ሲሳይ አጌና

የዛሬ 2 ዓመት በፓርቲዎች የክርክር መድረክ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 ወዲህ ስላሰፈነው አፈና እና የአፈናው ማሳያ የሆኑትን የጸረ ሽብር እና መሰል ሕጎችን በመጥቀስ ተከራከረ። የሕወሀት አገዛዝ ወደ ለየለት ዕመቃ የገባው በነጻ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ላይ እንደማይቀጥል በማመኑ እንደሆነም አመላከተ። ይህን ቀድሞ የተነበየውና ትንቢቱ በራሱ ላይ የተፈጸመበት አንዱዓለም አራጌ ነው።

 

 

የአፈናው ማሳያ እንደሆነ ባመላከተው ሕግ ከዓመት ከመንፈቅ በሁዋላ ወደ ወህኒ ቤት ተግዟል፤ የሰው ነፍስ አጥፍቶ ሞት በተፈረደበት የሕወሀት መልዕክተኛም የካቲት 7/2004 የግድያ ሙከራ ተደርጎበታል፤ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ ጠብቆ እግር እንደሚቆርጥ በምስጢር ያቀደውን አንዱዓለም በአደባባይ ነግሮን ነበር፤ እነሆ እግሩን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ጭምር ሊያስከፍሉት ነፍሰ ገዳይ አሰማርተው በቆሻሻ ስራ ተጠምደዋል። (እግር መቁረጥ- ከፖለቲካው ሜዳ ማስወጣት መሆኑ ነው)

 

በ1999 መጨረሻ የቅንጅት መሪዎች ሊፈቱ ዋዜማ አቶ መለስ "... እግር እንቆርጣለን " በማለት በምስጢር የተናገሩትን ከሕወሐት ሰዎች ውጭ ሌሎች የኢህአዴግ መሪዎች ስለመስማታቸው እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል፤ አቶ መለስን ክንፍ አልባ መልዓክ አድርገው የሚያመልኩባቸው አቶ በረከት እንደሰሙት ግን አያጠራጥርም፤ አቶ በረከት ለአቶ መለስ ቅርብ የመሆናቸው እና ሌሎች ነባሮች ሲገፉ ርሳቸው በመድረኩ ላይ በተዋናይነት የመቀጠላቸው ምስጢር ለአቶ መለስ ስልጣን የማያሰጉ እና ራሳቸውን በወጉ ግርጌ ስላስቀመጡ እንደሆነ ይታመናል፤ በእርግጥ እንደ አቶ መለስ እና አቶ ስብሃት ነጋ ጥላቻ አናታቸው ላይ የወጣ በመሆኑ በባለ አክስዮን ድርሻነታቸው (የጥላቻው አክስዮን ማለቴ ነው) በጫዋታው ሜዳ በቀጣይነት ውርውር እንዲሉ አስችሏቸዋል፤ በሕወሀት የትግል ስኬት ላይ ከጽናቱ ባሻገር ጥላቻ የተጫወተውን ሚና እና ከመቶኛ የነበረውን ድርሻ መፈተሽ ከህወሀት ጋር ለሚደረገው ትግል የሚያግዝ ይመስለኛል፤ ይህ ራሱን የቻለ ሰፊ ጉዳይ በመሆኑ ከርዕሱ እንዳንወጣ እንመለስ።

 

አቶ መለስ “ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃቸዋለን፤ እግር ሲያወጡ ግን እግራቸውን እንቆርጣለን” ያሉት የህወሀትን ሰዎች አዲስ አበባ "ጆን ትራቮልታ" መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ባነጋገሩበት ወቅት ነበር (አሁን የጠ/ሚ/ሩ ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚባለው) የቅንጅት መሪዎች መፈታታቸው የግድ ሲል እና የማይቀርበት ደረጃ ላይ ሲደርስ አቶ መለስ በአደባባይ በፓርላማ የቅንጅት መሪዎች እንደሚፈቱ ፍንጭ ሰጡ፤ ይሄኔ በጥላቻ አድገው በጥላቻ የጎለመሱት የሕወሐት የጦር አዛዦች ማጉረምረም ጀመሩ፤ የሽሮ ድንፋታ የሚሉት አይነት መሆኑ ነው፤ አቶ መለስ ጠሩዋቸው እና ቅንጅቶች ይፈታሉ ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴም ይመለሳሉ አሉና አስደነገጧቸው፤ ነገር ግን አታስቡ እግር አስኪያወጡ ጠብቀን እግራቸውን እንቆርጠዋለን አሉና የጥላቻ ደቀመዛሙርቱን አስተነፈሷቸው፤ በዊኪሊክስ ሰነዶች ላይም የህወሃት ሰዎች የቅንጅት መሪዎች ለምን ይፈታሉ ብለው ስለ ማጉረምረማቸውም ተጽፏል፤ ከአዲስ አበባው የአሜሪካ ኤምባሲ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተላከው ሪፖርት ላይ ማለት ነው።

