(ቻላቸው ዓባይ፤ ከጐሹ ገብሩና፣ ከአብዩ በለው)

የህወሓት ቡድን በወልቃይትና በጠገዴ ሕዝብ ላይ ከ30 ዓመታት በላይ በኃይል የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን አስከፊ የዘር ማጽዳት ወንጀል (Ethnic Cleansing ) በዝርዝር የሚያስረዳና በተጨባጭ የሰነድ ማስረጃዎች የተደገፈ የአቋም መግለጫ በየካቲት 7/2004 ዓ.ም የዘር ማጽዳት ዘመቻ በወልቃይትና በጠገዴ ማህበረሰብ በሚል ማውጣታችን ይታወሳል።

 

 

በዚያ ዘገባ ላይ የወያኔ አስከፊ ወንጀሎች ከሁለት አንኳር ሀሳቦች እንደሚነሱ አሳይተናል። ለማስታወስ ያህል፡-

1ኛ/ ወያኔ እንደለመደው ታሪክን በማጎላደፍ ወልቃይት፣ ጠገዴንና ጠለምትን ከጎንደር ግዛት ገንጥሎ ወደ ትግራይ በታሪክ ስም ማጠቃለልና ለታለመችው ለ“ታላቋ ትግራይ”ና ለ”ትግራያዊው ወርቅ ህዝብ” ለዘመናት የምግብ ዋስትና የሚሰጥ ለም መሬት ማረጋገጥና፤

2ኛ/ ኢትዮጵያዊነቱንና ጎንደሬነቱን በኩራትና በክብር የሙጥኝ ብሎ የያዘውን የወልቃይትን፣ የጠገዴና የጠለምት ማህበረሰብ እንደ እባብ መቀጥቀጥና በሁሉም ዘርፍ ማድቀቅ፤ ከአደገበትና ከኖረበት ቀዬ በኃይል ማፈናቀልና (systematic ethnic cleansing) በምትኩም በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በማስፈር አካባቢውን የ“ትግራውያን” እንዲሆን ማድረግ ናቸው።

 

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ሁለት አበይት አላማዎችን ለመተግበር ወያኔ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ያለማቋረጥ የፈጸመብንን ዝርዝር ወንጀሎችንም በየካቲት 7/2004 ያወጣነው ዘገባ በከፊል ያካትታል።

 

እነሆ የአካባቢውን የህዝብ ስብጥር ሚዛን /Demography/ በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ ትግሪያዊነት በመቀየር አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ትግሪያዊ ማድረግና ታሳቢውን እቅድና ውጤት ሊያደናቅፉ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰቡትን ሁሉ በማሰር፣ በማሰደድና፣ በመግደል መንገዱን ማለስለስ ነበር።

 

እንግዲህ በትግራዩ ነፃ አውጪ ቡድን ቅዠት መሰረት እነሆ ጎባጣው ቀንቷል፣ ገደሉ ሞልቷል፣ ሸለቆው ተስተካክሏል። የቀረው የ“ሶስተኛውና የአራተኛው” መንገድ መከሰት ብቻ ይመስለናል።

 

እነዚህን የጥፋት መንገዶች በሂደት የህጋዊነት ወይም የፍትሃዊነት ሽፋን ለመስጠት ዛሬም የትግራይ ነፃ አውጪው ቡድን ሁለት ፍትሃዊነት የጎደላቸውና እስከ አሁን የቆየውን ችግር ወደ ላቀ የግፍ ደረጃ ለማሳደግና ብሎም ችግሩን በመላው የትግራይ ህዝብና በጎንደር ህዝቦች መካከል በሚኖረው የበቀል ይዘት ለማስፋት በማቀድ ቀጣይ እርምጃዎች ወይም በእኛ እምነት ህወሓታዊ ቀጣይ ሴራ በወያኔ አኮፋዳ ውስጥ አድፍጠው እንደሚጠብቁን በተለያዩ የወያኔ ቱባ ባለስልጣናት አማካኝነት በተለያዩ ጊዜያት ደርሰውናል።

