ሰይድ ሐሰን (Murray State University)- መጋቢት 2/2004 ዓ.ም.

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም አነጋጋሪ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ሙስና ነው። ሙስና ዋና መነጋገሪያ ሆኖ አሁን የተገኘው፤ በአዲስ መልክ ስለተስፋፋ አይደልም። ምክንያቱም ሥር ከሰደደ በርካታ ዓመታት አልፈውታልና! ይህንንም በሚመለከት እኛም ፅፈናል፤ ተናግረናልም፤ ያውም ብዙ! እንደነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ያሉ ምሁራንም፤ በኢትዮጵያ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመታደገ የሚደረገው ድርጊት “አሳ ነባሪዎችን (ትላልቅ አሳዎችን) የማይደፍርና ነገር ግን ትናንሽ አሳዎችን የሚያባርር ነው” ብለውትም ነበር። በተለይ ሁለት ጋዜጦች፤ ሪፖርተርና ፍትህ ደጋግመው ሙስና የተደበቀ ፍንጂ እንደሆነ ደጋግመው አሳስበው ነበር። ግን ከመንግሥት በኩል ማ ሰማ?!

 

 

ሙስና አሁን መነጋገሪያ ሆኖ ከቀረበበት ምክያንቶች ጥቂቶቹን ለማለት ያህል፤ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዘናዊ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት የነገሱ መሆናቸውን ማመናቸውና በመደጋግማቸው ነው። ለምሳሌ ከአንድ ዓመት በፊት ለሰበሰቧቸው ነጋዴዎች ባቀረቡት ወቀሳ፤ አላግባብ እየከበሩ ያሉ ሰዎች የሰበሰቡትን የሀብት ብዛትና  ምንጭ  ለመሸፈን ሲሉ በተለያዩ ስሞች፤ አቅመ-አዳም ባልደረሱ ልጆቻቸውንም ጨምረው እንደሚሰይሙት/እንደሚያስመዘግቡት፤ ከዚያም አልፎ አንዳንዶች የንግድ ፈቃዶቻቸውን  በውሾቻቸው ስም ሳይቀር እንደሚስመዘግቡት (የንግድ ፈቃድ እንደሚያወጡ) ነገሩንና፤ ከዚያም አልፈው ባልሀብቶች ብረት ቀጥቅጠው እንዱስትሪ ከመሥራት ይልቅ፤ ቤቶችን በመሥራትና በማከራየት፤ እንደተሰለፉ፤ የሰሯቸውን ቤቶች ለውጭ ሀገር ሰዎችና ኤምባሲዎች በዶላር መልክ እንደሚያከራዩ፤ ውጭ ሀገር ቤቶችን እንድሚገዙ፤ እንደሚገነቡ፤ በውጭ ምንዛሬ መልክ የሚከፈላቸውም ኪራይ አግሪቱን ለቆ እየወጣ መሆኑንና፤ በሳቸው ግምት በቤት ኪራይ መልክ አገሪቱን ለቆ የወጣው ሀብት በአሜሪካ ዶላር እስከ ሁለት ቢሊዮን እንደሚደረስ ነገርውን ነበር። በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ደግሞ፤ ይህንኑ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሰጥተውት ከተናገሯቸው መካከል “...የመንግሥትን ግብር ግን አሁን መንግሥት ብቻ አይደለም እየሰበሰበ ያለው። ከመንግሥት ውጪ የመንግሥትን ግብር እየሰበሰቡ ያሉ ሁለት ክፍሎች አሉ። አንደኛው የመንግሥት ሌባ ነው። ሁለተኛው የግል ሌባ ነው። እነዚህ ሁለቱ አንድ ላይ ሆነው ለመንግሥት መግባት የሚገባውን ይካፈሉታል” ስላሉን ነው።

 

ሁለተኛው ደግሞ የዓለም ባንክ አዘውትሮ በየሀገሮች ውስጥ የሚያደርገው የሙስና አሰሳ (ጥናት) በኢትዮጵያም ጊዜው ደርሶ፤ “ጥናቱ (አሰሳው) መደረግ አለበት ስላለና፤ ቆይቶም፤ ይህንኑ ጥናት (አሰሳ) ለማድረግ ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል የሚባለው የአማካሪ ድርጅት ተቀጥሮ ይህም ድርጅት “የኢትዮጵያ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን” ተብሎ ከሚጠራው ጥርሰ-ቢስ ደርጅት ጋር በመተባበር፤ ጥናቱን ጨርሶ ስላቀረበ ነው። በድርጅቱ ተጠንቶ የቀረበው ጥናት (አሰሳ) ለኢሕአደግና ለደጋፊዎቹ (በአቶ መለስ አባባል በሌባዎቹ) በሚጥም መልክ ተጠናቆ እስከሚቀርብ ድረስ፤ እንዲሁም ሕዝብን እንዳያስበረግግ (እንዳይስቆጣ) ሆኖ እስኪቀርብ ድረስ፤  የስንኩሉን የጥናት ውጤት ከወድሁ ለማሽመድመድ፤ ለማልኮፍኮፍና ለማርከስ ተብሎ የተደረገ ይመስላል። የአቶ መለስ ዘናዊም “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚባለውን ማደናገሪያ ሀሳብ በሚሰለች መልኩ ደጋግመው መናገራቸው፤ ከዚሁ ከማልኮፍኮፍና ከማንቀዝ (ከማርከስ) የመነጨ እርኩስ ሀሳብ ነው ብለው የሚያስቡ በርካታ ናቸው። ሆኖም ግን ይኸው ለጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዘናዊ ተጠሪ በሆነው የኢትዮጵያ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ትብብርነት የተደረገው የሕዝብን አስተሳሰብ የሚዳሥሰው ጥናት (corruption perception survey) ደካማ (ተልካሻ) እንደሚሆን ቢጠበቅም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቃቸውንና በየእለቱ የሚጋፈጣቸውን ገፍጋፊ ሙሰኞች ላይ ለዘብ ያለ ክሱን በማቅረቡ ሊመሰገን ይገባዋል። ከነዚም መካከል አምስቱ በሙስና የናጠጡ የመንግሥት ተቋማት፤ ፍርድ ቤት፤ ፖሊስ፤ ግምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን፤ የወረዳ አስተዳደርና የማዘጋጃ ቢቶች እንደሆኑ ተነግሮናል።