 

አቶ መለስ ጣት ስለመቀንጠስ፣ እግር እና ምላስ ስለመቁረጥ የሚፎክሩበት የጠ/ሚ/ሩ ቢሮ አዳራሽ ለምን ጆን ትራቮልታ እንደታባለም ማስታወሱ ክፋት የለውም፤ በደርግ የስልጣን ዘመን ማክተሚያ አካባቢ ሕንጻው ሲሰራ የህንጻው ቅርጽ በወቅቱ ታወቂ ከነበረው አሜሪካዊ የፊልም አክተር ጆን ትራቮልታ የጸጉር ስታይል ጋር ስለሚመሳሰል በተለምዶ ያገኘው ስያሜ ነው፤ እንደዛሬው ዲሞክረሲ በሀገራችን ሞልቶ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከመፍሰሱ በፊት ቤተመንግስቱ ዋና በር አጠገብ የአውቶብስ ማቆሚያ ስለነበር ሕንጻውን በቅርጽ፣ የቤተመንግስት ጠባቂዎቹንም በመልክ መለየት ይቻል ነበር፤ አሁን ሕንጻውን በቴሌቪዥን ውስጡን ካልሆነ ውጩን አይተነው ስለማናውቅ ይሄኔ ወይ ሐየሎም አሊያም ሌላ የህወሀት ታጋይ ስም ሰጥተውት ይሆናል፤ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ለሶስት የህወሃት ሰዎች ሀውልት ሲቆም፣ ይቅርታ አንድኛው ሃውልት የቆመላቸው ለካ አባ ጳውሎስ ናቸው!! ሌሎቹ ጄኔራል ሳሞራ እና ጄኔራ ል ሐየሎም አርአያ ሲሆኑ፣ ከብአዴን የወጡት ጄኔራሎች ጄኔራል ተፈራ ማሞ እና ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ውለታቸው በሃውልት ሳይሆን በእስራት እየተመለሰ ቃሊቲ ይገኛሉ፤ ከኦህዴድ የወጡት ጄኔራል ከማል ገልቹ እና ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ ለጥቂት አምልጠው ጸረ ሕወሀት ትግሉን ተቀላቅለዋል፤ ውርደት በቃን ብለው አፈሙዛቸውን አዙረዋል፤ ማዕረጋቸውን ተገፈው የተባረሩት ጄኔራል አለምሸት ደግፌ እና ጄኔራል ኩመራ አስፋው የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አይታወቅም።ዕውነትም የዕኩልነት ዘመን!!

 

ወደ አንዱዓለም እንመለስ፤ ዛሬ በነፍሰ ገዳይ የህወሃት መልክተኛ የተደበደበው አንዱአለም አራጌ በምርጫ ክርክሩ ወቅት ያነሳው ይህንን በጆን ትራቮልታ ሕንጻ የተነገረውን የጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን ፉከራ ነበር፤ ደብዳቢው የኦሮሞ ተወላጅ ስለሆነ የኦህዴድ መልዕክተኛ ነው የሚል የዋህ ካለ ቃሊቲ እስር ቤት ኦሮሞዎች በወህኒ ቤቱ ፍርግርግ ውስጥ እንጂ በስህተት እንኳን ስልጣን ላይ እንደሌሉ የዓይን ምስክሮች ብዙዎች ነን፤ ዛሬ አንዱዓለም ላይ የተፈጸመው ድብደባ አንዱዓለምን ለመስበር ከመሞከር ባሻገር በኦሮሞ ተወላጅ መከወኑ የፖለቲካ ዓላማ የለውም ማለት አይቻልም፤ ምርጫ 1997ን ተከትሎ የቅንጅት መሪዎች እስር ቤት በነበሩበት ወቅት በቅንጅት ታሳሪዎች እና በኦነግ ሳቢያ የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ለማጋጨት የተሞከረውን እዚህ ላይ ማስታወሱ የዛሬውን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፤ በእስር ቤት ውስጥ በቅንጅት መሪዎች እና በኦነግ ሳቢያ በታሰሩ ኢትዮጵያውያን መሃል ግኑኝነቱ እጅግ የጠነከረ መሆኑ እስር ቤቱን በሚያስተዳድሩት የሕወሀት ሰዎች እንዳልተወደደ ምልክቶች ሲታዩ ቆይተዋል፤ በሂደትም ሁለቱን ወገኖች ለማጋጨት አንዳንድ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዱዓአለም አራጌ ለቤተሰቦቻቸው ከኦነግ ነፍሰ ገዳዮች ጋር ታስረናል በማለት ተናግረዋል የሚል ወሬ ተናፈሰ፤ የወሬው ምንጭ የሕወሃት ሰላዮች መሆናቸው እስኪታወቅ ውዥንብሩ ቀላል አልነበረም።