 

እቅድ አንድ፡ “ህዝበ ውሳኔ” /Referendum/

ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን እኩይ አጀንዳ ያረዱን የቀድሞው የወያኔ ም/ጠ/ሚ የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ ሲሆኑ። ይህም በነሐሴ ወር 2006 ዓ.ም ወደ ኮሎምበስ ኦሃዮ በመምጣት ጥቂት የአካባቢውን ተወላጆች እየተሹለኮለኩ ባነጋገሩበት ወቅት ነበር። በዚህም ወቅት ከእነዚህ የዋህ ወንድሞች ለቀረበላቸው የ“ዕርስታችንን መልሱልን” መሰረታዊ የማንነት ጥያቄ የሰጡት መልስ ግልፅና ቀጥተኛ ነበር። የኸውም “እንደ ስልጢ ህዝብ በህዝበ ውሳኔ/ Referendum/” አንዲሰጣችሁ ጠይቁና በዚያ መንገድ መልስ እንዲያገኝ እንረዳችኃለን የሚል ነበር።

 

በእኒህ ወኔ ቢስ ግለሰብ በኩል የደረሰን መርዶ ለሁለተኛ ጊዜ ያረጋገጡልን ሌላው የህወሃት መስራችና የ“ታላቋ ትግራይ” ቅዠት አርቃቂ የነበሩት የዛሬው ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ሲሆኑ ይህንንም ህወሃታዊ ቀጣይ የጥቃት ካርድ እንደተደገሰልን ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ወቅት “የወልቃይት ህዝብ ችግር እንዴት ይፈታል?” ለሚለው ጥያቄ በመለሱት መልስ “የአንድ ክልል የግዛት ወሰን የመጥበብና የመስፋት ጉዳይ መሆኑንና መፍትሄውም በአንድ ሃገርነት ስር እስከተካተትን ድረስ በቀላሉ በዚያው የሚመለስ” መሆኑንና በግልጥ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማፅዳት ወንጀል እንደ ተራ የአስተዳደር ችግር በማስመሰል አለባብሰው ለማለፍ ሞክረዋል።

 

ይህ በእንዲህ እያለ ነበር የቀድሞው የህወሃት መከላከያ ሚንስትርና የአሁኑ የመድረክ ሰው አቶ እስዬ አብርሃ እዚህ ሰ/አሜሪካ በምርጫ 2002 ወቅት በመጡበት ጊዜ ይህን የወልቃይት ጠገዴ በደል እንዴት ሊፈታ እንደሚችል ጥያቄ ባቀረቡላቸው ወቅት “ህዝበ ውሳኔ / Referendum/” መፍትሄ ነው የሚል “የተጠና መዝሙራቸውን” አስደምጠዋል። በወቅቱ የአቶ እስዬ መዝሙር ትዝብትን አተረፈላቸው እንጂ በእርግጥ ከቀደመው ህወሃትነታቸው “መቀየራቸውን” ሊያሳምን አልቻለም።

 