ሦስተኛው የሕወሃት መስራችና በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የሚታሙት አቶ ስብሀት ነጋና የኮሙኒኬሽን ድሬክተር (ሚኒስተር) አቶ በረከት ስሞን አገሪቱን ወጥሮ የያዛት የጠነባ ሙስና አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን መግለፃቸው ነው። አቶ ስብሀት ነጋ “በኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለው ሙስናን ለማጥፋት ፍላጎት እንጂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብሎ ነገር የለም። ይኼ በሌለበት ተግባርም ውጤትም አይኖርም። ቁርጠኛ ሌባ አለ፤ ቁርጠኛ ተዋጊ ግን የለም” ካሉ በኋላ ጨምረውም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሰኞች ላይ እንዲዘምት ጠይቁ። የሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎችም እንደዘገቡት፤ አቶ ስብሀት ነጋ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሳተፉበት ታላቅ የፖለቲካ ሙስና ወይም በእንግሊዝኛው “ግራንድ ኮራፕሽን” እንጂ ጥቃቅን ሙስና (ፔቲ ኮረፕሽን) አይደለም የሚል ክርክርና የሀሳብ አዝማሚያ ሲነሳ፤ ይህንን ለመካድና ለመቃውም ቃጣቸው። ሀሳባቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲገነዘቡ፤ እንደመደናገርና ግራ መጋባት አሉና ከገቡበት አጣብቂኝ ለመውጣት ሲሉ የፈረደበትን የሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ከሚሽን ተብየውን “ኮሚሽኑ ለምን ኃይሉን አያሰባሰብም? በሁሉም የሙስና ዓይነቶች ላይ ለምን አይዘምትም? ሕዝቡንም በሙሰኞች ላይ ማሰለፍ ይችላል” ብለው ከሰሱ (አሟከኩ)። ልክ ነዎት አቶ ስብሀት፤ ይህ ጥርሰ-ቢስ ድርጅት በመጀመሪያስ የተቋቋመው ለዚሁ አይደል!

 

የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ አቶ ስብሀት ለመካድ የፈለጉትን ታላቅ ፖለቲካዊ ሙስና (ግራንድ ኮራፕሽን) በኢትዮጵያ መኖሩን ብቻ ሳይሆን፤ ሀገሪቱን ከሚፈታተኗት አንዱና በቀዳሚ ደረጃ የሚገኝ ችግር መሆኑን፤ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲም ሆነ ፓርቲውን ተጠግተው አላግባብ ሀብት የሰበሰቡትን ግለሰቦችና “ሀብታችን” የሚሉትን ሁሉ ጠራርጎ ሊውስድ እንዲሚችል፤ ይህ ከሆነም ሁሉም ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል ለማሳየት ነው። ይህ በክፍል ሁለት ከዚህ በታች ይቀርባል።

 

አቶ መለስ “ኪራይ ሰብሳቢ!” “ኪራይ ሰብሳቢ!” “ኪራይ ሰብሳቢ!” ... እያሉ ከዓመት በላይ መለፍለፋቸው ሲገርመንና ሲያናድደን የከረመው አንሶ፤ አሁን ደግሞ “የመንግሥት ሌባና የግል ሌባ” ተስማምተው የሀገሪቱን ሀብት እየመነዘሩት መሆናቸውን፤ ለልማት የሚሆነውን ገንዘብ እያሳጣ መሆኑን፤ “እድገት” የሚሉትንም ተስፋ  እያጨማለቀባቸውና እያሽመደበደ መሆኑን፤ ሲነግሩን፤ የማናቀውን ማሳወቃቸው አይደለም ብለው የሚያስቡ በርካታ ናቸው። በብዙዎች አስተሳሰብ፤ አንዱና ዋናው አላማቸው፤ ኢትዮጵያን ወጥሮ የያዛትን፤ የተከሉት መንግሥታዊ  አወቃቀርና ሥርዓት የፈጠረውን ትልቁን ችግር ለማርከስ፤ ለማሸማደድ፤ ለማልኮፍኮፍ (ዴማጎግ ለማድረግ) ነው። የአቶ ስብሀት ነጋም ስለ ሙስና ማውራት አንድም የኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ጥናት (አሰሳ) ከመውጣቱ በፊት ቀድመው ስለችግሩ በመናገር በአንድ በኩል እንደ መሲህ ሆነው ለመቅረበና አቶ መለስ እንደሚያደርጉትም በኢትዮጵያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ድርጅት ትብብርነት የተደረገው ተልካሻን ጥናት (አሰሳ) አልኮፍኩፈው ለማርከስ፤ ለማጃጃልና ለማጣጣል ያቀዱት ይሆናል ብለው ነው የሚሉ ብዙ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ እነ አቶ መለስና አቶ ስብሀት የኢትዮጵያን ሀዝብ እያዋከበ ያለውን የሙስና አባዜ (ችግር) መናገራቸው፤ “አድማጮቻቸውንና በአጠቃላይም የኢትዮጵያን ሕዝብ ስለሚንቁ ነው” ይላሉ። በአንድ ምሁር ጓደኛየ አስተሳሰብ ደግሞ፤ የአቶ ስብሐት ነጋ አነጋገር፤ የአቶ መለስ መንግሥት በሙና ቀውስና ማጥ ላይ ስለገባ ይህንን ችግር በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ላይ አሟክከው ከአቶ መለስ ትከሻ ላይ ለማውረድና የተለመደውን የፖለቲካ የክርስትና አባትነት ግልጋሎታቸው ለመለገስ ያደረጉት ይምስላል፤ በተጨማሪም፤ የአቶ መለስ ስለሙስና ማንሳታቸውም፤ መንግሥታቸው በቅርቡ ያወጣውን የከተማ መሬት የሊዝ አዋጅ አልቀበልም ስላለ፤ ሙስናውን ከከተማ መሬት ይዘት ጋር አያይዘው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሊዝ አዋጁን እንዲቀበል ለማግባባት ያደረጉት ጥረትም ይመስላል ይላሉ። አንዳንዶች ከዚህ በላይ የሰፈሩት ሀሳቦች ወይ አልዋጥ ያሏቸው ጉዳዩን በበጎ መልክ እንድናየው መንገድ መስጠት አለብን የሚሉት ደግሞ (በተወሰነ መልኩ እኔንም ጨምሮ)፤ “ምናልባት የችግሩን ግዙፍነትና የሚያስከተለውንም አባዜ ተገንዝበው፤ ከፍርሃትና ከመርበርበድ ... የተነሳ ነው፤ ይህም አስተሳሰብ መልካም ጎን አለውና ልናበረታታቸው ይገባል” የሚሉም አሉ።

