ግርማ ደገፋ ገዳ

ሰው ስለመሆናችን ብቻ አናስብ። ከዚያ ባሻገር ያለው ሁሉ፣ ቁምነገር እንዲመስል እንፈልጋለን እንጂ፤ ቁምነገርነቱ ብዙ አይደለም። የጓደኛችን ቋንቋው፣ ዘሩ፣ ሃይማኖቱና ፖለቲካዊ አመለካከቱ ምን ያደርግልሃል? ደጋ ውስጥ ቢፈጠር ቆላ፣ ወይናደጋ ቢወለድ ተራራ ጫፍ ላይ፤ አንዴ ተፈጥረናልና ሰው ስለመሆናችን ብቻ ማሰቡ ይበልጣል። …


በነዚያ ክፉ ምክንያቶች በምንም ተአምር ለኢሕአዴግ መንግሥት አታግዝ። መንግሥት ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት ትክክለኛ ቢሆን እንኳ ለቀረችው አንዲት ፐርሰንት ስትል መንግሥትን አትደግፍ። በዚያች አንዲት ፐርሰንት ውስጥ ብዙ ጉድ አለ። መአት በደል ተከምሯል። የሚሰቃዩ እንደ አሸን ናቸው። ለመገደል ተራ የሚጠብቁ አሉ። እስር የመረራቸው ሞልተዋል። በፖለቲካ ውስጥ የአንዲት ፐርሰንት ስቃይ ቀላል አይደለም። ያንን እያሰብን፣ የዛሬው ጽሑፍ፤ ኢሕአዴግ የሰለጠነ ስላለመሆኑ፣ መለስ እስከ 2020 ድረስ እንደሚቆይና ስለወደቦች ይነካካል።

 

አንድ፦ የየትም ሀገር መንግሥት ብዙ ክፋት አለበት። የኢትዮጵያ ሲሆን ደግሞ ይጨምራል። አንድ ነገር ሲባሉ “የሰለጠነ ፖለቲካ ያስፈልጋል…..በሰለጠነ መልኩ መወያየት የስልጣኔ ምልክት ነው” የሚሉት የመንግሥት መሪዎች፣ ራሳቸው ያልሰለጠኑ ግን የሰየጠኑ ናቸው። ያልሰለጠኑ ለመሆናቸው እማኙ የራሳቸውን ዜጋ በጥይት ሲቆሉ መክረማቸው ነው። ድንጋይና አርጩሜ ይዞ መንግሥትን ለመቃወም ሰልፍ የወጣ ወጣትን በመትረየስ የጨፈጨፈ ነው “ያልሰለጠነ” ማለት። እንዴት ነው አንድ ታንክና አንዲት ጠጠር የሚወዳደሩት? የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነ’ኮ ታንክ አሰልፎ ለሕዝብ ማሳየት አይደለም። “ሕዝብ አልፈልግህም!” ሲለው ወደ ቤቱ መመለስ ነው። መንግሥት የሚመራው በሰዎች በመሆኑ እነዚያ ሰዎች ወደ ቤታቸው ሄደው ማረፍ አለባቸው። “እሺ፤ ለማረፍ ሄጃለሁ” ብሎ መድፍ ይዞ መመለስ ለማንም አልበጀም። ወይም ከጅምሩ “አላርፍም!” እያሉ የዜጋው አፍንጫ ላይ ቦምብ ማስቀመጥ አያዋጣም። ያ መሰልጠን ሳይሆን መሰይጠን ነው።

 

እውነት ኢሕአዴግ የሰለጠነ ነው? ጀርመን ሀገር የምትታተም ‘ጥላ’ የተባለች መጽሔት፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ አሜሪካውያን፣ መንግሥታቸውን የመሩ አራት ፕሬዚዳንቶችን ሲያስተናግዱ፤ ኢትዮጵያ እስካሁን የምትመራው በአንድ ሰው መሆኑን ጽፋለች። እንግሊዝ አራት ጠቅላይ ሚኒስትርን ስትቀያይር ኢትዮጵያ እስከአሁን የምትመራው በአንድ ሰው መሆኑን አሳይታለች። ‘የአሜሪካና የእንግሊዝ መሪዎች “ስማርት” አይደሉም ማለት ነው?’ ወይም ‘አልሰለጠኑም?’ የሚል ጥያቄ እንደተለመደው መጣ።  የአሜሪካ ምርጫ ቀጥታ ፕሬዝዳንታዊ ቢሆንም የእንግሊዝ ግን ፓርላሜንታዊ ነው። ኢትዮጵያም የእንግሊዝ ዓይነት ምርጫ ነው የምትከተለው። ግን ሕዝቡ በሃያ ዓመት ውስጥ አራት ማየት ለምን ተከለከለ? የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ በኩል አልሰለጠነም?