እንግዲህ ለምሳሌነት የእነዚህን የወያኔ ነባር አመራሮች አቋምና የ“መፍትሄ ሃሳቦች” አነሳን እንጂ ነገርዬውን በብዙ የበታች ሹማምንትና “ትግራያዊ ምሁራን” በኩል ከበሮ እየተደለቀበት ይገኛል። ይባስ ብሎ ከሰሞኑ ደግሞ ዶ/ር ገላውዲዎስ የተባሉ ለ“ኢትዮጵያ መላው ጭቁን ህዝብ” እታገላለሁ ይሉ የነበሩ የታሪክ ምሁር ዛሬ እራሳቸውን በወያኔ የታሪክ ቀበኛነት “ጫማ” ስር ወሽቀውና እጅግ አዋርደው በወገናችን ላይ እየተፈፀመበት የሚገኘውን የዘር ማፅዳትና በትግሪያዊነት የመተካት ወንጀል ከማጋለጥና ከማውገዝ አፈግፍገው ለወያኔ አፀያፊ ወንጀል አሳፋሪ የታሪክ ሽፋን ለመስጠት “አራምባና ቆቦ” ሲረግጡ ለማየት ተገደናል። ዛሬ ለዶ/ር ገላውዲዎስና ለመሰሎቻቸው ታሪክን የማጎላዳደፍ ክፉ አባዜ ተገቢውን መልስ መስጠት በወደድን ነበር። ነገር ግን የዚህ ጦማር አላማ አይደለምና በይደር እናቆየዋለን። ይሁን እንጂ ለማስታገሻ ወማስተንፈሻ ይረዳ ዘንድ ግን ለዛሬ የሚከተለውን ኢሳት “በታሪክ ማህደር” ዝግጅቱ ያቀረበውን “Ethnicity and Fascism in Ethiopia Part 1” ጥናታዊ ትምህርት ይመለከቱ ዘንድ በአክብሮት እንጋብዛለን።

 

 

እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝቦች ግን ተሓሕትን ከስረ-መሰረቷ የምናውቃትና መሰሪ አላማዋንም የምንረዳ በመሆናችን የዚህኛው “ህዝበ ውሳኔ” መነሻና መድረሻ ለቀደመው የዘር ማፅዳት ወንጀል ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚደረግ “ማሟሟቅ” መሆኑን እናውቀዋለን።

 

ይሁንና አለኝታና ተስፋችን ለሆነው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀደም ሲል ስለ በደላችን የያዘውን ግንዛቤ ለማጠናከርና ተከታዩን ሴራ ለማጋለጥ ይረዳን ዘንድ እንደሚከተለው ባጭሩ አስቀምጠናል።

 

በመሰረተ ሃሰብ ደረጃ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ በማንነቱ ላይ “ህዝበ ውሳኔ” እንዲሰጥ ማንንም ጠይቆ አያውቅም። ለወደፊትም አይጠይቅም። ለዚህም ምክንያቱ አንድና አንድ፤ ፍንትው ያለ ግልፅ እውነት!!

 

እኛ የወልቃይት ጠገዴንና ጠለምት ማህበረሰቦች በማንነታችን ላይ ብዥታም ሆን ጥርጣሬ ጭራሹንም የለለብንና “ሲያልፍም የማይነካን” በመሆኑ ነው

በመሆኑም እኛ ማንነታችንን በሚመለከት “ህዝበ ውሳኔ” የምንሰጥበት መነሻም ሆነ መድረሻ ምክንያትና ግብ የለንም። ሊኖረን አይችልም። ይልቅስ እኛ እያልን ያለነው እጅግ በጣም ቀላልና ግልፅ ነው። ይኸውም መሬታችንና ማንነታችን ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይመለስልን። አራት ነጥብ!!!

 

እንዳውም ከተናገርን አይቀር ዛሬ እዚችው ርዕስ ስር ጨርሰን እንናገረውና እንወረደው።

 

በአንድ ወቅት ልክ እንደኛው በማንነታቸው ላይ የዘመተውን ታሪክ አጎልዳፊ ሁሉ ለማኮላሸት የቆረጡት ታላቁ የአፋር አባት ሱልጣን አሊሚራህ “የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል” በማለት ለአንዴና ለመጨረሻ ከሃዲውን ሁሉ እንዳደባዩት እኛም

የወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን ዕርስት፣ ድንበርና፣ ማንነት እንኳንስ እኛ፣ እንኳንስ የቋራና የአርማጭሆ ህዝብ፣ እንኳንስ የጎንደር ህዝብ፣ እንኳንስ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና ርስታችንን ዙሪያውን አካሎ ከትግራይ ጋር ያደናበረን/ድንበር የሆነን/ የተከዜ ወንዝ ጠንቅቆ ያውቀዋልና እርሱኑ ጠይቁት። ተከዜንም አድምጡ ብለናል። ጨረስን።