 

ወህኒ ቤቱን ከላይ እስከታች በሃላፊነት የወረሩት የሕወሃት ታጋዮች ናቸው፤ የመንግስት እስር ቤት ሳይሆን የህወሀት የምርኮ ማዕከል ነው የሚመስለው፤ የጤና ባለሙያዎቹም በአብዛኛው እነሱ ሲሆኑ፣ በትግል ሜዳ የልምድ ሐኪም የነበሩትን ነርስ እያሉ አስቀምጠዋቸዋል፤ ፐሮስቴት (የሽንት ፊኛ ችግር) አለብኝ ያሉትን እስረኛ የሕወሃቱ ታጋይ ሀኪም የሽንት ምርመራ እንዳዘዘላቸው ሰምተን እስረኛ የጤና ባለሙያዎች ሲስቁ እኛንም ፈገግ አሰኝተውናል፤ በሽንት ምርመራ የፕሮስቴት ችግር ማወቅ ይቻላል የሚል የምርምር ውጤት ይፋ መሆን የጀመረው እ/ኤ/አ ከ2008 ጀምሮ በመሆኑ ተራራውን ያንቀጠቀጡት ሰዎች የሳይንሱንም ዓለም ቀድመው እያንቀጠቀጡት ይሆን? እ/ኤ/አ 2006 ላይ የሳቅነውስ ዛሬ እንፈር? ለሆድ ቁርጠትም፣ ለቁስልም፣ ለጨጓራም፣ ለአሜባም የሚታዘዝልን ፓናዶል ነው እያሉ እስረኞች በግምገማ ሰዓት ቅሬታ ማቅረብ መብታቸው ቢሆንም፣ መፍትሄ ማግኘት መብታቸው ሳይሆን ግን ቀጥለዋል፤ እኔም በግሌ የአፍንጫ ሳይነስ እያስቸገረኝ በሌላም በኩል ጥርሴን እያመመኝ ታጋዩ ሀኪም ፊት ቀረብኩኝ፤ ከሁለት አንዱን ምረጥ እና ታከም ሁለቱን በአንዴ አላክምህም ሲል ገደበኝ፤ አባባሉ ቢገርመኝም ለሁሉም የሚታዘዘው ያው ፓናዶል ስለሆነ ላይሰማኝ ምን አጨቃጨቀኝ በማለት ለሳይነስ የሚሆን መድሃኒት እንዲሰጠኝ ጠይቄው የጥርሴን ጉዳይ አሰንብቼው ተመለስኩ፤ እንደምንም ፖሊስ ሆስፒታል ያልደረሰ ታማሚ የእነዚህ መጫወቻ ነው የሚሆነው።

 