 

ሙስናን አልኮፍኮፎ ማርከስ ከተነሳ አይቀር፤ ኮርጀው ወይም የራሳቸው አስመስለው ቀድተው መፃሀፍ ፅፈዋል ተብለው የሚታሙት (ይህ ሀሜታ ትክክል ከሆነም የወጣለት ሌብነት ነው!) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር  አቶ በረከት ስሞንም እሳቸው እራሳቸው በሚቆጣጠሩት የመገናኛ መሣሪያ ቀርበው ቃለ-መጠይቅ ሲሰጡ፤ ነገሩን ለማለት ብቻና በማይገናኝ መልኩ ገስግሰውና ጀርጅረው፤ ኢትዮጵያን ወጥረው ከያዟት መቅሰፍቶች መካከል ዋናው “ኪራይ ሰብሳቢነት ነው” ብለው እንደተናገሩ ተዘግቧል። አቶ በረከት ስሞን “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚለው የተወሳሰበ ሀሳብ የገባችው አይመስለኝም።ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ይህንን ሀረግ ደጋግመው ስለሚሉት አቶ በርከትም የበቀቀነት (parrot) ልማዳቸውን ለማድረስ (ሱሳቸውን ለማርካት)ነው መሰል፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያሸማቀቀና እያዋከበ ያለውን “ኪራይ ሰብሳቢነት” አልኮፈኮፉት፤  አጃጃሉት፤ አረከሱት። ይህ ትልቁን ችግር የማራከስ ተግባር ምንጩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመናቅ የመነጨም ይሁን፤ ለማደናገር፤  ወይም ችግሩን ለማርከስ... እንደነ አቶ በርከት ያሉ ሰዎች ችግሩን ሲያረክሱት ያበሳጫል! በጣም! ስለሙስናው ስንፅፍና ስንናገር የነበረነውንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያናዳል፤ በጣም!

ንደቱንና ብስጭቱን ለማሳየት በህይወቴ ካየሁት ተጨባጭ ታሪክ ጋር እንዳያይዘው ይፍቀዱልኝ።

 

አንዳንዶቻችሁ እንደምታውቁት፤ በንጉሡ ዘመን የተለያዩ የመሬት ሥሪቶች ነበሩ። በወሎ ክፍለ-ሀገር ከነበሩት የመሬት ስሪቶች መካከል ሁለቱ  የማደርያ መሬት እና የጉልት መሬት የሚባሉት ነበሩ።  የማደርያ መሬት የሚባለው ጊዜያዊ በመሬት የመጠቀም መብት የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም ይሰጥ የነበረው በብዛት ለወታደሮችና ለሲቪል ሠራተኞችም ነበር::   መሬቱን የሚጠቀሙበት ጭሰኞችም በአገልግሎት ላይ እስካሉ ብቻ ነበር:: አገልግሎት ካስተጓጎሉ ወይም አስራት “በቂ ነው” ተብሎ በሚታሰብ መልኩ  ካልከፈሉ ግን መሬቱን የመነጠቅ ዕድሉ ሰፊ ነበር:: የጉልት መሬትን የተመለከትን እንደሆነ ጉልት በራሱ በመሬት የመጠቀም መብት ሳይሆን በመሬቱ ላይ በሰፈሩ አራሾች ላይ የነበረ መብት ነበር:: ጉልት የሚሰጠው ለመኳንንት፣ ለሹማምንት፣ ለጦር አለቆች፣ ለንጉሣውያን ቤተሰቦችና ለቤተክርስቲያኗ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን) ሲሆን፣ ባለጉልቱንም በመሬቱ ላይ በሰፈሩ ሰዎች ላይ የማስተዳደር፣ የዳኝነትና ግብርና አስራት የመሰብሰብ ሥልጣን ነበረው:: በዚህ የመሬት ስሪት መሠረት ባለርስቱ መሬቱን በማልማት የሚጠቀም ሲሆን፣ ባለጉልቱ ደግሞ አራሹ ያፈራውን በግብርና በአስራት መልክ በመቀበል ይተዳደር ነበር። እንደሚታወቀው፤ አልጋ-ወራሽ አስፋ ወሰን የወሎ እንደራሴ ነበሩ፤  በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በዓመት(ሲመቻቸው)፤ ካልሆነም በየሁለት ወይም ሦስት ...  አመቱ ወሎን ይጎበኙ ነበር። ወሎን ሲጎበኙም አጅበዋቸው የሚመጡ ባላባቶች፤ ወይንም መሬት ተሰጥቷቸው ባላባት ለመሆን የሚፈልጉ ነበሩ። አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንም የወሎ ክ/ሀገር የበላይ ገዢ ስለነበሩም፤ የማደሪያና የጎልት መሬቶችን ከአንዱ ባላባት (አባቢድራ) ነጥቀው ወደ ሌላው ያዛውሩት ነበር። በነዚህ የመሬት ሥሪቶች ላይ የሰፈረ ጭሰኛም ደስተኛ አልበረም። ደስተኛ ካለመሆኑም አልፎ፤ አልጋ ወራሽ አስፋ-ወሰን ወደ ወሎ ሊመጡ ነው ሲባል ይጨነቅ፤ ይሸበርም ነበር። ለጭንቀቱና ለሽብሩ አንዱ ምክንያት ጭሰኞች ከተላመዱትና ካወቁት ባላባት ወደማያውቁት ባላባት (አባቢድራ) መዛወራቸውን ስለማፈልጉት ነበር። ሌልው ደግሞ፤ በአዲስ መልክ የተተከሉት ባላባቶች (አባቢድራዎች) የሚያስከፍሉት የምርት ድርሻ በጣም ከፍ እያለ መምጣቱና በአዲስ መልክ የተተከሉት ባላባቶች፤ የጭሰኝነቱን “መብት” ካንዱ ነጥቀው ወደ-ሌላው ጭሰኛ ማዘዋወራቸው ነበር። በዚህም የተነሳ፤ ባላባቶችና ጭሰኞች በፍርድ ቤት ይካሰሱ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ የጭሰኞቹን አቤቱታ በነፃ አገልግሎት ከሚጽፉት አንዱ ነበርኩ (ከሀብታም ነጋዴው ዘምዴና ከነገረ-ፈጆች ጋር በመተባበር)። ይህ የነፃ አገልግሎት ከምኮራበት የሕይወት ታሪኬ አንዱ ነው። ወደ-ፖለቲካ እንድገባ የገፋፋኝም ይኸው ልምድ ሳይሆን አይቀርም።