 

በተለያዩ ወቅቶች፣ ያልሰለጠነውን የኢሕአዴግን ሥርዓት ከስሩ ቆርጦ በሌላ የተሻለ ሥርዓት ለመለወጥ፤ አልያም መሻሻል ግድ የሚለውን ለማሻሻል ነው የተሞከረው እንጂ፤ ሕገመንግሥቱን ለማፍረስ አይደለም። “የሕገመንግሥቱን ሥርዓት ሕገመንግሥታዊ ባልሆነ አካሄድ ሊጥሉ!” አትበሉ። “እኛን፣ በሥልጣን ላይ ተጣብቀን የሞጨጭነውን ሊደረምሱን ነበር” በሉ። እንደዚያ ስትሉ በሥልጣን ላይ መቆየታችሁ ኢትያጵያዊውን በሙሉ አንጀቱን እያቃጠለው፣ ግን በምትሰጡት መልስ አንዳንዱ ደስ ሊለው ይችል ይሆናል። ‘ይችል ይሆናል’ እንጂ የሰለጠነ ፖለቲካ ማለት ያ ነው ማለት አይደለም። የሰለጠነ ፖለቲካ ማለት፣ ሃያ ዓመት አንድን ሰው ዙፋን ላይ ተወትፎ አለማየት ነው፤ አሻሚ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም ሀገር የአንድ ሰው ወይም የአንድ ቡድን የግል ወይም የቡድን ንብረት አይደለችም። ሀገሩን ለመግዛት ሳይሆን ለማስተዳደር ፍላጎት ላለው ዜጋ ሁሉ የመወዳደሪያ ሜዳው እኩል መሆን አለበት። ለተቃዋሚዎች ማራቶን ለኢሕአዴግ መቶ ሜትር መስጠት፤ ተቃዋሚዎችን የሽቦ እሾክ ላይ እያሮጡ ኢሕአዴግን ስቦንጅ ላይ መመደብ፤ ተቃዋሚዎች በበቅሎ እንኳ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ ከልክሎ ኢሕአዴግ በሄሊኮፕተር መቀስቀሱ፤ መሰልጠን አይደለም። መሰይጠን እንዳይሆን የሚከለክለውም የለም። ኢሕአዴግ ብቀላ ያለቀቀው፣ ግድያን አቅፎ የሚዞር ያልሰለጠነ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ለማሳየት ብዙ ማስረጃዎችን በመደዳ ማሰፍ ይቻላል።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ችግር ምንጩ ሕገመንግሥቱ አይደለም። ሕዝቡም ሊገለብጠው የሚፈልገው እሱን ሳይሆን ኢሕአዴግን ነው። ያልሰለጠነውን ኢሕአዴግ! ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ‘ሌባ ስናይ ያጥወለውለናል’ ያሉ በሚቀጥሉት ዓመታት ራሳቸውን ሌባ ያደረጉትን! …..ስኳር፣ ወርቅ፣ ገንዘብ፣ ማሽን፣ ድምጽ፣ ሥልጣን፣ ሰው፣ ነፍስ፣ ሀገር፣ ስክሩ ድራይቨር፣ ወልቃይት ጠገዴና የብረታ ብረት ዓይነት በሙሉ የሰረቁትን። በተለይ ደግሞ ውሸታምና ፈሪ የሆኑትን። መብት ረጋጭ ቁንጮ መሪዎቹን።  እነሱን ለመከርበት ነው። ምንም ማታለል የለም፤ ሕገመንግሥቱ ላይ አታላክኩ። ሕገመንግስቱን የጻፈው ወይም ከሆነ አገር ኮፒ ያደረገው ሰው ነው። ሰው ከፈለገ ሕገመንግሥትን ያሻሽላል፤ ይጨምራል፣ ይቀንሳል። ሕገመንግሥት ያለ ሰው ወይም ያለ ሕዝብ ምንም ማለት አይደለም። የፖለቲካ ድርጅትም ቢሆን የጥቂት ዜጎች ስብስብ እንጂ ከሕዝብ አይበልጥም። በሕገመንግሥት ላይ ዜጋው “በአደባባይ የመሰብሰብ መብት” እንዳለው ከተጻፈ፣ ግን ያንን በኢሕአዴግ አፈሙዝ ምክንያት ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ፣ ሕገመንግሥቱ እንደማንኛውም ወረቀት ንጹህ ወረቀት ባይሆንም ጥቁር ቀለም ያረፈበት የተበላሸ ወረቀት ነው። ሕገመንግሥቱ ሕገ-ገዥዎች ሆነ ማለት ነው። ሕገ-አፈሙዝ። የሸምሱ ሱቅ የስኳር መጠቅለያ ወረቀት ከሱ በላይ ጥቅም አለው። ስለዚህ፣ የጻፉትን ሕገመንግሥት የሚያከብሩና በሕገመንግሥት ስም የማይነግዱ ፖለቲከኞችን ወደ መንግሥት ማምጣት ያስፈልጋል። ለዚያም ዓላማ ያልሰለጠነው ኢሕአዴግ መገልበጥ አለበት። ከተቻለ ብዙ ጊዜ! “ወዮ! ወዮ!” እስኪል ድረስ። ኢሕአዴግም ያ የሚያስከፋው አለመሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል። ‘ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም! …..ሕገመንግሥቱን ብቻ አትንኩ፤ እኔን ግን እንደ ጦስ ዶሮ አዙራችሁ ስትፈልጉ ዋርካ ሥር፣ ስትፈልጉ ወንዝ ዳር ድፉኝ፤ ለዚያም መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ!’ ብሏል። እንደፍላጎቱና እንደኑዛዜው በሰላማዊ ሰልፍ ጎትቶ ከሾላ ጋር ማጣበቅ ነው እንጂ!

