብሎ ይታወቅ በነበረው ዞን እንኳን ይህን የመሰለ ነገር አልፈጸምኩም።
በጊዜው አብረውኝ የታሰሩ ጓደኞቼ እንደሚያስታወሱት አልፎ አልፎ ፀቤ ከፖሊስ ጋር ነበር። ከፖሊስም ጋር ቢሆን የነበረኝ አለመግባባት ”ለምን የእስረኛ መብት አይከበርም? ለምን እስረኛ ይደበደባል?” በሚል ነበር። ይሄንንም በግልጽና በአክብሮትከመግለጽ ውጭ የተለየ አቀራረብ ኑሮኝ አያውቅም። አቶ ይብሳ አስፋውንም ቢሆን ለረጅም አመታት የታሰሩና የዔች አይቪ ታማሚ በመሆናቸው፣ ከማክበርና ከመንከባከብ ውጭ አንዳች ቅር የሚያሰኝ ነገር ተናግሪያቸው ወይንም ፈጽሜባቸው አላውቅም።
ነገር ግን ገና አንድ ሳምንት ሳይሞላቸው ጀምሮ፣ በጋዜጣ ላይ ሊገለጹ የማይችሉ አያሌ ፈታኝ ነገሮች ያደርሱብኝ ጀመር። መዝለፍ የእለት ተእለት ሕይወቴ ሆነ። እንደ ድመት በጥፍሬ ቆሜ መውጣትና መግባት የዘውትር የአኗኗር ዘይቤዬ ሆነ። ከአለፈው እሥር ተመክሮዬ በመነሳት ያረጋጋቸዋል ብዬ የማስበውን ነገር ሁሉ ባደርግም አልተሳካልኝም። ያለ አንዳች ማጋነን ክብራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከተናካሽ ውሻ ጋር ከመታሰር ፈጽሞ የተለየ አልነበረም። ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ተራ ስድብ እየተሰደብኩም ሁሉንም በጸጋ ከመቀበል ባለፈ ሌላ አማራጭ አላገኙሁም። አስቀድሜ እንደግለጽኩት ያለሁበት እሥር ቤት ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ የሆኑ እስረኞች በሌሎች የወህኒ ቤቱ ዞኖችማ አደገኛ የተባሉ እስረኞች ለቅጣት የሚመጡባት ቤት ነች።
ታዲያ ሰውዬው እኔና ሌሎች በጣት የምንቆጠር እስረኞች ወዳለንበት ቅጥር ለምን መጡ? ከቀድሞ የእሥር ቤት ቆይታዬ እንደተረዳሁት እስረኞችን እንዲሰልሉ የሚመደቡ እስረኞች አሉ። ስለደብዳቤዬ ከታሳሪዎች ከተረዳሁትን በላይ፣ በተለያዩ ወቅት ከተለያዩ ፖለቲከኞች ጋር መታሰራቸው ለምን ይሆን? የሚለው ጥያቄ እየተመላለሰ ሳያሳስበኝ አልቀረም። መጀመሪያ ባይገባኝም፣ በእድሜ የተፈረደባቸው እስረኛ በመሆናቸው፣ ለ16 አመታትም እንደሚሉት የታሰሩ በመሆናቸው፣ ክፍለ ሃገር በዝውውር ቢሄዱ ኑሮ እስከአሁን ሊፈቱ ይችሉ እንደነበር በማንሳት ይቆጫሉ። ወደ ክፍለ ሃገር ለመዘዋወር ጠይቀዋል። እስከ አሁንም ባይዘዋወሩም ውትወታቸውን ቀጥለዋል። የወህኒ ቤቱን ሃላፊዎች ከረጅም ቆይታቸው የተነሳ እስከቤተሰብ ድረስ እንደሚያወቋቸውና የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሊያስረዱን ሞክረዋል።
ከድብደባው 10 ቀናት በፊት ወደ ዋናው የወህኒ ቤቱ ሃላፊ ቢሮ፣ ቀን በቀን ማለት ይቻላል፣ በጥበቃ ፖሊሶች አማካኝነት ይመላለሱ ነበር። ሁኔታው ለሁላችንም ግልጽ ነበር። የስለላ ስራ እየሰሩ ነበር። በዚያ ወቅት በእኔ በኩል በወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 148፣ ንኡስ አንቀጽ 1 መሰረት ለፍርድ ቤት ለማቅረብ በመጻፍ ላይ ነበርኩን። ወረቀቱንም ልነጠቅ እንደምችል የራሴን ግምት ወስጃለሁ። የተለየ አማራጭም ሆነ የሚደበቅ ጉዳይ ባለመኖሩ የመጣው ይምጣ ብዬ መጻፌን ቀጠልኩ። የኔ ሃሳብ የነበረው ወህኒ ቤቱ በፍተሻ ሰበብ ይወስድብኛል የሚል ነበር። የተፈጠረው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ሆነ።