የመንግስት እስርቤትን በእውነት የመንግስት እስር ቤት ለማድረግ 20 ዓመት አይደለም 20 ወራት እንኳን ከበቂ በላይ ነው፤ አብረዋቸው የታገሉት የብአዴን እና የኦህዴድ ሰዎች ከ20 ዓመት በሗላ ለእስር ቤት ሃላፊነት እንኳን ተመጣጣኝ ውክልና አለማግኘታቸው የሚያሳፍረው እነ ብአዴንን ብቻ ሳይሆን፣ ማሰብ የሚችሉ የሕወሀት ደጋፊዎችን ጭምር መሆን ነበረበት፤ በዘረኝነት ውስጥ ሎጂክ እና ህሊና ቦታ ስለሌላቸው የጥላቸው ማህበር እስኪፈርስ የሕወሐት ደጋፊዎች የሚያስብ ሕሊና፣ የሚሰማ ጆሮ አይኖራቸም፤ እነዚህ የእስር ቤት ሃላፊዎች ደግሞ በሕወሀት ጥላቻ ያደጉ፣ በአብዛኛው ከሕብረተሰቡ ተገልለው በራሳቸው ዙሪያ የሚኖሩ በመሆናቸው እነርሱ የሚያራምዱት ጥላቻ በእርግጥ የሚጠበቅ ነው፤ በፖለቲካ ልዩነት የታሰረ እና የሕወሀትን ታላቅነት፣ የአቶ መለስን ሊቀሊቃውንትነት ያልተቀበለ ሁሉ ለእነሱ ጠላት ነው፤ እንኳን ኢትዮጵያን አፍሪካን እንመራለን የሚለውን እብደታቸውን ተከትሎ ልብሱ ከፍከፍ ያላደረገ በነርሱ መስፈርት ጤነኛ አይደለም፤ ለከርሞ የሚያብድ ዘንድሮ ልብሱን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጀምራል የሚለውን ብሂል ልብ ይሏል! እነዚህ ወገኖች በነፍስ ማጥፋት፣ በዘረፋ ወዘተ ተከሰው ከታሰሩት ውስጥ በአብዛኛው ታሳሪ የህወሀት አባላትን በሰላይነት በማስቀመጥ ንጹሃንን ሲያጠቁና ሲያስጠቁ ኖረዋል፤ በ1998 ዓ.ም ጋዲሳ ሂርጳሳ የተባለ እና በኦነግነት ወንጅለው ያሰሩትን የአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሞባይል ይዘህ ተገኝተሃል ብለው ባደረሱበት ድብደባ፣ ፍርድ ቤት ቀርቦም ሰሚ አጥቶ በቀጠለበት ማሰቃየት ቃሊቲ ወህኒ ቤት ሕይወቱ አልፏል፤ ልማደኞች ናቸው ለማለት ነው።

 

አንዱዓለም ላይ የተፈጸመው ድብደባ መመሪያው የወረደው ከእስር ቤቱ ሃላፊዎች ሳይሆን ከላይ ምናልባትም የደህንነት ሃላፊውን እነ ጌታቸው አሰፋን አልፎ ጠ/ሚኒስትሩ ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ይታመናል፤ ለዚህ መነሻው ደግሞ የስዊዲን ጋዜጠኞች መፈታታቸው የማይቀር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊታይ ይገባዋል፤ የአውሮፓ ሕብረት በሊዊ ሚሼል በኩል ለአቶ መለስ ጠንካራ መልዕክት በማስተላለፉ የስዊዲናውያኑ ጋዜጠኞች መፈታት የማይቀር እና ያበቃለት ሆኗል፤ በቅንጅት መሪዎች ክስ ወቅትም በአሜሪካ መንግስት ጫና በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሶስት ወራት ውስጥ ክሳቸው መሰረዙ ይታወሳል፤ ስዊዲናውያኑ ጋዜጠኞች ከተፈቱ ኢትዮጵያውያንንም በተመሳሳይ መልቀቁ አቶ መለስ እንደ ልማዳቸው ለነጭ ተንበረከኩ ከሚል ትችት ያድናል፤ ስለሆነም ሌሎች የአሸባሪነት ታርጋ የተለጠፈባቸውን ሁሉ የመፍታት እቅድ እንዳለ ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ፍንጭ ሰጥተዋል፤ እንቅስቃሴም በይፋ ተጀምሯል፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ ታሳሪዎቹ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው።

 

በቀረበበት ክስ እየተገረመ፣ በአቃቤ ህግ የገለባ ክምር እየሳቀ ችሎቱን የሚያሳልፈው እና በፍርድ ቤት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አንዱኣለም አራጌ ይቅርታ አይጠይቅም የሚል ዕምነት በገዢዎች ሰፈር እንዳለ ይታመናል፤ በምርጫ 1997 ማግስት በታሰረበት ወቅትም የቅንጅት መሪዎች ፈርመን እንውጣ ሲሉ አንፈርምም ካሉት ሰዎች አንዱ አንዱዓለም ነበር፤ አንዱዓለምን በእስር ቤት ውስጥ ሰላም ብንነሳው በቀድድነው ቦይ ይፈሳል በሚል ስሌት ድብደባው እንደተቀነባበረ መገመት ይቻላል፤ ድብደባ ወይንም ሌላ ማስገደጃ በእስክንድር እና በሌሎችም ላይ ይቀጥል ይሆናል። ከዚህ ውጭ አንዱዓለም አደገኛ ቦዘኔ ክልል በቅጣት ሲወስዱት እንኩዋን አደገኛ ቦዘኔ ከተባሉት ጋር የሰላም ግዜ ያሳለፈ ተግባቢ መሆኑን በድርጊት አስመስክሮ በሰላም ተለይቷቸዋል፤ ከአንዱዓለም ጋር ከአንድ ዓመት በላይ አብሬው ታስሬያለሁ፤ ከገዢዎች እና በጭፍን ከሚያገለግሉት ፖሊሶች ጋር እንጂ ከእስረኛ ጋር ተከባብሮ ሲኖር እንጂ መጥፎ ቃላት ሲለዋወጥ አልሰማሁም።