 

ለነገሩ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ሕገመንግሥትን ከራሱ የፖለቲካ ድርጅት ፖለቲካዊ ፕሮግራም መለየት የሚችል መንግሥት ነው ‘ሕገመንግሥቴ ተነካ!’ ብሎ ማልቀስ ያለበት። ሕገመንግሥቱ ላይ በአደባባይ ቂሌ የሚጫወት መንግሥት፣ ዓይን አውጣነት ካልሆነ በቀር ‘ወዮ ለነገደ ጎበዜ!’ ማለት የለበትም። ኢሕአዴግ ሕገመንግሥቱን የሚያከበር፣ ለሕገመንግሥቱ የሚገዛ ድርጅት ቢሆን ኖሮ፣ በጣት ለሚቆጠሩ ጥቂት ዓመታት ነበር በኢትዮጵያ የሥልጣን ታሪክ ላይ ቦታ ሊኖረው የሚችለው። ያንን ባለማድረጉ ዛሬም ድረስ ሥልጣን ላይ በስቃይ አለ። ለራሱ ብዙ ሰዓት መድቦ እንደ እብድ ለብቻው የሚያወራ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ለማየት ተረግመናል። በሀገር ደረጃ ሃያ ዓመት ሙሉ ወሬ!..... እንዴ ይሰለቻል’ኮ! …..ሕዝቡ ሰለቸው። ሌላ ፊት ማየት ይፈልጋል! …..አሜሪካ አራት ፕሬዚዳንት ….እንግሊዝ አራት ጠቅላይ ሚኒስትር በሃያ ዓመት! ኢትዮጵያ በሃያ ዓመት ውስጥ አንድ ብቻ! …..በድርጅት ደረጃ ያለው ሲጨመርበት እስካሁንም መኖራችን ወይ መኖሩ አንዲት የአወልያ ተማሪ እያለቀሰች እንዳለችው ወንድ ጠፍቶ መሆን አለበት። እንዲህ ነው ያለችው፦ “ፕሊስ ወንዶች እኛ በጣም በጣም መሮናል! በአሁኑ ሰዓት እኛ ወንድ አጥተናል! ወጥተን ወንድ መሆን ነው የቀረን! ሁላችሁም ሊሰማችሁ ይገባል! እኛ ወንዶች ሆነን ወጥተን አንናገር! የሆነ ነገር አናደርግ!”

 

የኢሕአዴግ መንግሥት፤ ‘የቀለም አብዮት፣ የኖራ አብዮት፣ የጄሶ አብዮት፣ የብጥብጥ አብዮት፣ የድንጋይ ውርወራ አብዮት፣’ ይበለው የምን…. መድሃኒቱ እሱ ብቻ ነው። ስለሚፈራውም ነው ደጋግሞ የሚያነሳው። በዚያም ምክንያት ነው በአደባባይ የሚደረግን ሰልፍ ማየት የማይፈልገው። ሰልፍ ከተነሳ ጠዋት ቤተመንግሥት የነበሩ ሰዎች ምሳ ሠዓት ላይ አድራሻቸው ከርቸሌ እንደሚሆን ያውቃሉ። ጓደኞቻቸውም በብርሃን ፍጥነት ነው የጎረቤት ሀገራት ጠረፍ ላይ የሚደርሱት። የሕዝባዊ ሰልፍ ስም ሲነሳ ሰይጣን እንዳለበት ሰው ያርገፈግፈዋል። የሰላማዊ ሰልፍ ጉዳይ ሲነሳ ዛሬም ሕጻን ነው። ዳይፐር ቁጡ ላይ ለጥፎ የቆቅ ኑሮ ነው የሚኖረው። እንዲያ እያደረገ አፍሪካ ውስጥ በመከራ የሚኖር የፖለቲካ ድርጅት ቢኖር ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ኮቱን ወደ ላይ ከፍ አድርጋችሁ እዩት፤ የዳይፐሩ አናት ፈጦ ካላያችሁ፣ ኢሜይል አድርጉልኝ። በመሆኑም ሕዝባዊ አልገዛም ባይነት፣ ሕዝባዊ በቃኝነት፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ያስፈልጋል። ውኃን የሚያጮኸው ድንጋይ ነው። ኢሕአዴግ ከሕዝቡ መሃል ተነቅሎ ሲወጣ ሕዝቡ ሰላም ይሆናል። ሕዝባዊ ተቃውሞ…..መድሃኒቱ እሱ ነው። ያልሰለጠነውን ግን ሰልጥኛለሁ ብሎ የሚያሾፈውን የኢሕአዴግን መንግሥት ከዙፋኑ ላይ የሚቆርጠው እሱ ነው።

 