 

ታዲያ ይህ መንገድ በፍፁም እንደማይሳካ ከ“ጊዜ ደጉ” ጋር አብረን የምናየው ይሆናል። ነገር ግን በወያኔ በኩል ይህኛው ሴራ ከጨዋታ ሲወጣ /Phase Out/ የከፋውና ሌላኛው መርዘኛ እቅድ ገበያ ላይ እንዲውል ይደረጋል። ይኸውም ለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የ“ራስ ገዝ አስተዳደር” ማጎናፀፍ የሚል። ድንቄም የ“ራስ ገዝ”! እስኪ ይህን የ“አህይት”ን መርሆ የተከተለ ሴራ እኛ በተረዳነው መንገድና መጠን ለእርስዎ ለክቡር ኢትዮጵያዊ ወገናችን እንደሚከተለው እናካፍልዎ።

 

እቅድ ሁለት፡ የራስ-ገዝ አስተዳደር

የራስ ገዝ አስተዳደር (self determination) ሤራ፡ ይህ ዕቅድ ደግሞ ከ“ሕዝበ ውሳኔ” ( Referendum) ሌላ ገብያ የሚወጣ መርዘኛ አማራጭ ነው። በአጭሩ “ሕዝበ ወሳኔና“ “ራስ ገዝ አስተዳደር” የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የራስ ገዝ አስተዳደር ዋና ግቡ:

 

ሀ) ግዜ መግዛት፤ በዛ በታቀደው ግዜ ውስጥ የትግራይ ሰፋሪዎችን በሁሉም መልክ በበለጠ ማጎልበት፣ አካባቢውን ባለቤት አልባ ማድረግና፣ በአንፃሩ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ የበለጠ ማድቀቅ፣

ለ) የወጣቱን ባህል ከአማርኛ ቋንቋና ከአማራነት ስነልቦናው ፈጽሞ መለየትና ከታሪካዊ ማንነቱና በደም ከተሳሰረው ጎንደሬነቱ ማላቀቅ፣

ሐ) ከሁሉም በላይ ደግሞ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ፡ ከአርማጭሆ፤ ከቆላ ወገራ፤ ከሰሜን፤ ከቋራና ከሌላው የጐንደር ሕዝብ ጋር ያለውን ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ለአንዴና ለመጨረሻ ፈጸሞ መበጣጠስ ነው።

 

በ1928 ዓ.ም. ጣሊያን ወደ ጐንደር በመጀመሪያ የገባው በኦማሃጀር በኩል ተከዜን ተሻግሮ ከዚይም ሁመራን፤ ጠገዴንና አርማጭሆን አቋርጦ ነበር። ወራሪው ሃይል ተከዜን በተሻገረ በበነጋው ጀምሮ የወልቃይት፤ የጠገዴ የአርማጭሆና የቋራ አርበኞች መግቢያ መውጫ ስላሳጡትና ወደ ቀሪዎቹ የጎንደር አካባቢዎች የሚያደርገውን ወረራ ስላኮላሹበት ነበር በብዙ ሽህ የሚቆጠር የሰው መስዋዕትነት ከፎሎ የሊማሊሞን ገደል በመቅደድ የሰሜንና የጐንደር ከተማን ማገናኘት የቻለው።

 

እንዲሁም በምዕራብ ጐንደር በደረሰበት ከፍተኛ ሽንፈት ምክንያት ባደረበት ቁጭት አርበኛውን ለማዳከምና ክልላዊ ሰሜት ለመፈጠር ሲል የወልቃይት ጠገዴና የጠለምት ማህበረሰብ ከጐንደር ውጭ ነው ብሎ አወጀ። ይሁን እንጂ በአያቶቻችን ክቡር መስዋዕትነት ያ የጣሊያን ቅዥት የትም አልደረሰም ነበር።