 

ከላይ እንደጠቀስኩት ጭሰኞችና ባላባቶች ይካሰሱ ነበር። የሚካሰሱበትም፤ የምርት ድርሻን መካፍልን አስመልክቶ፤ በተለይም ባላባቱ ጭሰኛውን መሬቱን ሲነጥቀው ነበር። አብዛኞቹ ከሳሾችም ጭሰኞች ነበሩ። ነገር ግን አንዳንድ ባላባቶች (አባቢድራዎች) - በተለይም ነባር ጭሰኞችን መሬቱን ነጥቀው ለሌላ ጭሰኛ ይሰጡ የነበሩት-  በጭሰኛው ላይ ቀድመው ክስ ይመሰረቱ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ባላባቶችም (አባቢድሮችም) ጭሰኞቻቸው እንደሚከሷቸው ስለሚያውቁ አስቀድመው ክሳቸውን ይመሰረቱ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን፤ አንድ ሲወልድ-ሲዋለድ ይዘውት የነበረውን መሬት የተቀሙት ጭሰኛ፤ ክሳቸውን ለመመሥረት ወደ ወረዳ ፍ/ቤት ሄዱና በባላባቱ መከሰሳቸውን ተነገራቸው። ከሳሻቸውም ክሳቸውን ቀምቷቸው አገኙት። ጠበቃቸውን ገዝተው መከራከር እንደሚችሉም ተነገራቸው። ደነገጡ! ተርበደበዱ! ተናደዱም። በዚህም የተነሳ ብዙም ሳይተንፍሱ ወደ ማታ ሲሆን ከፍ/ቤት ተመልሰው፤ ከኛ ጋር ተደባለቁ። “እንዴት ሆኑ፤ አባ እገሌ፤ የፃፍንላቸውን ማመልከቻ አስገቡ?” ብለን መጠየቅ ስንጀምር፤ በከፍተኛና በማያቋርጥ (ጎረቤቱን ሁሉ አስበርግጎ በሰበሰበው) ጩኸታቸው፤ ኡ!ኡ!ኡ!ኡ! እሪ! እሪ! እሪ! እሪህ!!  ኡ!ኡ!ኡ!ኡ! እሪ! እሪ!እሪህ!!! ያገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ! አሉ። [አጢኑት! እኒያ ጭሰኛ መንግሥት ከጎናቸው ያልቆመ መሆኑን ተገንዝበው ስለነበር፤ “የመንግሥት ያለህ!” አላሉም።] በጩኸታቸው ተደናግጥው የተሰበሰቡት ጎረቤቶቻችንና ለሰኞ ገባያ የመጣው ገጠሬ “ምን ሆነው ነው” ብሎ ሲጠይቃቸው፤ “ጩኸቴን ተቀማሁ! ውይ! ውይ! ጩኸቴን ቀሙኝ! “ አሉ። እነ አቶ መለስ፤ ስብሀት ነጋና በረከት ስሞን ጩኸታችንን ከኛ ከጯሂዎቹ ነጥቀው ስላላገጡብን ምናልባት ሰሚ ብናገኝ እኛም “እሪህ! እሪህ! ኡ!ዑ...ኡህ!...!”  እንበል እንጂ ጃል!። [ይህንን የብሶት መግለጫ ኡኡታየን ያጫወትኳቸው ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ “ኡኡታህን እንዲትነጠቅ ያደረገህ አንዱ ምክንያት “የመብት ማስከበሪያ የንግድ ምልክት ስላላደረግክበት ነው” ብለው ሲወቅሱኝ፤ “አሁን በኢትዮጵያ ጩኸት ቀርቶ ምን የማይቀማ ነገር አለ?” ብየ ጠየቅኋቸውና ሳቅና ሀዘን የተደባለቁበት ውይይታችን  በዚያው ተገታ!]   

 