ብዙ ዓመታት በነጻነት የቆየች ሀገር ውስጥ፣ አብዛኛው ዜጋ ቢታመም ሕክምና የለውም። ረሃብተኛ ነው። ውኃ ይጠማዋል። ልጆቹን ለማስተማር አይችልም። ቀላል በሽታዎች ያንገላቱታል። ልብስ ያሳስበዋል። ጫማ ይቸግረዋል። የሌለ የችግር ዓይነት የለም። በመከራ የተማሩት በቂ ደመወዝና ነጻነት የላቸውም። የኢትዮጵያ የሕክምና ዶክተሮች ቦትስዋና፣ ናሚቢያና ሞዛንቢክን ነው የሚያገለግሉት። ኢትዮጵያ ውስጥ በነጻ የትምህርት እድል ተምረው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ነው የሚመስለው። ይሄ ሁሉ አንሶ ዜጋውን መንግሥት ይጫወትበታል። አንገቱን ያንቀዋል። ታዲያ የሁሉም በር ከተዘጋ፣ እየተንኳኳም አልከፈት ካለ፣ ከበሩ ጀርባ ሆኖ ድምጽ ለመስጠት የማይፈልገውን ፍጡር ለማየት በሩን መበርገድ ያስፈልጋል። በሩ ሥር ቆሞ ሃያ ዓመት ሙሉ እየየ ማለት አላዋጣም። የሕዝባዊና ሀገራዊ ሰላማዊ ጥሪ ምላሽ አፈሙዝ ከሆነ…..ጊዜ ማቃጠል አያስፈልግም። በሃያ ዓመት በልመንና እሹሩሩ የተገነደሰ መንግሥት የለም። ሕዝብ ያለውን ኃይል ማሳየት አለበት። ከአፈሙዝ የሚበልጥ መሆኑን ማሳየትን መምረጥ ያስፈልጋል። ኃይሉን በየግድግዳው ላይ የተቃውሞ ወረቀትና ፎቶ በመለጠፍ ብቻ መገደብ የለበትም። ኢሕአዴግ፣ ሰውን ብቻ ሳይሆን ቁልቁል ወርዶ ኢሜይና ስልክ የመጥለፍ ደረጃ ላይ የደረሰው፣ የውስጥ ሰላም ስለሌለው ብቻ ሳይሆን፤ አንገቱን ሊያንቀው የሚችለውን ኃይል በመናፈቅ ጭምር ነው። ተስፋዬ ገብረአብ አንድ ነገር ብሏል ‘መለስ ጀርባውን በሰንሰለት ጅራፍ የሚዠልጠው ይፈልጋል።’ ለዚህ የአወልያ ትምህርት ቤት ንቅናቄ ማስረጃ ነው።

 

ሙስሊሙ ማመጽ ጀመረ። አወልያን አናስነካም አለ። ኢሕአዴግ፤ ቱኒሲያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ ታወሱት። እንደተለመደው መንበጭበጭ ጀመረ። ሥልጣኑ ሲናጋና ከዙፋኑ ሲሽቀነጠር ታየው። ከዛ ለመትረፍ አንድ መላ መጣለት። ኦርቶዶክስን ማባበል። የተረሳውን የእርቅ ድርድር መጀመር። በውጭ ባለው እና በአዲስ አበባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ መካከል የእርቅ ማውረድ ፕሮፓጋንዳን መንዛት። የድርድሩ ዋና ዓላማው አዲስ አበባ እየተደረገ ያለው የሙስሊሞች ንቅናቄን ተከትሎ በኦርቶዶክስ ክርስትያን በኩል ሌላ ንቅናቄ እንዳይከፈት በቅድሚያ መዝጋት ነው። መሄጃ የሌለው ኢሕአዴግ በየአቅጣጫው ተወጥሯል። ሌላ እንዲጨመርበት አይፈልግም።

 

ስለዚህም በምንም ተአምር ላልሰለጠነው የኢሕአዴግ መንግሥት አታግዝ። መንግሥት ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት ትክክለኛ ቢሆን እንኳ ለቀረችው አንዲት ፐርሰንት ስትል መንግሥትን አትደግፍ። በዚያች አንዲት ፐርሰንት ውስጥ ብዙ ጉድ አለ። መአት በደል ተከምሯል። የሚሰቃዩ አሉ። የሚገደሉ ተራ እየጠበቁ ነው። እስር የመረራቸው ሞልተዋል። ያንን አስብ እንጂ ከዚያ ባሻገር ባለው ነገር አትታለል። እሱ ባዶ ነው። የባዶ ጥርቅም ከሆነ ስንት ጊዜው። ከቀበሮ ዋሻ በቀር ደሳሳ ጎጆ ያለነበርው ሁሉ በአንድ ሌሊት ሕንጻዎች ሲያንጽ፣ ዲጅኖ ይዘህ ለነሱ ፎቅ መሰረት ቆፋሪ አትሁን። አንተ በቆፈርከው መሰረት ላይ ሕንጻ አቁመው በዶላር ሲያከራዩ ዝም ብለህ አትይ። ሀገርህ ነው። ድርሻ አለህ። ድርሻህን በሙሉ ለሌላ አሳልፈህ ሰጥተህ በገዛ ሀገርህ ኢትዮጵያዊ ባሪያ አትሁን። የጓደኛችን ቋንቋው፣ ዘሩ፣ ሃይማኖቱና ፖለቲካዊ አመለካከቱ ምን ያደርግልሃል? ሰው ስለመሆናችን ብቻ እያሰብክ አንገትህ ላይ የታሰረውን የማይታይ የባርነት ካቴና በጥሰህ ጣለው። ዲጂኖውን ወርውረህ ካልሰለጠነው ኢሕአዴግ ነጻ ውጣ! ነጻ ኢትዮጵያዊነትህን አውጅ!