 

ይህን የብሄር በሄሮች አስተዳደር (Ethnic Federalism)ና እስከ ባድመ የድንበር ክልል ድረስ ያለውን አንኳር ሴራ እነ ስብሃት ነጋ የኮረጁትና የህወሃት አብይ መርህ ያደረጉት ኢትዮጵያን በመጥላትና በመበቀል ከሚጋራቸው የነብስ አባታቸው ከሞስሎኒ ነበር።

 

እኛ የወልቃይት፤ ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ፡ ጋብቻችን፤ ልቅሷችን፤ በአጠቃላይ ኑሯችን ከአርማጭሆው፣ ከቋራው፣ ከሰሜንና፣ ከወገራው ጋር ነው። ዋና ከተማችንም መቀሌ ሳይሆን ጐንደር ነው። ይህ እውነታ ሊፋቅ የማይችል ታሪካችንም ማንነታችንም ነው። አሁንም ይህን ታሪካችንና ማንነታችን ለመፋቅ የተደገሰ የባንዳው የወያኔ ሴራ በወልቃይት፤ በጠገዴ በአርማጭሆ በቋራና በጎንደር እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እንደሚኮላሽ ለማረጋገጥ እንወዳለን።

 

ከዚህ ሀቅ ባላነሰ መልኩ መታወቅ ያለበት ደግሞ እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ፀረ-ትግሬ አለመሆናችን ነው። ወገናችን ከሆነው ከትግራይ ማህበረሰብ ጋር ለዘመናት አብረን ተጎራብተን ተዛዝነን ኑረናል። ክፉውን ቀን ያለንን ተካፍለን በልተናል። አሳልፈናልም። ለአንድ አገር ሲባል በአንድ ጦር ሜዳ አባቶቻችን ውለዋል። አሁን ደግሞ እኛ ተከዜን ተሻግረን የትግራይ የከብት መስደጃ አልቀማነም፣ ወይም የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት የያዘው ርስቱ አፈናቅለን አልስፈርንበትም፣ ወይም የትግራይን ሴቶች ግብረ ስጋዊ አመፅ አላካሄድንም፣ ወይም ወጣትና ሽማግሌ ወንዶችን እንዳውሬ እያደን ከጉድጓድ እስር ቤቶች አልወረወርንም፣ በግፍ አልገደልንም። ይህ ሁሉ በደል የተፈፀመውና እየተፈፀመ ያለው በኛ ላይ ነው። በእርግጥ በውጭ አገርና በትግራይ ውስጥ ያለው የትግራይ ማህበረሰብ እኛን ወገኖቼ ናቸው ብሎ ካመነ ይህን ዘመን የወለደውንና የታሪክ አሜኬላ የሆነውን የተሐህት ባእዳዊና ፋሸስታዊ ሥራና ግፍ እንዲሰምርና እንዲያብብ ማቀንቀን ሳይሆን እንዲኮላሸና እንዲመክን ለማድረግ ግንባር ቀደም መሰዋዕትነት መክፈል ይጠበቅበታል። እንጠብቃለንም። የወያኔ ቁርጠኛ ውሳኔ በደልን በማጧጧፍ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የመጠላላትና የመጠፋፋት ዋስትና ለማረጋገጥ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታልና ነው።

 

ይሁንና እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ታሪካዊ እውነትና ፅኑ የነፃነት ጥማት ስላለን ብቻ በመራር ትግላችን ይህንን የትግራይ ተስፋፊዎችን ግፍና የህወሃትን በደል እንገታዋለን። የቀደመ ታሪካችን በደማቁ እንደሚያዘክረው የአባቶቻችንን አኩሪ ታሪካዊ መንገድ ስንከተል እንደሆነም በፅኑ እናምናለን። እንታመናለን።

 