ክፍል ሁለት፤ ሥልጣን ጠላፊው ከፍተኛ የፖለቲካ ሙስና (ግራንድ ኮረፕሽን) በኢትዮጵያ

መግቢያ፤

በፍኖተ ነፃነት 2ኛ ዓመት ቅጽ.2 ቁ.14 መግቢያ ላይ እንደገለጽኩት የሶሻሊስቱ (የኮሙኒስቱ) ሥርዓት ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ከዚያ በፊት ታይቶ ያልታወቀ ግዙፍ ሙስና መከሰቱን ነበር። በዚህም የተነሳ ሙስናዎች በሁለት ፀንፎች መልክ ተመድበው እንዲታዩ የግድ ብሏል። እነዚህም (1) በመንግሥታዊ አስተዳደር ብልሹነት መስክ የሚሰባሰቡ ወይም የሚገለፁ ወይም የሚከሰቱ ሙስናዎች (በእንግሊዝኛው administrative corruption) እና፤ (2) የመንግሥቱን የሥልጣን አውታር፤ አስተዳደሩን፤ ህጎቹን፤ ወ.ዘ.ተ. በመጥለፍ/በመማረክ የሚገለፁ የሙስና ጠባዮች (state capture) ናቸው። የአስተዳደሩን ብልሹነት ተጠግተው የሚከሰቱ ሙስናዎች ሕጎቹና ደንቦቹ ሳይደመሠሡ (እንደተጠበቁ ሆነው) ነገር ግን የህጎቹና የደንቦቹን አፈፃፀሞች በድብቅና ህጋዊ ባልሆነ መልክ የግለሰቦችን ጥቅሞች ማካበቻ ማድረግ  እንደሆነና  እነዚህም ከተራ ጉቦ ጀምሮ እስክ ታላላቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያሳተፉ ከፍተኛ ሙስናዎች/ምዝበራዎች ሊሆኑ  እንደሚችሉ ተገልጿል። በሁለቱ ተከታታይ መጣጥፎቼም የዚሁኑ በመጀመሪያ መልክ ያሰፈርኩትን የሙስና ክስተቶች፤ጠባያትና፤ ጠንቆች በመጠኑ ዘርዘር አድረጌ አቅርቤ ነበር። በዚህ ተከታይ ጽሁፍ ደግሞ የሁለተኛውን የሙስና ክስተቶች፤ጠባያትና፤ ጠንቆች አጠር አድርጌ አቀርባለሁ። ይህም ሙስና ጠባዩና ከስተቱ፤ የመንግሥትን ሥልጣን፤ ህጎችንና የአስተዳደር ደንቦችን በመማረክ/በመጥለፍ የሚከናወን፤ እንዲሁም የአንዲት ሀገር  ህጎችን፤ ደንቦችን፤ ሥርዓቶችንና ቁጥጥሮቹን፤ (laws, regulations, decrees, and other government policies) በማስቀየርና በመቀየር/በመጥለፍ ላይ የሚከሰት ሆኖ፤ የመግሥት አውታር ጠላፊዎቹም የራሳቸውን ጥቅሞች በማካበት የሕዝቡንና የሀገርን ጥቅም በመጉዳት እንደሚከሰት ነው። ጠላፊዎቹም/ማራኪዎቹም (በእንግሊዝኛው captors የሚባሉት) ሥልጣን ተሻሚ ግለሰቦች፤ ተመሳጣሪ ቡድኖች፤ በአምባገነናዊ መልክ ሥልጣን ላይ የወጡ ቡድኖች (oligarchy)፤ ባለጌ ባለሥልጣኖች ሊሆኑ ይችላሉ። እንደዚህ አይነቱ ሙስናም የተከሰተው የሶሻሊዝም/ኮሙኒዝም አይዲዮሎጂ መርህን ይከተሉ በነበሩ ሀገሮች እንደነበርና እነዚህም ሀገሮች “የነፃ ገባያን” (capitalist market economy) መርህ ለመከተል ሲፈልጉ አብሮ የሚከሰት ነው። የዚህ አይነቱ ሙስና ወደ ከፍተኛ እና የከፋ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ ጠላፊዎቹ የመንግሥት ሥልጣኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልክ በእጃቸው ያስገቡና ሙስናው እጂግ የከፋ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ ሙስና ሚዛኑ የሰፋና ውጤቱ የከፋ ከመኑም በላይ የፖለቲካ ፓርቲ ሀብቶች የሆኑ ኦሊጋርኮች (oligarchs) እና ክምችት የበዛባቸው ባለሀብቶችን (Business Empires) መፍጠር ነው። 

 

ይህ የአንዲት ሀገርን የፖለቲካ ሥልጣንና ኤኮኖሚን በመመማረክ የተከሰተው ሙስና ጠባዮች በርከት ያሉና እንደየሀገሩ ለየት ያሉ ጠባዮችና ክስተቶች ቢኖሩትም፤ በርካታ ተመሳሳይ ጠባዮችም አሉት። እነዚህ ክስተቶች ከሞላ ጎደል፤ በአልባኒያ፤ በአርሜኔያ፤ በአዘርብጃን፤ በክሮኤሽያ፤ በሰርቢያ፤ በላትቪያ፤ በሩሲያ፤ በዩክራይን፤ በቤላሩስ፤ በቱርክሜንስታን፤ በሌሎቹን እንዲሆም በአፍሪካ ውስጥ፤ በዩጋንዳና በሩዋንዳ በሰፊው የተንፀባረቁ ሲሆን፤ በከፊልም ቢሆን በሆስኒ ሙባረክ ትመራ በነበረችው ግብፅ፤ በቱኒሲያ፤ በደቡብ የመንና በከፊልም በደቡብ አፍሪካ ተንፀባርቋል። በእኔ አስተሳሰብና ምርምር ለእንደዚህ አይነቱ ሙስና በዋናነት የምትቀርበው አፍሪካዊ ሀገር ኢትዮጵያ ስትሆን፤ እንዳውም በኢትዮጵያ የተከሰተውን የጠላፊ ሙስናን የከፋና “ልዩ” የሚያደርጉትም ክስተቶች በርካታ ናቸው።  እነዚህን በሌላ ጊዜ እንመጣበት ይሆናል።

 

“የሥልጣን ጠላፊው” ሙሳና (ግራንድ ኮረፕሽን) ተግባራትና ተግባራዊ ምሰሎች (Variation in the Pattern of State Capture Corruption)

ከዚህ በታች (በከፊል) የጠቀስኳቸው “የሥልጣን ጠላፊው” ሙስናዎች ከላይ በጠቀስኳቸው ሀገሮች  ውስጥ (ኢትዮጵያንም ጨምሮ) የተከሰቱ ናቸው።