 

ሁለት፦ መለስ ለሁለት ነገሮች ብሎ ሥልጣን ላይ እስከ 2020 (እኤአ) መቆየት መርጧል። ለሚሊኒየም ግድብ እና የኤርትራን ጉዳይ ለመደምደም። “ተባለ እንዴ!” የሚባለውን የጸሐዬን ዘፈን አሁን ነው መልቀቅ። የመለስ ከሥልጣን መወገድ የራሳቸውን የሥልጣን ሱሳቸውን የሚበጥስባቸው አሉ። እነዚያ የመለስን ከስልጣን መነሳት በምንም ምክንያት አይፈልጉም። በመለስ እየነገዱ፣ እያተረፉ፣ ሌላ ሃያ ዓመት የስልጣንና የዘረፋ ጊዜ ያምራቸዋል። መለስ ስመ-ጥር አምባገነን በመሆኑ፣ ከመንግሥት እስከ ቤተሰቡ ባሉት ጉዳዮች ላይ ከወዲያና ወዲህ ስድብ፣ ትችትና ተቃውሞ ይሸምታል። ተቃዋሚዎችና አስተያየት ሰጪዎች ያለእረፍት መላ ቅጡን ያወጡታል። በስልጣን ላይ እንዲበሰብስ የሚፈልጉት የስልጣን ጥማተኞች፣ ስድቡ እና ትችቱ የሱን ያህል ስለማይጠበጥባቸው፤ እሱን ከፊት አስቀድመው በግድብና በኤርትራ ስም ተጨማሪ ሃያ ዓመት ይመኛሉ። መሄጃ የሌላቸው አዜብና ሳሞራ ‘መለስ ሥልጣኑን ይልቀቅ!’ ይላሉ ብለን መቼም አንጠብቅም። እሱ መሄጃ አግኝቶ ጉዞ ሲጀምር፣ ጀርባቸው እስኪላጥ ድረስ ሻንጣ ከሚሸከሙት አንዱ ሳሞራ ነው። ማእረጉን ከግራና ቀኝ ትከሻው ላይ አኑሮና ጀርባው ላይ ራስዳሸንን የሚያክል ሻንጣ ተጭኖ መታየትን እንደናፈቀ አይቀርም። አንድ ቀን ስለቱ ይሰምርለታል። በሀዘን ብዛት ሰክሮ፣  ጭነቱን እያስተካከለና ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ‘ኡኡኡ!’ የሚልበት ቀን ይመጣል።

 

መጀመሪያ ላይ ‘ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ እና ለብሔር ብሔረሰቦችና እንዲሁም ሕዝቦች እኩልነት ሲባል መለስ ከስልጣን ዞር አይበል’ ተባለ። የማያልቅ የለምና የዴሞክራሲው ቱልቱላ ብዥታ ሆነና ያ ዘመን እንደ ዋዛ አለቀ። ‘መለስ ዞር ካለ አንዱ ብሔር አንዱን ይግጠዋል’ ቀጠለ። ዛሬ ያ ሁሉ ምክንያት ኤክስፓየርድ አደረገና መለስ በሥልጣን ላይ መቆየት ያለበት ‘ለግድብና ለኤርትራ ጉዳይ’ ሆነና ቁጭ አለ። ሲጀመር ለአምስት ዓመት ተብሎ ያልሆነው የአምስት ዓመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን መርሃግብር፣ በተፎከረበት አምስት ዓመት ሊያልቅ እንደማይችል የታወቀ አስመሰሉ። የልማትና የትራንስፎርሜሽኑ እቅድ፣ እንኳን አስር ዓመት አስራ አምስት ዓመት ከበቃው መልካም ነው። ለሚሊኒየሙ ግድብ የተሰበሰበውን ገንዘብ  አይቶ ለመተንበይ አይከብድም። የሱን ያህል ለመሰብሰብ አሥር ዓመት ድረስ መጓዝ ግድ ነው። ያውም ውጭ ሀገር በሄዱበት ሥፍራ ሁሉ መሰደቡ ካላንገሸገሻቸው። ‘የሶማሊያ አክራሪዎች ምሳ አዲስ አበባ ሊበሉና ጸሎታቸውንም በአንዋር መስኪድ ሊያደርጉ ነው’ የተባለው አባባል፤ በጣት ለሚቆጠሩ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በሥልጣን ላይ ተወትፎ ለመቅረት አንዱ ምክንያት ነበር። ከሃያ ዓመት የምሳዎች ጭፍጨፋ በኋላ፣ የምክንያት ዓይነቶችን ሁሉ ጨረሱና ዛሬ ግድብና ኤርትራ ላይ ደረሱ።

 