ግልሰቡ በ 6/6/2004 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ እንደተለመደው ዋና አስተዳዳሪው ቢሮ ውለው መጡ። እንደመጡም ፍራሻቸውን አሁን ወዳሉበት ዞን ለመላክ ሲሞክሩ ግራ ከመጋባት በዘለለ የተለየ ሃሳብ አልያዝኩም። መጻፌን ግን ቀጥያለሁ። በዚያው እለት ማታ ሽንት ቤት ገብተው ሲወጡ ቧንቧ ”ባለመዝጋታችሁ ውሃ ፈሰሰብኝ ” በማላት እናንተ ትናንሾች በማላት ሦስታችንንም በጅምላ ሰደቡን። አሰዳደባቸውንና ሁኔታቸው ከሌላ ጊዜ የከረረና እንደምንም ምክንያት ፈልገው አካላዊ ግጭት ውስጥ ለመግባት የመፈለግ ፍላጎት ይነበብባቸው ነበር።
ሦስታችንንም ለመሃላ እንኳን አንዳች ሳንተነፍስ ምሽቱም እየገፋ ነበርና እንደተገረፉ ሕጻናቶች አፋችንን ውጠን ወለሉ ላይ እንደ አስክሬን ተገጥግጠን አንቀላፋን። በማግስቱ የግድያ ሙከራ ባደረጉብኝ ቀን፣ አርፍደው ከእንቅልፍ ነቁ። አቶ በቀለ ገርባ ያነባል። እኔ አሁንም እየጻፍኩ ነው። አቶ ይብሳ እንደተነሱ በመጮህ ያዘጋጀሁትን በሶ ትጠጣላችሁ አትጠጡም?” አሉ። ሁለቱ የነርሱን ድርሻ መጠጣታቸውን ሲገልጹ፣ እኔ መጠጣት እንደማልፈልግ ገለጽኩላቸው። ይሄ የሆነው ከቀኑ 5 ሰዓት ገደማ ነው።
ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን በፀጥታ የተቀመጥኩበት ክፍል በር በኃይል ተከፈተ። ደብዳቤዬ ለረጅም ሰዓት ከቤት ውጭ ቆይቷል። ሃሳባቸው ሌሎች እስረኞች ሲወጡ ጠብቀው ውሳኔያቸውን ለመፈጸም እየተጠባበቁ ነበር። እንደተረዳሁት። በአጋጣሚ ሁላችንም በስራ በመጠመዳችን ከተቀመጥንበት አልወጣንም። ጊዜ እየመሸባቸው ስለነበር ያላቸው አማራጭ ባለው ሁኔታ እርምጃውን መውሰድ ነበር። በሩን እንደከፈቱ ተንደርድረው በመግባት አሳልፈው ይሰጡብኛል ብዬ የሰጋሁባቸውን ወረቀቶች ከሌሎች ወረቀቶች እየለዩ፣ ጉዳዩን ይከታተሉ ስለነበር፣ ከያሉበት ለቀሟቸው። ከማስታወሻ ደብተሮች በተጨማሪ 40 ገጽ ወጥ ጽሁፍና ሌሎችም ሰነዶችን በጄ ላይ የነበረውን ጨምረው ነጠቁኝ።
ይሄ ነገር እንደሚመጣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እጠብቀው ነበርና ዝምታን መረጥኩ። በበኩሌ ከማንም ሰው ጋር ቢሆን ግብግብ መግጠም አልፈልግም። ዝምታዬ መፍትሄ አልሆነም። ከተቀመጥኩበት ተንደርድረው ከኮንክሪት ግድግዳ ጋር አጣብቀው ጭንቅላቴን ረገጡኝ። ተንሸራትቼ በቀኝ ጎኔ የሰሚንቶውን ወልል ላይ ተነጠፍኩ። አሁንም አልበረደም። ከወለሉ ላይ ጭንቅላቴን ሦስት ጊዜ እንደረገጡኝ አቶ በቀለ መሃል በመግባት ለማስጣል ሲሞክሩ በሰመመን ውስጥ ሆኜ እሰማለሁ። ”እገለዋለሁ። ብገለው ስድስት ወር ብቻ ነው ካቴና የሚገባልኝ” ይላሉ። አቶ በቀለንም ዘወር ካላለ እንደሚደበድቡት ይዝታሉ። ”ደብድበኝ እንጂ ስትጨርሰው ዝም ብዬ አላይም” እያሉ ግብግብ ገጥሟል።