“የሥልጣን ጠላፊው”  (state capture) ሙስና፤

  1. የአንዲት ሀገርን ፖሊቲካዊና ኤኮኖሚያዊ አውታሮችን ለመቀማት ካስቻሏቸውና ከሚያስችሏቸው አንዱና ዋናው መንገድ፤ የሀገሪቱን የሕግ፤ የአስተዳደር፤ የወታደራዊ፤ የሕግ አስከባሪ፤ ማለት የፍርድ ቤቶችንና የፖሊስ አውታሮችን (apparatus) ማላላት/ማዳከም/መበተን ወይም እንዲዳከሙ ማድረግ (weakening state institutions) ነው። እነዚህን መግሥታዊ አውታሮች ከማዳከሙ/ከመበተኑ ጋር ተያይዞ የሀገርቷን ሀብት መበዘበር በሰፌው ይካሄዳል፤ ለቀጣይ ምዝበራ አመቺ ሁኔታዎችንም መፍጠር አንዱ ተግባራቸው ነው።
  2. የሥለጣን፤ የመንግሥት አውታርና የኤኮኖሚ ጠላፊዎቹ፤ የኤኮኖሚ ለውጡን (Economic Reform) ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ከማድረገቻውም በላይ፤ ለውጡ በተገቢው እንዳይከናወን፤ እንዲቀለበስም ያደርጋሉ። የኤኮኖሚ ለውጥ ሂደቱን ተጠቅመውም የራሳቸውን ሀብት ያካብታሉ። ከሚጠቀሙምባቸውም መንገዶች መካከል፤ በመግሥት ሥር የነበሩትን ኩባንያዎችና የኤኮኖሚ አውታሮችን ወደግል ባለሀብትነት ለመለወጥ  በሚደረገው የሀራጅ ሂደት በረካሽ ዋጋ ለራሳቸውና ለጥቅም ተጋሪዎቻቸው እንዲዛወሩ በማድረግ ነው።
  3. በሥልጣን ላይ በመባለግና ኤኮኖሚውን ወደ-ግል ባለሀብትነት ለመለወጥ በሚደረገው ሂደት ላይ ጣልቃ በመግባታቸው የተነሳ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በትክክል ወደ-ግል ሀብትነት (free market economy) እንዳይሸጋገር መሰናክል ይሆናሉ። በዚህም የተነሳ የሀገሪቱን ኤኮንሚ ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት (true market reform) እንዲጨናገፍ ስልጣንን ተጠቅመው ጋሬጣ ይሆናሉ። ይህ አይነቱ ክስተት የተጠናወታቸው ሀገሮችም፤ ወይ ሶሻሊስት፤ ወይ የገባያውን የኤኮኖሚ መስመር ሳይከተሉ ይቀሩና የኮኖሚው መሻሻልም (privatization and reform) ተጨናግፎ ይቀራል።
  4. “የኤኮኖሚውን ሥርዓት መለወጥ/ማሻሻል” (privatization and reform) ተብሎ የሚጠራውን አላማ እና በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚገፋውን መርህ ተጠቅመው የተቀናበረ ዝርፊያ ያደርጉና ባንኮችን፤ በመንግሥት ሥር ያሉና የነበሩ ድርጅቶችንና ኩባንያዎችን፤ የአስመጭና ላኪ የንግድ ዘርፎችን፤ የአከፋፋይና የተራ ንግድ ዘርፎችን፤ የከተማ መሬትንና በተለይም የመገናኛ ዘዴዎችን (media) ሆን ብለው/ትኩረት ሰጥተው በቁጥጥራቸው ሥር ያሰገቡና የራሳቸውን የላቀና ከፍ ያለ በተለይም ከፖለቲካው ጋር የተዛመደ ኤኮኖሚንም (empires and oligarchs) ይመሰርታሉ። ይህ ተግባር በአብዛኞቹ ድህረ-ኮሙኒስት (Post-communist) ሀገሮችም ወደ የሞኖፖሊ ያዘነበለ/ያዘመመ የኤኮኖሚ ሥርዓትና አያያዝ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።  
  5. የጠላፊዎቹ ቁጥጥርና ጣልቃ ገብነቱ በበዛባቸው ሀገሮች፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ፓርቲያቸው በሕግ አስከባሪና አስፈፃሚ ውስጥም ገብተው ለመቆጣጠር ችለዋል። ፍርድ ቤቶችንና የሕግ አስከባሪ አውታሮችን በመቆጣጠርና ከነሱም ጋር በመተባበርም፤ የሀገርን ሀብት ዘርፈዋል። ዜጎችን ያለ-ምክንያት እስር-ቤቶች ከተዋል። እንደ ማፊያ ሆነው በመደራጀትና በመሥራትም፤ ድራሻቸውንም አጥፍተዋል።  
  6. የጠለፉትን ሥልጣን ተጠቅመው ለግላቸው (ለቡድኖቻቸው) ለገነቧቸው/ለመሰርቷቸው የኤኮኖሚ አውታሮች (their own empires and oligarchs) በሕገ-ወጥነት ከወለድ ነፃ የሆነ “ብድር” እንዲገፋላቸው ያደርጋሉ። የሥራ ፈቃድን “ለወገኖቻቸው” ብቻ ያድላሉ፤ ያለ-ጨረታ ኮንትራት ይሰጣሉ፤ ከግምሩክና ከታክስ ክፍያ ነፃ ያስደርጋሉ። ብዙ ጊዜም “ብድር” ተብሎ የተሰጠው ሳይከፈል ይቀራል።   
  7. ከውጭ በእርዳታ የተገኙ ብድሮችንም ሆነ ጭሮታዎችን እንዲሆም መዋዕለ-ንዋይ ለራሳቸውና “የእኛ” ለሚሏቸው አድሎ በማድረገ ይሰጣሉ። 
  8. ያቋቋሟቸውን “ኩባንያዎች” ለመጥቅም፤ የውሽት (በማር የተቀባ እሬታዊ ሕጎችን- phony  regulations) አውጥተው ይጠቀማሉ።  
  9. በዝርፊያ በመሠርቷቸው ታላላቅ አውታሮች (Economic Empires and Oligarchs) እራሳቸውንና በተወሰነ ደረጃም የሚያምኗቸውን ሰዎች የቦርድ አባልና መሪ በማድረግ ይሾማሉ። ይህ ተግባር የኤኮኖሚውን ዋና ዋና አውታሮች ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ፤ የገቢ ምንጮቻቸውን ያበዛላቸውዋል።  
  10. በአስመሳይነት የፈጠሯቸውን “ኩብናያዎች” (shell companies and oligarchs) ተጠቅመው የዘረፉትን ሀብት ወደ-ውጭ ሀገር ያሸሻሉ።  
  11. በጠለፋ ሙስና የተዘፈቁት ቡድኖች፤ የተወሰኑ ዖሊጋርኪ ተቋማትን በመገንባት ብቻ ሳይወሰኑ በየቦታው፤ በየከፍለ-ሀገሩ፤ በውጭ ሀገርም ጭምር የተለያዩ የኤኮኖሚ ዘርፉን ለመቆጣጠር በርካታ የንግድ ዘርፎችን ያቋቁማሉ (በእንግሊዝኛው create constellation of businesses, crony capitalism and predatory activities የሚባለው ነው)።  
  12. የማፊያ አይነት፤ አድሎ የበዛበት፤ ዘረኝነትም የሰፈነበት የኤኮኖሚ አውታር እንደ-ሸረሪት ድር ዘርግተው “የእኛ ወገን አይደለም” የሚሉትን የግል ባለሀብት ያገለለ የኤኮኖሚ ሥርዓትን ይመሰረታሉ። የማፊያ ጠባይ ስላላቸውም የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች የበለጠ ሲቀናቸውና እነሱን ሲበልጧቸው፤ ይቀኑና ግለሰቦቹንና ድርጅቶቹን አስፈራርተው ወይም ቀምተው (Blackmailing private firms) ያባራሉ።  
  13. ሙስናው ተስፋፋቶ ሲመጣ፤ ከሕዝቡም ሆነ ከለጋሽ ሀገሮችና ድርጅቶች ቅሬታ ይነሳል። ሕዝቡንና ለጋሾቻን ለመሸንገል፤ ከእነሱ ቁጥጥር ሥር ያልወጣ የፀረ-ሙስናው ተቋምን ያቋቁሙና (phony anti-corruption regulations) ከእጃቸው እንዳይወጣ አድርገው ይመሠርቱትና በሙስና ላይ የሚደረገውን ጦርነት እንዲኮላሽ ያደርጋሉ። በግልም ሆነ በሌሎች ድርጅቶች የተቋቋሙትን የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴዎችን ይጠልፉና በቁጥጥራቸው ያስገባሉ። የፀረ-ሙስናው ትግልም ተኮላሽቶ ይቀራል። ሕዝቡም በመግሥትና በፀረ-ሙስና ተቋሙ ላይ ተስፋውን ያጣል።  
  14. የ”ሥልጣን ጠላፊ ሙስና” በተስፋፋባቸው ሀገሮች በመንግሥትና በፖለቲካ ፓርቲዎች፤ እንዲሁም በመንግሥታዊ ድርጅቶችና በፖለቲካ ድርጆቶች መካከል መኖር የሚገባው ልዩነት የደበዘዘ ነው። ይህም የደበዘዘ ግንኙንት (ልዩነት)ም የሙስና መስፋፋት ምክንያትና አንዱ ጠባዩም ነው።
  15. በጠላፊ ሙስና የተመሰረቱት “ኩባንያዎች” ሀብት የፖለቲካ ፓርቲን ለመገንባት ሕገ-ወጥና አድሎአዊ በሆነ መልክ ይውላል።
  16. የሥልጣን ጠላፊው ሙስናም በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በሀብት ካለመጠን እንዲናጥጡ ያደርጋል። ይህም ተግባር በድሃና በሀብታም መካከል ያለውን የሀብት ልዩነት በከፋ መልኩ ይለጥጣል።
  17. በችኮላ አዳዲስ ሕጎችን በፓርላማ ፀድቀው እንዲወጡ ማድረግና  ለፖለቲካ መሣርያነት መዋል።  
  18. አንዳንድ በሙስና የተዘፈቁ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ ያፓርላማ አባላትና የጥቅም ተጋሪዎችን ካንዱ መሥሪያ ቤት ወደሌው በማዛወር (በመሾም) ወይም የሙና ክስ እንዳይቀርብባቸው ማድረግ ወይም ምህረት መሥጠትን ይጨምራል። 
  19. ባጠቃላይ፤ የሀገሪቱን ዋና ዋና የደም-ሥር ሀብቶች በቁጥጥራቸው ውስጥ በማስገባትና የሞኖፖሊ ሥርዓትን በማስፈር አጠቃላይ የሀገሪቱን የኤኮኖሚ እቅድ ለመግታት እንዲያስችላቸው (በእንግሊዝኛው cornering ) ካማድረግ አይቆጠቡም።