የሚቀጥለው የድጋፍ ፕሮፓጋንዳ ይሆናል። ሕወሓት ይጀምራል፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድ፣ ደኢሕዴን እያለ እስከ አፋር ብሔራዊ ዴሞክራቲክ ፓርቲና የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ድርጅቶች ድረስ ይወርዳል። በተመሳሳይ መልእክት የአየር ሞገዱን ያጨናንቁታል። የተሻለ ባሪያ ለመሆን እጅ እያወጡ እንደ መኪና እሽቅድምድም የሚወዳደሩትም፤ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቃለምልልስ ይጋበዙና የመለስን አርቆ አስተዋይነትና የልማት መሪነትን ለሕዝቡ በግድ ይግታሉ። መለስ አርቆ አስቦ 20 ዓመት ላይ መድረሱ ብቻ ሳይሆን ሌላ 20 ዓመት ‘ቢስ’ ሊባል የሚገባው ምርጥ የአፍሪካ መሪ መሆኑን ይናገራሉ። በትላልቅ ከተማዎች ስብሰባዎች ይደገሳሉ። የወጣቶች፣ የሴቶችና የነጋዴዎች፤ ወጣ እየተባለም የገበሬዎች ስብሰባዎች፤ ይጧጧፋል። በአንዳንድ ኮሌጆችም ተማሪዎችን ጠርተው፣ ምን እንደተባባሉ ባይሰማም፤ በቴሌቪዥን የኮሌጁን መግቢያና የተማሪዎችን ምስል እያሳዩ፤ “ተማሪዎች ከመለስ ጎን ቆሙ…..በሳቸው የልማት አመራር ሀገሪቷ የትና የት መድረሷን መሰከሩ…..ለሚቀጥሉት ዓመታትም የጀመሩትን ልማቶች በሙሉ እንዲጨርሱ ያላቸውን ድጋፍ ሰጡ” የሚባል ሪፖርት ይሰማል። ምናለፋችሁ፣ ላለፉት 20 ዓመታት የታዩትና የተሰሙት ድራማዎች በሙሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ ይከለሳሉ። መሄጃ የሌለው ኢሕአዴግ እንዲያ እየተፈራገጠ ነው ቀጣይ ሕይወቱን የሚያረጋግጠው።

 

ለመሆኑ የኤርትራ ጉዳይ ምንድ ነው የቀረው? መለስ አይደለም እንዴ የኤርትራን ጉዳይ ደብዳቤ ጽፎ የጨረሰው? የቀረው ነገር ባይገባኝ ‘ደደብ!’  ልባል አይገባኝም። የተፈለገው ኤርትራን ወዲህ ለማምጣት፣ ወይስ ወደ ባሕር ገፍትሮ ለመጨመር? ኢሕአዴግ የሥልጣን ኮርቻውን እስከተፈናጠጠ ድረስ በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲሁም በሶማሊያ መካከል የማያልቅ እንጂ የሚያልቅ የሚባል ችግር የለም። የችግሩ መነሾ እንዲህ እንደዋዛ መጨረሻ ሊኖረው አልተፈጠረም። ኢሕአዴግ ከሁለቱም ሀገራት ችግሮች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ መፍትሄ ሊኖረው አይችልም። ለሁለቱም ሀገራት የችግሩ አካል በመሆኑ የመፍትሄ አካል የሚሆንበት ጎን የለውም።

 

ሶስት፦ “በዪ እንግዲህ ላሙ ሄጃለሁ”

“ምነው ጅቡቲ ቀረ ማለት ነው?”

“አዎ። ለጅቡቲ መብራት አስገብተንላቸዋል …..ይበቃል!”

“ላሙስ ምን ልታስገቡ ነው?”

“ወደብ ልናንጽላቸው ነው። ከተቻለ በኳንተም ሌቪቴሽን የሚሰራ ባቡር።”

“አሰብ ላይ የነዳጅ ማጣሪያ ሰራን። ….መቼ ነው ለኢትዮጵያ ቁም ነገር የምንሰራው?”

“ከላሙ ስመለስ ጠይቂኝ!”

 

የኢትዮጵያ መብራት እየተጎተተ ጅቡቲ ገባ። ሱዳን ጠረፍም ደረሰ። ኬንያም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይደርሳል። ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ አንዲት አምፑል ቤቱ ውስጥ የለውም። ቦለቄ፣ ሰሊጥ፣ ኑግ በአጠቃላይ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ወደ ውጭ ገበያ በኤክስፖርት ስም ይወጣል። ግን አብዛኛው ዜጋ ዘይት ያለው ምግብ ከተመገበ ታሪክ ሆነ። ዘመዶቻቸው መብራት እንደሌላቸው የሚያውቁት ብዙዎቹ ደግሞ “ጅቡቲ የኢትዮጵያ መብራት ደረሰ” ሲባል ያጨበጭባሉ። ‘ዋው! ኢትዮጵያን ኢሕአዴግ አሳደጋት!’

 