ከዚህ በኋላ ሌሎች እስረኞች በመጨመራቸው ወለሉ ላይ እንደወደኩ ደብዳቤዬን ገፋፍተው አስወጧቸው። ትንሽ ራሴን ማወቅ ስጀምር ጭንቅላቴ ላይ ድብደባ ስለተፈጸመብኝ ሕክምና የማግኝበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹልኝ ፖሊሶችን ጠየኩኝ።
የተከበሩ አዘጋጅ፣
እስካሁን የገለጽኩልዎ ሁሉ እውነት ስለመሆኑ በፈጣሩ ስም አረጋግጥልዎታለሁ።
ከፍ ብዬ አጠቃላይ ሂደቱን ልገልጽልዎ ሞክሪያልሁ። አሁንም ደግሞ የወህኒ ቤቱ አስተዳደር ሁኔታውን አስመልክቶ በጋዜጣዎ ባወጣው ምላሽ ላይ የእኔን እምነት እንድገልጽ ፈቃድዎትንና ትእግስትዎትን በአክብሮት እጠይቃለሁ።
እውነቱን ለመናገር የእኔ ጉዳይ በአሳሪዎቼ በአቶ አመለስ እጅ እንጂ በወህኒ ቤቱ አሊያም በፍርድ ቤቱ እጅ ነው የሚል አንዳች ብዥታ ኑሮኝ አያወቅም።
ስለዚህ ከወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪዎችም ሆነ ከፖሊሶች ጋር ከወንድማማችነትና ከአክብሮት ውጭ ሌላ የተከተልኩት መንገድ ኑሮ አያውቅም። ደብዳቢዬ አስተዳዳሪው ቢሮ ሲመለሱ ግን ምን እየተጋገረ እንደነበረ ለማሽተት ብዙ አስቸጋሪ አልነበረም። የግድያ ሙከራውም ቢሆን አሳሪዎቼ የወህኒ አስተዳደሩን በመጠቀም ሊወስዱብኝ ያሰቡት እርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በታች የማነሳቸው ነጥቦች የግድያ ሙከራው በአሳሪዎቼ እንጅ በደብዳቤዬ የግል ፍላጎት ላለመፈጸሙ አሥረጅ ናቸው ብዬ አምናለሁ።
1ኛ – ከሌሎች እስረኞች ተነጥዬ ከመጀመሪያው እንዲህ አይነት ቦታ የገባሁት ይኼን መሰል እርምጃ ለመውሰድ ያመች ዘንድ ነው ብዬ አምናለሁ።
2ኛ – እስካሁን በነበረው የወህኒ ቤቱ አሰራር፣ በእስረኛ ላይ የግድያ ሙከራ የሚያደርግ ቀርቶ ግጭት እንኳን ቢፈጥር አስተዳደሩ በአፋጣኝ በካቴና አስሮ ማማ በማስገባት ቅጣት ይፈጽም ነበር። እኔን ለመግደል የሞከሩት እስረኛ ግን ሊቀጡ ቀርቶ ከሦስት ሳምንታት በላይ አንዳች ተግሳጽ እንኳን ሳይደርስባቸው እኛ ካለንበት በእጅጉ በተሻለ ቦታ ታስረው ይገኛሉ።
3ኛ – ችግሩ እንደተፈጠረ ተጠርተው የመጡት የአስተዳደሩ አባላት ለአቶ ኢብሳ የጀግና አቀባበል ነበር ያደረጉላቸው ማላት ይቻላል። ”አንተ ፖሊስ ወይንም የአስተዳደሩ አባል ባለመሆንህ ሰነዱን ቀድሞውንም መንጠቅ አልነበረብህም። አሁንም በአስቸኳይ መልስ” ማለት ሲገባቸው ሰነዶቹን በፈገግታ ተቀብለው ሰውዬውን ወደ ተሻለ ማረፊያ ቤት እኔን ደግሞ ባላሁበት ቅጣት ቤት እንድቀጥል አድርገዋል።
4ኛ – ተጎድቼ ወደ ሕክምና እንዲወስዱኝ በምጠይቅበት ሰዓት ቢሮ አስገብተው ወረቀቱን የነጠቁኝ የረሃብ አድማ ለማድረግ ሃሳብ ላይ መሆኔን ስለደረሱብኝ መሆኑንና የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ይሄኑ እንደሚጠረጥሩ ገለጹልኝ። በእኔ በኩል የሚባለው ነገር ፍጹም ሃሰትና ነገሩን ለማድበስበስ ተብሎ የቀረበ መሆኑን ገልጬ የግድያ ሙከራው ባለቤቶች እነርሱ መሆናቸውንና ንብረቴን ከእነርሱ እንደምጠብቅ አስረዳሁ።