 

አንባቢ መርሳት የሌለበት ነገር ቢኖር ምንም እንኳ በአስተዳደር ብልሹነት (አነስተኛና ጥቃቅን ላይ የተመሠረተ) ሙስናና ህጎችንና ደንቦችን በመማረክ/በመጥለፍ የሚከሰቱት (ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሳተፉበት) ሙስና በሥነ-ልቦናና አንዳንድ ጊዜም በተግባር ልንለያቸው ብንችልም፤ አብዛኛውን ጊዜ አንዱን ከሌላው መነጠል ያስቸግራል። በተለይም ህጎችንና ደንቦችን በመማረክ/በመጥለፍ የሚከሰተው ሙስና (state capture) የከፋ ስለሆነ በአስተዳደር ብልሹነት (administrative corruption) የሚከሰቱት ሙስናዎችንም ስለሚጨምርና ስለሚያካትት ነው።

 

ማጠቃላያ፤ ማሳሰቢያና የትብብር መልዕካት

እነ አቶ መለስ ዘናዊ፤ ስብሀት ነጋ፤ በረከት ስሞንና መሰሎቻቸው ስለ-ሙስና ማላዘናቸውና መጮሀቸው በሁለት መልክ መታየት ይችላል። በአንድ በኩል፤ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ ችግሩን ለማርከስ የታሰበ እርኩስ ተግባር ሊሆን ይችላል። እነ አቶ መለስ ዘናዊ፤ ስብሀት ነጋ፤ በረከት ስሞንና መሰሎቻቸው ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር ግን፤ ይህን የሚያደርጉት ስለሙስና ችግር ለማላዘን ከሆነ የበለጠ ይከፋናል፤ይሰድበናል እንጂ ሙስናው አይቀነስልንም። በኢትዮጵያ ተንሠራፍቶ ያለው አሰቃቂው የሥልጣን ጠላፊ (State Capture) ሙስና እንደሆነ፤ የሙስናውን መርዝ የሚረጨው በታላላቆቹ የኢሕአዴግ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሆነም ያውቃል። ሥልጣንን ተደግፈውና ጠልፈው የሀገሩ ኤኮኖሚ እንደተዘረፈም፤ ዘራፊዎቹ እነማን እንደሆኑም ያውቃል። ከላይ የዘረዘርኳቸው የሥላጣን ጠላፊ ግዳንግድ ሙስና ክስተቶችና ከዚያም የበለጡ ወንጀሎች (Variation in the Pattern of State Capture) በኢትዮጵያችን እንደተከሰቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ ያውቃል። እናንተም ታውቁታላችሁ። የተረጨውም መርዝ እታች ወረዶ መላ ቅጡን ያጣ መሆኑን መርዙ በእየለቱ የሚለከፈው ሕዝብ በደንብ ያውቃል። ከነአቶ ስብሀት ነጋ እንዲነግረው አይፈልግም!