በፊት ‘በሞምባሳ ወደብ እንጠቀማለን’ ነበር የሚባለው። አሁን ደግሞ ‘ላሙ’ ወደብ ተብሏል። በርበራንም ሲነግሩን ነበር። ሞምባሳ ሲባል ሞያሌ አጠገብ ያለ እንዲመስለን አድርገው ነው የሚነግሩን። ላሙ ደግሞ ትንሽ ጠጋ ብሎ ዲላ አካባቢ። ስለ የሰሜን ሶማሊያው በርበራ ወደብ ሕዝቡ እንደነቃባቸው ተረዱት መሰለኝ ሲያነሱት አይሰማም። ኢትዮጵያ እንደ ድርሻዋ የባቡር ሃዲዱን የምትገነባው ከአዲስ አበባ እስከ ላሙ ኬንያ ነው ወይስ ከሞጆ እስከ ሞያሌ ድረስ? …..ስንት ዓመት ይፈጃል? ዘጠና ዘጠኝ? ራዲዮና ቴሌቪዥን አለን ብላችሁ በፕሮፓጋንዳ አትጫወቱ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሰዎች “የላሙ ወደብ ለኢትዮጵያ ካለው ቅርበት አንጻር ኢኮኖሚያዊው ፋይዳ የጎላ ይሆናል” ሲሉም ተሰማ። የልማት ጋዜጠኛ ሲሆኑ የስድስተኛ ክፍልን ጆግራፊ ረሱ ማለት ነው? ከwww.worldatlas.com/travelaids/driving_distance.htm ላይ በተገኘው መረጃ መሰረት፣ በመኪና ከአዲስ አበባ─አሰብ 873 ኪ.ሜ.፤ ከአዲስ አበባ─ጅቡቲ 862 ኪ.ሜ.፤ ከአዲስ አበባ─ሞምባሳ 1836 ኪ.ሜ.፤ ከአዲስ አበባ─ላሙ 1736 ኪ.ሜ.፤ ከአዲስ አበባ─በርበራ 931 ኪ.ሜ. እና ከሞጆ─ሞያሌ 698 ኪ.ሜ. ነው። በኬንያ በኩል ያለው የሕንድ ውቅያኖስ እንዴት ነው ለኢትዮጵያ ቅርበት ሊኖረው የሚችለው? ሱፐርሶኒክ ባቡር ልታስገቡ ነው? ወይስ ባቡራችሁ በኳንተም ሌቪቴሽን ሊሰራ ነው? ከአሰብ በምን ያህል ነው ላሙ ለኢትዮጵያ የሚቀርበው? …..ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ የነበረውን ባቡር ማስተዳደር አቅቷቸው ድምጥማጡን ያጠፉት የኢሕአዴግ ቁንጮዎች፣ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን የባቡር ሃዲዶች ሊዘረጉ እንደሆነ ለሕዝቡ ሲነግሩት ትንሽም እፍረት አይሰማቸውም። ስልጣን ላለመልቀቅ እየተሰቃየ በዚያው ሰበብ ሕዝብን እያሰቃየ የሚኖረው ኢሕአዴግ፣ አንዲት ቀን ስልጣን ላይ ለመቆየት ብሎ የልማት ጋዜጠኞቹም እያገዙት የቅዠት ዓይነቱን  በየሞዴሉ ያሳየናል።

 

ኢትዮጵያን፣ ወደቧን አስረክባ ወደብ ፍለጋ በየውኃው ዳርቻ የምትንከራተት ከርታታ ሀገር ያደረጋት ኢሕአዴግ ነው። የወደብ ነገር ሲነሳ ትቀላውጣለች። የሰው ሀገር ላይ ወደብ ለመገንባት መከራ ታያለች። በብዙ ነገሮች ከምንመሳሰለው ኤርትራ ጋር፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን አድረጎ የአሰብን ወደብ መጠቀም ያልቻለው ኢሕአዴግ፤ ኬንያ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ኢትዮጵያ ያላትን ገንዘብ በስመ የሶስትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ሰበብ እንደለመደው ለመድፋት መንደረደሩ የሚደገፍ አይደለም። ምክንያቱም ኢሕአዴግ የሚዋዋላቸው ውሎች በሙሉ ችግር አለባቸው። ውሎቹ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ አይደሉም። ግልገል ግቤ2 የተመረቀ ሰሞን ኢሕአዴግ ፈነጠዘ። ሚዲያ ሁሉ አልበቃ አለው። ልክ እንደባድሜው! …..መጥፎነቱ ዋሻው ተደፈነ። ሥራውም ቆመ። ዋሻውን የሰራው ‘ሳሊኒ’ የተባለው የጣሊያን ኩባንያ፣ ላደረሰው ችግር ተጠያቂ የሚያደርገው ምንም የሕግ ድጋፍ አልነበረም። ቦለቄ፣ ኑግና ተልባ ከልጆቿ አፍ ላይ እየቀማች ኤክክስፖርት የምታደርገውና መዓት ብድር የተቆለለባት ኢትዮጵያ፣ እንደ ፈረደባት በድጋሚ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ለማውጣት ተገደደች። ያንን ጉዳይ የሚመለከታቸው አንድ ባለሥልጣንም በቪኦኤ ሲጠየቁ ‘ሕጉን እንተወውና መጀመሪያ ችግሩን እንቅረፈው’ አሉ። አዎን፤ እውነታቸውን ነው። ሁሌም እንዲያ ናቸው። የኢሕአዴግ የሕግ ጠቢባንና ፍርድ ቤቱ፣ ንጹሃን ዜጎች ላይ 16 እና 20 ዓመት መፍረድ ብቻ ነው የሚያውቁት። የገዛ ዜጋቸውን እያነቁ እስር ቤት ውስጥ መወርወር እንጂ፤ የነሱ የሕግ ባለሙያዎችና የሚያዘጋጁት ዓለም አቀፍ ውል፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች አሸንፎ አያውቅም።

 

እህቶቻችን በየአረብ ሀገራት አስፋልት ዳር እንደ እንሰሳ ሲጎተቱ፣ የፈላ ውኃ በአናታቸው ሲደፋ፣ በእምነታቸው ሰበብ እስር ቤት ሲወረወሩ፣ እጅግ በሚያሳዝን ድምጽ አብዛኛዎቻችን በምናውቀው አማርኛ ቋንቋ እያለቀሱ ሕይወታቸውን የሚያተርፍላቸው መንግሥት ፍለጋ የድረሱልን ጥሪያቸውን ሲያሰሙ፤ መልስ የሚሰጣቸው ኢትዮጵያዊ መንግሥት፣ ኢትዮጵያዊ የሕግ ተቋምና መንግስት የወከለው ኢትዮጵያዊ ባለሙያ የለም። ምክንያቱም የኢሕአዴግ ባለሥልጣናትና የሕግ ሰዎች ብቃትና የሕግ እውቀት ስለሌላቸው፣ ለኢትዮጵያዊ ዜጋና ለኢትዮጵያ ቆመው በዓለም አቀፍ መድረክ ሊያሸንፉ እንደማይችሉ አስቀድመው ያውቃሉ። ስለሆነም ጉዳዩን ሰምተው እንዳልሰሙ መሆን ነው ማምለጫቸው።