 

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሽብር ክስ እየተባለ በሚቀርበው ውንጀላ እና በሚታዩ ማስረጃዎች ባዶነት ላይ የያዘው ከፍተኛ ግንዛቤ ገዢዎቻችን ለእርጥባን ሲሉ መውጫ ቀዳዳ እየፈለጉ መሆኑንም ያመላክታል፤ የሕወሀቱ ሊቀ ሊቃውንት አቶ መለስ ዜናዊ የስዊዲን ጋዜጠኞች ላይ በፍርድ ቤታቸው በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማቓረጥ በሚል የጥፋተኛነት ውሳኔ አሰጥተው፣ ሽብርተኛ መርዳት የሚለውን ክስ ጥለው በቀላል እስር ቢለቋቸው በኢትዮጵያ ነጻ ፍርድ ቤት አለ የሚል ብዥታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ በመፍጠር የፖለቲካውን ቁማር በወጉ ባስኬዱት ነበር፤ በዘረኝነት እና በአመራር ችግር ካልሆነ በቀር በፖለቲካ ብልጠት የማይታሙት መለስ ዜናዊ የፖለቲካ ብልጠትም የ”ኤክስፓየሬሽን ዴት” እንዳለው ያመላክቱን ይዘዋል፤ አሊያ እውነትም ምክር መስማት ጀምረዋል ማለት ነው፤ ከብሄራዊ ጸጥታ አማካሪያቸው አለቃ ጸጋዬ በርሔ። የሀገሪቱ ብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ሁሌ ከሕወሃት የሚሆንበት፣ የደህንነት ሃላፊዎችም በተመሳሳይ ከአንድ ምንጭ የሚቀዱት እስከመቼ ይሆን? ”አኬልዳማ” የሚያቀነባብር አቶ ጌታቸው አሰፋ እና አቶ ኢሳይያስ ወልደጊዮርጊስን የሚተካ ከኦሮሞ፣ አማራ፣ ደቡብ ወዘተ የለምን? ኦህዴድ እና ብአዴን እንዲታመኑ ሌላ 20 ዓመት ይበቃ ይሆን? ወይንስ ብሄራዊ ጸጥታ የሚባለው ሁሌም እኛ እንደ ምንገምተው እና እናንተም እንደቆማችሁለት አስከመቼ ይቀጥላል? መልስ አላችሁ? እነሱ ካልመለሱት ሌሎች የመመለስ ግዴታ አለብን።እስከዚያው ወደ አንዱ ዓለም እንመለስ፤

 