ወላጆቻችን፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን ከጥንት ጀምሮ ለሃገራቸው ለታለቋ ኢትዮጵያና ለመላው ህዝቦቿ ነፃነትና ለዳር ድንበሯ መከበር፤ ደሙን ከደሙ ቀላቅሎ የቅድስት ሃገሩን ጋራ ሸንተረር ያረሰረሰ፣ አጥንቱን ከአጥንቱ አማግሮ ዳርድንበሩን በጀግንነት ያጠረ ኩሩ ህዝብ ልጆች ነንና ዛሬም እኛ የአባቶቻችን ታማኝና ባለአደራ በመሆናችን እንደ ቀደሙት ሁሉ ከመላው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ጋር በማበር ይህን ዘመን የወለደውን የታሪክ አሜኬላ የሆነው የህወሃት አገር የማፍረስ፣ ታሪክ የመበረዝና፣ ርስት የመንቀል እኩይ ባንዳዊ አላማ እናኮላሻለን።

 

ከዚህ በመነሳት እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰቦች በ“ትግራይ ነፃ አውጪ” ቡድን ለተፈፀመብን የዘር ማፅዳት/Ethnic Cleansing/ ወንጀል እውነተኛውን “ፍትህ” በአለም ደረጃ ለመጎናፀፍ ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሃገራችን ያለውን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከሲቪክ ማህበራትና፣ ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከሚመለከታቸው ሁሉ አጋርነት በአፋጣኝ እንሻለን።

 

አካባቢውም ከፍተኛ ወንጀል የሚፈፀምበትና እስከ አሁንም ድረስ ለማንኛውም ገለልተኛ አካላት በተለይም ለጋዜጠኞችና ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዝግ በመሆኑና እስከዛሬም ቢሆን ለማንኛውም ገለልተኛ አካል ምርመራና እይታ ክፍት ሆኖ የማያውቅ በመሆኑ ይህ አፈናና ወጥመድ ተሰብሮ፡-

- የወገናችን በደል ለዓለም ሰላም ወዳድ ህዝቦች እንዲደርስ፣

- የተፈፀመውና እየተፈፀመ ያለው ወንጀል በገለልተኛና ነፃ ወገኖች እንዲጣራ፣

- ከጥቃቱ ማምለጫ መንገድ ያጡትን ንፁሃን ወገኖቻችን ለመታደግና እነሱም ዘንድ የሚገኙትን አስፈላጊና ጠቃሚ መረጃዎችን ለአለማቀፋዊ የፍትህ አካላት እንዲደርስና፣

 

በመጨረሻም በዓለማችን ላይ እጅግ የከፋው የዘር ማፅዳት ወንጀል ዛሬ በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ መሆኑን በተጨባጭ በማጋለጥ ወንጀለኞቹን በዋናነት፡-

1ኛ. መለሰ ዜናዊ፤ ስብሃት ነጋና በየወቅቱ የነበረው የሕወሃት አመራር ቡድን፣

2ኛ. ከ1984ዓ.ም ጀምሮ የተፈራረቁት የትግራይ ክልል መስተዳድር መሪዎችና አስተዳደራቸው፤ በወገናችን ላይ የተፈፀመውን የዘር ማፅዳት ዘመቻ በማቀነባበርና በመምራት ዘራችንን በማሰር፣ በማሰደድና፣በመግደል እንዲሁም በትግሪያዊነት የመተካቱን ሂደት/Tigirianaization/ በማሳለጥ የተራዱ በየደረጃው ያሉ ገዳዮችና ግብረ በሎቻቼውን ሁሉ ለፍርድ ለማቅረብና ወንጀለኞቹም ፍርዳቸውን ያገኙ ዘንድ በምናደርገው መራራ ትግል ከጎናችን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ሁሉ ታደርጉልን ዘንድ መራር ጥሪያችን ይድረሳችሁ።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝቦችም እንዲሁ! መጋቢት 7, 2004 ዓ.ም


(ቻላቸው ዓባይ፤ ከጐሹ ገብሩና፣ ከአብዩ በለው)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!