5ኛ – በደረሰብኝ ከፍትኛ ድብደባ እስከ አሁኗ ሰዓት ደረስ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ብሆንም ተገቢውን የሕክምና ክትትል ማግኘት አልቻልኩም። ሌሊትም ሆነ ቀን ከፍተኛ የስቃይ ስሜት ሲሰማኝ፣ በጥበቃ ላይ የሚገኙ ፖሊሶችና በጤና ጣቢያው ያሉ የሕክምና ባለሞያዎች የቻሉትን ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ግልጽ በሆነ የአቅም ውስንነት ምክንያት ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን ከማድረግ ባለፈ፣ ከስቃዬ ሊታደጉኝ አልቻሉም። ይሄ ሁኔታ በውል እየታወቀ የተሻለ የሕክምና ክትትል በድንገተኛ እንኳን እንዳገኝ አለመደረጉ፣ ያልተፈለገው ሕይወቴ ይቀጥል ዘንድ ባይፈለግ ነው የሚል ከፍተኛ ስጋት አለኝ።
6ኛ – ክስ የምመሰርት ከሆነ በአስተዳዳሪዎቹ ተጠይቄ ነበር። ግለሰቡ በራሳቸው ተነሳሽነት አደረጉት ብዬ እንደማላምን በመግልጽ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለጽኹ። አክለውም ምስክሮች እንዳሉኝ ጠይቀው እነርሱ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸው ቢሄዱም በጉዳዩ ላይ ከዚህ ግባ የሚባል ነገር ሳያደርጉ አያሌ ቀናት አልፈዋል። ይሄም እውነት በግለሰቡ የተፈጸመ ቢሆን ኑሮ ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ በቸልተኝነት እንደማይያዝ መረዳት አያስቸግርም።
7ኛ – የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪዎች የተወሰዱብኝን ሰነዶች ሙሉ በሙሉ እንዲመልሱልኝ ብጠይቅም፣ ቀደም ብለው በጋራ እያየን የሚመለስ ካለ እንደሚመለስ የማይመለስ ካለ ለምን እንዳማይመለስ እንደሚገለጹልኝ ነግረውኝ ነበር። በአጋጣሚ አደጋው ከተፈጠረ በኋላ ተቀይረው የመጡት አስተዳደሮችም በተገለጸው መሰረት ይፈጽሙልኛል ብዬ ባስብም፣ አልተሳካም። ከወሰዷቸው ሰነዶች፣ የፍርድ ቤት የክስ ወረቀቴንና አንድ የተገነጠለ የደብተር ሽፋንና የተቀደዱ አንዳች ነገር ያልተጻፈባቸው የተቀደዱ ወረቀቶችን መለሱልኝ። ብዙ የደከምኩባቸው ጽሁፎች የውሃ ሽታ ሆኑ። በሁኔታው ማዘኔንና አዲስ እንደመሆናቸውም ከእነርሱ ጋር እሰጣገባ ውስጥ መግባት እንደማልፈልግ ገልጬ፣ መብቴን እየገፈፉ ግን በዝምታ እንደማልቀጥል ስገልጽላቸው፣ ደብዳቢዬን ወረቀቶቹን ከሰጡዋቸው እንደሚጠይቋቸው፣ ካልመለሱላቸው ግን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ገለጹልኝ። ”ዶሮን ሲያታልሏት” የሚባለው በእንዲህ ያለ ጊዜ ነው። አንድ እስረኛ ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ እንደሆነ ማን ሊያምን ይችላል? ሰነዱንስ ቀደም ብለው ሊመልሱልኝ፣ የማይመመለስም ካላ ለምን የሚለውን እንደሚያስረዱኝ ተገልጾልኝ እንደነበረ ዘንግተውት ወይንስ …!