አንዱዓለም በ2002 የምርጫ ክርክር ከ97 ጀምሮ የሰፈነውን ፍርሃት ለመስበር እና በምርጫ ሂደቱም ላይ መነቃቃት እንዲኖር አብይ ሚና ተጫውቷል፤ በ1997 ምርጫ ክርክር ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር ኮከብ የነበረው አቶ ልደቱ አያሌው በ2002 ምርጫ ከምርጫ 97ቱ በተሻለ ተዘጋጅቶ ብዙ የሮጠ ቢሆንም፣ ለቲያትሩ ድምቀት ባሳየው የትወና ችሎታ ያልተገረመ የለም፤ ከቁም ነገር የወሰደው ስለመኖሩ ትዝ የሚለኝ አንድ የቀድሞ የብአዴን ሰው ከአሜሪካ የሰደዱት መጣጥፍ ብቻ ነው፤ ..አንዱዓለም ከልደቱ ጋር አንድ ፓርቲ ውስጥ ብዙ ዓመታት ያሳለፉ ሲሆን፣ ልደቱ የፓርቲው ዋና ጸሃፊ በነበረበት ወቅት አንዱዓለም ምክትል ነበር፤ ሕወሐት እውነተኛ ፈተና ላይ ሲወድቅ ከሕወሃት የተለዩት ከሕወሀት ጋር እንደቆሙት ሁሉ ልደቱም ቡግና ላይ የካድሬ ስልጠና ወደ ሰጡት ሲመለስ፣(1) አንዷለም ወደ እስር ቤት ተወሰደ፤ ጨለማ ቤትም አስገቡት፤ አደገኛ ቦዘኔ በተባለ ክልልም አሰሩት፤ ከላይ እንደገለጽኩት ሃምሌ 12/1999 የተፈረመውን የይቅርታ ሰነድ አንፈርምም ብለው ካንገራገሩት ሶስት ሰዎች አንዱ ነበር፤ እንፈርም እያሉ የሚያግባቡት ወገኖች ሰላማዊ ትግል ስላበቃ ወጥተን ሌላ መስመር እንያዝ እያሉ ሲሰብኩ፣ ሰላማዊ ትግል አላበቃም የምንለውስ ፈርምን የፖለቲካ ሞት ልንሞት ነውን? እያለ በሰላማዊ ትግል ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየው አንዱዓለም አራጌ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ሌሎችም በአሸባሪነት ከታሰሩ ዛሬ መጋቢት 3/2004 ስድስት ወር ሞላቸው።

 

በምርጫ 2002 ክርክር የዝምታውን ድባብ ከመግፈፍ ባሻገር፣ በዚሁ ምርጫ 2002 ክርክር የተናገረው ሳንሱር የተደረገበት ብቸኛው ተከራካሪም አንዱዓለም ነበር፤ አንዱዓለም የቅንጅት መሪዎች ጎራ ለይተው ሲቧደኑ ሁለቱን ወደ አንድ ለማምጣት ብዙ ጥሯል፤ በመጨረሻ አንድነትን ከተቀላቀለ በሁዋላ በፓርቲው ውስጥ በሚያደርገው ጉልሕ እንቅስቃሴ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ላይ ሲደርስ እግር ሲያወጡ እግር መቁረጥ የጆን ትራቮልታ አዳራሽ እቅድ ወደ ገቢር ተለወጠ፤ የሽብር ሙከራ ላይ ስለመሆናቸው አስተማማኝ ማስረጃ የተባለው ለፍርድ ቤት ቀረበ፤ ችሎቱን የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚናገሩት አንዱዓለም ማስረጃ ተብሎ በሚቀርበው ክምር ይስቃል፤ በቴሌዥን እየተሰራባቸው ያለውን ፕሮፓጋንዳ እንዲያስቆም ፍርድ ቤቱን በመጠየቅ ፍርድ ቤቱ ትዝብት ላይ የጣለውን ምላሽ እንዲሰጥ ምክንያት ሆኗል፤ ያልተፈረደባቸው ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው ተብሎ በቴሌቪዥን የቀረበውን አኬልዳማ ፊልም ፍርድ ቤቱ ለህዝብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው ብሎ ሲናገር የተሸማቀቁት ሕግ የተማሩት ብቻ ሳይሆኑ፣ የሚያመዛዝን ሕሊና ያላቸው ሁሉ ናቸው፤ አስፈጻሚው አካል ድርጊቱ ሕገ ወጥ መሆኑን አምኖ፣ ራሴን ለመከላከል ሕግ ጥሻለሁ ሲል በአደባባይ ማለትም ፓርላማው ፊት ባመነበት የዳኞቹ ውሳኔ የፍትህ ስርኣቱ በአፍጢሙ መደፋቱን ብቻ ሳይሆን፣ ላይድን ጣዕር ላይ መሆኑን፣ በአጭሩ ኮማ ውስጥ መግባቱን ያመላከተ ሆኖ አልፏል። እነዚህ ዳኞች የሚማሩበት ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ድንጋይ ማምረቻ እንደሚባል ፓርላማው ፊት አቶ መለስ ባሉበት ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ነግረዋቸው ነበር፤ አቶ መለስ ምክር በደምብ ይሰሙ የለ! በደንብ አሻሽለው ባልጩት ማምረቻ አደረጉ እና አረፉት!


I(1) አቶ በረከት በመጽሃፋቸው ከአቶ ልደቱ ጋር ትውውቃችን ስልጣን ሳንይዝ ቡግና ላይ ነው ሲሉ አስፍረዋል - መጋቢት 03/2004

እነሆ አድራሻዬ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!