 

እነ አቶ መለስ ዘናዊ፤ ስብሀት ነጋ፤ በረከት ስሞንና መሰሎቻቸው ስለ-ሙስና  መጮሀቸው በጎ ጎን ሊኖረው ይችላል። እንደዚህ ከሆነ ልንተባበራቸው ይገባናል (ከኔ ጀምሮ!) ሙስናን ያጠኑ ምሁራንና በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩትንና ጥናት የሚያደርጉትን ጨምሮ - ለምሳሌ የዓለም ባንክ ተመራማሪዎች- በኤኮኖሚና የፖለቲካን ጠለፋን መሠረት ያደረገ ሙስና የአሸበሪነት ጠባይ እንዳለው፤ በዚህም የተነሳ ተሰባሪ እንደሆነ ጽፈዋል፤ ተገንዝበዋል። (በንግሊዝኛው Oligarchic corruption is unstable by its nature and violent as well የሚባለው ነው።) በኢትዮያ ላይ የተከሰተው የጠላፊ ሙስና የከፋና ለብዙ ዓመታት መቆያቱ የራሱ መግልጫዎች ቢኖሩትም፤ ሲበተን የሚያስከተላቸው መዘዞች ሕዝብን የሚያጫርስ፤ ሀብትንም የሚደመሥስ፤ አገርንም የሚያፈርስ ሊሆን ይችላል። እንግድህ እነ አቶ መለስ ዘናዊ፤ ስብሀት ነጋ፤ በረከት ስሞንና በተለይም ኢህአደግን ተጠግተው የከበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች፤ ሙስናው በጣም ገምቶ መሆኑንና አደጋው ታይቷቸው፤ አደጋው ደርሶ ሁሉንም ጠራርጎ፤ አገርንም አፍርሶ ከመሄዱ በፊት መላ ለመምታት ከሆነ፤ ሊበረታቱ ይገባቸዋል። በሙስና ላይ በሚደረገው ጦርነት ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የሲቪክ ማህበራት፤ የረድኤት ድርጅቶች፤ በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊተባበራቸው ይገባል፤ እንደሚተባበራቸውም እርግጠኛ ነኝ። ምንም እንኳ አቶ መለስ አሁን ጠቅልለው የያዙት የፖለቲካ ሥልጣን የፈለጉትን እንዲፈጽሙ (እንዲሠሩ) ሊያደርጋቸው ቢችልም፤ እንደዚህ ያለውን የጠነባ ሙስና ለመታገድ፤ ከፓርቲ አባሎቻቸው ያለመተባበር እምቢተኝነት (resistance) የሚጋጥማቸው መሆኑ ስለማይቀር ትብብሩን ከኢሕአዴግ አባላት ሳይሆን ከተቃዋሚ ድርጅቶች፤ ከሲቪክ ማህበራት፤ ከእርዳታ ለጋሾችና በተለይም ከኢትዮጵያ ሕዝብ መሆን አለበት። ይህ ትብብር እንዲገኝ በተለይ አቶ መለስ ዘናዊ ቦዩን መቅደድ ይችላሉ። ከነዚህም መካከል አንደኛው በኢትያጵያ ተንዘራፍቶ ያለው ሙስና ከፍተኛ ፖሊቲካዊ ሙስና (state capture) መሆኑን መገንዘብና ከላይ ሆነው መርዙን የሚረጭቱን እባቦች እራስ-እራሳቸውን ለማለት ቁርጠኛ ሆኖ መነሳትና መንገዱን በምሳሌነት ማሳየት ነው። [Recognizing the existence of large-scale and systemic state capture, that this state capture type of corruption is the root of widespread corruption, and that it is has undermined the country’s potential transition communism to a market economy is paramount and a step in the right direction.  Acknowledging that, in Ethiopia today, that it is the EPRDF’s ethnic parties and their regional kingmakers who are appropriating state and public assets and who are systematically plundering the country’s resources, who are expanding their political and financial power, influence and ability to employ their relatives and party cronies at the expense of the country, and who are promoting the personal and corporate interests of the political and economic elites would be a good beginning. Recognizing this fact helps us to be on the same page and allows us to collaborate in designing the methods of fighting the corruption scourge. ]

 

ሁለተኛው፤ አቶ ስብሀት ነጋ በትክክል ያስቀመጡት; ማለትም፤ “በኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለው ሙስናን ለማጥፋት ፍላጎት እንጂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብሎ ነገር የለም” ላሉት በቀርጠኝነት መፍትሔ መሻት ነው። ሦስተኛው ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ፤ የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ድርጅቱ የፖለቲካ ሥልጣን ካለው ፓርቲና ከሌሎቹም ሀይለኞች (powerful forces) ነፃ ማድርግና፤ ገለልተኛ በሆኑና ተዓማኒነትና ባላቸው ግለሰቦች እንዲመራ ማድረግ ነው። ሁላችንም ተጠራርገን ወደ ቆሻሻ ከምንሄድ፤ በቁጭት፤ በብስጭትና በንዴት ከምተላለቅ፤ አገርም ከመፍረሷ፤ ልንተባበር ይገባል። ትብብር ካለ ደግሞ ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን። በአንድና በዋናው በኩል የጥልፊያ ሙስናውን የምናቃልልበትና የሕዝብን ሀብት የምናስመልስባቸውን መንገዶች በጋራ መቀየስ እንችላለን። ለምሳሌ አንዳንዶቻችን፤ በምሥራቅ አውሮፓ ተፈጥሮ የነበረውን የማፊያ ጠባይ የነበረውን ኦሊጋርካዊ ሙስና እነዚያ ሀገሮችና የአውሮፓ ማህበር እንዴት ሊታደገው እንደቻለ፤ በራሽያ ደግሞ እነ ቭላዲር ፑትን የተጠቀሙባቸውን ዘዴዎችንና ልምዶች፤ አጥንተንና አስሰን ማሳየት እንችላለን። በሌላው ጎን ደግሞ ከፀረ-ሙስናው ጦርነት በጣም ሊጠቀሙ የሚችሉት ሀብት የሰበሰቡት ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው። ለምሳሌ፤ በንፁህ መልክ ሀብት የመሠረቱት ባለሀብቶች፤ ሀብታቸው በወላፈኑ እንዳይደመሰስባቸው፤ ያላግባብ የከበሩትም እንዲተርፋቸው መንገድን ይፈጥራል። ፈረንጆች ሁሉም አትራፊ (win-win situation) ይሆናል እደሚሉት ማለት ነው። እነዚህን ለማድረግ ኳሱን አስቀድሞ ማንከባለል ያለበት ኢሕአዴግ ነው። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