8ኛ – እየተፈጸመብኝ ያለው ግፍ ሳያንስና ጥዋትና ማታ ከሞት ጋር ግብግብ በገጠምኩበት ሁኔታ፣ የወህኒ ቤቱ አስተዳደር በጋዜጣዎ ላይ ነገሩን ተራ ጉዳይ፣ ተራ ግጭት አስመስሎ ለማቅረብ መሞከሩ፣ ሃዘኔን አክብዶታል። ስቃዬንም አብዝቶታል። ከፍ ሲል የገለጽኩት የግድያ ሙከራ ሲፈጸምብኝ አንዳች ቃል እንዳልተነፈስኩ፣ ራሴንም እንኳን ለመከላከል እንጄን እንዳላነሳው በሚገባ እየተረዱ፣ ጉዳዩን የግድያ ሙከራ ሳይሆን ግጭት ለማስመሰል መሞከራቸው ከበደል ሁሉ የከፋ በደል ነው።
በሰውነት ከተቸረኝ ክብር ውጭ የምጠቅሰው ሌላ ክብር የለኝም። ነገር ግን የወህኒ ቤቱ እርምጃ እኔን ተራ አምባጓሮ ፈጣሪ በማስመሰል ለማብጠልጠል የታቀደ እንደሆነ እገነዘባለሁ።
ለመሆኑ ምንስ የሃሳብ ልዩነት ቢኖረኝ ሰውነቴን ይጠራጠራሉ? ወይንስ ኢትዮጵያዊነቴን? ከእስር አያያዝ ጀመሮ ከፍ ብዬ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የገለጽኳቸው በደሎች ሳያንሱ እኔን እንደ ምግባረ ብልሹ አድርገው ለአንባቢ ለማቅረብ መሞከራቸው አሳዝኖኛል።
በአጠቃላይ ወህኒ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ እያሳየ ያለው ነገር በገሃድ የሚያሳየው የጉዳዩ ባለቤት አሳሪዎቹ መሆናቸውንና ያንንም ለመሸፈን ሲሉ ከፍ ያለ ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን ነው።
ነገር ግን ይሄን መሰሉ ተግባር ለተቋም ግንባታም ሆነ ወንድማማችነትን እና መልካም ሁኔታዎችን ሲፈጠር አይታየኝም። የፓርቲዬ የአንድነት ለዲሞርካሲና ለፍት ፓርቲ አላማ እንዲህ አይነት የሸፍጥኛ የመጠፋፋት አዙሪት ቆሞ ፍትህ፣ ዴሞርካሲ፣ ነጻነትና ወንድማማችነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማማየት ነው።
ክቡርነትዎ እንዲረዱልኝ የምፈልገው ይሄንን የመሰለ ደብዳቤ ስጽፍ ማንንም ለመበቀል ወይንም ለማንቋሸሽ ሳይሆን እውነቱ ፍንጥቅ ብሎ እንዲወጣ፣ ስቃዬን ሕዝብ እንዲያውልኝ ከመሻት የተነሳ መሆኑን ነው።
ለዚህ እውነት ደግሞ ግራና ቀኛቸውን ለይተው ከማያወቁ ልጆቼ ተለይቼ ዘመኔን በሙሉ በወርደት ለመጨረስ ብቻ ሳይሆን፣ ለመሞትም ዝግጁ መሆኔን አሳዳጆቼ እንዲያወቁት እወዳለሁ።
መቼም እኔ ባለሁበት ሁኔታ ያለ ሰው ነገር ቢያበዛ ቅር እንደማይሰኙ ተምምኜ፣ ነገሬን ዘለግ ማድረጌን ይረዱልኝ። ስለትብብርዎ በቅድሚያ እያመሰገንኩ እውነቱን የማሳወቅ ስራዎ እንዲሳካ እመኛለሁ!!!
አክባሪዎ
አንዱዋለም ዓራጌ
የሕሊና እስረኛ
የካቲት 25/2004 ዓ.ም.
ከቃሊት ወህኒ ቤት