 

የኢሕአዴግ መንግሥት የቀጠረው አሜሪካዊ የሆነ የሕግ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ባለሥልጣናትን ግፍ ለመከላከል በየወሩ ብዙ ዶላር ሲከፈለው፤ ኢትዮጵያዊ ሴቶች ለእሪታቸው ማንም ሳይደርስላቸው እንደወጡ ይቀራሉ። የኢትዮጵያን ሪቪው አሳታሚና ዋና አዘጋጅ የሆነውን ኤሊያስ ክፍሌን፤ ለንደን፣ ዋሽንግተን ዲ.ሲና አዲስ አበባ ላይ መክሰስና የፍርድ መዓት እንዲቆለልበት ለማድረግ የሚችላቸው የለም። የሀገር ጥቅምና የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ሲሆን የብቃት ማነሱ ጉዳይ እንደተለመደው አደባባይ ስለሚወጣና በተበደሉ ዜጎች ምክንያት የገንዘብ ጥቅማቸውን ማጣት ስለማይፈልጉ፣ የኢትዮጵያውያንን እንባ በልብወለድ መልክ በፊልም እንደሚታይ አስመስለው ያልፉታል። ‘የሀገሪቱ የሕግ ሥርዓትና የስግብግብ ባለሥልጣናት ነጸብራቅ በመሆኑ እንግዲህ ምን ይደረጋል?’ ተብሎ በዝምታ የሚታለፍ መሆን የለበትም። ዜጎች ከዶላርና ከኢሕአዴግ ድርጅት በታች ሆነው የሚኖሩት ለስንት ዘመን ነው?

 

ኢሕአዴግ ያልሰለጠነ ግን የሰየጠነ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለዚህ’ኮ ነው ከቤት ውጭ ሰልፍ እንዳይደረግ በሩን ባለ በሌለ እጁ አንቆ የያዘው። የአስራ ሰባት ዓመት ንግድና የሃያ ዓመቱ ክምር ድንፋታ በአንድ ሰዓት ሰልፍ ፍርስርሱ እንደሚወጣ መች አጣው! ከዚያም መሄጃ የለውም፤ እሱም ያሳስባል፤ እንደውም ዋናው ነው። የወደብ ጉዳይ እንዲህ ናላን የሚያዞር ከሆነ “ሲፈልጉ ግመላቸውን ውኋ ያጠጡበት” አባባል አይሰራም ማለት ነው። እነሱስ “ግመላቸውን ያጠጡበት” ተባለ። ኢሕአዴግ ‘ላሙ’ ድረስ የሚሄደው ለምንድ ነው? ራሱ ከሕንድ ውቅያኖስ ሊጠጣ ነው ወይስ ግመል ሊያጠጣ? ግመሎቹስ እዚያ ድረስ እንዴት ነው የሚደርሱት? በኳንተም ሌቪቴሽን ባቡር እየተጫኑ? …..ኢትዮጵያ ለኢሕአዴግ የዝርፊያና የስልጣን መለማመጃ ሜዳ ሆና ቀረች። ከ2020 በኋላ፣ ‘ወደ ጅቡቲ የወሰድነውን የመብራት ገመድ ወደ ኢትዮጵያ ለመጎተት፣ መለስ አምስት ዓመት ሥልጣን ላይ ይቆይልን’ የሚባል ነገርም እንሰማለን። የኢሕአዴግ ሰዎች ፌዘኞች ስለሆኑ፤ ላሙ ላይ የከሰከስነውን ገንዘብ ለመመለስ፣ አሰብ ወደብ ላይ የባሕር ውኃ የሚጠጡ ግመሎችን ለማገድ፤ ሊቁ መለስ አምስት፣ አምስት ዓመት ይንከስልን’ ማለታቸው አይቀርም። አምስት አምስቱን እየነጨ፣ ኢትዮጵያንም እዳ በእዳ አድርጎ፣ ወህኒ ቤቶችንም በሕሊና እስረኞች አጭቆ፣ መቃብሮችን አብዝቶና በመቃብሮቹ ውስጥ ጥቁር ካባ ለብሶ እየተንጎራደደ ይከርምና የሥልጣን መጨረሻው እንደ ፕሬዚዳንታችን በዊልቼር ይጠናቀቃል ማለት ነው። የክፋት አስተዳደር ብዛት ሰለባ የሆነው አብዛኛው ዜጋም “ፕሊስ ወንዶች፣ እኛ በጣም በጣም መሮናል! በአሁኑ ሰዓት እኛ ወንድ አጥተናል! ወጥተን ወንድ መሆን ነው የቀረን! ሁላችሁም ሊሰማችሁ ይገባል! እኛ ወንዶች ሆነን ወጥተን አንናገር! የሆነ ነገር አናደርግ!” የመሰለውን ጥሪ እየሰማ ጭቆናውን ያጣጥመዋል። በርታ!


ግርማ ደገፋ ገዳ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!